loader
 • ስለኪሣራው አሠራር የሚደረግ ዘዴ ፤ ስምምነት (የ፲፱፻፶፪ ዓ.ም. የንግድ ሕግ አዋጅ ፥ አንቀጽ ፪ ፥ ምዕራፍ ፭ ፥ ምዕራፍ ፮ ፥ ክፍል ፩።)

  @በህግ አምላክ   3 months ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!
 • loader Loading content ...
 • @በህግ አምላክ   3 months ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!

  የ፲፱፻፶፪ ዓ.ም. የንግድ ሕግ አዋጅ። የኪሣራና የመጠበቂያ ስምምነት። አንቀጽ ፪። ስለ መክሠር። ምዕራፍ ፭። የገንዘብ መጠየቂያ መብቶችን ስለ መመርመር። ምዕራፍ ፮። ስለኪሣራው አሠራር የሚደረግ ዘዴ። ክፍል ፩። ስምምነት።


  ቁጥር ሺ፹፩። የስምምነት አሳብ ስለ ማቅረብ።
  (፩) በቁጥር ሺ፵፮ የተመለከተው ቀን ካለቀበት አንሥቶ በማናቸውም ጊዜ የከሠረው ነጋዴ ለገንዘብ ጠያቂዎቹ አንድ የስምምነት አሳብ ለማቅረብ ይችላል። ይኸውም አሳብ የሚቀርበው በተለይ ለመርማሪው ዳኛ ነው።
  (፪) በሚቀርበው አሳብ ውስጥ ዋስትና ለሌላቸው ገንዘብ ጠያቂዎች የሚሰጠው በመቶ ይህን ያህል የሚባለው ገንዘብና ባለዕዳው ለመክፈል እስከዚህ ቀን ይሁንልኝ ሲል የጠየቀው ግዜ ይጠቀሳል እከፍለለሁ ላለው ገንዘብና ለሥነ ሥርዐት ወጪና ለንብረት ጠባቂዎች ኪሣራ ማረጋገጫ እንዲሆን የሚሰጠውን ዋስትና መጥቀስ አለበት።
  (፫) ስለ ስምምነት የቀረበው አሳብ የሒሳብ ማጣራቱን ያግዳል።

  ቁጥር ሺ፹፪። የቀረበውን ስምምነት ስለ መመርመርና የተባለውን አሳብ ለገንዘብ ጠያቂዎች ስለ ማስታወቅ።
  (፩) የስምምነቱ አሳብ የቀረበለት መርማሪ ዳኛ የንብረት ጠባቂዎችንና የገንዘብ ጠያቂዎችን ኮሚቴ ሐሳብ ይቀበላል።
  (፪) የቀረበው አሳብ የሚገባ ነው ሲል የገመተ እንደ ሆነ፤ ዳኛው ገንዘብ ጠያቂዎቹ እንዲያውቁት በፍጥነት እንዲተላለፍላቸው ያዛል።
  (፫) ይህ ለገንዘብ ጠያቂዎች የሚላከው ማስታወቂያ በፍርድ ቤቱ መዝገብ ቤት ሹም በኩል ሆኖ ለያንዳንዱ ገንዘብ ጠያቂ በሚላከው በሬካማንዴ ደብዳቤ ይፈጸማል። ስለሆነም የገንዘብ ጠያቂዎቹ ብዛት ለያንዳንዱ ማስታወቂያ ለመላክ የማይፈቀድ በሚሆንበት ጊዜ ፍርድ ቤቱ፤ የንብረት ጠባቂዎቹን እና የሕግ አስከባሪውን አሳብ ከሰማ በኋላ ለመርማሪው ዳኛ ስለ ስምምነቱ የቀረበው አሳብ የሕግ ማስታወቂያዎችን ለመቀበል በተፈቀደለት ጋዜጣና በንግድ ኦፊሲዬል ጋዜጣ እንዲወጣ ለማዘዝ ይፈቅድለታል።
  (፬) ማስታወቂያውም፤ የከሠረው ነጋዴ ካቀረበው አሳብ በላይ ንብረት ጠባቂዎቹና የገንዘብ ጠያቂዎቹ ኮሚቴ የሰጡትን አሳብ ያመለክታል። በመክሠር አሠራር ሁኔታ፤ በተፈጸሙት ሥርዐቶችና በተደረጉት ሥራዎች ላይ ንብረት ጠባቂዎቹ ያቀረቡት መግለጫ ከዚህ ማስታወቂያ ጋራ ይያያዛል።
  (፭) ስለስምምነቱ በተላለፈው ማስታወቂያ ውስጥ ከሓያ ቀን የማያንስ ከ፴ቀን የማይበልጥ ጊዜ ለገንዘብ ጠያቂዎቹ ይወሰናል። በዚሁም ጊዜ ውስጥ በሐሳቡ ያልተስማሙት ገንዘብ ጠያቂዎች የከሠረው ሰው ያቀረባቸውን አሳቦች ያለመቀበላቸውን ለፍርድ ቤቱ መዝገብ ቤት ማስታወቅ አለባቸው።

