loader
 • በ፲፱፻፳፰ (1928) ዓ.ም. በኢትዮጵያ እና በኢጣልያን መካከል የተካሄደው ጦርነት መነሻ ምንድነው?

  @መርሻ   2 years ago
  Interested in just about everything!
 • loader Loading content ...
 • @መርሻ   2 years ago
  Interested in just about everything!
  አፄ ምኒልክ ሲሞቱ የልጅ ልጃቸው እያሱ መንግስቱን እንዲመሩ ተናዘዙ። ልጅ እያሱ መንግስቱን በሞግዚትነት ይዘው ማስተዳደር ጀመሩ። ልጅ እያሱ መንግስቱን በያዙበት ጊዜ አንደኛው የዓለም ጦርነት በመቀስቀስ ላይ ስለነበር ልጅ እያሱ ከሰላሙ በጥባጮች ከጀርመን አና ከቱርክ ጋር ተዋዋሉ። የነዚህ የጦር ጏዶች ተቃራኒ የሆኑት ፈረንሳይ, እንግሊዝና ኢጣልያ እያሱን ለመጣል ሲሉ ተፈሪን አቀፉ። በገንዘብም ሆነ በስብከት የኤሮፓ ሃያላን እያሱን አስጥለው ዘውዲቱን ንግስት፤ ተፈሪን አልጋ ወራሽ አስደረጉ።

  ይህ ከመሆኑም በፊት እንግሊዝና ኢጣልያ "በኢትዮጵያ ውስጥ ያለንን ጥቅም ለማስከበር" በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ በ1891 ዓ.ም. በመጋቢት አና በሚያዚያ ወር ውል ተፈራርመዋል። እንደገናም ከሶስት ዓመት በሁላ እ.ኤ.አ. በግንቦት ወር በ1894 ዓ.ም. "አንግሎ ኢጣልያ አግሪመንት" በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ ውስጥ ያላቸውን ያንዱን ጥቅም አንዱ ላይነካ የወዳጅነት ውል ተፈራረሙ።

  የእነኚህ የሁለቱ ሃያላን የጥቅም ማስከበር አንደኛዋን ባለጥቅምና ሃያል የሆነችውን ፈረንሳይን ስለተዋት እንደገና እ.ኤ.አ. በ1904 ዓ.ም. ፈረንሳይን ጨምረው ሶስቱ ሃያላን የኤሮፓ መንግሥታት ትሪፓርቲት (Tripartite) አግሪመንት የሚባለውን ውል ተፈራረሙ። እንግሊዝ የዚያን ጊዜ እንግሊዝ ሶማሊላንድ ይባል የነበረውን፣ ኬንያን እና ሱዳንን፤ ፈረንሳይ ጅቡቲን፤ ኢጣልያ ያዛን ጊዜ ኢጣልያ ሶማሊላንድ ይባል የነበረውንና ኤርትራን በቅኝ ገዢነት ይዘው ኢትዮጵያን ዙሪያዋን ከበዋት ነበር። ስለዚህ ሶስቱም ከኢትዮጵያ ጋር የቅኝ ግዛት ወሰንተኞች ሲሆኑ ሁሉም ከኢትዮጵያ ጥቅም ስለነበራቸው በጥቅማቸው ምክንያት እርስ በራሳቸው እንዳይጣሉ የሚያደርጉት ውል ነው። በውሉ ውስጥ ኢትዮጵያ እንድትገባ መጥራት ቀርቶ እንድታውቀው እንኩአን አልተደረገም። የውሉ ጉዳይ ግን የሚመለከተው በቀጥታ ኢትዮጵያን ነበር። የጥቅም ማስከበሩ ሁኔታ በየቅኝ ግዛቶቻቸው ውስጥ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው ስለሚኖራቸው ጥቅም ጭምር ነበር።

