loader
 • የመጠበቂያ ስምምነት (የ፲፱፻፶፪ ዓ.ም. የንግድ ሕግ አዋጅ ፥ አንቀጽ ፫።)

  @በህግ አምላክ   3 months ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!
 • loader Loading content ...
 • @በህግ አምላክ   3 months ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!


  የ፲፱፻፶፪ ዓ.ም. የንግድ ሕግ አዋጅ። የኪሣራና የመጠበቂያ ስምምነት። አንቀጽ ፫። የመጠበቂያ ስምምነት።


  ቁጥር ሺ፻፲፱። ስለ መጠበቂያ ስምምነት የሚቀርብ ጥያቄ።

  ማናቸውም ዕዳውን መክፈል አቋርጦ ወይም ሊያቋርጥ ደርሶ የመክሠር ማስታወቂያ ያልተፈረደበት ነጋዴ፤ በዚህ አንቀጽ ውሳኔዎች መሠረት የመጠበቂያ ስምምነት ሥነ ሥርዐት እንዲከፈትለት ፍርድ ቤቱን ለመጠየቅ ይችላል።


  ቁጥር ሺ፻፳። ስለ ጥያቄው አቀባበል ሁኔታዎች።

  (፩) ስለ መጠበቂያው ስምምነት የሚቀርበው ጥያቄ ተቀባይነት እንዲያገኝ ግልጽ በሆነ በማስታወቂያ ጽሑፍ ሆኖ ለፍርድ መዝገብ ቤት መቅረብ አለበት።

  (፪) በቁጥር ፱፻፸፫ ከተመለከቱት ዝርዝሮች ጋራ ባለዕዳው፤ ዕዳዎችን ከመክፈል ያቋረጠበትን ወይም ሊያቋርጥ ያሰበበትን ምክንያቶችና የመጠበቂያ ስምምነት የጠየቀበትንም ምክንያት የሚያመለክት መግለጫ ጨምሮ ማቅረብ አለበት።

  (፫) ከዚህም በቀር ባለዕዳው፤

  (ሀ) እጅግ ቢያንስ ከሁለት ዓመት ወዲህ ወይም የንግዱን ሥራ የጀመረው ከሁለት ዓመት በታች እንደ ሆነ፤ ይህን ሥራ ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ በንግድ መዝገብ መጻፉን፤

  (ለ) በተመለከተው ጊዜ ውስጥ ደንበኛ የሒሳብ አያያዝ መዝገብ ያለው መሆኑን፤

  (ሐ) በአለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ የመክሠር ማስታወቂያ ፍርድ ያልወጣበት የመጠባበቂያ ስምምነትም ያልተደረገበት መሆኑን፤

  (መ) በራሱ ጥፋት በተንኰል በሕግ የተከለከለውን ነገር ወይም በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቁጥር በቁጥር ፮፻፹ እስከ ፮፻፹፰ የተመለከቱትን ወንጀሎት ሠርቶ በመገኘት ያልተቀጣ መሆኑን ማስረዳት አለበት።


  ቁጥር ሺ፻፳፩። በሚቀርበው ጥያቄ ውስጥ ስለሚገለጹት አሳቦች።

  (፩) የሚቀርበው ጥያቄ እጅግ ቢያንስ ከዚህ በታች ያሉትን አሳቦች የያዘ መሆን አለበት።

  (ሀ) ዋስትና የሌላቸው ገንዘብ ጠያቂዎች ከሚጠይቋቸው ዕዳዎች ዋና ገንዘብ ላይ ስምምነቱ ከጸደቀበት ቀን አንሥቶ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ቢያንስ ኅምሳ በመቶ የተወሰነው ጊዜ የዐሥራ ስምንት ወር ሲሆን ሰባ አምስት በመቶ የተወሰነው ጊዜ የሦስት ዓመት የሆነ እንደ ሆነ መቶ በመቶ ለመክፈል ቃል መስጠትን

  (ለ) ከዚህ በላይ (ሀ) የተሰጠውን ቃል ለመፈጸም የሚያረጋግጥ የዕቃ ወይም የሰው ዋሶች ለመስጠት ቃል መስጠትንና ለዋስትና የሚጠሩትን ሰዎች ዋሶች ለመስጠት ቃል መስጠትንና ለዋስትና የሚጠሩትን ሰዎች ወይም ዕቃዎች ዝርዝር።

  (፪) ባለዕዳው የመጠበቂያ ስምምነት እንዲደረግለት ጥያቄውን ባቀረበበት ጊዜ ያለውን ንብረት ሁሉ ለገንዘብ ጠያቂዎቹ ሁሉ በመልቀቅ መስማማትን ሊመርጥ የሚችለው የንብረቶቹ ግምት በንኡስ ቁጥር (፩) ውስጥ በተመለከተው መጠን ገንዘብ ጠያቂዎቹ የሚጠይቁትን ዕዳ ለመክፈል በቂ ሆኖ የተገኘ እንደ ሆነ ነው።


