loader

Topics (525)


loader Loading content ...

Explanations (525)


 • @በህግ አምላክ   4 days ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!

  የ፲፱፻፺፮ ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ ፥ በሰዎችና በንብረቶች ላይ የሚፈፀሙ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች ፥ ምዕራፍ አራት ፥ በኢኮኖሚ፣ ንግድና የባሕር አስተዳደር ጉዳዮች ላይ የሚፈጸሙ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች


  አንቀጽ ፰፻፷፫ የንግድና የሂሳብ መዛግብትን የሚመለከቱ ድንጋጌዎችን መተላለፍ
  ማንም ሰው ከሕግ፣ ከደንብ ወይም ከመተዳደሪያ ደንብ የመነጨ ግዴታን በመተላለፍ በየጊዜውና በሥነ-ሥርዓት የንግድና የሂሳብ መዛግብትን ሳይዝ የቀረ ወይም ለመያዝ ችላ ያለ ወይም ከሥራው ጋር የተገናኙ መጻጻፎችን፣ ፋክቱሮችን ወይም ሌሎችን የንግድ ሰነዶችን በሕግ እስከተወሰነው ጊዜ ድረስ ሳያቆይ የቀረ ወይም ለማቆየት ችላ ያለ እንደሆነ፤
  በመቀጮ ወይም ከአንድ ወር በማይበልጥ የማረፊያ ቤት እስራት ይቀጣል።

  አንቀጽ ፰፻፷፬ በግዴታ የፍርድ አፈፃፀም ሥርዓት ላይ እምቢተኛ መሆን
  ማንም ባለዕዳ ወይም ሦስተኛ ወገን በወንጀል ሕጉ በአንቀጽ ፯፻፳፰‐፯፻፴ መሠረት ከሚያስቀጣው ሁኔታ ውጭ፣ የመክሰስ ወይም ሂሳብ የማጣራት ሥልጣን ያለው አካል የሰጠውን ግልጽና ሕጋዊ ትዕዛዝ ለመፈጸም እምቢተኛ የሆነ እንደሆነ፤ በተለይም እምቢተኛነቱ የሚመለከተው፡-
  ሀ/ በይዞታው የማይገኝ ቢሆንም እንኳ የራሱ ጠቅላላ ንብረት አካል የሆነውንና የሚፈለገውን ዕቃ ብድር፣ የዕዳ ጥያቄ፣ ያለበትን ዕቃ፣ የማይንቀሳቀስ ወይም የሚንቀሳቀስ መያዣ ወይም ይህን የመሳሰለ ማናቸውም ሌላ ግዴታ የማስታወቅ፣ የመግለጽ ወይም የማቅረብ ግዴታን ሲሆን፤ ወይም
  ለ/ ቃሉ እንዲሰማ ወይም በሌሎች ፊት እንዳይቀርብ፣ ስብሰባ እንዲከፈል፣ በድምፅ አሰጣጥ ላይ እንዲሳተፍ ወይም የዕዳ አከፋፈል ወይም የግዴታ የፍርድ አፈጻጸም ሥርዓትን በሚመለከት የሕግ ድንጋጌ የታዘዘውን ማናቸውም ሌላ ድርጊት እንዲፈጽም የደረሰውን ደንበኛ ጥሪ የመመለስ ግዴታን ሲሆን፤
  በመቀጮ ወይም ከስምንት ቀን በማይበልጥ የማረፊያ ቤት እስራት ይቀጣል።

  አንቀጽ ፰፻፷፭ ስለንግድ መርከቦች የወጡትን ደንቦች መጣስ
  ማንም ሰው፡-
  ሀ/ የመርከቡ ካፒቴን፣ መኮንን ወይም ሠራተኛ ያለበትን እንደምልክት የመስጠት፣ መርከብን የመጐብኘት የመመርመር፣ የመቆጣጠርና የመሳሰለውን የደኀንነት እርምጃ የመውሰድ ግዴታ፤ ወይም
  ለ/ የመርከቡን የባህር መዝገቦች፣ መዝገቦች ወይም የሌሎች ሰነዶችን አያያዝ፤ ወይም
  ሐ/ በባሕር ወይም በወደብ ላይ ጭነትን፣ ፖስታን ወይም መንገደኞችን ማጓጓዝን፣ ማሳፈርና ማውረድን፣ መጫንና ማራገፍን ወይም መንቀሳቀስን፤ ወይም
  መ/ ጽዳት ወይም ጤና አጠባበቅን፤
  በሚመለከት የወጡ የንግድ መርከብ ሕጐችን፣ ደንቦችን ወይም መመሪያዎችን የጣሰ እንደሆነ፤
  የወንጀል ሕጉ ወይም ይህን የሚመለከት ሕግ ሌላ ድንጋጌ ተፈፃሚ ካልሆነ በቀር፤ በመቀጮ ወይም በማረፊያ ቤት እሥራት ይቀጣል።

  ምንጭ:
  የ፲፱፻፺፮ ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ
 • loader Loading content ...
 • @በህግ አምላክ   4 days ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!

  የ፲፱፻፺፮ ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ ፥ በሰዎችና በንብረቶች ላይ የሚፈፀሙ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች ፥ ምዕራፍ ሦስት ፥ በንብረት ላይ የሚፈፀሙ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች ፥ ክፍል ሦስት ፥ በንብረት ላይ የሚፈፀሙ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች በጠቅላላው


  አንቀጽ ፰፻፶፰ የሌላውን ሰው ጥቅም በተንኰል መጉዳት
  ማንም ሰው ሕገ-ወጥ ብልጽግናን ለማግኘት በማቀድ ሳይሆን በክፋት፣ ለመጉዳት በማሰብ ወይም በማናቸውም ሌላ ምክንያት ተነሳስቶ የማጭበርበር ወይም የማሳሳት ዘዴ በመጠቀም አንድ ሰው የራሱን ወይም የሌላ ሦስተኛ ወገንን የንብረት ጥቅም የሚጐዳ ድርጊት እንዲፈጽም ያደረገ እንደሆነ፡
  በመቀጮ ወይም ከአንድ ወር በማይበልጥ የማረፊያ ቤት እስራት ይቀጣል።

  አንቀጽ ፰፻፶፱ ወስላታነት
  ማንም ሰው መክፈል እንደማይችል እያወቀ ለሕዝብ አገልግሎት በሚሰጡ ምግበ ቤቶች፣ ቡና ቤቶች፣ ሆቴሎች ወይም መኝታ ቤቶችና በመሳሰሉት የንግድ ተቋማት ገብቶ ምግቦችን፣ መጠጦችን፣ መኝታን ወይም ማናቸውም ዓይነት ጥቅሞችን ያዘዘ ወይም ያገኘ እንደሆነ፤
  በመቀጮ ወይም ከአንድ ወር በማይበልጥ የማረፊያ ቤት እስራት ይቀጣል።

