loader
 • ስለ እንደራሴነት ጠቅላላ ድንጋጌዎች (የ፲፱፻፶፪ ዓ.ም. የፍትሐ ብሔር ሕግ ፥ አንቀጽ ፲፬ ፥ ምዕራፍ ፩)

  @በህግ አምላክ   3 months ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!
 • loader Loading content ...
 • @በህግ አምላክ   3 months ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!

  የ፲፱፻፶፪ ዓ.ም. የፍትሐ ብሔር ሕግ። አንቀጽ ፲፬። ስለ እንደራሴነት። ምዕራፍ ፩። ጠቅላላ ድንጋጌዎች።


  ቁጥር ፪ሺ፻፸፱። የእንደራሴነት ምንጭ።
  የሌላ ሰው እንደራሴ በመሆን ሥራዎችን የመፈጸም ሥልጣን የሚገኘው ከሕግ ወይም ከውል ነው።

  ቁጥር ፪ሺ፻፹። ስለ ሥልጣን ፎርም።
  ስለ ውሉ አፈጻጸም፤ ሕጉ አንድ ዐይነት ፎርም እንዲደረግ ያስገደደ እንደሆነ ውሉን የሚፈጽምበት ሥልጣን በዚሁ ዐይነት ፎርም ለወኪሉ መስጠት አለበት።

  ቁጥር ፪ሺ፻፹፩። ስለ ሥልጣን ወሰን።
  (፩) የእንደራሴነት ሥልጣን የተገኘው በውል መሠረት የሆነ እንደሆነ፤ ሥልጣኑ የሚወሰነው በተዋዋዮቹ ስምምነት ነው።
  (፪) እንደራሴው የተሰጠውን ሥልጣን ሦስተኛ ወገን ለሆነ ሰው አስታውቆ እንደሆነ፤ በሦስተኛው ሰው ላይ ሥልጣኑ የሚጸናው፤ ባስታወቀው ማስታወቂያ መሠረት ነው።
  (፫) የእንደራሴነት ሥልጣን የሚተረጐመው ሳይስፋፋ በጠባቡ ነው።

  ቁጥር ፪ሺ፻፹፪። ስለ ሥልጣኑ መቅረት።
  (፩) ተቃራኒ የሆነ ውል ከሌለ በቀር፤ እንደራሴው ወይም ሿሚው መሞቱ ወይም የሌለ መሆኑ ወይም ችሎታ የሌለው መሆኑ ወይም ደግሞ መክሠሩ የተገለጸ እንደሆነ ከአንድ ጽሑፍ የተገኘው ሥልጣን ይቀራል።
  (፪) እንዲሁም የሰውነት መብት የተሰጠው ድርጅት መኖሩ ሲቀር ይህ ሥልጣን ይቀራል።

  ቁጥር ፪ሺ፻፹፫። ሥልጣንን ስለ መውሰድ።
  (፩) እንደራሴ ሿሚው በማንኛውም ጊዜ በእሱ ስም ሆኖ እንዲሠራ በሦስተኛ ወገን ሰዎች ፊት ለእንደራሴው የሰጠውን ሥልጣን ሊቀንስበት ወይም ጨርሶ ሊያስቀርበት ይችላል።
  (፪) ይህን መብት የሚያስቀር በውሉ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ ፈራሽ ነው።

  ቁጥር ፪ሺ፻፹፬። እንደራሴነትን ስለ መመለስ።
  (፩) ሥልጣኑን የሚያረጋግጥ ጽሑፍ የተሰጠው እንደራሴ በተሰጠው ሥልጣን የሚሠራበት ጊዜ ሲፈጸም፤ ይህን የተሰጠውን የሥልጣን ጽሑፍ ለሿሚው መመለስ አለበት።
  (፪) እንደራሴው ሒሳቡ ሳይጣራና የሚገባኝን ሿሚው ሳይሰጠኝ የተሰጠኝን ሥልጣን ይዤ እቆያለሁ ለማለት አይፈቀድለትም።