  ቁጥር ሺ፻፳፪። ጥያቄውን ስላለመቀበል።

  በቁጥር ሺ፻፳ ከተነገሩት ሁኔታዎች አንዱ ሳይፈጸም የቀረ እንደ ሆነ ፍርድ ቤቱ የሕግ አስከባሪውን ቃል ከሰማ በኋላ ስለ መጠበቂያ ስምምነት የቀረበውን ጥያቄ የማይቀበለው መሆኑን ያስታውቃል።


  ቁጥር ሺ፻፳፫። ጥያቄውን ስላለመቀበል ተጨማሪ ምክንያቶች።

  (፩) ጥያቄው ተቀባይነት ሊያገኝ በሚችልበት ጊዜ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ባለዕዳው በቁጥር ሺ፻፳፩ መሠረት የሰጠውን ቃል ለመፈጸም የማይቻል መሆኑን የገመተ እንደ ሆነ ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን አልቀበልም ሊል ይችላል።

  (፪) ባለዕዳው ሱቁን ዘግቶ ሸሽቶ እንደ ሆነ ወይም የራሱ ከሆነው ገንዘብ አንዱን ክፍል በተንኰል ደብቆ ወይም ቀንሶ የተገኘ እንደ ሆነ ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን አልቀበልም ማለት አለበት።

  (፫) በዚህ ቁጥር ወይም በቁጥር ሺ፻፳፫ የተመለከቱት ሁኔታዎች ባጋጠሙ ጊዜ ባለዕዳው ዕዳውን ለመክፈል ያቋረጠ እንደ ሆነ፤ ፍርድ ቤቱ ነጋዴው ከሥሮዋል ሲል በሥልጣኑ ፍርድ ይሰጣል።


  ቁጥር ሺ፻፳፬። ስለ ክስ አቤቱታ።

  (፩) በቁጥር ሺ፻፳፪ እና ሺ፻፳፫ ንኡስ ቁጥር (፩) እና (፪) መሠረት የተሰጠው ፍርድ እንዲፈርስ አቤቱታ ሊቀርብ አይችልም።

  (፪) በቁጥር ሺ፻፳፫ ንኡስ ቁጥር (፫) የተሰጠው ፍርድ እንዲፈርስ ግን በቁጥር ፱፻፹፬ እስከ ፱፻፹፰ በተመለከቱት ውሳኔዎች መሠረት አቤቱታ ሊቀርብ ይችላል።


  ቁጥር ሺ፻፳፭። የመጠበቂያ ስምምነት ሥነ ሥርዐትን ለመክፈት ስለሚሰጠው ፍርድ።

  (፩) ፍርድ ቤቱ የቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ሊያገኝ የሚችልና የሚፈቀድ ሆኖ ያገኘው እንደ ሆነ የመጠበቂያ ስምምነት ሥነ ሥርዐት መጀመሩን ያስታውቃል። በዚህም ውሳኔ ላይ ማናቸውም አቤቱታ ሊቀርብ አይችልም።

  (፪) በዚህ በተሰጠው ፍርድ፤ ፍርድ ቤቱ፤

  (ሀ) አንድ ወኪል ዳኛና በቁጥር ፱፻፺፬ ንኡስ ቁጥር (፩)፤(፬) እና (፭) መሠረት አንድ መርማሪ ሰው ይመርጣል።

  (ለ) እጅግ ቢበዛ ፍርዱ ከተሰጠበት ጊዜ አንሥቶ በሠላሳ ቀን ውስጥ እንዲሰበሰቡ ለገንዘብ ጠያቂዎቹ ጥሪ ያደርግላቸዋል። እንዲሁም ፍርዱ በማስታወቂያ የሚወጣበትንና ለገንዘብ ጠያቂዎች የሚነገርበትንም ቀን ይወስናል።

  (ሐ) ባለዕዳው የገንዘብ ጠያቂዎቹን ስም ዝርዝር ሞልቶ በቶሎ ለማቅረብ ያልቻለ መሆኑን በጥያቄው ውስጥ ባስረዳ ጊዜ ፍርድ ቤቱ ለተባለው ባለዕዳ ዝርዝሩን ለመሙላት ከስምንት ቀን ሊያልፍ የማይችል ጊዜ ይወስንለታል።

  (መ) ለሥነ ሥርዐቱ መፈጸሚያ አስፈላጊ የሆነውን በቂ ገንዘብ በፍርድ ቤቱ የመዝገብ ቤት የሚያስቀምጥበትን ጊዜ እጅግ ቢበዛ ስምንት ቀን ይወስንለታል።

  (፫) ባለዕዳው በንኡስ ቁጥር (፪) (ሐ) እና (መ) የተሰጡትን ትእዛዞች ያልጠበቀ እንደሆነ፤ በቁጥር ሺ፻፳፫ ንኡስ ቁ (፫) የተመለከቱት ድንጋጌዎች ተፈጻሚዎች ይሆኑበታል።