  አንቀጽ ፰፻፷ ሌሎች ጥቅሞችን በማጭበርበር ማግኘት
  ማንም ሰው በክፍያ ብቻ የሚገኙ ጥቅሞች መሆናቸውን እያወቀ በማጭበርበር ያለክፍያ ጥቅሙን ያገኘ እንደሆነ፤ በተለይም፡-
  ሀ/ በየብስ፣ በአየር ወይም በውሃ ላይ የመሳሰሉ ማናቸውም ዓይነት በሕዝብ ወይም በግል የመጓጓዣ ዘዴዎች የተገለገለ እንደሆነ፤ ወይም
  ለ/ ወደ ትርዒት፣ መዝናኛ፣ ተውኔት፣ ኤግዚቢሽን ወይም ለትርፍ ወደ ተዘጋጀ ማናቸውም ተመሳሳይ ዝግጅት ውስጥ የገባ እንደሆነ፤ ወይም
  ሐ/ ሳንቲም በማስገባት በሚሠሩ ኦቶማቲክ ማሽኖት በመገልገል እቃዎችን፣ ያገኘ እንደሆነ፤
  በመቀጮ ወይም ከአንድ ወር በማይበልጥ የማረፊያ ቤት እሥራት ይቀጣል።

  አንቀጽ ፰፻፷፩ አውቃለሁ ባይነት
  ማንም ሰው በወንጀል ሕጉ በአንቀጽ ፯፻ መሠረት ከሚያስቀጡት ሁኔታዎች ውጭ፡-
  ሀ/ የሌላውን ሰው በነገሮች ቶሎ የማመን ዝንባሌ ተጠቅሞ በማናቸውም ዓይነት ሁኔታ በሚደረግ የአውቅልሃለሁ ጥንቆላ፣ መናፍስትን በመጥራት፣ የተሸሸገ ገንዘብ የሚገኝበትን ዘዴ ማመላከት ወይም ይህን በመሰለ ማናቸውም ሁኔታ ገንዘብ የተቀበለ እንደሆነ፤ ወይም
  ለ/ በማስተዋወቅ ወይም በሌላ መንገድ ጥቅም ለማግኘት እንደዚህ ዓይነት ሥራዎችን ወይም አገልግሎቶችን እንደሚሰጥ በይፋ ያቀረበ እንደሆነ፤
  በመቀጮ ወይም ከአንድ ወር በማይበልጥ የማረፊያ ቤት እሥራት ይቀጣል።

  አንቀጽ ፰፻፷፪ ያለፈቃድ ገንዘብ መሰብሰብ
  ማንም ሰው በሕግ ወይም አግባብ ባለው ባለሥልጣን ሳይፈቀድለት በአደባባይ እየዞረ ገንዘብ የሰበሰበ ወይም የጠየቀ እንደሆነ፤
  በመቀጮ ወይም በማረፊያ ቤት እስራት ይቀጣል።
  ገንዘብ መሰብሰቡ የተፈጸመው ሀይማኖታዊ ሥርዓት በሚፈጸምባቸው ሕንፃዎች ውስጥ ወይም በግለሰብ፣ በሙያ፣ በስፖርት ወይም ሌሎች ክለቦች፣ በልዩ ልዩ ማኀበሮች ወይም ክበቦች አካባቢና በተለይም የገንዘብ ማሰባሰቡ የተደረገው ለበጐ አድራጐት ወይም ለሥራቸው ማስኬጃ እንደሆነ፤ የዚህ አንቀጽ ድንጋጌ ተፈጻሚ አይሆንም።

  ምንጭ:
  የ፲፱፻፺፮ ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ
 • loader Loading content ...
 • @በህግ አምላክ   4 days ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!

  የ፲፱፻፺፮ ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ ፥ በሰዎችና በንብረቶች ላይ የሚፈፀሙ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች ፥ ምዕራፍ ሦስት ፥ በንብረት ላይ የሚፈፀሙ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች ፥ ክፍል ሁለት ፥ ሌሎች ንብረቶችን መጠበቅ


  አንቀጽ ፰፻፶፩ የመንግሥት እና የግል ንብረቶችን መጠበቅ
  ማንም ሰው በወንጀል ሕጉ በአንቀጽ ፮፻፹፭-፮፻፹፯ መሠረት ከሚያስቀጡት ሁኔታዎች ውጭ፣ የመንግሥት ወይም የግል ንብረትን ለመጠበቅ የወጣ ሕግን፣ ደንብን ወይም መመሪያን የተላለፈ በተለይም፡-
  ሀ/ በሚገባ ሳይፈቀድለት በመንግሥት ወይም በግል ይዞታ ስር ከሆነ መሬት ላይ አፈር፣ ድንጋይ፣ እንጨት፣ አሸዋ ወይም ከመሬት ላይ የሚገኝ ሌላ ነገር፣ ሣር፣ በመደዳ የተተከሉ ዕፅዋቶችን፣ አትክልት ወይም ፍራፍሬ ወይም ሌላ ነገር የወሰደ፣ ወይም
  ለ/ በማናቸውም ወቅት ቢሆን ሳይፈቀድለት ወይም መብት ሳይኖረው በታጠረ ወይም በተዘራ መሬት ወይም አዝመራ ወይም ፍሬ በያዘ መሬት መካከል የገባ ወይም ያለፈ ወይም በእንደዚህ ዓይነቱ ቦታ ላይ የቀንድ ወይም የጋማ ከብቶቹን እንዲያልፉ የነዳበት፣ የለቀቀ ወይም አሰማርቶ ያስጋጠ፤ ወይም
  ሐ/ በተከለከለ የአደን ወይም የዓሣ ማጥመጃ ስፍራ ውስጥ በሕገ-ወጥ መንገድ የገባ፤
  እንደሆነ በመቀጮ ወይም በማረፊያ ቤት እስራት ይቀጣል።

