loader

Topics (6)


loader Loading content ...

Explanations (6)


 • @Kibur Metekia Hailemichael   8 months ago
  Sewasewer

  ርዕስ አንድ :-ድመቷ አይጧና እኛ.....
  ርዕስ ሁለት:- የአክሊሉ ሃብተወልድ ነገር
  {(ክቡር መተኪያ ሃይለሚካኤል)}
  ++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++
  #መራር እውነታ
  #ረዘም ያለ ጠመዝማዛና አቀበት የበዛበት ጽሁፍ ስለሆነ ተጠንቅቀህ አንብብ
  #ለአንባቢ ብቻ
  ++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++
  አንድ ሁሌም የሚከነክነኝ ጉዳይ አለ::እዚህ ፌስቡክ መንደር ላይ ስንት ሊያሳውቅና ሊያዝናና የሚችል ጉዳይ እያለ እንደ መንደር ባልቴት ጥግና ጥግ ይዞ አንተ የእንትና ትውልድ አንት የእንትና ዘር እይተባባሉ መጠዛጠዝ::አንድ ቁም ነገር እዝች ጋር እናንሳ::ድመት አይጥን ለመብላት ስታሯሩጣት ያለውን ቅጽበት::ድመቷ ረሃቧን የማስታገስ ጉዳይ ሆኖባት አይጧት ታሯሩጣለች::አይጧ ደሞ የመኖር ያለመኖር ጉዳይ ሆኖባት ትሸሻለች::እኛ ደግሞ በሰው ሰውኛ ይሄንን ትእይንት እንደ ሰርከስ ትርኢት እየተሳሳቅን እናየዋለን::እንግዲህ አንድ የአዳኝና ታዳኝ ጉዳይ ለአይጧ “የመኖር ያለመኖር” ለድመቷ “ረሃብ የማስታገስና ያለማስታገስ”  ለኛ ለተመልካቾች ደግሞ “የመዝናናትና ያለመዝናናት” ጉዳይ ይሆናል::

  አለም ከድምጽ የፈጠነ አይሮፕላን ሰርቶ ከቃሊቲ ታክሲ ተሳፍረን መርካቶ ሳንደርስ አንድ ሰው በሱፐር ሶኒክ ጀት ከደቡብ አፍሪካ ናይሮቢ ኬንያ ይደርሳል::የምድሩ አይበቃንም ብሎ ጠፈር ላይ ስለመኖር ንድፍ ይነድፋል::ባለ አስራ ሁለት ፎቅ መርከብ ሰርቶ በደስታ ይንፈላሰሳል::እንኳን ያዘዝነውን ያሰብነውን ዱብ የሚያደርግ የፋይበር ኦፕቲክስ ኢንተርኔት ሰርቶ አለማችን መንደር ነች ይለናል::ይሄን ሁላ አለም ከደቂቃ ጋር እየተሽቀዳደመ ሲሰራ እኛ የቱ  ጋር ነን?? እ??እኛማ የዛሬ መቶ አመት ጡት ተቆርጧል አልተቆረጠም?ቆራጩ ምኒልክ ነው አይደለም?አማራ አለ የለም?የኦሮሞ ቁጥር ይበልጣል የአማራው?ትግሬ ጨቁኖናል አልጨቆነንም? እየተባባልን የአይጣና የድመቷን ፍልሚያ ወጥረን ስንፋለም ከጸቡ ተጠቃሚ የሆኑት ደግሞ “ጃስ” ሲሉት የሚናከስ ውሾቻቸውን በየፌስቡኩና በየፌክ አካውንቱ አሰማርተው ይደበሩብናል::

  ዳንኤል ክብረት በአንድ መጣጥፉ ላይ አንድን የትግራይ ተረት በጥሩ ትንተና አቅርቦልን ሳነብ አስታውሳለው::ነገሩ እንዲህ ነው::አንድ ቀን ባልና ሚስቱ በተቀመጡበት አይጢቷ ከጎሬዋ ወጥታ ወዲህ ወዲያ ማለትና ጭራዋን መነስነስ ትጀምራለች::ይሄን ግዜም አባወራው ደህና ፍልጥ ይዘው አይጧን ማሯሯጥ ይጀምሩና በዱላ መትተው ለመግደል ሲሞክሩ በተደጋጋሚ እየሳቷት አንዴ መሬቱን አንዴ ግርግዳውን አንዴ ሰፌዱን አንዴ ሌማቱን እየመቱ አይጧን ሊገድሉ ሳይቻላቸው ቀረ::በመጨረሻም አይጧ ከተደበቀችበት ወጥታ እምጣዱ ላይ ቁጭ ስትል ምቹ ሁኔታን ያገኙት አባወራም ኮቴያቸውን አጥፍተው አይጧን ሊገድሉ ዱላቸውን ሲቃጡ እማወራዋ ተሽቀዳድመው የባላቸውን ክንድ ግጥም አድርገው ያዙ::ይሄኔም አባወራው “እዋ ሉቆቂኝ ሉግዶላት እንጅ”ሲሉ እማወራዋም ቀበል ብለው “ምእንቲ ምጎጎ እታ አንጭዋ ትሕልፍ” (ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ) ”አሉ::ያው አንዲት አይጥ ለመግደል ስንት ሙሽት ስንት ማገዶ ስንት ሸክም ስንት ገንዘብ የወጣበትንና ስንት እንጀራ የሚጋግር ምጣድ መስበሩ አያዋጣምና ነው::እንጂማ ሴቲዮዋ የባላቸውን ክንድ መያዝ አይጧን ለማዳን ለአይጧ ተከላካይ ጠበቃ መሆን ሳይሆን ምጣዱን ለማዳን ያለ ብቸኛ አማራጭ ስለሆነ ነው::

  ዛሬ ዛሬ በየጡመራ ገጾች በየመጽሃፎች በየድረገጹ የሚለቀቁ እጅግ ጠቃሚና አስተማሪ ጽሁፎች ቢኖሩም “በማር የተለወሱ መርዞችም” አብረው እየተነዙ ምርቱን ከግርዱ መለየት አዳግቷል:: በተለይ የዛሬውን በቴክኖሎጂ ደንዝዞ ታሪክና ማንነቱን የዘነጋ ትውልድ ይበልጥ የጥፋት ቁልቁለት ላይ ከጀርባው ገፍትሮ እያንደረደሩት ናቸው::በታሪካችን ድል እንዳለ ሽንፈትን ተጎንጭተናል::በታሪካችን ልማት እንዳለ ጥፋት ነበር::በታሪካችን ደግነት እንደነበር ክፋትም ነበር::ታሪካችን ብስል ከጥሬ ነው::ዛሬ ላይ ልንማርበት የሚገባን ስንት መልካም ታሪካችን እላዩ ላይ ቅርቃር ተመትቶበትና በጓጉንቸር ቁልፍ ተቆልፎበት ክፉ ክፉውን አንዳችም እርባና የሌለውን የታሪክ ጉድፍ አብዝቶ ከግራ ቀኝ መቀባበሉ በቋፍ ላይ ያለውን የተስፋ ጭላንጭል ሻማ ንፋስ ላይ ማስቀመጥ ነው::

  እሁድ ታህሳስ አንድ 2010 በራስ ሆቴል የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሃብተወልድ ዲቪድ ምረቃ ፕሮግራም ላይ ተገኝቼ ነበር::እንደውነቱ ከሆነ ኤርትራን በፌደሬሽን ያስመለሱትና በጣልያን ወረራ ወቅት ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ተጋድሎ የፈጸሙት ጸሃፊ ትእዛዝ አክሊሉ ሃብተወልድ አንዲት የ80 ደቂቃ ዶክመንታሪ እጅግ ቢያንስባቸው እንጂ ማንም ይበዛባቸዋል የሚል እንደማይኖር ተስፋ አደርጋለሁ:: (በነገራችን ላይ አክሊሉ ማን እንደነበሩ ምን እንደሰሩ ለኢትዮጵያ ምን እንደነበሩና ፍጻሜያቸው እንዴት እንደነበር አቅሜ በፈቀደና ባወቅኳት መጠን ጽሁፉን በተከታታይ አቀርባለሁ::)እናም የዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ ጉዳይ የጸሃፊ ትእዛዝ አክሊሉ ሃብተወልድ ወዳጆች የእርሳቸውን ዝክረ ነገሮች በጽሁፍ መምስልና በቪዲዮ እያስደገፉ ሲያወሷቸው መመልከቴና ጎን ለጎንም “አክሊሉ ሃብተወልድ ከነማንነቱ ማነው?”እያለ ከሚጠይቀው ጀምሮ አክሊሉ ሃብተወልድ ይሄንን ሃገር ያልጠቀሙ የግል ንብረት ያካበቱ በስልጣን የሚመኩ ዘረኛ ናቸው እስከሚለው ብሎም መልካም ስራቸውን አምኖ ክፉ ምግባራቸውንም እናስታውስ እስካለው ክርክርና እሰጥ አገባ ድረስ መመልከቴ ነው::እንግዲህ የጽሁፌ ፍሬ ነገርም ይሄ (መልካም ስራቸውን አምኖ ክፉ ምግባራቸውንም እናስታውስ)የሚለው ሲሆን ሌላው ሌላው በተከታታይ በቅርቡ በምፖስተው ጽሁፍ የምሟገትበት ጉዳይ ይሆናል::

  ታሪክ የአንድ ህዝብ ማንነትና ምንነት ማሳያ መስታወት ነው::ታሪክ የሌለው ህዝብ እንደ መኮሮኒ ከላይ ድፍን ውስጥ ውስጡ ግን ክፍት ነው::ታሪክ የማንነታችን ማሳያ መስታወት ነውና የታሪክ ምሁራኑም “ከታሪክ ምድጃ ላይ አመዱን ትታችሁ ፍም እሳቱን ጫሩ”ብለውናል::እርግጥም ድንቅ አባባል ነው::ከታሪክ ምድጃ ላይ ፍሙ እያለ አመዱ አይበጀንም::እህሉ እያለ ገለባው አይጠቅመንም::ነበልባሉ እያለ ጭሱ አይረባንም::ዛሬ ላይ በጉዞ ማስታወሻቸውና ማስረጃ ይኑረው አይኑረው ያልተረጋገጠ መረጃቸውን በተለያየ መገናኛ ብዙሃን እየሰጡን ያሉትን መጽሃፍ እንደነጋበት ጅብ ዝም ብለን ማጋበሱ ከታሪክ ከመማር ይልቅ ቂምና በቀልን መውረስ ይሆናል ውጤቱ::መሰረታዊ የታሪክ አላማንም ያስተናል::ታሪክ ካለፈው ለመማሪያ የድሮውን አውቀን የወደፊቱን እንድንተነብይ እንዲረዳን የምናጣቅሰው ዶሴ እንጂ “ቅድም አያትህና ቅምንዥላትህ የቅም ቅም አያቴን ጡትና እግር ቆርጧል ዘሬን ሰድቧል መሬቴን ወርሷል ስሜን ቀይሯል ስልጣኔን ነጥቋል እያልን ቢላዋ የምናፏጭበት ቃታ የምንስብበት ከሆነ ጊደራችንን ልናስርበት የሚገባንን ገመድ ሸምቀቆ ሰርተን ለአንገታችን መታነቂያ አደረግነው ማለት ነው::

  ታሪክና እውነት

  የተቆለፈበት ቁልፍ እና ሌላ ሰው የተሰኘውን የዳጎሰ መጽሃፍ ያበረከተልንና በሸገር ኤፍ ኤም ከመአዛ ብሩ ጋር በመሳጭ ንግግሩ የምናውቀው የስነ አይምሮ ሃኪሙ ዶክተር ምህረት ደበበ በአንድ ወቅት ስለ እውነት ምንነት ያቀረበው የሸገር ካፌ ጭውውት የዚህኛው አንቀጽ መነሻ ሃሳቤ ነው::እዚህ ላይ ንግግሩን ቃል በቃል ለማቅረብ ሳይሆን የንግግሩን ፍሬ ነገር ለማቅረብ እወዳለሁ::እውነት በራሱ እውነት አይደለም::እውነት የማህበረሰብ ስምምነት ነው::እውነት ከተነሳንበር አውድና አመክንዮ ተነስተን የምናቀርበው ነገር ካልሆነ እውነትነቱ ተቀባይነት አይኖረውም::አልያ ደግሞ ደረቅ እውነት ይሆናል::ለምሳሌ ከተኮራረፉ በኋላ ችግራችውን ይቅር ለእግዚሃር ተባብለው የተታረቁና በጸብ ሰሞናቸው ስላረጉት ሁላ ስለፍቅር ብለው የተው ሁለት ፍቅረኛሞች ከእለታት በአንዱ ቆንጆ  የፍቅር ምሽታቸው ላይ “እውነቱን እንናገር ከተባለ እኮ አንቺ እኔን በወላጆችሽ ፊት ያዋረድሽኝ ከጓደኛዬ ጋር የተዳራሽ ገንዘብ ወዳድ መሆንሽን ልትዘነጊው አይገባም” ብሎ “እውነት ነው”ያለውን ቁስል ጨው ሊነሰንስ ቢሞክር ትርፉ የመፋቀሪያ ግዜን አፈር ከድሜ ማስበላት ነው::እንደ ዶክተሩ አባባል “እውነቱ ባቡር ቢሆን መረጃው ሃዲድ ነው:: ያ ሃዲድ ወደ ትክክለኛ ቦታ ይወስዳል ወይ?መረጃውስ ምን ይፈይድልናል ነው ቁምነገሩ”::በባህላችንስ ቢሆን ስለነውር ብዙ ይባል የለ::ቢያንስ ነውር በጓዳ ነው እንጂ በአደባባይ አይወጣም::እውነት ሳይሆን ቀርቶ ሳይሆን መሸፈኑ የተሻለ ነገር ስለሚፈጥር ነው:: ታሪካችንም ላይ ያለው ጠባሳ እርቅ ፍቅር መተሳሰብ መዋደዱና መሰልጠኑ ከመጣ ከብዙ ግዜ በኋላ እያነሳነው ልንወያይበት “ስህተታችንን አንድገም የውሾን ነገር ያነሳም ዉሾ ይሁን” ልንባባልበት ይገባል:: (እንደ ህብረተሰባችን ንቃተ ህሊናና የታሪክ እውቀት) እንጂ ገና ትከሻው ላልደነደነ ታዳጊ ህጻን ወፍጮ ማሸከም እንዳይሆንብን::

  ደሞስ ነገሩ እውነት ነው ወይ? ከዚህኛውና ከዛኛው እውነት የትኛው ያዘነብላል?

  እንግዲህ ከላይ በስሱ ለማለት እንደሞከርኩትና የንትርኩ መነሻ የንጉሰ ነገስቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጸሃፊ ትእዛዝ አክሊሉ ሃብተወልድ የኦሮሞ ተወላጅ የነበሩትን ታደሰ ብሩን አይሆኑ ንግግር ተናግረዋቸዋል የሚባለው ጉዳይ አንዳንዶች በማስረጃነት (የመጽሃፍ ርዕሱንና ገጹን ከነፍሬ ሃሳቡ) ጠቅሰው የሚሞግቱ በእውቀት ላይ የተመረኮዙ ሰዎች ናቸው:: ነገሩ በዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ “ዳንዲ የነጋሶ መንገድ” እንዲሁም በኦላና ዞጋ ግዝትና ግዞት መጽሃፍ ላይ ተጠቅሶ የምናየው የሜጫና ቱለማው ታደሰ ብሩ ማህበሩን ለመቀላቀል የወሰኑበት አጋጣሚ ጸሃፊ ትእዛዝ አክሊሉ ሃብተወልድ “ኦሮሞ ሰፊና ውቅያኖስ የሆነ ህዝብ ነው የተማረ እንደሆነ ያጥለቀልቀናል” የሚለው ስጋት አዘል ንግግራቸው እንደሆነ ነው::እንግዲህ ይሄንን ንግግር አሉ የተባሉት አክሊሉ ሃብተወልድ ነገሩን ስለማለታቸው እንዳንጠይቃቸው አፈር ተጭኗቸው ወደዚያኛው አለም ከተጓዙ የአንድ ጎልማሳ እድሜን አስቆጥረዋል::ታደሰ ብሩም ቢሆኑ በአጸደ ስጋ ስለሌሉ ወሬውን በሰነድ (ካላቸው)ማረጋገጥ አንችልም::ስለዚህ ለዚህ መሟገቻችን ግለሰቦቹ በተለያየ አጋጣሚ ለሰው ተናገርውታል የሚሉትንና ነግሮኛል የሚለውን ግለሰብ ቃልና ጽሁፍ ነው::ይሄ ደግሞ ነገሩን ወደ አንድ የአስተሳሰብ ደረጃ ከመውሰድ ያለፈ ስለ እውነትነቱ ማረጋገጫ ሊሆነን የሚችልበት የታሪክ ማስረጃ እድል የለውም:: (እንደ ታሪክ ማስታወሻ ልናነበውና ልንነጋገርበት ግን በሚገባ እንችላለን)ይህ በዚህ እንዳለ ደሞ ሰሞኑን በህብር ሬዲዮ የቀረቡት ፕሮፌሰር ህዝቄኤል ጋቢሳ ያቀረቡትና የታደሰ ብሩን ንግግር የሚሞግትና “እንዲያውም ጸሃፊ ትእዛዝ አክሊሉ ሃብተወልድ በቦታው አልነበሩም ለዚህም ማስረጃዬ ይሄ ይሄ ይሄ ነው”ብለው ሲከራከሩ የነበረው መከራከሪያ (ARGUEMENT) እጅግ የሰላ እንደሆነ በስፋት እየተደመጠ ነው::ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተጠናከረ መልኩ በኦሮሞነታቸው ምንም ጥርጥር የሌላቸውና እንዲያውም ፓርላማ ውስጥ በኦሮምኛ በመናገር አልፎ  አልፎም በአስቂኝ ንግግራቸው የምናስታውሳቸው አቶ ቡልቻ ደመቅሳም ተናገሩት የተባለው ንግግር ሌላው ለዚህ ለታደሰ ብሩ “ተወረፍኩኝ”ንግግር የሃሳብ መሞገቻ ሆኖ ሊቀርብ ይቻለዋል::