  ቁጥር ሺ፻፳፮። ስለወኪሉ ዳኛ ትእዛዞች።

  ወኪሉ ዳኛ በሰጣቸው ትእዛዞች ላይ ማናቸውም ጥቅም ያለው ሰው በቁጥር ፱፻፺፪ መሠረት፤ መቃወሚያ ለማቅረብ ይችላል።


  ቁጥር ሺ፻፳፯። ለስምምነቱ ስለተመረጠው መርማሪ።

  ለመጠበቂያው ስምምነት በተመለረጠው መርማሪ ዳኛ ላይ፤ ከቁጥር ፱፻፺፪ እስከ ሺ፻፩ ውስጥ የተጻፉት ድንጋጌዎች ተፈጻሚዎች ይሆናሉ።


  ቁጥር ሺ፻፳፰። ፍርዱን ስለ ማስታወቅ።

  (፩) ስለ መጠበቂያ ስምምነት የተሰጠው ፍርድ በመዝገብ ቤቱ ሹም አማካይነት በፍርድ ቤቱ መግቢያ በር ላይ ይለጠፋል፤ የዚህም ማስታወቂያ ቅጅ ሕጋዊ ማስታወቂያን ለመቀበል በተፈቀደለት ጋዜጣ ይወጣል።

  (፪) የፍርድ መዝገብ ቤቱም ሹም በቁጥር ፱፻፹፫ (፬) በተደነገገው መሠረት ፍርዱ በንግድ መዝገብ እንዲገባ ያደርጋል።

  (፫) ወኪል የሆነው ዳኛና የመዝገብ ቤቱ ሹም ፈርመውበት በባለዕዳው መዝገቦች ከተጻፉት ጽሑፎች ቀጥሎ ፍርድ መስጠቱን ምልክት ካደረጉ በኋላ የተባሉትን መዝገቦች ለባለዕዳው ይመልሱለታል።


  ቁጥር ሺ፻፳፱። ለገንዘብ ጠያቂዎቹ የሚሰጥ ማስታወቂያ።

  (፩) ወኪል የሆነው ዳኛ ገንዘብ ጠያቂዎቹ የሚሰበስቡትን ቦታና ጊዜ ይወስናል።

  (፪) በቁጥር ሺ፻፷፭ ንኡስ ቁ (፪) (ለ) መሠረት ፍርድ ቤቱ በወሰነው ጊዜ ውስጥ የመዝገብ ቤቱ ሹም እንዳስፈላጊነቱ በሬኮማንዴ ደብዳቤ ወይም በቴሌግራም ለያንዳንዱ ገንዘብ ጠያቂ ቀጥሎ የተዘረዘሩትን የያዘ ማስታወቂያ፡-

  (ሀ) የባለዕዳውን ወኪል የሆነውን ዳኛና የመርማሪውን ስም፤

  (ለ) ለገንዘብ ጠያቂዎቹ ጥሪ የተደረገበት ፍርድ የተሰጠበትን ቀንና የስብሰባውን ጊዜና ቦታ፤

  (ሐ) ባለዕዳው ያቀረባቸውን አሳቦች በአጭሩ ጨምሮ ይልካል።


  ቁጥር ሺ፻፴። ሥርዐቶቹ መፈጸማቸውን ስለሚያስረዱ ጽሑፎች።

  ለገንዘብ ጠያቂዎቹ የተላለፉትን መግለጫዎችና ማስታወቂያዎችን የሚያስረዱ ጽሑፎች ከዶሴው ጋራ ተያይዘው መቀመጥ አለባቸው።


  ቁጥር ሺ፻፴፩። ስለ መጠበቂያ ስምምነት የቀረበው ጥያቄ ውጤቶች።

  (፩) ጥያቄው ከቀረበበት ቀን አንሥቶ ስለ ስምምነቱ መጽደቅ የተሰጠው ፍርድ የመጨረሻ እስከሆነበት ጊዜ ድረስ ፍርዱ ከመሰጠቱ በፊት መብቱን ያገኘ ማናቸውም ገንዘብ የያቂ ቢሆን የማስፈጸምን ሥርዐት ለመጀመር ወይም ለመቀጠል፤ በባለዕዳው ንብረቶች ላይ የቀዳሚነትን መብት ለማግኘት ወይም የመያዣን መብት ለማጻፈ አይችልም።

  (፪) እንዲሁም የይርጋ ዘመን መቆጠር፤ የክስ መቀጠል መብት ማጣት፤ ወይም ከመብት መካከል ሁሉ ይታገዳል።

  (፫) አንዳችም የቀዳሚነት መብት የሌላቸው ተራ የሆኑት ዕዳዎች የመክፈያቸው ጊዜ እንደ ደረሰ ይቆጠራል። እንዲሁም የሚሰጡት ወለድ አቆጣጠር በገንዘብ ጠያቂዎቹ በኩል ብቻ የታገደ ይሆናል።

  (፬) በቀረጥ ስም ተከፋይ የሚሆኑት ገንዘቦች፤ የቀዳሚነት መብት ባይኖራቸውም እንኳ፤ በዚህ ቁጥር የተመለከቱት ውሳኔዎች አይፈጸሙባቸውም።


