loader
 • ስለ ሥራ ውል በጠቅላላው ፤ ስለ ሠራተኛው ሥራ (የ፲፱፻፶፪ ዓ.ም. የፍትሐ ብሔር ሕግ ፥ አንቀጽ ፲፮ ፥ ምዕራፍ ፩ ፥ ክፍል ፪)

  @በህግ አምላክ   3 months ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!
 • loader Loading content ...
 • @በህግ አምላክ   3 months ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!

  የ፲፱፻፶፪ ዓ.ም. የፍትሐ ብሔር ሕግ። አንቀጽ ፲፮። የሥራዎች አገልግሎት መስጠትን የሚመለከቱ ውሎች። ምዕራፍ ፩። ስለ ሥራ ውል በጠቅላላው። ክፍል ፪። ስለ ሠራተኛው ሥራ።


  ቁጥር ፪ሺ፭፻፳፫። ግዴታው የራሱ ስለመሆኑ።
  በውሉ ወይም በሁኔታዎቹ ተቃራኒ ነገር ከሌለ በቀር ሠራተኛው ሊሠራው ቃል የሰጠበትን ሥራ ራሱ መፈጸም አለበት።

  ቁጥር ፪ሺ፭፻፳፬። የትጉህነት አሠራር ግዴታ።
  (፩) ሠራተኛው ሥራውን በጥንቃቄ መሥራት አለበት።
  (፪) አስቦ ወይም በቸልተኛነት ወይም ባለመጠንቀቅ በአሠሪው ላይ ለሚያደርሰው ጉዳት አላፊ ነው።
  (፫) አላፊነት አለበት ወይም የለበትም ብሎ ለመገመት የሚቻለው አሠሪው ለሠራተኛው ቃል የሰጠበትን ሥራ ዐይነት እንዲሁም የሠራተኛውን የትምህርት ደረጃ ችሎታዎችና የሥራ ደረጃውን አሠሪው የሚያውቀው ወይም ይገባው የነበረውን ማወቅ መሠረት በማድረግ ነው።

  ቁጥር ፪ሺ፭፻፳፭። የሥራው ሥነ ሥርዐት (ዲሲፕሊን)።
  የሥራውን አፈጻጸም የሚመለከቱ የአሠሪው ትእዛዞች፤ ለውሉ ለሕጉና ለመልካም ጠባይ አንዳችም ተቃራኒነት ከሌላቸውና እነዚህንም መፈጸም አደጋ የማያመጣ ከሆነ ሠራተኛው መታዘዝ አለበት።

  ቁጥር ፪ሺ፭፻፳፮። መሠራት የሚገባው ሥራ። (፩) መሠረቱ።
  ሠራተኛው ሊሠራው ግዴታ የገባበትን ሥራ ብቻ መሥራት አለበት።

  ቁጥር ፪ሺ፭፻፳፯። (፪) ስለ ሥራ መለወጥ።
  (፩) ቢሆንም ተቃራኒ የውል ቃል ከሌለ በቀር አሠሪው ስለ ሥራው ማካሄጃ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ የሠራተኛውን ደመወዝ የሚቀንስ ወይም ከሁኔታው ዋና ነገር የሚለዋወጥ ካልሆነ በቀር ሌላ ልዩ ሥራ መስጠት ይችላል።
  (፪) አዲሱ ሥራ ሠራተኛው ከተቀጠረበት ሥራ ይበልጥ ከፍ ያለ ደመወዝ ያለው እንደሆነ፤ ሠራተኛው ይህን ደመወዝ ለማግኘት መብት አለው።

  ቁጥር ፪ሺ፭፻፳፰። (፫) ስለ ተጨማሪ ሥራ።
  (፩) አሠሪው በውሉ ከተመለከተው በላይ የሥራ ፍሬ እንዲሰጥ ሠራተኛውን መጠየቅ ይችላል።
  (፪) ሠራተኛው ይህን ተጨማሪ ሥራ መሥራት ከቻለና አልሠራም ማለቱም ለቅን ልቡና አሠራር ተቃራኒ የሆነ እንደሆነ፤ ሠራተኛው ይህን ተጨማሪ ሥራ መሥራት አለበት።
  (፫) ሠራተኛውም አስቀድሞ በተስማሙበት ደመወዝ አንጻር በተወሰነውና በሁኔታዎቹ ዐይነት ለዚህ ተጨማሪ ሥራ ተጨማሪ የሥራ ዋጋ ለማግኘት መብት አለው።

  ቁጥር ፪ሺ፭፻፳፱። (፬) በቁጥር ወይም በሙሉ ሥራን ስለ መሥራት።
  (፩) በቁጥር ወይም በሙሉ ሥራው ደመወዝ የሚከፈለው ሠራተኛ አሠሪው ከሆነው ሰው ውሉ በሚጸናበት ጊዜ ሁሉ በቂ የሆነ ብዛት ያለው ሥራ እንዲሰጠው ለመጠየቅ መብት አለው።
  (፪) በቁጥር ወይም በሙሉ የሚሠራ ሥራ፤ ለመስጠት ካልቻለ አሠሪው በሰዓት ወይም በቀን ሠራተኛውን ሊያሠራው ይችላል።

  ቁጥር ፪ሺ፭፻፴። መሣሪያዎችን መሥሪያዎችን (፩) ስለማቅረብ።
  (፩) ተቃራኒ የውል ቃል ወይም ልማድ ከሌለ በቀር ለሥራው አስፈላጊ የሚሆኑትን መሥሪያዎችና መሣሪያዎች ለሠራተኛው የሚያቀርበው አሠሪው ነው።
  (፪) ሠራተኛው ግዴታ ሳይኖርበት በሙሉ ወይም በከፊል ያቀረባቸው እንደሆነ፤ አሠሪው ኪሣራውን ይከፍለዋል።

  ቁጥር ፪ሺ፭፻፴፩። (፪) በጥበቃ ስለ ማኖር።
  ሠራተኛው ለሥራው አፈጻጸም የተሰጡትን ነገሮች በጥንቃቄ መያዝ አለበት።

  ቁጥር ፪ሺ፭፻፴፪። ሠራተኛው ስለሚፈጥረው ነገር።
  (፩) ለአሠሪው ሥራ ሲል ሥራውን በሚሠራበት ጊዜ ቢሆንም እንኳ ሠራተኛው ፈጥሮ ያወጣው ነገር የራሱ ነው።
  (፪) ነገር ግን ሠራተኛው ፈጥሮ ወይም ፈልጎ እንዲያወጣ በተለይ ተቀጥሮ እንደሆነ ለአሠሪው ይሆናል።

  ቁጥር ፪ሺ፭፻፴፫። የሥራ ማካሄጃን ስለሚመለከቱ መግለጫዎች።
  (፩) ሠራተኛው የሥራው ውል ካለቀ በኋላም ቢሆን በሥራው ጊዜ ያወቃቸውን የአሠሪውን ምስጢሮች መጠበቅ አለበት።
  (፪) በአሠሪው ላይ ጉዳት በማድረግ ዐይነት በሥራው ጊዜ ያገኛቸውን መግለጫዎች ሊሠራባቸው አይገባውም፡

  ምንጭ:
  የኢትዮጵያ የ፲፱፻፶፪ ዓ.ም. የፍትሐ ብሔር ሕግ (፲፱፻፶፪)
 • loader Loading content ...

Load more...