loader
 • አርብ የሚጸለይ አምላክን የወለደች የድንግል ማርያም ምስጋና

  @Mikurab Zeleke   5 months ago
  Sewasewer
 • loader Loading content ...
 • @Mikurab Zeleke   5 months ago
  Sewasewer

  ፩. ከሴቶሽ ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ። የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው ያለርኩሰት አምላክን የወለድሽ ድንግል ማርያም ሆይ እውነተኛ ፀሐይ ከአንቺ ወጣልን (ጌታ ተወለደልን) በክንፈ ረድኤቱም አቀረበን። እርሱ ፈጥሮናልና። ቅድስት ሆይ ለምኝልን። 

   

  ፪. አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ሆይ የብርሃን እናት ነሽና አንቺን በክብር በምስጋና እናገንሻለን። የተባረክሽ አንቺ ከመላእክት ትበልጫለሽ ከደቂቀ አዳምም ትበልጫልሽ ከአሳቦች ሁሉ ትበልጫልሽ ገናንነትሽን መናገር የሚቻለው ማነው አንቺን የሚመስል የለምና። ማርያም ሆይ መላእክት ያገኑሻል ሱራፌልም ያመሰግኑሻል። በኪሩቤልና በሱራፌል ላይ አድሮ የሚኖር ጌታ መጥቶ በማኅፀንሽ አድሮአልና። ሰውን የሚወድ ወደ እርሱ አቀረበን። ክብር ምስጋና ያለው እርሱ የእኛን ሞት ተቀብሎ የእርሱን ሕይወት ለእኛ ሰጠን። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።  

   

  ፫. የደናግል መመኪያቸው አምላክን የወለድሽ ድንግል ማርያም ሆይ የተባረክሽ ነሽ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። ከዓለም በፊት የነበረ እርሱ ሰው ሆኖዋልና ከአንቺ የተወለደ ሥጋችንን ነሣ (ተዋሐደ) መንፈስ ቅዱስንም ሰጠን። በቸርነቱ ብዛት መሳዮቹ አደረገን። ጸጋንና ክብርን ከተቀበሉ ብዙ ሴቶች አንቺ ትበልጫለሽ። አምላክን የወለድሽ ማርያም ሆይ ልዑል እግዚአብሔር ያደረብሽ (የከተመብሽ) ረቂቅ ከተማ ነሽ። በኪሩቤልና በሱራፌል ላይ የሚኖረውን ጌታን በመኻል እጅሽ ይዘሽዋልና። በቸርነቱ ብዛት ሥጋዊ ፍጥረትን ሁሉ የሚመግብ እርሱ ጡትሽን ይዞ ጠባ። ይኸውም ሁሉን የሚያድን አምላካችን ነው። ለዘለዓለሙ ይጠብቀናል። እንሰግድለትና እናመስግነው ዘንድ እርሱ ፈጥሮናልና። ቅድስት ሆይ ለምኝልን። 

   

  ፬. ድንግል ማርያም የሽቱ መኖሪያና የሕይወት ውኃ ምንጭ ናት። የማኅፀኗ ፍሬ ሰውን ሁሉ አድኖአልና። ከእኛም እርግማንን አጠፋልን። በመካከላችንም ሆኖ በመስቀሉ አስታረቀን በልዩ ትንሣኤውም ሰውን ዳግመኛ ወደ ገነት መለሰው። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።  

   

  ፭. ንጽሕት ድንግል ማርያም የታመነች አምላክን የወለደች ናት። ለሰዎች ልጆችም የምሕረት አማላጅ ናት። ኃጢአታችንን ያስተሠርይልን ዘንድ ወደ ልጅሽ ወደ ክርስቶስ ለምኝልን። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።  

   

  ፮. ድንግል ማርያም በቤተ መቅደስ አሰምታ ትናገር ነበር። መልአኩ ቅድስት ድንግል ሆይ ሰላምታ ይገባሻል ብሎ አክብሮ ከነገረኝ ነገር በቀር ምንም ምን ሌላ የማውቀው እንደሌለኝ እግዚአብሔር ያውቃል አለች። የማይቻለውን ቻልሽ የማይወሰነውንና ምንም ምን የሚወስነው የሌለውን ወሰንሽ። በክብር ሁሉ ላይ ጸጋን የተመላሽ ሆይ ምስጋናሽ ይበዛል ክብርሽ ፍጹም ነው። የአብ ቃል ማደሪያ ሆነሻልና የክርስቲያን ወገኖች ምእመናንን የምትሰበስቢያቸውና ማሕየዊ የሚያድኑን ለሆኑ ሥላሴ ሰጊድን (መሰገድን) የምታስተምሪላቸው ሰፊ መጋረጃ ሙሴ ያየውን የእሳት ዓምድ የተሸከምሽ አንቺ ነሽ። ይኸውም መጥቶ በማኅፀንሽ ያደረው የእግዚአብሔር ልጅ ነው። ሰማይና ምድርን ለፈጠረ ጌታ ማደሪያ ሆንሽ። ዘጠኝ ወር በማኅፀንሽ ተሸከምሽው። ሰማይና ምድር ለማይወስኑት የታመንሽ አንቺ ነሽ። ከምድር ወደ ሰማይ ለማረግ መሰላል ሆንሽ፤ ብርሃንሽ ከፀሐይ ብርሃን ይበልጣል። ቅዱሳን በፍጹም ደስታ ያዩት ኮከብ ካንቺ የተወለደ ምሥራቅ አንቺ ነሽ። ይኸውም በጻርና በምጥ ትወልድ ዘንድ በሔዋን የፈረደባት ነው። አንቺ ማርያም ግን ጸጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ የሚል ቃልን ሰማሽና መጥቶ ያዳነን የፍጥረት ሁሉ ገዥ የሆነ ንጉሥን ወለድሽልን። ስለዚህ ማርያም ሆይ የተባረክሽ ነሽ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። ጸጋን የተመላሽ ሆይ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነውና ደስ ይበልሽ እያልን መልአኩ ገብርኤል እንዳመሰገነሽ እናመሰግንሻለን። ቅድስት ሆይ ለምኝልን። 


 • loader Loading content ...

Load more...