  እንግዲህ ይሄ የአክሊሉ ሃብተወልድ ተባለ የሚባለው ንግግር “አንዱን ኦሮሞ አስከፍቶ አንዱን የሚያስደስት ነው” እስካልተባለ ድረስ ተጨባጭ የሆነ የሰነድ ማስረጃ ያልቀረበበት እንደ ሰርገኛ ጤፍ የተቀየጡ የኦሮሞና የአማራ ህዝቦችን የተሳሰረ ስር ለመበጠስ የተሞረደ መጥረቢያ ሆኖ ከማገልገል ብሎም የአክሊሉ ሃብተወልድ ዝክረ ነገራቸው ከመጠቀስ ይልቅ ግዜንና እውቀትን በንትርክ እንድናባክን ከመዳረግ ያለፈ እርባና የሌለው በማር የተለወሰ መርዝ ነው::እዚህ ላይ ሆኗል ተብሏል ተናግረዋል ብለን ብናስብ እንኳ ጥቅሙ ለማንም የማይበጅ ተራ ጉዳይ ነው::አንዳንድ ግዜ እኮ በቀና ልቦና ካሰብነው አንዳንት ቅዱስ ሃጥያት አንዳንድ ክፉ እውነት አለ:: ለምሳሌ በሞት አፋፍ ላይ ያለን ህጻን ልጅ ከአንድ ሃብታም ሰውዬ ኪስ 100 ብር ሰርቀን ወተት አጠጥተን ህይወቱን ብንታደጋት ሃጥያትነቱ ባይካድምና ንሰሃ መግባት የግድ ቢሆንብንም ቅሉ ገና ለገና ጻድቅ ልሁን ብለን ፈጣሪ ይሁነው ብለን ትተነው ብንሄድ ጸጸቱም እንቅልፍ አያስተኛን::ደግሞም ሁለት ፍቅረኛሞች ሲጣሉ ለመሸምገል ይቅር ለእግዚሃር ተባባሉ ችግራችሁን ተነጋገሩ በማለት ፋንታ በፍቅረኞች መሃል ገብቶ “እውነቷንማ እንነጋገር አንቺ ከአከሌ ጋር አይቼሽ ከአከሌ ጋር ሰምቼብሽ” ብሎ ቢዘላብድ ምንም እንኳን የሚናገረው እውነት ቢሆንም “እውነቱ” ግን ሊጠግግ የነበረውን ሰባራ ትዳር ከእጅ አምልጦ እንደወደቀ ብርጭቅ እንክትክቱን ሊያወጣው የሚችል ክፉ ንግግር ነው::በነገራችን ላይ የዛሬ ሃምሳ አመት ገደማ የሰው ልጅ የግንዛቤ ደረጃ የንግግር ክህሎት በዛሬ ሚዛን መመዘንስ ተገቢና ያልተዛባ ፍርድ ያስፈርዳል ብላችሁ ታምናላችሁ?::

  ምሳሌ አንድ...

  አጼ ቴዎድሮስ የንግስና አክሊላቸውን ከመድፋታቸው በፊት የለየላቸውና ሃገር የፈራቸው ሽፍታ ነበሩ:: (ያው ሽፍታ ደግሞ ያላረሰውን የሚቅም ያልዘራውን የሚያጭድ ያልለፋበትን ደሞዝ የሚቀበል ዘራፊ ነው::በመንገድ የገጠመውን ምስኪን እሺ ካለው ዘርፎ ባዶ እጁን ሊሰደው አንገቱን ከነቀነቀበት ደግሞ በቢላዋ ሊሸልተው ይቻለዋል::በዚህም አጼ ቴዎድሮስ ብዙሃኑን ሲዘርፉ ከሌሎች ሽፍቶች ጋር አብረው  የተጠናከረ የሽፍትነት ስራን ሲሰሩ እንደኖሩ በማያጠራጥርና ግልጽ በሆነ ማስረጃ ዝክረ ነገራቸው ላይ ተቀምጧል::እዚህ ላይ የሟች ቤተሰብ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ነገር ማሰብ የህሊና ፍርድ እንድንፈርድ ይረዳናል::አልገብር ያሉትን የሸዋ ባላባቶች ክንድ ክንዳቸውን ጎምደዋል::በሽፍትነት የገንዘብ ክፍፍል ላይ የተጣሏቸውን ሽፍቶች ጉልበት ጉልበታቸውን ቆርጠውና ቁምጣ አስመስለዋቸው ዶሮ ጠባቂ አርገዋቸዋል::)ነገር ግን አንድ ቁም ነገር እንይ ይሄ ሁላ ግን በዛሬ ሚዛን መታየት ያለበት ጉዳይ አይደለም::በቅድሚያ በወቅቱ የነበረው ሃገርና ግዛትን የማስከበር ጉዳይ የፈርጣማ ጡንቻን የማሳየትና የመብለጥ ጉዳይ ምንም አማራጭ ያልነበረው መንገድ ስለነበር ነው::ሁለተኛውና ወሳኙ ቁም ነገር አጼ ቴዎድሮስ እንደ አውሬ ተበታትኖ ሲኖር የነበረን ህዝብ አንድ ማድረጋቸውና ሃገር ማረጋጋታቸው:በጠላት እጅ ከምሞት እራሴን አጠፋለሁ ብለው ሽጉጣቸውን መጠጣታቸው እንዲሁም ሌላው ሌላው ቁም ነገር ብዙ መጽሃፍና ብዙ መጣጥፍ ሊወጣው የሚችል ጉዳይ ስለሆነ የእርሳቸው ቅልጥም መቁረጥ ሽፍታ መሆንን ማውራቱ የሚጠቅመን ጉዳይ አይደለም::ወይም ደግሞ የአጼ ቴዎድሮስን ዝክረ ነገር በበቂና በጥሩ ሁኔታ ስለተረክን የእርሳቸውን ጥቂት ስህተቶች ወይንም ጭካኔ ብናወራም እንኳ ከህዝቡ ልቦና ውስጥ እርሳቸውን ማውጣት በጣም ከባድ ነው:: (ያው ቅድሚያ የሰጠነውና ያወራነው የእርሳቸውን መልካምነት ስለሆነ ክፉም ቢወራ አይጎረብጠንም::)የአክሊሉ ሃብተወልድንም ተጋድሎና ልፋት በብዛት ካወራንና በህዝቡ ዘንድ ፍቅር ከዘራን በኋላ ወደኋላ ልንመለስ እንችላለን::ክፉንና ደጉን ልንመዝን እንችላለን::አንድ ስርአት ውስጥ ክፉም ደግም ድርጊት ይኖራል::ቁም ነገሩ የትኛው ያመዝናል የሚለው ጉዳይ ነው የዚያ መንግስት መታወሻ::

  ምሳሌ ሁለት...

  የዛሬ መቶ ምናምን አመት ገደማ ወደሃገራችን የገቡ የትንፋሽ መሳሪያዎችን ለመጫወት የመሃል ሃገር ህዝብ ፍቃደኛ ስላልሆነና አዝማሪነት “የተረገመ” ሙያ ስለነበር እነ አጼ ምኒልክ አማካኝነት ከቤኒሻንጉል የመጡ ወጣቶች ይሄንን የትንፋሽ መሳሪያ እንዲጫወቱ ተደርጎ ህዝቡ ሲደነቅበት ነበር::ሆኖም ግን ህዝቡ “ቱልቱላ ነፊ ወላሞ” የሚል ተቀጽላ ስም ይሰጣቸው ነበር::ታዲያ ለዚህ ተጠያቂው የትኛው ብሄር ነው? አማራው ?ኦሮሞው? ትግሬው ? ጉራጌው ?ወይስ መላው ህዝብ ? የትኛውም ፍርድ ለማንም አይበጀን::ህሊና ትንሹ እግዚሃር እስከሆነ ድረስ ይሄንን ብሄር አከሌ ወይንም አከሊት እንዲህ አለችው የሚል ፍረጃ መቼውንም አይበጀን::እንዲያ ከተባለማ በአንዳንድ ኦሮሚያ አካባቢ በስሜታዊነት የሚባለው “ቁምጥናን “ይሄ” (እዚህ ጋር ብሄሩን መጥቀስ ተራ እውነት ስለሆነብኝ ዘልዬዋለሁ) ብሄር ነው ያመጣው”: እየተባለ የሚነገረው የመላው ኦሮሞ አቋም ነው ብለን ወስደን የተዋደዱና የተዋለዱ ብሄሮችን ልናጣላ ነው? ነው ወይ?::በመሰረቱ በስሜታዊነት ሰው የተናገረው ንግግር እንደ ቁም ነገር ከተቆጠረ ማናችምን ከታሪክ ፍርድ ተጠያቂነት አንድንም::

  ወዳጄ ሆይ !! ከዚህኛው “እውነት”ነው እያልን ከምናንቋርርለት ጉዳይ ይልቅ ግን በሰነድ በጽሁፍ በአርካይቭ በብዙ የሰዎች ምስክር የተረጋገጠውና እውነትነቱ ላይ ማንም የማይከራከርበት የአክሊሉ ሃብተወልድ የውጭ ሃገር የነጻነት ተጋድሎ :የኤርትራ በፌደሬሽን ወደ እናት ሃገሯ የመመለሷ ጉዳይ :የተባበሩት መንግስታት የሰውዬው የብቻቸው ትግል: በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሃገር ማገልገላቸው: ይሄ ሁሉ ስራቸው ተቆጥሮ በስማቸው ፋውንዴሽን ሳይቋቋም በስማቸው መንገድ ሳይሰየም ሳይሸለሙ ተገቢው የአዛውንትነት ክብር ሳይሰጣቸው የጥይት እራት ስለመሆናቸው ብናወራ አይሻለንምን? ኧረ እሱ ያዋጣናል ዘመዴ::የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረትስ ቢሆን አክሊሉ ሃብተወልድ ከእነ ከተማ ይፍሩና ከእነ አጼ ሃይለስላሴ ጋር ባያብሩ ኖሮ  ይሳካ ነበር ብሎ ማሰቡ ትንሽ ስሜታዊ አያደርግም ወይ?ከጣልያን ዘመን ጀምሮ በኦሮሞና በአማራ መካከል የውሸትም ይሁን የግነት ታሪክ እየተፈጠረ  ህዝብን ለመለያየት የሚሰራን ስራ ቆም ብለን እስካልመረመርን ድረስ ይሄ እንደቦረንትቻ ደም የለመደ ጸባችንን ሌላ የጭዳ በግ የሚሆነውን የአክሊሉ ሃብተወልድና የታደሰ ብሩን ቁርሾ ለምን እናቀርብለታለን?

  ለፍቅር የተሰጠ ልብ ለጥላቻ ግዜ አይኖረውም::ቅድሚያ ግን ባለታሪካችንን አክሊሉ ሃብተወልድን ጠንቅቀን እንወቃቸው::ያን ግዜ ሰሩ የተባለውን መልካም ስራ ስንኮራበትና የታሪክ ጎዶሏችንን ስንሞላ የመውደዱም የመጥላቱም መብቱ ይኖረናል::ስህተታቸው “ቢኖር እንኳ” እደግመዋለሁ “ቢኖር እንኳ” ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ (ምእንቲ ምጎጎ እታ አንጭዋ ትሕልፍ)ብለን እንደምናልፋቸው የሰናፍጭ ቅንጣት ታክል ጥርጥር የለኝም::

  //ክቡር መተኪያ ሃይለሚካኤል// (Facebook /kibur metekia hailemichael) ( Kibur7@gmail.com)
 • loader Loading content ...
 • @Kibur Metekia Hailemichael   8 months ago
  Sewasewer

  ባለ ግዜ ሆይ ጠላትህን በቁልቁለት አታባረው የዞረብህ ለት ዳገት ይሆንብሀልና
  (ክቡር መተኪያ ሀይለሚካኤል)

  /facebook\kibur metekia hailemichael

  ምግብ በልተን በጠገብን ሠአት “ከዚያ በሁዋላ ምግብ አይኑንም አላይ” እንላለን:: ጥምብዝ ብለን ሠክረን ያደርን ለታ በንጋታው በሀንጎቨር “መጠጥ የደረሠበት አንደርስም” ብለን እንምላለን::ሠው ነንና ነገ ሥሜታችን ምን ሊሆን እንደሚችል ከእሥከዛሬው የመጠጥ ጥም ወይንም የምግብ ፍላጎታችን ባህርይ ትምህርት አንወሥድም::
  ስልጣን ይሉዋት ነገርም እንዲህ ነች...እንደ ወይን ጠጅ እየተጎነጩዋት ሢሄዱ እያሣሣቀች እያጫወተች በአፍጢም እሥክትከነብል ድረሥ "ካንቺ ሞት ይለየኝ" ታሥብላለች::በታሪክ ተመዝግበው ያሉ አምባገነኖች ፍጻሜያቸው ምን እንደሆነ በትረ ስልጣኗን የጨበጡ መሪዎች ለሰከንድ እንኳ ሊያስቡት የማይፈልጓት ሃቅ ነች::አንዴ የሥልጣንን ሥኳር ከላሡ ወዲህ ወደዛች ወንበር ዝር ያሉትን ሁላ አባቴ ነው:እናቴ ነች: ወንድሜ :እህቴ :ልጄ: ዘመዴ: ወዳጄ የክፉ ቀን ጓዴ ብለው ሳያመነቱ ከፍ ብለው አንገቱን ዝቅ ብለው ብልቱን ሊቆርጡለት ሢወስኑ ሁለቴ እንኳ አያስቡም::
  ከዚህ ጽሁፍ ጋር አያይዤ የለጠፍኩት የእነዚህ የሶስት ሰዎች ምስል የሀገር መሪ የሚለው የቀድሞ ማእረጋቸው ከላያቸው ተገፍፎ “የቀድሞው ፕሬዚደንት” የሚል ተቀጽላ ተለጥፎባቸዋል::እንዲያውም ሁለቱ “ሟቹ” እየተባሉ ይጠሩ ጀምረዋል:: “ሟቹ የየመን ፕሬዚደንት አሊ አብደላ ሳልህ:ሟቹ የሊቢያው ፕሬዚደንት ሙአመር ጋዳፊና የቀድሞው የግብጽ ፕሬዚደንት ሞሃመድ ሆስኒ ሙባረክ”::

  የአሊ አብደላ ሳልህ ነገርና ፍጻሜያቸው::

  ከቀናት በፊት የኳታሩ የዜና ማሰራጫ አልጀዚራ በእርስ በርስ ጦርነት እየታመሰች ያለችው የመንን ከሠላሣ አመታት በላይ የመሩዋትና በህዝብ አመጽ ሥልጣናቸውን የለቀቁት የቀድሞ ፕሬዚዳንቷ አሊ አብደላ ሣልህ በሁቲ አማጽያን እንደተገደሉ በሰበር ዜናው አስታወቀ::ሠውዬው እንደነ ጋዳፊ እንደ ጋማል አብዱል ናሥርና እንደነ መንግሥቱ ሀይለማርያም ሥልጣንን በአቁዋራጭ ነበር የያዙት::እንዴት ቢባል በታጣቂዎች በተገደሉት የሰሜን የመን ፕሬዚደንት አህመድ ቢን ሁሴን አል ጋህሲም ምትክ ወታደራዊ ካውንስል ሲቋቋም በቅድሚያ አባል ከዚያም በፓርላማው ምርጫ ፕሬዚደንት በመሆን ነው:: 
  በቱኒዝያ ተቀስቅሦ የአረብ ሀገራትን ከዳር እሥከዳር ያናወጠውና በፖለቲከኞቹ አጠራር "the arab spring"በመባል በሚታወቀው እንቅሥቃሤ ከተናጡ ሀገራት መካከል አንዱዋም የመን ነበረች::ሰሞኑን መገደላቸው የተነገረላቸው አሊ አብደላ ሳልህም የመን በአመጸኞቹ በምትናጥበት በአንዱ ቀን ሀገር አማን ብለው በቤተ መንግሥታቸው ውሥጥ ነበሩ::በፍጹም ባላሰቡት አጋጣሚም ከአማጽያኑ የተተኮሠባቸው አዳፍኔ አራት ጠባቂዎቻቸውን ሢገድል እርሣቸው የድመት ነብስ ይዘው ኖሮ በተአምር ተረፉ።ከዚያም የድምጽ መልእክት በመላክ በህይወት መትረፋቸውን ከገለጹ በኋላ በንጋታው ሳውዲ በሚገኘው የህክምና ማእከል ህክምና ተደርጎላቸው ለደጋፊዎቻቸውም ከፈንጂ የተረፈና ብረት ምጣድ መሥሎ የተለበለበ ፊታቸውን በከፊል ጠምጥመው “አለሁ እኖራለሁ እንተያያለን” ብለው እየፎከሩ ወደቲቪው ብቅ አሉ::ከወራት የህክምና ቆይታ በኋላም እንደ እባብ ቆዳቸውን ገፍፈው ጡንቻቸውን አደድረው ወንበሯን ገና መች ጠገብኳትና ብለው የስልጣናቸውን ብሎን ያጠባብቁ ጀመር::ሆኖም ግን የህዝብ ግፊቱ እየበዛባቸው መጥቶ ስልጣናቸውን ለምክትላቸው ሊያስረክቡ ተገደው ነበር::
  አሊ አብደላ ሣልህ የሚመሯት የመን ከሀገሬ ኢትዮጵያ በባሠ ድህነት እግሩን አንፈራጦ የሚኖርባት ሀገር ሆና ሣለ ሠውዬው ግን 70 ቢሊየን ዶላር (ልብ በሉልኝ ሠባ ቢሊየን ዶላር)በተለያዩ ሀገራት እንደቀረቀሩ ታውቆባቸው ነበር::ሙሠንነታቸው አምባገነንነታቸውና የመሪነት እጥረቱን ህዝቡ መቀበል እንዳቃተውና ግድያው እሥራቱ አፈናው የትም ድረሥ እንደማያሥኬዳቸው ያወቁት አሊ አብደላ በቅርቡ ሥልጣናቸውን ለቀውና ከሁቱ አማጽያን ጋር ይፋዊ በሆነ ስምምነት አብሮነታቸውን ገልጸው ሳውዲ መራሹን ጦር ሲመክቱ ኖሩ::በፖለቲካም ቋሚ ወዳጅ ዘላቂ ጠላት እንደሌለ ጠንቅቀው የሚያውቁት አሊ አብደላ ቆዩና ደግሞ “ከሁቲ አማጽያን ተገንጥያለሁ” ብለው ባወጁበት ሰሞን ነበር ከአጋሮቻቸው ከሁቲ አማጽያን ጋር መፋለም የጀመሩት::ከአሣዳጃቸው ሣውዲ አረብያ ጋር አብሬ ነኝ የሰላሙን መንገድ አብረን እንፈልጋለን ማለት በጀመሩ በሣምንቱም ባሣደጉት ውሻ ተነከሡ::
  በማህበራዊ ድረገጾች የተለቀቀው የአሊ አብደላ ሣልህ ቪድዬ ለማየት ከፍተኛ ድፍረትን የሚጠይቅ ነበር።እንዲያ በሚሄዱበት ሁላ ጋሻ ጃግሬያቸው አይኑን ከግራ ቀኝ እያንቀዠቀዠ እንዳላጀባቸውና መሬት እንዳላረገደችላቸው ቀይ ምንጣፍ እንዳልተነጠፈላቸው የግራ ጭንቅላታቸው ተገምሦ ሙሉ ልብሣቸውን እንደለበሡ በአበያ ጨርቅ ተጠቅልለው ሬሣቸው እንደ አህያ ሬሣ በየመንገዱ እየተጎተተ በመኪና ላይ ሢጫን ታየና የሰውየው ሞት ተረጋገጠ::

  ጋዳፊ...

