loader
 • የሰሞኑ የአሊ አብደላ ሳልህ ጉዳይና አንዳንድ ነገሮች
  (ክቡር መተኪያ ሀይለሚካኤል)

  @Kibur Metekia Hailemichael   3 months ago
  Sewasewer
 • loader Loading content ...
 • @Kibur Metekia Hailemichael   3 months ago
  Sewasewer

  ባለ ግዜ ሆይ ጠላትህን በቁልቁለት አታባረው የዞረብህ ለት ዳገት ይሆንብሀልና
  (ክቡር መተኪያ ሀይለሚካኤል)

  /facebook\kibur metekia hailemichael

  ምግብ በልተን በጠገብን ሠአት “ከዚያ በሁዋላ ምግብ አይኑንም አላይ” እንላለን:: ጥምብዝ ብለን ሠክረን ያደርን ለታ በንጋታው በሀንጎቨር “መጠጥ የደረሠበት አንደርስም” ብለን እንምላለን::ሠው ነንና ነገ ሥሜታችን ምን ሊሆን እንደሚችል ከእሥከዛሬው የመጠጥ ጥም ወይንም የምግብ ፍላጎታችን ባህርይ ትምህርት አንወሥድም::
  ስልጣን ይሉዋት ነገርም እንዲህ ነች...እንደ ወይን ጠጅ እየተጎነጩዋት ሢሄዱ እያሣሣቀች እያጫወተች በአፍጢም እሥክትከነብል ድረሥ "ካንቺ ሞት ይለየኝ" ታሥብላለች::በታሪክ ተመዝግበው ያሉ አምባገነኖች ፍጻሜያቸው ምን እንደሆነ በትረ ስልጣኗን የጨበጡ መሪዎች ለሰከንድ እንኳ ሊያስቡት የማይፈልጓት ሃቅ ነች::አንዴ የሥልጣንን ሥኳር ከላሡ ወዲህ ወደዛች ወንበር ዝር ያሉትን ሁላ አባቴ ነው:እናቴ ነች: ወንድሜ :እህቴ :ልጄ: ዘመዴ: ወዳጄ የክፉ ቀን ጓዴ ብለው ሳያመነቱ ከፍ ብለው አንገቱን ዝቅ ብለው ብልቱን ሊቆርጡለት ሢወስኑ ሁለቴ እንኳ አያስቡም::
  ከዚህ ጽሁፍ ጋር አያይዤ የለጠፍኩት የእነዚህ የሶስት ሰዎች ምስል የሀገር መሪ የሚለው የቀድሞ ማእረጋቸው ከላያቸው ተገፍፎ “የቀድሞው ፕሬዚደንት” የሚል ተቀጽላ ተለጥፎባቸዋል::እንዲያውም ሁለቱ “ሟቹ” እየተባሉ ይጠሩ ጀምረዋል:: “ሟቹ የየመን ፕሬዚደንት አሊ አብደላ ሳልህ:ሟቹ የሊቢያው ፕሬዚደንት ሙአመር ጋዳፊና የቀድሞው የግብጽ ፕሬዚደንት ሞሃመድ ሆስኒ ሙባረክ”::

  የአሊ አብደላ ሳልህ ነገርና ፍጻሜያቸው::