  ቁጥር ሺ፻፴፪። የባለዕዳውን ንብረቶች ስለ ማስተዳደር።

  የመጠበቂያ ስምምነት ሥነ ሥርዐት በሚፈጸምበት ጊዜ፤ ባለዕዳው፤ በመርማሪው ተጠባባቂነትና ወኪል በሆነው ዳኛ መሪነት የንብረቶቹን አስተዳዳሪነትና የሥራውን ማካሄድ እንደ ያዘ ይቆያል። ዳኛውና መርማሪው ሰው ሁል ጊዜ መዝገቦቹንና ሒሳቡን ለማወቅ ይችላሉ።


  ቁጥር ሺ፻፴፫። ባለዕዳው የሚያደርጋቸው ሥራዎች በገንዘብ ጠያቂዎቹ ላይ መቃሚያ ስለ መለመሆናቸው።

  (፩) የመጠበቂያ ስምምነት ሥነ ሥርዐት በሚፈጸምበት ጊዜ ባለዕዳው የሚያደርጋቸው ስጦታዎችና ሌሎች የችሮታ ሥራዎች ወይም የሚሰጣቸው ዋስትናዎች በገንዘብ ጠያቂዎቹ ላይ መቃወሚያ ሊሆኑባቸው አይችሉም።

  (፪) እንደዚሁም ወኪል የሆነው ዳኛ በጽሑፍ ሳይፈቅድለት፤ ፈቃዱንም ዳኛው ለመስጠት የሚችለው ግልጽ የሆነ ጥቅም በሚገኝበት ጊዜ ሲሆን ባለዕዳው በሐዋላ ወረቀት ወይም በተስፋ ሰነድ ቢሆንም እንኳ ብድር የገባባቸው ውሎች፤ ያደረጋቸውን ግልግሎች ወይም ስምምነቶች ለንግዱ ሥራ አስፈላጊ ሳይሆን ያደረገው የንብረት ማስተላለፍ፤ ወይም የመያዣ መብት እንዲጻፍበት መፍቀድ፤ ወይም የሰጣቸው መያዣዎች ሁሉ በገንዘብ ጠያቂዎች ላይ መቃወሚያ ሊሆኑባቸው አይችሉም።


  ቁጥር ሺ፻፴፬። የመጠበቂያ ስምምነት ሥነ ሥርዐት በሚፈጸምበት ጊዜ ስለሚደረግ የመክሠር ማስታወቂያ።

  ባለዕዳው በቁጥር ሺ፻፴፪ እና ሺ፻፴፫ የተጻፉትን ድንጋጌዎች የተላለፈ እንደሆነ፤ ወይም ከንብረቱ አንዱን ክፍል የደበቀ፤ በተንኰል አንዳንዶቹን ገንዘብ ጠያቂዎች ሳይቆጥር የተወ ዕዳውን ከፍ አድርጎ ያሳየ ወይም በጠቅላላው የተንኰል ሥራዎችን ሠርቶ የተገኘ ለመሆኑ የተረጋገጠ እንደሆነ፤ ወኪል የሆነው ዳኛ የመርማሪውን ሐሳብ ሰምቶ ነገሩን ለፍርድ ቤት ያስታውቅና በባለዕዳው ላይ የሚወስኑት የወንጀል ቅጣቶች እንደ ተጠበቁ ሆነው፤ ፍርድ ቤቱ የባለዕዳውን መክሠር ያስታውቃል።


  ቁጥር ሺ፻፴፭። ስለ መርማሪው ተግባሮች።

  ለስምምነቱ የተመረጠው መርማሪ፤ የባለዕዳውን የዕቃ ዝርዝር መዝገብ ያደራጃል። የገንዘብ ጠያቂዎቹንና የባለዕዳዎቹን ዝርዝር ይመረምራል። ስለ ንግዱ ሁናቴና ስለ ባለዕዳው ዐመል ለስምምነት ስለቀረቡት አሳቦችና ለገንዘብ ጠያቂዎች ስለ ቀረቡት ተያዦች የሚያስረዳ መግለጫ ያዘጋጃል። መግለጫውም ገንዘብ ጠያቂዎቹ ከመሰብሰባቸው በፊት እጅግ ቢያንስ ከአምስት ቀን አስቀድሞ ለፍርድ መዝገብ ቤት ሹም ይሰጣል።


  ቁጥር ሺ፻፴፮። ስለ ገንዘብ ጠያቂዎቹ ስብሰባ።

  (፩) የገንዘብ ጠያቂዎቹ ሰብሳቢ፤ ወኪል የሆነው ዳኛ ነው።

  (፪) ማናቸውም ገንዘብ ጠያቂ በጥሪው ማስታወቂያ ላይ በጽሑፍ በማመልከት ብቻ ወክሎ በራሱ ፋንታ ወኪሉን ለመላክ ይችላል።

  (፫) ባለዕዳው ወይም ሕጋዊ የሆነው ወኪሉ ራሱ መቅረብ አለት። ልዩ ወኪልን እንዲልክ የሚፈቅደው ወኪል የሆነው ዳኛ ያረጋገጠው ፍጹም የሆነ መሰናክል ሲኖር ነው።

