loader
 • በአፄ ምኒልክ እና በጣሊያን መንግስት መካከል የተፈረመው የውጫሌው ውል።

  @Gosa   2 years ago
  ጎሳ ሰው ነው።
 • loader Loading content ...
 • @Tola (ቶላ)   2 years ago
  ከተኛ አንበሳ ዞር ዞር ያለ ቀበሮ ይሻላል!
  ታዋቂው የውጫሌ ውል በሚያዚያ ፳፭ ቀን በ፲፰፻፹፩ ዓ.ም. በውጫሌ ሰፈር የተፈረመ ሲሆን በዚህ ውል ውስጥ ከተጠቀሱት ዓንቀጾች መካከል አንዱ ለአድዋ ጦርነት መነሻ እንደሆነ ይታወቃል። ይህንን ውል በጣልያን በኩል የተዋዋለው አንቶኔሊ ሲሆን በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ ዓጼ ምኒልክ እራሳቸው እንደሆኑ የታሪክ መዝገቦች ያመለክታሉ።


                 ንጉሰ ነገስት ዓጼ ምኒልክ


                 የውጫሌውን ውል ከኢጣሊኛ ወደ አማርኛ የተረጎሙት ግራዝማች ዮሴፍ ንጉሴ።

  መግቢያ
  የኢጣሊያ ንጉሥ ኡምቤርቶ በስም መጀመርያ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ ምኒልክ ዘኢትዮጵያ መንግስት ለኢጣሊያ መንግስት የሚጠቅም ለልጅ ልጅ የሚኖር ሰላምና እርቅ ለማድግረግ የፍቅርና የንግድ ውል ተዋዋሉ።

  የኢጣሊያ ንጉሥ ኮንት አንቶኔሊን በኢጣልያ መንግስት ዘውድ ኒሻን ኮማንዳቶሬ ተብሎ የተሾመ፤ ተመርጦ እንደራሴ ሆኖ ወደ ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ሙሉ ሥልጣን ተቀብሎ የተላከ፤ የተቀበለውንም ሙሉ ሥልጣን በንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ፊት በርግጥ የተቀበለ ስለሆነ ንጉሰ ነገስት ምኒልክ የኢትዮጵያን አልጋ የወረሱ እርስዎ ስለሆኑ ይህን ከዚህ ቀጥሎ የተፃፈውን ውል ከኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ምኒልክ ጋራ ትውውልን።


                 የኢጣሊያ ንጉስ ኡምቤርቶ ቀዳማዊ።


                 በኢጣሊያ በኩል የውጫሌውን ውል የተዋዋለው ፒዮትሮ አንቶኔሊ።

  መጀምርያ ክፍል
  በኢጣሊያ ንጉስና በኢትዮጵያ ንግሰ ነገስት መካከል በወራሾቻቸውና በህዝቦቻቸውም፤ እነዚህንም በተጠጉ ህዝብ መካከል ሰላምና ፍቅር ሳይጎድል ለዘወትር ለልጅ ልጅ ይኖራል።

  ፪ኛ ክፍል
  እነዚህ ሁለቱ አሁን የተዋዋሉት በየሃገራቸው በየምስለኔዎቻቸው ይነጋገራሉ። አንዱ ካንዱ አገር ቆንሲልም የቆንሲል ወኪልም መሾም ይቻላቸዋል። እነዚህም ሹሞች እንደ አውሮፓ ነገስታት ሥርኣት መታፈርና መከበር አይጎድልባቸውም።

