loader
 • ካሣ ስለሚጠየቅበት ክስ (የ፲፱፻፶፪ ዓ.ም. የፍትሐ ብሔር ሕግ ፥ አንቀጽ ፲፫ ፥ ምዕራፍ ፩ ፥ ክፍል ፭)

  @በህግ አምላክ   3 months ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!
 • loader Loading content ...
 • @በህግ አምላክ   3 months ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!

  የ፲፱፻፶፪ ዓ.ም. የፍትሐ ብሔር ሕግ። አንቀጽ ፲፫። ከውል ውጭ ስለሚደርስ አላፊነትና ያላገባብ ስለ መበልጸግ። ምዕራፍ ፩። ከውል ውጭ ስለሚደርስ አላፊነት። ክፍል ፭። ካሣ ስለሚጠየቅበት ክስ።


  ቁጥር ፪ሺ፻፴፯። የማይደፈሩ ሕጋዊ መብቶች (፩) ነጋሢ።
  ጥፋትን ምክንያት በማድረግ በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ምንም የኀላፊነት ክስ አይቀርብም።

  ቁጥር ፪ሺ፻፴፰። (፪) ስለ ሚኒስትሮች፤ ስለ ፓርላማ አባሎችና ስለ ዳኞች።
  (ሀ) በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት አባሎች ላይ፤
  (ለ) በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት በፓርላማ አባሎች ላይ፤
  (ሐ) በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ዳኞች ላይ፤
  የሥራቸው ነክ በሆነው ተግባር የኀላፊነት ክስ ሊቀርብባቸው አይቻልም።

  ቁጥር ፪ሺ፻፴፱። ልዩነት።
  ከዚህ በላይ በተነገረው ቁጥር ደንብ የተከበሩት ሰዎች በሥራቸው ምክንያት ባደረጉት ተግባር፤ በወንጀል ተቀጥተዋል ብሎ ከሳሹ ጠቅሶባቸው እንደሆነ ይህ ደንብ አይጸናላቸውም።

  ቁጥር ፪ሺ፻፵። የአስተዳደር ሕግ ስለሚወስናቸው ተግባሮች።
  መንግሥት በአላፊነት በሚጠየቅበት ጊዜ ክስ በማን ላይ መቅረብ የሚገባው ለመሆኑና እንደዚሁም የትኛው መሥሪያ ቤት ወይም ክፍል በመጨረሻው ዐይነት አከፋፈል ወይም በእንዴት አኳኋን ዕዳውን መክፈል የሚገባው ለመሆኑ ያስተዳደር ደንቦች ይወስናሉ።

  ቁጥር ፪ሺ፻፵፩። አስረጅ ለማቅረብ ግዴታ ያለበት።
  የደረሰበትን ጉዳት ልክና እንዲሁም የአካባቢ ሁኔታዎች መሠረት በማድረግ ተከሳሹን ካሣ እንዲከፍለው ያለበትን ግዴታ ማስረዳት ያለበት ጉዳት የደረሰበት ሰው ነው።

  ቁጥር ፪ሺ፻፵፪። ጉዳት አድራጊውን ለይቶ ስለ ማወቅ።
  (፩) ከብዙ ሰዎች መካከል ጉዳቱን የፈጸመው ማን እንደሆነ በርግጥ ለማወቅ ባልተቻለ ጊዜ በርትዕ አስፈላጊ ሆኖ ሲታይ አድርጓል ለማለት የሚቻለውን ስብሰባና በዚሁ መካከል አጥፊው በርግጥ እንደሚገኝ የታወቀውን ዳኞች ለጉዳቱ እንዲክስ ሊፈርዱበት ይችላሉ።
  (፪) ይህን የመሰለ ነገር ባጋጠመ ጊዜ ዳኞቹ በፍትሐ ብሔር በኩል ለአድራጊው አላፊ የሆነው ሰው ለጉዳት እንዲክስ ለመፍረድ ይችላሉ።
  ቁጥር ፪ሺ፻፵፫። ክስ ስለሚቀርብበት ጊዜ።
  (፩) ተበዳዩ ክስ ማቅረብ የሚችለው ካሣ የሚጠይቅበት ጉዳት ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ሁለት ዓመት ድረስ ነው።
  (፪) ስለሆነም ጉዳቱ በወንጀል የሚያስቀጣ ሆኖ የይርጋ ዘመኑ ርዝመት የበለጠ እንደሆነ፤ የካሣው ጒዳይ ክስ የይርጋ ዘመን ልክ በዚሁ መሠረት ይሆናል።
  (፫) ተበዳዩ የራሱ የሆኑትን ነገሮች የሚጠይቅበትና ያለ አገባብ ስለ መበልጸግ በተነገሩት ድንጋጌዎች መሠረት የሚከራከርበት መብቱ የተጠበቀ ነው።

