loader
 • በ፲፱፻፳፰ (1928) ዓ.ም. የኢትዮጵያ እና ኢጣልያን ጦርነት ወቅት የኢጣልያን ጦር ዝግጅት ምን ይመስል ነበር?

  @መርሻ   2 years ago
  Interested in just about everything!
 • loader Loading content ...
 • @መርሻ   2 years ago
  Interested in just about everything!
  ደራሲ እና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ የኢጣልያንን ጦር ዝግጅት እንደሚከተለው ይተርክልናል

  ---------------------------

  ሙሶሎኒ በ1926 ዓ.ም. የቅኝ ግዛቱን ሊብያን ጎብኝቶ ነበር። ሊብያን እየተዘዋወረ ከጎበኘ በሁላ ወደ ሮማ ለመሄድ ከዋናዋ ከተማ ከትሊፖሊ ሲነሳ ለተሰበሰበው የኢጣልያ ሰራዊት ንግግር ሲያደርግ "... ሶማሊያን ጎብኝቻለሁ። ይሄው አሁን ደግሞ ሊብያን ጎበኘሁ። ሁለቱም አሸዋ የተሞሉ ሳጥኖች ናቸው። ወደ ኢትዮጵያ ግፉ። ..." ማለቱን ቤትሪስ የተባለ ደራሲ ዋት ኔክስት፤ ኦ ዱቼ በተባለው መፅሐፉ ገልፆታል። ከዚህ ንግግሩ ቀደም ብሎ በመስከረም ወር ዲስኩር ሲያደርግ "... የኢጣልያ መመርያ መቶ ዓመት በግ ሆኖ ከመኖር አንድ ቀን አንበሣ መሆን ይመረጣል የሚባለውን ፍልስፍና መከተል ነው..." ብሎ ነበር።

  ዱቼ ሙሶሎኒ ከሁለቱም ዲስኩሮቹ በፊት በነሐሴ ወር ብቻ አምሳ ታላላቅ የኢጣልያ የወታደር መርከቦች በስዊዝ ካናል በኩል ወደ ምስራቅ አፍሪካ አልፈዋል። የኢጣልያ መንግስት ወታደሮቹንና የጦር መሣርያውን በስዊዝ ካናል በኩል ሲያሳልፍ 250,000 የእንግሊዝ ፓውንድ ለካናሉ ኪራይ ከፍሏል። የኢጣልያ ጦር ወደ ምስራቅ አፍሪካ ማለት ያን ጊዜ የኢጣልያ ቅኝ ግዛቶች ወደነበሩት ወደ ኤርትራ እና ወደ ሶማሊያ የተጉዓዘው ሰባት ወር ሙሉ ነው።


                             ወደ ኢትዮጵያ የሚጏዘው የኢጣልያ ጦር ስዊዝ ካናልን በመርከብ ሲያቇርጥ።

  ጠቅላላ የጦሩ ዝግጅትና ክምችት ተጠናቆ ያለቀው በነሐሴ ወር ነው። በኤርትራ እና በሶማሊያ የሚከማቸው ጦር ተዘጋጅቶ ካለቀ በሁላ 250,000 የሚሆኑ የኢጣልያ ወታደሮች "ሂዱ" የሚለውን ትዕዛዝ ብቻ ይጠባበቃሉ። ዝግጅቱ በጦር መሳሪያና በወታደር በኩል ብቻ ሳይሆን የወታደሩ ስንቅና ቁስለኛው የሚታከምበት የመርከብ ላይ ሆስፒታሎች ሁሉ ተዘጋጅተዋል። ሙሉ የሆስፒታል ድርጅት ያላቸው መርከቦች ስምንት ሲሆኑ በእነኚህም መርከቦች ውስጥ 6000 ያህል አልጋዎች ተዘርግተውባቸዋል። የእነኚህም መርከቦች ስም ኡራያን፤ ቴቬራ፤ ካሊፎርኒያ፤ ቪዮና፤ ሄለን፤ ቼሳሬ፤ አኩሊያ፤ ግራዲቫ ይባላሉ።