  ፫ኛ ክፍል
  በነዚህ በሁለት ነገስታት ወሰን ጠብና ክርክር እንዳይነሳ በዕውቅ የተመረጡ ከሁለቱ ወገኖች ሁለት ሽማግሌዎች ልከው በማይጠፋ ምልክት የግዛቱን ድንበር ይወስናሉ። ከድምበሩ ወዲህ የሚጨመሩት አገሮች እነዚህ ናቸው። የደጋው አፋፍ ከኢትዮጵያና ከኢጣልያ መሃል ወሰን ይሆናል። ከራፋሊ ጀምሮ ሃላይና፤ ሰገነይቲ አስመራ ሶስቱ የኢጣልያ መንግስት መንደር ይሆናሉ። ዳግመኛ በቦገስ በኩል አዲ ነፋስና ዓዲ ዋንስ በኢጣልያ ድንበር ውስጥ ይሆናሉ። ከአዲ ዋንስ መንደር ጀምሮ ከምስራቅ ወደ ምዕራብ ባቀና ይከፋፈላል።

  ፬ኛ ክፍል
  የደብረ ቢዘን ገዳም ከነጉልቱ ከነርስቱ የኢትዮጵያ መንግስት እንደሆነ ይቀራል። የጦር አምባ መሆን ግን አይቻለውም።

  ፭ኛ ክፍል
  ከምጥዋ የሚወጣ የንግድ እቃ የሚገባም የንግድ እቃ ከመቶ ፲ በገቢ እቃ እየተገመገመ በገቢ አንድ ጊዜ ይከፈላል።

  ፮ኛ ክፍል
  የጦር መሳርያ ንግድ በምጥዋና በኢትዮጵያ መካከል የሚመላለሰው ለንጉሰ ነገስት ብቻ ይፈቀድልዎታል። ሲያሥመጡም ባለ ማህተም ደብዳቤዎን ለኢጣልያ ሹማምንት እየላኩ ያስመጣሉ። ለፍጡንም የያዘውን ሰፈር ከምጥዋ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድምበር ድረስ የኢጣልያ መንግስት ወታደሮች ዘበኛ ሁነው ይሸኛሉ።

  ፯ኛ ክፍል
  የነዚህ የሁለቱ ውል ያደረጉት ነገስታት ዜጎች የንግድ እቃቸውን ይዘው አንዱ ካንዱ አገር መሄድና መምጣጥ ይቻላቸዋል። በየመንስግቱና በየወረዳው ባለው ሹም ጥግነት ደስ ብሏቸው ይመላለሳሉ። ነገር ግን ከሁለቱም ወገኖች የጦር መሣርያ የያዘ ብዙ ሆኖ ከአንዱ ድምበር ወደ አንዱ ድምበር መተላለፍ ተከልክሏል። እንዲህም ማለት አንዱ ያንዱን ከብት እንዳይዘርፍ በሁሉ ነገር እንዳይነካካ ተከልክሏል።

  ፰ኛ ክፍል
  የኢጣልያ ሰዎች በኢትዮጵያ፤ የኢትዮጵያ ሰዎች በኢጣልያ የኢጣልያ መንግስት በሚገዛው አገር ቢሆንም እንዳገሩ ልማድ መግዛት መሸጥ መከራየት ይቻላቸዋል።

  ፱ኛ ክፍል
  የነዚህ የሁለቱ ነገስታት ዜጎች አንዱ ካንዱ አገር ቢሄድ በየሃይማኖታቸው ይኖራሉ።

  ፲ኛ ክፍል
  የኢጣሊያ ሰውና የኢጣሊያ ሰው የተካሰሱ እንደሆነ እነዚያ በመረጡት ዳኛ ለዚያውም ተያይዘው ምጥዋ ወርደው ይዳኛሉ። የኢትዮጵያ እና የኢጣሊያ ሰው የተጣላ እንደሆነ ግን የኢትዮጵያ መንግስት ወኪልና የኢጣሊያ የምጥዋ ሹም አንድነት ሆነው ይዳኛሉ።

  ፲፩ኛ ክፍል
  የኢጣሊያ ሰው በኢትዮጵያ የሞተ እንደሆነ የኢትዮጵያ ሰው በኢጣሊያ አገርና የኢጣሊያንም መንግስት በሚገዛው አገር የሞተ እንደሆነ የሟቹ መንግስት ወገን ገንዘቡን የሚቀበል ሰው እስኪመጣ ድረስ የሁለቱ ነገስታት ሹማምንት ገንዘቡን ጠብቀው ያስቀምጣሉ።