  ከቀናት በፊት የኳታሩ የዜና ማሰራጫ አልጀዚራ በእርስ በርስ ጦርነት እየታመሰች ያለችው የመንን ከሠላሣ አመታት በላይ የመሩዋትና በህዝብ አመጽ ሥልጣናቸውን የለቀቁት የቀድሞ ፕሬዚዳንቷ አሊ አብደላ ሣልህ በሁቲ አማጽያን እንደተገደሉ በሰበር ዜናው አስታወቀ::ሠውዬው እንደነ ጋዳፊ እንደ ጋማል አብዱል ናሥርና እንደነ መንግሥቱ ሀይለማርያም ሥልጣንን በአቁዋራጭ ነበር የያዙት::እንዴት ቢባል በታጣቂዎች በተገደሉት የሰሜን የመን ፕሬዚደንት አህመድ ቢን ሁሴን አል ጋህሲም ምትክ ወታደራዊ ካውንስል ሲቋቋም በቅድሚያ አባል ከዚያም በፓርላማው ምርጫ ፕሬዚደንት በመሆን ነው:: 
  በቱኒዝያ ተቀስቅሦ የአረብ ሀገራትን ከዳር እሥከዳር ያናወጠውና በፖለቲከኞቹ አጠራር "the arab spring"በመባል በሚታወቀው እንቅሥቃሤ ከተናጡ ሀገራት መካከል አንዱዋም የመን ነበረች::ሰሞኑን መገደላቸው የተነገረላቸው አሊ አብደላ ሳልህም የመን በአመጸኞቹ በምትናጥበት በአንዱ ቀን ሀገር አማን ብለው በቤተ መንግሥታቸው ውሥጥ ነበሩ::በፍጹም ባላሰቡት አጋጣሚም ከአማጽያኑ የተተኮሠባቸው አዳፍኔ አራት ጠባቂዎቻቸውን ሢገድል እርሣቸው የድመት ነብስ ይዘው ኖሮ በተአምር ተረፉ።ከዚያም የድምጽ መልእክት በመላክ በህይወት መትረፋቸውን ከገለጹ በኋላ በንጋታው ሳውዲ በሚገኘው የህክምና ማእከል ህክምና ተደርጎላቸው ለደጋፊዎቻቸውም ከፈንጂ የተረፈና ብረት ምጣድ መሥሎ የተለበለበ ፊታቸውን በከፊል ጠምጥመው “አለሁ እኖራለሁ እንተያያለን” ብለው እየፎከሩ ወደቲቪው ብቅ አሉ::ከወራት የህክምና ቆይታ በኋላም እንደ እባብ ቆዳቸውን ገፍፈው ጡንቻቸውን አደድረው ወንበሯን ገና መች ጠገብኳትና ብለው የስልጣናቸውን ብሎን ያጠባብቁ ጀመር::ሆኖም ግን የህዝብ ግፊቱ እየበዛባቸው መጥቶ ስልጣናቸውን ለምክትላቸው ሊያስረክቡ ተገደው ነበር::
  አሊ አብደላ ሣልህ የሚመሯት የመን ከሀገሬ ኢትዮጵያ በባሠ ድህነት እግሩን አንፈራጦ የሚኖርባት ሀገር ሆና ሣለ ሠውዬው ግን 70 ቢሊየን ዶላር (ልብ በሉልኝ ሠባ ቢሊየን ዶላር)በተለያዩ ሀገራት እንደቀረቀሩ ታውቆባቸው ነበር::ሙሠንነታቸው አምባገነንነታቸውና የመሪነት እጥረቱን ህዝቡ መቀበል እንዳቃተውና ግድያው እሥራቱ አፈናው የትም ድረሥ እንደማያሥኬዳቸው ያወቁት አሊ አብደላ በቅርቡ ሥልጣናቸውን ለቀውና ከሁቱ አማጽያን ጋር ይፋዊ በሆነ ስምምነት አብሮነታቸውን ገልጸው ሳውዲ መራሹን ጦር ሲመክቱ ኖሩ::በፖለቲካም ቋሚ ወዳጅ ዘላቂ ጠላት እንደሌለ ጠንቅቀው የሚያውቁት አሊ አብደላ ቆዩና ደግሞ “ከሁቲ አማጽያን ተገንጥያለሁ” ብለው ባወጁበት ሰሞን ነበር ከአጋሮቻቸው ከሁቲ አማጽያን ጋር መፋለም የጀመሩት::ከአሣዳጃቸው ሣውዲ አረብያ ጋር አብሬ ነኝ የሰላሙን መንገድ አብረን እንፈልጋለን ማለት በጀመሩ በሣምንቱም ባሣደጉት ውሻ ተነከሡ::
  በማህበራዊ ድረገጾች የተለቀቀው የአሊ አብደላ ሣልህ ቪድዬ ለማየት ከፍተኛ ድፍረትን የሚጠይቅ ነበር።እንዲያ በሚሄዱበት ሁላ ጋሻ ጃግሬያቸው አይኑን ከግራ ቀኝ እያንቀዠቀዠ እንዳላጀባቸውና መሬት እንዳላረገደችላቸው ቀይ ምንጣፍ እንዳልተነጠፈላቸው የግራ ጭንቅላታቸው ተገምሦ ሙሉ ልብሣቸውን እንደለበሡ በአበያ ጨርቅ ተጠቅልለው ሬሣቸው እንደ አህያ ሬሣ በየመንገዱ እየተጎተተ በመኪና ላይ ሢጫን ታየና የሰውየው ሞት ተረጋገጠ::

  ጋዳፊ...

