loader

Topics (12)


loader Loading content ...

Explanations (12)


 • @Befkadu Getachew   2 years ago
  Sewasewer


  …..በበቀለ ታዬ……
  :
  (ይህ ጽሁፍ የጥምቀት በአል ከሰአት በኋላ ላይ ጽፌዉ ሳልፖስተዉ ረስቼዉ የነበረ ሲሆን የሚነበብ ካጣችሁ ብቻ ለዛሬ ተደበሩበት በ“በቀለ ታዬ“ ያልኩትም ለደህንነቴ ስል እንጂ ጸሃፊዉስ እኔዉ ነኝ )
  በጥምቀት ጥዋት አልጋዬ ላይ ሆኜ የጄምስ ብራዉንን “ፕሊስ ፕሊስ“ የሚለዉን የ1950 ዎቹ ተወዳጅ ዜማ እያዳመጥኩ ነበር፡፡ ከሳሎን ኢቲቪ ሲያላዝን ይሰማኛል፡፡ግን የኢቲቪ ሰዎች ሁል ግዜ አንድ አይነት ልፍለፋ አይሰለቻቸዉም….አንድ ዜማ …አንድ ቅኝት…… 
  አንዳንዴ ሳስበዉ ኢቲቪ አዝማሪ ቢሆን የሆነ ማሲንቆዉን ይዞ
  “በጎድጓዳ ስፍራ ይበቅላል ደደሆ“ 
  …“በጎድጓዳ ስፍራ ይበቅላል ደደሆ“ …
  “በጎድጓዳ ስፍራ ይበቅላል ደደሆ“ 
  አሁንስ ወደ ቀጣዩ ግጥም ሊያልፍ ነዉ ስትሉ 
  “በጎድጓዳ ስፍራ ይበቅላል ደደሆ“ 
  “በጎድጓዳ ስፍራ ይበቅላል ደደሆ“ 
  እያለ ቀኑን ሙሉ ሙዝዝ የሚል ልጋጋም አዝማሪ ይመስለኛል……“ፕሊስ ፕሊስ“ የጀምስ ብራዉን ዘፈን ከ ሸክላ ላይ ባይሆንም ሸክላ ላይ ከተቀመጠዉ ፍላሽ ማጫወቻ በለሆሳስ ይወጣል……...እኔም ሳላዉቀዉ ኢቲቪን ይሁን መንግስትን ይሁን አምላክን ይሁን ብቻ የሆነ ለራሴ ያላወኩትን የሆነ አካል “ፕሊስ….ፕሊስ“ እያልኩኝ ነዉ (ያዉ በዉስጤ ነዉ ታዲያ) 
  “ኤጭ ኢቲቪ!“ ብዬ ወደ ጃንሜዳ ለመሄድ ተነሳሁ፡፡ቲቪዉን ልዘጋዉ ስል “ጠ/ሚኒሲቴር መለስ ዜናዊ በምስራቅ አፍሪካ ትልቅ ቦታ የሚሠጣቸዉ መሪ እንደነበሩ አንድ ሰዉዬ የጻፈዉ መጽሀፍ አመለከተ“ ይላል ዜናዉ ፡፡ እና ምን ይጠበስ!? 
  አንድ ነጭ እንደዚህ ብሎ ስለጻፈ መወራት አለበት?! እስቲ አስቡት በናታችሁ…. ባለፈዉ አንድ ከአሌክስ አብርሃ ብሎግ ያነሰ ፎሎወር ያለዉ የአፍሪካ መጽኄት ጠ/ሚ ሃይለማሪያምን የአፍሪካ ምርጡ መሪ ብሎ መረጣቸዉ ሲባል ሰምተን “አሁን ይሄ ዜና ነዉ?!“ ብለን ሼም ይዞን ሰነበትን….. አንዳንዴ “እነኚህ ሰዎች አሁንም ጫካ ያሉ ነዉ እንዴ የሚመስላቸዉ?!“ እላለሁ(በሆዴ) ፡ ማለቴ ኢትዮጲያን የሚያህል ትልቅ እና ታሪካዊ ሀገር መሪ አንድ ተራ ነጭ ሰዉዬ በጻፈዉ መጽሀፍ ዉስጥ መወደሱ በሀገሪቷ “ዋና“ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ “ሄድ ላይን“ መሆን ነበረበት?! እንዲህ አይነት ሪኮግኒሽን የሚያስደስተዉ እኮ የሆነ የ“ጎሬላ ፋይተር“ መሪን እንጂ እንደ ኢትዮጲያ አይነቷን ታላቅ ሀገር የሚመራን መሪ አይደለም…አረ ጎበዝ ለራሳችን ክብር እንስጥ!በሌላዉ አለም ስለ አጼ ሃይለስላሴ የሚባለዉን ብንሰማ ይህ ዜና እንዴት ዜና እንደማይሆን እና እኔ ምን እንደዚህ እንደሚያንጨረጨረኝ ይገባን ነበር! 
  ቀጠለ ዜናዉ “ኢቲቪ ሃምሳኛ አመቱን ሲያከብር ከሰራዊት ፍቅሬ ጋር በመተባበር መሆኑን ገለጸ“ አሉ ደግሞ፡፡ እሺ! ይህ እንኳን አሪፍ ማች ነዉ ……እኒህ ሁለቱ አብረዉ ማዝገም ይችላሉ…….
  ኢቲቪ እንደተለመደዉ የጥምቀት በአልን በተመለከተ የሆኑ ነጠላ(ሲንጉላር) የለበሱ ነጮች ጮክ ብለዉ ብዙም እንግሊዝኛ ከማይችሉ የኢትዮጲያ ጋዜጠኞች ጋር ሲያወሩ እያሳየ ነዉ፡፡ ያዉ ለባለፉት 15 አመታት ከጃሜዳ እንዳደስተላለፈዉ ማለት ነዉ፡፡ ኤጭ “በጎድጓዳ ስፍራ ይበቅላል ደደሆ“ ቀጠለ…..