  ፲፪ኛ ክፍል
  በማናቸውም ሃጢያት ተከሶ የተያዘ የኢጣልያ ሰው በኢጣልያ ሹማምንት ይዳኛል። ስለሆነም ግን ታላቅ ሃጢያት ሰርቶ የተገኘውን የኢጣሊያን ሰው ፈጥኖ ይዘው ለምጥዋ ሹማምንት መስጠት ነው። ደግሞ በኢጣልያ መንግስት ግዛት የኢትዮጵያ ሰው ታላቅ ሃጢያት ሰርቶ የተገኘ እንደሆነ በኢትዮጵያ ዳኛ ይዳኛል።

  ፲፫ኛ ክፍል
  የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስትና የኢጣሊያ ንጉስ ብርቱ ሃጢያት የሰራ ሰው ካንዱ ግዛት ወደ አንዱ ግዛት ሸሽቶ የሄደ እንደሆነ ሁለቱም እያሰሩ ይልካሉ።

  ፲፬ኛ ክፍል
  የባሪያ ንግድ በክርስቲያን ሃይማት የተከለከለ ስለሆነ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት በሚቻላቸው ነገር ሁሉ ባገራቸው ባሪያ እንዳይነገድ ይከላከላሉ።

  ፲፭ኛ ክፍል
  ይህ አሁን የተፃፈው ውል ለኢትዮጵያ መንስት ሁሉ ውል ነው።

  ፲፮ኛ ክፍል
  ይህ ውል በተደረገ ከ፭ አመት በሇላ ከሁለቱ መንግስታት አንዳቸው ውል ለመጨመር ወይም ለመለወጥ የፈለጋቸው እንደሆነ ከዐመት በፊት አስቀድሞ መናገር ይገባቸዋል። ነገር ግን የንግድ ውል ብቻ ማረም ማስጠንቀቅ ይቻላቸዋል እንጂ፤ ዛሬ የተለየውን የድንበር ወሰን ማፍረስ አይቻላቸውም።

  ፲፯ኛ ክፍል
  የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ከኣውሮፓ ነገስታት ለሚፈልጉት ጉዳይ ሁሉ በኢጣሊያ መንግስት አጋዥነት መላላክ ይቻላቸዋል።

  ፲፰ኛ ክፍል
  የኢትዮጵያ ነጉሰ ነገስት ከሌላ መንግስት ሰዎች ጋራ የጥበብ የንግድ ነገር ለመዋዋል የፈለጉ እንደሆነ ከሁለቱም ውል አንድ እንደሆነ ለኢጣሊያ ሰው ይሰጡታል።

  ፲፱ኛ ክፍል
  ይህ አሁን የተደረገው ውል በአማርኛ እና በኢጣልያ ቇንቇ  ትክክል ሆኖ ተገልብጦ ሲያበቃ የታመነ ምስክር ይሆናል።

  ፳ኛ ክፍል
  ይህ አሁን የተፃፈው ውል ለሮማ ከተማ ፈጥኖ ይጠነቀቃል። ነገር ግን ይህን ውል ኮንት ፒየትሮ አንቶሌኒ በኢጣሊያ ንጉስ ስም ነንጉሰ ነገስት ምኒልክ ጋራ ተዋውለው አትመው ጨርሰዋል። በሚያዝያ ፳፭ ቀን ፲፰፻፹፩ ዓ.ም. በውጫሌ ሰፈር ተፃፈ።

  ምንጭ:
  "የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግስተ ሳባ እስከ ታላቁ የአድዋ ድል"
  በብላቴን ጌታ ህሩይ ወልደስላሴ።
 • loader Loading content ...

Load more...