loader
 • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የፓትርያርክ ስልጣኗን ለማግኘት ከግብፅ ቤተክርስትያን ጋር ያረገቸው ተጋድሎ ምን ይመስል ነበር?የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክስ ማን ናቸው?

  @ሊ/ትጉሃን እምሩ   3 years ago
  Sewasewer
 • loader Loading content ...
 • @ሊ/ትጉሃን እምሩ   3 years ago
  Sewasewer
  በፍትሐ ነግስቱ ዓንቀጽ 4፣ ቁጥር 50 መሰረት የግብፅ አለክሳንድርያ ቤተ ከርስትያን ለ1600 አመታት ያህል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያንን ሹማ በመትልከው ሊቀ ጳጳስ አማካኝነት ስታስተዳድር ቆይታለች። ይህም ዓንቀጽ እንዲህ ይላል:
  'የኢትጵያ ሰዎች ከዐዋቂዎቻቸው ወገን በራሳቸው ፈቃድ ሊቀ ጳጳሳትን ለራሳቸው አይሹሙ። ጳጳሳቸው ከስክንድርያው በዓለ መንደር ስልጣን በታች ነውና። ከሊቀ ጳጳሳት በታች የሆነውን ሊቀ ጳጳስ ከእርሱ ወገን ሊሾምላቸው የሚገባውም እርሱ ነው' 
  ኢትዮጵያዊያን አባቶች ይህ አሰራር ቀርቶ ቤተክርስትያኗ ከራሷ አብራክ በተከፈሉ እና በምእመናኗ ቇንቇ በሚናገሩ ኢትዮጵያውያን አባቶች ትመራ ዘንድ ከፍተኛ ትግል ሲያደርጉ ቆይተዋል። የታሪክ መዛግብት እንደሚያመለክቱት 'ቁጥራቸው ብዙ ለሆነው የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ምእመናን በራሳቸው ቇንቇ ተዟዙሮ የሚያስተምራቸው ኢትዮጵያውያን እፒስ ቆጶሳት ያስፈልጋቸዋል' ብሎ ለመጀመሪያ ጊዜ ድምፁን ያሰማው የኢትዮጵያ ንጉስ ቅዱስ ሐርቤ (1060 እስከ 1077) ነበር። በጊዜውም ለነበረው ግብፃዊ የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ (አባ ሚካኤል) ጥያቄውን ቢያቀርብም፣ ሊቀጳጳሱ ግብፅ ካሉት ፓትርያርክ ጋር መክሮ ጥያቄውን ውድቅ አድርገውበታል። ከንጉስ ሐርቤም ቀጥሎ ያሉት ነገስታት ምንም እንኯን አዎንታዊ መልስ ባያገኙም ጥያቄያቸውን በግብፅ ለነገሱ የእስላም ነገስታት አቅርበዋል።

  ወደ 19ኛው መካከለኛ ክፍለ ዘመን ስንመጣም አፄ ሚንልክ ከነገሱ በሇላ ይሄው የኢትዮጵያውያኑ ጥያቄ በአማርኛ ቇንቇ እየተዘጋጁ ይታተሙ የነበሩትን 'አእምሮ' ና 'ብርሃንና ሰላም' የተሰኙ ጋዜጦችን ሽፋን እያገኘ፣ ሊቃውንቱም በህትመቶች ሀሳባቸውን እየገለፁ ሄዱ። በዚህም ምክንያት ነገሩ እየጠነከረ መጣ። 