  ቁጥር ሺ፹፫። ገንዘብ ጠያቂዎች ስለሚሰጡት ድምፅ።
  (፩) የሚሰጠው ድምፅ በፕሮሴቬርባል ተጽፎ መርማሪው ዳኛና የፍርድ መዝገብ ቤት ሹም ይፈርሙበታል።
  (፪) በውለታ ወይም ለጊዜው የተቀበሏቸው ቢሆንም፤ መብታቸው በአገባብ የታወቀላቸው ገንዘብ ጠይቂዎች ሁሉ የድምፅ መስጠት መብት አላቸው።
  (፫) ልዩ ማረጋገጫዎች ያሏቸው ገንዘብ ጠያቂዎች፤ የቀረበውን የስምምነት አሠራር በሚመለከተው ጉዳይ ስላላቸው መብት ድምፅ ለመስጠት የሚችሉት ማረጋገጫቸውን የለቀቁ እንደ ሆነ ነው። ስምምነቱ ሳይደራጅ ወይም ፍርድ ቤቱ ሳያጸድቀው የቀረ፤ ወይም የተሰረዘ ወይም የፈረሰ እንደ ሆነ፤ ማረጋገጫቸውን መልቀቃቸው ቀሪ ይሆናል።
  (፬) የከሠረው ሰው ባል ወይም ሚስት፤ እስከ አራት ቤት የሚቆጠሩ የሥጋ ወይም የጋብቻ ዘመዶች እና እንዲሁም የመክሠሩ ማስታወቂያ ከተነገረበት ጊዜ አስቀድሞ በአንድ ዓመት ውስጥ ከነዚሁ ሰዎች መብት የተላለፈላቸው ወይም የገዙ ሰዎች ድምፅ ለመስጠትና ከድምፅ ብልጫው ቁጥር ውስጥ ለመግባት አይችሉም።
  (፭) የመክሠሩ ማስታወቂያ ፍርድ ከወጣ በኋላ የተደረጉት የገንዘብ ጠያቂዎችን መብት ማስተላለፍ የድምፅ መስጠትን መብት አይሰጡም።

  ቁጥር ሺ፹፬። ስምምነቱን ስለማጽደቅ።
  (፩) ስምምነቱ ውድቅ እንዳይሆን፤ ከዕዳው ከሦስት ሁለት እጅ ባላቸው የንዘብ ጠያቂዎች ድምፅ ብልጫ እንዲጸድቅ ያስፈልጋል። ይሁን እንጂ፤ ድምፅ በሚሰጥበት ጊዜ ያልነበሩት ሰዎች በድምፅና በገንዘብ ብልጫው አቆጣጠር ውስጥ አይገቡም።
  (፪) የከሠረው ሰው ያቀረበውን የስምምነት አሳብ አንቀበልም ሲሉ፤ በቁጥር ሺ፹፪ ንኡስ ቁ (፭) በተመለከተው ጊዜ ውስጥ ያላስታወቁ ገንዘብ ጠያቂዎች ስምምነቱን እንደ ተቀበሉ ይቆጠራሉ።
  (፫) ይህ የተነገረው ጊዜ ካለፈ በኋላ ከሚሰጠው ውሳኔ የተነሣ መብታቸውን የተቀበሏቸው የንዘብ ጠያቂዎቹ ቁጥር ወይም የሚጠይቁት ገንዘብ ልክ ቢለዋወጥም የድምፅ ብልጫውን አቆጣጠር አይለውጠውም።

