loader
 • የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ምን አይነት ቦታ አላት?

  @መርሻ   2 years ago
  Interested in just about everything!
 • loader Loading content ...
 • @መርሻ   2 years ago
  Interested in just about everything!
  የኔፕልስ ልዕልት በመወለዷ ግራዚያኒ የደስታ መግለጫ ገንዘብ እሰጣለሁ ብሎ ከዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከድሮው ቤተመንግስት ድሆች እንዲሰበሰቡ አዘዘ። ከድሆቹ በስተቀር ታላላቅ የኢጣልያ ሹማምንት፣ የሜትሮፖሊታን ጳጳስ አቡነ ኪርልና ሌሎችም መኩአንንት ነበሩ። ለእያንዳንዱ ድሀም ሁለት ማርትሬዛ ብር እንዲሰጥ ተወስኖ ነበር።

  እኩለ ቀን ገደማ ላይ 3000 የሚሆኑ ድሆች ከቤተ መንግስቱ ገቡ። ወዲያው በግቢው በር በኩል አንድ ቦምብ ፈነዳ። ቀጥሎም ሌላ ፈነዳ። ለሶስተኛ ጊዜ የተጣለው ቦምብ የፋሺስት ኢጣልያ መክዋንንት ካሉበት ቦታ ፈነዳ። ግራዚያኒ ጀርባውን ቆስሎ ወደቀ። በቀጠለው ጥቂት ደቂቃ ውስጥ ሌሎች ቦምቦች ተከታትለው ተጣሉ። በጠቅላላው በግቢው ውስጥ ሰባት ቦምቦች ፈነዱ። ጄኔራል ሊታዩ፣ የአዲስ አበባው ከንቲባ ጉይዶ ኮርቴሲ፣ ጋዜጠኛው ማርዮ አፔሎስ እና ሌሎች 30 ያህል ሰዎች ቆሰሉ። የቦምቡ ፍንዳታ ጋብ እንዳለ አድፍጠው ተኝተው የነበሩ ወታደሮች ተነስተው ተኩስ ከፈቱ። በዚያ ግቢ ውስጥ ያለማቁዓረጥ ሶስት ሰዓት ሙሉ ተኩስ ተካሄደ።

  ከጥቂት ጊዜ በህዋላ ባለ ጥቁር ሸሚዞች፣ የኢጣሊያ ሾፌሮች፣ የቅኝ ግዛት ወታደሮች በአዲስ አበባ ከተማ እየዞሩ ሕዝቡን ይፈጁት ጀመር።

  አንጄሎ ዴል ቦካ በመፅሐፉ "... በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖር አንድ ኢጣልያዊ ወዳጄ ሲኞር ዲ ስሜን አትግለጥብኝ ብሎ እንዲህ ሲል አጫወተኝ። አየህ፣ የዚያን እለት ብዙ ኢጣልያኖች ብዙ ሥራ ሰርተዋል። ወደማታ ገደማ ካንድ ጉዋደኛዬ ጋር ስንገናኝ ያ ጉዋደኛዬ ቦምብ ስጥል የዋልኩበት እጄ ዝሏል ብሎ ነገረኝ። አንዱ ኢጣልያዊ ሲያጫውተኝ ባንዲት ትንሽ ጣሳ በያዝክዋት ቤንዚን አስር ቤቶች አቃጠልኩባት አለኝ። በዋናው የጦርነት ጊዜ ጥይት ተኩሰው የማያውቁ ኢጣልያውያኖች ሁሉ በዚያን ቀን ሲተኩሱ ዋሉ ስል አጫወተኝ..." በማለት ፅፏል።

