loader
 • አቡነ ጴጥሮስን የሃይማኖት አባትም አርበኛም ናቸው ያሠኛቸው ሥራቸው ምንድን ነው?

  @Hilina   2 years ago
  Sewasewer
 • loader Loading content ...
 • @Dani   2 years ago
  Sewasewer
  በ1875  አመተ  ምህረት  በበፊቱ  አጠራር በሰሜን  ሸዋ  ሠላሌ  አውራጃ  በፍቸ  ከተማ  የተወለዱት  አቡነ ጴጥሮስ  የጵጵሥና ማዕረጋቸውን ከማግኘታቸው በፊት መምህር ሃይለማርያም በሚለው መጠሪያ ይታወቁ ነበር። ገና ትንሽ ልጅ እያሉ አባታቸው በመንፈሣዊ ትምህርት እንዲማሩ ከፍተኛ ጉጉት ሥለነበራቸው ደብረሊባኖሥ ገዳም ውሥጥ ያሥተምሩ ከነበሩት መምህር ተድላ ከሚባሉ አባት ጋ አሥገቧቸው። በአጭር ጊዜ ውሥጥ ከንባብ እሥከ ቅኔ ያለውን ትምህርት ማጠናቀቅ በመቻላቸው ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ጎጃም ዋሽራ ተላኩ። ዋሽራ ውሥጥም የጠለቀ ቅኔን እና ለመምህርነት የሚያበቁ የተለያዩ ትምህርቶችን ተማሩ። ይህንን እንዳጠናቀቁም ጎንደር ውስጥ የዜማ ትምህርትን ተማሩ። ከዚያም ወደወሎ ሄደው ሥለ መፅሃፍ ትርጏሜ ተማሩ። እነኘህን ትምህርቶች ተምረው እንዳጠናቀቁም ወሎ ውሥጥ በሚገኘው ምሥካበ ቅዱሳን ገዳም ውሥጥ ከ1900 ጀምሮ ለአሥር አመታት አሥተምረዋል። ከዚያም በ1909 ደብረ ሊባኖሥ ውሥጥ ሥርዓተ ምንኩሥናን ፈፅመውና የቅሥናን ማዕረግ ተቀብለው ለትንሽ ጊዜ እዚያው አገለገሉ። ከዚያም በ1910 መምህር ሃይለማርያም ተብለ በመሾም ወላይታ ውስጥ በሚገኘው ደብረ መንክራት ምሁር እየሡሥ ተብሎ በሚጠራው ገዳም ውሥት ለሥድሥት አመታት አገለገሉ። ክሥድሥት አመታት አገልግሎት በሇላም በዝዋይ ድብረ ጽዮን ማርያም ገዳም በመምህርነት ተሾሙው አገልግለዋል። 

  መምህር ሃይለማርያም በ1916 ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ተደርገው የመንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ መምህር ሆነው ማገልገል ቀጠሉ። እዚሁ ቤተክርሥትያን እያሥተማሩም የልዑል አልጋወራሽ ተፈሪ መኮንን በሇላም ቀዳማዊ ሃይለሥላሤ የንስሃ አባት ሆኑ። 

  የግብፅ ቤተ ክርስትያን ምንም እንኯን ለጊዜውም ቢሆን የሊቀ ጵጵስናውን መንበር አለቅም ብትልም፣ ከአንድ ሺ ስድስት መቶ አመታት በሇላ የኢትዮጱያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን በዕውቀተ መንፈሳዊ ከሷ ተወልደው በእቅፏ ውስጥ ባደጉ ኢትዮጵያን ጳጳሳት እንድትመራ ፈቃዷን ስትገልፅ በትምህርታቸውና በስነ ምግባራቸው የተመሰከረላቸው አምስት ኢትዮጵያን አባቶች ተመርጠው ነበር። ከተመረጡትም አባቶች አንዱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ነበሩ። በዚህም መሰረት በ1921 ወደግብፅ እሥክንድርያ ተልከው የጵጵሥና ማዕረግ ተቀብለው ተመለሡ። ወደ ሃገራቸውም ከተመለሱ በሇላ 'አቡነ ጴጥሮስ ጳጳሰ ዘምስራቅ ኢትዮጵያ ተላዌ አሠሩ ለአቡነ ኢየሱስ ሞዓ' ተብለው በያኔው መንዝና ወሎ ሀገረ ስብከት ተሾሙ።  