  “እኔ ግን ምን አዳረቀኝ?!“ ብዬ በቀጥታ ትላንት የሸኘሁትን የአጥቢያዬን ታቦት ለመመለስ ወደ ጃን ሜዳ አቀናሁ (ለደህንነቴ ሲባል የአጥቢያዬ ታቦት ማን እንደሆነ ከመግለጽ ተቆጥቤያለሁ …ኡራኤልን! ሚስጥረኛ ለመሆን ሳይሆን የሴኩሪቲ ነገር ሆኖብኝ ነዉ!) ጃንሜዳ ስደርስ የሰዉ ብዛት የጸበል መጠመቂያዉ ጋር አያስደርስም…በጃንሜዳ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች ክብ ሰርተዉ ይጫወታሉ (የተለያዩ ያልኩት የተለያዩ የራያ ግሩፖችን እንጂ እዉነቱን ለመናገር ሌላ “ብሄረሰቦችስ“ አላየሁም)
  ከጭፈራዎች ሌላ ብዙ አይነት ምርጫ ቦርድ ያዘጋጃቸዉ የሚመስሉ ጫወታዎች(ቁማሮች) አሉ፡፡ ለምሳሌ የሆነች ጠባብ ቀለበትን ወርዉሮ በጠርሙስ አንገት ማስገባት ፡ እጅግ በጣም እሩቅ ከሆነ ቦታ ላይ አንዲት ግማሽ ሌትር የምትይዝ ሃይላንድን በኳስ መምታት ፡ አይን ታስሮ የሆነ የተንጠለጠለ ማሰሮ በዱላ ሄዶ መስበር ወ.ዘ.ተ ወዘተ ናቸዉ፡፡ ጨወታዎቹ የተሳታፊዉን ሳንቲም ከመብላት ዉጪ ተሳታፊዉ የሚያሸንፍበት እድል ጠባብ ስለሆነ ነዉ “ምርጫ ቦርድ ያዘጋጃቸዉ ይመስላሉ“ ያልኩት፡፡ ይህን ነጥብ እመለስበታለሁ ግን በዚህ አጋጣሚ ዚስ ዴይስ የጀመረኝን ሁሉንም ነገር ፖለቲሳይዝ የማድረግ ሱስ ልንገራችሁ....
  ባለፈዉ የገና ዋዜማ የነብስ አባታችን እቤት መጥተዉ በዋናነት ፖለቲካ መጻፍ እንዳቆም በሚያጠነጥን ሀሳብ ላይ ማብራሪያ እየሠጡ በዛዉም ስለ ገና እና ስለ ጌታ ዉልደት አንዳንድ ነገሮች እየነገሩን ነበር፡፡ሚስቴ በመሀል እምጵጽ ….እምጵጽ ትላለች ፡፡ በነገራችን ላይ ስብከቱ ዉስጥ ምንም እምጵጽ የሚያስብል ነገር የለም፡፡
  “ይሄዉላችሁ ልጆቼ የጌታን ዉልደት ልብ ብላችሁ ካያችሁት ብዙ ነገር መማር ትችላላችሁ“ አሉ አባ ከፊታቸዉ እጅ በደረት አድርገን ለምንሰማቸዉ እኔና ባለቤቴ…. “ጌታ በቤተመንግስት እንደሚወለድ ሲጠብቁት እሱ ግን በከብቶች በረት ነዉ የተወለደዉ“ አሉ…. ሚስቴ እምጵጽ ትላለች…(የእኔ አእምሮ ግን የሚያስበዉ ግን ቤተ-መንግስት ከሚለዉ በመነሳት ስለ ሌላ ፖለቲካ ነበር) … ቀጠሉ አባ …“ስንት የተከበረ ሙያ እያለ ከድንጋይ ጠራቢ ቤተሰብ ተወለደ….እንዲወለድበት የመረጠዉ ወር ራሱ ልብ ብላችሁ ካያችሁት ከወራት ሁሉ አስከፊዉን ዲሴምበርን ነዉ! ከተወለደ በኋላ በበረት ዉስጥ በትንፋሽዋ ያሞቀችዉ አህያ ከእንስሳት ሁሉ የተናቀች ነች! እዩት ጌታ የሚመርጠዉን !“አሉ የእኔ አእምሮ ደግሞ “ በዚህ አይነት ጌታ ኢሃዲግን ሳይወድ አይቀርማ!“ የሚል የጅል የፖለቲካ ሀሳብ ያስባል…..መጥፎ ሱስ ይዞኛል፡፡
  እና ወደ ጃንሜዳ ጫወታዎች እንመለስ ……. “በአንድ ብር አስር ብር ያሸንፉ!“ ይላል የሃይላንድ ጠርሙስ በኳስ ከረጅም እርቀት ላይ የመምታት ቁማር የሚያጫዉተዉ ልጅ፡፡ኳሷ ያለችበትን እርቀት ብታዩት እንኳንስ ምእመኑ ሮናልዶና ሜሲም ተመካክረዉ ቢመቱ ሃይላንዷን አያገኟትም፡፡በአጭበርባሪነታቸዉ ተናድጄ አንድ ብሬን መዥረጥ አድርጌ ኳሷን ተቀበልኩ እና አነጣጥሬ መታሁ፡፡መቼም የዚህ ጽሁፍ ጸሃፊ እኔዉ ስለሆንኩ በዛ ላይ ሃይላንዷን ሜሲም እንኳን አያገኛትም ስላልኩ አታምኑኝም እንጂ በእልህም ጭምር ስለመታኋት ነዉ መሰለኝ እኔም ሳትኳት፡፡
