loader
 • በዘመድ ዳኛ የመጨረስ ስምምነት (የ፲፱፻፶፪ ዓ.ም. የፍትሐ ብሔር ሕግ ፥ አንቀጽ ፳ ፥ ምዕራፍ ፪)

  @በህግ አምላክ   3 months ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!
 • loader Loading content ...
 • @በህግ አምላክ   3 months ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!

  የ፲፱፻፶፪ ዓ.ም. የፍትሐ ብሔር ሕግ። አንቀጽ ፳። ስለ ግልግልና ስለ ስምምነት የሚደረግ ውል። ምዕራፍ ፪። በዘመድ ዳኛ የመጨረስ ስምምነት።


  ቁጥር ፫ሺ፫፻፳፭። ትርጓሜ።
  (፩) የግልግል ስምምነት ማለት ተዋዋይ ወገኖች ያንድ ክርክርን ውሳኔ ለአንድ የዘመድ ዳኛ ለሆነው ለአንድ ሦስተኛ ሰው አቅርበው የዘመድ ዳኛው ውል በሕግ አግባብ መሠረት ይኸንኑ ክርክር ለመቁረጥ የሚያደርገው ውል ነው።
  (፪) የዘመድ ደኛው በሕግ በኩል ነገሩ የሚያስከትለውን ውጤት ሳይወስን አንድ የተለይ ጕዳይ ብቻ እንዲያረጋግጥ ሊመረጥ ይችላል።

  ቁጥር ፫ሺ፫፻፳፮። ችሎታና ፎርም (፩) መሠረቱ።
  (፩) መብትን ያለ ዋጋ ለመስጠት ስለ መቻል የሚያስፈልገው ችሎታ በዚሁ መብት የተነሣውን ክርክር በዘመድ ዳኛ ለመጨረስ ለሚደረገውም ውል አስፈላጊ ነው።
  (፪) በዘመድ ዳኛ ለመጨረስ የሚደረገው ስምምነት በሕግ ይህንኑ መብት ያለ ዋጋ ለመስጠት አስፈላጊ በሆነው ፎርም ዐይነት መፈጸም አለበት።

  ቁጥር ፫ሺ፫፻፳፯። (፪) የተጠበቀ ሁኔታ።
  (፩) ከዚህ በላይ ያለው ቁጥር ድንጋጌዎች ይህ ሕግ ወደ ሽምግልና ዳኝነት እንዲቀርብ በግልጽ ባዘዘው ጕዳይ ተፈጻሚ አይሆኑም።
  (፪) ለእንደዚህ ያለው ጕዳይ በሽምግልና ዳኝነት የመጨረሱን ስምምነት አካለ መጠን ባላደረሰው ወይም በተከለከለው ሰው ስም ሞግዚቱ ሊፈጽም ይችላል።
  (፫) በሽምግልና ዳኝነት ለመጨረስ የሚደረገው ስምምነት ማናቸውንም ፎርም መከተል የለበትም።

  ቁጥር ፫ሺ፫፻፳፰። የደረሰና ያልደረሰ ክርክር በዘመድ ዳኛ ለመጨረስ ስለሚደረግ ስምምነት።
  (፩) ለዘመድ ዳኛ የቀረበው ክርክር ቀድሞውኑ የነበረ ክርክር መሆን ይችላል።
  (፪) እንዲሁም አንድ ውል በሚደረግበት ጊዜ ተዋዋይ ወገኖች በአጋጣሚ በዚህ ውል ለመነሣት የሚችለውን ክርክር ለዘመድ ዳኛ ለማቅረብ ይችላሉ።
  (፫) ወደፊት የሚነሡትን ክርክሮች ለዘመድ ዳኛ ለማቅረብ ሲባል የሚደረገው ስምምነት ዋጋ ያለው የሚሆነው ስምምነቱ በአንድ ውል ወይም በተለየ በመብት ገዥነት ላይ የሆነ እንደሆነ ነው።