  የሶስቱን መንግሥታት ውል ባጭሩ ብንመለከትው እንግሊዝ ከጥቁር አባይ መመንጫ ጀምሮ እስከ መውጫው ኢትዮጵያና ሱዳን ወሰን ድረስ ያለውን አካባቢ ሲነካ፤ ግብፅና ሱዳን በውሃ እጥረት ጉዳት ስለሚያገኛቸው ጥቅሟ የሚነካ መሆኑን ሁለቱ መንግሥታት ፈረንሳይና ኢጣልያ አውቀው አረጋገጡላት።

  ፈረንሳይ ከጅቡቲ እስከ አዲስ አበባ የተዘረጋው የባቡር ሐዲድ ስራው ቢቁአረጥ ወይም ቢደክም የጅቡቲ መድከም በመሆኑ ከጅቡቲ እስከ አዲስ አበባ የተዘረጋውን የባቡር ሐዲድ መስመር ተከትሎ ያለው ሁሉ ጥቅሟ መሆኑን እንግሊዝና ኢጣልያ አወቁላት።

  ኢጣልያ፤ በማሃል ጅቡቲና እንግሊዝ ሶማሌ ጣልቃ ገብተው ሁለቱን ቅኝ ግዛቶቿን ኤርትራን እና ሞቃዲሾን ስለለዩባት እነኚህን ሁለቱን ቅኝ ግዛቶቿን በማገናኘት በኢትዮጵያ መሃል ለመሃል አቁአርጦ የሚሄድ የባቡር ሐዲድ ለመዘጋት የምትችል መሆኗን ፈረንሳይ እና እንግሊዝ አውቀው ተፈራረሙ። ይህ ሁሉ ሲሆን ኢትዮጵያ የተጠየቀችው ምንም ነገር የለም።

  ይህ የሶስቱ ሃያላን መንግሥታት ውል እ.ኤ.አ. እስከ 1922 ዓ.ም. ድረው በሥራ ላይ ቆይቶ በ1922 ዓ.ም. በውሉ ላይ ተጨማሪ አንቀፅ ገባ። ይህም አንደገና ተስፋፍቶ የታደሰው ውል እንግሊዝ ጣና ሀይቅ አጠገብ ግድብ ለመስራት የምትችል መሆኗን ይፈቅድላታል። ይህንንም ግድብ በምትሰራበት ጊዜ ኢጣልያ እንግሊዝን በዲፕሎማቲክ መንገድ እንድትደግፋት ይወስናል።

  የኢጣልያ መንግስትም የተለያዩ ሁለቱን ቅኝ ግዛቶቿን ለማገናኘት የምትሰራው የባቡር ሐዲድ ከአዲስ አበባ ከተማ ምአራብ በኩል አልፎ እንዲሄድ ይወስንና ይህ ሐዲድ በሚዘረጋበት ጊዜ የእንግሊዝ መንግስት ሙሉ የዲፕሎማቲክ ድጋፉን ይሰጣል ይላል።

  ይህም ውል ለሶስት አመታት ያህል በተግባር ሳይውል ቆይቶ እ.ኤ.አ. በ1925 ዓ.ም. ውሉ ዝርዝር ጉዳዮችን ጨመረ. ባንድ የሃዲድ ጥቅም የታሰረችው ፈረንሳይ ከውጭ ቀርታ እንግሊዝ እና ኢጣልያ ውላቸውን አሻሽለው አደሱት። የእንግሊዝ መንግስት ጣና ሀይቅ አጠገብ ግድብ ሰርቶ ሃይቁን በሚያስፋፋበት ጊዜ ከሱዳን ወሰን አንስቶ ጣና ሀይቅ ድረስ የመኪና መንገድ ለመስራት ሙሉ መብት ሲሰጠው; ኢጣልያ ደግሞ ሁለቱን ቅኝ ግዛቶቿን ለማገናኘት የምትዘረጋው የባቡር መስመር በትግራይ እና በጎንደር አልፎ አዲስ አበባን ወደ ምስራቅ እየተወ ደጋ ደጋውን ይዞ ሞቃዲሾ ይገባል ይላል። የዚህም የባቡር ሐዲድ ርዝመት 780 ማይልስ ወይም 1248 ኪ.ሜ. እንደሚሆን ይደነግጋል።