                    አቡነ ጴጥሮስ ጳጳሰ ዘምስራቅ ኢትዮጵያ ተላዌ አሠሩ ለአቡነ ኢየሱስ ሞዓ    

  የጣልያንን ወረራ ለመከላከል  በ1928 አዋጅ በታወጀ ጊዜ አቡነ ጴጥሮሥ ንጉሠነገሥቱን ተከትለው ወደማይጨው ዘመቱ። በ1928 ሐምሌ21 ቀን የተባበሩት የአርበኞች ግምባር አዲስ አበባ ላይ የሠፈረውን የጠላት ጦር ለመዋጋት በአደረገው ቀጠሮ መሠረት አቡነ ጴጥሮሥ በነደጃዝማች አበራ ካሣ ይመራ ከነበረው የሠላሌ ጦር አብረው ወደ አዲስ አበባ ገቡ። ይህ ጦር ግን የሚፈለገው ውጤጥ አለመምጣቱን በመገንዘብ ወደመጣበት ሢያፈገፍግ አቡነ ጴጥሮሥ የአዲስ አበባን ህዝብ ሠብከው በጠላት ላይ ለማሥነሣት በማሠብ ከጦሩ ተለይተው አዲስ አበባ ቀሩ። ብዙም ሣይቆዩ አንድ ቀን ብቻ እንደቆዩ ተይዘው የኢጣልያ የጦር መሪዎች ፊት ቀረቡ። 

  ብፁእነታቸው በተጠቀሰው ቀን ከተያዙበት ጊዜ ጀምሮ በጠላት የጥይት እሩምታ እስከተገደሉበት ጊዜ ድረስ የነበረውን ሂደት 'ኮርየር ዴላሴራ' የተባለው ጋዤጣ ወኪል እና የምስራቅ አፍሪካ ዜና መዋዕል አዘጋጅ የነበረው ፖጃሌ የተባለ ጋዜጠኛ እ.ኤ.አ. ሰኔ 15 ቀን 1936 ዓም አዲስ አበባ በነበረ ጊዜ ሂደቱን ባየውና በተመለከተው መንገድ እንደሚከተለው ፅፎ ነበር

  "ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ቁመታቸው ረዘም ፊታቸውም ዘለግ  ያለና መልካቸው ጠየም ያለ ዐዋቂነታቸውና ትሕትናቸው ከገጻቸው  የሚነበብ ሲሆን በዚህ ጊዜ ለብሰውት የነበረው ልብሰ ጵጵስና ጥቁር  ካባ ያውም በጭቃ የተበከለ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ  ወደ ችሎት ቀረቡ፡፡ ለፍርድም የተሠየሙት ዳኞች ሦስት ሲሆኑ  እነዚህም ጣሊያኖችና የጦር ሹማምንት ናቸው፡፡ የመካከለኛው ዳኛ  ኮሎኔል ነበር፡፡ የቀረበባቸውም ወንጀል 'ሕዝብ ቀስቅሰዋል፣ ራስዎም ዐ ምፀዋል፣ ሌሎችንም አንዲያምፁ አድርገዋል' የሚል ነበር፡፡  ዳኛውም 'ካህናቱም ሆኑ የቤተ ከህነት ባለሥልጣኖች ሊቀ ጳጳሱ  አቡነ ቂርሎስም የኢጣሊያንን መንግሥት ገዢነት አምነው አሜን  ብለው ሲቀበሉ አርስዎ ለምን ዐመፁ፣ ለምን ብቻዎን አፈንጋጭ  ሆኑ?' ሲል ጠየቃቸው ፡፡ አቡነ ጴጥሮስም የሚከተለውን መለሱ''፡፡ 