  አንቀጽ ፰፻፶፪ ቀላል ስርቆት
  ፩ ማንም ሰው በችግር ወይም በፍላጐት ተነሳስቶ ወይም ሕሊና በማጣት ባለአነስተኛ ዋጋ የሆነውን የሌላ ሰው ንብረት ወዲያውኑ ሊበላው ወይም ሊገለገልበት የወሰደ እንደሆነ፤
  ከሃምሳ ብር በማይበልጥ መቀጮ ወይም ከአሥራ አምስት ቀን በማይበልጥ የማረፊያ ቤት እስራት ይቀጣል።
  ጥፋተኛው ስርቆቱን የፈፀመው በአግባቡ በተረጋገጠ ችግር ወይም እጦት ወይም ተገፋፍቶ እንደሆነ፤ ፍርድ ቤቱ ቅጣት ላይወስንበት ይችላል።
  ፪ ወደላይ በሚቆጠር ወላጅ፣ ወደታች በሚቆጠር ልጅ ወይም ባልተፋታ የትዳር ጓደኛ ላይ የተፈጸመ ቀላል ስርቆት የሚያስቀጣ አይሆንም።
  ፫ የተሰረቀው ነገር ባለአነስተኛ ዋጋ መሆን አለመሆን፤ ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና የማግኘት አሳብ /አንቀጽ ፮፻፷፭/ ለቀላል ስርቆት ተቀባይነት ይኑረው አይኑረው የሚለው መመዘን ያለበት እንደነገሩ ሁኔታ፣ በአካባቢው ልማድ መሠረት እና የተሰረቀውን ነገር በማየት ይሆናል።

  አንቀጽ ፰፻፶፫ እሸት መቅጠፍና ከማሣ መቃረም
  ማንም ሰው በዓመቱ በመናቸውም ወቅት፡-
  ሀ/ እስፍራው ላይ ለመብላት የሌላ ሰው ንብረት የሆነውን ፍራፍሬ፣ የእህል እሸት፣ አትክልት እና ሌሎች የእርሻ ወይም አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ያለፍቃድ የቀጠፈ ወይም የለቀመ እንደሆነ፤ ወይም
  ለ/ በሌላ ሰው ይዞታ ስር ካሉ እርሻዎች፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ቦታዎች ወይም ሰብላቸው በሙሉ መጥለቂያ መካከል ባለው ሰዓት፤ እህሎችን፣ ፍራፍሬዎችንና ይህን የመሳሰሉ ሌሎች ነገሮችን የቃረመ፣ የሰበሰበ ወይም የለቀመ እንደሆነ፤
  ከዚህ በላይ በተመለከተው ቅጣት ይቀጣል።

  አንቀጽ ፰፻፶፬ አጠራጣሪ የሆኑትን አንዳንድ ዕቃዎች ያለምክንያት መያዝ
  ማንም ሰው ከየት እንዳመጣቸው ወይም ለምን አገልግሎት እንደሚጠቀምባቸው በበቂ ምክንያት ለማስረዳት የማይቻለው ሆኖ ቁልፎችን፣ መክፈቻዎችን፣ የቁልፍ ማንጠልጠያ ቀለበቶችን፣ ጉጠቶችን፣ ልዩ ልዩ ምሣሮችን፣ መሣሪያዎችን፣ ባለዋጋ የሆኑ ሰነዶችን ወይም ሌሎች ዕቃዎችን ይዞ የተገኘ እንደሆነ፤
  ከአንድ መቶ ብር በማይበልጥ መቀጮ ወይም ከአሥራ አምስት ቀን በማይበልጥ የማረፊያ ቤት እሥራት ይቀጣል።

  አንቀጽ ፰፻፶፭ ንብረቶችን መሰወርና አግባብ ላለው ባለሥልጣን አለማስታወቅ
  ማንም ሰው፡-
  ሀ/ ሌላ ሰው የረሳውን ወይም የጠፋበትን ዋጋ ያለው ዕቃ ወይም መሬት ተቀብሮ የተገኘን ዕቃ /አንቀጽ ፮፻፹/ አግኝቶ፤ ወይም
  ለ/ በስርቆት ወይም በንብረት ላይ በተፈፀመ ሌላ ወንጀል የተገኘውን ማናቸውም ዓይነት ዕቃ ሳያውቅ ከሌላ ሰው ካገኘ ወይም ከተቀበለ በኋላ ንብረቱ የወንጀል ውጤት መሆኑን ጠርጥሮ፣ አውቆ ወይም አረጋግጦ፤
  ሁኔታዎችና ሌሎች የአካባቢ ምክንያቶች እንዲያስታውቅ እንደፈቀዱለት ወዲያውኑ አግባብ ላለው ባለሥልጣን ሳያሳውቅ የቀረ እንደሆነ፤
  በመቀጮ ወይም ከአንድ ወር በማይበልጥ የማረፊያ ቤት እሥራት ይቀጣል።

  አንቀጽ ፰፻፶፮ የሌላ ሰውን ንብረት ማበላሸት ወይም ዋጋው እንዲቀንስ ማድረግ
  ማንም ሰው በወንጀል ሕጉ በአንቀጽ ፮፻፹፱ እና ፮፻፺(፩) መሠረት ከሚያስቀጡት ሁኔታዎች ውጭ፣ በጥሩ ሁኔታ የመያዝ ኃላፊነት ያለበትን የሌላውን ሰው ቤት፣ ህንፃ ወይም ግድግዳ በበቂ ሁኔታ ባለመያዝ ወይም ባለመጠገን፣ በሌላ ሰው መሬት ላይ የግንባታ ሥራዎችን በማድረግ፣ መግቢያ መውጫ በማሳጣት፣ አንዳንድ ማቴሪያሎችን ወይም ዕቃዎችን በመጣል፣ የውሃ ወይም የሌላ ፍሳሽ መፍሰሻ ቦዮችን አቅጣጫ በመቀየር ወይም በተገቢ ሁኔታ ባለመያዝ፣ ተሽከርካሪዎችን ወይም ጐታች የጭነት ወይም የግልቢያ እንስሳዎችን በመጥፎ ሁኔታ ወይም ከተገቢው ፍጥነት በላይ በመንዳት ወይም አብዝቶ በመጫን፣ የጦር መሣሪያዎችን ወይም ሌሎች መሣሪያዎችን አጠቃቀም ሳያውቅ ወይም በግዴለሽነት በመጠቀም ወይም በቸልተኛነት የሌላውን ሰው ንብረት ያበላሸ ወይም ዋጋው እንዲቀንስ ያደረገ እንደሆነ፤
  በመቀጮ ወይም በማረፊያ ቤት እስራት ይቀጣል።

  አንቀጽ ፰፻፶፯ በሕዝብ ሀውልቶች ላይ ጉዳት ማድረስ
  ማንም ሰው ከባድ ጉድለት ሲደርስ በወንጀል ሕጉ በአንቀጽ ፮፻፺(፪) መሠረት ከሚያስቀጣው ሁኔታ ውጭ፣ ለሕዝብ አገልግሎት ወይም መደሰቻ ተብሎ የተሠራውን ሐውልት፣ ህንፃ ወይም የተቀረፀ የመታሰቢያ ምስል ወይም ይህን መሰል ሌላ ሥራን ያበላሸ ወይም ያቆሸሸ እንደሆነ፤
  በመቀጮ ወይም በማረፊያ ቤት እሥራት ይቀጣል።

  ምንጭ:
  የ፲፱፻፺፮ ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ
 • loader Loading content ...
 • @በህግ አምላክ   4 days ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!