  አዲስ አበባ የነበረው የሃንጋሪው ሀኪም ዶክተር ላድስላስ ሳቫ ደግሞ "... ኢትዮጵያውያን ሁሉ በሰላም እና በፍቅር ከቤተ መንግስቱ ግቢ ተሰበሰቡ። ጥቂት ቆይቶ ግራዚያኒና መክዋንንቱ ከጠቀመጡበት ጠረጴዛ አጠገብ ቦምቦች ተወረወሩ። ቦምቡ እንደተጣለ ግራዚያኒ ጠረጴዛው ስር ተደበቀ። ሌሎች ኢጣልያኖች ግን ከመሬት ተኙ። ቦምቡን የጣለው በኢጣልያኖቹ ዘንድ በአስተርጉዋሚነት የሚሰራ የኤርትራ ክፍለ ሃገር ተወላጅ ነው።"
   
  "ለጥቂት ጊዜ ፀጥ አለ። ኢጣልያኖቹ ሌላ የሚወረወር ቦምብ እንደሌለ ካወቁ በህዋላ ከተኙበት ተነሱ። ወዲያው ካርቴሲ ወደ ኢትዮጵያውያን መክዋንንት ሽጉጡን አነጣጥሮ የመጀመሪያዋን አንድ ጥይት ተኮሰ። ካራቢኔሪዎችም ምሳሌውን ተከተሉ። በጥቂት ጊዜ ውስጥም በዚያ ግቢ 300 ሬሳዎች ተከመሩ።"

  "ኃይለኛና ተገቢ ያልሆነ ጭፍጨፋ ነበር። ሽማግሌዎች፣ እውሮች፣ እግር የሌላቸው ለማኞች፣ ድሆች እናቶች ከነልጆቻቸው ነበሩበት። ባለጥቁር ሸሚዞች በግቢው እየተሯሯጡ በሕይወት ያለ ኢትዮጵያዊ ይፈልጉ ነበር። ከሬሳዎቹ መሀልም የሚተነፍስ ካለ እያሉ እየመረመሩ ይገድሉ ነበር። ከጥቂት ደቂቃዎች በህዋላ ባለጥቁር ሸሚዞች፣ ካራቤኔሮዎችና የጦር ወታደሮች በከተማው ውስጥ ይሯሯጡ ጀመር። ሱቆች ሁሉ እንዲዘጉ አደረጉ። የውጭ አገር ስዎችም ከቤታቸው እንዳይወጡ አዘዙ። በተለይ ፎቶግራፍ ማንሻ እየተፈተሸ ይወሰድ ጀመር። መንገዱ ሁሉ ጭር አለ። የፖስታና የስልክ አገልግሎት ተቁዋረጠ። በቤተ መንግሥቱና ባካባቢው ያሉት መንገዶች በሙሉ በሬሳ ተሸፈኑ።"

  "በምን አይነት አጨካከን ነው? ደም እንደውሀ ሲፈስ በየመንገዱ ላይ ያየሁት የዚያን ጊዜ ነው። የወንዶች፣ የሴቶች፣ የልጆች እሬሳ በያለበት ተኝቷል። ወዲያውም ከባድ የቃጠሎ ጭስ ተነስቶ ከተማዋን አጨለማት። የህዝቡ ቤት ከተፈተሸ በህዋላ ሰዎቹ በውስጡ እንዳሉ ቤቱ በእሳት ይቃጠላል። ቃጠሎው ቶሎ እንዲያያዝም በቤንዚንና በዘይት ይጠቀሙ ነበር። ሰው እሳቱን እየሸሸ ከቤቱ ሲወጣ በመትረየስ ይገድሉታል። ሌሊቱንም ሲገድሉና ሲያቃጥሉ አደሩ። የማልረሳው ነገር፣ በዚያ ሌሊት የኢጣልያ መኮንኖች በሚያማምር አውቶሞቢላቸው ከሚስቶቻቸው ጋር ሆነው ብዙ ሬሳ ከተከመረበትና ብዙ ቃጠሎ ከሚታይበት ቦታ በሰው ደም ላይ እየቆሙ ያን እልቂት እየተመለከቱ ይስቁ የነበረበት ሁኔታ ነው።"