  (፬) የድምፅ መስጠትን ውጤት በቁጥር ሺ፹፫ ንኡስ ቁ (፩) በተመለከተው ፕሮሴቬርባል ላይ መርማሪው ዳኛ ያረጋግጠዋል።ቁጥር ሺ፹፭። ስምምነቱን ስለ መቃወም።
  (፩) በስምምነቱ ውስጥ ለመግባት መብት የነበራቸው ወይም ከዚያ ወዲህ መብታቸው የታወቀላቸው ገንዘብ ጠያቂዎች ሁሉ በስምምነቱ ላይ መቃወሚያ ለማቅረብ ይችላሉ።
  (፪) ተቃዋሚነቱ ምክንያት ያለው መሆን አለበት። መቃወሚያው ምክንያት ካልተሰጠበትና ድምፅን በተሰጠበት በስምንት ቀኖች ውስጥ ለባለዕዳውና ለንብረት ጠባቂዎቹ ካልተላለፈላቸው ፈራሽ ይሆናል። ይኸውም መቃወሚያ በፍርድ ቤቱ መጀመሪያ ችሎት ለመቅረብ ጥሪ ይኖረዋል።

  ቁጥር ሺ፹፮። ስምምነቱን ስለ ማጽደቅ።
  ማናቸውም ጥቅም ያለው ወገን ፍርድ ቤቱ ስምምነቱን እንዲያጸድቀው ጥያቄ ለማቅረብ ይችላል። የሆነ ሆኖ ፍርድ ቤቱ በቁጥር ሺ፹፭ ከተወሰኑት ስምንት ቀኖች በፊት ለመወሰን አይችልም።
  (፪) በዚህ በተባለው ጊዜ ውስጥ መቃሚያዎች ቀርበው እንደ ሆነ ፍርድ ቤቱ ስለነዚህ መቃሚያዎችና እንዲጸድቅ ስለ ቀረበው ጥያቄ ባንድ ፍርድ ይወሰናል።
  (፫) ስለ ስምምነቱ መጽደቅ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ፍርድ ቤቱ የሚከተሉትን መመልከት አለበት፡-
  (ሀ) መርማሪው ዳኛ ስለ መክሠሩ አሠራርና ስምምነቱ ሊፈቀድ የሚችል ስለ መሆኑ ለፍርድ ቤቱ የሚያቀርበውን መግለጫ እና፤
  (ለ) ንብረት ጠባቂዎቹ በቁጥር ሺ ፹፪ ንኡስ ቁጥር (፬) መሠረት የሚያቀርቡትን መግለጫ እና፤
  (ሐ) ያለም እንደ ሆነ ከከሠረው ሰው ጋራ በጋራ ተገዳጅ የሆኑት ሰዎች የሚያቀርቡትን ማስገንዘቢያ።
  (፬) መቃወሚያውንም ፍርድ ቤቱ የተቀበለው እንደ ሆነ፤ ስምምነቱ ባለጉዳዮች በሆኑት ሰዎች በኩል ሁሉ ፈራሽ መሆኑን ይወስናል።

  ቁጥር ሺ ፹፯። ስምምነቱን ለማጽደቅ ስላለመቀበል።
  ፍርድ ቤቱ ስምምነቱን የማያጸድቀው፤
  (ሀ) ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት ደንቦች ያልተፈጸሙ እንደ ሆነ፤ ወይም
  (ለ) ስምምነቱን ማጽደቅ የሕዝብን ወይም የገንዘብ ጠያቂዎቹን ጥቅም የሚቃወም የሆነ እንደ ሆነ ነው።
  ቁጥር ሺ ፹፰። የስምምነቱን አፈጻጸም ስለ መጠባበቅ።
  (፩) ከስምምነቱ መጽደቅ በኋላ መርማሪው ዳኛ፤ ንብረት ጠባቂዎቹና የገንዘብ ጠያቂዎች ኮሚቴ ስለ ስምምነቱ መጽደቅ በተሰጠው ፍርድ በተወሰኑት አደራረጎች መሠረት የስምምነቱን መፈጸም ይጠባበቃሉ።
  (፪) የስምምነቱ ውለታዎች ከተፈጸሙ በኋላ የገንዘብ ጠያቂዎች ኮሚቴ ለኅብረቱ የተሰጠው የመያዣ መብት እንዲነሣ ለመፍቀድ ሥልጣን አለው።

