loader
 • የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ የተሰጠው ገንዘብ ጠያቂ ቀደምትነት የብልጫ መብት (የ፲፱፻፶፪ ዓ.ም. የፍትሐ ብሔር ሕግ ፥ አንቀጽ ፲፰ ፥ ምዕራፍ ፬ ፥ ክፍል ፪ ፥ንኡስ ክፍል ፩)

  @በህግ አምላክ   3 months ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!
 • loader Loading content ...
 • @በህግ አምላክ   3 months ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!

  የ፲፱፻፶፪ ዓ.ም. የፍትሐ ብሔር ሕግ። አንቀጽ ፲፰። የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን ስለ ሚመለከቱ ውሎች። ምዕራፍ ፬። ስለማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣና ስለ ወለድ አግድ። ክፍል ፪። የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ ውጤቶች።ንኡስ ክፍል ፩። የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ የተሰጠው ገንዘብ ጠያቂ ቀደምትነት የብልጫ መብት።


  (ሀ) ይህ መብት የሚመለከታቸው ንብረቶች። ቁጥር ፫ሺ፷፬። ከንብረቱ ጋራ አንድ የሆነና ተጨማሪ። (፩) መሠረቱ።
  (፩) የማይንቀሳቀስ ንብረት የመያዣ መብት በማይንቀሳቀሰው ንብረት ላይና ከንብረቱ ጋራ አንድነት ባላቸው ክፍሎች እንዲሁም ተጨማሪ ክፍሎችንም ጭምር የሚጠቀልል ነው።
  (፪) በመያዣው ውል ላይ እንደ ንብረቱ ተጨማሪ ሆነው በግልጽ የተመለከቱት ዕቃዎች በዚሁ ዐይነት ይቆጠራሉ።
  (፫) ተቃራኒ ማስረጃ የማቅረብ መብት የተጠበቀ ነው።

  ቁጥር ፫ሺ፷፭። የሦስተኛ ወገኖች መብት።
  (፩) የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ ያለው ገንዘብ ጠያቂ የመያዣው መብት ከሚመለከተው ከማይንቀሳቀሰው ንብረት ላይ በተለዩትና ባለሀብትነታቸውም ለሦስተኛ ወገኖች በተዛወሩት ክፍሎች ወይም ተጨማሪ ዕቃዎች ላይ የባለመያዣነት መብቱን ሊሠራበት አይችልም።
  (፪) እንደዚህ ያለ ሁኔታ በአጋጠመ ጊዜ መያዣ የሆነው የማይንቀሳቀስ ንብረት ዋጋ ቢቀነስ ቢጠፋ ወይም ቢበላሽ በዚህ ሕግ አንቀጾች በታወቁለት መብቶቹ ብቻ ሊገለገልባቸው ይችላል።

  ቁጥር ፫ሺ፷፮። የማይንቀሳቀሰውን ንብረት አዲስ ሥራ ስለ መሥራትና ስለ ማሻሻል። (፩) መሠረቱ።
  የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዝ መብት የመያዣው መብት በሚመለከተው የማይንቀሳቀስ ንብረትና እንዲሁም በዚሁ ንብረት ላይ የሚሠሩትን አዳዲስ ሥራዎች፤ ተክሎችና ሰብሎች የሚጠቀልል ነው።

  ቁጥር ፫ሺ፷፯። (፪) የሥራ ተቋራጮችና የዕቃ አቅራቢዎች ልዩ መብት።
  (፩) ስለሆነም ከዚህ በላይ ባለው ቁጥር የተጠቀሰውን በማደስ የማሻሻል ሥራና የሕንጸሥራ የፈጸሙ ሥራ ተቋራጮችና ለሥራው አስፈላጊ የሆነውን የማደሻውን ዕቃ የሸጡ አትክልት ዘር ወይም የሰብል ፍሬ ያቀረቡ ዕቃ አቅራቢዎች፤ ለፈጸሙት ሥራና ላቀረቡት ዕቃ ስለሚከፈላቸው ገንዘብ ጒዳይ የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ መብት ካላቸው ገንዘብ ጠያቂዎቹ (ብልጫ) ቅድሚያ ይሰጣቸዋል።
  (፪) በዚህም በክፍያ ክርክር የተነሣ እንደሆነ ዳኞች የድርሻውን ልክ ይወስናሉ።
  (፫) እንዲሁም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በልዩ ልዩዎች ሥራ ተቋራጮችና በዕቃ አቅራቢዎች መካከል የሚደረገውን የክፍያ ጒዳይ ይወስናሉ።