  ቁጥር ፫ሺ፫፻፳፱። አተረጓጐም።
  የዘመድ ዳኛ ሥልጣንን የሚመለከቱ የዘመድ ዳኛ ስምምነት ቃሎች በጠባቡ መተርጐም አለባቸው።

  ቁጥር ፫ሺ፫፻፴። የተሰጠው ሥልጣን ስላለው ሥልጣን።
  (፩) የዘመድ ዳኛው ስምምነት፤ የዚሁ ስምምነት አተረጓጐም ያነሣሣውን ችግር በሥልጣኑ እንዲወሰን ለዘመድ ዳኛው ሊፈቅድለት ይችላል።
  (፪) በተለይም የራሱን ሥልጣን የሚመለከቱትን ክርክሮች በሥልጣኑ እንዲወሰን ለዘመድ ዳኛው ሊፈቅድለት ይችላል።
  (፫) የዘመድ ዳኛው በማናቸውም ሁኔታ የዘመድ ዳኛ ስምመነት ዋጋ ያለው ወይም የሌለው ነው ብሎ በሥልጣኑ ሊወስን አይችልም።

  ቁጥር ፫ሺ፫፻፴፩። የዘመድ ዳኛ ስለ መምረጥ። (፩) በተዋዋይ ወገኖች ስለ መመረጥ።
  (፩) የዘመድ ዳኛው በዘመድ ዳኛው ስምምነት ውስጥ ሆኖ ወይም ከዚሁ ስምምነት በኋላ መመረጥ ይችላል።
  (፪) ስምምነቱም አንድ ወይም ብዙ የዘመድ ዳኞችን የሚኖሩ መሆናቸውን አስቀድሞ ለመወሰን ይችላል።
  (፫) የዘመድ ዳኞች ስንት እንደሚሆኑ ወይም እንዴት እንደሚመረጡ ስምምነቱ ያላመለከተ እንደሆነ እያንዳንዱ ወገን አንድ የዘመድ ዳኛ ይመርጣል።

  ቁጥር ፫ሺ፫፻፴፪። (፪) በዘመድ ዳኞች ወይም በዳኞች ስለ መመረጥ።
  (፩) ተቃራኒ የውል ቃል ከሌለ በቀር የዘመድ ዳኞች ብዛት በጥንድ የሚቆጠሩ እንደሆነ በሥራው ከመግባት በፊት አንድ ሌላ የዘመድ ዳኛ ይመርጣሉ። ይኸውም የተመረጠው የዘመድ ዳኛ ለዘመድ ዳኝነቱ ሰብሳቢ ይሆናል።
  (፪) ብዛታቸው በጥንድ የማይቆጠሩ የሆኑ እንደሆነ የዘመድ ዳኞቹ ከመካከላቸው ለዘመድ ዳኝነቱ ሰብሳቢ የሚሆነውን ይመርጣሉ።
  (፫) በዘመድ ዳኞቹ መካከል ስምምነት የሌለ እንደሆነ ከተዋዋይ ወገኖች አንዱ በሚያቀርበው ጥያቄ እነዚህ ምርጫዎች በዳኞች የሚደረጉ ይሆናሉ።

  ቁጥር ፫ሺ፫፻፴፫። (፫) የምርጫው ሥነ ሥርዐት።
  (፩) አስፈላጊ ሲሆን የዘመድ ዳኛውን ስምምነት የሚጠይቀው ወገን የሚያነሣውን ክርክር ገልጦ አንድ የዘመድ ዳኛ ይመርጣል።
  (፪) እንዲህም በሆነ ጊዜ ላንደኛው ወገን ወይም በዘመድ ዳኝነት ስምምነት መሠረት የዘመድ ዳኛውን እንዲመርጥ ለተደረገው ሰው ማስታወቂያ ይሰጣል።

  ቁጥር ፫ሺ፫፻፴፬። (፬) የተወሰነ ጊዜ።
  (፩) አንደኛው ወገን ወይም አንድ የዘመድ ዳኛ እንዲመርጥ የተጠየቀው ሰው በሙሉ በሠላሳ ቀን ጊዜ ውስጥ ያልመረጠ እንደሆነ ዳኞች ይህን የዘመድ ዳኛውን ይመርጣሉ።
  (፪) ጊዜው መቆጠር የሚጀምረው ከዚህ በላይ ባለው ቁጥር የተመለከተው ማስታወቂያ ከደረሰበት አንሥቶ ነው።
  (፫) የዘመድ ዳኛ ስምምነት እነዚህን ደንቦች ለመለዋወጥ ይችላል።

  ቁጥር ፫ሺ፫፻፴፭። (፭) የተዋዋይ ወገኖች ትክክለኛነት።
  የዘመድ ዳኛው ስምምነት የዘመድ ዳኞች ስለ መምረጥ በሚመለከተው ጕዳይ ከተዋዋይ ወገኖች ላንዱ ልዩ የሆነ አንድ የበለጠ የመብት ሁኔታ የፈቀደለት እንደሆነ ዋጋ ያለው አይሆንም።