  (፬) መርማሪው ያቀረበው መግለጫ ከተነበበ በኋላ ባለዕዳው የመጨረሻ ሐሳቦቹን ያቀርባል።


  ቁጥር ሺ፻፴፯። ለስምምነቱ በቀረቡት አሳቦች ላይ ስለሚደረጉ ክርክሮች።

  (፩) ማናቸውም ገንዘብ ጠያቂ ስለ ስምምነቱ የቀረቡትን አሳቦች የማይቀበልበትን ምክንያት ለመግለጽና አንድነት በሚቀርቡት የገንዘብ መጠየቂያ መብቶች ላይ ክርክርን ለማንሣት ይችላል።

  (፪) ባለዕዳውም በበኩሉ፤ ምላሽ ለመስጠትና በሚቀርቡትም ዕዳዎች ላይ ክርክር ለማንሣት ይችላል። የሚጠየቅባቸውን ማስረጃዎች ሁሉ መስጠት አለበት።

  (፫) የነዚህ ክርክሮች ሁሉ አጭር ቃል በፕሮሴቬርባል ገብቶ አስረጂዎችም እንዳሉ መያያዝ አለባቸው።


  ቁጥር ሺ፻፴፰። የስብሰባውን ጊዜ ስለ ማስረዘም።

  በተወሰነው ጊዜ ሥራዎቹን ሁሉ ለመጨረስ ያልተቻለ እንደ ሆነ ለገንዘብ ጠያቂዎቹ፤ ለሌሉትም ቢሆን ሌላ ማስታወቂያ ሳይደረግ፤ ስብሰባው ቀጥሎ ለሚገኘው የሥራ ቀን ይቀጠራል። እንደዚሁም ሥራዎቹ እሰኪያልቁ ድረስ ጊዜው እየተራዘመ ይሄዳል።


  ቁጥር ሺ፻፴፱። ክርክር የተነሣባቸውን ዕዳዎች ለጊዜው ስለ መቀበል።

  (፩) ወኪል የሆነው ዳኛ ድምፅ ለመስጠትና ለድምፅ ብልጫ አቆጣጠር ብቻ ሲል ክርክር የተነሣባቸውን ዕዳዎች በሙሉ ወይም በከፊል ሊቀበላቸው ይችላል። ይህ መፍቀድ ግን፤ ስለነዚሁ ዕዳዎች ተገቢነት በመጨረሻ የሚሰጠውን ውሳኔ የማይነካ ነው።

  (፪) መብታቸውን ሳይቀበሏቸው የቀሩት ገንዘብ ጠያቂዎች፤ መብታቸው ተቀባይነት አግኝቶ ቢሆን ኖሮ የድምፅ ብልጫውን አቆጣጠር ይለውጠው ነበር በሚባልበት ጊዜ ስምምነቱ ለመጽደቅ በሚቀርብበት ችሎት ክስ ለማቅረብ ይችላሉ።


  ቁጥር ሺ፻፵። ስምምነቱን ለመቀበል ስለሚያስፈልገው የድምፅ ብልጫ።

  (፩) የመጠበቂያው ስምምነት ተቀባይነት እንዲያገኝ የቀዳሚነት መብት ወይም የመያዣ መብት ከሌላቸው የገንዘብ መጠየቂያ መብቶች ቢያንስ ከሦስት ሁለት እጅ ባላቸውና ድምፃቸውንም በሰጡት ገንዘብ ጠያቂዎች የድምፅ ብልጫ መደገፍ አለበት።

  (፪) በባለዕዳው ንብረቶች ላይ መያዣ ያላቸው ገንዘብ ጠያቂዎች ዋስትናቸውን ካልለቀቁ በድምፅ ብልጫው ሥራ ተካፋይ ለመሆን አይችሉም። ይኸውም የመያዣ መብትን መልቀቅ በከፊል ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ዋስትና ካለው ተፈላጊው ጠቅላላ ገንዘብ አንድ ሦስተኛ ማነስ የለበትም።

  (፫) መያዣ ያለው ገንዘብ ጠያቂ፤ በንኡስ ቁጥር (፪) መሠረት መያዣውን በከፊል ሳይለቅ፤ ድምፅ በመስጠቱ ተከፋይ ሆኖ፤ በቁጥር ሺ፻፵፩ መሠረት ስምምነቱን ተቀብሎ እንደ ሆነ፤ ገንዘብ ጠያቂው ያለውን የመያዣ መብት በሙሉ እንደ ለቀቀ ይቆጠራል።

  (፬) ፍርድ ቤቱ ስምምነቱን በሚያጸድቅበት ጊዜ በንኡስ ቁ (፪) መሠረት በተሰጡት ድምፆች ምክንያት ወይም በንኡስ ቁ (፫) መሠረት በተደረገው መቀበል ምክንያት፤ የባለዕዳው ንብረት ሊያገኝ የሚችለውን ብልጫ በግምት ውስጥ ያገባዋል።