  ቁጥር ሺ ፹፱። ስለ ስምምነቱ ውጤቶች።
  (፩) የንብረት መያዣ ካላቸውና መያዣቸውንም ካልለቀቁት ገንዘብ ጠያቂዎች፤ እንዲሁም መብታቸውን ያገኙት የመክሠሩ አሠራር በሚፈጸምበት ጊዜ ከሆኑት መያዣ ከሌላቸው ገንዘብ ጠያቂዎች በቀር የስምምነት መጽደቅ ገንዘብ ጠያቂዎችን ሁሉ ያስገድዳል።
  (፪) በቁጥር ሺ፮ መሠረት በከሠረው ሰው የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ላይና፤ እንዲሁም በቁጥር ሺ፯ መሠረት በንግዱ ላይ ለገንዘብ ጠያቂዎቹ ያላቸው በኅብረቱ ስም የተመዘገበውን የመያዣ መብት፤ የስምምነቱ መጽደቅ አይለውጠውም። ስለዚህ፤ ንብረት ጠባቂዎቹ ስለ ስምምነቱ መጽደቅ የተሰጠውን ፍርድ ሥልጣን ባለው መሥሪያ ቤት ያስመዘግቡታል።
  (፫) ስምምነቱ ቢኖርም ቅሉ፤ ገንዘብ ጠያቂዎቹ ስለሚጠይቁት ሙሉ ገንዘብ በባዕዳው የጋራ ተገዳጆች ላይ ያላቸውን የክስ ማቅረብ መብት እንደ ያዙ ይቆያሉ።

  ቁጥር ሺ፺ ስለ መክሠሩ ሙጤቶች መቅረት።
  (፩) ስለ ስምምነቱ መጽደቅ የተሰጠው ፍርድ የመጨረሻ ፍርድ በሆነ ጊዜ፤ ወዲያው ስለ መብት እጦት በቁጥር ሺ፳፪ የተጻፈው ቃልና ለስምምነቱ እፈጻጸም በቁጥር ሺ፹፰ የተደነገጉት ድንጋጌዎች እንደ ተጠበቁ ሆነው፤ የመክሠሩ ውጤቶች ይቀራሉ።
  (፪) ንብረት ጠባቂዎቹ፤ በመርማሪው ዳኛና በገንዘብ ጠያቂዎች ኮሚቴ ፊት፤ ለባለዕዳው የመጨረሻውን ሒሳብ ያስረክባሉ። በዚህም ሒሳብ ክርክር ከተደረገበት በኋላ ሒሳቡን ያቆማሉ። ለባለዕዳው፤ ንብረቶቹን፤ መዝገቦቹን፤ ወረቀቶቹንና ዕቃዎቹን በሙሉ ይመልሳሉ። ባለዕዳውም ደረሰኝ ይሰጣቸዋል። ባለዕዳው ሳይረከባቸው ቢቀር ንብረት ጠባቂዎቹ የመጨረሻውን ሒሳብ ካሰናዱበት ጊዜ አንሥቶ ለሁለት ዓመት ብቻ ኅላፊዎች ይሆናሉ።
  (፫) ለዚህ ሁሉ መርማሪው ዳኛ አንድ ፕሮሴቬርቫል ያዘጋጃል። ክርክር በሚነሣበት ጊዜ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ይሰጥበታል።

  ቁጥር ሺ ፺፩። ከጸደቀ በኋላ ስለ ስምምነቱ መፍረስ።
  (፩) ከስምምነቱ መጽደቅ ወዲህ በተገለጸው ተንኰል ምክንያት ካልሆነና፤ ተንኰሉም የተገኘውን ሀብት ከመደበቅ ወይም ዕዳውን ከማጋነን የተፈጠረ ካለሆነ በቀር፤ ስምምነቱ ከጸደቀ በኋላ እንዲፈርስ የሚቀርበው ማናቸውም ክስ አይሰማም። ይኸንንም ክስ አንድ ገንዘብ ጠያቂ ራሱ ሊያቀርበው ይችላል። ነገር ግን ሊቀርብ የሚችለው፤ ተንኰሉ በተገለጸ በአምስት ዓመት ውስጥ ብቻ ነው።
  (፪) የከሠረው በተንኰል ነው የሚል ፍርድ የተሰጠ እንደ ሆነ፤ የተደረገው ስምምነት ፈራሽ ይሆናል። ይኸውም የስምምነቱ መፍረስ ለተንኰሉ ግብረ አበሮች ከሆኑት በቀር፤ ዋሶቹን ሁሉ በደንብ ነጻ ያወጣቸዋል።