  እጅግ በጣም የሚገርመው ነገር ኢትዮጵያ ነፃ መንግስትና ወሰኗን አስከብራ የምትኖር አገር ሆና ሳለች የንቀታቸው ንቀት እንግሊዝ ጣና ላይ ግድብና ከግድቡ የሚያደርስ የመኪና መንገድ ለመስራት በሰው አገር ገብተው ባለሙሉ ስልጣን ሆነው እንግሊዝ የተዋዋለው ከጣና ጌታ ከኢትዮጵያ ጋር ሳይሆን ከኢጣልያ ጋር ነበር።

  ኢጣልያም የባቡር ሃዲዱን በደንከል ምድር አድርጎ ጥግ ጥጉን በበረሃው ለመዘርጋት እንኩአን ቢሆን ፍቃድ መጠየቅ እና መዋዋል ያለበት ከባለ መሬቱ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር መሆን ሲገባው፣ እንደማይሆን ሆኖ ከአስመራ መቃዲሾ ለመሄድ በመቀሌ፤ በጎንደር፤ ከአዲስ አበባ ጉአሮ ዞሮ ይጉአዛል የሚለውን ውል ከኢትዮጵያ ጋር ሳይሆን ከእንግሊዝ ጋር ተዋዋለ። የሁለቱም መንግሥታት ሃሳብ የሁለቱን መጋጨት ብቻ የሚመለከትና ሁሉም በየሆዱ ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ይዞ ካላቸው የቅኝ ግዛት ጋር ለመደባለቅ ነበር።

  በዚህ ውል የተናደደ አንድ ኢትዮጵያዊ መጋቢት 8 ቀን 1919 ዓ.ም. በወጣው ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ ላይ ፋሺስትና ኢትዮጵያ በሚል ርዕስ "... ሙሶሎኒ አይኑን ከጣለባቸው አገሮች አንዱ ኢትዮጵያ ነው. እንግሊዞች ከሙሶሎን ጋር ሲዋዋሉ እነሱ በጣና ባህር ሊያዙበት፤ ሙሶሎኒ ምጥዋ አንስቶ ትግሬን፤ ጎንደርን አድርጎ አዲስ አበባን ወደ ምስራቅ እየተወ እስከ ህንድ ውቅያኖስ የምድር ባቡር ሊሰራ፤ ለዚህም ስራቸው ሁለቱም ሁሉ የኢትዮጵያን መንግስት ፍቃድ ሊለምኑ በዚህ እርዳኝ እረዳሃለሁ ተባብለዋል ..." በማት ሰፊ ሐተታ ፃፈ። ይህ ሐተታ በተፃፈበት ጊዜ የኢጣልያ መስፍን ወደ አዲስ አበባ የሚመጣበት ጊዜ ተቃርቦ ስለነበረ መጋቢት 15 ቀን 1919 ዓ.ም. የወጣው ያው ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ "ስለዱክ አብሩስ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት" በሚል ርዕስ ተነስቶ የመስፍኑን መምጣት ካተተ በሁአላ "... ይህም አደራረግ የሁለቱን መንግሥታት ወዳጅነት የምያሰፋና የሚያፀና መሆኑን ያስረዳል። በዚህም መካከል አንድ ሰው መጋቢት 8 ቀን በብርሃንና ሰላም አንድ የጋዜጣ ቃል አሳትሞ ስላወጣ የወጣውን ጋዜጣ የሚያነቡ አንዳንድ ሰዎች ይህ ጋዜጣ የተፃፈበት ምክንያት ሳይገባቸው ቀርቶ ተቸግረው ነበር። ነገር ግን ይህን ጋዜጣ ያሳተመው ሰው ለሀገሩ እንግዳ መሆኑንና የመንግስት ሰራተኛ አለመሆኑን ... የራሱን ሃሳብ ፅፎ ስላሳተመ ነው እንጂ የሚበልጠው ቃል ከውጭ አገር ጋዜጣ የተገለበጠ ነው. ... አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ለጊዜው የማያስፈልግ መስሎ ስለታያቸው፣ የፃፈው ሰውና ያሳተመው የብርሃንና ሰላም ዲሬክተር መቀጫ እንዲከፍሉ አዘዋል ሲሉ ሰምተናል። ስለዚህ መጋቢት 8 የወጣው ጋዜጣ እንደቁምነገር አለመቆጠሩን የብርሃንና ሰላም አንባቢዎች ሁሉ ሳያውቁት አይቀሩም" በማለት ማስተባበያ አወጣ። በሱማሌ የጥጥ እርሻ ያላቸው የኢጣልያኑን ልዑል ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ምክንያት ሆኖ የወጣ መግለጫ እንጂ ነገሩ ትክክለኛ ነው. አልጋ ወራሹ ቀጡ የሚለውም ለይስሙላ ነበር።

