loader
 • በ፲፱፻፳፰ (1928) ዓ.ም. የኢትዮጵያ እና ኢጣልያን ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያ ሰራዊት ዝግጅት ምን ይመስል ነበር?

  @መርሻ   2 years ago
  Interested in just about everything!
 • loader Loading content ...
 • @መርሻ   2 years ago
  Interested in just about everything!
  ደራሲ እና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ የኢትዮጵያን ጦር ዝግጅት እና አጠቃላይ ሁኔታ እንደሚከተለው ይተርክልናል 

  --------- 

                                የክተት አዋጅ ነጋሪት ሲመታ።

  የኢትዮጵያ ወታደር ብዛት ዊልያም ማኪን ሲገልፅ ከነጀሌው 700,000 ያደርሰውና ".. ካኪ ለብሶ የሚታየው የሰለጠነው ወታደር ግን 25,000 ይሆናል" ይላል። ይህ እንግዲህ በጠቅላላው ኢጣልያንን ሊመክት የተሰለፈው ጦር ነው። 


                         መረብ ላይ የኢጣልያን ዘመናዊ ጦር ለመግጠም የተሰለፈው የኢትዮጵያ ጦር።

  ኢጣልያኖች በሰጡት ግምት የኢትዮጵያ ወታደር 350,000 ነው ይሉና 400,000 ጠመንጃ በያይነቱ፤ 200 መድፍ፤ አምሳ ቀላልና ከባድ ኦርሊኮን (ፀረ አውሮፕላን) አላቸው ብለዋል። ልዎናርድ ሞስሌ እንደፃፈው ደግሞ የኢትዮጵያ ጦር 200 ትናንሽ የተለያዩ መድፎች፤ ለእያንዳንዱ መድፍም 500 ጥይት፤ 3500 መትረየስ፤ 15 አይሮፕላን፤ ለስምንት ወር ከሚበቃ ቤንዚን ጋር ኢትዮጵያውያን ነበራቸው ብሏል።


                       ወደምስራቅ ግንባር የዘመተው የኢትዮጵያ ጦር።

  የኢትዮጵያ ሕዝብ ድል ለመሆን የበቃው በጦር መሪዎቹ የአመራር ችሎታ ማነስና ጠላትን በመናቃቸው ነው። እያንዳንዱ መኩዋንንትም የርስ በርስ ቁርሾ ስላለበት አንዱ አንዱን በመጋፈጥ፤ በጦር ሜዳ ላይ ሹም ሽር በማድረግ፤ ለዘውዱና ለስልጣን የነበራቸው ሽሚያ ሁሉ ተጨምሮ ህዝቡን በአንድነት ሊያስተባብረው ባለመቻሉ ኢጣልያ ድል ለማድረግ ቻለች። ይህን የኢጣልያ ጦር መሪዎች ሁሉ አምነውበታል።


                በዘመናዊ ሁኔታ የሠለጠነው የኢትዮጵያ ጦር በሰልፍ።

  የዚያን ጊዜውን የሁሉንም አሳብ አሁን መናገር አይቻልም እንጂ እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ጦር መሪ ምን አይነት ስህተት እንዳደረገ አለፍ አለፍ እያልን በመጠኑ እናየዋለን። የኢትዮጵያ ጦር አማካሪ የነበረው ሩስያዊው ኮሎኔል ኮኖቫሎፍ (T.E. Konovaloff) በመፅሐፉ "... ራስ ስዩም የተከበሩ እና ክብራቸውን የሚጠብቁ ሰው ናቸው... የቶፖግራፊ ካርታ ሳሳያቸው በዚህ ጉዳይ አትጨነቅ። አልፈልገውም። የካርታ ጉዳይ ስሜት ያለው ራስ ካሳ ነው። በእነሱም ላይ ካርታ ብቻ ሲመለከት ብዙ ሰዓት ያጠፋል። ለኔ ግን ምንም ስሜት አይሰጡኝም። በዚህ ምክንያትም እባክህ አታስቸግረኝ ይሉኛል..." ሲል ፅፏል። ኮኖቫሎፍ የሚያቀርበው ካርታ የኢጣልያ ጦር በየት ቢመጣ በየት በኩል መግጠም እንደሚቻል የሚያስረዳ ነበር። ግን ተቀባይነት አጥቶ ጦሩ እንደዝንጀሮ ገደል እየቧጠጠ እንዲዋጋ እና እንዲያልቅ ሆነ።

  በደቦኖ ቦታ የተተካው ዋናው የኢጣልያ ጦር አዛዥ ማርሻል ባዶልዮም ቢሆን በሁዋላ ጊዜ ባሳተመው መፅሐፉ የኢትዮጵያውያንን የጦር መሪዎች ሁኔታ ገልፆታል "... የኢትዮጵያ ጦር አዛዦች በሙሉ የጦር አዛዥነት ችሎታ ፈፅሞ የላቸውም ... ጉዳዩን ሁሉ በቀላሉ የሚገምቱና የምመፃደቁ ናቸው... " ብሏል።