  ቁጥር ፫ሺ፫፻፴፮። ስለ አንድ የዘመድ ዳኛ መቅረት (፩) መተካት።
  (፩) አንድ የዘመድ ዳኛ የዘመድ ዳኛ ሆኖ መመረጡን አልፈልግም ያለ እንደሆነ ወይም የሞተ ወይም ችሎታ ያጣ ወይም ስንብት የጠየቀ እንደሆነ፤ ከዚህ በፊት ባሉት ቁጥሮች መሠረት እርሱ እንደተመረጠው ዐይነት በርሱ ምትክ ሌላ ይመረጣል።
  (፪) የዘመድ ዳኛው የተሻረ እንደሆነ አዲሱን የዘመድ ዳኛ ዳኞች ይመርጣሉ።
  (፫) የዚህ ቁጥር ውሳኔዎች በተዋዋይ ወገኖች ስምምነት ሊለዋወጡ ይችላል።

  ቁጥር ፫ሺ፫፻፴፯። (፪) የስምምነቱ ቀሪነት።
  (፩) የሆነ ሆኖ ዘመድ ዳኛው ስሙ ተጠርቶ በዘመድ ዳኛ ስምምነት ውስጥ የተመረጠ ሆኖና ተዋዋይ ወገኖች በርሱ ምትክ ለማድረግ ያልተስማሙ እንደሆነ የዘመድ ዳኛ ስምምነት ቀሪ ይሆናል።
  (፪) ቢሆንም ወደፊት ለሚደርስ ክርክር ይኸውም ክርክር በደረሰ ጊዜ የዘመድ ዳኛውን መሰናክል የሆነው ነገር ቀርቶ እንደሆነ የዘመድ ዳኛው ስምምነት የሚረጋ ይሆናል።
  (፫) የዚህ ቁጥር ውሳኔዎች በሁለቱ ወገኖች ስምምነት ለመለዋወጥ ይችላሉ።

  ቁጥር ፫ሺ፫፻፴፰። ከተዋዋይ ወገኖች ያንዱ መሞት።
  ተዋዋይ ወገኖች በሌላ ሁኔታ የውል ቃል ካላገቡ በቀር ያንደኛው ወገን መሞት የመረጡትን የዘመድ ዳኛ ተግባር አያስቀረውም።

  ቁጥር ፫ሺ፫፻፴፱። የተገላጋዩ ተግባር።
  (፩) ማንኛውም ሰው ሁሉ የዘመድ ዳኛ ሆኖ ለመመረጥ ይችላል።
  (፪) የዘመድ ዳኛው ዜግነት ለመመረጥ ከግምት አይገባም።
  (፫) ለዘመድ ዳኝነት የተመረጠው ሰው ይህን ሥራ ለመቀበል ወይም ላለመቀበል ነጻ ነው።

  ቁጥር ፫ሺ፫፻፵። የዘመድ ዳኛውን ስለ ማስወገድ (፩) ምክንያቶች።
  (፩) አንድ የዘመድ ዳኛ አካለ መጠን ያልደረሰ እንደሆነ ወይም በርሱ ላይ በደረሰበት በአንድ ቅጣት ምክንያትም ቢሆን፤ ወይም ክፉና ደጉን መለየት ባለመቻሉ በበሽታ፤ በመጥፋት፤ ወይም በማናቸውም ሌላ ምክንያት ተገቢ በሆነ የተወሰነ ቀን ውስጥም ቢሆን ለማስወገድ ይቻላል።
  (፪) በተዋዋይ ወገኖች ስምምነት ወይም ባንድ ሦስተኛ ወገን የተመረጠው የዘመድ ዳኛ ባለማዳላቱ ወይም በነጻነቱ ላይ ጥርጣሬን ለማስገባት የሚችል አንዳንድ አካባቢ ምክንያት ካለ ሊወገድ ይችላል።
  (፫) በዘመድ ዳኝነት ሰብሳቢ የሆነውም ሰው ይኸንኑ በመሰለ ምክንያት ሊወገድ ይቻላል።