  ዱቼ ሙሶሎኒ ቀደም ብሎ እ.ኤ.አ. መጋቢት 8 ቀን 1935 ዓ.ም. ለምሥራቅ አፍሪካው የኢጣልያ ጦር አዛዥ ለጄኔራል ደቦኖ በፃፈላቸው ደብዳቤ ላይ "... ጦርነቱ በጥቅምት መጨረሻ ወይም በህዳር ወር እንዲጀመር ይሁን። ... ከሁለቱ ቅኝ ግዛቶቻችን ከጨቸመሩት አንድ መቶ ሺህ ጥቁር ወታደሮች ጋር አሁን ሶስት መቶ ሺህ ወታደር አለህ። በተጨማሪ አምስት መቶ ያህል አውሮፕላኖች ሶስት መቶ መኪናዎችም እልክልሃለሁ። እደግመዋለሁ፤ አስር እልክልሃለሁ። አምስት ዲቪዚዮን ከመደበኛው ወታደር፤ አምስት ዲቪዚዮን ደግሞ በፈቃደኝነት ከምዘምቱ ባለጥቁር ሸሚዞች እልክልሃለሁ። እነኚህም የምልክልህ በጥንቃቄ የተመረጡና የሰለጠኑ ናቸው። ... በጥቂት ሺህ ሰዎች እጥረት ምክንያት የአድዋን ድል አጣነው። ያን ስህተት ዛሬ አንደግመውም። ..." የሚል ቃል ላከለት።


                                     ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የኢጣልያ ጦር ምፅዋ ወደብ ላይ ሲራገፍ።

  ሙሶሎኒ እና ደቦኖ ይህን ደብዳቤ በተፃፃፉበት ጊዜ ኢጣልያ በሁለቱ ቅኝ ግዛቶቿ ያሰፈረችው ጦር ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ሀገሮችም ማስገበሪያ ጭምር በቂ ነው ተብሎ ተገምቷል። በዚያን ጊዜም 298, 821 ወታደር 19,233 የጭነት እንስሳት፤ 5000 መኪናና ሞተር ብስክሌት፤ 207, 219 ቶን የሚመዝን የጦር መሳሪያ፤ 26,000  መንገድ የሚሰሩ ተራ ኢጣልያኖች በሁለቱ ቅኝ ግዛቶቿ ውስጥ ነበሯት። ሙሶሎኒ በደብዳቤው ለጄኔራል ደቦኖ ቃል በገባለት መሰረት ጦርነቱ ሊጀመር ሲል የጦሩ ዝግጅት ብዛት 360,000 ወታደር፤ 30,000 እንስሳት (በቅሎና ፈረስ)፤ 6500 መኪናና ሞተር ሳይክል፤ ሶስት ሚሊዮን ቶን የሚመዝን የጦር መሳሪያና 50,000 መንገድ ሰሪ ተከማቼ።