  ቁጥር ፫ሺ፷፰። የቤትና የእርሻ መሬት ኪራይ።
  (፩) በኪራይ የተሰጠውን የማይንቀሳቀስ ንብረት የሚመለከተው የመያዣ መብት ንብረቱ በፍርድ ከተያዘበት ቀን አንሥቶ የሚታሰበውን የቤትና የርሻ ኪራይን ይጠቀልላል።
  (፪) ቤት ተከራዮችና የእርሻ መሬት ተከራዮች መያዣ የተሰጠበት የማይንቀሳቀስ ንብረት በፍርድ መያዙ ማስታወቂያ ከተሰጣቸው በኋላ የቤቱን ወይም የመሬቱን ኪራይ ዋጋ ለማይንቀሳቀሰው ንብረት ባለሀብት በሚጸና አኳኋን ሊከፍሉ አይችሉም።

  ቁጥር ፫ሺ፷፱። ለማይንቀሳቀስ ንብረት የተመደበ ኪሣራ። (፩) መሠረቱ።
  (፩) የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ መብት፤ ንብረቱ በጠፋ ወይም በተበላሸ ጊዜ ለዚሁ ሊከፈል የሚገባውን አሹራንስ ወይም በአላፊነት የሚከፈል የኪሣራን ሒሳብ የሚጠቀልል ነው።
  (፪) እንዲሁም የማይንቀሳቀሰው ንብረት መያዣ ንብረቱ በሚወሰድበት ጊዜ ለባለዕዳው (ለባለሀብቱ) የሚከፈለውን ግምት የሚጠቀልል ነው።

  ቁጥር ፫ሺ፸። (፪) ስለ አከፋፈሉ የገንዘብ ጠያቂው ፈቃድ።
  (፩) በማይንቀሳቀሰው ንብረት ላይ የመያዣ መብታቸውን ያስመዘገቡት ገንዘብ ጠያቂዎች ሁሉ ካልፈቀዱ በቀር፤ በአሹራንስ በኀላፊነት ወይም ንብረት በመልቀቅ ምክንያት መያዣውን ለሰጠው ባለዕዳ የሚከፈሉት ኪሣራዎች ሊሰጡት አይቻልም።
  (፪) ይህን የመሰለ ኪሣራ ሊከፈለው የሚገባው የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ የሰጠ ባለዕዳ ለተመዘገቡት ገንዘብ ጠያቂዎች የኪሣራውን ልክና ምክንያት እንዲሁም የሚከፍለውን ሰው ስምና አድራሻ ያስታውቃል።
  (፫) ለዚህ አከፋፈል ይህ ማስታወቂያ ከተደረገበት ቀን አንሥቶ በሠላሳ ቀን ጊዜ ውስጥ የማይንቀሳቀስ ንብረት የመያዣ ባለመብት የሆኑ ገንዘብ ጠያቂዎች መቃወማቸውን ያልገለጹ እንደሆነ ኪሣራው ለባለዕዳዎች እንዲከፈል እንደተስማሙ ያህል ይገመታሉ።

  ቁጥር ፫ሺ፸፩። የማይንቀሳቀስ ንብረትን መያዣ የሰጠ ባለዕዳ መብት።
  (፩) የማይንቀሳቀስ ንብረትን የመያዣ መብት ለሰጠ ባለዕዳ የሚከፈለው ኪሣራ ከአምስት መቶ የኢትዮጵያ ብር ያልበለጠ እንደሆነ ለሱው እንዲከፈለው ለማስገደድ ይችላል።
  (፪) የማይንቀሳቀስ ንብረት የመያዣ መብት የሰጠ ባለዕዳ በኪሣራው ገንዘብ የማይንቀሳቀሰውን ንብረት እንደገና ለመሥራት ወይም ለማደስ የሚያውለው ለመሆኑ ግዴታ የገባ እንደሆነና ተስፋ የሰጠበትንም ነገር ለመፈጸም ማረጋገጫ እንዲሆን በቂ ሆነው የሚገመቱ ዋስትናዎች ወይም ሌሎች መያዣዎች ያቀረበ እንደሆነ ለኪሣራ የሚከፈለው ገንዘብ እንዲሰጠው ለማስገደድ ይችላል።
  (፫) በማናቸውም አኳኋን ቢሆንም የማይንቀሳቀሰውን ንብረት የመያዣ መብት የሰጠ ባለዕዳ ለሱ የሚከፈለውን ኪሣራ ዳኞች በመረጡት በትእዛዝ ባለአደራ ተይዞ እንዲቀመጥ ለማስገደድ ይችላል።