  "ግራዚያኒን ሆስፒታል አስገብተውታል። ግራዚያኒ ሆስፒታል ሆኖ በመስኮት የከተማዋን መቃጠል እያየ ይስቅ ነበር። ዳግማዊ ኔሮ። በዓለም ጦርነት ጊዜ ቁስለኛ ለማንሳት ከግንባር ቀደሙ ጦር ጋር በአምቡላንስ ውስጥ እሰራ ነበር። በሌላም ጦርነቶች ተካፋይ ሆኛለሁ። እንደ አዲስ አበባው ያለ እልቂት ግን አላየሁም።"

  "በመክናዎቹ እየዞሩ ሬሳ ያነሳሉ። ባለጥቁር ሸሚዞች ወደ ኢጣልያ ባንክ እየገቡ ሌሊት የሰርቁትን ብርና ወርቅ ያስቀምጣሉ። ዘረፋው በቤት ውስጥ ብቻ አልነበረም። ከሚገድሏቸው ሴቶች አንገትና ጆሮ ላይ የሚገኘውን ወርቅ ሁሉ ይወስዱ ነበር።"

  "ሕክምና በምሰራበት ቦታ ብዙ ኢጣልያኖች የመጡ ነበር። እያንዳንዱ ኢጣልያም ምን ያህል ሰው እንደገደለ በኩራት ይናገራል። አንዳንዶቹ 80 ገደልኩ ሲሉ አንዳንዶቹ ደግሞ መቶ እንደገደሉ ይናገራሉ። አንድ ኢጣልያዊ ብቻ እያዘነ እኔስ የገደልኩት ሁለት ብቻ ነው ብሎ ሲናገር ሰምቻለሁ። ... የማልረሳው ነገር፣ ግድያው እንዲቆም በተደረገበት ጊዜ ታላቁ ግራዚያኒ ለሕዝብ በማዘን ግድያው ይቁም ብለዋል ተብሎ የተነገረው ነው። ግሩም አዘኔታ ..." በማለት በሰፊው ፅፏል።

  በቁጥር 14154 ግራዚያኒ ሮማ ላለው ለቅኝ ግዛት ሚኒስቴር ባስተላለፈው ቴሌግራም "እነኚህ ጥቁሮች የኛን ወታደር ሲያዩ ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር ይላሉ። ይህን የሚሉትንም ለመቀጣጫ ሁሉንም አስጨረስክዋቸው። እደግመዋለሁ፣ አስጨረስክዋቸው" ብሏል። በዚያው ዘመን እ.ኤ.ዓ. የካቲት 22 ቀን (በኛ የካቲት 14 ቀን) የወጣው ጋዜጣ ዴል ፖፖሎ ሲፅፍ "... የአዲስ አበባ አጋማሽ በአሰሳው ፀድቷል። 2000 ኢትዮጵያውያን ተይዘው ወደ ደናኔና ወደሌሎችም ማሰሪያ ቦታዎች ተልከዋል..." ይላል።

  የካቲት 12 ቀን በተጀመረው እልቂት በሶስት ቀን ውስጥ 30000 ሰዎች በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ከተገደሉ በህዋላ ሌላው እየታፈሰ ወደ በረሃ እስር ቤቶች ተላከ። እስር ቤቶቹ እንዴት ነበሩ? ለጦር ወንጀለኞች አጣሪ ኮሚቴ፣ ብላታ በቀለ ሃብተ ሚካኤል ከተናገሩት ውስጥ በመጠኑ እንጥቀስ። "... መቃዲሾ እንደደረስን በቀጥታ ከዋናው ወህኒ ቤት አገቡን። በማግስቱም ወደ ደናኔ ወሰዱን። 200 ሰዎች ባንድ ቦታ አጎሩን። ይሰጡን የነበረው ምግብ ለጤናችን ፈፅሞ የማይስማማ ነበር።"