  'ፈአቡነ ቄርሎስ  ግብፃዊ ናቸው፣ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር  የለም፡፡ አኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ ሐላፊነትም ያለብኝ የቤተ ከርስ ቲያን አባት ነኝ፡፡ ስለዚህ ስለ ሀገሬና ስለ ቤተ ከርስቲያኔ አቆረ ቆራለሁ፡፡ ከዚህ በቀር ለእናንተ ችሎት የማቀርበው ነገር የለኝም፡፡  ለፈጣረዬ ብቻ የምናገረውን አናገራለሁ፡፡ እኔን ለመግደል እንደ ወሰናችሁ ዐውቃለሁ፡፡ ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፡፡  ግን ተከታዮቹን አትንኩ' አሉ፡፡
  ይሀንንም ብለው በጥይት ተደብድበው ሲገደሉ እንዲያይ  ተጋብዞ ለተሰበሰበው ሕዝብ የሚከተለውን ሕያው መልእከት  አስተላለፉ፡፡ 

  ''አረማዊ የሆነው የፋሺስት መንግሥት ቤተ ክርስቲያንን ለማቃጠል፣ ሕዝበ ክርስቲያንን ለመግደል፣ ሃይማኖትን  ለማጥፋት፣ ታሪካችንን ለማበላሸት የመጣ ነው፡ እንጂ በጎ  ለመሥራት፣ እውነተኛ ፍርድ ለመስጠት ስላልመጣ ለዚህ ለግፈኛ  አትገዙ። ስለ ውድ ህገራችሁ፣ ስለ ቀናች ሃይማኖታችሁ ተከላከለ።  ነጸነታችሁን ከሚረክስ ሙታቹህ ስማችሁ ሲቀደስ ታላቅ ዋጋ ያለው ክብር ታገኛላችሁ። የኢትዮጵያ ህዝብ ለዚህ ለጠላት እንዳይገዛ አውግዣለሁ፤ የኢትዮጵያ መሬት ጠላትን ብትቀበል የተረገመች ትሁን። በፈጣሪየ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተገዘተች ትሁን።''
  ከዚያ በኋላ ስምንት ወታደሮች በስተጀርባቸው ሃያ ርምጃ  ርቀው ተንበርክከው በተጠንቀቅ ቆሙ። ወዲያው አዛዡ 'ተኩስ'  በማለት ትእዛዝ ሲስጥ ስምንቱም ተኩስው መቱዋቸው። ግን  በስምንት ጥይት ሳይሞቱ ቀሩ። መሞታቸውንና አላመሞታቸውን  ለማረጋገጥ ዶክተር ተጠራ። ዶክተሩም እንዳልሞቱ አረጋገጠ።  ከዚያም ሌላ ወታደር በሦስት የሽጉጥ ጥይት ራስ ቅላቸውን መትቶ  ገደላቸው፡፡"

  ጠላት ድል ተደርጎ ሀገራችን ነፃነቷን ከተቀዳጀች በኋላ  የብፁዕነታቸውን አኩሪ ታሪክ ትውልድ ሲዘክርላቸው እንዲኖር  መታሰቢያ ይሆናቸው ዘንድ በግርማዊ ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት  አሳሳቢነት ሐምሌ 16 ቀን 1938 ዓም በአዲስ አበባ ከተማ  እምብርት ሐውልት ቆሞላቸዋል። ከድል በኋላ የብፁዕነታቸው  ሐውልት ተመርቆ የቤተ መንግሥቱም ሆኑ የቤተ ክህነቱ  ባለሥልጣናት የአበባ ጉንጉን ከሐውልቱ ሥርአሥቀምጠውላቸዋል።
    

   
  አዲስ አበባ ውሥጥ የሚገኘው የአቡነ ጴጥሮሥ መታሠቢያ ሃውልት

                    አቡነ ጴጥሮስ መታሰቢያ ሃውልት ሲቆምላቸው የበዓሉ አከባበር

  በግድያቸው ወቅት የነበረውን ሙሉ ሂደት እና ክስተት እዚህ ( http://www.sewasew.com/phrases/1353?withDetails=1 ) ይመልከቱ