  በልዑል አልጋ ወራሽነት መዓረግ ባለ ሙሉ ስልጣን እንደራሴ የነበሩት ራስ ተፈሪ መኮንን (በሇላ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ) ከጊዜ ወደ ጊዜ የነገሩን ጥንካሬ ማግኘት በመገንዘብ አጀንዳው የቤተመንግስቱ እንዲሆን አደረጉ። ከዚህም በሇላ ከግብፅ ቤተክርስትያን ፓትርያርክ ጋር ባደረጉት ብዙ የቴለግራም ልውውጥ በሇላ 'ብዙ ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት ይሾሙልን' ብለው ያቀርቡት ጥያቄ የሚከተለውን የቴለግራም መልስ አግኝቷል:
    'ኢትዮጵያ መምህራን አምስት ሰዎች ተመርጠው ጳጳሳት ሆነው አምስት የኢትዮጵያ እጲስ ቆጶሳት ሹመት እንዲሾሙ ፈቅደናል፤ አምስት መነኮሳት እንዲልኩልን እንለምናለን '
   በዚህም ፈቃድ መሰረት አምስት አባቶች ማለትም ብፁዕ እጨጌ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ መምህር ደስታ፣ መምህር ኃይለ ማርያም፣ መምህር ወልደ ኪዳንና መምህር ኃይለ ሚካኤል ተመርጠው፣  ነገር ግን ብፁእ እጨጌ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በህመም ምክንያት ቀርተው፤ አራቱ አባት አቡነ ጴጥሮስ፣ አቡነ አብረሃም፣ አቡነ ይስሐቅና አቡነ ሚካኤል ተብለው በ 1921 ዓም ግብፅ ላይ ተሾሙ። እንግዲህ አርበኛው እየተባሉ የሚጠሩትና በኢጣልያን መንግስት የተገደሉት አቡነ ጴጥሮስ አንዱ ነበሩ ማለት ነው።

  እንዲህ እያለ በውቅቱ የኢጣልያ ወረራ ይመጣና በወቅቱ የኢትጶጵያ ሊቀ ጳጳሳት የነበሩት ግብፃዊው አቡነ ቄርሎስ በጦርነቱ ምክንያት ሹመቱን በተጠባባቂ ሊቀ ጳጳስነት ለኢትዮጵያዊው አባት ለአቡነ አብረሃም ሰተው ወደ ግብፅ ይገባሉ።  ይህ በእንዲህ እያለ የኢጣልያ መንግስት በቤተክርስትያናችን ላይ የፈፀውን ግፍ ለማስረሳት በዚህም እሷን መሳሪያ አድርጎ በየቦታው የእግር እሳት የሆኑበትን አርበኞችን ለማስታገስ ሲል በ1930 ዓም የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን የራሷን ሊቀ ጳጳሳትና እጲሥ ቆጶሳት መሾም ትችላለች በማለት ዐወጀ። በዚህም ምክንያት ከተለያዩ ክፍለ ሃገራት የተውጣጡ አባቶች የተሳተፉበት ጉባኤ ተደርጎ ውይይት ተደርጎ ቀደም ሲል ወደ ግብፅ ሂደው የተሾሙትን አቡነ አብርሃምን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ሊቀ ጳጳሳት እንዲሆኑ እና ሊሎች ጳጳሳት እና ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ የሚል ታሪካዊ ውሳኔ አሳልፏል።

  ኢትዮጵያውያን ችግር ባጋጠማቸው ጊዜ በአቡነ ቄርሎስ አማካኝነት ሀገሪቷን የሸሸችው የግብፅ ቤተክርስትያንም ይህንን ሹመት በሰማች ጊዜ ድርጊቱንም ሆነ የድርጊቱን አስፈጻሚ አቡነ አብርሃምን አወገዘች። ከውግዘትም ጋር ህዝቡ ከእሳቸውም ሆነ እሳቸው ከሾሟቸው አባቶች መስቀል እንዳይሳለም ጥሪ አቀረበች። ነገር ግን ኢትዮያውያኑ አባቶች እንዲሁም ምእመኑ ለውግዘቱ ቦታ ሣይሠጡ አገልግሎታቸውን ቀጠሉ። ከዓመት በሇላ ሐምሌ 14 ቀን 1931 ዓም ሽምግልና ተጭጫኗቸው የነበሩት ብፁዕ አቡነ አብርሃም ዐረፉ። በመሁኑም በእርሳቸው ቦታ የሚተካውን ሊቀ ጳጳስ ለመምረጥ ከየክፍሉ የተውጣጡ ሊቃውንት ቤተ ክርስትያን መስከረም  ቀን 1932 ዓ ም  እንደ ገና  ጉባ ዔ  አድርገው  አቡነ  ዮሐንሥን  መንበረ  ሊቀ  ጵጵስናውን  እንዲረከቡ ፣  እርሳቸውም  ሊሎ ች  ጳጳሳትን  እንዲሾሙ  ተመረጡ