  "የሚሰጡንም በላዩ ላይ ብዙ ትላትሎች የሚታዩበት የደረቀ ቂጣና ሻይ ነበር። በዚህም ምክንያት ብዙዎቻችን ታመምን። የዚያን ጊዜ የእስር ቤቱ ኃላፊ ብርጋዴር ባሮኒ ነበር። ስለምግባችን ብዙ ጊዜ እየቀረብን ብናመለክትም ትዕዛዙ የበላይ ስለሆነ ምንም ማድረግ እንደማይቻል ይነግረን ነበር። በግራዚያኒ ሕይወት ላይ አደጋ ከተጣለ በህዋላ ብዙ እስረኞች ወደኛ መጡ። ቦታ ስለጠበበ ሜዳው በሽቦ ታጥሮ ከዚያ ሰፈሩ። እኛንም ወስደው ከነሱ ጋር ደባለቁን። ከተደባለቅን በህዋላ የምግብ ጉዳይ የባሰ ሆነ። በምግቡ ምክንያት በየቀኑ አራትና አምስት ሰዎች እየሞቱ ይጣሉ ጀመር..." ብለዋል። የተባበሩት መንግሥታት ከተመሰረተ በህዋላ በዚሁ ስር ለተቁዋቁዋመው አጣሪ ኮሚሽን ቃላቸውን ከሰጡት እስረኞች መሃል ሌላው አቶ ሚካኤል ተሰማ ናቸው። እሳቸው እንዲህ ብለው ነበር "... በደናኔ እስር ቤት ሶስት ዓመት ከሶስት ወር ታስሬ ቆይቻለሁ። የወህኒ ቤቱም ሁኔታ እንዲህ ነበር። ላንድ ወታደር ማደሪያ የተሰራች አንዲት ድንክዋን ለሶስት ኢትዮጵያውያን ተሰጠችን። ምግባችን የደረቀ ጋሌታ ነው። የውቅያኖሱን ውሃ መጠጣት እንደጀመርንም ብዙዎቻችን ታመምን። በየቀኑ ከስድስት እስከ ሰላሳ ሰዎች በተቅማጥ በሽታ ይሞቱ ነበር። በጠቅላላውም 3175 ሰዎች ሞቱ። ይህንንም ቁጥር ለማወቅ የቻልኩት በክሊኒኩ ውስጥ ረዳት ሀኪምና የበሽተኞች ሁኔታ መዝጋቢ ስለነበርኩ ነው። በደናኔ እስር ቤት የነበርነው 6500 ሰዎች ነን። ከነዚሁ ውስጥ 3175 ሰዎች ሞቱ። ዓመት ከታሰርን በህዋላ ስጋ፣ ማካሮኒ እና ሩዝ በሳምንት አንድ ጊዜ ይሰጠን ጀመር። እስረኞቹን ይጠብቁ ከነበሩት ኢጣልያኖች መሃል ብርጋዴር ባሮኒ፣ 50 አለቃ ቶሳቶ እና አሁን ስሙን የረሳሁት የካራሚኔሪዎች ማርሻል እስረኞቹን በመግረፍ የታወቁ ነበሩ።"

  "ስራችን አትክልት መኮትኮት፣ የሚነድ እንጨት መስበርና መንገድ መስራት ነበር። በሥራ ቦታ ድካም የሚያሳዩ ሴቶች ሆኑ ወንዶች እጆቻቸውን የሁዋሊት እየታሰሩ ለሰባት ቀናት ጣሪያ ላይ ይንጠለጠላሉ። በእንዲህ ያለው ቅጣጥም ሁለት ሰዎች እጆቻቸው እየተገነጠሉ ሞተዋል። እስረኛ ታሞ ወደ ክሊኒክ በሚመጣበት ጊዜ ካፒቴን አንቶኒዮ እነዚህ ሰዎች ከሚኖሩ ቢሞቱ ይሻላቸዋል በማለት አርሴኒክ እና እስትሪቺኒን የተባሉ መርዞችን በመርፌ በመውጋት ይገድላቸው ነበር። አንዳንዶቹንም ለህክምና የሚመጡትን እጅና እግራቸውን እያሰሩ ገላቸውን በምላጭ በመተልተል ይጫወቱባቸው ነበር። ..." ሲሉ የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