  ቁጥር ፪ሺ፻፹፭። የእንደራሴነቱ ጽሑፍ ስለ መጥፋት።
  እንደራሴው የሹመቱ ወረቀት መጥፋቱን ያስታወቀ እንደሆነ ሿሚው በእንደራሴው ኪሣራ ከፍርድ ቤቱ የእንደራሴነቱን መሰረዝ የሚገልጽ ውሳኔ ለማግኘት ይችላል።

  ቁጥር ፪ሺ፻፹፮። ሥልጣንን ስለ ማረጋገጥ።
  ከአንድ እንደራሴ ጋራ ሕጋዊ ተግባር የፈጸመ የሦስተኛ ወገን ሁል ጊዜ እንደራሴው ሥልጣኑን እንዲያረጋግጥለት ሊያስገድድና እንደዚሁም የእንደራሴነቱ ተግባር በጽሑፍ የተደረገ እንደሆነ፤ እንደራሴው ስለዚሁ ተግባር በሚገባ የፈረመበትን ግልባጭ እንዲሰጠው ለማስገደድ ይችላል።

  ቁጥር ፪ሺ፻፹፯። ተቃዋሚ ጥቅሞች።
  (፩) እንደራሴው በፈጸመው ውል ምክንያት የሿሚውና የእንደራሴው ጥቅሞች የሚቃወሙ የሆኑ እንደሆነ ይህን ውል የፈረመው 3ኛ ወገን ይህን ሁኔታ የወቀና ሊያውቀውም የሚገባ የሆነ እንደሆነ በሿሚው ጥያቄ መሠረት ይህ የተፈጸመው ውል ሊፈርስ ይችላል።
  (፪) ሿሚው የዚሁኑ አካባቢ ሁኔታ ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ሁለት ዓመት ድረስ ውሉን ለማፍረስ አሳቡን ማስታወቅ አለበት።
  (፫) አንደኛው ወገን ተዋዋይ ይህን ማስታወቂያ ከተቀበለ ወዲህ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ውሉን የመቀጠል አሳቡን ያልገለጠ እንደሆነ ውሉ ይፈርሳል።

  ቁጥር ፪ሺ፻፹፰። ከገዛ ራስ ጋራ ስለሚደረግ ውል።
  (፩) እንደራሴው ለራሱ ጒዳይ በመሥራትም ሆነ ወይም በሌላ ሰው ስም ለሌላ ሰው ጒዳይ በመሥራት ውሉን ከራሱ ጋራ ባደረገ ጊዜ ሿሚው ይህ ውል እንዲፈርስ ለመጠየቅ ይችላል።
  (፪) ከዚህ በላይ በተጻፈው ቁጥር በ2ና በ3 ንኡስ ቁጥሮች የተሰጡ ውሳኔዎች ለዚህም ተፈጻሚነት አላቸው።
  (፫) ስለ ኮሚሲዮኔሮች የተሠሩ ልዩ ድንጋጌዎች የተጠበቁ ናቸው።

  ቁጥር ፪ሺ፻፹፱። ፍጹም ስለሆነ እንደራሴነት።
  (፩) እንደራሴው ከወኪልነቱ ሥልጣን ወሰን ሳያልፍ በሌላ ሰው ስም የመዋዋል ተግባሮችን የፈጸመ እንደሆነ፤ እነዚህ በርሱ የተፈጸሙት ተግባሮች በቀጥታ በሿሚው እንደተፈጸሙ ሆነው ይቆጠራሉ።
  (፪) ነገር ግን ውሉ በተደረገበት ጊዜ በእንደራሴው ፈቃድ ላይ የተፈጸሙትን ጒድለቶች ሿሚው ለራሱ ጥቅም ጠቅሶ ሊከራከርባቸው ይችላል።
  (፫) ከእንደራሴው ጋራ የውል ስምምነት ያደረገ ሰው እንደራሴው ባደረሰበት የማሳሳት ጉዳት ሿሚውን ሊከራከረው ይችላል።