  እግዚአብሔር በአምስቱ የመከራ ዘመናት በየቦታው  የፈሰሰውን የንጹሐን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ደም  ጩኸት፤ እንዲሁም በየዋሻው ዘግተው የሚጸልዩትን አባቶችና እናቶ ች ጸሎት ሰምቶ በ1933 ዓም ሀገሪቷ ከወራሪው ኃይል ነጻ  ወጣች። ንጉሡም ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ። በዚህ ጊዜ የሁለቱን ወዳጅ  ሀገሮች (የግብፅንንና የኢትዮጵያን) ፓለቲካዊ ግንኙነት ለመጠ በቅ በሚል በወቅቱ  የተሾሙት አባቶች በየሀገረ  ስብከታቸው ያለ ምንም ሥራ እንዲቀመጡ ሆ። የቤተ ክህነቱንም  ሥራ በወቅቱ የደብረ ሊባኖስ ገዳም ዕጨጌ የነበሩት ዕጨጌ ገብረ  ጊዮርጊስ እንዲመሩት ተደረገ።

  ከዚህ በኋላ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥቱ ተቋርጦ የቆየው የሁለቱ  አብያተ ክርስትያኑ ግንኙነት እንዲቀጥል ለግብፅ ቤተ ክርስቲያን  ጥያቄ አቀረበች። በጥያቄውም መሠረት የግብፅ ቤተ ክርስቲያን  በወረራው ወቅት ሸሽተው ወደ ሀገራቸው በሔዱት አቡነ ቄርሎስ  የሚመራ አንድ ልኡከ ወደ ኢትዮጵያ ላከች።  ልዑኩ በቤተ መንግሥቱ  ከተወከሉ ኢትዮጵያውያን ጋር ከተወያየ በኋላ የኢትዮጵያን "ግዝቱ  ይነሣልን" ጥያቄ ይዞ ወደ ካይሮ ተመለሰ። በዚህ ጊዜ አቡነ ቄርሎስ  አዲስ አበባ ቀሩ። ጉዳዩን መስመር ለማስያዝ በሚልም በወቅቱ  የሊቀ ጳጳሳትነቱን ቦታ ይዘው የነበሩት ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ የመንበረ ሊቀ ጳጳሱን ግቢ እንዲለቁ ተደርጎ ግብፃዊው ሊቀ ጳጳሳት በዚያ እንዲቀመጡ ተደረገ።

  አቡነ ቄርሎስ አዲስ አበባ ተቀምጠው በሁለቱ ቤተክርስትያናት እንዲሁም በቤተ መንግስቱ መካከል ልዑካን ቢመላለሱም ነገሩ የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ቤተ ክርስትያን በምትፈልገው መልኩ ሊሄድ አልቻለም።  ቀድሞ በመከራ ዘመን የግብፅ ቤተ ክርስቲያን  ባደረገችው ፊትን የማዞር ድርጊት፤ ከነጻነትም በኋላ ግዞቱን  ላለማንሳት እየሰጠችው ባለው ሐላፊነት የጎደለው መልሰ  ክፉኛ ያዘነው የመንፈሳዊ ጉባኤውም በመደበኛ አማካሪዎቹ  አማካይነት አዲስ አበባ ላይ ሰፊ ውይይት ያዘ፡፡ በጉዳዩ ላይ በስፋት ከ ተወያየበት በኋላም ሐምሌ 6 ቀን 1937 ዓም አንድ ከባድ ውሳኔ  አሳለፊ። ይኸውም "የግብፅ ቤተ ክርስቲያን እየተደረገ ባለው  ውይይት ያሳለፈችውን ግዝት ታንሣ። ከአሁን በኋላም የግብፅን ቤተ  ክርስቲያን እምነት ባንለውጥም ከግብፅ ምንም ዓይነት ሊቀ ጳጰሳትን  አንፈልግም። በቋንቋችን የሚናገርና የሚያስተምር ሊቀ ጳጳሳት እ ንፈልጋለን" የሚል ነበር። የውሳኔው ሙሉ ቃል በእጨጌ ገብረ  ጊዮርጊስ እንዲፈረምበት ከተደረገ በኋላ ለንጉሠ ነገሥቱ ተላከ።

