loader
 • በግዴታ የሚሆን የንብረት ማጣራት (የ፲፱፻፶፪ ዓ.ም. የንግድ ሕግ አዋጅ ፥ አንቀጽ ፪ ፥ ምዕራፍ ፭ ፥ ምዕራፍ ፮ ፥ ክፍል ፪።)

  @በህግ አምላክ   3 months ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!
 • loader Loading content ...
 • @በህግ አምላክ   3 months ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!

  የ፲፱፻፶፪ ዓ.ም. የንግድ ሕግ አዋጅ። የኪሣራና የመጠበቂያ ስምምነት። አንቀጽ ፪። ስለ መክሠር። ምዕራፍ ፭። የገንዘብ መጠየቂያ መብቶችን ስለ መመርመር። ምዕራፍ ፮። ስለኪሣራው አሠራር የሚደረግ ዘዴ። ክፍል ፪። በግዴታ የሚሆን የንብረት ማጣራት።


  ቁጥር ሺ፻፩። ስምምነቱን ያለመቀበል ስለሚያስከትላቸው ውጤቶች።
  ስለ ስምምነቱየቀረበው አሳብ ቁጥር ሺ፹፬ የሚያስገድደውን ዕጥፍ የሆነውን የድምፅ ብልጫ ያላገኘ እንደ ሆነ፤ ንብረቱ በግድ እስኪሸጥና ገንዘብ ጠያቂዎቹም የሽያጩን ድርሻ ጨርሰው እስኪከፋፈሉ ድረስ የመክሠሩ ሥራዎች ሳያቋርጡ ይቀጥላሉ።

  ቁጥር ሺ፻፪። ለከሠረው ሰው ስለሚደረገው ዕርዳታ።
  ከሚከፋፈለው ንብረት ላይ ለከሠረው ሰው ወይም ለቤተሰቡ ርዳታ ለመስጠት ይቻል እንደ ሆነ፤ ለማወቅ መርማሪው ዳኛ የገንዘብ ጠያቂዎቹን ኮሚቴ ያማክራል። ኮሚቴው አሳቡን በመልካም የተቀበለው እንደ ሆነ፤ መርማሪው ዳኛ ንብረት ጠባቂዎቹ ባቀረቡት አሳብ መሠረት የተፈቀደውን ርዳታ ልክ ይወስናል።

  ቁጥር ሺ፻፫። ስለ ንብረቱ ማጣራት ሥራዎች።
  (፩) ንብረት ጠባቂዎቹ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዐት ሕግ መሠረት የባለዕዳውን የሚንቀሳቀሱትንና የማይንቀሳቀሱትን ንብረቶች ይሸጣሉ። ባለዕዳውም ለነዚህ ሥራዎች መጠራት የለበትም።
  (፪) ከሽያጩም የተገኘው ገንዘብ በቁጥር ፱፻፺፮ በተመለከተው መሠረት ይቀመጣል።
  (፫) ንብረት ጠባቂዎቹ ባለዕዳው ሳይጠራ፤ በቁጥር ሺ፴፰ እንደተመለከተው ስለማንኛውም ዐይነት፤ የባለዕዳውን መብቶች የሚመለከቱ ስምምነቶችንና ግልግሎችን ለማድረግ ይችላሉ።

  ቁጥር ሺ፻፬። የማይንቀሳቀሱትን ንብረቶች ስለ መሸጥ።
  ግደታ የሆነው ማጣራት ከመከፈቱ በፊት የተጀመረ የማይንቀሳቀሱትን ንብረቶች የማስለቀቅ ሥራ የሌለ እንደ ሆነ፤ የመሸጥን ሥራ ለመሥራት የሚችሉት ንብረት ጠባቂዎች ብቻ ናቸው። እነርሱም በመርማሪው ዳኛ ፈቃድ በስምንት ቀን ውስጥ ሥራውን ለመጀመር ይገደዳሉ።

  ቁጥር ሺ፻፭። የንግድ መደብርን ስለ መሸጥ።
  የነጋዴው ንብረት በፍርድ ቤት እንዲጣራ ከመደረጉ በፊት የንግድ መደብሩ አንዲያዝ የታዘዘ ካልሆነ በቀር፤ የንግድ መደብሩ እንዲሸጥ የሚያስፈልገውን ለማድረግ የሚችሉት ንብረት ጠባቂዎች ብቻ ናቸው። እነሱም በመርማሪው ዳኛ ፈቃድ፤ በቁጥር ሺ፩፻፮ የተመለከተው እንደ ተጠበቀ ሆኖ የንግዱን መደብር ለመሸጥ ይችላሉ።