  ቁጥር ፪ሺ፻፺። የሥልጣን ወሰን ስለ ማለፍ፤ ወይም ቀሪ ስለሆነ ሥልጣን።
  (፩) እንደራሴው የሥልጣኑን ወሰን በመተላለፍ በሌላ ሰው ስም የሠራ እንደሆነ፤ በስሙ የተሠራለት ሰው ራሱ እንደ ፈቀደ እንደራሴው የፈጸመውን ተግባር ለማጽደቅ ወይም ለማፍረስ ይችላል።
  (፪) እንደዚሁም እንደራሴው ቀሪ በሆነው ሥልጣን መሠረት በሌላ ሰው ስም በሠራ ጊዜ በስሙ የተሠራለት ሰው እንደ ፈቀደ በስሙ የተሠራውን ሥራ ለማጽደቅ ወይም ለመሻር ይችላል።

  ቁጥር ፪ሺ፻፺፩። ለሿሚ ስለ ተሰጠው ምርጫ።
  (፩) ከእንደራሴው ጋራ የተዋዋሉ ሦስተኛ ወገኖች ሿሚው በስሙ የተሠራለትን ሥራ ለማጽደቅ ወይም ለማፍረስ የቆረጠውን ውሳኔ በፍጥነት እንዲያስታውቃቸው ለማስገደድ ይችላሉ።
  (፪) ሿሚው የመቀበሉን ውሳኔ በፍጥነት ሳያስታውቃቸው የቀረ እንደሆነ፤ እንደራሴው የሠራውን ሥራ እንዳልተቀበለው ይቆጠራል።

  ቁጥር ፪ሺ፻፺፪። የመቀበሉ ውጤት።
  ሿሚው እንደራሴው የፈጸመውን ተግባር ያጸደቀ እንደሆነ፤ እንደራሴው የፈጸመውን ተግባር ከውክልናው ሥልጣን ሳያልፍ እንደ ፈጸመው ይቆጠራል።

  ቁጥር ፪ሺ፻፺፫። ያለመቀበል የሚያስከትለው ውጤት።
  (፩) እንደራሴው የሠራውን ሥራ ሿሚው ባልተቀበለው ጊዜ በዚህ ሕግ ስለ ውሎች በጠቅላላው በሚለው አንቀጽ በተለከተው መሠረት ስለ ውሎች መሰረዝና መፍረስ የተነገሩት ድንጋጌዎች ተፈጻሚዎች ይሆናሉ።
  (፪) ከእንደራሴው ጋራ የስምምነቱን ተግባር የፈጸመው ሦስተኛ ወገን የእንደራሴነትን ሥልጣን መኖሩን በቅን ልቡና በማመኑ ስለ ደረሰበት ጉዳት ከዚህ ቀጥሎ ባሉት ቁጥሮች ድንጋጌ መሠረት ካሣ እንዲከፈለው ለመጠየቅ ይችላል።

  ቁጥር ፪ሺ፻፺፬። ስለሚደርሱት አላፊነቶች።
  (፩) ስለ ደረሰው ጉዳት ኪሣራ እንዲከፍል መጠየቅ የሚገባው እንደራሴው ነው።
  (፪) ስለሆነም፤ የእንደራሴነቱን ሥልጣን የሚያስቀረውን ምክንያት ባለማወቅ በቅን ልቡና ሠርቶት እንደሆነ፤ በአላፊነት አይጠየቅም።
  (፫) እንደዚህም በሆነ ጊዜ ስለ ደረሰው ጉዳት ኪሣራ እንዲከፍል የሚጠየቀው ሿሚው ነው።