  ከወራት በኋላም ኅዳር 9 ቀን 1938 ዓም ጠቅላላ መን ፊሳዊ ጉባኤው እንደገና ተሰበሰበ። በዚህም መሠረት ባለፉት  ጊዜያት የተደረጉትን ውይይቶችና የተከናወኑትን ድርጊቶች ሪፖርት  በመስማት በሐምሌ የአማካሪዎች ጉባኤ ያስተላለፈውን ውሳኔ በመቀ በል ተጨማሪ የውሳኔ አሳቦችንና ማሳሰቢያዎች በማስተላለፍ  ተበተነ።

  በዚህ የሊቃውንቱ ቆራጥ ዐቋም የተነሣም በችግር ጊዜ ወደሃገራ ቸው ሸሽተው ሔደው የነበሩትና በኢትዮጵያውያን አባቶች  ሊቃውንት እንዲሁም አርበኞች ደም ሰላም ከመጣ በኋላ ተመልሰው  መጥተው የነበሩት አቡነ ቄርሎስ ኢትዮጵያን ለቀው ሄዱ። ከላይ  በተገለጠው ዓይነት የተላለፈው የመንፈሳዊ ጉባኤው የመጨረሻ  ውሳኔ የደረሰው ቤተ መንግሥትም በጉዳዩ ላይ ከመከራ በኋላ  ከመንፈሳዊ ጉባኤው አቋም ለየት ያለ አሳብ አቀረበ፡፡ ይህውም  ከግብፅ ቤተ ክርስቲያን ጋር በዚህ ዓይነት ከምንለያይ ለተጨማሪ  ውይይት ጊዜ መስጠት ይኖርብናል የሚል ነበር። ቤተ መንግሥቱ  ይህንን አሳቡንም በፅጨጌ ገብረ ጊዮርጊስና፡ በሌሎች  አማካይነት ለመንፈሳዊ ጉባኤው ገለጸ።

  የሊቃውንቱ ጉባኤ ምንም እንኯን "አስከመቸ እ ንወያያለን?" በሚል በተወሰነ ደረጃ የቤተ መንግሥቱን ጥያቄ  ላለመቀበል ተቃውሞ ቢያሰማም በመጨረሻ ግን "ይሁን፣ ጥቂት  ጊዜ ይሰጥ" በሚል ተስማማ። አቋሙ አንዳልተቀየረ፣ ጥያቄው  ተግባራዊ ይሆን ዘንድ ብቻም ተጨማሪ ጊዜ እንደ ሰጠ በመግለጽ  አንደ ገና በእጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ ፊርማ ለቤተ መንግሥቱ  አቀረበ። በዚህ ደብዳቤ የሚከተለው ሃሳብ ተካቶበታል።

  "... መላው ጉባኤ በኢትዮጵያ የሚገቡት ነገሮች እንዲሰጡ ሊቀ ጳጳሳትም ከኢትየጵያ ተወላጆች ውስጥ እንዲመረጥ ማስፈለጉን ተስማምቶበታል። ይኸውም እሳብ በመንግሥታችን ወገን የተደገፈ ስለሆነ መንግሥታቸን መልእክተኞችን ልኮ እሳቡን ለማስፈጸም የሚከናወንለት ክሆነ ጉባኤው ተቃዋሚ እይደለም፤ ስለዚህ የቤተ መንግሥታቸን እሳብና ምኞት መልእክተኞቹን ልኮ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የጠየቀችውን ሁሉ በእስክንድርያው ፓትርያርክ ተጠባባቂ ወይም ከጉባኤው
  ጋር በሰላም ለመጨረስ ስለሆነ ይህንኑ በቶሎ በፍጻሜ እንዲያደርስላት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስተያን ግርማዊነትዎን በጸሎት እየደገፈች ትለምናለች። ነገር ግን ግርማዊነትዎ መልእክተኞችን ልኮ ከአሁን በፊት በዚሁ ነገር ቤተ ክህነት የደከመችውን ያህል በነገሩ ደክመውበት በእስክንድርያው ፓትርያርክ ተጠባባቂ ወይም በጉባኤው ፍሬ ያለው ምላሽ ያልተገኘ እንደሆነ ግርማ ዊነትዎ የተስማማ እንደሆነ ባለመጠራጠር እናምናለን፡፡"