  በአንድ ወቅት ወዳጅና ጓደኛ ሆነው በየስብሰባው ሲተቃቀፉ ይታዩ የነበሩትና እዚሁ ፎቶ ላይ ያሉት የሊቢያው መሪ ሞአመር ጋዳፊም ሥልጣን የያዙት እንደኛው ደርጎች የህዝቡን አመጽ በድንገት ቀልብሠው በአቁዋረጭ ነበር::ያን ግዜ ጋዳፊ ሥልጣን ሢይዝ ገና የሀያ ሠባት አመት ጎረምሣ ነበር..ይሄን የሊቢያ ነዳጅ እየሸጠ ያጠራቀመው ዶላር የልብ ልብ ሠጥቶት ሥልጣንን እንኩዋን ሊያሥረክብ የገዛ ህዝቡን በጥይት ሢረፈርፍ ኖረ:: የአረብ ሀገር አመጽ ሢነሣ  አማጽያኑን ጠርቶና አግባብቶ እንደመደራደር ወይም ሥልጣንን ቀሥ ብሎ እንደ ሙጋቤ እንደመልቀቅ "እነዚህ አይጦችና በረሮዎች" እያለ ሢሣደብ ላየ ሠው ፍጻሜው እንደ ውሻ ከትቦ ውሥጥ መጎተት ነው ያለ ማንም አልነበረም።

  ሙባራክ...

  የግብጹ ፕሬዚደንት መሀመድ ሆሥኒ ሙባረክም ቢሆን ሥልጣን እይዛለሁ ብሎ በህልሙም በውኑም ባላሠበው አጋጣሚ ነው ድንገት ከወንበሯ ላይ እመር ብሎ የተከመረው::.በአንድ የህዝባዊ ዝግጅት ላይ በአንድ አክራሪ እሥላም ወታደር የግብጹ ፕሬዚደንት አንዋር ሣዳትን በጥይት ሢገደል በትረ ሥልጣኑን የወቅቱ ምክትል ፕሬዚደንት ሆሥኒ ሙባረክ ያዘና ግብጽን እንዳሻው ሢገዛ ኖሮ ይሄው የአረብ ሀገራት አመጽ ሢቀሠቀሥ ልክ ሙጋቤ ከሥልጣን እንደወረደው አወራረድ ሣይታሠብ ሥልጣኑን ለቀቀና በተሽከርካሪ ቃሬዛ እየተጎተተ ፍርድ ቤት ለፍርድ ቤት መመላለሥ ቁርሥና ምሣው ሆነ።ከጋዳፊ ከአሊ አብደላና ከሆሥኒ ሙባረክ አወዳደቅ አንጻር የሆሥኒ ሙባረክ ከሥልጣን አወራረድ ፍጹም የተሻለና የከብር ነው ማለት ይቻላል:: ይሄም ምናልባት ከየመንና ከሊቢያ ህዝብ ይልቅ የግብጽ ጦርና ህዝብ ፍጹም የሠለጠነና ህዝባዊ ከመሆኑ አንጻር ሣይሆን አይቀርም::

  እኛና እነሱ...

  በተለያየ አጋጣሚዎች ዛሬ ላይ ከሥልጣናቸው የተወገዱት እነዚህ ሦሥት መሪዎች ከሀገራችን ኢትዮጵያ ጋር በክፉም በደግም የተቆራኘ አንዳንድ ገጠመኞችና ታሪክ አላቸው::

  ሙባረክና ግብጽ

  ግብጽ የኢትዬጵያ ታሪካዊ ጠላት ከመሆኑዋና በአባይ ወንዝ ዙሪያ ከዛሬ ነገ ይፈነዳል በሚባለው ጦርነት ሁሌም ሥትታወሥ ብትኖርም በ1980 ዎቹ አጋማሽ አማታት ለአፍሪካ ህብረት ሥብሠባ ወደ አዲሥ አበባ የመጡት የግብጹ ፕሬዚደንት ሆስኒ ሙባረክ በወቅቱ የአፍሪካ ቀንድን እቆጣጠራለሁ እያለ ሢደነፋ በነበረው አል ኢትሀድ አል ኢሥላሚያ ታጣቂዎች ቦሌ መንገድ ላይ አደገኛ የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸው ነበር።ሆኖም ጥይት የማይበሣውን መኪና በአንድ የደህንነት አማካሪያቸው ምክር አሥጭነው መጥተው ሢጉዋዙበት ሥለነበሩና ንቁ ጠባቂዎቻቸው አይናቸውን ሣያራግቡ ሢጠብቁዋቸው ሥለነበር እንዲሁም በየህንጻው ማማ ላይ ተሠቅለው የእንግዶችን ደህንነት ሢጠብቁ የነበሩት የኢትዮጵያ ነጥሎ ተኩዋሽ ወታደሮች ገዳዮቻቸውን ተኩሠው በመጣል ህይወታቸውን አትርፈውላቸዋል።

  ሊቢያና ጋዳፊ...

  ጋዳፊ መቼም ታሪካቸው ተነግሮ አያልቅም..በአንድ ወቅት ስድስት መቶ አጃቢዎቻቸውን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ እገባለሁ ያሉት ጋዳፊ ከወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሬዚደንት ከመንግሥቱ ሀይለማርያም የደህንነት ሠራተኞች ጋር ከፍተኛ ጸብ ገጥሞዋቸው እንደነበር ይነገራል።በወቅቱ የደርግ የደህንነት ሠራተኞች “ይሄን ያክል በኛ ጥበቃ አልተማመንም ካልክ ቀኝ ሁዋላ ዞረህ ወደሀገርህ ተመለስ” ብለው እንዳባረሩትና ከዚያም ሁዋላም ኢትዮጵያን ሣለ ደርግ እንዳልረጋጣት ይወራ ነበር።

  አሊ አብደላ ሳላህና የመን...

  አሊ አብደላ ሣላህ በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግሥት በጽኑ ሢፈልገው የነበረውንና የእድሜ ይፍታህ ፍርድ በሌለበት ፈርዶበት የነበረውን የግንቦት 7 ምክትል ሊቀመንበሩን አንዳርጋቸው ጽጌን ለትራንዚት ካረፈበት የመን አየር ማረፊያ በቁጥጥር ሥር አውሎት ለኢትዮጵያ መንግሥት እጁን ይዞ መሥጠቱ በወቅቱ ከፍተኛ ውዝግብ አሥነሥቶ ነበር::የመንግሥት ደጋፊዎች መንግሥት በሽብርተኝነት የፈረጀው አንዳርጋቸውን የመን አሣልፋ መሥጠቱዋ የምን ግዜም ወዳጃችን መሆኑዋን ያሣያል ሢሉ ታቃዋሚዎች በበኩላቸው ሀያ ሚሊዮን ዶላር ተቀብላ ከአቪዬሽን ህግ ውጪ እንግዳዋን አሣልፋ ሠጠች እያሉ ዛሬ ላይ የሞቱትን የየመኑን ፕሬዚደንት የእጃቸውን አገኙ እያሉ ሢያወሩ ተደምጠዋል።
  ያም ተባለ ያ ዛሬ ላይ ሦሥቱም ሥልጣናቸው ላይ የሉም ግዜ የሠጠን እኛ ይሄንን ሁላ ታሪክ ቁጭ ብለን እናያለን።አምባገነን መሪዎች ይሄንን አይነት አሠቃቂ አወራረድ እያዩ ለግፈኛ አገዛዛቸው ምክንያት መሥጠታቸውን አጫፋሪያቸውን መልካም ስማቸውን እያወደሱ ሲያስወሩ ፈጣሪ እስከፈቀደው ቀን ይኖራሉ። "እሱ እኮ በህዝብ ስላልተመረጠ ነው እኔን ህዝብ ይወደኛል መርጦኛል ህዝቤና ፓርቲዬ ይፈልገኛል" እና የመሣሠሉት ምክንያቶች መሠጠታቸውና ከሥልጣን ወንበር ላይ ተሠፍተው መክረማቸውን ይቀጥላሉ።ህዝብም ማሌቴ ቄል ፋሬሥ እያለ ማጉተምተሙን ይቀጥላል:: (ማኔ ማለት፥ እግዚአብሔር መንግሥትህን ቆጠረው ፈጸመውም ማለት ነው። ቴቄል ማለት፥ በሚዛን ተመዘንህ፥ ቀልለህም ተገኘህ ማለት ነው። ፋሬስ ማለት፥መንግሥትህ ተከፈለ፥ ለሜዶንና ለፋርስ ሰዎችም ተሰጠ ማለት ነው።) 
  ሀገር ለመሪው “ሚስቱ”: ሃገር ለህዝብ “እናቱ” የሆነች ይመስላል:: መሪው ሚስቴን እንዳሻኝ ባረጋት ማናባቱ ያዘኛል ምን የጎበረበት ይላል ::እንዳሻው ወዲህ ሂጅ ወዲህ ተመለሽ ይላል።ህዝብ ደሞ ሀገሩን እናቴ ነች ይላል ጥቃቱዋ መከፋቱዋ መበደሉዋ መነካቱዋ ያንገበግበዋል።ህዝብ አልቅሶ ሳያባራ የበቀል ሰይፉ ከአ ፎቱ መዝዞ የአምባገነን መሪዎቹን ሬሳ እንደ አህያ ሬሳ በየመንገዱ ሲጎትት እንደ ሆሊውድ ፊልም ማየት ስራችን ከሆነ ቆየ::ነገም ፍጻሜ መንግስታቸው የሚበሰር የበርካታ አምባገነን መሪዎችን ፍጻሜ ጊዜ ደጉ ጊዜ ጀግናው እንደማያሳየን ማን ያውቃል?

  ማንም!!


   