  “ሌቦች!“ ብዬ ወደ ሌላ ግሩፕ አለፍኩ፡፡ የሆኑ ወጣቶች አርሞኒካ እየነፉ ይጫወታሉ፡፡ ሁሌም ግርም የሚለኝ አርሞኒካ አሁን የት እንደሚሸጥ እና ልጆቹ የሚጫወቷት ዜማ ከአዉራጃ አዉራጃ (የድሮ ስርአት ናፋቂ መሆኔን ልብ ይሏል) አንድ መሆኗ ነዉ ፡፡ 
  እነኚህንም ትቻቸዉ ወደ ሌላ ግሩፕ አለፍኩ፡፡ እዚህኛዉ ጨወታ ላይ ተሳታፊዉ አይኑ በጨርቅ እንደታሰረ ማሰሮዋን መስበር ከቻለ አጫዋቹ እንደነገረን ማሰሮዉ ዉስጥ ያለዉን ሰማንያ ብር ይወስዳል፡፡ 
  እኔ ስደርስ የሆነች ልጅ አይኗ በጨርቅ እየታሰረ ነበር፡፡ ሰዉ ሁሉ ከቦ በጉጉት ያያል፡፡ ልጅቷ የማሰሮዉ አቅጣጫ እንዲጠፋባት አይኗን ያሰረዉ ልጅ ሶስት ግዜ አሽከርክሮ አሽከርክሮ ለቀቃት፡፡ ዱላዋን እያወዛወዘች ማሰሮዉ ይገኝበታል ብላ ወደ አሰበችዉ አቅጣጫ ተጓዘች፡፡ጨዋታዉ በብዙ መልኩ የኢትዮጲያ ብሄራዊ ምርጫን ይመስላል፡፡ መንግስት ለህዝቡ እንደ ተሰቀለቸው ማሰሮ “በምርጫ ልታወርደኝ ትችላለህ“ ብሎ በዱላ መልክ የምርጫ ካርድ ሰጥቶታል፡፡ከምርጫዉ በፊት ግን አሁን ልጅቷን እንዳደረጓት አይነት ህዝቡ የሚፈልገዉን ፓርቲ እንዳያዉቅ አይኑን በጨርቅ ያስረዋል ከዛም ልክ እንደልጅቷ አሽከርክሮ አሽከርክሮ (ያዉ ተስፋ ያላቸዉን በማሳደድ እና በማዋከብ ተስፋ አስቆርጦ ሲያበቃ ) “በል መርጠህ ምታ“ ብሎ ይለቀዋል፡፡
  በነገራችን ላይ ልጅቷ በቀጥታ ወደ ማሰሮዉ አቅጣጫ እየገሰገሰች ነዉ፡፡
  ዙሪያዋን የከበባት ህዝብ እኔን ጨምሮ “በርቺ በርቺ!“ እያለ በትክክለኛ አቅጣጫ እንደሆነች እና መስመሯን እንዳትስት በመንገር ማበረታት ቀጠልን፡፡ግማሹ “ወደ ቀኝ!“ ይላል ግማሹ “ወደ ግራ ብራቮ በርቺ!“ ይላል፡፡ ልጅቷ ቆም ብላ ህዝቡ የሚላትን ለመስማት ስትሞክር የበለጠ ግራ ይገባታል፡፡የሕዝቡ ምክር እና የልጅቷ ግራ መጋባት የምርጫ ሰሞን የሚወጡ ጋዜጦችን እና የ97 ቱን ቅንጅት አስታወሰኝ፡፡ ልጅቷ ቀጥ ብላ ወደ ማሰሮዉ ተጠጋች፡፡ማሰሮዉን ልታነካክተዉ ስትል አጫዋቾቹ ጨነቃቸዉ መሰለኝ ከመካከላቸዉ እንደኛዉ ቀጥ ብሎ ሄዶ ክንዷን ያዘና አሽከርክሯት ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ መራትና ተመለሰ ፡፡
  “እንዴ ይሄማ ፌይር አይደለም!“ ብለን ቀወጥነዉ፡፡ ገንዘብ ለሚሰበስበዉ ልጅ “እንዴት እንዲህ ታደርጋላችሁ!“ ብዬ ቅሬታ አቀረብኩ፡፡ የመለስናት ጥፋት ስላጠፋች ነዉ ብሎ የሆነ የጸረ ሽብር አዋጁን የሚስል ህግ ጠቀሰና የመለሳትም ልጅ ምንም እንዳለጠፋ ገልጾልኝ ፍጥጥ ብሎ አየኝ…የሆነ ነገሩ ፕሮፌሰር መርጋ በቃናን ይመስላል፡፡
  ልጅቷ ግን የዋዛ አይደለችም፡፡ እንደምንም ብላ የማሰሮዉን አቅጣጫ ይዛ ጥረቷን ቀጠለች፡፡ ማሰሮዉን ያገኘችዉ ሲመስላት ባለ በሌለ ሃይሏ ዥዉ ታደርጋለች፡፡ የኢትዮጲያ ህዝብ ልክ እንደዚህ አይኗን የታሰረች ልጅ ይመስለኛል፡፡ ዱላዉን እያወዛወዘ ጨቁኖኛል የሚለዉን መንግስትን አነክቶ ለመጣል ይፈልጋል…… መአት ጩኸት ከዚህም ከዚያም ይሰማል…..የደረሰበት ሲመሰለዉ ዥዉ ያደርጋል! ግን አያገኘዉም!……. ልጅቷ በሚገርም ፍጥነት ወደ ማሰሮዉ እየተጠጋች ነዉ…….ጩኸቱ በርክቷል…… ጋይስ እኔ የምሸኘዉ ታቦት ተነስቷል እንጂ ይህንን ወሬ ብንጨርሰዉ ደስ ይለኝ ነበር ….“አንባቢ ሆይ ልጅቷና ህዝቡ ይህንን ባዶ እንስራ ያገኙት ይሆን!?“ ….ሌላ ቀን እንመለስበታለን.....
  .ይመቻችሁ
 • loader Loading content ...
 • @Befkadu Getachew   2 years ago
  Sewasewer