  ቤተ መንግሥቱም ይህንን የመሰለ ጠንካራ ማሳሰቢያ ከቤተ ክርስቲያኗ ሊቃውንት ከተቀበለ በኋላ በጉዳዩ ላይ ከግብፅ ቤተ ክርስቲያን ጋር መክረው የኢትዮጵያን ጥያቄ ያሰፈጽሙ ዘንድ ክቡር  ፊታውራሪ ታፈሰ ሀብተ ሚካኤልንና ብላታ መርሥዒ ኀዘን ወልደ  ቂርቆስን ጥር 1 ቀን 1938 ዓም ወደ ካይሮ ላከች። ልዑኩ ወደዚያ ሲሔድ ከንጉሠ ነገሥቱ ዘንድ ለፓትርያርኩ የተጻፈ ደብዳቤ ይዞ  ነበር። ጉዳዩ በኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ዘንድ ተጠናክሮ መቀጠሉ ን የሰማው የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ግን ኢትዮጵያውያኑ  ልዑካን ካይሮ ከመድሪሳቸዐኑ በፊት አንድ ውሳኔ አሳለፈ። ያህውም  ለሚሾሙት ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት ጋር ሁለት የግብፅ ጳጳሳትም ተሹመው  ወደ ኢትዮጵያ ይምጡ የሚል ነበር።

  ከባድና ታሪካዊ ተልዕኮ ይዘው የሄዱት ሁለቱ ልዑካንም  ካይሮ እንደደረሱ ውሳኔው ተገለጸላቸው። ይሁን እንጂ በቀረበ ላቸው ውሳኔ ባለመስማማት ክርክራቸውን ቀጠሉ። ከብዙ ክርክርና  ውይይት በኋላም የግብፅ ቤተ ክርስትያን የኢትዮጵያን ጥያቄ እንደ ተቀበለች፣ በጥያቂው መሠረትም የኢትዮጵያውያኑ አባቶች ሹመት በግንቦት ወር ለሚደረገው የአዲስ ፓትርያርክ ሹመት ጋር እንደሚፈፀም  ለዚያም አምስት አባቶች ተመርጠው እንዲላኩ ለልዑካኑ  ተገለጸላቸው።

  በውሳኔውም መሠረት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት በዕውቀት እና በምግባር የተመሰከረላቸው አምስት ሊቃውንት መርጠው በፊታውራሪ ታፈሰ ሀብተ ሚካኤልና በብላታ መርሥዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ መሪነት ሚያዝያ 28 ቀን 1938 ዓም ወደ ካይሮ ላኩ። የግብፅ ቢተ ክርስትያን አስቀድማ በገባችው ቃል ኪዳን መሰረት የግብፅ  115ኛ ፓትርያርክ ከሆኑት አቡነ ዮሳብ ጋር ግንቦት 2 ቀን 1938 ዓም ሊሾሙ ወደ ካይሮ የገሰገሱት አባቶች በሰላም ገብተው ዝግጁነታቸውን ገለጡ። ነገር ግን ባልጠበቁት ሁኔታ በግብፆች የተዘጋጀና የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ሙሉ በሙሉ ነፃነቷን እንዳታውጅ የሚያደርግ ሰነድ ቀረበላቸው። ሰነዱም የሚሾሙት ጳጳሳት ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ሌላ ኤጲስ ቆጶስ እንዳይሾሙ የሚያግድ ሲሆን ኢትዮጵያውያኑ አባቶች ከመሾማቸው በፊት እንዲፈርሙበት ይጠይቃል። የግብፆችን ተንኮል በሚገባ የተረዱት አባቶችም ሲኖዶሱ ያሳላፈውን ውሳኔ ባለመቀበል ተቃውሞዋቸውን በፊታውራሪ ታፈሰ ፊርማ ለተጠባባቂ ፓትርያርኩ አሳወቁ። ወዲያውኑ ሲኖዶሱ ያቆያቸውን ውሳኔ በተጠባባቂ ፓትርያርኩ በኩል ለግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እንዲላክ አደረጉ። ንጉሰ ነገሥቱም ውሳኔውን በሚገባ ከመረመሩ በኋላ ኢትዮጵያ የማስማማባቸውን ነጥቦች በዝርዝር በማስቀመጥ ኢትዮጵያኑ ልዑካን ካፓትርያርኩ ጋር ይወያዩባቸው ዘንድ ለፊታውራሪ ታፈሰ ላኩላቸው። ይህንንም እንዳደርጉ ለፓትርያርኩ በደብዳቤ አሳወቁ። የንጉሱ ደብዳቤ የደረሳቸው ተጠባባቂ ፓትርያርክም ለንጉሱ የመልስ ደብዳቤ ከፃፉ በኋላ ከልዑካኑ ጋራ የጋራ ስብሰባ አድረገው ተዋያዩ። ከውይይቱም በኋላ ኢትዮጵያውያኑ አባቶች አዲሱ ፓትርያርክ ከመሾማቸው በፊት ሊሾሙ አይቻልም ከሚል ውሳኔ ላይ ስለደረሱ እና አንዳንድ ተጨማሪ ግልፅ ያልሆኖ አሳቦች ስለ ነበሩ ተጠባባቂ ፓትርያርኩን በመሰናበት ከወራት ፍሬ ቢስ ቆይታ በኋላ ሐምሌ 29 1938 ዓም ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ። በዚህ የተነሳ ከግብፅ ቤተ ክርስትያን ጋር የነበረው ግንኙነት ለሁለት አመታት ያህል ተቋረጠ። ይህንን በያሉበት ሆነው የሰሙት ኢትዮጵያውያኑ ሊቃቅንትና መምህራን ምንም እንኳን እንዳለፉት አይነት ጉባኤያት አድረገው ባይወያዩም በያሉበት ሆነው ድምፃቸውን ሲያሰሙ ቆዩ።