 • loader Loading content ...
 • Sewasewer
  አሃዱ ሳቡሬ........አጠገበኝ ወሬ
  ===ክፍል ሁለት===
  (ክቡር መተኪያ ሃይለሚካኤል) 
  =ጋዜጠኝነት ግዞተኝነትና ዝነኝነት=
  ስለ ጉምቱው ጋዜጠኛና አምባሳደር አሃዱ ሳቡሬ በመጀመሪያው ክፍል ወጋችን ከውልደት እስከ እድገታቸው አውርተናል::ከዚያም በወቅቱ እንደ ብርቅ ይታዩ  በነበሩ በቅድሚያ የፈረንሳይ በመቀጠል የጣልያን ትምህርት ቤቶች ገብተው በመማር ቀደም ብለው ከሚያውቁት ቋንቋ በተጨማሪ የፈረንሳይኛና የጣልያንኛ ቋንቋ በማወቃቸው በአስተርጓሚነትና በጸሃፊነት እንደተቀጠሩ: ከለውጡ በኋላም ወደ ጋዜጠኝነቱ ቀስ በቀስ እንደገቡበት ዘክረናል::በዚህኛው ክፍል ወጋችን ደግሞ አሃዱ የህይወት መስመራቸው እንዴት ባለ መልኩ እንደተለወጠ እናያለን:: 
  1953 ወርሃ ታህሳስ
  ለዝነኛው የ1966 የኢትዮጵያ አብዮት መንደርደሪያ የሆነውና የንጉሰ ነገስቱን ዙፋን በብርቱ የነቀነቀው ክስተት የተከሰተው በ1953 አመተ ምህረት በወርሃ ታህሳስ ነበር::የቀዳማዊ ሃይለስላሴ የክብር ዘብ ወታደራዊ ክፍል ሃላፊ የነበሩት ጀነራል መንግስቱ ንዋይና ታናሽ ወንድማቸው ገርማሜ ንዋይ “የንጉሰ ነገስቱ ስርአት ፍጹም ፊውዳላዊ ስለሆነ አስተዳደሩ ህገ መንግስታዊና ስልጣኑ የተገደበ መሆን አለበት” በሚል የሃሳብ መነሻነት የቀዳማዊ ሃይለስላሴን መንግስት ለመገልበጥ በድብቅ ተስማሙ::ለዚሁ አላማቸውም ሃሳባቸውን ተቀብለው የተስማሙ ባለስልጣኖችን ከጎናቸው በማሰለፍ ለለውጡ ደንቃራ ይሆናሉ ብለው ያሰቧቸውን ሹማምንት ደግሞ በቅድሚያ ገነተ ልኡል ቤተ መንግስት (የዛሬው ስድስት ኪሎ ዩንቨርሲቲ)ካሰሯቸው በኋላ በጥይት ደብድበው ረሸኗቸው::ከዚያም ወንድማማቾቹ ጀነራሎች በኮተቤ መስመር ነብሳቸውን ለማዳን ሲሸሹ ድንገት የንጉሱ ታማኝ ዘቦች ደርሰው ከበቧቸውና እጃቸውን ሊይዟቸው በተቃረቡ ግዜ የመንግስቱ ንዋይ ታናሽ ወንድም “በጠላቶቻችን እጅ አንወድቅም” በማለት በቅድሚያ ወንድማቸው ገርማሜ ንዋይ ላይ ተኮሱና ከዛ አፈሙዙን ወደራሳቸው አዙረው ተኮሱና እራሳቸውን አጠፉ::ገርማሜ ንዋይ እራሳቸውን ከመግደላቸው በፊት የተኮሷት ጥይት የታላቅ ወንድማቸውን ነብስ ሳትነጥቅ አገጫቸውንና ጉንጫቸውን አቁስላ ወደቀች::ገርማሜም በአሳዳጆቻቸው እጅ ወደቁ::
  ይህ የሃገሪቱ ጉምቱ ጉምቱ ባለስልጣናትን እንደ ጭዳ በግ ደማቸውን ያንዠቀዠቀ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ሲደረግ አሃዱ ሳቡሬ በፖለቲካ ታዛቢነት ኮንጎ ሄደው ነበር::የዛን ግዜዋ ኮንጎ በትጥቅ ትግልና በፖለቲካዊ ድርድር ከቤልጂየም ነጻ ለመውጣት እልህ አስጨራሽ ትግል አድርጋ ስታበቃ ነጻነቷን ይሁን ብለው ነጮቹ ፈቀዱላት::ሆኖም ግን የሰላሳ አራት አመት ጎልማሳው ፓትሪክ ሉሙምባ ጠቅላይ ሚኒስቴር ተደርጎ ከተመረጠ በኋላ ፍጹም ሃገር ወዳድና የነጮችን የእጅ አዙር አገዛዝ የማይቀበል ስለነበር ምእራባዊያኑ ፕሬዚደንቱን ካሳ ቩቡን ጭምር አሳመጹበት::በአልማዝና በነዳጅ ሃብቷ የበለጸገችዋን የካታንጋን ግዛት ደግሞ ሙሴ ቾምቤ ተከታዮቹን ይዞ ድርሻዬ ነች አለ::ይሄንን የፖለቲካ ውጥንቅጥ መፍትሄ ለመስጠትና የሰላም አስከባሪ በመላክ ሃገሪቷን ሰላም ለማድረግ በወቅቱ ነጻ ሃገር የነበረችው ኢትዮጵያና ግብጽ ነበሩ ቀድመው የተገኙት::እንግዲህ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሰላም ብላ የፖለቲካ ታዛቢዋ አሃዱ ሳቡሬን ወደ ኮንጎ በላከችበት ወቅት ይህ የታህሳሱ ግርግር ተከሰተ::
  አሃዱ አዲስ አበባን እንደረገጡ እንደ ጋዜጠኝነታቸው በኢትዮጵያ ተከስቶ ስለነበረው የፖለቲካ ቀውስ የመፈንለ መንግስት ሴረኞች ስላደረጉት እንቅስቃሴ ስለወደመ ውድመት አድመኞቹ ስላከሰሩት ኪሳራና ስለ ህዝቡ አስተያየት ዋነኛ የመንግስት ልሳን በሆነው የአዲስ ዘመን መጽሄት ላይ ተከታታይ ጽሁፍ እንዲጽፉ በተለይ ደግሞ የፍርድ ቤቱን ውሎና የችሎት ሁኔታ እንዲዘግቡ ታዘዙ::በዚህም ግዜ ግራ ቀኙን በማየት የወቅቱ የህዝቡን የአስተሳሰብ ንቃተ ህሊና ደረጃ በማመዛዘንና የመፈንቅለ መንግስት ጠንሳሾች ያሰቡትን አላማ ከግምት ውስጥ በማስገባት አዲስ ዘመን መጽሄት ላይ በተከታታይ የግራና የቀኙን አስተሳሰብ : የመንግስትና የተቃዋሚዎቹን ሁኔታ ፍጹም ሚዛናዊነት በተመላበት ሁኔታና በተለይ የመፈንቅለ መንግስቱ ጠንሳሽ ጀነራሎች ሃዘኔታ የተመላው (SYMPATHETIC) ጽሁፍ አቀረቡ::እንግዲህ እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባ አንድ ቁም ነገር አለ::የንጉሰ ነገስቱ ዙፋንን መመኘት ቀርቶ ማለም አንገት ላይ መታነቂያ ሸምቀቆ ማስገባት በሆነበትና የዘውዳዊው ስርአት ልሳን በሆነው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ንጉሱን ከመደገፍ ፈቀቅ ብሎ ንጉሱ ላይ ቅዝምዝም ለሰነዘረ ሃዘኔታ አዘል(SYMPATHETIC)ጽሁፍ መጻፍ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለመገንዘብ ቀላል ነው::ስለዚህ ጉዳይ አሃዱ ሲጠየቁ “በእርግጥ በመፈንቅለ መንግስቱ ሴራና ተሳትፎ ውስጥ በፍጹም አልነበርኩበትም::ነገር ግን ለውጥ እንደሚያስፈልግ በጽኑ አምንበት ነበር በዚያ ላይ የመፈንቅለ መንግስቱ መሪዎች በተለይ መንግስቱ ንዋይ የቅርብ ጓደኞቼ ነበሩ” ብለዋል::
  ከታሪክ በተደጋጋሚ እንደሰማነው እድሜ ፈቅዶልንም እንዳየነው በተለያየ አጋጣሚም እንደታዘብነው ፖለቲካ የህሊና ዳኝነት የሞራል ህግ ይሉት ጨዋታ አይጥማትም::(ፖለቲካ የጥሎ ማለፍ ዋሽቶ የማሳመን ዘላቂ ጥቅምን የማስከበር ጨዋታ ነውና)::አሃዱ ሳቡሬ የጋዜጠኝነት ሙያ ስነምግባር (PROFESSION ETHICS) በሚያዘው መልኩ የግራ ቀኙን እውነት በመዘገባቸው: መንግስቱ ንዋይ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው ተክለሃይማኖት አደባባይ ተሰቅለው እየተወራጩ ሲሞቱ ቦታው ድረስ ሄደው ባለማየታቸውና ቀደም ያለው የመንግስቱ ንዋይና የአሃዱ ጓደኝነት ታይቶና ተገምግሞ ከሚሰሩበት የመገናኛ ብዙሃን መስሪያ ቤት ተነስተው በግዞት ወደ አርሲ ጠቅላይ ግዛት ተላኩ::አንድ ኩንታል ማኛ ጤፍ በአምስትና በአስር ብር ሙክት በግ በአስራ አምስት ብር ይበላ በነበረበት በዛ በጥጋብ ዘመን አሃዱ ይከፈላቸው የነበረው የአምስት መቶ ብር ወርሃዊ ክፍያ እጅግ የተመቻቸ ኑሮን እንደሚያኖራቸው ሲታወቅ በአዲስ ዘመን ለጻፉት ጽሁፍ ቅጣት ወደ አርሲ በግዞት ሲላኩ የደሞዛቸው ሶስት አራተኛው ተቀንሶ በደሞዝተኛ ደንብ ሳይሆን በግዞተኛ አግባብ መንግስት ቆጥሯቸው አሰላ ከተማ ውስጥ በምትገኝ አንዲት አነስተኛ የአፈር ቤት ውስጥ ኑሯቸው ተወስኖ በጠባቂዎቻቸው “ወዲህ ተመለስ ወዲህ ተቀለስ” የሚባሉ በቀን አንድ ግዜ ለመናፈስና የቤተ ክርስትያን ደጃፍ ለመሳም የሚፈቀድላቸው እስረኛ ሆኑና አረፉት::
  ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ሃይለስላሴ በተለያየ ግዜ የታሰሩ ሰዎችን በንግስና በአላቸው በበአለ ሲመታቸው በአዲስ አመትና በተለያዩ  ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ለእስረኞችና ለግዞተኞች ምህረት የመስጠት ጥሩ ልማድ ነበራቸው::አንድ ቀንም አሃዱ ባልጠበቁት ምክንያት ከግዞት ሃገራቸው ከአርሲ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡና ለንጉሰ ነገስቱ በአለ ሲመት በወቅቱ እንደነበረው ልማድ ለንጉሰ ነገስቱ እጅ እንዲነሱ ተደረገ::ከዚያም ከጥቂት ግዜ በኋላ “በሶማሊያ የግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ሃይለስላሴ ልዩ መልእክተኛና ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር” የተሰኘ ግዙፍ ማእረግ ተሸከሙ::አሃዱ ወደ ሶማሊያ ከተላኩበት ዋነኛ ምክንያት የሱማሌኛ ቋንቋ ችሎታቸው ታይቶ  ቢሆንም በሹመት ስም ገለል እንደማድረግ ወይንም እራሱን የቻለ ግዞት ሊሆን እንደሚችል ብዙሃኑ ይስማሙበታል::
  ሶማሊያ በተባበሩት መንግስታት ጉባኤ እንደ ሃገር እውቅና ሳይሰጣት በነበረበት ወቅት ኢትዮጵያ በሶማሊያዋ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ  ቆንስላ ጽህፈት ቤት ከፍታ ኤርትራዊውን አቶ ፍጡር አብርሃን ቆንስላ ጀነራል አድርጋ ሾማ ነበር::ሶማሊያ እንደ ሃገር እውቅና ካገኘች በኋላ ደግሞ ባለ ሙሉ ስልጣን ተደርገው ሲሾሙ አምባሳደር አሃዱ ሳቡሬ የመጀመሪያው ሰው ናቸው::አሃዱ በሶማሊያ አምባሳደር በነበሩበት ወቅት ሶማሊያ ከኢትዮጵያ አንድ ሶስተኛውን ግዛት ይገባኛል ብላ የምትጠይቅበት ከዛሬ ነገ የጋሻ ጃግሬዋን የሶቭየት ህብረት እርዳታን ተማምና መጣሁ መጣሁ እያለች ኢትዮጵያን የምታስፈራራበት አስቸጋሪ ወቅት ነበር::ያም ሆኖ አስቸጋሪውን ግዜያቸውን በብቃት ተወጥተው አምስት አመት ያክል በአምባሳደርነት ካገለገሉ በኋላ ወደ አዲስ አበባ መጡና አፍታም ሳይቆዩ ቀድሞ ሃገሪቷን ወደሚያውቋት ወደ ያኔዋ የፈረንሳይ ግዛት ጅቡቲ “በአምባሳደር ማእረግ ቆንስል ጀነራል”ተደርገው ተላኩ::በዚያም ለሰባት አመታት ያክል በአምባሳደርነት ማእረግ የቆንስላው ጀነራል ሆነው ለሰባት አመት ያክል እንደቆዩ የየካቲቱ አብዮት መጣ::
  በወርሃ የካቲት የተለኮሰው የኢትዮጵያ አብዮት አሉታዊም ይሁን አዎንታዊ ስር ነቀል ለውጥን በሃገራችን ስለማምጣቱ ታሪክ ምስክር ሆኖ ይነግረናል::በወቅቱ የተቃዉሞ ሰልፍ እዚህም እዚያም በነበረበትና ሁሉም በየሙያ ማህበሩ የተለያየ ጥያቄዎችን ያነሳ ስለነበር ወታደሩም በበኩሉ የጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሃብተወልድ ካቢኔ ተበትኖ በምትካቸው የቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው ልጅ የሆኑት ልጅ እንዳልካቸው መኮንን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ካቢኔያቸውን እንዲያዋቅሩ ጥያቄ አቅርቦ ጥያቄው በንጉሰ ነገስቱ ተቀባይነት አገኘ::በዚህ ግዜም ልጅ መኮንን እንዳልካቸው መኮንን ጅቡቲ በአምባሳደርነት እያገለገሉ ያሉት አሃዱ ሳቡሬ ጋር በመደወል የአዲሱ ካቢኔያቸው አባል እንዲሆኑና የማስታወቂያ ሚኒስቴርንም በሚኒስትርነት እንዲያገለግሉ ግብዣ አደረጉላቸው::
  አሃዱ ይሄንን ጥሪ እያመነቱ ከተቀበሉት በኋላ ቀድመው የሚያውቁትንና ለአስራ ሁለት አመታት ያገለገሉበትን ቢሮ ከብዙ አመታት በኋላ ተመልሰው ሲመጡ የሚያውቋቸው ሰዎች ሁሉ ሁሉ ወይ በዝውውር አልያ በሌላ ምክንያት ከቢሯቸው ስላልነበሩ ፍጹም ባይተዋርነት ተሰማቸው::ቀደም ብለው የሬዲዮ ፕሮግራም አብረው ከሚያቀርቡት ከዝናኛው ጋዜጠኛ አሰፋ ይርጉና ከሌሎች እጅግ በጣም ጥቂት ጋዜጠኞ በስተቀር ሌሎች አዳዲስና ወጣት ጋዜጠኞች ቤቱን አጥለቅልቀውት ነበር::አሃዱ በዚህ የባይተዋር ቢሮ ውስጥ ሳሉ ግን አንድ ያልታሰበ ችግር ገጠማቸው::
  አዲስ አበባ እንዲያ ባለው በለውጥና በነውጥ ማእበል እየተናጠች በየቦታው የስራ ማቆም አድማ እየተካሄደ በየቢሮው ሰራተኛው አለቃውን አልታዘዝም እያለ በየካምፑ ወታደሩ አዛዡን እያገተና እያሰረ የነበረውን ሁኔታ አሃዱ የማስታወቂያ ሚኒስትርነታቸው በብሄራዊ ሬዲዮ ይተላለፍ ዘንድ አዘዙ::ይሄን ግዜ የንጉሰ ነገስቱ የቅርብ ሰው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳልካቸው መኮንን “እንዴት ተብሎ” ብለው ሞገዱ:: “አሁን በዚህ ሁኔታ እነዚህን ሁኔታዎች በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ማስተላለፍና መዘገብ በእሳት ላይ ቤንዚን እንደማርከፍከፍ ያለ ማባባስ ነው”ብለው ነበር ልጅ እንዳልካቸው ለአሃዱ በአጽህኖት የነገሯቸው::አሃዱም በበኩላቸው “የአመጹ ተሳታፊዎችን አላማና እውነት እንዲህ ነው እንዲህ መደረግ አለበት እንዲህ ያለ ሃሳብ አላቸው ወዘተረፈ እያልን ደጋፊም ነቃፊም አንሁን እንጂ በአለም አቀፍ ደረጃ በእነ “AJANCE FRANCE PRESS” በእነ “REUTERS” በእነ “ASSOCIATED PRESS” እኔ በሌሎች ታላላቅ መገናኛ ብዙሃን የተዘገበ ዘገባን እኛ ላለማጋጋልና <የአመጻው እሳት ላይ ቤንዚን ላለማርከፍከፍ> ብለን አለም ያወቀውን ጸሃይ የሞቀውን ሃቅ ብንደብቅ ትርፉ ትዝብት ነው::”ብለው የአመጹን እንቅስቃሴ የቻሉትን ያክል በብሄራዊ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ማስተላለፋቸውን ቀጠሉ::ይህ ጉዳይ ደግሞ ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ለልጅ እንዳልካቸው መኮንን ፈጽሞ  የሚዋጥ ስላልሆነላቸውና ከአሃዱ ጋር መስማማትም ስላልቻሉ አሃዱ በድጋሚ ከሚዲያው ስራ ተለይተው ወደ ጅቡቲ አምባሳደርነታቸው ተመለሱ::
  ከዚያስ ?
  ከዚያማ ጅቡቲ በአምባሳደርነት ስራቸው ሃገር አማን ብለው ስራቸውን እየሰሩ ሳለ የመስከረም ሁለት 1967 ለውጥ ተከሰተ::የአሃዱስ እጣ ፈንታ ?
  ይቀጥላል.....!!!
 • loader Loading content ...
 • Sewasewer

  አሃዱ ሳቡሬ........አጠገበኝ ወሬ
  ===ክፍል አንድ===
  (ክቡር መተኪያ ሃይለሚካኤል)

  “ታሪክን በመጽሃፍ መልኩ ሰንዶና ደጉሶ ለማቅረብ የእለት ተእለት ዘገባን ሲያጠናቅሩ የኖሩት አንጋፋ ጋዜጠኞችን የሚያክል ተመራጭና ዉጤታማ ጸሃፊ የለም” እያሉ ብዙሃኑ የታሪክ ተመራማሪዎች ሲናገሩ ይደመጣሉ::የቀዳማዊ ሃይለስላሴን አነሳስና የአገዛዝ ዘመናቸውን እንዲሁም “የኤርትራ ጉዳይ” የተሰኘውን እጹብ መጽሃፍ የጻፉልን አምባሳደር ዘውዴ ረታ የቤተ መንግስቱ ቃል አቀባይ የነበሩና በኋላም የብሄራዊው ሬዲዮ ጣብያውን በጋዜጠኝነት ያገለገሉ ሰው ነበሩ::ስለ አጼ ምኒልክ ስለ አጼ ቴዎድሮስ እና ስለሌሎች ታላላቅ ሰዎች በመጽሃፍ ጽፎ ያስነበበን ጳውሎስ ኞኞም ቢሆን ምትክ አልባ ጋዜጠኛ ነበር::እኝህ የዛሬው ባለታሪካችንም ጉምቱ ጋዜጠኛ የነበሩና “የቀዳማዊ ሃይለስላሴ መንግስት ፍጻሜና የደርግ አነሳስ” የተሰኘውን ዳጎስ ያለ መጽሃፍ የጻፉ ሰው ናቸው::

  አምባሳደርና ጋዜጠኛ አሃዱ ሳቡሬ::

  የቀዳማዊ ሃይለስላሴ መንግስት ውስጥ ጉልህ ተሳትፎ የነበራቸውና በባለስልጣንነት ያገለገሉት አብዛኛዎቹ ሰዎች ወይ የደርግ ጥይት እራት ሆነዋል: ወይም ደግሞ ከእስር ተለቀው በእድሜ ግስጋሴ ተገዝግዘው ያስቀመጠበትን የማይረሳው ሞት ወደ ዘለአለማዊ ቤታቸው ወስዷቸዋል::አሃዱ ሳቡሬ ግን “እነሆ ተተኪውን ትውልድ ያየከውን ተርክለት የምታውቀውን ጽፈህ አስነብ” ሲላቸው ከሞቱት እንደ አንዳቸው ሳይሆኑ እድሜን ጠግበው ጤንነታቸው ሳይጓደልአሉልን::

  መስከረም አንድ ቀን 1917 አመተ ምህረት አዲጋላ የጉምሩክ ጣቢያ ነበር አሃዱ ሳቡሬ የጉምሩክ ሰራተኛ ከነበሩት አባታቸው የተወለዱት::በሶስት አመት እድሜያቸው ወደ ድሬዳዋ ከሄዱ በኋላ ጣልያን ሃገራችንን እስከወረረበት እስከ 1928 አመተ ምህረት ድረስ እዛው ድሬዳዋ ከተማ ውስጥ ይገኙ ከነበሩ መደበኛና የፈረንሳይ(ፍራንኮፎን)ትምህርት ቤቶች የቀለም ትምህርትንና የፈረንሳይኛ ቋንቋን በአንድነት ተማሩ::በዚህም ምክንያትነት የፈረንሳይኛ ቋንቋን አቀላጥፈው መናገር መጻፍና ማንበብ ችለው በነበረበት ወቅት ወራሪው የጣልያን መንግስት ሃገራችንን ወረረና “ኢትዮጵያ ሌላኛዋ ግዛቴ ነች” የሚል ፕሮፓጋንዳ መንዛት ጀመረ::