  ናይጀል ቢንስ የብዙ ታላላቅና ዝነኛ ሰዎችን ምስል እንዲሁም ታሪካዊ ሃውልቶችን በመቅረጽ ራሱ ዝነኛ መሆን የቻለ Sculptor... ቀራጺ ነው። በአንድ አጋጣሚ ከቴድ ዓለማየሁ ጋር ሆነን አገኘነውና ስለ ሰራቸውና ወደፊት ሊሰራቸው ስላቀዳቸው ነገሮች ሲነግረን ተማረክን። በተለይ ኢትዮጵያ ላይ ሊያቆመው ስለሚፈልገው ጥልቅ ፍልስፍና ያለው ግዙፍ ሃውልት (ላንድማርክ) ሲነግረን ተደሰትን። በመቀጠልም የሚሰራበትን ቦታ እንድንጎበኝለት ጋበዘንና ግብዣውን ተቀብለን ጎበኘነው። 
  ናይጀል ሰዓሊ፥ ቀራጺና ማርሻል አርቲስት ሲሆን በማርሻል አርቲስትነቱም በጃኪ ቻን The Big Brawl ፊልም ላይ ተሳትፏል። የማይክል ጃክሰን አጃቢ ሆኖም ሰርቷል። በሰዓሊነትና በቀራጺነትም በብዙ ቦታዎች አሻራዎቹን አሳርፏል። በቅርቡ በአዲስ አበባ (በኢትዮጵያ አቪዬሽን አካዳሚ) ታሪካዊ ሃውልት ለማስቀመጥም ሽርጉድ ላይ ነው። ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝም ይሄው ታሪካዊ ሃውልት ነው። ናይጀል ቢንስ አሜሪካዊ ቢሆንም ልቡ ያለው ግን አፍሪካ... በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያ እንደሆነ በመኖሪያ ቤቱና በወርክሾፑ ውስጥ ካሉት የስዕልና የቅርጻ ቅርጽ ስራዎቹ መመልከት ችያለሁ። አፍሪካ ላይ ለመስራት ባቀደው ትልቅ ሃውልት (ላንድማርክ) አማካይነት ስለ ናይጀል ወደፊት ብዙ እንሰማለን። ለዛሬ ግን በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ ስለሚልከው ታሪካዊ ቅርጽ (ሃውልት) ልንገራችሁ...