  ቁጥር ፪ሺ፻፵፬። ስለ ተበዳዩ ወራሾች።
  (፩) በተበዳዩ ላይ ለደረሰው የገንዘብ ጉዳት ወራሾች ካሣን ለመጠየቅ ይችላሉ። ስለሆነም በሕጉ ላይ ተቃራኒ ድንጋጌ ከሌለ በቀር፤
  (፪) የተበዳዩ ወራሾች በተበዳዩ ላይ ለደረሰው ለሕሊና ጉዳት ካሣ ለመጠየቅ የሚችሉት ተበዳዩ በሕይወቱ ሳለ ክስ ጀምሮ እንደሆነ ብቻ ነው።
  (፫) የጉዳቱ አላፊ የሆነ ሰው ወራሾች ልክ እንደ ኀላፊው ተቆጥረው ለደረሰው ጉዳት ካሣ እንዲከፍሉ ይገደዳሉ።

  ቁጥር ፪ሺ፻፵፭። ከተበዳዩ ላይ ገንዘብ የሚጠይቁ ሰዎች።
  (፩) ገንዘብ የሚጠይቁ ሰዎች ይህ ባለዕዳቸው ጉዳት ደርሶበት እንደሆነ ጉዳቱም ሰውነቱን ሙሉ አካሉን ወይም ክብሩን የሚነካ እንደሆነ በሱ ስም ሆነው ለደረሰበት ጉዳት ካሣ ሊጠይቁ አይችሉም።
  (፪) ባለገንዘቦቹ ካበደሩበት ቀን በኋላ በባለዕዳው ላይ የገንዘብ ጥቅምን ብቻ የሚነካ ጉዳት የደረሰበት እንደሆነ የተባሉት ባለገንዘቦች በዚህ ሕግ ስለ ውሎች በጠቅላላው በሚለው አንቀጽ የተወሰኑትን ሁኔታዎች በመከተል የባለዕዳውን የክስ መብት ሊሠሩበት ይችላሉ።

  ቁጥር ፪ሺ፻፵፮። የገንዘብ መብት የማይተላለፍ ስለ መሆኑ።
  (፩) ለተበዳዩ የሚከፈለው ካሣ መኖሩና፤ ልኩም በፍርድ እስኪታወቅና እስኪወሰን ድረስ ተበዳዩ ለጉዳቱ አላፊ በሚሆነው ሰው ላይ ያለውን የገንዘብ መጠየቅ መብት ሊያስተላልፍ አይችልም።
  (፪) በፍርድ ከታወቀለትና ልኩም ከተወሰነለት በኋላ በዚህ ሕግ ስለ ውሎች በጠቅላላው በሚለው አንቀጽ መሠረት ሊያስተላልፍ ይችላል።

  ቁጥር ፪ሺ፻፵፯። አላፊ ስለ መሆን የሚደረግ የውል ስምምነት።
  (፩) አንድ ሰው ራሱ የሠራው ጥፋት የሚያስከትለውን አላፊነት ለማስወረድ ለማስወገድ መዋዋል አይፈቀድለትም።
  (፪) ሌላው ለሚሠራው ጥፋት በፍትሐ ብሔር በኩል በአላፊነት ሊጠየቅ የሚገባው ሰው ለሚሠራው ጥፋት አላፊ እንዳይሆን ለመዋዋል ይችላል።
  (፫) በዚህ አንቀጽ መሠረት ጥፋትም ባይኖር በሚደርሰው አደጋ ሁሉ ካሣ መክፈል የሚገባም ሆኖ ቢገኝ ጥፋት ካልተደረገ በቀር ካሣ አይከፈልም የሚል ስምምነት ለመዋዋል ይቻላል።

  ቁጥር ፪ሺ፻፵፰። ግልግል።
  አንድ አደጋ ከተደረገ በኋላ ሁለቱ ወገኖች ለዚሁ አደጋ መሻሻያ ካሣ የማይከፈልበት መሆኑን ሊስማሙበት ወይም ይህ አደጋ በምን ዐይነት እንደሚካሥ በስምምነት ሊገላገሉ ይችላሉ።

  ቁጥር ፪ሺ፻፵፱። የወንጀል ፍርድ ቤት በፍትሐ ብሔር ስላለው ሥልጣን።
  በፍትሐ ብሔር በኩል ጥፋት ተደርጓል ብሎ ለመወሰን በወንጀል ፍርድ ተከሳሹ ነፃ መለቀቁ ወይም በወንጀል አያስከስሰውም ተብሎ መበየኑ፤ ዳኞቹን አያግዳቸውም።