                                   ለውጊያ የመጡ አውሮፕላኖች ወደብ ላይ ከመርከብ ሲራገፉ።


                                  ለውጊያ የመጡ ፈረሶች ምፅዋ ወደብ ላይ ከመርከብ ሲራገፉ።

  ኢጣልያ የተዘጋጀችው በጦር መሳሪያ ብቻ አልነበረም። ሰላዮቿ ባቀርቡላት የኢትዮጵያ ሁኔታም ጭምር ነበር። በተለይ ደጃች ኃይለስላሴ ጉግሳ አስጠንተው ለደቦኖ የሰጡት የኢትዮጵያ ካርታ ጥሩ መመሪያ እና ጠቃሚ ሆኗል። ሌሎቹም ሰላዮች ቀደም ብለው በመግባት የመሄጃ መንገዱንና የማጥቂያ ቦታውን ሁሉ አጥንተው አቅርበዋል። ጠቃሚ ጥናት ካቀረቡት ሰላዮችም መሃል ቱሊዮ ፓስቶሪ ይገኝበታል። ቱሊዮ ፓስቶሪ በስለላ ተግባሩ ምን እንደሰራ ለአንጄሎ ዴል ቦካ አጫውቶት አንጀሎ በመፃፉ ፅፎታል። እንዲህ ይላል "... ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ አመታት የቆየሁ ነኝ። 64 ዓመት ሙሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ተዘዋውሬአለሁ። ከንጉሥ ምኒልክ ጋርም ወዳጅ ነበርን። ... በ1924 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ.) በሁዋላ ጄኔራል የሆነው ካፒቴን ማላድራ (Malladra) ጠራኝ እና አንድ ሚሽን ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ ስላሰብን አብረህ ለመሄድ ፍቃደኛ ነህን? አለኝ። ... ጅኦሎጂስት ነኝና በኢትዮጵያ ውስጥ በማዕድን ፍለጋ ስም ገብተን የኢጣልያን ጦር በጉዞው ላይ ሊያጋጥመው የሚችሉትን የመንገድ መሰናክሎች ማለት ወንዞች እና ተራራዎችን እንድናጠና ነበር። ... ወንዞች በበጋ እና በክረምት ያላቸውን የውሃ ብዛት ሁሉ በሚገባ እየለካሁ እንዳጠናና ውሃ የምበዛባቸውንም ወንዞች በየት በኩል ማቁዓረጥ እንደሚቻል የመሸጋገሪያውን መልካ ሁሉ እንዳጠና ነበር። ... ዝግጅታችን ካለቀ በሁዋላ በ1928 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ.) ከእንግሊዛዊው ጂኦሎጅስት ኔስቢት (L.M. Nesbitt) ጋር ሆነን ከአዲስ አበባ እስከ ደንከል በረሃ እስከ ዳሎል ድረስ አጠናን። ... በተለይ ከአዲስ አበባ ጅቡቲ የሚወስደው የባቡር ሐዲድ የሚያልፍበትን የአዋሽን ድልድይ ደህና አድረጌ አጠናሁት። የድልድዩን ደካማ ጎኑንም አጠናሁ። ይህን በምሰራበት ጊዜ በጉዟችን ላይ ለሚያጋጥሙን መኩዋንንቶች ሁሉ በንጉሡ ላይ አድማ አድርገው እንዲነሱም እንሰብክ ነበር። ... አሁን አንዳንድ ሰዎች ደጃች ኃይለስላሴ ጉግሳን ያስከዳው ባሮን ፍራንኬቴ ነው ይላሉ። እሱ አይደለም። ኃይለስላሴ ጉግሳን ያስከዱት የሚስጥር ሰራተኞቻችን ሰርጀንት ኢሬ እና ሲኞር ሜኦ ናቸው። ... በዚህ ስብከታችን ምክንያት ጦርነቱ በተጀመረ ጊዜ ከኢትዮጵያ ጦር ሶስት እጁ ያህል ሳይዋጋ ቀረ። ለምሳሌ እንደ ደጃች አያሌው ብሩ ያሉት ጦራችንን በደስታ ተቀብለው የሸኙ ሰው ናቸው። በዚህ በኩል የፖለቲካ ሰዎቻችን መልካም ውጤት አስገኝተዋል..."

  የኤርትራ ገዢ የነበረው ኮራዶ ዞሊ "... በኢትዮጵያውያን መካከል ከባድ ብጥብጥ እንዲነሳ የመከፋፈሉን ተግባር ያካሄድ የነበረው የኤርትራው ግዛት ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ አስጨናቂና አስቸኩአይ የመንግስት ግልበጣዎች እንዲጠነሰሱ አድርገናል። ... አብዛኛውም ቅስቀሳችን በትግሬዎችና በአማራዎች መሃል ጥላቻ እንዲፈጠር ነበር። በተለይ በሸዋ ...." በማለት እትዮፒያ ዲ ኦጂ በሚባለው መፅሐፉ ውስጥ ፅፎታል።

  በዝግጅቱ አለመሟላት አዝኖ የነበረው ደቦኖ በዝግጅቱ መሟላት ተደሰተ። በህዋላ ጊዜ በፃፈው መፅሃፉም ይህን ሁኔታ ያብራራና "... አሁን ሁሉም ተልኮልናል። በመጀመሪያ ድቪዝዮናችን ውስጥ የነበሩት ወታደሮች በሚገባ የተመረጡ አልነበሩም። በክፍለ ጦሩ ውስጥ 12,000 መምህራን፤ አራት መድሃኒት ቀማሚዎች ሶስት ጠበቆች፤ ዘጠኝ ሰዓት ሰራተኞችና ብዙ ጠጉር ቆራጮች ሁሉ ወታደር ተብለው ተልከው ነበር። ያኔ የተገኘውን ሁሉ እያጋበሱ መላክ ነበር። ..." ብሏል።