  ምንጭ:-
        1)   ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን (ዲ/ን መርሻ አለሀኝ)
        2)  ታሪካዊ መዝገበ ሠብ (ፋንታሁን እንግዳ)

 • loader Loading content ...
 • @Tola (ቶላ)   2 years ago
  ከተኛ አንበሳ ዞር ዞር ያለ ቀበሮ ይሻላል!
  ሎውሬት ፀጋዬ ገብረመድህን የሚከተለውን ግጥም ለኚህ ጀግና ሰው ፅፎላቸዋል።  የግጥሙ ርዕስ "ጴጥሮስ ያቺን ሰዐት ይሰኛል"

  አዬ፣ ምነው እመ ብርሃን? ኢትዮጵያን ጨከንሽባት?
  ምነው ቀኝሽን ረሳሻት?
  እስከመቼ ድረስ እንዲህ፣ መቀነትሽን ታጠብቂባት?
  ልቦናሽን ታዞሪባት?
  ፈተናዋን፣ ሰቀቀኗን፣ ጣሯን ይበቃል ሳትያት?
  አላንቺእኮ ማንም የላት….
  አውሮጳ እንዲሁ ትናጋዋን፣ በፋሽስታዊ ነቀርሳ
  ታርሳ፣ ተምሳ፣ በስብሳ
  ሂትለራዊ እባጭ ጫንቃዋን፣ እንደኮረብታ ተጭኗት
  ቀና ብላ እውነት እንዳታይ፣ አንገቷን ቁልቁል ጠምዝዟት
  ነፍሷን ድጦ ያስበረከካት
  ሥልጡን፣ ብኩን፣ መፃጉዕ ናት፤ ….
  እና ፈርቼ እንዳልባክን፣ ሲርቀኝ የኃይልሽ ውጋገን
  አንቺ ካጠገቤ አትራቂ፣ በርታ በይኝ እመ ብርሃን
  ቃል ኪዳኔን እንዳልረሳት፣ እንዳልዘነጋት ኢትዮጵያን፡፡
  አዎን፣ ብቻዬን ነኝ ፈራሁ
  እሸሸግበት ጥግ አጣሁ
  እምፀናበት ልብ አጣሁ
  እማማ ኢትዮጵያን መንፈሴ፣ ተፈትቶ እንዳይከዳት ሠጋሁ …
  አዋጅ፣ የምሥራች ብዬ፣ የትብት ምግቤን ገድፌ
  ከእናቴ ማኅፀን አርፌ
  ከአፈርዋ አጥንቴን ቀፍፌ
  ደሜን ከደሟ አጠንፍፌ
  ከወዟ ወዜን ቀፍፌ
  በሕፃ እግሬ ድሄባት፣ በህልም አክናፌ ከንፌ
  እረኝነቴን በሰብሏ፣ በምድሯ ላብ አሳልፌ
  ከጫጩት እና ከጥጃ፣ ከግልገል ጋር ተቃቅፌ፤
  በጋው የእረኛ አደባባይ፣ ክረምት እንደወንዙ ፍሳሽ
  በገጠር የደመና ዳስ፣ በገደል ሸለቆ አዳራሽ
  ከቆቅ እና ከሚዳቋ፣ ከዥግራ ጠረን ስተሸሽ
  በወንዝ አፋፍ ሐረግ ዝላይ፣ መወርወር መንጠልጠል ጢሎሽ
  ከፍልፈል ጋር ሩጫ ስገጥም፣ ከቀበሮ ድብብቆሽ
  ከናዳ ጫፍ ሣር አጨዳ፣ ለግት ላሜ ትንሽ ግጦሽ
  ለጥጃዬ የሌት ግርዶሽ 
  ለጥማድ በሬዎች ራት፣ ለማታቸው ትንሽ ድርቆሽ