  ቁጥር ፪ሺ፻፶። የኪሣራው መገመቻ ጊዜ።
  (፩) ዳኞች በተበዳዩ ላይ የደረሰበትን ጉዳት ለማመዛዘን የፍርድ ውሳኔ የሚሰጡበትን ቀን መሠረት አድርገው መያዝ አለባቸው።
  (፪) ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ፍርድ በሚወስንበት ጊዜ ለመገመት የማይቻል መስሎ የታያቸው እንደሆነ ለጊዜው ብቻ የሚጸና ትእዛዝ ፍርድ ሰጥተው ይህ ፍርድ እንደገና እንዲታይ ጥያቄ ማቅረብ ይችላል የሚል ፈቃድ መስጠት ይችላሉ።
  (፫) ይህ ፍርድ እንደገና ይታይልን የማለት ጥያቄ ለጊዜው የተሰጠው ትእዛዝ ፍርድ ከተወሰነበት ቀን ጀምሮ እስከ ሁለት ዓመት ከዘገየ ለመቅረብ አይችልም።

  ቁጥር ፪ሺ፻፶፩። በፍርድ ያለቀ ነገር መጽናት።
  (፩) ከዚህ በላይ በተጻፈው ቁጥር የተመለከተው ነገር ከሌለ በዳኞች የተደረገ የጉዳት ግምት የመጨረሻ ነው።
  (፪) ጉዳት የደረሰበት ሰው የተባለው ጉዳት በአመጣጡ ምክንያት አስቀድሞ ካሣ ከጠየቀበት ጉዳት ጋራ ግንኙነት የሌለው ካልሆነ በቀር ለዚሁ ለደረሰበት ጉዳት በአዲስ ክስ ካሣ ለመጠየቅ አይችልም።

  ቁጥር ፪ሺ፻፶፪። የይግባኝ አለመኖር።
  ስለ ኪሣራ ጥቅም አከፋፈል በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞች የተወሰነ ፍርድ ለበላይ ፍርድ ቤት ለይግባኝ ለመቅረብ አይችልም።

  ቁጥር ፪ሺ፻፶፫። የተጠበቁ ሁኔታዎች።
  ቢሆንም ከዚህ በላይ ባለው ቁጥር የተመለከተው ደንብ ልዩ አስተያየት የሚሰጠው፤
  (ሀ) ዳኞች ሊገምቱት የሚገባቸውን የነገሩን አጋጣሚ ሁኔታ ያላገባብ በመያዝ ውሳኔ ሰጥተው እንደሆነ ወይም ሊገምቱ የሚገባቸውን ትክክለኛውን መንገድ ትተው ያላገባብ የሆነውን ያገማመት መንገድ ይዘው የተገኙ እንደሆነ፤
  (ለ) በዳኞች የተወሰነው የኪሣራ ገንዘብ ልክ በግልጽ ከአእምሮ ግምት ውጭ የሆነና የተወሰነውም በማድላት ወይም በዝንባሌ መሆኑ እርግጥ ሆኖ የተገኘ እንደሆነ፤
  (ሐ) በዳኞቹ የተወሰነው የጉዳቱ ካሣ በሒሳብ ማሳሳት ሆኖ የተገኘ እንደሆነ ነው።

  ቁጥር ፪ሺ፻፶፬። በየጊዜው ስለሚከፈል ገንዘብ።
  (፩) የዚህ ዐይነት የኪሣራ ሒሳብ አከፋፈል እንደ ጊዜው አጋጣሚ ሁኔታ ተስማሚ መሆኑን የሚያሳስብ በቂ ምክንያት በተገኘ ጊዜ ዳኞች የካሣው ሒሳብ በየጊዜው እንዲከፈል ለመወሰን ይችላሉ።
  (፪) ይህ ሲሆን ባለዕዳው ኪሣራውን በየጊዜው ሊከፍል የሚችል ስለ መሆኑ የሚያረጋግጥ በቂ ዋስትና መስጠት አለበት።

  ቁጥር ፪ሺ፻፶፭። ያንድነት ኀላፊነት።
  (፩) ብዙዎች ሰዎች አንድ በሆነው ጒዳይ ለደረሰው ጉዳት ካሣን እንዲከፍሉ የተገደዱ እንዳሆነ፤ በአንድነት እያንዳንዳቸው ኀላፊ ይሆናሉ።
  (፪) ለበደሉ ተግባር አነሣሽ በሆነውና በዋናው አድራጊ፤ በበደሉ ተግባር ተባባሪዎች፤ መካከል ልዩነት አይደረግም።
  (፫) እንዲሁም የግዴታው መነሻ ለየአንዳንዶቹ ከውል ውስጥ ለየአንዳንዳቸው ከውል ውጭ የሆነ አላፊነት ነው ተብሎ ልዩነት ሳይደረግ አንድ ለሆነ ጉዳት እንዲክሡ ግዴታ ባለባቸው ሰዎች መካከል ያለው አላፊነት የአንድነት አላፊነት ነው።