  ቁጥር ፫ሺ፫፻፵፩። (፪) ጥያቄን ስላለመቀበል።
  ተቃራኒ የውል ቃል ከሌለ በቀር አንዱ ወገን ራሱ የመረጠውን የዘመድ ዳኛ ከዚህ ምርጫ በኋላ ለደረሰው ምክንያት ወይም ይህ ምርጫ ከሆነ በኋላ ምክንያቱን ማወቁን ካላረጋገጠ ሊያስገድደው አይችልም።

  ቁጥር ፫ሺ፫፻፵፪። (፫) ሥነ ሥርዐት።
  (፩) የማስወገዱ ጥያቄ መቅረብ፤ ለዘመድ ዳኝነት ባለሥልጣኖች ለሆኑት ውሳኔያቸውን ከመስጠታቸው በፊትና ጥያቄውንም የሚያቀርበው ወገን ምክንያቱን እንዳወቀው ወዲያውኑ መሆን አለበት።
  (፪) ተዋዋይ ወገኖች የመወገዱ ጥያቄ ለሌላ ባለሥልጣን ይቀርባል ብለው መስማማት ይችላሉ።
  (፫) የቀረበውን የመወገድ ጥያቄ አንቀበልም ተብሎ የተወሰነ እንደሆነ ይህኑ ውሳኔ እስከ ዐሥር ቀን በዳኞች ላይ ለመቃወም ይቻላል።

  ቁጥር ፫ሺ፫፻፵፫። የዘመድ ዳኛውን ስለ መሻር።
  አንድ የዘመድ ዳኛ ሥራውን ተቀብሎ ከመፈጸም በማይገባ የዘገየ እንደሆነ በተዋዋዮቹ ስምምነት የተመረጠው ባለሥልጣን ወይም በዚሁ ስምምነት አላደረጉ እንደሆነ ከተዋዋዮቹ አንዱ ወገን ባቀረበው ጥያቄ ዳኞች የዘመድ ዳኛውን ለመሻር ይችላሉ።

  ቁጥር ፫ሺ፫፻፵፬። ባለመፈጸም ስለሚደረግ ቅጣት።
  (፩) ለዘመድ ዳኝነት ስምምነት ካደረጉት አንዱ ወገን በዚሁ ስምምነት ውስጥ ለተመለከተ ክርክር ወደ ዳኞች የሄደ፤ ወይም የዘመድ ዳኝነት ለማደራጀት አስፈላጊ የሆኑትን ተግባሮች ለመፈጸም እንቢ ያለ፤ ወይም በዘመድ ዳኛ ስምምነት የተያዝኩ አይደለሁም ባይ የሆነ እንደሆነ ሌላው ወገን እንደመረጠው በዘመድ ዳኝነት የተደረገውን ስምምነት እንዲፈጸም ለማስገደድ ወይም በተለይ ለተነሣው ክርክር ስምምነተ ቀሪ እንደሆነ ለመቁጠር ይችላል።
  (፪) አንዱ ወገን ስለ አንድ የዘመድ ዳኛ ስምምነት አንድ የአጠባበቅ ጥንቃቄ ዳኞችን ለመጠየቅ ያደረገው ተግባር የዚህን ስምምነት ቀሪነት አያስከትልም።

  ቁጥር ፫ሺ፫፻፵፭። ወደ ሥነ ሥርዐቱ ሕግ ስለ መምራት።
  (፩) የዘመድ ዳኝነት የሚከተለው ሥነ ሥርዐት በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዐት ሕግ ተደንግጓል።
  (፪) እንዲሁም የዘመድ ዳኛ ውሳኔ አፈጻጸምን ወይም ለዚሁ ውሳኔ ተቃራኒ የሆኑ አቤቱታዎችን ለሚመለከቱ ነገሮችም ይኸው ሕግ ተፈጻሚ ይሆናል።

  ቁጥር ፫ሺ፫፻፵፮። የዘመድ ዳኝነት አሠራር።
  በዚህ ምዕራፍ ‹‹የዘመድ ዳኛ ስምምነት›› ‹‹ወይም›› የተዋዋዮቹ ስምምነት የተባሉት ቃሎች ተዋዋዮቹ ለመጥቀስ የፈለጉትን የዘመድ ደኛ አሠራር ድንጋጌዎችን ይጠቀልላሉ።

  ምንጭ:
  የኢትዮጵያ የ፲፱፻፶፪ ዓ.ም. የፍትሐ ብሔር ሕግ (፲፱፻፶፪)
 • loader Loading content ...

Load more...