  የኤርትራ ክፍለ ሃገር ተወላጅ ደጃዝማች ሪሳርዮ ጊላ እግዚዕ በግራዚያኒ ላይ ቦምብ በተጣለ ጊዜ ከዚያው ስለነበሩ የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል። ደጃዝማች በእውነት እመሰክራለሁ ብለው ከማሉ በህዋላ "... የተኩስ ድምፅ ሰማሁ። መኪናዎች እዚህም እዚያም ይሯሯጣሉ። ሰውም ይሯሯጣል። መትረየስ ይተኮሳል። ሁሉም ነገር ተመሰቃቅሏል። ኢትዮጵያውያኖች ከኢጣልያኖች ይሸሻሉ። ኢጣልያኞቹ ደግሞ ከኢትዮጵያውያኖቹ ይሸሻሉ። ኢጣልያኖቹ እንደገመቱት በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ከብቦ የነበረው ሽፍታ ከተማዋን የወረራት መስሏቸዋል። ከዚያ በፊት ራስ ደስታ ከአዲስ አበባ ገብተው የኢትዮጵያ አርበኞች ከከተማዋ ያለውን ኢጣልያዊ በሙሉ ይገድላሉ እየተባለ ይወራ ስለነበር ነው..." ብለዋል።

  ደጃዝማች ሪሳሪዮ ከሁለት ኢጣልያኖች ጋር ወደፋሺስት ጠቅላይ ፅህፈት ቤት ሄደው በዚያ ስላዩት ሲናገሩ "... ከፋሺስት ዋና ፀሀፊ ከጉይዶ ኮርቴሲ ጋር ተገናኘን። ዙሪያውንም ብዙ የፋሺስት ሹማምንት አሉ። ኮርቴሲም ለነኛ የፋሺስት መኮንኖች ... ወንድሞቼ ሆይ፣ ዛሬ ድል የማድረጋችንና የበላይነታችንን የማሳወቂያ ቀናችን ነው። በዚች በሶስት ቀን ውስጥ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ አጥፉ። ለዚህ ለሶስት ቀን የሚሆንም የነጭ ሽብር (ካርታ ቢያንካ) ፍቃድ እሰጣችዋለሁ። ይህም ፍቃድ ለማጥፋት፣ ለመግደልና በኢትዮጵያውያኖች ላይ የፈለጋችሁትን ለማድረግ የሚያስችላችሁ ነው አላቸው።"

  "ከዚህ በህዋላ እነኚያ የፋሺስት መኮንኖች ወጥተው ሄዱ። ሁሉም የጦር መሳሪያቸውን በክንዳቸው እንደያዙ ነበር። ልክ እንደወጡም ስራቸውን ጀመሩ። በካራሚኔሪዎች ያልታሰረ፣ በመንገድ ላይ ሲሄድ ወይም እቤቱ ውስጥ አርፎ የተቀመጠው ሁሉ ተገደለ። ... ቤቶች ሲቃጠሉ አይቻለሁ። ... ከሚቃጠለው ቤት ልጆች ሲወጡ በኢጣልያኖች እየተገፉ ከእሳቱ ውስጥ ሲጨመሩ አይቻለሁ።"

  "በማግስቱ ቅዳሜ ቀን ነበር። በዚያም ቀን ኢጣልያኖች ትንንሽ ቤቶችን ሲያቃጥሉ ዋሉ። በትልልቆቹ ቤቶች ላይ ግን ስማቸውን እየፃፉባቸው ያልፋሉ። ይህም ቤቱ የተያዘ መሆኑን ለመግለፅ ያህል ነው። ..." በማለት መስክረዋል።