  ቁጥር ፪ሺ፻፶፮። የማይከፋፈል ጥፋት። (፩) መሠረቱ።
  አላፊዎች ከሆኑ ሰዎች ውስጥ አንዱ ብቻ ጥፋት የሠራ እንደሆነ፤ በመጨረሻው የተወሰነውን ዕዳ እርሱ ራሱ ብቻ መቻል አለበት።

  ቁጥር ፪ሺ፻፶፯። (፪) በርትዕ ልዩነት ስለ ማድረግ።
  (፩) የመንግሥት ሠራተኛ፤ የሰውነት መብት የተሰጠው የአንድ ማኅበር እንደራሴ ወይም ወኪል ወይም ደመወዘኛ ጥፋቱን የፈጸመው ሥራውን በሚሠራበት ጊዜ እንደሆነ፤ በመጨረሻው ጊዜ ዕዳውን በሙሉ ወይም በከፊል መንግሥት ወይም ማኅበር ወይም አሠሪው ይከፍላሉ ብለው ዳኞች ለመወሰን ይችላሉ።
  (፪) ዳኞቹ ውሳኔያቸውን በሚሰጡበት ጊዜ፤ የተሠራውን ጥፋት ከባድነትና አድራጊው ጥፋቱን ሲሠራ የተሰጡትን ሥራዎች አብልጦ ለመፈጸም ሲል የነበረውን ፈቃድ መገመት አለባቸው።

  ቁጥር ፪ሺ፻፶፰። ማመዛዘንን የሚያስፈልጉ ነገሮች።
  (፩) ዳኞች ጥፋት አድራጊው ጥፋት በአደረገበት ጊዜ ፈቃዱ ሥራውን በመልካም ለማከናወን መሆኑንና ያደረገውንም ጥፋት ከባድነት ያመዛዝናሉ።
  (፪) ዳኞቹ ኀላፊ ናቸው የተባሉት ሰዎች ያላቸውን የየአንዳንዳቸውን ሀብት መሠረት አድርጎ መያዝ የለባቸውም።

  ቁጥር ፪ሺ፻፶፱። የዚህ ልዩነት ወሰን።
  በዳኞቹ በኩል አንዳች የኀላፊነት ክፍያ የማይፈቀደው፤
  (ሀ) ኀላፊነቱን ያመጣው ሥራ ታስቦ ለመጉዳት የተደረገ እንደሆነ፤
  (ለ) ወይም ይህ ተግባር ወንጀል ሆኖ አድራጊው ቅጣት ተፈርዶበት እንደሆነ ነው።

  ቁጥር ፪ሺ፻፷። የሚከፋፈል ጥፋት።
  (፩) ብዙዎች ሰወች አንድ በሆነ ጒዳይ የጥፋት ተግባርን በመፈጸም ላይ የተባበሩ እንደሆነ፤ ዳኞች በመጨረሻ በየአንዳንዳቸው መካከል ሊከፈል የሚገባውን ዕዳ በርትዕ ይወስኑባቸዋል።
  (፪) ዳኞች በሚሰጡት ውሳኔ የነበሩትን ምክንያቶች ሁሉ በተለይም የየአንዳንዱን በደለኛ ጥፋት ያደረሰውን የጉዳት ተግባር መጠንና የጥፋቱንም ከባድነት መገመት አለባቸው።

  ቁጥር ፪ሺ፻፷፩። ስለ መዳረግ።
  (፩) አንድ ሰው ከሚወሰነው ዕዳ የክፍያውን ድርሻውን መክፈል የሚገባው ሲሆን፤ ዕዳውን በሙሉ የከፈለ እንደሆነ፤ ከእርሱ ጋራ ዕዳውን እንዲከፍሉ ግዴታ ባለባቸው ሰዎች ላይ የመጠየቅ መብት አለው።
  (፪) ጥያቄውን ለማቅረብ የተበደለው ሰው መብቶች እንደ ገባ የቆጠራል።

  ምንጭ:
  የኢትዮጵያ የ፲፱፻፶፪ ዓ.ም. የፍትሐ ብሔር ሕግ (፲፱፻፶፪)
 • loader Loading content ...

Load more...