  ሙሶሎኒ በቅኝ ግዛቱ በሊብያ ውስጥ ያጋጠመው ችግር አላራምድ አለው። እንግሊዝም ብትሆን በቱርክ እና በኢራቅ መሃል የተነሳው የወሰን ጭቅጭቅ ቢኖርባትም በንግድ ምክር ቤቷ እና ኢምፓየር ኮተን ግሮውንግ ኮርፖሬሽን ዲሬክተር የሆኑት ሰር ጀምስ ኩሪ "... የጣና ግድብ መሰራት በሱዳንና በግብፅ ውስጥ በብዛት ጥጥ ማምረት ያስችለናል።" የሚል መግለጫ ሰጡ።

  በማሃሉም እንግሊዝኛ ኢጣልያ በየስምምነታቸው አለመግባባት ስለመጣ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እንግሊዝን ለማጥቃት ከጣልያን ጋር ተወዳጁ። በአልጋ ወራሽነታቸው ዘመን በ1916 ዓ.ም. የኢጣልያን አገር ጎብኝተው ከተመለሱ በሇላም ለጉብኝት መልስ የእጣልያኑ ንጉስ አጎት የሆኑት የአብሩዚ መስፍን ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ተደረገ።

  ፍራንክ ሐርዲ "... ምንሊክ ቢሆን እንዲህ አይነቱን ችግር ይፈታው ነበር። ተፈሪ ግን አልፈታውም። አይፈታውምም። በ1926 ዓ.ም. በሰኔ ወር ተፈሪ አዲስ አበባ ላለው ለብሪትሽ ሚኒስቴር 'በአገሬ ጉዳይ ኢጣልያ ጣልቃ እየገባ የሚያስቸግረኝን ያህል እንግሊዞች አያስቸግሩም' ብለው ከነገሩት በሁላ ለኢጣልያው ሚኒስትር ደግሞ 'ሙሶሎኒ የተከበሩ ሰው ናቸው። በአመራራቸውም እንተማመናለን።' ብለው ነገሩት። በዚያው እለት ደግሞ 'እንግሊዝ እና ኢጣልያ በ1925 ዓ.ም. ያደረጉትን የህብረት ስምምነት እንቃወማለን' በማለት ለሊግ ኦፍ ኔሽን ዋና ፀሀፊ ደብዳቤ ላኩ። ... ሙሶሎኒም ተፈሪ ምን ያክል ታማኝ ነው? እያለ ይጠይቅ ጀመር ..." በማለት አትቷል።

  ኢትዮጵያ ከኢጣልያ ጋር ወዳጅነት እንደጀመረች በ1927 ዓ.ም. እ.ኤ.ዓ. ሙሶሎኒ አዲስ አበባ ላለው ሚኒስትሩ "የእንግሊዞችን ድጋፍ በመጠኑ አድርገህ; ስለኢትዮጵያ ጥቅም ተከራከር" አለው። በዚህ ጊዜ እንግሊዞች የጣናን ግድብ እንስራ ብለው የኢትዮጵያን መንግስት ጠየቁ።