  የባዶሊዮ የቅርብ ረዳት የነበረው ጄኔራል ኯሪኖ አርሜሊኒ (Quivrino Armellini) ስለኢትዮጵያውያን የጦር መሪዎች ሲገልፅ "... ራስ ካሳ፤ ራስ ሙሉጌታ፤ ራስ ስዩምና ራስ እምሩ ስለጦርነት የተማሩት ትምህርት የለም። ... ታላቅ ሰውነታቸ ብቻ ለጦር አዝማችነት አበቃቸው። ... ምንም አይነት የጦር ትምህርት ሳይኖራቸው, በዘመናዊ የጦር ትምህርት የሰለጠነውን ወታደር፤ ዘመናዊውን መሳሪያና ዘመናዊ ጦር አዛዥችን እንዲገጥሙ ታዘዙ። ይህ ነው ድል ለመሆን ያበቃቸው ምክንያት ..." ብሏል።

  ባዶልዮ ስለራስ ካሳ ሲፅፍ "... የማዘዝ ልምድ የለውም። በደህና ጦርነት ቦታ ውሎ ደህና ውጊያ እንክዋን አላየም። ሌላው ቀርቶ የራሱን ወታደሮች እንክዋን ሥራ ማሰራት አይችልም። ወታደሮቹ ግን ምርጥ ምርጦች ናቸው። ባለፈውም ሆነ አሁን የአበሻ ጦር መሪዎች ከፊታቸው ካለው ጠላት ይልቅ ከሁዋላ የቀረውን ወዳጃቸውን ይፈራሉ። በዚህም ፍራቻ ምክንያት ያላቸውን ኃይል ሁሉ ባንድነት ሰብስበው ከጠላት ጋር አይታገሉበትም። ከሀይላቸው ግማሹ ተከፍሎ በመንደር ይቀርና የጌታውን ክብር እንዲጠብቅ ይደረጋል..." ብሏል። በሌላው የመፅሐፉ ገፅ ላይ ደግሞ ይህንኑ ጉዳይ አንስቶ "... በኢትዮጵያውያን ጦር መሪዎች መሃል መለያየት እና የውስጥ መጠራጠር እንደተፈጠረው ሁሉ ወታደሩም ጌታውን እየተከተለ ተሸካክሯል። ለዚህ ሁሉ መለያየት ያበቁት ንጉሡ ናቸው። ... ራስ ስዩም፤ የግል ጉዳይ የሆነ የማዕረግ ነገር ቂም አለባቸው። ራስ ካሳ ጥሩ የቤተክርስቲያን ሰው ናቸው። ሙሉጌታ ጦረኛና በጦር ያደገ ሰው ነው። በዚህም በጦረኛነቱ ምክንያት ጠቅላይ የኢትዮጵያ ጦር አዛዥ ሆኖ ተሾሞ ነበር..." ብሏል።

  ባዶሊዮ ራስ ሙሉጌታን "... ተሾሞ ነበር..." ያለው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ጦር አዛዥ የነበሩት ራስ ሙሉጌታ ተሽረው ራስ ካሳ ከተሾሙ በሁዋላ ያተተው ነው። ስለራስ ሙሉጌታ መሻርና ስለራስ ካሳ መሾም ባርከር ሲፅፍ "... ንጉሡ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ከታላላቅ ሰዎች የተወለዱ ናቸው እንጂ የጦር አመራር ችሎታ ያላቸው አይደሉም። ለመጀመሪያ ጊዜ ጦርነቱ ውስጥ ለመግባት ደሴ ሲደርሱ የስራ መጀመሪያ ያደረጉት ራስ ሙሉጌታን ሽረው የቅርብ ወዳጃቸውን ራስ ካሳን መሾም ነበር። የጦር ሚኒስትሩ ራስ ሙሉጌታ የታወቀ ጎበዝ ሰው ነበር። የሚጠበቀውና የሚፈራውም የሱ ጦር አመራር ነበር። የወታደሮች ወታደር ነበር። ራስ ካሳ ግን ምንም የጦር ጥበብ የማያውቅ ሰው ነው። ከነገሥታት ትውልድ እና በፖለቲካም ተሰሚነት ስላለው ብቻ ጠቅላይ ጦር አዛዥ ሆነ። ለዚህ ነው ባዶሊዮ የሙሉጌታን መሻርና የካሳን መሾም ሲሰማ የተደሰተው። ..." ካለ በሁላ በሌላ የመፅሐፉ ገፅ ደግሞ "... ሙሉጌታ ተሽሮ ካሳ ሲሾም አምባራዶም ያለው ሙሉጌታና ጎንደር ያለው እምሩ የካሳን ትዕዛዝ ላለመስማት ጆሯቸውን ደፈኑ። ሙሉጌታ የሚደርሰውን ትዕዛዝ እንዳልሰማ እየሆነ ምንም የሰማሁት የለም ይላል። እምሩም የተነሳብኝን ያገር ውስጥ ሽፍታ በመከላከል ላይ ነኝ እያለ አይታዘዝም። የካሳ ትዕዛዝ ተቀባይ አጣ። እነዚህ ሁለት ታላላቅ ጦረኞች የሚያስቡት ሃሳብ ካሳ የሚገጥመውን ገጥሞ እንዲዋረድና ከፍ ያደረገው የንጉሥ አይን ዝቅ እንዲያደርገው ነው ..." በማለት ይተነትናል።