  የ፲፱፻፺፮ ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ ፥ በሰዎችና በንብረቶች ላይ የሚፈፀሙ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች ፥ ምዕራፍ ሦስት ፥ በንብረት ላይ የሚፈፀሙ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች ፥ ክፍል አንድ ፥ ብሔራዊ ሀብቶችን መጠበቅ


  አንቀጽ ፰፻፵፱ ታሪካዊ፣ ኪነ-ጥበባዊ እና የተፈጥሮ ሀብቶችን መጠበቅ
  ማንም ሰው በወንጀል ሕጉ መሠረት ከሚያስቀጣው ሁኔታ ውጭ፡-
  ሀ/ ታሪካዊ፣ የጥንታዊ ቅሪት /አርኪኦሎጂካዊ/ ወይም ኪነ-ጥበባዊ ሀብቶችን፣ የተፈጥሮ መስህብነት ያላቸውን የተጠበቁ ስፍራዎች፣ ምንጮች ወይም ማናቸውም ዓይነት ብሔራዊ ሀብቶች ስለመጠበቅ፤ ወይም
  ለ/ ብሔራዊ ጠቀሜታ ያላቸው ታሪካዊ፣ የጥንታዊ ቅሪት /አርኪኦሎጂካል/፣ መልክአምድራዊ ወይም ተፈጥሮአዊ ሀብቶች መገኘታቸውን መግለጽን ግዴታ ስለመሆኑ፤ ወይም በቅርሶች ወይም በውድ ወይም በተከለከሉ ማናቸውም ዓይነት ነገሮች ስለመነገድ ወይም እነዚህኑ ወደውጭ ስለመላክ ወይም ወደአገር ውስጥ ስለማስገባት፣ ስለመከልከል፣ ስለመወሰን፣ ወይም ስለመቆጣጠር፤ ወይም
  ሐ/ ታሪካዊ ወይም ጥንተ-ቅሪታዊ ሀውልቶችን፤ ተፈጥሮአዊ መስህብ ያለው ስፍራን ወይም በተለይ የተጠበቀ ቦታን ዋጋ ስለመጉዳት፣ ስለማበላሸት፣ ወይም ጉዳት ላይ ስለመጣል፤
  የወጣውን ሕግ፣ ደንብ ወይም መመሪያ የጣሰ እንደሆነ፤
  በመቀጮ ወይም በማረፊያ ቤት እሥራት ይቀጣል።

  አንቀጽ ፰፻፶ እፅዋትንና እንስሳት መጠበቅ
  ማንም ሰው ብሔራዊ ዕፅዋትንና ደንን፣ እንስሳትንና የዱር አራዊትን ስለመጠበቅ የወጣውን ሕግ፣ ደንብ ወይም መመሪያ የጣሰ እንደሆነ፤
  በመቀጮ ወይም በማረፊያ ቤት እስራት ይቀጣል።

  ምንጭ:
  የ፲፱፻፺፮ ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ
 • loader Loading content ...
 • @በህግ አምላክ   4 days ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!

  የ፲፱፻፺፮ ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ ፥ በሰዎችና በንብረቶች ላይ የሚፈፀሙ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች ፥ ምዕራፍ ሁለት ፥ በሰዎች ላይ የሚፈፀሙ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች ፥ ክፍል ሁለት ፥ በመልካም ጠባይ /ሞራሊቲ/ ላይ የሚፈፀሙ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች


  አንቀጽ ፰፻፵፭ በመልካም ሥነ ምግባርና መልካም ጠባይ /ሞራሊቲ/ ላይ የሚፈፀሙ ጥፋቶች
  ማንም ሰው በወንጀል ሕጉ በአንቀጽ ፮፻፴፱-፮፻፵፩ መሠረት ከሚያስቀጡት ሁኔታዎች ውጭ፣ በአደባባይ ወይም ሕዝብ በሚያየው ቦታ መልካም ሥነ-ምግባርን ወይም መልካም ጠባይን የሚነካ ድርጊት አስቦ የፈጸመ እንደሆነ፤
  በመቀጮ ወይም በማረፊያ ቤት እሥራት ይቀጣል።

  አንቀጽ ፰፻፵፮ አስነዋሪ የዝሙት ጥያቄ እና የብልግና ተግባር
  ማንም ሰው በመንገድ፣ በአደባባይ ወይም ለሕዝብ ክፍት በሆነ ሥፍራ፡-
  ሀ/ መልካም ስነ-ምግባርን ወይም መልካም ጠባይን በሚቃረን መንገድ፣ ያልፈለገውን ወይም ያልጠየቀውን ሰው በድሪያ መልክ በመነካካት ያበሳጨው፤ ወይም
  ለ/ ተገቢ ባልሆነ ጥያቄ ሌላው ሰው የግብረ ሥጋ ግንኙነት ወይም ለመልካም ስነ-ምግባር ተቃራኒ የሆነ ድርጊት ወይም በኀብረተሰቡ የተወገዙ ማናቸውንም ዓይነት የብልሹነት ድርጊት እንዲፈጽም የገፋፋ፤ ወይም
  ሐ/ በዝሙት ወይም በኀብረተሰቡ በተወገዙ ይህን መሰል ድርጊቶች በመሠማራት የጐረቤቶቹን ወይም የአካባቢውን ነዋሪዎች ያወከ፤
  እንደሆነ፤ በመቀጮ ወይም ከአንድ ወር በማይበልጥ የማረፊያ ቤት እሥራት ይቀጣል።

  አንቀጽ ፰፻፵፯ ለብልግና ተግባር የሚያነሳሳ ማስታወቂያና መግለጫ ማውጣት
  ማንም ሰው የብልግና ተግባርን ለማበረታታት ወይም የሌላውን ሰው ፍትወተ ሥጋ ለማርካት ሲል ዝሙት የፈለገ ሰው በእንደዚህ ዓይነት ቦታ ራሱን ሊያስደስት ይችላል ብሎ በማናቸውም ዘዴ በይፋ ያስታወቀ እንደሆነ፤
  በመቀጮ ወይም በማረፊያ ቤት እሥራት ይቀጣል።

  አንቀጽ ፰፻፵፰ የማስወረጃ ዘዴዎችን ማስተዋወቅ
  ማንም ሰው በሕግ ከተፈቀደው ውጭ ፅንስን ለማስወረድ የታቀዱ ዘዴዎችን ወይም ምርቶችን ያስተዋወቀ ወይም ለሽያጭ ያቀረበ ወይም የማስወረድ አገልግሎት እሰጣለሁ ብሎ በይፋ ያስተዋወቀ እንደሆነ፤
  በመቀጮ ወይም በማረፊያ ቤት እስራት ይቀጣል።

  ምንጭ:
  የ፲፱፻፺፮ ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ
 • loader Loading content ...
 • @በህግ አምላክ   4 days ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!