  (፭) ስምምነቱ ያልተፈጸመ ወይም ያልጸደቀ ወይም የተሰረዘ ወይም የፈረሰ እንደ ሆነ፤ የተደረገው የመያዣ መብት መልቀቅ፤ በከፊልም ቢሆን፤ ውጤቱ በደንብ ቀሪ ይሆናል።

  (፮) ለመጠበቂያ ስምምነት ስለሚሰጠው ድምፅ በቁጥር ሺ፹፫ ንኡስ ቁ (፬) እና (፭) የተወሰኑት ድንጋጌዎች ተፈጻሚዎች ይሆናሉ።


  ቁጥር ሺ፻፵፩። የተደረገውን ስምምነት ስለመቀበል።

  (፩) ስለ ገንዘብ ጠያቂዎች ስብሰባ በሚደረገው ፕሮሴቬርባል ላይ የድምፅ ሰጪዎቹን ስምና እያንዳንዳቸው የሚጠይቁትን ጠቅላላ ዕዳ ጭምር፤ ድምፃቸውንም የሰጡት ስምምነቱን በመደገፍ ወይም በመቃወም መሆኑ ተለይቶ ይጻፋል። በፕሮሴቬርባሉም ወኪል የሆነው ዳኛ፤ መርማሪው፤ የመዝገብ ቤቱ ሹም ይፈርሙበታል።

  (፪) ፕሮሴቬርባሉ በተዘጋ በ፲ ቀን ውስጥ በቴሌግራም ወይም በደብዳቤ የሚላኩት የስምምነቶች አቀባበሎች በድምፅ ብልጫ ውስጥ ይገባሉ። እነዚህንም ተጨማሪ ስምምነቶች የመዝገብ ቤቱ ሹም በፕሮሴቬርባሉ ኅዳግ ላይ ይጽፋቸዋል።


  ቁጥር ሺ፻፵፪። ስምምነቱን ስለ መለመቀበል።

  የመጠበቂያውን ስምምነት ስለ መቀበል በቁጥር ሺ፻፵ እና ሺ፻፵፩ የተነገሩት ሁኔታዎች ያልተገኙ እንደ ሆነ፤ ወኪል የሆነው ዳኛ ወዲያውኑ ለፍርድ ቤቱ ያስታውቃል፤ ፍርድ ቤቱም ሰውዬው መክሠሩን በሥልጣኑ ያስታውቃል።


  ቁጥር ሺ፻፵፫። ስምምነቱን ለማጽደቅ ስለሚደረገው ሥነ ሥርዐት።

  (፩) ከሓያ ቀን ለማለፍ በማይችል ጊዜ ውስጥ ስለ ስምምነቱ መጽደቅ በተወሰነው ቀን ባለጉዳዮቹ እፍርድ ቤት ቀርበው እንዲሰሙ ወኪል የሆነው ዳኛ፤ ፕሮሴቬርባሉ ከመፈረሙ በፊት በፕሮሴቬርባሉ ውስጥ ጽፎ ባለጉዳዮቹን ይቀጥራቸዋል።

  (፪) የስምምነቱን መጽደቅ ለመስማት ለተወሰነው ችሎት ሦስት ቀን ሲቀረው፤ መርማሪው አሳቦቹን ከነምክንያቱ ለፍርድ መዝገብ ቤት ያስረክባል፤ ነገሩ በሚሰማበት ችሎት ወኪል የሆነው ዳኛ መግለጫውን ያቀርባል።

  (፫) ገንዘብ ጠያቂዎቹና ባለዕዳው በጉዳዩ ክርክራቸውን ለማቅረብ መብት አላቸው።


  ቁጥር ሺ፻፵፬። ስለ ስምምነቱ መጽደቅ የሚሰጥ ፍርድ።

  (፩) ስምምነቱ ተቀባይነት እንዲያገኝ የሚያስፈልጉትን ሁኔታዎች መኖር እና የሥነ ሥርዐቱን መፈጸም ከመረመረ በኋላ፤ ፍርድ ቤቱ፤

  (ሀ) የንግዱ ድርጅት በያዘው ሥራና ባለው ችሎታ መሠረት፤ ለገንዘብ የያቂዎቹ ስምምነቱ የሚጠቅማቸው መሆኑን መገመት እና፤

  (ለ) በሕግ ተፈላጊ የሆነው የገንዘብ ጠያቂዎቹ ድምፅ ብልጫ መገኘቱን ማረጋገጥ ስለዚሁም፤ በኋላ የሚሰጡት የመጨረሻ ፍርዶች ሳይጓደሉ የተፈለገውን ድምፅ ብልጫ መገኘት ለማረጋገጥ ይችል ዘንድ፤ ፍርድ ቤቱ የተጠየቁትን ዕዳዎች ከፍተኛነትና መጠን ለጊዜውና በግምት መወሰን፤