  በአንድ ወቅት ወዳጅና ጓደኛ ሆነው በየስብሰባው ሲተቃቀፉ ይታዩ የነበሩትና እዚሁ ፎቶ ላይ ያሉት የሊቢያው መሪ ሞአመር ጋዳፊም ሥልጣን የያዙት እንደኛው ደርጎች የህዝቡን አመጽ በድንገት ቀልብሠው በአቁዋረጭ ነበር::ያን ግዜ ጋዳፊ ሥልጣን ሢይዝ ገና የሀያ ሠባት አመት ጎረምሣ ነበር..ይሄን የሊቢያ ነዳጅ እየሸጠ ያጠራቀመው ዶላር የልብ ልብ ሠጥቶት ሥልጣንን እንኩዋን ሊያሥረክብ የገዛ ህዝቡን በጥይት ሢረፈርፍ ኖረ:: የአረብ ሀገር አመጽ ሢነሣ  አማጽያኑን ጠርቶና አግባብቶ እንደመደራደር ወይም ሥልጣንን ቀሥ ብሎ እንደ ሙጋቤ እንደመልቀቅ "እነዚህ አይጦችና በረሮዎች" እያለ ሢሣደብ ላየ ሠው ፍጻሜው እንደ ውሻ ከትቦ ውሥጥ መጎተት ነው ያለ ማንም አልነበረም።

  ሙባራክ...

  የግብጹ ፕሬዚደንት መሀመድ ሆሥኒ ሙባረክም ቢሆን ሥልጣን እይዛለሁ ብሎ በህልሙም በውኑም ባላሠበው አጋጣሚ ነው ድንገት ከወንበሯ ላይ እመር ብሎ የተከመረው::.በአንድ የህዝባዊ ዝግጅት ላይ በአንድ አክራሪ እሥላም ወታደር የግብጹ ፕሬዚደንት አንዋር ሣዳትን በጥይት ሢገደል በትረ ሥልጣኑን የወቅቱ ምክትል ፕሬዚደንት ሆሥኒ ሙባረክ ያዘና ግብጽን እንዳሻው ሢገዛ ኖሮ ይሄው የአረብ ሀገራት አመጽ ሢቀሠቀሥ ልክ ሙጋቤ ከሥልጣን እንደወረደው አወራረድ ሣይታሠብ ሥልጣኑን ለቀቀና በተሽከርካሪ ቃሬዛ እየተጎተተ ፍርድ ቤት ለፍርድ ቤት መመላለሥ ቁርሥና ምሣው ሆነ።ከጋዳፊ ከአሊ አብደላና ከሆሥኒ ሙባረክ አወዳደቅ አንጻር የሆሥኒ ሙባረክ ከሥልጣን አወራረድ ፍጹም የተሻለና የከብር ነው ማለት ይቻላል:: ይሄም ምናልባት ከየመንና ከሊቢያ ህዝብ ይልቅ የግብጽ ጦርና ህዝብ ፍጹም የሠለጠነና ህዝባዊ ከመሆኑ አንጻር ሣይሆን አይቀርም::

  እኛና እነሱ...

  በተለያየ አጋጣሚዎች ዛሬ ላይ ከሥልጣናቸው የተወገዱት እነዚህ ሦሥት መሪዎች ከሀገራችን ኢትዮጵያ ጋር በክፉም በደግም የተቆራኘ አንዳንድ ገጠመኞችና ታሪክ አላቸው::

  ሙባረክና ግብጽ

  ግብጽ የኢትዬጵያ ታሪካዊ ጠላት ከመሆኑዋና በአባይ ወንዝ ዙሪያ ከዛሬ ነገ ይፈነዳል በሚባለው ጦርነት ሁሌም ሥትታወሥ ብትኖርም በ1980 ዎቹ አጋማሽ አማታት ለአፍሪካ ህብረት ሥብሠባ ወደ አዲሥ አበባ የመጡት የግብጹ ፕሬዚደንት ሆስኒ ሙባረክ በወቅቱ የአፍሪካ ቀንድን እቆጣጠራለሁ እያለ ሢደነፋ በነበረው አል ኢትሀድ አል ኢሥላሚያ ታጣቂዎች ቦሌ መንገድ ላይ አደገኛ የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸው ነበር።ሆኖም ጥይት የማይበሣውን መኪና በአንድ የደህንነት አማካሪያቸው ምክር አሥጭነው መጥተው ሢጉዋዙበት ሥለነበሩና ንቁ ጠባቂዎቻቸው አይናቸውን ሣያራግቡ ሢጠብቁዋቸው ሥለነበር እንዲሁም በየህንጻው ማማ ላይ ተሠቅለው የእንግዶችን ደህንነት ሢጠብቁ የነበሩት የኢትዮጵያ ነጥሎ ተኩዋሽ ወታደሮች ገዳዮቻቸውን ተኩሠው በመጣል ህይወታቸውን አትርፈውላቸዋል።

  ሊቢያና ጋዳፊ...