  የ፲፱፻፺፮ ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ ፥ በሰዎችና በንብረቶች ላይ የሚፈፀሙ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች ፥ ምዕራፍ ሁለት ፥ በሰዎች ላይ የሚፈፀሙ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች ፥ ክፍል አንድ ፥ ለሰውነት ጥበቃ የወጡ ደንቦችን መተላለፍ


  አንቀጽ ፰፻፵ የእጅ እልፊትና ቀላል የኃይል ድርጊት
  ማንም ሰው በወንጀል ሕጉ በአንቀጽ ፭፻፷(፩) መሠረት ከሚያስቀጣው ሁኔታ ውጭ፡-
  ሀ/ ሌላውን ሰው ሳይመታ ወይም ሳያቆስል የእጅ እልፊት ወይም ቀላል የኃይል ድርጊት የፈጸመበት እንደሆነ፤ ወይም
  ለ/ በሌላ ሰው ላይ ቆሻሻ፣ የሚያውክ ወይም የሚቀነቅን ወይም የሚያቆሽሽ ጠጣር ነገር ወይም ፈሳሽ የጣለበት ወይም ያፈሰሰበት ወይም የወረወረበት እንደሆነ፤
  ከአንድ መቶ ብር በማይበልጥ መቀጮ ወይም ከስምንት ቀን በማይበልጥ የማረፊያ ቤት እስራት ይቀጣል።

  አንቀጽ ፰፻፵፩ አስከሬን ወይም ቁስለኛን አለማስታወቅ
  ማንም ሰው፡-
  ሀ/ ለሚመለከተው ባለሥልጣን ሳያስታውቅ ሞቶ የተወለደን ወይም ሞቶ የተወለደ ነው የተባለውን ሕፃን ወይም ሌላ የሰው ሬሳን የደበቀ፣ የቀበረ፣ ውሃ ውስጥ የጣለ፣ ያቀጠለ ወይም በማናቸውም ሌላ ሁናቴ እንዲጠፋ ያደረገ ወይም ሬሳን አግኝቶ ለተባለው ባለሥልጣን ሳያስታውቅ የቀረ፤ ወይም
  ለ/ ባልሞት ባይ ተጋዳይነት ወይም በአስገዳጅ ሁኔታ ምክንያት ሌላውን ሰው አቁስሎ ወይም ገድሎ ይህንኑ ለሚመለከተው ባለሥልጣን ሳያስታውቅ የቀረ፤
  እንደሆነ በመቀጮ ወይም በማረፊያ ቤት እስራት ይቀጣል።

  አንቀጽ ፰፻፵፪ በግል ነፃነት ላይ የሚፈፀሙ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች
  ማንም ሰው በወንጀል ሕጉ በአንቀጽ ፭፻፹፭ መሠረት ከሚያስቀጣው ሁኔታ ውጭ፣ ለአካለመጠን ያልደረሰ ልጅን፣ ኃላፊነት የሌለበትን ወይም የአእምሮ ጉድለት ያለበትን ሰው ወይም በሕግ ወይም በሌላ መንገድ በእርሱ ጥበቃ ስር የሆነውን ሰው በመንግሥት ወይም በግል ተቋም ውስጥ እንዲገባ ወይም በቁጥጥር እንዲውል ወይም የተባለውን ሰው ከደንብ ውጭ ወይም በሕግ ከተቀመጡት የጥንቃቄ እርምጃዎች ተቃራኒ በሆነ መልኩ በእንደዚህ ዓይነቱ ተቋም ውስጥ እንዲገባ ወይም ቁጥጥር ስር እንዲውል ያደረገ እንደሆነ፤
  በመቀጮ ወይም በማረፊያ ቤት እሥራት ይቀጣል።

  አንቀጽ ፰፻፵፫ የግል ምስጢር የመጠበቅ መብትን መንካት
  ማንም ሰው የፈፀመው ጥፋት ቀላል በመሆኑ ምክንያት በወንጀል ሕጉ አንቀጽ ፮፻፮ የተመለከተውን ቅጣት የማያስወስንበት ሆኖ ሲገኝ የሌላውን የግል ሕይወቱንና የኑሮውን ወይም በደብዳቤ የሚላላከውን የግል ምስጢሩን የገለፀበት እንደሆነ፤
  በመቀጮ ወይም ከአሥራ አምስት ቀን በማይበልጥ የማረፊያ ቤት እስራት ይቀጣል።

  አንቀጽ ፰፻፵፬ በክብር ላይ የሚፈጸሙ ቀላል ጥፋቶች
  በወንጀል ሕጉ በአንቀጽ ፮፻፲፭ መሠረት መቀጣት የማይገባቸው ቀላል የስድብ ወይም የማዋረድ ድርጊቶች በተፈጸሙ ጊዜ በተለይም ስድቡ ወይም ማዋረዱ ያልተሰራጨ ወይም ሦስተኛ ወገኖችን ወይም ተበዳዩን ያልገባው ሲሆን፣ ተበዳዩ አፀፋውን በሚመልስበት ወይም ጥፋተኛው በተናገረው ተጸጽቶ ይቅርታ በሚጠይቅበት ጊዜ ከቅጣት ነፃ ስለማድረግ የተመለከቱት አጠቃላይ ድንጋጌዎች እንደተጠበቀ ሆነው ፍርድ ቤቱ እሰከ አንድ መቶ ብር ለመድረስ የሚችል መቀጮ ወይም እስከ ስምንት ቀን ለመድረስ የሚችል የማረፊያ ቤት እስራት ሊወስን ይችላል።

  ምንጭ:
  የ፲፱፻፺፮ ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ
 • loader Loading content ...
 • @በህግ አምላክ   4 days ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!

