loader
 • ፉከራ ወይም ድንፋታ ምንድነው?

  @Demoze   1 year ago
  Sewasewer
 • loader Loading content ...
 • @Demoze   1 year ago
  Sewasewer
  ፉከራ ወይም ድንፋታ፣ ጀግኖች ለገዢዎቻቸው ወይም ለአለቆቻቸው ከፍ ያለ ድምፅ በማሰማት ወኔአቸውን የሚገልፁበት የጦር ግጥም ነው።

  ሸላዮች በጦር ሜዳ ላይ የተደረገውን ታላቅ ጀብዱ በማውሳት ባማረ ድምፅ ባቅራሩ ጊዜ ጀግኖቹ ደማቸው ይፈላና በፈጣን ንባብ ግጥም እየደረደሩ ጋሻቸውን አንግበው ጎራዴያቸውን ጨረቃ አስመስለው በሚታዘዙበት ቦታ ሁሉ ደማቸውን ለማፍሰስ ዝግጁ መሆናቸውን በሲቃና በወኔ በአንድ እግራቸው ተንበርክከው ወይም በተቅበጠበጡ ፈረሶች ሆነው እያስጨፈሩ፤ ጦር እየሰበቁ፣ ቃታ እየፈለቀቁ ወዲያና ወዲህ እየተንጎራደዱ የገደሉበትንና ጀብዱ የሰሩበትን ቦታ ወንዙንና መልካውን ለይተው በምስክር እያረጋገጡ ይፎክራሉ። የግጥሙ ስልት ከሽለላ ያጥራል። በውስጡም ደጊመ ቃል ይገኝበታል፤ ለምሳሌ: ዘፋፍ፤ ዘፋፍ፤ የጠቅል አሽከር የጠቅል ሎሌ ማለት የተለመደ ነው። ጀግና የሆነ ሰው ሲፎክር ጀግንነቱን የሚያውቁለት ኖር ብለው ይነሱለታል፤ እሱም በእግዚዓብሄር ተቀመጡ ይልና ፉከራውን ይቀጥላል። በመሃከሉም ሙያውን የሚያውቁለትን እህ እገሌ፣ እህ እገሌ ብሎ ሲጠይቃቸው፣ ለካ ፣ ለካ፣ አይተናል፣ ሰርቷል እያሉ ያረጋግጡለታል። እሱም ደስ ብሎት ከኣይናቹ ያውጣኝ ጌቶቼ፣ ወንድሞቼ ተቀመጡ ይላል፤ ሽለላው ሲቀጥል ደግሞ ሌላው ጀግና ይተካል። አንዱ ሲፎክር ሌላው ተደርቦ የደነፋ እንደሆነ ምነው በላዬ በምን በልጠኸኝ ነው? ተባብለው ሙያቸውን ይቋጠራሉ፤ ለበለጠው ቅድሚያ ይሠጠዋል። ስለዚህም በሙያ ለመብለጥ በአደባባይ ለመከበር ሹመት ሽልማት ለማግኘት፣ ሃገር እና መንግስትን ለማስከበር ሲሉ ወታደሮች በጦር ሜዳ ላይ ያለፍርሃትና ስጋት ቀርበው ጠላታቸውን በጎራዴ ያጠቁ እንደነበር ይነገራል።

  ከዚህም የተነሳ ቀረርቶ ወይም ሽለላ፤ ፉከራ ወይም ድንፋታ በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ውስጥ ከፍ ያለ ቦታ ይዘው ይገኛሉ። እነዚህም ግጥሞች ደፋርነትን፣ ቆራጥነትን፣ ልበ ሙሉነትንና ከግንነትን በኢትዮጵያውያን ልብ ውስት የሚቀርፁ ናቸው። ቀረርቶ የሚሰማ፣ ድንፋታ የሚያይ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ልበ ሙሉ ይሆናል፤ ባላጋራውንም ከፊቱ ያየ ይመስል ጠጉሩ ይቆማል ደሙ ይፈላል። በተለይ የሚፎክረው ሰው ሲቅበጠበጥ ቁጭ ብድግ ሲል ለተመልካች የራበው አንበሳን ይመስላል። እልሁ ያነቀው ጀግና ጠላቱን ያገኘ ያህል አይኑን አፍጥጦ ወዲያና ወዲህ ሲንጎራደድ ካራስ ነበር የበለጠ ያስፈራል። ፉከራ ለጀግኖች ሃይልን ይሰጣል፣ ለፈሪዎች ህሊናን እንዲገዙ ያደርጋል። በተለይም በገለሌ ውስጥ የሚገኙት ቃላት በጣም ወኔ የሚቀሰቅሱ በመሆናቸው ለፈሪ እንኳን ድፍረትን ይሰጣሉ፤ ወጣቶችም ይህንን ባዩና በሱም ጊዜ አባቶቻቸውን ለማከል እንዲያውም ለመብለጥ ይጥራሉ።