  ጣልያን ሃገራችንን በወረረ ማግስት ኢትዮጵያ እንደ ሊቢያ እንደ ሶማሊያና እንደ ኤርትራ ጸጥ ለጥ ብላ “በእርሶ መጀን” ብላ ትገዛልኛለች ፍቃዴንም ትፈጽምልኛለች ብሎ በማሰብ “የታላቋ ሮም አንዷን ግዛት ኢትዮጵያን”የጣልያን ስልጣኔ ነጸብራቅና የቴክኖሎጂ ዉጤቶቿ ማሳያ ትሆን ዘንድ ያማሩ መንገዶች ግዙፍ ህንጻዎች ምቹ መኪናዎችና የጣልያንኛን ቋንቋ አብዝተው የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች በሃገሪቱ መስፋፋት ጀመሩ::በዚህም ወቅት የአስራ አንድ አመት ታዳጊ የነበረው ብላቴናው አሃዱ በዚሁ በጣልያን ትምህርት ቤት ገብቶ ከመደበኛው የቀለም ትምህርቱ ጎን ለጎን የጣልያንኛ ቋንቋን ልቅም አድርጎ ተማረና የጣልያንኛ ቋንቋን ቀደም       ብሎ ካወቃቸው ቋንቋዎቹ መደዳ አሰለፈው::አሃዱ ይሄንን የጣልኛንኛ ቋንቋ በሚገባ ለማወቅ የፈጀበት ሁለት አመት ብቻ ነበር::ከሁለት አመት ትምህርት በኋላ የአስራ ሶስት አመቱ አሃዱ ከጣልያን መንግስት ካዝናበሚወጣ ገንዘብ የስም ዝርዝራቸው ከደሞዝ ተከፋዮች መደዳ ሆነው ጥሩ ክፍያ ከሚቀበሉ ተቀጣሪዎች አንዱ ሆኖ በጣልያንኛና በሶማሊኛ አስተርጓሚነት የስራ መደብ ላይ የተቀጠረ ወጣት ሆነ::

  ታዳጊው አሃዱ ከወላጅ እናቱ ጋር አይሻ ወደተሰኘች አንዲት አነስተኛ ከተማ ለአንድ የመሬት ጉዳይ ሲመላለሱ የአውራጃዋ አስተዳዳሪ ቀልጣፋነቱንና የቋንቋ ችሎታውን አይቶ ነበር ለዚህ ስራ ያጨው::በዚህም ስራው ወዲህ እየተመሰገነ ወዲያ የስራ ልምዱን እያዳበረ ከቆየ በኋላ እድሜው አስራ ስድስት አመት ሲሆንና ወራሪው የጣልያን መንግስት ብርቱውን የአርበኞቻችንን ክናድ ቀምሶ ሽንፈቱን እንደ እንቆቆ ተግቶ ከሃገር ሲወጣ አንድ ሆነ::በዚህ ግዜ ከስደት ተመላሹ ንጉሰ ነገስት አጼ ሃይለስላሴ ከሰሩት ተግባሮች አንዱ የድሬዳዋ መዘጋጃ ቤትን ማቋቋምና ማደራጀት ነበር::ይህ ማዘጋጃ ቤት ደግሞ በስሩ የግብር መሰብሰቢያ ክፍል አብሮ ተቋቁሞ ነበርና አሃዱ የዚህ ክፍል ሰራተኛ ሆኖ ተቀጠረ:: ነጻነቷን ባስከበረችው ሉአላዊት ሃገርም የመጀመሪያ የመንግስትን ስራውን “ሀ” ብሎ ጀመረ::

  አሃዱ ከልጅነቱ ጀምሮ እጅግ ፈጣን ልጅ እንደነበር የሚያውቁት በምስክርነት ሲናገሩ የህይወት ታሪኩ የተከተበበት ደግሞ መጽሃ ቋሚ ምስክር ሆኖ ያሳውቀናል::አሃዱ ገና ሮጦ ባልጠገበበት በአፍላ የጉርምስና እድሜው ብዙሃን ታላላቆቹ ተመኝተው ያልተሳካላቸውን የመንግስት ስራ ገና በአስራዎቹ የእድሜው ክልል ውስጥ ሆኖ አንዴ በጣልያን የመንግስታዊ መዋቅር አንዴም ነጻነቷን ባስጠበቀችው ሉአላዊት ሃገር ውስጥ መስራቱን ቀጠለ::የድሬዳዋ የግብር መሰብሰቢያ ቢሮ ውስጥ ተቀጥሮ ጥቂት እንደቆየደግሞ የሃረርጌን አውራጃዎች የአሰራር ሂደት እንዲቆጣጠር ታስቦ በተቋቋመው የሃረርጌ አውራጃ ግዛት የኢንስፔክሽን ቢሮ ውስጥ በጸሃፊነት ተቀጠረ::መች ይሄ በቅቶት::ለድሬደዋ አቅራቢያ ወደነበረችው ወደ ሃገረ ጅቡቲ ተሻግሮ በወቅቱ በኤምባሲ ደረጃ ባልተቋቋመው የቆንስላ ጽህፈት ቤት ውስጥ እንደገና በጸሃፊነት ተቀጠሩ::

  አሃዱ ከታዳጊነትእስከ ወጣትነት በኖረባት በጅቡቲ ከተማ በምትገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ውስጥ እየሰራ በነበረበት ወቅት አንድም ለደሞዙ የመንግስት ጸሃፊነት ስራውን እያቀላጠፈ አንድም የነብስ ጥሪው የሆነውን የስነ ጽሁፍ ዝንባሌውን እያዳበረ መጣ:: “ያን ግዜ በወጣትነት መንፈስ ተነሳስቼ በዚህ በአዲሱ ዘመን ውስጥ መስራት ያለብን ስራ ምንድን ነው ብዬ በማሰብ ‘አዲሱ ስራችን’በሚል አርእስተ ጉዳይ አንዳንድ ጽሁፎችን ለጋዜጦች እጽፍ ነበር::”ይላሉ አሃዱ የዛሬ ስልሳና ሰባ አመት ትዝታቸውን ወደ ኋላ ተመልሰው እያስታወሱ::እንግዲህ ይህ የስነ ጽሁፍ ዝንባሌያቸው ታይቶና ተገምግሞ ነበር በወቅቱ በነበረው አሰራር የጽህፈት ሚኒስቴር በጻፈውና “አቶ አሃዱ ሳቡሬ የተባሉ በጅቡቲ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት በጸሃፊነት እያገለገሉ ያሉ ሰራተኛችን ይህ ደብዳቤ በእጃችሁ ከገባበት እለት አንስቶ የድርጅታችሁ ቅጥረኛ እንድታደርጉዋቸው ይሁን::” የሚል ይዘት ባለው የማዘዣ ደብዳቤወጣቱ አሃዱ አንቱ ተሰኝቶ የጋዜጣና ማስታወቂያ መስሪያ ቤት ቅጥረኛ ሆነ::

  ያን ግዜ የጋዜጣና ማስታወቂያ መስሪያ ቤት በጽህፈት ሚኒስቴር ስር እንደ አንድ ክፍል የነበረ እንጂ እራሱን ችሎ የተቋቋመ መስሪያ ቤት አልነበረም::የጋዜጣና የሬዲዮ ነገርም ቢሆን እምብዛም በህዝቡ ዘንድ አልሰረጸም:: በተለይ ሬዲዮ ብዙ ሰው ጋር የማይገኝ የቅንጦት እቃ ስለነበር በወቅቱ በዋና ዋና አደባባዮች ማለትምየካቲት 12 አደባባይ: አቡነ ጴጥሮስ አደባባይና ሌሎችም ህዝብ በብዛት በሚገኝበትና ገበያ በሚገበያይበትስፍራ ጣልያን ሃገሪቷን ተቆጣጥረው በነበረበት ዘመን ለፕሮፓጋንዳ የሰቀላቸውና የኢትዮጵያ መንግስትም በተጨማሪነት ሬዲዮ ለሌላቸው ሰዎች ዜና ማዳመጫ ይሆን ዘንድ ብሎ ያኖራቸው ትልልቅ ስፒከሮችን በመጠቀም ይበልጡኑ የአዲስ አበባ ህዝብ በሬዲዮ ይተላለፍ የነበረውን ዜና ማስታወቂያ ሙዚቃና አንዳንድ ዝግጅቶች ልቅም አድርጎ ያዳምጥ ነበር::በመሆኑም እነ አሃዱ ሳቡሬ እነ አሰፋ ይርጉ እና ሌሎችም የዘመኑ ወጣት ጋዜጠኞች ስመ ገናና ሆነው በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ዝናን አተረፉ::አሃዱ በዋነኛነት የአዲስ ዘመንና የሰንደቅ አላማችን ዋና አዘጋጅ ለነበሩት ብላታ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሃንስ የቅርብ ረዳት በመሆን በዋነኛነት የተቀጠሩ ቢሆንም በብቃታቸው ታይተውና ተገምግመው የዜና አንባቢና የልዩ ልዩ ፕሮግራሞች ተናጋሪ የዜና ሃተታ አዘጋጅና አቅራቢ በመሆን ሲሰሩ ቆይተዋል::

  በሃገራችን የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ታሪክ ግንባር ቀደሙ ሬዲዮ መሆኑና ይህም የሚዲያ ዘርፍ የእድሜ ስፍሩ ቢለካ ከሰማንያ አመታት በላይ ብዙም ፈቀቅ እንደማይል ስለ ሃገራችን ሚዲያ የተሰሩ ጥናቶች ይመሰክራሉ::ሬዲዮ ትኩስ ዜናን ለማስተላለፍ አይነተኛ የመገናኛ ብዙሃን እንደመሆኑና በሃገራችን ቀድመው ከተቋቋሙት የመገናኛ ብዙሃኖች ማለትም የህትመትና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች (PRINTING MEDIA AND ELECTRONICS MEDIA) አንዱ በመሆኑ ለዜና:ለዘገባ:ለዶክመንታሪ:ለሪፖርታዥና ለመሳሰሉት ግብአት የሚሆን እንደ ኢንተርኔት ያለ የመረጃ ቋት ፈጽሞ አልነበረም::ይሄኔ እነ አሃዱ በየ አደባባዩ የተሰቀሉት ሜጋፎኖች ላይ ጆሮውን ቀስሮ ለሚጠባበቃቸው ህዝብ ወደ ቤተ መንግስቱ በቴሌግራም ይላክ የነበረውን የፈረንሳይኛና የእንግሊዝኛ ዜናዎች በየእለቱ እየተረጎሙና እያጠናቀሩ ለህዝቡ እነሆ ይሉ ነበር::ከምንም በላይ የእነ አሃዱ ሳቡሬን የሬዲዮ ፕሮግራም ተወዳጅና ተደማጭ ያደረገው አለም ለሁለት ተከፍሎ ሳንጃ ለሳንጃ ሲሞሻለቅ የነበረበትን የሁለተኛው የአለም ጦርነት በየቀኑ መዘገባቸው ነበር::ከዚህ ባልተናነሰ ምናልባትም ባስ ባለ መልኩ የነ አሃዱ ሚዲያ ይበልጥ ዝናን ያተረፈው ደግሞ ግርማዊ ቀዳማዊ ሃይለስላሴ በአሜሪካ በካናዳና በሜክሲኮ ያደረጉት የ1940 ዎቹ አመታት ይፋዊ ጉብኝት ነው::ንጉሱ የመካከለኛውንና የሰሜን አሜሪካዎቹን ሃገሮች ሊጎበኙ ሽር ጉዱና ትርምሱ ዘርፈ ብዙ በነበረበት ወቅት ከተሰናዳው ዝግጅት አንዱ የንጉሱን የጉብኝት ሁኔታ በስፋት ለመላው ሃገሪቱ ማዳረስና መስደመጥ ነበር::ለዚህም በየ ክፍለ ሃገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች ልክ እንደ አዲስ አበባው ያለ ሜጋፎን በየዋና ዋና ቦታዎች ተሰቅለው ሲያበቁ ከአዲስ አበባ የሚያገኙትን ዜናዎች በቅብብል ለከተሜው ህዝብ እንዲያሰሙ ሆነ::

  ከዚያስ......?

  ከዚያማ በአዲስ አበባ ተወስኖ የነበረው የአሃዱ ስም ከምስራቅ እስከ ምእራብ ከሰሜን እስከ ደቡብ ይዳረስ ጀመረ::

  ይቀጥላል......!

 • loader Loading content ...
 • Sewasewer

  አንዳንድ ግዜ በአንድ ስርአተ ማህበር ወይንም ፖለቲካዊ የአገዛዝ ሂደት ውሥጥ እያገለገሉ ያሉ ምንም ያክል መልካም ቢሆኑ በጅምላ ተፈርጀው ከኑግ ጋር እንደተገኘ ሰሊጥ አብረው እየተወቀጡ በወል ስም ውስጥ ተፈርጀው ያለስማቸው ስም ያለድርጊታቸው ተቀጽላ የተሰጣቸው ሰዎችን አለማችን ለዘመናት አስተናግዳለች::ዛሬ ዛሬ የኢትዮጵያ ታሪክ በግራና በቀኝ ጽንፈኞች የፊጥኝ ተይዞ እየተጎተተ “ያልሆነው ሆነ የሆነውን አልሆነም” እየተባለ ጸአዳ መልኩ ጥላሸት እየተቀባ ባለበት ቀን ይቅርና በደጉ ቀንም እንኳ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ስርአት ውስጥ ያሉ እና ያለፉ ሰዎች ስለማንነታቸው የሚሰጠው አተያይ እንደየምሁሩና እንደየተመራማሪው ለየቅል ነው::

  በአዝጋሚነቱና በስር ነቀልነቱ የምናውቀው: በየካቲት 1966 ተቀስቅሶ በመስከረም 1967 የተጠናቀቀው የኢትዮጵያን አቢዮት ተከትሎ የስልጣን እርካቡን የተቆናጠጠው የደርግ መንግስት:እጁን በደም ወጭት ውስጥ ለመንከር ከሰባ ሁለት ቀን በላይ መቆየት አልተቻለውም ነበር::“ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚለውን መፈክሩን በጫጭቆ መሬት ጣለውና በዛች ህዳር 14 በተባለች የተረገመች ምሽት 59 የቀድሞው ስርአት ሹማምንትና አንድ የደርጉ ሊቀመንበር በድምሩ 60 ሹማምንት በአንድ ለሊት ከመረሸናቸው ተያይዞ ነበር“ደርግ”ይሉት ስም ከደም ማፍሰስ ከመረሸን ጋር እየተያያዘ እንዲያውም የወል ትርጉሙ “ጉባኤ ወይንም ስብስብ”መሆኑ ተረስቶ ደርግ እንደ ምህጻረ ቃል “ደብድብ ርገጥ ግዛው” እየተባለ እስከመተርጎም ደረሰ::

  በአጼ ሃይለስላሴ ሹማንንት ርሸናና በቀይ ሽብር ነጭ ሽብር የግድያ አመታት ውስጥ ደርግ በሚል ስያሜ የተሰባሰበው የወታደር ቡድን በጨካኝነትና በአምባገነንነት በብዙሃኑ ዘንድ ቢፈረጅም በውስጡ ግን አንዳንድ ስለሃቅ ኖረው ስለሃቅ የሞቱ ብሎም የስርአቱን አስከፊነት በግልጽ እና በይፋ ተናግረው የሞቀ ኑሯቸውን የደመቀ ጥቅማቸውን ጣጥለው የተሰደዱ:ስማቸው ከሙስናና ከዘር ማጥፋት ወንጀል ጋር የማይያያዝ እንደነ ጎሹ ወልዴ አይነት ጉምቱ ባለስልጣንና እውቅ የጦር መኮንን ጥሩ ምሳሌ ናቸው::ይህንን ሃቅ መካድ ግን አይቶ አላየሁም ሰምቶም አልሰማሁም አይነት ድርቅና ይሆናል::

  ======ከልጅነት እስከ ሹመት======

  ኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሮችን ሾማ ማሰራት ከጀመረችበት ከአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ጀምሮ  አሁን በቅርቡ እስከተሾሙት ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ድረስ 29 (ሃያ ዘጠኝ) ያህል በሚኒስትር ማእረግ ያሉ ሰዎች ሃገራችንን በዉጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት አገልግለዋል::እንደ አውሮፓውያን ቀመር ከ1910 -1911 አመተ ምህረት የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሆነው ካገለገሉት ከነጋድራስ ይገዙ በሃብቴ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ሹመት አሃዱ ተብሎ ከተጀመረ በኋላ ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ አስራ ስምንተኛው የኢትዮጵያ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር (አንዳንድ መረጃ ምንጮች ሃያ አንደኛው ሚኒስትር እንደሆነ ይናገራሉ) ተደርገው የተሾሙና ሃገራቸውን በቅንነት ለሶስት አመታት ያክል በሚኒስትርነት ማእረግ ያገለገሉ ጠንካራ ዲፕሎማትና ቆፍጣና ወታደር ናቸው::

  ዶክተር ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ ተወልደው ያደጉት በያኔው ኢሉባቦር ጠቅላይ ግዛት ጎሬ በተባለች አነስተኛ ከተማ እንደሆነ የቅርብ ወዳጆቻቸው ሲናገሩ ይደመጣሉ::የያኔው ወጣት ጎበዝ ተማሪ ጎሹ መደበኛ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ በመግባት የህግ ትምህርቱን በከፍተኛ ነጥብ በማጠናቀቅ እንደተመረቀና እስከዛሬም ድረስ ሰቅሎ ያስመዘገበው ነጥብ እስካሁን እንዳልወረደም  ይወራለታል::ጎሹ ከዚህ አስከትሎ ያመራው ወደያኔው ስመ ገናና የሃረር ጦር አካዳሚ ገባ::ከዚያም በመኮንንነት ተመርቆ  እንደወጣ በንጉሰ ነገስቱ አስተዳደር ውስጥ በተለያየ ቦታ እንዳገለገለ: በሙያውና በስነ ምግባሩም እጅግ የተመሰገነ ሰው እንደነበር አብረው የሰሩ የቀድሞ ባለስልጣናት ምስክርነት ሰጥተዋል::የ1966 የኢትዮጵያ አቢዮትን ተከትሎ በትረ ስልጣኑን ከተቆናጠጠው የደርግ መንግስት ጋርም ወጣቱ ጎሹ ተቀራርቦ ለመስራት በንጉሰ ነገስቱ ዘመን ያሳየው ብቃትና ተወዳጅነት ረድቶት ኖሮ የጠቅላይ ጦር ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ ሆኖ ሊሾም በቃ::ኮሎኔል ጎሹ መንግስት ከሰጠው የአቃቤ ህግ ሃላፊነት አንስቶ ታጠቅ የጦር ሰፈር ወስዶ ሲሾመው የሚሰጠውን ምልምል ወታደሮች የማሰልጠን ሃላፊነት በቀላሉና በብቃት እንደሚወጣው በመተማመን ነበር::