  የ፲፱፻፺፮ ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ ፥ በሰዎችና በንብረቶች ላይ የሚፈፀሙ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች ፥ ምዕራፍ አንድ ፥ ጠቅላላ ድንጋጌዎች


  አንቀጽ ፰፻፴፰ በዚህ ርዕስ ሥር ባልተሸፈኑ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች ያለውን ተካፋይነት የሚመለከት ጠቅላላ ድንጋጌ
  ድርጊቱ በወንጀል ሕጉ ወይም በሌላ የተለየ ሕግ ድንጋጌ መሠረት የሚያስቀጣ ካልሆነ በቀር፣ ማንም ሰው በዚህ የደንብ መተላለፍ ሕግ ልዩ ድንጋጌዎች ውስጥ ከተመለከተው ውጭ ሰዎችን ወይም ንብረትን ለመጠበቅ የወጣውን ሕግ፣ ደንብ፣ ትዕዛዝ፣ መመሪያ ወይም የጥንቃቄ እርምጃ የጣሰ እንደሆነ፤
  በዚህ የደንብ መተላለፍ ሕግ ጠቅላላ ድንጋጌዎች መሠረት በሚወሰን መቀጮ ወይም የማረፊያ ቤት እስራት ይቀጣል።

  አንቀጽ ፰፻፴፱ የሕግ ሰውነት የተሰጠው ድርጅት በዚህ ርዕስ ሥር በተመለከቱት የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች ያለው ተካፋይነት
  ፩ የሕግ ሰውነት የተሰጠው ድርጅት ሃላፊ ወይም ሠራተኛ ከድርጅቱ ሥራ ጋር በተያያዘ ሁኔታ የድርጅቱን ጥቅም በሕገወጥ መንገድ ለማራመድ በማሰብ ወይም የድርጅቱን ህጋዊ ግዴታ በመጣስ፣ ወይም ድርጅቱን በመሳሪያነት ያለአግባብ በመጠቀም በደንብ ተላላፊነት /አንቀጽ ፴፪ እና ፴፬/ ሕግን፣ ደንብን ወይም መመሪያን በመጣስ በዚህ ርዕስ ከተመለከቱት ድንጋጌዎች አንዱን በሚተላለፍበት ጊዜ፣ ቀጣሪው ድርጅት ፯፻፶፪ እና ፯፻፷፰-፯፻፸ በተመለከተው መሠረት ይቀጣል።
  ፪ ከላይ በንዑስ አንቀጽ ፩ በተመለከተው ሁኔታ የደንብ መተላለፍ ጥፋት በሚፈፀም ጊዜ በድርጅቱ የሥራ አመራር ውስጥ ባለው የሥራ ድርሻ የተነሳ በደንብ መተላለፍ ጥፋቱ ተካፋይ የሆነ የድርጅቱ ኃላፊ ወይም ሠራተኛ በዚህ ርዕስ ስር በተመለከቱት አግባብነት ባላቸው ድንጋጌዎች መሠረት ይቀጣል።

  ምንጭ:
  የ፲፱፻፺፮ ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ
 • loader Loading content ...
 • @በህግ አምላክ   4 days ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!

  የ፲፱፻፺፮ ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ ፥ በሕዝባዊና በማህበራዊ ጥቅሞች ላይ የሚፈፀሙ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች ፥ ምዕራፍ አራት ፥ በመንግሥት የሥራ ግዴታዎች እና በመንግሥት መሥሪያ ቤት /ባለሥልጣን/ ላይ የሚፈፀሙ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች ፥ ክፍል ሁለት ፥ በመንግሥት መሥሪያ ቤት ላይ የሚፈፀሙ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች


  አንቀጽ ፰፻፪ ኦፊሴላዊ ማስታወቂያዎችን መጉዳት
  ማንም ሰው በወንጀል ሕጉ በአንቀጽ ፬፻፴፪ መሠረት ከሚያስቀጣው ሁኔታ ውጭ፣ በአደባባይ የተለጠፈውን ኦፊሴላዊ ማስታወቂያ ወይም መግለጫ /ፕላካርድስ/ ከስፍራው ያነሳ፣ የቀደደ፣ ያበላሸ፣ የሰረዘ፣ የደለዘ፣ አስቦ የጐዳ ወይም ያቆሸሸ እንደሆነ፤
  ከአንድ መቶ ብር በማይበልጥ መቀጮ ወይም ከአሥራ አምስት ቀን በማይበልጥ የማረፊያ ቤት እሥራት ይቀጣል።

  አንቀጽ ፰፻፫ አስገዳጅ የሆኑ ኦፊሴላዊ መግለጫዎችን ወይም የሚመዘገቡ ነገሮችን አለመስጠት ወይም አለማስመዝገብ
  ፩ ማንም ሰው በወንጀል ሕጉ በአንቀጽ ፬፻፴፬ ወይም በሌላ ልዩ ሕግ ድንጋጌ መሠረት ከሚያስቀጡት ውጭ፣ መስጠት ወይም ማስመዝገብ የሚገባውን ማናቸውንም ዓይነት ኦፊሴላዊ መግለጫ ወይም ተመዝጋቢ ነገር በሕግ በተወሰነው ጊዜ ውስጥ ሳይሰጥ ወይም ሳያስመዘግብ የቀረ እንደሆነ፤
  በመቀጮ ወይም ከአሥራ አምስት ቀን በማይበልጥ የማረፊያ ቤት እሥራት ይቀጣል።
  ፪ ጤናን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ስለሚሰጡ የሙያ መግለጫዎች የሚመለከተው ልዩ ድንጋጌ /አንቀጽ ፰፻፴፭/ እንደተጠበቀ ነው።

  አንቀጽ ፰፻፬ ተገቢ ያልሆነ ማስታወቂያ
  ማንም ሰው በወንጀል ሕጉ በአንቀጽ ፬፻፴፭ እና ፬፻፶፩ መሠረት ከሚያሰቀጡት ሁኔታዎች ውጭ፣ የአንድ የመንግሥት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ተግባሮችን፣ ውይይቶችን ወይም ውሳኔዎችን መግለፅ የሚከለክለውን ኦፊሴላዊ ሕግ የጣሰ እንደሆነ፤
  በመቀጮ ወይም በማረፊያ ቤት እሥራት ይቀጣል።

  አንቀጽ ፰፻፭ በሌለው ሥልጣን መገልገል
  ማንም ሰው በወንጀል ሕጉ በአንቀጽ ፬፻፴፮ ከሚያስቀጡት ሁኔታዎች ውጭ፣ በሕግ አግባብ ያጣውን ወይም ለሌላ ሰው ያስተላለፈውን ወይም በፍርድ ለጊዜው የታገደበትን ወይም እሰከ ጭራሹ የተከለከለውን ሥልጣን እንዳለ በማድረግ አውቆ የተገለገለበት እንደሆነ፤
  በመቀጮ ወይም በማረፊያ ቤት እሥራት ይቀጣል።