  የሊቃውንቱ ድምፅ ከፍ እያለ እንደ ገና ጉባኤ ወደ መጥራት አዝማሚያ ሲደርስ ሀምሌ 9 1940 ዓም የግብፅ ቤተ ክርስትያን ፓትርያርክ አቡነ ዮሳብ ለግርማዊ ንጉሰ ነገሥቱ አንድ መልእክት ላኩ። መልእክቱም የግብፅ ቤተ ክርስትያን ኢትዮጵያውያኑን አባቶች ለመሾም መወሰኗን የሚገልጥ ነበር። በዚህም መሰረት ከሁለት አመታት በፊት ተመርጠው ይሾሙ ዘንድ ወደ ካይሮ ሄደው የነበሩት አምስት አባቶች እንደ ገና ወደ ካይሮ ሄዱ። እንደ ደረሱም ኢትዮጵያውያኑ በተስማሙበት አንድ ፕሮቶኮል ላይ ፈርመው ሐምሌ 18 ቀን 1940 ዓም ካይሮ ላይ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ዮሳብ እጅ ተቀብተው ጳጳሳት ሆኑ። ከተፈራረሙትም ፕሮቶኮል ውስጥ "አንድ ኢትዮጵያዊ ሊቀ ጳጳሳት ከመሾሙ በፊት አሁን በኦፊሴል ሊቀ ጳጳሳት ዘኢትይዮጵያ ተብለው የሚታወቁት ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ማረፍ አለባቸው" የሚል ይገኝበታል።

  ሐምሌ 18 ቀን 1940 ዓም ስርአተ ሲመት ተፈፅሞላቸው ሐምሌ 22 ቀን 1940 ዓም አዲስ አበባ የገቡት ኢትዮጵያውያን አባቶች የሚከተሉት ነበሩ።
  1. ብፁዕ እጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ - አቡነ ባስልዮስ
  2. መምህር ገሪማ ወልደ ኪዳን - አቡነ ሚካኤል
  3. ሊቀ ስልጣናት መልእክቱ ወልደ ማርያም - አቡነ ባስልዮስ
  4. መምህር ዘፈረ ብርሃን ገብረ ፃዲቅ - አቡነ ያዕቆብ
  5. መምህር ጌታሁን ወልደ ሐዋርያት - አቡነ ጢሞቲዎስ

   