  የኢትዮጵያ መንግስትም "ግድቡን የኢትዮጵያ መንግስት ይሰራዋል። መንግስት የማይችለው ቢሆን ደግሞ ኩባንያ ያቇቁማል። የዚያን ጊዜ እንግሊዞች ሼር ሊገዙ ይችላሉ።" ብሎ በመስከረም ወር መልስ ሰጠ።

  በ1919 ዓ.ም. በግንቦት ወር የአብሩዚ መስፍን ለጉብኝት አዲስ አበባ በመጡ ጊዜም ከአሰብ እስከ ደሴ ኢጣልያ መንገድ ሊሰራ ንግግር ተደረገ። ከሁለት ዓመት በሁላ በ1921 ዓ.ም. አልጋ ወራሽ ተፈሪ ከአሰብ እስከ ደሴ ያለው የመንገድ ሥራ ለደች ተቁአራጭ መሰጠቱን አሳወቁ። ይህን ስያሳውቁም "... በወሰን መሃል ሆነው የሚያስቸግሩትን ሽፍቶች ለማጥፋት ግን የኢትዮጵያ መንግስት ከኢጣልያ መንግስት ጋር የሰላም ወዳጅነት ውል ለመፈራረም ፈቃደኛ ነው..." በማለት ገለጡ። ሙሶሎኒም ስለመገዱ ሥራ የነበረው ንግግር መፍረስ ቢያስቀይመውም ጊዜው እስኪሞላለት ድረስ ያን ትቶ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ሐምሌ 26 ቀን 1921 ዓ.ም. "... ወደፊት የሚሰሩ መንገዶች ለኢጣልያ ይሰጣሉ..." የሚል የወዳጅነትና የሰላም ውል ተዋዋሉ።

  ኢጣልያ እና ኢትዮጵያ በዚህ የወረቀት ወዳጅነት ላይ እንዳሉ ሶስቱ ሃያላን መንግሥታት ማለትም ፈረንሳይ፣ ኢጣልያ እና እንግሊዝ ወደ ኢትዮጵያ የጦር መሳርያ እንዳይገባ የሚወስን እ.ኤ.ዓ. በ1930 ዓ.ም. ተዋዋሉ። በኤርትራ፣ በጅቡቲ፣ በእንግሊዝ ሶማሌ፣ በኢጣልያ ሶማሌ፣ በኬንያ እና በሱዳን በኩል ወደ ኢትዮጵያ የጦር መሳርያ እንዳይገባ ወስነው ሲዋዋሉ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ የተወሰነ ጥይትና ጠመንጃ ብቻ ለመግባት እንዲፈቀድ ተዋዋሉ።

  ከዚህ ውል ቀደም ብሎ በ1920 ዓ.ም. ኢጣልያ በኦጋዴን ውስጥ በግጦሽ ሳርና በውሃ ምክንያት ወሰኗን በወታደር አጥራ ነበር። በተለይ የኢትዮጵያ ግዛት ከሆነው ወልወል ላይ ብዙ የውሃ ጉድጉአዶች ስለነበሩ ኢጣልያ ወሰን አልፋ ወልወልን ያዘች። ወዲያውኑም ሙሶሎኒ የኢጣልያን ሕዝብ ሰብስቦ "... ኢጣልያ በምስራቅ አፍሪካ ያላትን ቅኝ ግዛቶች ኤርትራን እና ሱማሊያን በጦር ኃይል ለመውሰድ ኢትዮጵያ ጦሯን አደራጅታለች። እኛም ብንሆን በጦርነት ሳንጋጠም ቅኝ ግዛቶቻችንን እጃችንን አጣምረን እያየን የምንለቅ አይደለንም። ስለዚህ አገርህን የምትወድ ኢጣልያዊ ሁሉ ተነስ..." አለ። የ1928ቱ በኢትዮጵያ እና በኢጣልያ መካከል የተደረገው ጦርነት መነሻ ሰበብም ወልወል አካባቢ የተፈጠሩ ግጭቶች ናቸው።

  ምንጭ:
  የኢትዮጵያ እና የኢጣሊያ ጦርነት
  በጳውሎስ ኞኞ 
 • loader Loading content ...

Load more...