  የፉከራ ምሳሌ
  -------------

  አካኪ ዘራፍ አካኪ ዘራፍ፤

  ጭው ሲል ገዳይ ደጀን ሲላላ፣
  የጠቅል አሽከር የጠቅል ባላ።

  ጎራዴ መዞ ሲሄድ ከቤቱ፣
  ወየው ሰው ፈጀ አለች እናቱ።

  እንኳን እናቱ የወለደችው፤
  ኮራች አማቱ የተጋባችው።

  በሰፊ አውድማ የተበጠረው፤
  ገለባው ሄዶ ምርቱ የቀረው።
  ዘራፍ ሰው ብሰው፣
  በደረሰበት ባፎቄ እሚያርሰው።

  ሰንደቅ አላማ ኮከብ ሲመስል፣
  ነጋሪት አብጅር አብጅር ሲል፣
  መትረየስ ሲጮህ መድፉ ሲያጓራ፣
  ደጀን ሲበተን እርሳስ ሲዘራ፣
  ኣጣድፎ ገዳይ በያዘው ጣምራ፤
  ባባቱ ወጥቷል ልጁም አይፈራ፤
  አንድ ለናቱ የሜዳ ጎራ።

  ገዳይ ንጉስ ሲቆጣ፣
  አይዞህ ባይ ቱኒ አፉ ሲነጣ፣
  ባለህ እርጋ ባይ ብኩን መድረሻ ሲያጣ።

  ዘራፍ የተፈራ ጦር ኣጋጣሚ፣
  አፋ ቸምቻሚ ባለጅ አድካሚ።

  አጯጯሂ በየጎራ፣
  ገትሮ ቋሚ እንደ ወጋግራ፤

  አባሮ ገዳይ ጋራ ለጋራ፣
  ሳያንቆበርር ሳያንጠራራ፤
  ከያዘም አይለቅ እንደ ዳሞትራ።

  ሽምልምል ያለ እንደ ቀጭን ልብስ፣
  ባንድ ጊዜ ሲቃ አንጀት የሚያርስ።

  ይምጡ ባይ ይሰብሰቡ ባይ፤
  እኒያ ሲመጡ አይበቁንም ባይ።

  ዘራፍ፣ ዘራፍ፣ አካኪ ዘራፍ፤

  ንጉሱ ጠቅል አሽከሩ አንበሳ፣
  ብቅ አለ ወጣ ያው እያገሳ።

  ዝሆን ገዳይ ለጉትቻ፣
  አውራሪስ ገዳይ ለመምቻ፣
  ጎሽ ገዳይ ለመመከቻ፣
  ጎፈር ገዳይ ለደጌቻ፣
  ጎበዝ ገዳይ ለቁትቻ።

  ምንጭ:
  የብላቴን ጌታ ማህተመ ስላሴ ወ/መስቀል ስብስብ ስራዎች
 • loader Loading content ...
 • @መርሻ   1 year ago
  Interested in just about everything!
  I like this man! Thank you!
  ጎራዴ መዞ ሲሄድ ከቤቱ፣ 
  ወየው ሰው ፈጀ አለች እናቱ። 

  እንኳን እናቱ የወለደችው፤ 
  ኮራች አማቱ የተጋባችው።
 • @ቀዮ   1 year ago
  ብልህ እያንዳንዱን አጋጣሚ ከሌሎች ለመማር ይጠቀምበታል!
  አንድ የጓደኛችን ሰርግ ላይ ፉከራ ሲፎከር አይቼ ተመችቶኝ ነበር :) በደህናው ቀን ዝምተኛ የነበሩት ወንዶች ሁሉ እሳት ጎርሰው እሳት ልሰው ሳያቸው ተገርሜ፣ ተገርሜ :)

Load more...