  ከሦስት አመታት በኋላ ግብፃዊው የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳሳት አቡነ ቄርሎስ ሲያርፉ ቀደም ሲል በተፈረመው ፕሮቶኮል መሰረት ብፁዕ አቡነ ባስልዮስ በብፁዕ አቡነ ዮሳብ የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳሳት ሆነው ተሾሙ። ይህም ለዘመናት እልህ አስጨራሽ ክርክር ላደረገቸው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን ቤተ መንግስት ከፍ ያለ ደስታን ፈጠረ።
  የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያንም ከዚያ በኋላ እንደ ፍላጎቷና እንደ ሕዝቧ ጥያቄ ኤጲስ ቆጶሳትንና ጳጳሳትን እየሾመች ለአገልግሎት በማሰማራት የስብከተ ወንጌል አገልግሎቷን ማስፋፋቷን ቀጠለች። ይህ በእንዲህ እንዳለ በ1948 ዓም በግብፅ ቤተ ክርስትያንቅዱስ ሲኖዶስ አባላት መካከል መለያየት ተከሰተ። በዚህም የተነሳ ፓትርያርኩን በተቃወሙ አባላት ምክንያት የግብፅ ቤተ ክርስትያን ፓትርያርክ የነበሩትና የሁለቱን እህት አብያተ ክርስትያናት ወደ ላቀ ደረጃ ያደረሱት ብፁዕ አቡነ ዮሳብ ከመንበረ ፓትርያርክነታቸው ተነሱ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ይህንን ድርጊት በመቃወም ድምጿን አሰማች። አንድ በጉዳዩ መክሮ የሚመለስ ልዑክም ወደ ካይሮ ላከች። ይሁን እንጂ ፓትርያርኩን ከመንበራቸው ባወረዷቸው አባቶች እምቢታ የተነሳ ልኡኩ ያላ ውጤት ተመለሰ።

  የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን ይህ እና ሌላም አንድ ልዑኳ ካለ ፍሬ ከተመለሰ በኋላ ጉዳዩን በረቀት እየተከታተለች ምፍትሄ የሚገኝበትን መንገድ ስታፈላልግ ፓትርያርኩ አቡነ ዮሳብ ህዳር 4 ቀን 1949 ዓም ከዚህ አለም በሞት ተለዩ። በዚህም መሰረት በእርሳቸው መንበር የሚተካውን ፓትርያርክ ለመምረጥ የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን መራጭ ወኪሎችን እንድትልክ ግብዣ መጣላት። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን በፓትርያርክ ምርጫ ላይ ያላት አግባብ በግልፅ ያልተወሰነ በመሆኑ ባለፉት ፓትርያርክ ላይም ያደረጋችሁት አድራጎት ጥሩ ባለመሆኑ እናዝናለን በማለት ግብዣውን እንደማትቀበለው አሳወቀች።

  በዚህም ምክንያት የሁለቱ ቤተክርስትያኖች ግንኙነት ተቋርጦ ቆየ። ነገር ግን አዲሱ የተሾሙት ፓትርያርክ ባልተጠበቀ ሁኔታ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን መዓረግ ወደ ፓትርያርክነት ደረጃ ከፍ ለማድረግ ያሰቡ መሆናቸውን የሚያትት ደብዳቤ አስይዘው ሦስት ጳጳሳትና አራት ምእመናን ወደ አዲስ አበባ ላኩ።

  መልእክተኞችም አዲስ አበባ ላይ ከቤተ ክህነትና ከቤተ መንግስት ሰዎች ጋር ሰፊ ውይይት ሲያደርጉ ከሰነበቱ በኋላ ወደ አንድ ስምምነት በመድረስ የውል ስምምነት በሁለቱ ቤተ ክርስትያኖች መካከል ተፈረመ። በስምምነቱ መሰረት በወቅቱ የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳሳት የነበሩት ብፁዕ አቡኔ ባስልዮስ ሰኔ 21 ቀን 1951 ዓም በብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ተቀብተው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ሆነው ተሾሙ። በስነ ስርዓቱም ላይ ግርማዊ ንጉሠ ነገስቱ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሤ ተገኝተው ነበር። 

  በዚህም ወቅት 21 መድፍ ተተኮሰ። በአዲስ አበባ የሚገኙ አድባራትና ገዳማት በደወል ድምፅ ደስታቸውን አሰሙ። ምእመናንም በእልልታ አጀቧቸው።

  ምንጭ 
  • ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን (ዲ/ን መርሻ አለሀኝ)
 • loader Loading content ...
 • @Tesfaw   1 year ago
  Sewasewer
  ምስጋና ሊ/ትጉሃን እምሩ! እጅግ ጠቃሚ አና አስትመሪ መረጃ ነው።

Load more...