  ቁጥር ፪ሺ፻፺፭። (፩) ስለ ሿሚው አላፊነት።
  በሌላው በኩል በሚደርሰው ጉዳት ሁሉ ሿሚው ከእንደራሴው ጋራ በሙሉ አላፊ የሚሆነው፤
  (ሀ) ሿሚው ለሌላ ሦስተኛ ወገን የእንደራሴነቱን ሥልጣን አስታውቆ ሳለ፤ የሰጠውን የእንደራሴነት ሥልጣን በሙሉ ወይም በከፊሉ መሰረዙን ለዚያው ለሦስተኛ ወገን ያላስታወቀ እንደሆነ፤
  (ለ) ሿሚው ለእንደራሴው የሰውን የእንደራሴነት ሥልጣን ጽሑፍ እንዲመልስለት እንደራሴውን ከማስገደድ ችላ ያለ እንደሆነና እንዲሁም ይህ ሿሚው የሰጠው የእንደራሴነት ሥልጣን ጽሑፍ በፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲሰረዝ ያላደረገ እንደሆነ፤
  (ሐ) በማናቸውም ሌላ አኳኋን ሿሚው በሚሰጣቸው መግለጫዎች ወይም በሥራው ወይም በአመራሩ ወይም ሊያደርግ የሚገባውን ባማድረጉ ከእንደራሴው ጋራ ስምምነት የሚያደርጉት ሦስተኛ ወገኖች እንደራሴው ይህ ሥልጣን ያለው መስሎዋቸው ስሕተት ያደረሰባቸው እንደሆነ ነው።

  ቁጥር ፪ሺ፻፺፮። ከአላፊነት ውጭ ስለ መሆን።
  (፩) ከእንደራሴው ጋራ የተዋዋለው ሌላ ሦስተኛ ወገን ከመዋዋሉ በፊት የእንደራሴነቱን ሥልጣን ጽሑፍ ዐውቆ የተዋዋለ ከሆነ፤ በነገሩ የማታለል ሥራ ከሌለበት በቀር ከሥልጣኑ አልፎ የሠራውን እንደራሴ ማንኛውንም ኪሣራ ሊጠይቀው አይችልም።
  (፪) እንዲሁም ሦስተኛው ወገን የሚዋዋለው ማንም ቢሆን ግድ የሌለው ከሆነና እንደራሴውም ለሌላ ሰው የተፈጸመውን ውል በራሱ ስም ለማድረግ የተቀበለ እንደሆነ ሦስተኛው ወገን ማንኛውንም ኪሣራ ለመጠየቅ አይችልም።

  ቁጥር ፪ሺ፻፺፯። እንደራሴው በራሱ ስም ስለሚፈጽመው ተግባር።
  (፩) እንደራሴው በራሱ ስም የተዋዋለ እንደሆነ፤ ሌሎች ሦስተኛ ወገኖች ከእንደራሴው ጋራ መዋዋላቸውን ቢያውቁትም እንኳ፤ ከነዚህ ጋራ የፈጸማቸው ተግባሮች ለሚያስከትሉዋቸው ግዴታዎችና መብቶች እሱ ራሱ ባለቤት ይሆናል።
  (፪) እንዲህ በሆነ ጊዜ የተባሉ ሦስተኛ ወገኖች ከሿሚው ጋራ አንዳችም ቀጥታ ግንኙነት የላቸውም፤ ነገር ግን በእንደራሴው ስም ሆነው የእንደራሴውን መብት ከሿሚው ለመጠየቅ ይችላሉ።

  ቁጥር ፪ሺ፻፺፰። ስለ ሿሚው መብቶች።
  (፩) ሌሎች ሦስተኛ ወገኖች በቅን ልቡና ያገኙዋቸው መብቶች እንደተጠበቁ ሆነው እንደራሴው ለሿሚው ሲል በራሱ ስም ያፈራቸውን ተንቀሳቃሽ ንብረቶች፤ ሿሚው ገንዘቦቼ ናቸው ብሎ ለመጠየቅ ይችላል።
  (፪) እንደዚሁም እንደራሴው ለሿሚው ሲል ያገኛቸውን የገንዘብ መብቶች ሿሚው በእንደራሴው ተተክቶ ሊጠይቅ ይችላል።
  (፫) ስለሆነም፤ ሿሚው በበኩሉ በእንደራሴው ዘንድ ያሉበትን ግዴታዎች ፈጽሞ ካልተገኘ በቀር እነዚህን መብቶች ለመጠየቅ አይችልም።

  ምንጭ:
  የኢትዮጵያ የ፲፱፻፶፪ ዓ.ም. የፍትሐ ብሔር ሕግ (፲፱፻፶፪)
 • loader Loading content ...

Load more...