  (ሐ) ስምምነቱ እንዲፈጸም ለማረጋገጥ የቀረቡት ዋስትናዎች በቂ መሆናቸውንና፤ በቁ ሺ፻፳፩ ንኡስ ቁ (፪) እንደተመለከተው ሁኔታ ሲሆን፤ ባለዕዳው ለንዘብ ጠያቂዎቹ የለቀቀው ንብረት በቁጥር ሺ፻፳፩ በንኡስ ቁ (፩) በተወሰነው መጠን፤ የባለዕዳው የሚፈለገውን ገንዘብ ለመክፈል በቂ መሆኑን፤ መመርመር፤

  (መ) የባለዕዳውን መክሠር ያመጡትን ምክንያቶችና አሠራሩን በመገንዘብ ይኸው ባለዕዳ ስምምነቱ ሊደረግለት የሚገባው መሆን አለመሆኑኑ መገመት አለበት።

  (፪) ፍርድ ቤቱ ያደረገው ምርመራ ውጤቶቹ ባለዕዳውን የሚረዱት የሆኑ እንደ ሆነ፤ ስምምነቱ እንዲጸድቅ ይፈርዳል። እንዲህ ካልሆነ ግን ባለዕዳው ከሥሮዋል ሲል ፍርድ ቤቱ በሥልጣኑ ይፈርዳል።

  (፫) ስምምነቱ እንዲጸድቅ በሚሰጠው ፍርድ፤ ፍርድ ቤቱ፤

  (ሀ) ለተገለጹት ዕዳዎች የሚደርሰው ድርሻ እንዲቀመጥ፤

  (ለ) ክርክር የተነሣባቸው ዕዳዎችን ለመክፈል የሚበቃ ገንዘብ እንዲቀመጥ፤

  (ሐ) ወኪል የሆነው ዳኛ እንዲወስን ካላዘዘ በቀር ስምምነቱን በመፈጸም በየጊዜው ሊከፈል የሚገባውን ገንዘብና የአከፋፈሉንም ዐይነት ይወስናል።


  ቁጥር ሺ፻፵፭። ንብረቶች በሚለቀቁበት ጊዜ ስለሚደረጉት አስፈላጊ ነገሮች።

  በቁጥር ሺ፻፳፩ ንኡስ ቁ (፪) መሠረት ባለዕዳው ንብረቶቹን እንዲለቅ ስምምነቱ የሚወስን እንደ ሆነ፤ ተቃራኒ የውል ቃሎች እንደ ተጠበቁ ሆነው፤ ፍርድ ቤቱ ስለ ስምምነቱ መጽደቅ በሚሰጠው ፍርድ፤

  (ሀ) አንድ ወይም ብዙዎችን ሒሳብ አጣሪዎችና፤ የማጣራቱንም ሥራዎች እንዲጠባበቁ፤ ሦስት ወይም አምስት አባሎች ያሉበት የገንዘብ ጠያቂዎች ኮሚቴ ይመርጣል።

  (ለ) የማጣራቱንመ አደራረግ ይወስናል።


  ቁጥር ሺ፻፵፮። በባለዕዳው ላይ ስለሚደረግ ክልከላ።

  (፩) በስምምነቱ ውስጥ ወይም በዚህ አንቀጽ መሠረት ተሰጥቶ ፍርድ ቤቱ ባጸደቀው ውሳኔ ውስጥ የገባ ተቃራኒ የሚሆን የውል ቃል ከሌለ በቀር፤ ባለዕዳው በስምምነቱ ውስጥ የተነገሩትን ግዴታዎች በሙሉ እስኪፈጽም ድረስ፤ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶቹን እንዳይሸጥ እንዳለወጥ ወይም እንዳይለውጥ ወይም እንዳያስዝ ወይም የመያዣ መብት እንዳይሰጥና በጠቅላላውም ለሥራው ዐይነት በሚያስፈልገው አኳኋን ካልሆነ በቀር ከንብረቱ እንዳይቀንስ ይከለከላል።

  (፪) በንኡስ ቁጥር (፩) የተመለከተውን ክልከላ በመጣስ የተሠራ ማናቸውም ሥራ የመጠበቂያው ስምምነት ከመጽደቁ በፊት የነበሩትን ገንዘብ ጠያቂዎች በሚመለከት ጉዳይ አንዳች ውጤት የለውም፤


  ቁጥር ሺ፻፵፯። ስለ ስምምነቱ መጽደቅ የሚሰጠው የፍርድ ማስታወቂያ።

  የመጠበቂያውን ስምምነት በማጽደቅ ወይም አይሆንም በማለት የተሰጡት ፍርዶች በቁጥር ፱፻፹፫ ከተወሰኑት ደንቦች ተገቢ የሆኑትን በመከተል በማስታወቂያ መውጣት አለባቸው።


  ቁጥር ሺ፻፵፰። ስምምነቱ እንዳይጸድቅ ስለ መቃወም።

  (፩) በነገሩ ያልተስማማው ገንዘብ ጠያቂ እና በዚህ ነገር ባለጉዳይ የሆነ ማናቸውም ሰው ፕሮሴቬርባሉ በተዘጋጀ በአምስት ቀን ውስጥ ስምምነቱ እንዳይጸድቅ ለመቃወም ይችላል።