  ሙሶሎኒ ለደቦኖ አንድ ቴሌግራም አሳለፈ። ቴሌግራሙም "... በሶስተኛው ቀን የወደፊት ጉዞህን እንድትጀምር አዝዤሃለሁ። ጥቅምት 3 ቀን እልሃለሁ። ..." የሚል ነበር። እ.ኤ.አ. ጥቅምት ሁለት ቀን ማታ ደቦኖ የሚከተለውን አዋጅ አወጀ። "የበላይ መኮንኖች፤ የበታች መኮንኖች፤ የምድር፤ የባህር እና የአየር ኃይል ወታደሮች፤ ባለጥቁር ሸሚዞች፤ ጥቁር ወታደሮች (አክሰሰሪ) -- በፀጥታ እና በሚደነቅ ዲስፕሊን እስከዚህች ቀን ድረስ ቆይታችዋል። ዛሬ ቀኑ ደረሰ። ግርማዊ ንጉሳችንና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ቤኒቶ ሙሶሎኒ ወሰን አልፋችሁ እንድትጉዋዙ አዟል። ኩራት እና ክብር ወደፊት ይመራችሁዓል። ባለኝ የአዛዥነት ልምድ በመላው ወታደር ዘንድ የጠበቀ ስነ ስርዓት እንዲኖር እፈልጋለሁ። ከባድ መስዋዕትነት የሚጠይቅ ጉዞ ነው። ጦረኛ የሆነ ጠላት ይጠብቃችሁዓል። የነፃና የጠራ ድል ግን የኢጣልያ ፋሺስት ይሆናል። -- ጄኔራል አሚሊዮ ደቦኖ"

  እ.ኤ.አ. ጥቅምት 3 ቀን 1935 ዓ.ም. በኛ አቆጣጠር መስከረም 23 ቀን 1928 ዓ.ም. ጦርነቱ እንዲጀመር ትዕዛዝ በተሰጠበት እና የኢጣልያ ጦር በተንቀሳቀሰበት እለት በኢጣልያ ከተሞች በሙሉ የቤተ ክርስቲያን ደውሎች ተደወሉ። ህዝቡ በሙሉ በየከተማዎቹ እየተዘዋወረ ታላቅ በዓል እና ሰልፍ አደረገ። ከሰዓት በሁዋላ ዱቼ ሙሶሎኒ በፓላዞ ቬኔዚያ ሆነው ለመላው የኢጣልያ ሕዝብ ንግግር አደረጉ "... እናንተ ባለጥቁር ሸሚዞች፤ የኢጣልያ ወንዶች እና ሴቶች፤ በመላው ዓለም የተበተናቹ፤ በተራራ ላይ፤ በባህር ዳርቻ ያላችሁ ሁሉ ስሙኝ። ለሀገራችን ታላቅ ታሪክ የሚሰራበት ሰዓት ተደወለ። በዚህች በአሁኗ ሃያ ሚሊዮን ኢጣልያውያን በኢጣልያ አደባባዮች ተሰብስበዋል። ... እንዲህ አይነት የህዝብ መሰብሰብ በታሪክ ውስጥ ያቶም ተሰምቶም አይታወቅም። ሃያው ሚሊዮን ሕዝብ የተሰበሰበው ባንድ ልብ፤ ባንድ ፍቃድ፤ ባንድ ውሳኔ ሆኖ ነው። ከብዙ ወራት ጀምሮ የክብራችን መንኮራኩር ሲሽከረከር ቆይቶ አሁን ወደ ግቡ በማምራት ላይ ነው። ጉዞው ፈጣን ነው። ረጅም ጉዞ ሳይግዋዝም አይቆምም። ጉዞው የወታደር ጉዞ ብቻ ሳይሆን የመላው የኢጣልያ ሕዝብ የተባበረ ጉዞ ነው። ጉዞው የአርባ አራት ሚሊዮን ነፍሳት ጉዞ ነው። ... አርባ ዓመት ሙሉ ኢትዮጵያን በትግስት ጠበቅናት። አሁን ግን በቃ ..." ሙሶሎኒ በዚህ ንግግሩ መላውን የኢጣልያ ሕዝብ ከመቀስቀሱ በፊት የመንኮራኩሯ ጉዞ ተጀምሮ ነበር። ይህ ዲስኩር ከመደረጉ በፊት በዋዜማው ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት የኢጣልያ ወታደር መረብን ተሻግሮ ነበር።