  በአውሮፕላን በረራ ታሪክ አፍሪካ አሜሪካዊያን የማብረርና የመዋጋት ችሎታንቸውን ያሳዩት ከ1ኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ጀምሮ ቢሆንም በዘረኝነት ምክንያት የአሜሪካ አየር ሃይል እንዳያበሩ ከልክሏቸው ነበር። በመሆኑም በ1ኛው የዓለም ጦርነት ላይ በተዋጊ አውሮፕላን አብራሪነት በመሳተፍ... የመጀመሪያው ጥቁር አሜሪካዊ አብራሪ ሆኖ በታሪክ የሰፈረው ኢጉን ቡላርድ አሜሪካ ማብረር ስትከለክለው የፈረንሳይን አየር ሃይል በመቀላቀል ነበር ተዋግቶ ታሪክ ያስመዘገበው። እንደሱ ወደ ፈረንሳይ ያልሄዱት ወገኖቹ ግን በዘረኝነት ወለድ ጥቁሮችን የመናቅ በሽታ... ውጊያ ላይ መሳተፍ ቀርቶ አውሮፕላን አንስተው ለማሳረፍ እንኳን አሜሪካ እምነት አልጣለችባቸውም ነበር። ይህ የዘረኝነት መድልዎ Tuskegee Institute የተባለውን ዝነኛ የጥቁር ፓይለቶች ማሰልጠኛ መስራች የሆነውን ኮሎኔል ጆን ሲ ሮቢንሰንን ጨምሮ በሁሉም ጥቁር ፓይለቶች ላይ የሚደረግ አሳዛኝ ክስተት ነበር። 
  ነጭ አሜሪካዊያን ፓይለቶች እንደ ወፍ ሰማይ ላይ ሲበሩ ኮለኔል ሮቢንሰንን ጨምሮ አፍሪካ አሜሪካዊያኑ ፓይለቶች ካምፕ ውስጥ ቁጭ ብለው ካርታ እንዲጫወቱ የዘረኝነት ፍርድ ተፈረዶባቸው ነበር። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉም ነበር ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን መውረሯን በሬድዮ የሰሙት። እናም የTuskegee Institute መስራቹና የዘር መድልዎውን ለማስቀረት ግንባር ቀደም ታጋይ ፓይለት የነበረው ኮሎኔል ሮቢንሰን ከኢትዮጵያ ጎን ቆሞ ፋሺስት ጣሊያንን ለመዋጋት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚዘምት አስታወቀ።