  ቁጥር ፫ሺ፸፪። በስመ ርስቱ ላይ የሚደረግ የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ ስለ መስጠት።
  በስመ ርስት ላይ የሚደግ የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ አላባው ባለቀ ጊዜ በሙሉ በርስቱ ላይ የሚጠቀለል ይሆናል።

  ቁጥር ፫ሺ፸፫። የማይንቀሳቀስ ንብረትን ዋጋ ስለ ማጓድል። (፩) የባለዕዳው አድራጎት።

  (፩) ባለዕዳው በራሱ አድራጎት ወይም ቸልተኛነት የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ የተሰጠበትን ንብረት ዋጋ እንዲቀነስ ወይም እንዲጎዳ ያደገ እንደሆነ ገንዘብ ጠያቂው አዲስ ዋስትና እንዲሰጠው ለማስገደድ ይችላል፡
  (፪) ለገንዘቡ ተገቢ ሆኖ በተወሰነው ጊዜ ውስጥ ዕዳ ከፋዩ እነዚህን መያዣዎች ያላቀረበ እንደሆነ፤ ለዕዳ መክፈያው ከተወሰነው ቀን አስቀድሞ ባለገንዘቡ ለዋስትናው በቂ የሆነ ገንዘብ መልሶ እንዲሰጠው ለመጠየቅ መብት ይኖረዋል።

  ቁጥር ፫ሺ፸፬። ንብረቱን የሚገዛ የሦስተኛ ሰው አድራጎት።
  ከባለዕዳው ላይ ንብረቱን በገዛ በሦስተኛ ሰው አድራጎት ወይም ቸልተኛነት የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ የተሰጠበት ንብረት ዋጋ የተቀነሰ ወይም የተጎዳ እንደሆነ የማይንቀሳቀሰው ንብረት መያዣ የተሰጠው ገንዘብ ጠያቂ በባለዕዳው ላይ እንዲሠራባቸው ባለፈው ቁጥር የተመለከቱት መብቶች ይኖሩታል።

  ቁጥር ፫ሺ፸፭። ሌሎች ምክንያቶች።
  ሌላ ምክንያት ያለበት የዋጋ መቀነስ ወይም ዋጋ ያስቀንሳል ተብሎ የሚያስፈራ ጒዳይ ከባለዕዳው አዲስ ዋስትናዎችን ለመጠየቅ ወይም መያዣ የተሰጠበትን ዕዳ በከፊልም ሆነ እንዲከፈለው ለመጠየቅ ለባለ ገንዘቡ መብት አይሰጠውም።

  (ለ) ቀደምትነት ያላቸው የገንዘብ መጠየቂያ መብቶች። ቁጥር ፫ሺ፸፮። የተመዘገበ የገንዘብ መጠየቂያ መብት ዋና ገንዘብ (ካፒታል)።
  በማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ መዝገብ ውስጥ የተመዘገበውን ገንዘቡን ከሌሎች ገንዘብ ጠያቂዎች በፊት በቀደምትነት እንዲከፈለው የማይንቀሳቀሰው ንብረት መያዣ ለገንዘብ ጠያቂው መድን ነው።

  ቁጥር ፫ሺ፸፯። የዋናው ገንዘብ ወለድ።
  (፩) እንዲሁም በማይንቀሳቀሰው ንብረት መያዣ መዝገብ ውስጥ በተመዘገበው የወለድ መጠን የዋናውን ገንዘብ ወለድ ከሌሎች ገንዘብ ጠያቂዎች አስቀድሞ ለመክፈል የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ ለባለገንዘቡ መድን ነው።
  (፪) ስለሆነም የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ የተሰጠው ገንዘብ ጠያቂ በዚህ መብተ መሠረት ከሁለት ዓመት ለበለጠ ጊዜ ወለዱ በቀደምትነት እንዲከለው ለመጠየቅ አይችልም።
  (፫) የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ መብት በሚመዘገብበት ጊዜ ወለዱ በቀደምትነት የሚከፈልበት ከሁለት ዓመት ለበለጠ ጊዜ ይሆናል ተብሎ ሊጻፍ አይቻልም።