  ቁጥር ሺ፻፮። በማጣራቱ ጊዜ ሥራውን ስለ መቀጠል።
  (፩) ዋስትና የሌላቸው ገንዘብ ጠያቂዎች መክሠሩ በሚጠራበት ጊዜ ሥራውን እንዲቀጥሉ ለንብረት ጠባቂዎች ውክልናቸውን ሊሰጡ ይችላሉ።
  (፪) ስለዚህ ጉዳይ በገንዘብ ጠያቂዎቹ ኮሚቴ አሳሳቢነት፤ መርማሪው ዳኛ ገንዘብ ጠያቂዎቹ በሬኮማንዴ ደብዳቤ አሳባቸውን ይጠይቃቸዋል። ከብዛታቸው የተነሣ ለያንዳንዱ ገንዘብ ጠያቂ ማስታወቂያ ለመላክ ያልቻለ እንደ ሆነ በቁጥር ሺ፹፪ ንኡስ ቁ (፫) የተጻፉት ድንጋጌዎች ይፈጸማሉ።
  (፫) ገንዘብ ጠያቂዎቹ ድምፃቸውን ለፍርድ መዝገብ ቤት በዐሥራ አምስት ቀን ውስጥ መስጠት እንዳለባቸው ይነግራቸዋል።
  (፬) ገንዘብ ጠያቂዎቹም የሥራው መቀጠል የሚቆይበትን ጊዜና የሥራውን ወሰን ይወስናሉ። እንዲሁም ለወጪዎችና ኪሣራዎች መክፈያ የሚሆን በንብረት ጠባቂዎች እጅ የሚቆየውን የገንዘብ ልክ ይወስናሉ። ውሳኔውም በቁጥርና በገንዘብ ሦስት ሩብ የሆነ አጠፌታ የድምፅ ብልጫ ያለው እንዲሆን ያስፈልገዋል። ይህንንም የሚያጸድቀው የመርማሪው ዳኛ ትእዛዝ ነው።

  ቁጥር ሺ፻፯። ያለውን ጠቅላላ ሀብት በአንደዜ ስለ መሸጥ።
  (፩) ፍርድ ቤቱ፤ መርማሪው ዳኛ የሚለውን ሰምቶ ያለውን ንብረት በከፊል ወይም በሙሉ ተንቀሳቃሽ እና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን በቁጥር ዋጋ ባንደዜ እንዲሸጡዋቸው ለንብረት ጠባቂዎቹ ሊፈቀድላቸው ይችላል።
  (፪) የገንዘብ ጠያቂዎቹ ኮሚቴ ወይም ባለዕዳው በሚያቀርበው ጥያቄ ይህን ፈቃድ ለመስጠት ይቻላል።
  (፫) በሁለቱም ጊዜ ለሚቀርበው ጥያቄ በቁጥር ሺ፻፮ ንኡስ ቁ ፬ በተደነገጉት ሁናቴዎች መሠረት ገንዘብ ጠያቂዎች አሳባቸውን ይጠየቃሉ፤ የሰጡትም ድምፅ በቁ ሺ፻፮ ንኡስ ቁ ፬ መሠረት በቁጥርም ሆነ በገንዘብ ከአራት እጅ የሆነ አጠፌታ የድምፅ ብልጫ ያለው እንዲሆን ያስፈልጋዋል።
  (፬) የውሎን ዕቅድ ፍርድ ቤቱ እንዲያጸድቀው ያስፈልጋል።
  (፭) ውሉም የጸደቀ እንደ ሆነ፤ በኅብረቱ በኩል ባለዕዳውን ነጻ ያደርገዋል።

  ቁጥር ሺ፻፰። ከሚጣራው ንብረት ስለሚበልጡ ግዴታዎች።
  የንብረት ጠባቂዎች ሥራዎች በመጣራት ላይ ካለው ንብረት በላይ የሆኑት ግዴታዎች ያስከተሉ እንደ ሆነ፤ በድምር መስጠት ሥራዎቹን የፈቀዱት ገንዘብ ጠያቂዎች ብቻ በንብረቱ ውስጥ ከሚደርሳቸው ድርሻ በላይ ለሆነው ገንዘብ ራሳቸው አላፊዎች ናቸው። ይኸውም የሚሆነው በሰጡት ሥልጣን መጠን ነው። በሚገባቸውም ገንዘብ መጠን በግዴታዎቹ ተካፋይ ይሆናሉ።