  አጭር ታሪካዊ ምልሰት (Flashback)

  ጣሊያን በ1888 በአምባ ላጀ፥ በመቐለና በዓድዋ ጦርነቶች በተከታታይ (በሃትሪክ) ከተሸነፈች በኋላ ለ40 ዓመታት ከፍተኛ ዝግጅት አድርጋ... የምድርና የሰማይ ዘመናዊ መሳሪያዎች ታጥቃ ኢትዮጵያን ለመበቀል ስትመጣ በተቃራኒው ሃገራችን በዓድዋው ጦርነት ከነበራት ወታደራዊ ቁመና ብዙ ርቀት አልሄደችም ነበር። (የጣሊያን አውሮፕላኖች ለብቀላ ዓድዋ ከተማን ሲደበድቡ ኢትዮጵያዊያን ከአውሮፕላኖቹ ጋር ለመዋጋት ጎራዴ መምዘዛቸውን ኮሎኔል ሮቢንሰን መስክሯል)

  ኮ/ል ሮቢንሰን በኢትዮጵያ

  ሃገራችን ለጣሊያን ዘመናዊው ብቀላ ፍጹም ባልተዘጋጀችበት ወቅት አሜሪካዊው የጦር አውሮፕላን ፓይለት ኮ/ል ሮቢንሰን የኢትዮጵያ አየር ሃይልን ለመቀላቀል በጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሳወቀ አጼ ሃይለ ስላሴ ሰምተው የግብዣ ደብዳቤ ላኩለትና ኢትዮጵያ ገባ። 
  የሮቢንሰን መቀላቀልም ለአየር ሃይላችን ከፍተኛ የሞራል መነቃቃተን ፈጠረ። ሮቢንሰን አየር ሃይላችንን ከማደራጀት እስከ መዋጋት ድረስ አኩሪ ታሪኮችን አስመዝግቧል። የኢትዮጵያ ጀብዱም በአሜሪካ ሚዲያዎች ይዘገብለት ነበር። በዘገባ ብቻም አላበቃም የኮ/ል ሮቢንሰን የኢትዮ - ጣሊያን ውጊያ ተሳትፎና ጀግንነት አሜሪካ በጥቁር አሜሪካዊያን ፓይለቶች ላይ የነበራትን የዘረኝነት ማዕቀብ እንድታነሳም ምክንያት ሆኗል። በመሆኑም ራሱ ኮ/ል ሮቢንሰን በመሰረተው Tuskegee Institute የሰለጠኑትና The Tuskegee Airmen በመባል የሚታወቁት ጥቁር ፓይለቶች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ላይ አስደናቂ የጀግንነት ታሪክ ሊያስመዘግቡ ችለዋል። ታሪካቸውም እንደ Red Tails ለመሳሰሉ ታሪካዊ ፊልሞች መነሻ ሆኗል። 
  አሜሪካኖቹም ሆኑ እኛ ብዙ ያልዘመርንለት ኮ/ል ሮቢንሰን ከኢትዮ - ጣሊያን ጦርነት በኋላም በኢትዮጵያ አየር ሃይልና በኢትዮጵያ አየር መንገድ አገልግሏል። 
  የማብረር ነጻነቱን በማጎናጸፍ ለሌሎች መሰል ወንድሞቹም የነጻነት ምክንያት እንዲሆን ላደረገችው... ኢትዮጵያ የነበረው ፍቅርም እስከ መቃብር ሆነ። የሚያሳዝነው ግን የቀበርነው አስክሬኑን ብቻ ሳይሆን ታሪኩም ጭምር ነበርና ገና አሁን ታሪኩም፥ የመቃብር ስፍራውም ተቆፍሮ እየወጣ ይገኛል። 
  ሰዓሊና ቀራጺ ናይጀል ቢንስ ለኮ/ል ጆን ሲ ሮቢንሰን መታሰቢያ የሰራው ሃውልት ከጥቂት ቀናት በኋላ ኢትዮጵያ ይደርሳል።