  ቁጥር ሺ ፺፪። ከስምምነቱ መጽደቅ በኋላ፤ በተገለጸው ተንኰል ምክንያት ክስ በሚቀርብበት ጊዜ ስለሚደረጉ መጠባበቂያዎች።
  (፩) ከስምምነቱ መጽደቅ በኋላ፤ ባለዕዳው በተንኰል መክሠር ተከሶ የተቀጣ እንደ ሆነ፤ ፍርድ ቤቱ አስፈላጊ መስለው የታዩትን የመጠባበቂያ ሥራዎች ለማዘዝ ይችላል።
  (፪) እነዚሁ አስፈላጊ ሥራዎች የሚያስከስስ ነገር የለውም ከተባለበት ቀን ወይም የከሠረው ሰው በነጻ ከተለቀቀበት ጊዜ ጀምሮ በደንብ ይቀራሉ።

  ቁጥር ሺ ፺፫። ስምምነቱን ስለ መሰረዝ።
  (፩) ባለዕዳው የስምምነቱን ውለታዎች ያልፈጸመ እንደ ሆነ፤ ያሉም እንደ ሆነ፤ ዋሶች ባሉበት ወይም በሚገባ ከተጠሩ በኋላ፤ ስምምነቱ እንዲፈርስ ለፍርድ ቤቱ ለማመልከት ይቻላል።
  (፪) ስምምነቱ በሙሉ ወይም በከፊል እንዲፈጸመ ዋስ የሆኑትን ሰዎች የስምምነቱ መፍረስ ነጻ አያወጣቸውም።

  ቁጥር ሺ ፺፬።ስምምነቱ ከተሰረዘ ወይም ከፈረሰ በኋላ የመክሠሩን አሠራር እንደገና ስለ መቀበል።
  (፩) ስምምነቱ የተሰረዘ ወይም የፈረሰ እንደ ሆነ፤ አስቀድሞ በተጻፈው የዕቃ ዝርዝር መዝገብ መሠረት፤ ንብረት ጠባቂዎቹ ሳይዘገዩ፤ እሽጎችም እንዳሉ ያሸገው ባለሥልጣን እየረዳቸው የተቆጠሩትን ባለዋጋ የሆኑትን ዕቃዎችና ወረቀቶችን ማረጋገጥ ይጀምራሉ። አስፈላጊ ሲሆኑም ተጨማሪ የዕቃ ዝርዝር መዝገብና የሒሳብ ሚዛን ያዘጋጃሉ።
  (፪) ወዲያውም በፍጥነት፤ ስለዚሁ የተፈረደውን ፍርድ ቅጅና፤ አዲስ ገንዘብ ጠያቂዎችም እንዳሉ፤ ገንዘብ የሚጠይቁባቸውን ሰነዶች፤ በቁጥር ሺ፵፫ በተመለከቱት ሁታዎች መሠረት ለምርመራ እንዲያቀርቡ በማሳሰብ ማስታወቂያ ያወጣሉ።

  ቁጥር ሺ ፺፭። የቀረቡትን አዲስ የንዘብ መጠየቂያ መብቶች ስለ መመርመር።
  (፩) በቁጥር ሺ፺፬ በተመለከተው መሠረት የቀረቡትን የገንዘብ መጠየቂያ ሰነዶች ንብረት ጠባቂዎች ይመረምራሉ።
  (፪) አስቀድሞ ተቀባይነት አግኝተው ስለነበሩት የገንዘብ መጠየቂያ መብቶች አዲስ ምርመራ አይደረግም። ይሁን እንጂ፤ ከዚያ ወዲህ በሙሉ ወይም በከፊል የተከፈሉትን ያለመቀበል ወይም የመቀነስ መብት ሳይነካ ነው።

  ቁጥር ሺ ፺፮። ስምምነቱ ከጸደቀ በኋላ ባለዕዳው ስላደረጋቸው ውሎች።
  ስምምነቱ በፍርድ ከመጽደቁ በኋላና ከስምምነቱ መሰረዝ ወይም መፍረስ በፊት ባለዕዳው ያደረጋቸው ውሎች፤ በገንዘብ ጠያቂዎች መብት ላይ ተንኰል በማድረግ ካልሆነ በቀር ፈራሽ አይሆንም።