  ቀደም ሲል በአጼ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ቆይቶ ደግሞ በ1969 አመተ ምህረት በዚያድባሬ ይመራ የነበረው የሶማሌ መንግስት ኢትዮጵያን በመውረር የሃገሪቱን ቀላል የማይባል ግዛት ተቆጣጥሮ ስለነበርና ወደ ስልጣን ከወጣ ገና ጥቂት አመት ብቻ ያስቆጠረው የደርግ መንግስትም በስንቅም በትጥቅም በፖለቲካዊ አመራር ብቃትም ከፍተኛ የሆነ የልምድና የአቅም ማነስ ይስተዋልበት ስለነበር ሳይሆን አይቀርም እንደነ ኮሎኔል ጎሹ አይነቶቹን ምሁራንና ቆፍጣና ወታደር ወደ አሳሳቢው የጦርነት ቀጠና የሳባቸው::

  በሰለሞናዊው ስርወ መንግስት የመጨረሻው የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት በመሆን ኢትዮጵያን ለአርባ አራት አመታት ዘውድ ጭነው ያስተዳደሩት ግርማዊ ቀዳማዊ ሃይለስላሴ በንግስና ዘመነ መንግስታቸው የዉጭ ጉዳዩን: የመከላከያውን: የደህንነቱን: የገንዘብ ሚኒስትሩንና የመሳሰሉ የሃገር ሁለንተናዊ ስልጣኖችን ለሌሎች ባለስልጣናት ሰጥተው እንዲያስተዳድሩ ካደረጉ በኋላ ከንጉሰ ነገስትነታቸው ደርበው የያዙት ስልጣን የትምህርት ሚኒስትርነትን ስልጣን ነበር::እናም ይሄ ከንጉሱ ግዜ ጀምሮ ትልቅ ስፍራ ትርጉም ያለው የመንግስት ስልጣን “በማን የአስተዳደር እዝ ስር ይሆናል?” የሚለው ጥያቄ ብዙዎች ሲያነሱ ሲጥሉት የነበረ ጉዳይ ሆኖ ሲያበቃ በመጨረሻ ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ እንዲይዙት ተደረገ::

  ደርግ በብዙሃኑ የኢትዮጵያውን አይምሮ ዘንድ በበዛ ክፋቱና ገዳይነቱ በተደጋጋሚ እንደሚታወስ የማይካድ ጉዳይ ቢሆንም ጥቂት በማይባሉ ጉዳዮች ወይንም ሴክተሮች ግን ዛሬም ድረስ ማስመዝገብ ያቃተንን ከፍተኛ ስኬት አስመዝግቧል::ከነዚህም ውስጥ

  -በመሬት ለአራሹ የገጠርና የከተማ መሬት ድልድል በርካታ ጭሰኞችና ቤት አልባዎች የመሬት ባለቤት ሆነዋል::

  -ከዚህ በተሻለና በበለጠ ደግሞ መሃይምነትን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ባለመው የእድገት በህብረት ዘመቻ ኢትዮጵያ ከምንግዜውም የላቀና ታይቶ የማይታወቅ ምሁራንን ማፍራት ከመቻሏም አልፋ ተርፋ ማንበብና መጻፍ የማይችሉ የነበሩ በጣታቸው ቀለም ነክረው ይፈርሙ የነበሩ መሃይማን በአመዛኙ ማንበብና መጻፍ እንዲችሉ ሆኗል::

  -ወራሪውን የሶማሊያ መንግስት አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶ እስከ ዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ ድረስ አሯሩጦ የተረከበውን የሃገራችንን ሉአላዊነት በአደራ አስረክቧል::

  -በአፍሪካ ወደርና አሻ የማይገኝለት ግዙፍ ጦር ሰራዊት ገንብቶ ሃገራችን ኢትዮጵያ በጠላቶቿ ተፈርታና ታፍራ እንድትኖር አድርጓል....ወዘተ::

  ይህም ደርጎች ወይንም የስርአቱ የቀድሞ ባለስልጣናት “ያኔ የሰራነው” ብለው ከሚመኩበት ስራዎቸው በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት ጉዳዮች ናቸው::ከእነዚህም መካከል መሃይምነትን ከሃገራችን ለማጥፋት ታቅዶ በተካሄደው የእድገት በህብረት ዘመቻ ላይ አንቀሳቃሽ ሞተሮች ከነበሩ ሰዎች ውስጥ ኢትዮጵያ ፈጽሞ ስማቸውን ልትዘነጋው ከማይገባ መሃይምነትን ከገጠሪቷ ኢትዮጵያ ጠራርገው ካጠፉ ጉምቱ ባለስልጣናት መካከል ኮሎኔል ጎሹ ወልዴን ሳይጠቅሱ ማለፍና ታሪክን አውሸልሽሎ ለመመዝገብ መሞከር በሽንቁር ገንቦ ውስጥ ውሃ ለማስቀመጥ እንደመሞከር ሳይሆን አይቀርም::ለዚሁ ስኬታማ ዘመቻ ሃገራችን ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት “መሃይምነትን ለማጥፋት ባደረግሽው ትግል”ተብላ ለሶስት ግዜ ያክል ተሸላሚ እንድትሆን ከማድረጋቸው አልፈው ተርፈው የመምህራኑ የኑሮ ደረጃና ገቢ እንዲጨምር የደረጃ እድገትና የሙያ ማሻሻያ ስልጠና እንዲሰጣቸው ስለማድረጋቸው በስፋት ይነገርላቸዋል::

  ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ ሲበዛ ደፋርና የመሰላቸውን ለመናገር አንዲት ስንዝር ታክል ወደኋላ ንቅንቅ የማይሉ የግንባር ስጋ የሚባሉ አይነት ተጋፋጭ አንደበተ ርቱእ የሆኑ ኢትዮጵያዊ ምሁር ናቸው::አንዳንዶች እንደሚሉት ደርግ በወቅቱ የወታደሮች ስብስብ ከመሆኑና በመሃከሉ ተራማጅ አስተሳሰብ ያለው ምሁር በማስፈለጉ ነበር ጎሹን በቅድሚያ ወደ ትምህርት ሚኒስትርነት በመቀጠልም ወደ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት እንዲመጣ ያደረጉት::ይህ ማለት እንግዲህ እንደነ ባሮ ቱምሳ እንደነ ሃይሌ ፊዳ አይነቶቹ ኮሎኔል መንግስቱን የሶሻሊስቱን ርእዮተ አለም ሀ ሁ አስጠንተዋል እንደሚባለው አይነት ሳይሆን አይቀርም::

  የኢትዮጵያን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ቦታ ሃያ ስምንት ሰዎች መርተዉታል::ከነዚህም መካከል ከጦር አዋቂው ፊትአውራሪ ሃብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ አንስቶ በቅርቡ በሞት እስከተለዩት ተስፋዬ ዲንቃ:ከያኔው ራስ ተፈሪ (ኋላ ቀዳማዊ ሃይለስላሴ)አንስቶ ዛሬ ጣልያን ኤምባሲ ተሸሽገው እስከሚገኙት ሌፍተናንት ጀነራል ሃዲስ ተድላ ከጸሃፊ ትእዛዝ አክሊሉ ሃብተወልድ አንስቶ  እስከ ዶክተር ቴዎድሮስ አስሃኖም:ከልጅ ሚካኤል እምሩ እስከ ስዩም መስፍን ከዶክተር ደጃዝማች ዘውዴ ገብረስላሴ አንስቶ እስከ ዶክተር ወርቅነህ ገበየው ድረስ ይጠቀሳሉ::በመሆኑም የዶክተር ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ ሹመት ከነዚህ ከላይ ከተጠቀሱት ኢትዮጵያዊያን ጋር በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ እየተሰባጠረ ብሎም እየተነጻጸረ መቅረቡ የማይቀር ጉዳይ ነው::ኮሎኔሉ አንደበታቸው የጣፈጠ ንግግራቸው ማራኪ ከመሆናቸውና ፍጹም የእንግሊዝ አፍ ነው በሚባልላቸው የተዋጣለት (FLUENT)የእንግሊዝኛ ንግግራቸውን ተጠቅመው ሃገራችን ኢትዮጵያን በብዙ አለም አቀፍ መድረክ ወክለው ለሶስት አመት ያክል (1976 እስከ 1979)በአስደናቂ ብቃት የተሰጣቸውን ግዳጅ ሲወጡ ኖረዋል::

  ======እህል ዉሃችን አለቀ በቃ======

  ደርግ ኢትዮጵያን በመራበት አስራ ሰባት አመታት ውስጥ የነበረው ቁርቋዞ በመንግስት ሹማምንት እና በህዝብ መካከል ብቻ ሳይሆን በመንግስት ባለስልጣናትና በመንግስት ባለስልጣናት እርስ በርስም ጭምር ነበር::በዚህ አንዱ አንዱን ለመጥለፍ አንዱ አንዱን ለመጣል አንዱ በአንዱ ትከሻ ላይ ተንጠላጥሎ አንገቱን ለማስገግ በነበረ ዉትብትብ የፖለቲካ ጨዋታ ጎሹ ወልዴ ድንገት ባላሰበውና ባልገመተው መልኩ ከጠላቶቹ ወጥመድ ውስጥ ከኮሎኔል መንግስቱ ጥርስ ውስጥ ዘው ብሎ ገባ::ጎሹ ሃገር ለቆ ከወጣ በኋላ ስም እየጠቀሰ የተቻቸው ባለስልጣናት የእርሱን ቦታ ማለትም የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትርነቱን ሲመኙ እንደነበር ለሊቀመንበሩ ስሙን ጥላሸት እየቀቡ ያቀርቡ እንደነበር በተለይ በተለይ እነ አሻግሬ ይግለጡ (አሻጥሬ ይላቸዋል እሱ)እነ ካሳ ከበደ እነ ፍቅረስላሴ ወግደረስ እና ሌሎችም እርሱን ለመጣል የተንኮል ሸማ ሲያሸምኑ እንደ ሹሩባና ወለባ ተዋደው እንደነበር ይገልጻል::ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጎሹ በተለያየ ጊዜያት ሃገራችንን ወክሎ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መድረክ ላይ በመቆም ብስለቱን በሚያስመሰክር መልኩ ንግግሮችን በሚያደርግበት ግዜ የተወሰኑ የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት በሸረቡት ሴራ በልኡካን ቡድን መሪነት ስም ጎሹን ሲሰልሉ ዉጭ ሃገር ሄዶ ምን እንደሚያደርግ ከማን ጋር እንደሚያወራ ወሬ እየለቃቀሙ ለሊቀ መንበር መንግስቱ ሹክ ይሉ እንደነበር ዛሬ ዛሬ እየታተሙ እየወጡ ያሉ የቀድሞውን ስርአት ምንነት የሚያሳዩ መጽሃፍ በስፋት እያብራሩት ይገኛሉ::

  የኮሎኔል ጎሹና የደርግ መንግስት የተሳሰሩበት ጅማት የመበጠሻዋ ቢላ መሞረድ የጀመረችው ቀደም ብላ ቢሆንም ነገሩ የተካረረውና አንዳንዶች እንደሚሉት ጎሹ የተጠመደላቸው ወጥመድ ዉስጥ የገቡት ብራስልስ ላይ በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት ጉባኤ መነሻነት ነበር::የዛን ግዜ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚደንት የነበሩት ጆርጅ ቡሽ በተገኙበት የብራስልሱ ጉባኤ ላይ የአፍሪካ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ኮሎኔል ጎሹ እነርሱን ወክሎ ንግግር እንዲያደርግ ይመርጡታል::በጉባኤው ላይ ንግግር እንዲያደርግ የተመረጠው ኮሎኔል ጎሹ ወልዴም የንግግሩ ፍሬ ሃሳብ የነበረው “አሜሪካ በሁለተኛው የአለም ጦርነት የተጎዳውን የምእራብ አውሮፓ በማርሻል ፕላን እንደታደገችው ሁላ አፍሪካንም በተመሳሳይ ፕላን ልትታደጋት ይገባል” የሚል ይዘት ነው የነበረው::እንደሚታወቀው ማርሻል ፕላን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር(SECRETARY OF STATE) በነበረው በጆርጅ ካትሌት ማርሻል የሃሳብ አመንጪነት የቀረበ እቅድ ሲሆን የእቅዱም አላማ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ለተጎዱት የምእራብ አውሮፓ ሃገራት አሜሪካ ለአራት አመት ፕሮጀክት 13 ቢሊየን (በዛሬው ስሌት 120 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ) ለአውሮፓ ሃገራት የመልሶ ግንባታ እንድታበድር: እግረመንገዷንም የምስራቅ አውሮፓ የሶሻሊስት ተስፋፊ ሃገሮችን እንድታዳክም የተነደፈ ፕላን ነበር::

  እናም በጉባኤው ላይ ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ በመንኮታኮት ላይ ስለነበረው የአፍሪካ ምጣኔ ሃብት የመልሶ ግንባታና የኢኮኖሚ ድቀት ማገገሚያ ይሆናል ብሎ እንደ ሃሳብ ለጉባኤው ተሳታፊዎች ያቀረበው ንግር ይህንኑ የማርሻል ፕላን አይነት እቅድ አሜሪካ እንድታደርግ ነበር::በዚህ ግዜ የጎሹን ንግግር ሰበዝ በሰበዝ እየሰነጠቁና የተባለውን ካልተባለው የታሰበውን ካልታሰበው እያቆራኙ ለሊቀመንበሩ ከጎሹ ወልዴ ድንቅ የእንግሊዝኛ ንግግር ክህሎት ጋር እያጣመሩ “ወትሮም የሲአይኤ ቅጥር ነው ስንልዎ አልሰሙንም ነበር ይሃው አሁን በአደባባይ አሜሪካ አፍሪካን እንድታጥለቀልቅና ኢምፔሪያሊዝም እንዲስፋፋ አቢዮቱም እንዲቀለበስ መስበክ ጀመረ የእንግሊዝኛው ቅልጥፍናም እኮ የሲአይ ኤ ወኪል ስለመሆኑ ማረጋገጫ ነው”በማለት በሊቀመንበሩ ደካማ ጎን በመግባት ወሬውን ሹክ አሉ::

  ይህ እና ሌሎች የተንኮል ድሮች የወታተቧቸው ኮሎኔል ጎሹ በአንድ ወቅት ለአንድ የስራ ጉዳይ ወደ ዉጭ ሃገር ከሄዱ በኋላ ዳግመኛ ወደ ትውልድ ሃገራቸው ሳይመለሱ ቀርተዋል::ኮሎኔል ጎሹ በወቅቱ አልመጣም ቀረሁኝ የሚልና “አብዮታችን ወደ ፍጹም አምባገነናዊነትና ጭካኔ ዘቅጧል”የሚል ይዘት ያለው ደብዳቤን ጨምሮ የዉሎ አበላቸውን ዶላር: የጉዞ ቲኬት እንዲሁም ጠቃሚ ዶክመንታቸውን ለሊቀበንበሩ በአድራሻቸው እንዲሰጥ ማድረጋቸው እጅግ መነጋገሪያ ሆኖ በወቅቱ በአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ በተደጋጋሚ ሲነገር ነበር::በወቅቱም የጎሹ ወልዴን መሄድ ከተሜው እንደጉድ ሲያወራበት ከረመ:: አዝማሪውም በቅኔ
  <ጫካና ጥሻውን ደኑን መንጥራችሁ
   ኒያላ አጋዘኑ ጎሹም ሄደላችሁ>ብሎ ተቀኝቷል::

  ጎሹ ወልዴ አስከፊውን የደርግ ስርአት ትተው ከመውጣታቸው የተነሳም ይሁን ወይም በግል ስብእናቸው ወይንም በሃቀነታቸው የተነሳ ስርአቱን ይቃወሙ የነበሩም ይደግፉ የነበሩም በተመሳሳይ መልኩ በአመዛኙ መልካም አስተያየት ሲሰጣቸውና በምሳሌነት ሲነሱ ኖረዋል::በስንዴ መሃል እንክርዳድ እንደማይጠፋ ሁላ በእንክርዳድ መሃልም ስንዴ ላይጠፋ ይችላል::እንግዲህ በአስከፊ ስርአት ዉስጥም ቢሆን እንደ ጎሹ አይነት ሃገር ወዳድና ቅን ሰው አይጠፋም::ደርግ ራሱ በኋላ ቀርነቱና በበዝባዥነቱ ከሚወቅሰው ከአጼ ሃይለስላሴ መንግስት ካቤኔ ውስጥ እነ ልኡል ራስ እምሩንና ሚካኤል እምሩን እንዲሁም እነ ራስ መንገሻ ስዩምንና በተራማጅነት ይጠቅሳቸው ነበር::የኢህአዴግ መንግስትም ቢሆን በደርግ መንግስት በሃቀኝነት ሲያገለግሉ ከነበሩ በርካታ ባለስልጣናት ጋር አሁንም ቢሆን አብሮ  እየሰራ መሆኑ ይታወቃል::በውጭ ሃገርም ቢሆን እጅግ ከፍተኛ ውድመትን ባስከተለው በሁለተኛው የአለም ጦርነት ዘዋሪ በነበሩት በእነ ሂትለር ስርአት ውስጥ ሆኖ  ሃገሩን በቅንነት ያገለገለው ፊልድ ማርሻል ሮሜል ተጠቃሽ ነው::በዚህም ምክንያት ዛሬ እንደ አብዛኛዎቹ የደርግ ባለስልጣናት ስማቸው ከክፋትና ከግፍ ጋር እምብዛም ሲያያዝ ከማይሰማ የስርአቱ ባለስልጣናት መካከል ዶክተር ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ አንዱ ናቸው ማለት ያስደፍራል::