  አንቀጽ ፰፻፮ ባለሥልጣንን የመርዳት እንቢታ
  ማንም ሰው በወንጀል ሕጉ በአንቀጽ ፬፻፵ ከሚያስቀጡት ሁኔታዎች ውጭ፣ የሥራ ግዴታውን እያከናወነ ያለ አንድ የመንግሥት ሠራተኛ ላንድ ለተወሰነ ዓላማ በተለይም የሕዝብ ሰላም መናወፅን፣ የወንጀል መፈፀምን ወይም የወንጀለኛ ማምለጥን ለመከላከል የሚረዳውን እጅግ አስፈላጊ የሆነውን እርዳታ ወይም ድጋፍ እንዲሰጠው ሲጠራው ወይም ሲጠይቀው ከአቅም በላይ የሆነ ኃይል ሳያጋጥመው ወይም የተጠየቀውን እርዳታ ቢሰጥ በራሱ ወይም በንብረቱ ላይ የሚደርስበት አደጋ ሳይኖር እምቢ ያለ እንደሆነ፤
  ከአንድ መቶ ብር በማይበልጥ መቀጮ ወይም ከአንድ ወር በማይበልጥ የማረፊያ ቤት እሥራት ይቀጣል።

  አንቀጽ ፰፻፯ ትዕዛዝን አለመፈፀም
  ፩ ማንም ሰው በወንጀል ሕጉ በአንቀጽ ፬፻፵ ከሚያስቀጡት ሁኔታዎች ውጭ፡-
  ሀ/ ስሙን ወይም ማንነቱን እንዲነግር፣ ሥራውን ሙያውን፣ መኖሪያ ስፍራውን፣ አድራሻውን ወይም የግል ሁኔታውን የሚመለከት ማናቸውንም ሌላ ዝርዝር ጉዳይ እንዲገልጽ፤ ወይም
  ለ/ እንዲቆም ወይም እንዲንቀሳቀስ/እንዲሄድ፣ የሕዝበ መተላለፊያ መንገድን እንዲለቅ፣ የያዛቸውን ሰነዶች፣ የጉዞ እቃዎች ወይም አጠራጣሪ የሆኑ ማናቸውንም ነገሮች እንዲያስፈትሽ ወይም ይህን የመሳሰለውን ማናቸውንም ሌላ ትዕዛዝ እንዲፈጽም፤
  የሥራ ግዴታውን በሚያከናውን አንድ የመንግሥት ሠራተኛ በአግባቡ ሲጠየቅ ወይም ሲታዘዝ እንቢተኛ የሆነ እንደሆነ፤
  ከአንድ መቶ ብር በማይበልጥ መቀጮ ወይም ከአንድ ወር በማይበልጥ የማረፊያ ቤት እስራት ይቀጣል።
  ፪ ማንም ሰው በዚህ አንቀጽ በንዑስ አንቀጽ /፩/ በፊደል (ሀ) ውስጥ የተመለከተውን ጉዳይ አስመልክቶ ያልሆነ መረጃ የሰጠ እንደሆነ፤ በተመሳሳይ ቅጣት ይቀጣል።

  ምንጭ:
  የ፲፱፻፺፮ ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ
 • loader Loading content ...
 • @በህግ አምላክ   4 days ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!

  የ፲፱፻፺፮ ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ ፥ በሕዝባዊና በማህበራዊ ጥቅሞች ላይ የሚፈፀሙ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች ፥ ምዕራፍ አራት ፥ በመንግሥት የሥራ ግዴታዎች እና በመንግሥት መሥሪያ ቤት /ባለሥልጣን/ ላይ የሚፈፀሙ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች ፥ ክፍል አንድ ፥ በመንግሥት የሥራ ግዴታዎች ላይ የሚደረጉ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች


  አንቀጽ ፯፻፺፮ በሥልጣን ያለአግባባ መገልገል
  ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ ፬፻፯ ከሚያስቀጣው ውጭ፣ ከተሰጠው ሥልጣን በላይ አሳልፎ የሠራ ወይም በሥልጣኑ አላግባብ የተገለገለበት እንደሆነ፤
  በመቀጮ ወይም ከሦስት ወር በማይበልጥ የማረፊያ ቤት እሥራት ይቀጣል።

  አንቀጽ ፯፻፺፯ የማስገደድ መብትን ከመጠኑ ማሳለፍ
  በወንጀል ሕጉ በአንቀጽ ፬፻፳፪-፬፻፳፬ መሠረት ከሚያስቀጡት ሁኔታዎች ውጭ ቤትን የመበርበር፣ ዕቃን የመያዝ ወይም የመውረስ፣ የማሸግ ወይም እሽግን የማንሣት፣ አካልን የመፈተሽ ወይም የመመርመር፣ ሰውን የመያዝ፣ የማሰር፣ በቁጥጥር ስር የማድረግ፣ የምርመራ ቃልን የመቀበል ወይም ይህን የመሰለ ማናቸውም ሌላ ተግባር እንዲፈጽም በሕግ ሥልጣን የተሰጠው የመንግሥት ሠራተኛ ይህንን ሥልጣኑን በተለይም የሚያበሳጭ፣ የሚያሳዝን፣ መልካም ሥርዓትን ያልተከተለ ወይም ትክክል ያልሆነ ዘዴን በመጠቀም ያለአግባብ የተገለገለበት እንደሆነ፤
  በመቀጮ ወይም በማረፊያ ቤት እሥራት ይቀጣል።

  አንቀጽ ፯፻፺፰ ሐቀኛነትን ማጓደል
  ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ በወንጀል ሕጉ በአንቀጽ ፬፻፲፩-፬፻፲፱ መሠረት ከሚያስቀጡት ሁኔታዎች ውጭ ሐቀኝነት የጐደለውን ድርጊት ለመፈጸም ሲል በተሰጠው ሥልጣን ያለአግባብ የተገለገለበት እንደሆነ፤
  በመቀጮ ወይም በማረፊያ ቤት እሥራት ይቀጣል።

  አንቀጽ ፯፻፺፱ የአድልዎ እርዳታ መስጠት
  ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ በወንጀል ሕጉ በአንቀጽ ፬፻፰፣ ፬፻፱ እና ፬፻፲፬ መሠረት ከሚያስቀጣው ሁኔታ ውጭ፣ ለግል ጥቅሙ ሲል ከእርሱ ዘንድ ጉዳይ ያለውን ወይም በእርሱ ሥልጣን ስር ያለውን ሰው በአድልዎ የረዳ እንደሆነ፤
  በመቀጮ ወይም ከሦስት ወር በማይበልጥ የማረፊያ ቤት እስራት ይቀጣል።