  ጋዳፊ መቼም ታሪካቸው ተነግሮ አያልቅም..በአንድ ወቅት ስድስት መቶ አጃቢዎቻቸውን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ እገባለሁ ያሉት ጋዳፊ ከወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሬዚደንት ከመንግሥቱ ሀይለማርያም የደህንነት ሠራተኞች ጋር ከፍተኛ ጸብ ገጥሞዋቸው እንደነበር ይነገራል።በወቅቱ የደርግ የደህንነት ሠራተኞች “ይሄን ያክል በኛ ጥበቃ አልተማመንም ካልክ ቀኝ ሁዋላ ዞረህ ወደሀገርህ ተመለስ” ብለው እንዳባረሩትና ከዚያም ሁዋላም ኢትዮጵያን ሣለ ደርግ እንዳልረጋጣት ይወራ ነበር።

  አሊ አብደላ ሳላህና የመን...

  አሊ አብደላ ሣላህ በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግሥት በጽኑ ሢፈልገው የነበረውንና የእድሜ ይፍታህ ፍርድ በሌለበት ፈርዶበት የነበረውን የግንቦት 7 ምክትል ሊቀመንበሩን አንዳርጋቸው ጽጌን ለትራንዚት ካረፈበት የመን አየር ማረፊያ በቁጥጥር ሥር አውሎት ለኢትዮጵያ መንግሥት እጁን ይዞ መሥጠቱ በወቅቱ ከፍተኛ ውዝግብ አሥነሥቶ ነበር::የመንግሥት ደጋፊዎች መንግሥት በሽብርተኝነት የፈረጀው አንዳርጋቸውን የመን አሣልፋ መሥጠቱዋ የምን ግዜም ወዳጃችን መሆኑዋን ያሣያል ሢሉ ታቃዋሚዎች በበኩላቸው ሀያ ሚሊዮን ዶላር ተቀብላ ከአቪዬሽን ህግ ውጪ እንግዳዋን አሣልፋ ሠጠች እያሉ ዛሬ ላይ የሞቱትን የየመኑን ፕሬዚደንት የእጃቸውን አገኙ እያሉ ሢያወሩ ተደምጠዋል።
  ያም ተባለ ያ ዛሬ ላይ ሦሥቱም ሥልጣናቸው ላይ የሉም ግዜ የሠጠን እኛ ይሄንን ሁላ ታሪክ ቁጭ ብለን እናያለን።አምባገነን መሪዎች ይሄንን አይነት አሠቃቂ አወራረድ እያዩ ለግፈኛ አገዛዛቸው ምክንያት መሥጠታቸውን አጫፋሪያቸውን መልካም ስማቸውን እያወደሱ ሲያስወሩ ፈጣሪ እስከፈቀደው ቀን ይኖራሉ። "እሱ እኮ በህዝብ ስላልተመረጠ ነው እኔን ህዝብ ይወደኛል መርጦኛል ህዝቤና ፓርቲዬ ይፈልገኛል" እና የመሣሠሉት ምክንያቶች መሠጠታቸውና ከሥልጣን ወንበር ላይ ተሠፍተው መክረማቸውን ይቀጥላሉ።ህዝብም ማሌቴ ቄል ፋሬሥ እያለ ማጉተምተሙን ይቀጥላል:: (ማኔ ማለት፥ እግዚአብሔር መንግሥትህን ቆጠረው ፈጸመውም ማለት ነው። ቴቄል ማለት፥ በሚዛን ተመዘንህ፥ ቀልለህም ተገኘህ ማለት ነው። ፋሬስ ማለት፥መንግሥትህ ተከፈለ፥ ለሜዶንና ለፋርስ ሰዎችም ተሰጠ ማለት ነው።) 
  ሀገር ለመሪው “ሚስቱ”: ሃገር ለህዝብ “እናቱ” የሆነች ይመስላል:: መሪው ሚስቴን እንዳሻኝ ባረጋት ማናባቱ ያዘኛል ምን የጎበረበት ይላል ::እንዳሻው ወዲህ ሂጅ ወዲህ ተመለሽ ይላል።ህዝብ ደሞ ሀገሩን እናቴ ነች ይላል ጥቃቱዋ መከፋቱዋ መበደሉዋ መነካቱዋ ያንገበግበዋል።ህዝብ አልቅሶ ሳያባራ የበቀል ሰይፉ ከአ ፎቱ መዝዞ የአምባገነን መሪዎቹን ሬሳ እንደ አህያ ሬሳ በየመንገዱ ሲጎትት እንደ ሆሊውድ ፊልም ማየት ስራችን ከሆነ ቆየ::ነገም ፍጻሜ መንግስታቸው የሚበሰር የበርካታ አምባገነን መሪዎችን ፍጻሜ ጊዜ ደጉ ጊዜ ጀግናው እንደማያሳየን ማን ያውቃል?

  ማንም!!


   


 • loader Loading content ...