  ፎር ጎድ ኤንድ ኤምፔረር በተባለው ድርሰታቸው ሚሲዮናውያኖቹ ሄር በርት እና ዴላ ሃንሰን እንደፃፉት "...  አዲስ አበባ የደረስነው እልቂቱ ከቆመ በህዋላ ነው። ከዚህ በፊት የህዝቡ መኖሪያ የነበሩ ቤቶች በሙሉ ተቃጥለዋል። ሌላው ቀርቶ የሆስፒታል ግድግዳዎች ሳይቀር በእሳት ተለብልበው ይታያሉ። በከተማዋ በሙሉ የሚታየው የከሰለ ቤት ፍራሽና በእሳት ተለብልቦ የጠቆረ ግንብ ነው። ይህንንም በማየታችን ልባችን ተነካ። በተለይም በጣም ያሳዘነን ነገር፣ ቤቶች ሁሉ የተቃጠሉት፣ ነዋሪዎች ውስጣቸው እንዳሉ ነው ቃሉን በህዋላ ነው።..." ብለዋል። በዚያን ቀን ስለተካሄደው እልቂት ብዙ የአይን ምስክሮች ብዙ አሰቃቂ ድርጊቶችን መስክረዋል። የሁሉንም ለማጠቃለል ራሱን የቻለ መፅሐፍ የሚወጣው ስለሆነ ትቼዋለሁ።

  ጋዜጠኛው ቺሮ ፖጃሊ የካቲት 13 ቀን ስላየው ሁኔታ "... ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሰዎች መደበቃቸው ስለተሰማ ቤተክርስቲያኑ ውስጥ ቤንዚን ተረጭቶ እሳት ተለቀቀበት። ይህንንም ያዘዘው ኮርቴሲ ነው። ... የቤተክርስቲያኑ መፅሃፍትና ስዕሎች ተቃጠሉ። ... ከቤተክርስቲያኑ ውስጥ ከእሳቱ ለመሸሽ 50 ያህል ሰዎች ሲወጡ ተያዙና ከቤተክርስቲያኑ ጉዋሮ ተወስደው በእሳት ይቃጠሉ ሲባል አንድ ኮሎኔል አዝኖላቸው መቃጠሉ ቀርቶ በቦምብ ይገደሉ ብሎ አዘዘና በሙሉ ተገደሉ።... በዚህ ቀን ኮሎኔል ማዚ የጠቅላላው የመገናኛ ራዲዮ ኃላፊ እንዳጫወተኝ ሶስት ጄኔራሎች መሞታቸው ተላልፏል አለኝ..." በማለት በመፅሐፉ ፅፎታል።

  የካቲት 12 ቀን ስለደረሰበት አደጋ ግራዚያኒ ለኢጣልያ ቅኝ ግዛቶች ሚኒስቴር ቴሌግራም ልኮ ነበር። የዚያም ቴሌግራም ግልባጭ በኢትዮጵያ ላሉ የኢጣልያ ሹማምንት ተላልፎ ነበር። ግራዝያኒ ባስተላለፈው ቴሌግራም "... ዛሬ ጧት በ11 ሰዓት (በኛ 5 ሰዓት) ግቢ ተገኝቼ ነበር። ታላላቅ መኩዋንንት፣ የኦርቶዶክስ እና የእስልምና ሃይማኖት መሪዎች ሁሉ ተሰብስበው ነበር። የስብሰባው ዋና ምክንያት የኔፕልስ መስፍን ስለተወለደ ሶስት ሺህ ለሚሆኑ ድሆች ምፅዋዕት ለመስጠት ነበር። 12 ሰዓት ሲሆን (በኛ 6 ሰዓት) በተሰበሰበው መኩዋንንት አስር የብሬዳ ሥራ የእጅ ቦምቦች ካልታወቁ ሰዎች ተጣሉብን። በዚህም ምክንያት ሰላሳ ሰዎች ቆሰሉ። ... በእኔ መቁሰል ምክንያት አገሪቱን የተከበሩ ፔትሬቴ እና ጄኔራል ጋርቦልዲ በህብረት እንዲጠብቁ አድርጌያለሁ። ለአዲስ አበባ ከተማ ፀጥታም አላፊ አድርጌያቸዋለሁ።" ብሏል።