                            ሙሶሎኒ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ማወጁን ለጣልያን ህዝብ ባደባባይ ሲገልፅ።

  "ወደፊት ሂዱ" የሚለው ትዕዛዝ እስኪደርስ ድረስ አንድ መቶ ሺህ የኢጣልያ ወታደር ከወሰኑ ከመረብ አካባቢ ሰፍሮ ነበር። ጄኔራል ቪላሳንታ በመረብ አካባቢ ለተሰበሰበው ወታደር "... መረብ ለአርባ አመታት ያህል የማይጠቅም የሰላም ውል ምልክት ሆኖ ቆየ ... አሁን ግን ያ ወረቀት መቀደዱ ነው..." በማለት ንግግር አደረገ።

  ይህ ወሰን አልፎ የገባው የኢጣልያን ጦር ወሰኑን ያቁዓረጠው በዕለቱ ስልሳ ኪሎ ሜትር ተጉዞ ነው። ወሰኑን አልፎ በዓል ከተደረገ በሁዋላ በጄኔራል ማራቬኛ የሚመራው ሁለተኛው ዲቪዥን ጦር በስተቀኝ በኩል ጉዞውን ወደ አድዋ ቀጠለ። በመሃል ደግሞ በጄኔራል ፒርዚዮ ቢሮሊ የሚመራው ጦር ወደ እንትጮ አቅጣጫ አመራ። በስተግራ በጄኔራል ሳንትኒ የሚመራው ጦር ወደ አዲግራት ተጉዋዘ። በዚህ ጉዞ ላይ ለእያንዳንዱ ወታደር አምሳ ኪሎ ግራም የሚመዝን ጥይት ተደልድሏል። እያንዳንዱ ወታደርም የአራት ቀን ምግቡንና ሁለት ሊትር በሚይዝ ኮዳ ውሃ ይዟል። ፀሐይዋ ሞቅ ባለች ጊዜ ወታደሩ ሁሉ እየዘመረ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ይጉዓዝ ጀመር።

  በጦሩ መሃል የጦሩን ሁኔታ የሚከታተሉና ታሪክ የሚፅፉ 300 ጋዜጠኞችና ደራስያን ነበሩ። ጋዜጠኛው ቼስኮ ቶማሲሊ ስለዚያች ጉዞ በመፅሐፉ ሲገልፅ እንዲህ ይላል። "... መንገደኛው ወታደር ሁሉ እያንዳንዱ በሚያልፍበት ቦታ አፈር በጣቱ እያነሳ በምላሱ የአፈሩን ጣዕም ይቀምስ ነበር። ይህም የአፈሩን አይነት ለማወቅና ለመለየት እያሉ ነው። ይህን ምርምር የሚያደርጉበት ምክንያት ከጦርነቱ በሁዋላ የምያለሙትን መሬት ለመምረጥ ብለው ነው። ከመጀመሪያው ጀምሮ ያገኙትንና የቀመሱትን ሁሉ ጥሩ አፈር ነው እያሉ ይነጋገራሉ። እልፍ ባሉ ቁጥር ደግሞ የተሻለ አፈር ያገኙና ይሄ የበለጠ ነው ይላሉ። ይሄ ባመት ሁለቴ ሰብል ይሰጣል። ይሄ ደግሞ በዓመት ሶስቴ ሰብል ይሰጣል እያሉ እየተነጋገሩ ይጉዋዛሉ..." ብሏል።


                                                       የኢጣልያን ጦር መረብን ሲያቇርጥ።

  የኢጣልያ ጦር ያለምንም ተከላካይ ተጉዋዘ። የኢትዮጵያ መንግስት የኢጣልያ መንግስት ወሰን አልፎ መጉዋዙን ለሊግ ኦፍ ኔሽንስ አመለከተ። ኢጣልያ መረብን እንዳትሻገር እንዲከላከሉ ራስ ስዩም ታዘው ነበር። ራስ ስዩም ግን በስፍራው አልተገኙም።

  ምንጭ:
  የኢትዮጵያ እና የኢጣልያ ጦርነት
  በጳውሎስ ኞኞ
 • loader Loading content ...

Load more...