  ቁጥር ፫ሺ፸፰። አስፈላጊ ወጪዎችና ለአሹራንስ የሚከፈል ዋጋ።
  እንዲሁም ባለዕዳው ሊከፍላቸው የሚገባ ሁኖ ሳለ፤ ገንዘብ ጠያቂው ለማይንቀሳቀሰው ንብረት ጥበቃ ያደረጋቸውን አስፈላጊ ወጪዎችና ለንብረቱ አሹራንስ የከፈላቸውን ዋጋዎች ከሌሎቹ ገንዘብ ጠያቂዎች በፊት በቀደምትነት ለመከፈል ያው የማይንቀሳቀሰው ንብረት መያዣ መድኑ ነው።

  ቁጥር ፫ሺ፸፱። በፍርድ ለማሲያዝ የሚደረጉ የተለመዱ ወጪዎች።
  እንዲሁም ገንዘብ ጠያቂው የማይንቀሳቀሰውን ንብረት መያዣ በፍርድ ለማሲያዝ ያደረጋቸውን ወጪዎች ከሌሎች ባለገንዘናበች በፊት በቀደምትነት ለመከፈል የማይንቀሳቀሰው ንብረት መድኑ ነው።

  ቁጥር ፫ሺ፹። ሕጋዊ ወለድ።
  (፩) ከዚህ በፊት ባሉት አራት ቁጥሮች የተመለከቱት ገንዘቦች፤ የመያዣ መብት የተሰጠበት የማይንቀሳቀስ ንብረት በፍርድ ከተያዘበት ቀን አንሥቶ ሕጋዊ የሆነ ወለድን ይሰጣሉ።
  (፪) በመያዣ የተሰጠ የማይንቀሳቀስ ንብረት በፍርድ ተይዞ ሐራጅ እስከተፈጸመበት ቀን ድረስ ባለው ጊዜ ለሚታሰበው የወለድ ገንዘብ በመያዣ የተሰጠው የማይንቀሳቀስ ንብረት መድኑ ነው።
  (ሐ) የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ መብት ያስመዘገቡ ብዙዎች ገንዘብ ጠያቂዎች።

  ቁጥር ፫ሺ፹፩። መሠረቱ።
  (፩) ባንድ በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ ብዙ ገንዘብ ጠያቂዎች የመያዣ መብት አስመዝግበው እንደሆነ የቀደምትነት መብታቸውን የሚሠሩበት ተራ የሚወሰነው መብታቸውን ያስመዘገቡበትን ቀን በመከተል ነው።
  (፪) የገንዘብ መጠየቂያ መብታቸው እርግጠኛ የሆነበት ወይም እንዲከፈል ለመጠየቅ የሚቻልበት ቀን በግምት ውስጥ አይገባም።

  ቁጥር ፫ሺ፹፪። ባንድ ቀን የተመዘገቡ ገንዘብ ጠያቂዎች።
  ባንድ ቀን ውስጥ የተመዘገቡ ገንዘብ ጠያቂዎች በየመጠናቸው ይከፋፈላሉ።

  ቁጥር ፫ሺ፹፫። ስለ መተካት።
  (፩) ማናቸውም የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ መብት ያለው ገንዘብ ጠያቂ ከርሱ በፊት ቀደምትነት ያለውን ገንዘብ ጠያቂ አስፈቅዶ የቀደምትነቱን ተራ ለመውሰድ ይችላል። በተራ ተከታይ የሆነው ገንዘብ ጠያቂ ባደረገው ጥያቄ መሠረት የመያዣ መብት የተሰጠበትን የማይንቀሳቀሰውን ንብረት በፍርድ እንዲያዝ አድርጎ እንደሆነ ግን ከርሱ በፊት ተራ የነበረውን ገንዘብ ጠያቂ ማስፈቀድ አስፈላጊው አይደለም።
  (፪) እንዲህም በሆነ ጊዜ በቀደምትነት ተራ የሚተካው ገንዘብ ጠያቂ ከርሱ በፊት የነበረው የገንዘብ ጠያቂው የቀደምትነት ተራ ይኖረዋል።

  ምንጭ:
  የኢትዮጵያ የ፲፱፻፶፪ ዓ.ም. የፍትሐ ብሔር ሕግ (፲፱፻፶፪)
 • loader Loading content ...

Load more...