  (፪) የመቃወሚያውም ምክንያት ተገልጾ መቃሚያውን ባለዕዳውና መርማሪው እንዲያውቁት መደረግ አለበት።


  ቁጥር ሺ፻፵፱። ስለ ስምምነቱ መጽደቅ በተሰጠው ፍርድ ላይ ይግባኝ ስለ ማለት።

  ስምምነቱን በማጽደቅ ወይም አይሆንም በማለት በተሰጠው ፍርድ ላይ ባለዕዳው ወይም በቁ ሺ፻፵፰ መሠረት የተቃወሙት ገንዘብ ጠያቂዎች ይግባኙ ሊሉ ይችላሉ። የይግባኙም ጊዜ የፍርዱን ማስታወቂያ ከወጣበት ቀን አንሥቶ እስከ ዐሥራ አምስት ቀን ድረስ ነው። የይግባኙም ክስ ባለዕዳው፤ መርማሪው፣ በክርክሩ ውስጥ የሚገኙት ባለጉዳዮች ሁሉ እንዲያውቁት መደረግ አለበት።


  ቁጥር ሺ፻፶። የስምምነቱ መጽደቅ ውጤቶች።

  (፩) በሚገባ የጸደቀው የመጠበቂያ ስምምነት፤ የጉዳዩ ሥነ ሥርዐት ከመከፈቱ በፊት የነበሩትን ገንዘብ ጠያቂዎች ሁሉ አስገዳጅ ይሆናል። ነገር ግን ለእነዚህ ገንዘብ ጠያቂዎች፤ በባለዕዳው የጋራ ተገዳጆች፤ በዋሶቹና ንብረቱን ባስተላለፉላቸው ሰዎች ላይ ያላቸው መብት በሙሉ እንደተጠበቀ ይቆያል።

  (፪) እነዚህ የተዘረዘሩት ሰዎች በስምምነቱ ላይ ማስገንዘቢያቸውን ለማቅረብ በክርክሩ ውስጥ ለመግባት ይችላሉ።


  ቁጥር ሺ፻፶፩። ስለ ስምምነቱ አፈጻጸም የሚደረግ ተጠባባቂነት።

  (፩) የመጠበቂያው ስምምነት ከጸደቀ በኋላ፤ ስለ ማጽደቁ በተሰጠው ፍርድ ውስጥ በተመለከተው አሠራር መሠረት ስምመነቱ የፈጸመ ዘንድ መርማሪው አፈጻጸሙን ይጠባበቃል።

  (፪) መርማሪው፤ የገንዘብ ጠያቂውን ለመጉዳት ምክንያት የሢሆነውን ማናቸውንም ነገር ሁሉ ወኪል ለሆነው ዳኛ ማስታወቅ አለበት።

  (፫) ማናቸውም ተቃራኒ የውል ቃል ቢኖርም እንኳ ከተመረጠበት ጊዜ አንሥቶ፤ ሥራዎቹ እስከቀሩበት ጊዜ ድረስ፤ ለመርማሪው የሚታሰብለትን ኪሣራና የሚገባዋን ገንዘብ ሁሉ ወኪል የሆነው ዳኛ ይወስንለታል።


  ቁጥር ሺ፻፶፪። የመጠበቂያ ስምምነትን ስለ መሰረዝና ስለ ማፍረስ።

  (፩) በንብረት ጠባቂው ቦታ የመርማሪው መተካት ብቻ የተጠበቀ ሆኖ፤ ከቁ ሺ፺፩ እና ሺ፺፫ የተጻፉትን ድንጋጌዎች፤ የመጠበቂያ ስምምነትን ለማፍረስና ለመሰረዝ በሚመለከተው ጉዳይ ተፈጻሚዎች ይሆናሉ።

  (፪) የመጠበቂያው ስምምነት፤ በቁጥር ሺ፻፳፩ ንኡስ ቁ (፪) መሠረት ንብረቶችን ለመልቀቅ የሚወስን በሚሆንበት ጊዜ፤ በንብረቶቹ መሸጥ የተገኘው ገንዘብ ከዕዳው አምሳ በመቶውን 50% ለመክፈል የሚበቃ ከሆነ ስምምነቱ አይፈርስም።


  ቁጥር ሺ፻፶፫። ወደተሻለ ዕድል ስለ መመለስ የሚል የውል ቃል።

  በመጠበቂያው ስምምነት ውስጥ፤ ባለዕዳው ከስምምነቱ ሰነድ ፈጽሞ ነጻ የሚሆነው፤ ወደ ተሻለው ዕድል ተመልሶ ያልተገኘ እንደ ሆነ ብቻ ነው የሚል የውል ቃል ገብቶበት እንደ ሆነ፤ የዚህ ውል ተፈጻሚነት ለአምስት ዓመት በሚሆን ጊዜ ይወሰናል፤ ያውም የባለዕዳው ንብረት እጅግ ቢያንስ ከዕዳው በላይ በመቶ ሓያ አምስት ጨምሮ ሲገኝ ነው።


  ምንጭ:

  የ፲፱፻፶፪ ዓ.ም. የንግድ ሕግ

 • loader Loading content ...

Load more...