  ቁጥር ሺ ፺፯። ከስምምነቱ አስቀድሞ ስላሉት የገንዘብ ጠያቂዎች መብት።
  ከስምምነቱ በት የነበሩት ገንዘብ ጠያቂዎች ባለዕዳውን ብቻ በሚመለከት ጉዳይ፤ ሙሉ መብታቸውን እንደገና መልሰው ይይዛሉ፤ ነገር ግን ከዚህ በታች በተመለከቱት መጠኖች ካልሆነ በቀር፤ ከኅብረቱ ውስጥ ለማግኘት አይችሉም። ይኸውም፤
  (ሀ) እንዲከፈላቸው ከጠየቁት ገንዘብ ምንም ድርሻ ያልወሰዱ እንደ ሆነ ለሚጠይቁት ገንዘብ በሙሉ፤
  (ለ) ገንዘብ ጠያቂዎች ከሚገባቸው ድርሻ በከፊል ተቀብለው እንደ ሆነ በሚቀራቸው ድርሻ ልክ ነው።

  ቁጥር ሺ ፺፰። ከስምምነቱ በኋላ አዲስ ለሆኑት ገንዘብ ጠያቂዎች ገንዘባቸው ባለመከፈሉ ምክንያት ሁለኛ ስለሚደረግ የመክሠር ማስታቂያ።
  ስምመነቱ ሳየሰረዝ ወይም ሳይፈርስ ከስምምነቱ በኋላ አዲስ የመጡት ገንዘብ ጠያቂዎች ይከፈለን የሚሉት ገንዘብ ሳይከፈላቸው በመቅረቱ ምክንያት ሁለተኛ የኪሣራ ማስታወቂያ የሚያስፈልግ ሲሆን፤ በፊተኛው የኪሣራ ማስታወቅ ጊዜ የነበሩት ገንዘብ ጠያቂዎች ይሆናሉ። ነገር ግን ከዚህ ጠያቂነታቸው የተነሣ አዲሶቹን ጠያቂዎች በሚመለከት ነገር ምንም ብልጫ አለን ለማለት አይችሉም፤ በቁጥር ሺ፺፯ የተወሰኑትም ድንጋጌዎች ይፈጸሙባቸዋል።

  ቁጥር ሺ ፺፱። ንብረትን በመልቀቅ ስለሚደረግ ስምምነት።
  (፩) የከሠረው ሰው ያለውን ንብረት በሙሉ ወይም በከፊል በመልቀቀ ስምምነት ሊያግድ ይችላል። ይህ የባለው ስምምነት፤ ልክ ለመደበኛው ስምምነት የሚሰጡትን ደንቦች በመከተል ይፈጸማል። የሚሰጣቸውም ውጤቶች እንደነዚያው ያሉ ውጤቶች ናቸው። የማሰረዘውም የሚፈርሰውም መደበኛው ስምምነት በሚሰረዝባቸውና በሚፈርስባቸው ምክንያቶች ነው።
  (፪) የተለቀቀውንም ንብረት የማጣራት ሥራ በቁጥር ሺ)1 እና በተከታዮቹ በተጻፈው መሠረት ይፈጸማል።
  (፫) ያለውን ንብረት በመልቀቅ የሚደረገው ስምምነት፤ በተለቀቀው ንብረት ውስጥ ያልገቡትንና የከሠረው ሰው በኋላ የሚያገኛቸው ንብረቶች እንዳይያዙ ያደርጋል።
  (፬) ስምምነቱ ቢኖርም ቅሉ፤ ገንዘብ ጠያቁዎቹ ከባለዕዳው በጋራ ተገዳጅ በሆኑት ሰዎች ላይ ያላቸው መብታቸውን እንደ ያዙ ይቆያሉ።

  ቁጥር ሺ፻። በንግድ መዝገብ ስለ መግባት።
  ስምምነቱ የጸደቀበት ወይም የፈረሰበት ወይም የተሰረዘበት ፍርድ በቁጥር ፱፻፹፫ (፬) በተደነገገው መሠረት የፍርድ መዝገብ ቤቱ ሹም በንግድ መዝገብ መግባታቸውን ማረጋገጥ አለበት።

  ምንጭ:
  የ፲፱፻፶፪ ዓ.ም. የንግድ ሕግ
 • loader Loading content ...

Load more...