  ዶክተር ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ ስርአቱን ተቃውመውና ስራቸውን በይፋ በመልቀቅ ከሃገር ከወጡ ብሎም ድምጻቸው ሳይሰማ ከአስተያየትና ከመገናኛ ብዙሃን ርቀው ለረዥም ጊዜ ከቆዩ በኋላ የአሜሪካ ሴናተር በጠራው ስብሰባ ላይ ተጋብዘው በመገኘት ስለ ሃገራቸው ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ባደረጉት ንግግር ነበር ብቅ ያሉት::በዚህ ንግግራቸው በወቅቱ ወደ ስልጣን ኮርቻ እየወጡ የነበሩትን የኢህአዴግና የሻእቢያ ሃይሎች በእጅጉ በተቃዉሞ እየሞገቱና የሃገሪቱ መጻይ እጣ ፈንታ በእጅጉ እንደሚያሰጋቸው ሰፋ ያለ ማብራሪያና ትንታኔ ሰጥተዋል::ይሄ ቪዲዮ በ “WWWYOUTUBE.COM” ድረ ገጽ ላይ ከሚገኙ የኮሎኔሉ በጣም ጥቂት ወይንም ከሁለት አንዱ ቪዲዮአቸው ሲሆን ከኮሎኔል ጎሹ ወልዴ ጎን ተቀምጠው የሚታዩት ጉምቱው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም መሆናቸው ይታወቃል::ይሄ ቪዲዮ ከታየ ከጥቂት ግዜያት በኋላ ደግሞ በሃገሪቱ እንደ አሸን ፈልተው መታተም በጀመሩትና የ1980 እና የ1990ዎቹ መገለጫ ሆነው በነበሩት የግል ጋዜጦች የኮሎኔሉን ቃለ መጠይቅ ወይንም ስለእርሳቸው የተጻፈውን ጽሁፍ ማንበብ የተለመደ የለት ተለት ውሎ ሆነ::ከዚያም ቀጠለና “መድህን የተባለ የተቃዉሞ ፓርቲ አቋቋምኩ” አሉና በይፋ የኢህአዴግን መንግስት ተቃዋሚ መሆናቸውን በማወጅ “ለኢትዮጵያ ይሄኛው አይነት የፖለቲካ ሳይሆን ይሄኛው ይሻላታል”ማለት ጀመሩና መገናኛ ብዙሃኑ ሁላ ጎሹ ጎሹ ማለት ጀመረ::ይህ ኮሎኔል ጎሹ ያቋቋሙት መድህን የተባለ የተቃዉሞ ፓርቲ ዝነኛውን የናሳ ሳይንቲስት ዶክተር ኢንጂነር ቅጣው እጅጉንና ሌሎች ታዋቂ ሰዎችን በውስጡ አቅፎ  የነበረ ሲሆን የኋላ ኋላ ከነ አቶ ልደቱ አያሌው ኢዴፓ ፓርቲ ጋር ግንባር በመፍጠር ኢዴፓ መድህን ተሰኝቶም ነበር::

  ======ዛሬ ዛሬ.....

  ሃገራቸውን በምሁርነት በዲፕሎማትነት በወታደርነት በሚኒስትርነት እና በሌሎች ሙያዎች በከፍተኛ ቅንነት ያገለገሉት ኮሎኔል ጎሹ አሁን አሁን ከሚዲያ ብዙ ርቀዋል::በአንድ ወቅት በየአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንና በየ ፕሬስ ኮንፍረንስ እንዳልተገኙ ሁሉ ሚዲያን “እርም የናቴ ጡት” ብለው ከሸሹ ሰነባብተዋል::አንዳንዶች “ፖለቲካን እርግፍ አድርገው ትተው የፕሮቴስታንት እምነት አቀንቃኝ ብሎም ሰባኪ ሆነው ነው የጠፉት” ሲሉ አንዳንዶች ደግሞ “የለም የቀድሞ የኢህአፓ ተቀናቃኞቻቸው እግር በእግር እየተከታተሉ አላስቆም አላስቀምጥ ብለዋቸው ከፖለቲካው ትራክ ገፍትረው አስወጧቸው”ይሏቸዋል::አንዳንዶች ደግሞ “በባለቤታቸው በሞት መለየት ቅስማቸው ተሰብሮ ነው” ባዮች ናቸው::ይህም ተባለ ያ ጎሹ ከ1990ዎቹ አጋማሽ በኋላ አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር በሚዲያ ብቅ ስለማይሉ “ጎሹ ወልዴ ሞቱ”ተብሎ እስከመወራት ሁላ ደርሶ ነበር::

  ኢትዮጵያ የሶስት ሺህ አመታት ታሪክ ያላት:የብዙሃን ህዝብ መኖሪያ: ብሎም የቀደምት ስልጣኔ ባለቤት ከመሆኗ ጋር ስለ ኢትዮጵያ የተጻፈው ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር ሲነጻጸር ልዩነቱ የሰማይ እና የምድር ርቀት ያክል ነው::እንኳን የጥንቱ ይቅርና የቅርብ ግዜው የአጼ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ክስተቶች እንኳ በአግባቡ ያልተሰነዱ ማንም እየተነሳ እንዳሻው ታሪክን እንደ ቆልማማ ምሳር እያወላገደ እሚከትባቸው መጻፍ የቻለ ሁላ እሚቸከችክባቸው ጥራዞች ሆነዋል::በተለይ የደርግ ግዜ ታሪኮችን ጉምቱ ጉምቱዎቹ ባለስልጣናት ያልጻፉትን ታሪክ ባለሌላ ማእረግተኞችና መስመራዊ መኮንኖች ሲጸፉት ተስተዉሏል::ይህም እንግዲህ “ቅቤ አንጣሪዋ እያለች ጎመን ቀንጣሿ ምች መታት” እንዲሉ ሳያስገድድ አይቀርም::እነ ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ እነ ተስፋዬ ገብረኪዳን እነ ካሳ ከበደ እነ አሻግሬ ይግለጡ እነ ብርሃኑ ባየህ እነ ለገሰ አስፋው እነ ተስፋዬ ወልደስላሴ እነ መላኩ ተፈራ ሁላ በደርግ ዘመነ መንግስት ግዜ እንደ አይን የሚቆጠር ትልቅ ቦታን ይዘው የነበሩ ሰዎች ቢሆኑም ቅሉ ስላሳለፉት የስልጣን ዘመን ለትውልድ ይሄ ነው የማይባል መጽሃፍ ያልጻፉ የታሪክ ተወቃሽ ሰዎች መሆናቸው ግድ ነው(እዚህ ላይ በተፈጥሮ ሞት ወይንም ከአቅም በላይ በሆነ አስገዳጅ ምክንያት መጽሃፍ ያልጻፉት የቀድሞ ባለስልጣናት ከዚህ ወቀሳ የጸዱ ናቸው)::በተለይ ኮሎኔል ጎሹ ያንን ሁላ ትምህርት ያካበተ ያንን ሁላ ስራ የሰራ ከጽሁፍና ከንባብ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ሰው ሆኖ ሳለ ለትውልድ እንካችሁ ብሎ የህይወት ጉዞውን በመጽሃፍ መልክ ያለማቅረቡ በዛሬው ትውልድ ዘንድ ካለመታወቅ አልፎ ሰርቶ እንዳልሰራ ለፍቶ  እንዳልለፋ ጥሮ እንዳልጣረ ሳያደርገው አይቀርም::

  ጎሹ ወልዴ ሌላው ከህይወት ታሪክ ጋር በእጅጉ እየተሰናሰለ ከሚጠቀስለት ታሪክ ዋነኛው ከአርባ ሁለተኛው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ቢል ክሊንተን ጋር የነበረው ጓደኝነትና የአብሮ ክፍል ተማሪነት(CLASS MATES)ነው::እንደሚባለው ከሆነ በአንድ ወቅት ቢል ክሊንተን ለአሜሪካ ፕሬዚደንትነት ከያኔው ፕሬዚደንት ጆርጅ ቡሽ ጋር ሲፋለሙ በነበረበት ወቅት አንድ ቦታ ላይ የቀድሞ የክፍል ጓዳቸውን ጎሹ ወልዴን ያገኙታል::እናም ሞቅ ባለ ሰላምታ ሰላም ካሉትና መደበኛ ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ የተማሪነቱን ግዜ በመጠኑ አንስተው ለመጨዋወት መሞከራቸው: ጎሹ በትምህርት ቤት በነበረበት ወቅት “ከኢትዮጵያ የመጣው ሰቃዩ  ተማሪ”እየተባለ ዝናው ከፍ ብሎ እንደነበር በማስታወስ እንዳወጉ ይወራላቸዋል::ይሁንና ጎሹ በወቅቱ ከክሊንተን ጋር አብሮ ስለመማሩ ያለማስታወሱን አስመልክቶ ሲናገር “ምናልባት እኔ ክሊንተንን አብረን እንደተማርን ያላስታወስኩት ጎበዝ ተማሪ ስላልነበረ ይሆናል::ሰቃይ  ተማሪ ቢሆን ኖሮ በቀላሉ አስታውሰው ነበር”ብለው አዝናኝ መልስ እንደሰጡ ይነገርላቸዋል::ይህ እና የመሳሰሉት ወሬ እየሰፋና እየተጨማመረ ሄዶ ሄዶ መጨረሻ ላይ “ደቡብ ከሚገኘው እዝ 10000 ወታደር ከነትጥቁ ከድቶ ኬንያ ገባ::ይህ ጦርም ኮሎኔል ጎሹን መርጧል::በኮሎኔሉ ፊት አውራሪነት በአዋሳ በኩልም እየገሰገሰ ዋና ከተማዋን ሊይዝ ተቃርቧል”እየተባለ በስፋት ተወርቶ  ወሬው በአሉባልታነት ቀረ::ቆይቶ ደግሞ  የቢል ክሊንተን የአሜሪካ ፕሬዚደንት ሆኖ መመረጥ ከኮሎኔል ጎሹ የክሊንተን ጥሩ ወዳጅነት እየተሰናሰለ “ኢህአዴግ ዘንድሮ አለቀለት የክሊንተኗ አሜሪካ በጎሹ ወልዴ ሎቢ ተደርጋ ኢህአዴግ ላይ ፊቷል ልታዞር ነው”እየተባለ በስፋት መወራቱ ቀጠለ ያም ቢሆን እንዲሁ በወሬነት ከመቅረት አልተረፈም::

  ጎሹ ለመጨረሻ ግዜ በመገናኛ ብዙሃን ድምጻቸው የተሰማው የፈረንጆቹ የ2017 ከመግባቱ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሞት ስለተለዩት ስለቀድሞ የደርግ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተስፋዬ ዲንቃ መጠነኛ አስተያየት ለመስጠት በአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ (VOA)በስልክ ድምጻቸው በተሰማበት ወቅት ነበር::በወቅቱ እጅግ ማራኪና በሳል ትንታኔ ከመስጠታቸው ባሻገር ገና ለገና ሟቹን ማወደስ አለብን በማለት ሳይሆን በቂ ማስረጃና አሳማኝ ነጥቦችን እያቀረቡ ነበር  ስለ ተስፋዬ ዲንቃ ታላቅ ዲፕሎማትነት አስተያየታቸውን ሲሰጡ የነበረው::

  በመጨረሻም.....

  የአንድ ስርአት መገለጫ የክፉና የደግ ስራው ሚዛን ነው::የትኛው ምግባሩ ሚዛን ይደፋል ነው ጥያቄው እንጂ የትኛውም ስርአት ድክመት ይኖራል ስህተት ይኖራል አለማወቅ ተንኮል ሸፍጥ ወዘተ ከፖለቲካ ጋር ድር እና ማግ ናቸው::ሸማ በየ ፈርጁ ይለበሳል እንዲሉ ደርግ የተባለው ቃል በተነሳ ቁጥር ጨፍጫፊነት: ገዳይነት: ጦርኛነት :ቅጠልያ የወታደር ዩኒፎርም: የጠመንጃ ካካታ: ቀይ ሽብርና የመሳሰሉት ጉዳዮች በተለይ በዛሬው ትውልድ አይምሮ  ዉስጥ ታትመዋል::ይሁንና አንዳንዴ ከንፍሮ መሃል ጥሬ እህል እንደሚገኝ ሁሉ በመጥፎው ስርአት ውስጥም ቢሆን መልካም ሰዎች ስለመኖራቸው ሁላችንም ልንረዳውና ልናምነው የሚገባ ቁልፍ ጉዳይ ነው::እንደነ ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ አይነት ሰዎች ባመኑበት አቋም ላይ የሚያሳዩት ከአቋም ያለማወላወል ጉዳይ ከስርአቱ ደጋፊዎችም ተቃዋሚዎችም ጭምር ጠላት እንዲያፈሩ አድርጓቸዋልዋል::ከዚህና ከሌሎቹ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ሳይሆን አይቀርም ኮሎኔል ጎሹ ከመገናኛ ብዙሃን መራቃቸው::ብሎም ስለእርሳቸው በቂ ማስረጃና በወቅታዊነት ስላሉበት ጉዳይ ማወቅ አዳጋችም አታካችም የሆነው::ይሄ ጽሁፍ ሰዉዬውን በአካል አግኝቶ በተደረገ ቃለ መጠይቅ :ወይንም የህይወት ታሪካቸው ቁልጭ ተደርጎ የተጻፈበት መጽሃፍ ወይንም ዶክመንተሪ ተገኝቶ የተሰናዳ መጣጥፍ ካለመሆኑና ከተለያዩ ጋዜጦች: መጽሄቶችና ዌብሳይቶች የተጠናቀረ በመሆኑ መረጃው ላይ አንዳንድ ክፍተቶችና ጉድለቶች ሊኖሩ ስለሚችሉ በማንኛውም ሰአት ለማረም ዝግጁ ነን::

  ገና በሃያዎቹ መጨረሻ እድሜያቸው ጀምረው ወደ መንግስት ከፍተኛ የስልጣን ኮርቻ ላይ ጉብ ያሉት ኮሎኔል ጎሹ የደርግን ስርአት በቃኝ ብለው ሃገር ጥለው ሲወጡ እድሜያቸው ገና በሰላሳዎቹ መጨረሻ ላይ ነበር::ምንም እንኳ የደርግ ስርአት ቁንጮ ከነበሩ ሰዎች አንዱ ቢሆንም በቀይ ሽብርና በዘር ማጥፋት በመሳሰሉት ወንጀሎች ጠቅላይ አቃቤ ህግም ይሁን የወንጀሉ ሰለባዎች የኮሎኔሉን ስም ሲያነሱት እምብዛም አይሰማም ወይንም ተሰምቶ አይታወቅም(ከኑግ ጋር የተገኘ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ ካልሆነ በቀር ማለት ነው):: ኢትዮጵያ ስማቸውን በበጎ ከምታነሳቸው ዲፕሎማት ወታደርና ሚኒስትሮች መደዳ ያሉት ጎሹ ዛሬ ኑሯቸውን በሃገረ አሜሪካ አድርገው እየኖሩ ነው::

  ተፈጸመ !!