  ቁጥር ሺ፻፱። ስለ አከፋፈሉ ድርጅት።
  (፩) በቁጥር ሺ፵፮ የተመለከተው ጊዜ ካለፈ አንሥቶ ንብረት ጠባቂዎቹ በየሁለቱ ወር የኪሣራውን ሁኔታ የሚያስረዳ መግለጫና በቁጥር ፱፻፺፮ መሠረት የተቀመጠውን ገንዘብ ዝርዝር ለመርማሪው ዳኛ ያስረክባሉ።
  (፪) የነዚህንም ገንዘቦች አከፋፈል ድርጅት ለዳኛው ያቀርባሉ።
  (፫) ዳኛውም የገንዘብ ጠያቂዎቹን ኮሚቴ ካማከረ በኋላ ጠቃሚ መስሎ የታየውን ማሻሻል በክፍያው ድርጅት ላይ አስፍሮ የተሻሻለው ድርጅት በፍርድ መዝገብ ቤት እንዲቀመጥ ያዛል። የድርጅቱንም መቀመጥ ገንዘብ ጠያቂዎቹ እንዲያውቁት ያደርጋል።
  (፬) ገንዘብ ጠያቂዎቹም ማስታቂያው ከተሰጣቸው በዐሥር ቀን ውስጥ ስለድርጅቱ አስተያየታቸውን ለማቅረብ ይችላሉ። ይህ የተባለው ጊዜ ሲያልፍ መርማሪው ዳኛ ማስገንዘቢያዎቹን ተመልክቶ ክፍያውን የሚወስን ትእዛዝ ይሰጣል።

  ቁጥር ሺ፻፲። ከማጣራቱ የተገኘውን ገንዘብ ስለ ማከፋፈል።
  ከማጣራቱ ከተገኘው ገንዘብ፤
  (ሀ) ለመክሠሩ አሠራር የወጣው ኪሣራና የተደረገው ወጪ ገንዘብ፤
  (ለ) እንዳለም፤ ለባለዕዳውና ለቤተሰቡ የተደረገው ርዳታ፤
  (ሐ) ልዩ መብት ላላቸው ገንዘብ ጠያቂዎች የተከፈለው ገንዘብ ከተቀነሰ በኋላ የሚቀረውን ገንዘብ በቁጥር ሺ፷፭– ሺ፷፮ እና ሺ፷፰ የተመለከተው እንደ ተጠበቀ ሆኖ ገንዘብ ጠያቂዎቹ ሁሉ በተረጋገጠላቸውና ተቀባይነት ባገኘው መብታቸው መጠን ይከፋፈሉታል።

  ቁጥር ሺ፻፲፩። ክርክር ያለባቸውን የገንዘብ መብቶች ድርሻ ጠብቆ ስለ ማቆየት።
  ተቀባይነት ስለ ማግኘታቸው ገና የመጨረሻ ውሳኔ ያልተሰጣቸው መብቶች ድርሻ ተጠብቆ ይቀመጣል።

  ቁጥር ሺ፻፲፪። ስለ አከፋፈሉ ሥርዐት።
  (፩) ንብረት ጠባቂዎቹ በቁጥር ፱፻፺፮ ድንጋጌዎች መሠረት በኪሣራው ስም ለመክፈሉ አሠራር ከተከፈተው ሒሳብ ላይ መብቱ ተቀባይነት ላገኘው ለያንዳንዱ ገንዘብ ጠያቂ ለሚደርሰው ክፍያ በስሙ የተጻፈ ቼክ ይልኩለታል።
  (፪) የተከፈለው ገንዘብ ገንዘብ ጠያቂው ባቀረበው ሰነድ ላይ ይጻፋል። ነገር ግን ሰነዱን ለማቅረብ በማይቻልበት ጊዜ መርማሪው ዳኛ የተቀመጠውን የዕዳ ሁኔታ የሚገልጸውን ፕሮሴቬርባል ተመልክቶ ክፍያውን ለመፍቀድ ይችላል።

  ምንጭ:
  የ፲፱፻፶፪ ዓ.ም. የንግድ ሕግ
 • loader Loading content ...

Load more...