  በርከር "... የተፈራው ጦር የሙሉጌታ ነበር ..." ያለው እውነቱን ነው። ይህን ነገር የኢጣልያ ጦር ጠቅላይ አዛዥ የነበረው ባዶሊዮም በመፅሐፉ እንዲህ ስል ይገልፀዋል "... የጦር ሚኒስትሩ ሽማግሌው ራስ ሙሉጌታ በአድዋ ዘመቻ ክንዱን ያሳየ በመሆኑ የኢትዮጵያን ጦር ፈርተን ብዙ መሳሪያ አከማችተን ነበር። ጦርነቱ እንደተጀመረ ንጉሡ፤ ራስ ሙሉጌታን ሽረው ቄሱን ራስ ካሳን የጦር ሚኒስትር አድርገው በመሾማቸው የኢጣልያ ጦር በቀላሉ ድል እንደሚያደርግ ገብቶን ተደሰትን። በመክዋንንቱ መሃከል ባለው የርስ በርስ ያለመግባባትም ተጠቀምን። ንጉሱም የራስ ሙሉጌታን ሰራዊት እንዲከዳ ስላደረጉ ራስ ሙሉጌታን ከጥቂት ከተረፉ ወታደሮቹ ጋር አዳል በረሃ ውስጥ አግኝተን በአይሮፕላን መትረየስ ገደልነው። በዚህም በሙሉጌታ ሞት የኢትዮጵያውያንን ሞራል ሰበርንው..."

  በኢትዮጵያውያን መሃል ባለው ያለመግባባት እና መለያየት ምክንያት ከውጭ አገር ኢትዮጵያን ለመርዳት የተነሱና በኢጣልያ ግፈኝነት የተበሳጩ የውጭ አገር ሰዎች ሁሉ ተቀባይ አጡ። ኢጣልያ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ባወጀች ጊዜ ከእንግሊዝ አገር ብቻ ሶስት ሺህ ሰዎች ኢትዮጵያን ለመርዳት በወዶ ዘማችነት ተመዝግበው ነበር። እ.ኤ.ዓ. ሴፕቴምበር 4 ቀን 1935 ዓ.ም. የወጣው ዴይል ኤክስፕረስ ጋዜጣ "... ንጉሡ ይህን እርዳታ አልተቀበሉትም። ያልተቀበሉበትም ዋና ምክንያት ለነዚህ ሰዎች የሚከፈል ምንም ነገር የለም ብለው ነው። ከኢትዮጵያውያን ጎን ተሰልፈን እንዋጋለን ያሉት እንግሊዞች ብቻ ሳይሆኑ በራንግል አርሚ ውስጥ የነበሩና ካገራቸው የከዱ ሩስያውያን፤ ቱርኮች፤ ሃንጋርያውያኖችና ቼኮዝሎቫክያን ሁሉ ናቸው። ..." ብሏል። ይህ ብቻ ሳይሆን በኒውዮርክ ከተማ ያሉ አሜሪካውያን በሰላማዊ ሰልፍ በመውጣት የኢጣልያን አድራጎት ተቃወሙ። በማዲሰን አደባባይ የተሰበሰቡ ዘጠኝ ሺህ አሜሪካውያን የሙሶሎኒን ፎቶግራፍ በማቃጠል ተቃውሟቸውን ገለፁ። በኢጣልያ ውስጥም ቢሆን ሳይፈሩ አድራጎቱን የተቃወሙ ሰዎች ነበሩ። በጀርመን ሲኒማ ቤቶችም የሙሶሎኒን ጦር ማጋዝና ማከማቸት የሚያሳየውን "ኢትዮፒያ 1935" የተባለው ፊልም ለሕዝብ እየታየ ህዝቡ ተቃውሞውን ይገልፅ ነበር። በካይሮም የእስልምና ሃይማኖት መሪዎች በየመስጊዱ ሕዝቡን እየሰበሰቡ ኢትዮጵያን በግፍ ከመጣባት መከራ እንዲያድናት እንዲፀለይ አዘዙ።

  ይህ ሁሉ ቢሆንም ጀናው የኢትዮጵያ ሕዝብ በመሪዎች ስህተትና በመሳሪያ እጥረት ድል እየሆነ ይሄድ ጀመር። ባዶሊዮ ራሱ ሲመሰክር "... የኢጣልያ አይሮፕላኖች ዘመናዊና ባለሙሉ ትጥቅ ባይሆኑ ኖሮ ኢትዮጵያውያን የአድዋውን ድል እንደገና ይደግሙ ነበር። በፓይለቶቻችን ታላቅ ተግባር ኢጣልያኖች ድል ለማድረግ በቃን።..." ብሏል።


  ምንጭ:
  የኢትዮጵያ እና የኢጣልያ ጦርነት
  በጳውሎስ ኞኞ
 • loader Loading content ...

Load more...