  (ክቡር መተኪያ ሃይለሚካኤል)FACEBOOK.COM/kibur metekia hailemichael

 • loader Loading content ...
 • Sewasewer


  ከጥቂት አመታት በፊት የታላቅ ወንድማቸውን በትረ ስልጣን የተቆናጠጡት የኩባው ፕሬዚደንት ራውል ካስትሮ ታላቅ ወንድማቸው የትግል አጋራቸውና የቀድሞው የኩባ ፕሬዚደንት ፊደል ካስትሮ በዘጠና አመታቸው ከዚህ አለም በሞት መለየታቸውን በብሄራዊ ቴሌቪዥን ብቅ ብለው ለህዝባቸው መርዶውን አረዱት::

  አለም በሁለት ሃያላን መንደር ማለትም በየሶቭየት ሶሻሊስና በአሜሪካ ኢምፔሪያሊስት ጎራ ተከፍላ በነበረችበት በነዛ ቀውጢ አመታት ውስጥ አብዮተኛው ፊዴል ካስትሮ እንደነ ሆቺሚኒ ከመሳሰሉ ጓደኞቹና ከታናሽ ወንድሙ ጋር በመሆን ነበር ዱር ቤቴ ብሎ የገባው::በወቅቱ ከአንድ መቶ ሃምሳ ኪሎሜትር በላይ ለአሜሪካ የማትርቀውና የእነርሱው አሼሼ ገዳሜ ማቅለጫ የወሲብ መዳሪያ የመጠጥ መራጫ የሃሺሽ ማጨሻ ሃገር የነበረችውን ኩባን ነጻ አውጥቶ ወደ ዋና ከተማዋ ሃቫና ለመገስገስና የስልጣን በትሩን ለመጨበጥ ሲጣደፍ ገና የ32 አመት አፍላ ጎረምሳ ነበር::ፊዴል ካስትሮ የወቅቱን አፍቃሪ አሜሪካውን የባፕቲስታ ስርአት ገርስሶ እንደ አውሮፓውያን ቀመር 1959 የተቆናጠጠውን የስልጣን እርካብ እስከ 2006 አመተ ምህረት ድረስ ሽምጥ ሲጋልበው ከርሞ በአንጀት ህመም ምክንያት ለታናሽ ወንድሙና ለትግል አጋሩ ለራዉል ካስትሮ ስልጣኑን ለማጋራት ተገደደ::ያ ከከንፈሩ ቶስካኖ ሲጃራ የማይለየውና የብዙሃኑ ወጣቶችን በአጫጫሱ ጭምር ቀልብ ይስብ የነበረው ፊዴል ካስትሮ ያንን ተወዳጅ ቅጠልያ ወታደራዊ መለዮውን በዛ ለግላጋ ቁመናውና ሰፊ ደረቱ ላይ ከተገጠገጡት ኒሻኖች ጋር አድርጎ ወደ አደባባይ ብቅ ሲል ግርማ ሞገሱ እጅግ ማራኪ የነበረው ሰው የገመምተኛ ቱታውን አድርጎ ከመኖሪያ ቤቱ የሚውል ግራና ቀኝ ክንዱን ጎበዛዝት ይዘው ወዲህና ወዲያ የሚያዘዋውሩት አዛውንት ሆነና አረፈው::

  ካስትሮ በ2008 አመተ ምህረት ስልጣኑን ለታናሽ ወንድሙ በይፋ ካስረከበ በኋላ በተደጋጋሚ ሞቷል እየተባለ ሲወራበት የነበረ ቢሆንም ሰውየው በዋዛ እጅ የማይሰጥ ነበርና በተደጋጋሚ በብሄራዊው የኩባ ቴሌቭዥን ጣብያ ብቅ እያለ ከዘራ ያልያዘበት እጁን በቡጢ አምሳያ ጨብጦ ሽቅብ ቁልቁል እያደረገ “አለሁ እኖራለሁ እንተያያለን” አይነት ፉከራ እየፎከረ በተደጋጋሚ ሲታይ ነበር::

  ሃገራችን በሶማሊያ ወራሪ ሃይል በተወረረችበት አፍላ የደርግ የስልጣን አመታትም ካስትሮ  አይነተኛ ዉለታ ለኢትዮጵያ ዉሎ እንደነበር በወታደራዊው ቡድን ዉስጥ ስልጣን የነበራቸው የወቅቱ ሹማምንት ዛሬ ዛሬ ጽፈው በሚያስነብቡን መጽሃፍ ልንረዳው ችለናል::በወቅቱ ንጉሰ ነገስት አጼ ሃይለስላሴ የወራሪው የሶማሊያን ጦር ለመመከት ከዚህም ከዚያም ብለው ያሟጠጡትን የሃገሪቱን አንድ መቶ ሚሊየን ዶላር ለአሜሪካን መንግስት ገቢ አድርገው መሳሪያ እንዲሰጧቸው ተደራድረው ነበር::የግዥው ሁኔታ በአግባቡ ሳይካሄድ የየካቲቱ አብዮት ደርሶባቸው ስልጣናቸውን ባጡት ንጉስ ምትክ ስልጣኑን የያዘው የደርግ መንግስትም ቀደም ሲል ክፍያ የተፈጸመበትን መሳሪያ የአሜሪካ መንግስት እንዲሰጠው ተደጋጋሚ ተማጽኖ ቢያደርግም ምላሹ ጆሮ ዳባ ልበስ ሆነበር::በዚህ ግዜ ነበር አፍለኛው የደርግ መንግስት ፊቱን ወደ ምስራቁ ጎራ በማዞር በወቅቱ የሶሻሊስት አቀንቃኝ የነበሩትን እንደነ ሰሜን ኮሪያ ኩባና ሶቭየትህብረትን መጎዳኘት የጀመረው::በወቅቱ ሶቭየት ህብረት በአፍሪካ ተወዳዳሪ የሌለው ጦር ሰራዊት የደርግ መንግስት እንዲገነባ የጦር መሃንዲሶቿን በአማካሪነት ጦር መሳሪያዎቿን ደግሞ በብዛት ወደ ኢትዮጵያ በመላክ መንግስታችንን እስከ አፍንጫው ልታስታጥቀው ችላ ነበር::ነገር ግን የኩባዊያኑ ዉለታ ከዚህ በእጅጉ የተለየ ነበር::ኩባ ሙሉ ትጥቅ የታጠቁ በበቂ ሁኔታ የሰለጠኑ ፋኖ ወታደሮቿን ከመሳሪያ እርዳታ ጋር አብራ ነበር ወደ ኢትዮጵያ የላከችው::

  ይህ በስተመጨረሻው ደርግን የልብ ልብ የሰጠው የሶማሊያ ጦርነት በኢትዮጵያ ፍጹም አሸናፊነት በተጠናቀቀበት ወቅት ቁጥራቸው ወደ 15000 የሚጠጉ (ቁጥሩን በተለያዩ  መዛግብት ላይ የተለያየ መጠን መሰጠቱን ልብ ይሏል)የኩባ ወታደሮች ደማቸውን ለኢትዮጵያ ማፍሰሳቸውን መዛግብት ይነግሩናል::ለዚህ መስዋእትነትና ወዳጅነት ሲባል ነበር ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አጠገብ የሚገኘው ባለ ቀይ ኮከቡ የ“ትግላችን”ሃውልት ተመርቆ ለመታሰቢያነት የቆመው::

  ካስትሮና ኩባ ለኢትዮጵያ ከሰጡት ዉለታ ሌላኛው ተጠቃሹ ጉዳይ በወቅቱ የነበረው የትምህርት ስልጠና (SCOLARSHIP)ነበር::ዛሬ ዛሬ በርካታ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ሰራተኞቻቸውን በገፍ ወደ ቻይና ይልኩ እንደነበረው የቀድሞ መንግስትም ካድሬዎቹንና ብቁ ተማሪዎቹን ወደ ቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት እንዲሁም ወደ ኩባ ይልኩ ነበር::በዚህም የኩባን ዉለታ ዛሬም ድረስ የያኔዎቹ የኩባ ተማሪዎች ያስታዉሳሉ::

  እኝህ በዘጠና አመታቸው ከሰሞኑ መሞታቸው የተነገረን የቀድሞው የኩባ ፕሬዚደንት ፊደል ካስትሮ ኢትዮጵያን ከአንዴም ሁለት ግዜ ጎብኝተው እንደነበር “አብዮቱና ትዝታዬ”በተሰኘው መጽሃፋቸው ላይ የቀድሞው የኢትዮጵያ ምክትል ፕሬዚደንት ሌተና ኮሎኔል ፍሰሃ ደስታ ይገልጻሉ::የመጀመሪያው ጉብኝታቸው የነበረው የኢትዮጵያ አብዮት በተካሄዴ በሁለተኛው አመት ገደማ ነበር::ወቅቱ የሶማሌ ወራሪ ጦር ኢትዮጵያን ወሮ ስለነበረና ካስትሮም ከሶማሊያው መሪ ዚያድ ባሬ ጋር ጥሩ ቀረቤታ ስለነበራቸው ሞቃዲሾን ከጎበኙ በኋላ ኢትዮጵያን በመጎብኘት የሽምግልና ስራን ለማከናወን እግረ መንገዳቸውንም የኢትዮጵያን አብዮት አይነቱንና ሁኔታዉን ለመረዳት ነበር ይፋዊ ላልሆነ ጉብኝት በመጋቢት ወር 1969 አመተ ምህረት በአንድ ሻምበል የኩባ ጦር ታጅበው ወደ አዲስ አበባ የመጡት::

  ሌላኛው የካስትሮ ጉብኝት ደግሞ በደርግ ግዛተ መንግስት ሁል ግዜ በድምቀት ይከበር በነበረው የመስከረም ሁለት በአራተኛው የአብዮት በአል ላይ ነው::ለብሄራዊ ክብረ በአሉ እጅግ ከፍተኛ ድምቀት ሰጥተውትም እንደነበር ዛሬም ድረስ የሚታየው ምስላቸው ቁልጭ አድርጎ ያሳያል::በወቅቱም በየቀበሌው ይገኙ የነበሩ የደርግ ካድሬዎች ህዝቡ የወቅቱ ዝነኛ የአብዮተኞች ምሳሌ የነበሩትንና ፋኖውን ፊዴል ካስትሮን በነቂስ ወጥቶ እንዲቀበሉት መታዘዙን ተከትሎ የተቀለደው ቀልድ ዛሬም ድረስ ይወራል::

  የመልእክቱ መደበኛ ይዘት የነበረው “የቀበሌ  ነዋሪዎች በሙሉ ፊዴል ካስትሮ ስለሚመጣ ወጥታችሁ ተቀበሉ”ነበር::ነገር ግን በወቅቱ በአንዱ ቀበሌ ይህንን መልእክት እንዲለፍፍ የታዘዘው ጡሩንባ ነፊ እምብዛም በትምህርቱ ያልገፋና ነገር ቶሎ የማይይዝ ስለነበር ፊዴል ካስትሮ የሚለው ስም አልያዝ ብሎት “የቀበሌ ነዋሪዎች በሙሉ “ፍየል ታስሮ” ስለሚመጣ ቢላዋ ይዛችሁ ተቀበሉት”ብሎ ለፈፈ ተብሎ  ሲቀለድ ነበር::ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሌላው ተጠቃሽ ቀልድ ደግሞ ኮሎኔል መንግስቱ ለመጀመሪያ ግዜ የኩባውን ፕሬዚደንት በአካል ተገናኙ በተባለበት ግዜ የተቀለደው ቀልድ ነው::በወቅቱ ፊዴል ካስትሮ  አዲስ አበባ እንደገቡ እጃቸውን በመዘርጋት ሙሉ ስማቸውን ጠቅሰው ነበር የተዋወቁት “ፊዴል ካስትሮ ሩዝ እባላለሁ”ባሉበት ግዜ መንግስቱ የሚያውቁት ፊዴል ካስትሮ  እሚለውን ስም ብቻ ስለነበርና የአያት “ሩዝ” የምትለዋ ተቀጥላ ስም ሳይሆን የሃገሪቱን ታዋቂ ምግብ የጠቀሱላቸው መስሏቸው ኮሎኔሉም እጃቸውን ዘርግተው “መንግስቱ ሃይለማርያም ቅንጬ” ብለው መልሰዋል እየተባለ ይወራ ነበር::

  ፊዴል ካስትሮ  እጅግ አወዛጋቢ እና ገራሚ ሰው ናቸው አሜሪካ ሰዉዬውን ለመግደል ያልቧጠጠችው ገደል ያልቆፈረችው ጉድጓድ ያልበጠሰችው ቅጠል ያልማሰችው ስር አልነበረም::ለዚህም አላማዋ የተመረዘ የጥርስ ብሩሽ የተበከለ ሲጃራ  በመርዝ ጭስ የታፈነ ስቱዲዮ ስልጡን እና ገዳይ ስኳዶች እና የመሳሰሉትን በማሰማራት ለ638 ግዜ ሰዉዬውን ልትገድላቸው ብትሞክርም ሳይሳካላት ቀርቶ ካስትሮ  በስልጣን ላይ ለ47 ሰባት አመት ሲቆዩ አስራ አንድ የአሜሪካ ፕሬዚደንቶች ተፈራርቀዋል::

  በ1960 ዎቹ የነበሩ የተማሪ እንቅስቃሴዎች እንደ መሪ መፈክርና እንደ ምሳሌ ሲያደርጓቸው ከነበሩ አብዮቶችና የትጥቅ ትግሎች መካከል የደቡብ አሜሪካዎቹ እንቅስቃሴዎች ተጠቃሾች ናቸው::ለዚህ ይመስላል “ፋኖ  ተሰማራ ፋኖ  ተሰማራ እንደ ሆቺሚኒ እንደ ቼጉቬራ”እያሉ ሲያዜሙ ይደመጡ የነበረው::እንደሚታወቀው ኤርኔስቶ  ቼጉቬራ ደግሞ ከተወለደበት ሃገር በይበልጥ በሌሎች ሃገሮች የነጻነት ተጋድሎው ስለሚታወቅና በተለይ በኩባ የነጻነት ትግል ባደረገው ጉልህ ተሳትፎ ብሎም ከፊዴል ካስትሮ  ጋር በነበረው የቅርብ ግንኙነት የኢትዮጵያ አብዮተኞች እንደ ምሳሌ ሲያነሱት በተደጋጋሚ ያነሱት ነበር::

  የፊዴል ካስትሮን ነገር ስነነሳ ከቀድሞው የኢትዮጵያ መሪ ከኮሎኔል መንግስቱ ጋር የነበራቸውን እጅግ የጠለቀ ግንኙነት ሳያነሱ መተው ታሪክን ጎምዶ እንደማስቀረት ይቆጠራል::በአስራ ሰባቱ የደርግ አገዛዝ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ ከአንዴም ሁለት ግዜ መጥተው የነበሩት ፊዴል ካስትሮ  በ1970 አመተ ምህረት ገደማ የኢትዮጵያን ሉአላዊ ግዛት በእብሪት ወሮ የነበረውን የሶማሊያውን መሪ ሞሃመድ ዚያድባሬንና መንግስቱ ሃይለማርያም ገጽ ለገጽ በማገናኘት ሁለቱ የሶሻሊስት ሃገሮች የድንበር ችግራቸውን በሰላም እንዲፈቱ ከፍተኛ ጥረት አድርገው እንደነበር: ነገር ግን በወቅቱ በሶቭየት ህብረት አለኝታነት እስከ አፍንጫው የታጠቀውን የጦር መሳሪያ በመተማመን መንግስቱ ሃይለማርያምን እንደ አንድ “ተራ ሻለቃ” እያጣጣለና ቅኝ ገዝዎች የሰጡትን የ“ታላቋ ሶማሊያ” ካርታ በተደጋጋሚ እንደ ምሳሌ በማንሳት የሰላም ድርድሩ እውን እንዳይሆን ስላደረገ ፊዴል ካስትሮም የዚያድባሬን ትምክህተኝነት በውል ስለተገነዘቡ ነበር ኢትዮጵያን ለመርዳት የወሰኑትና 15000 ወታደሮቻቸውን ህይወት ለመገበር የወሰኑት::

  ሌላው ከዚሁ ጋር በተያያዘ መልኩ ደርጎች በወቅቱ የጦር መሳሪያ ፍላጎታቸን ለማሟላት ፊታቸውን ያዞሩት ወደ ሶቭየት ህብረት ነበር::ሶቭየቶችም ጦር መሳሪያውን ከፊሉን በእርዳታ ከፊሉን ደግሞ በረዥም ግዜ ብድር እንዲከፈል ተስማምተው ስለነበር ሲያስታጥቁን የነበረው በወቅቱ በጦርነት ላይ ሌላ ጦርነት የተደራረበበት የደርግ መንግስት የብድሩ መጠን እጅግ በጣም የበዛ ሚሊየን ዶላር መሆኑ ስላሳሰበው በሊቀመንበሩ በኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማርያም አማካይነት ለመፈረም ሲያመነታ ቆየ::ይህንን የኮሎኔል መንግስቱን ፍራቻ የተመለከቱት ፊዴል ካስትሮም “መንግስቱ ሶቭየቶች እኮ ይህንን ሁላ ገንዘብ ችላችሁ እንደማትከፍሉት እያወቁ እኮ  ነው የሚያስፈርሟችሁ የነሱ ጽኑ ፍላጎት የሶሻሊዝም መስፋፋት ነው ብቻ አንተ በርትተህ ሶሻሊዝምን አስፋፋ ምን አለ በለኝ ብድሩን ወይ ይቀንሱታል ወይ ይሽሩታል::ካልሆነ እኛም እናግዝካለን”በማለት ነበር ፕሬዚደንት መንግስቱን ያበረታትቱትና በርካታ የጦር መሳሪያ ባለቤት እንድንሆን ያደረጉን::

  ቁመተ ለግላጋ ፊታቸው የማይፈታ ቆፍጣና ደረተ ሰፊ ወንዳወንድ መነጽር ከአይናቸው ቶስካኖ  ከአፋቸው የሚበዛው ፊዴል ካስትሮ ለሃያላኑ ምእራባዊያን ፈጽሞ ሳይበገሩ እድሜን ጠግበው በለሆሳስ ክንዳቸውን ተትተርሰው እስከወዲያኛው አሸለቡ::አሜሪካ “አምባገነን”እያለች እምትፈርጃቸውን የአለም መሪዎች በአንዱ ይሁን በሌላው መንገድ እየገዘገዘች ስትገነድሳቸው ኖራ የፊዴል ካስትሮ  ጉዳይ ግን አልሆን ብሏት ከረመ::እርሳቸውም ከአሜሪካ ጋር መሰዳደቡና እሰጥ አገባው የተመቻቸው ይመስል ነበር::ምን ያደርጋል እርጅና ጓዙን ይዞ እየተንኳተተ መጣና ከቤት አዋላቸው::እንደፎከሩትም አሜሪካ እጅ ላይ አልወደቁም::እንደ ሌሎች መሪዎችም በገዛ ወታደራቸው አልተገደሉም::በእርጅና ወሮቻቸው ጥቂቶች ብቻ በሚታደሉት መልኩ የህዝብና የመላው አለም ፍቅር አልተለያቸውም ነበር::አሜሪካ እንደሰጠቻቸው የ “አምባገነን”ስያሜ ሬሳቸው እንደ አህያ ሬሳ በየመንገዱ አልተጎተተም::እነሆ ኩባ ዘጠኝ የሃዘን ቀናትን አውጃ የመሪዋን ሞት ማቅ ለብሳ አመድ ነስንሳ ልታከብር ቀናትን እየቆጠረች ባንዲራዋንም ዝቅ አድርጋ እያውለበለበች ነው::እንዲህ ከነስህተቱ በህዝብ ዘንድ እስከ ሞት ድረስ የሚወደድ መሪ ዛሬ በህይወት ይኖር ይሆን::

   (ክቡር መተኪያ ሃይለሚካኤል)

 • loader Loading content ...
loader Loading content ...

Comments (1)


loader Loading content ...