  በሌላ ቀን ባስተላለፈው ቴሌግራሙ ደግሞ "... የተጣለብኝ ቦምብ ቢያንስ 18 ይህናል። አሳባቸው ባንድ ፈንጂ እኔን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም የመንግሥቱን ባለስልጣኖች ጠራርጎ ለማጥፋት ነበር።... ሊሆን ግን አልቻለም። ... የአዲስ አበባ ሰዎችም ጉዳይ ታውቁዋል። የአዲስ አበባን ከተማ ዙሪያ ከከበበው ሽፍታ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው የመከላከያ ኃይላችንን ከጀርባው ይወጉታል። ... በተጣለብኝም ቦምብ 250 ፍንጥርጣሪ ብረቶች ከገላዬ ወጥተዋል። እነኚህንም ፍንጥርጣሪዎች ለታላቅ መታሰቢያነት አስቀምጫቸዋለሁ።..." ብሏል።

  ግራዚያኒ የየካቲት 12 ቀንን እልቂት ባዘዘ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ የነበረው የኢጣልያ ወታደር 35000 ሜትሮፖሊታን ወታደሮች፣ 40000 ባለጥቁር ሸሚዝ ሚሊሺያ፣ 5000 የኤርትራ፣ 3000 የሊቢያ ተወላጅ ወታደሮች ነበሩ። የኤርትራ ተወላጅ ወታደሮች "እኛ ወታደሮች ነን። ከተማ ውስጥ ከሴትና መሳሪያ ከሌለው ጋር በጥይት ተኩስ አንተኩስም" በማለታቸው ብዙዎቹ ጦር ሰፈራቸው ውስጥ ተገደሉ። ሌሎችም ታሰሩ።

  የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. ዛሬ ዩኒቨርሲቲ በሆነው ግቢ ውስጥ ቦምቦች ሲፈነዱ ቦምቦቹ የተጣሉት ከሁለት ይሁን ከብዙ ሰዎች እስካሁን የታወቀ መረጃ የለም። ግራዚያኒ አጠገብ የፈነዳውን ግን አብርሃ ደቦጭ ከጉዋደኛው ከሞገስ አስገዶም ጋር እንደጣለው ይነገራል።

  ምንጭ:
  የኢትዮጵያ እና የኢጣልያ ጦርነት
  በጳውሎስ ኞኞ
 • loader Loading content ...
 • @Alembrehan   1 year ago
  Sewasewer
  ምስጋና@መርሻ ! አስተማሪ ፅሁፍ ነው !
 • @Bilen(ብሌን)   1 year ago
  Sewasewer
  Thanks you Mersha!
 • @Tesfaw   1 year ago
  Sewasewer
  ይህን ታሪክ ስላካፍልክን አመስግናለሁ!
 • @Tariku   1 year ago
  Sewasewer
  በእውነቱ የሰው ልጅ ጭካኔ ፣ በጣም ይዘገንናል! ሁሌም እየጎለጎላችሁ ታሪካችንን እንደዚህ አሳውቁን! ምስጋና!
 • @Yared   1 year ago
  Sewasewer
  በስንቱ ደም እና አጥንት መስዋእትነት የቆምሽ አንቺ አገር ፣ ሌላ ምን እልሻለሁ ፣ ገፅታሽ ይኑር ይከበር።

Load more...