  አንቀጽ ፰፻ በመንግሥት መሥሪያ ቤት የሚሰጡትን ኦፊሴላዊ ወረቀቶችን በግዴለሽነት መስጠት
  ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ፡-
  ሀ/ የተለመደውን የአንድን ሰው ማንነት ማረጋገጫ ዘዴ ሁሉ ተጠቅሞ የተባለውን ሰው ማንነት እና የተባለውን ሰነድ ወይም ኦፊሴላዊ ወረቀት የመቀበል መብቱን አስቀድሞ ሳያረጋግጥ ላልታወቀ ሰው የይለፍ ወረቀት/ፓስፖርት፣ መታወቂያ ደብተር፣ ፈቃድ፣ የወንጀለኞች ሪኮርድ ግልባጭ፣ የመልካም ጠባይ ምስክር ወረቀት ወይም የድሀነት ማስረጃ ወይም በጠቅላላው የአንድን ሰው ማንነት የሚገልፅ ሰነድን ወይም ኦፊሴላዊ የምስክር ወረቀትን የሰጠ፤ ወይም
  ለ/ ሌላው ሰው የሰነዱ ባለቤት አለመሆኑን ወይም በሰነዱ የመጠቀም መብት የሌለው መሆኑን እያወቀ በእንደዚህ ዓይነቱ ሰነድ ወይም ኦፊሴየላዊ ማስረጃ እንዲጠቀምበት የፈቀደለት፤
  እንደሆነ፤ በመቀጮ ወይም ከሦስት ወር በማይበልጥ የማረፊያ ቤት እሥራት ይቀጣል።

  አንቀጽ ፰፻፩ አነስተኛ የሆኑ ጉዳዮች፤ የሥነ ሥርዓት /የዲሲፕሊን/ ቅጣቶች
  አንድ የመንግሥት ሠራተኛ የመንግሥት ሥራውን በሚያከናውንበት ጊዜ አነስተኛ የሆነ የደንብ መተላለፍ ጥፋት የፈጸመ እንደሆነና ፍርድ ቤቱም ለዚህ ጥፋት የዲስፕሊን እርምጃ መውሰድ ብቻ በቂ መስሎ ሲታየው በዚህ ሕግ የተመለከተውን ቅጣት በመተው ለዚህ ውሳኔ የበቃበትን ምክንያት ገልጾ ተገቢ መስሎ የታየውን የዲስፕሊን /አስተዳደራዊ/ ቅጣት እንዲወሰንበት ደንብ ተላላፊው ወደሚመለከተው የአስተዳደር ክፍል አለቃ ያስተላልፈዋል።

  ምንጭ:
  የ፲፱፻፺፮ ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ
 • loader Loading content ...
 • @በህግ አምላክ   4 days ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!

  የ፲፱፻፺፮ ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ ፥ በሕዝባዊና በማህበራዊ ጥቅሞች ላይ የሚፈፀሙ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች ፥ ምዕራፍ ሦስት ፥ ወታደራዊ ግዴታዎችን መጣስ እና በመከላከያ ሠራዊት እንዲሁም በፖሊስ ላይ የሚፈፀሙ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች


  አንቀጽ ፯፻፺፪ ወታደራዊ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶችን መወሰን
  ወታደራዊ ወንጀሎችን በሚመለከቱ በዚህ የወንጀል ሕግ ድንጋጌዎች ውስጥ /አንቀጽ ፪፻፹፬-፫፻፳፭/ ከተደነገጉት ሁኔታዎች ውጭ፣ ወታደራዊ ግዴታዎችን መጣስ እና በወታደራዊ ዲሲፕሊን ላይ የሚፈጸሙ ጥፋቶች፣ አግባብ ያለው የመከላከያ ሠራዊት ባለስልጣን በሚያወጣው ትዕዛዝና ደንብ ይወሰናሉ።

  አንቀጽ ፯፻፺፫ ወታደራዊ የዲስፕሊን ቅጣቶች
  ፩ በወታደራዊ ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ ማንኛውም ማዕረግ ያለው የመከላከያ ሰራዊት አባል ወይም በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ የሚሠራ ማንኛውም ሌላ ሰው፣ የጦር ምርኮኛ ወይም ግዞተኛ አግባብ ባለው የመከላከያ ሠራዊት ደንብ ውስጥ በተመለከተው የዲሲፕሊን ቅጣቶች ይቀጣል።
  ፪ ለነሱ በተለይ ከተመለከቱት ልዩ ሁኔታዎች በቀር /አንቀጽ ፫፻፲፱ እና ፯፻፶፬/ እነዚህ ሰዎች መደበኛ የሆኑ ወንጀሎችን የፈጸሙ እንደሆነ፤ በመደበኛ ድንጋጌዎች ውስጥ በተመለከቱት መደበኛ ቅጣቶች ይቀጣሉ።

  አንቀጽ ፯፻፺፬ በመከላከያ ሠራዊት ላይ የሚፈፀሙ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች
  በመከላከያ ሠራዊት አባል ወይም በመከላከያ ሠራዊት ወይም በእነዚሁ ተቀጽላ አገልግሎቶች ላይ፣ የሚደረግ ማናቸውም ጥፋት እንዲሁም የእነዚህን ጥቅም በሚመለከት አግባብ ባለው ወታደራዊ ባለሥልጣን የሚወጡ ደንቦችን፣ ትዕዛዞችን ወይም የጥንቃቄ እርምጃዎችን መጣስ በወንጀል የሚያስቀጣ ካልሆነ በቀር፣ በደንብ መተላለፍ በመቀጮ ወይም ማረፊያ ቤት እሥራት ያስቀጣል።

  አንቀጽ ፯፻፺፭ ደንቡ ለፖሊስ ሠራዊት ተፈፃሚ መሆኑ
  ፩ ከዚህ በላይ የተመለከቱት መርሆች፣ ስለፖሊስ ግዴታዎችና በግዳጅ ላይ እያሉ ስለሚገባቸው ደህንነት በተደነገጉ ደንቦች ላይ የሚፈፀሙ የደንብ መተላለፍ ቅጣቶችን በሚመለከትም ተፈፃሚ ይሆናሉ።
  ፪ የፖሊስ አባላት እንደ መንግሥት ሠራተኛ ሆነው የሚያከናወኑትን ሥራ የሚመለከቱ ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ናቸው።

  ምንጭ:
  የ፲፱፻፺፮ ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ
 • loader Loading content ...
  Load more...
loader Loading content ...

Comments (0)


  This user has no comment yet.