  ለግልገሌ ካውሬ ከለል
  እማሳው ሥር ጎጆ መትከል
  ለፀሐይ የሾላ ጠለል፣ ለዝናብ የገሳ ጠለል
  ውሎ የንብ ቀፎ ማሰስ፣ ያበባ እምቡጥ ሲፈነዳ
  የግጦሽ ሣር ሲለመልም፣ ሲሰማሩ ሰደድ ሜዳ
  አዝመራው ጣል ከንበል ሲል፣ ከብቱ ለሆራ ሲነዳ
  ፈረስ ግልቢያ ስሸመጥጥ፣ ከወፎች ዜማ ስቀዳ
  ልቤ በንፋስ ተንሳፎ፣ በዋሽንት ዋይታ ሲከዳ …..
  ያቺን ነው ኢትዮጵያ የምላት
  እመ ብርሃን እረሳሻት?
  ያቺን የልጅነት የምሥራች? የሕፃንነት ብሥራት
  የሣቅ የፍንደቃ ዘመን፣ የምኞት የተስፋ ብፅአት
  ያቺን የልጅነት እናት?
  አዛኚቱ እንዴት ብለሽ፣ ጥርሶችሽን ትነክሺባት?
  ሥሜን በሥምሽ ሰይሜ፣ ባገልግሎትሽ ስዋትት
  ከዜማ ቤት እቅኔ ቤት፣ ከድጓ ቤት እመጻሕፍት
  ካንቺ ተቆራኝታ ዕድሌ፣ ካንቺ ተቆራኝታ ነፍሴ
  ከቀፈፋ ደጀሰላም፣ ከቤተልሔም ቅዳሴ
  እኰ፣ ቀፎ ዳባ ለብሶ
  ቅኔ ዘርፎ ግስ ገሦ
  መቅደስ አጥኖ ማኅሌት ቆሞ
  በልብስ ተክህኖ አጊጦ፣ በብር አክሊል ተሸልሞ
  እመ ብርሃን ያንች ጽላት፣ ነፍስ ላይ በእሳት ታትሞ
  የመናኒው ያባ ተድላ፣ ረድ ሆኜ፣ አብሮኝ ታድሞ
  ሕይወቴ እምነትሽን ጸንሶ
  ሥጋ ፈቃዴ ተድሶ
  ለሕንፃሽ መዲና ቆሞ፣ ለክብርሽ ድባብ ምሰሶ
  ሥሜን በሥምሽ ሰይሜ፣ ሆነሺኝ የእምነቴ ፋኖስ
  ለዋዜማሽ ግሸን ማርያም፣ ለክብርሽ ደብረ ሊባኖስ
  ስሮጥ፣ በወንበሩ አኖርሺኝ፣ በአንበሳው በቅዱስ ማርቆስ
  ታዲያ ዛሬ ኢትዮጵያ ስትወድቅ፣ ከምትሰጪኝ የፍርሃት ጦስ
  ምነው በረኝነት እድሜ፣ ዓይኔን በጓጎጣት የሎስ
  የጋኔል ጥንብ አንሳ ከንፎ፣ ወርዶ በጨለማ በርኖስ
  ባክሽ እመ ብርሃን ይብቃሽ፣ ባክሽ ምስለ ፍቁር ወልዳ
  ጽናት ስጪኝ እንድካፈል፣ የእናቴን የኢትዮጵያን ፍዳ፣
  ከነከሳት መርዝ እንድቀምስ፣ ከነደደችበት እቶን
  የሷን ሞት እኔ እንድሞታት፣ ገላዋ ገላዬ እንዲሆን፡፡ …..
  አዎን፣ ብቻዬን ነኝ ፈራሁ
  እምፀናበት ልብ አጣሁ፡፡

  ምንጭ፤ “ታሪካዊ ተውኔቶች” ጸጋዬ ገብረ መድኅን
  አሳታሚ፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ፤ 2003ዓ.ም

 • loader Loading content ...

Load more...