 • loader Loading content ...
 • @Befkadu Getachew   2 years ago
  Sewasewer
  ሼህ   ሁሴን   ጅብሪል   1811- 1908  እንደኖሩ   ጥላሁን   ብርሃነ   ሥላሴ   ቤተ  (1996  vii)

  በመጽሐፋቸው ጠቅሰዋል። ስለ ሸህ ሁሴን ጅብሪል የሕይወት ታሪክ በስፋት የጻፈ ቦጋለ
  ተፈሪ በዙ ነው:: አቶ ቦጋለ ተፈሪ  ሼህ ሁሴን ጅብሪል ከአባታቸው ከሼህ ጅብሪል በወሎ
  ክፍለ ሀገር በወረሄመኖ አውራጃ፣ በባዙራ ምክትል በባሆች ቀበሌ፣ ልዩ ስሙ እምበለ ሴዳ
  ተብሎ በሚጠራ ቦታ 1811 ገደማ ተወልደው 97 ዓመታቸው አንዳረፉ ጽፈዋል::
  አባታቸው በዘመኑ በቃሉ አውራጃ ታዋቂ ለነበሩት ለገታው ሼህ ቡሽራ አድረው ለሰላሣ
  ዓመታት በመውሪድነት አገልግለዋል:: (1985 21) ጌታው ሼህ ሁሴን መፍረ የጀመሩት ገና
  በሰባት ዓመታቸው እንደሆነና የሚናገሩትም መሬት ጠብ እንደማይል ተጽፏል:: አሐዱ
  ወይም ቢስሚላሂ ብለው ፍርድ የጀመሩት በአጼ ዮሐንስና በመምሬ ግርማ በተባሉ ቄስ ነው
  ይባላል። እየታወቁ ሲመጡ ወደፊት የሚሆነውንና የሚመጣውን ከነመፍትሔው
  መናገራቸውና መተንበያቸው ነበር:: የሚናገሩትም በግጥም ነበር። ከዚያ ነገሥታቱም፣
  መሳፍንቱም፣ ትንሹም ትልቁም እሳቸውን መጀን ማሌት ያዘ። (1985 24)
  ግጥሞቻቸውን ከእረኛ እስከ ቃዲ ያውቀዋል፣ይለዋል:: ሼህ ሁሴን የነቢዩ መሐመድ
  ተከታይ ነበሩ:: ቢሆኑም እንደ እስላሞች ጫት አይቅሙም፣ ሶላት አያደርሱም፣ መስገጃ
  ቁርበት፣ ውኃ መያዛ ጦሌ አያንጠለጥሉም:: እንደ ዓባይ ጠንቋይም መጽሐፍ አይገልጡም፣
  ጠጠር አይጥሉም:: ግን ሱረት (ሐቀኑርያሸታሉ፣ ብርዝ ይጠጣሉ፣ ፍርድም ሲፈርዱ
  ማለት የሚታያቸውን ሲናገሩ ብርዝ በፎሌ (በሽክናይዘው ነበር ይባላል:: (1985 25)
  በሕይወት ዘመናቸው በጊዜው ታዋቂ ከነበሩት ባለዐቢ ከጥቅሳው ሼህ፣ ወልይና አሊም ጋር
  ተጣልተውና ተቃቅረው እንደነበር፣ ወዲያውም በጠና ታመው እንደነበር አቶ ቦጋለ
  ጠቅሰዋል። ( 25) ከጥቅሳው ሼህ ጋር ጠባቸው ይፋ ከሆነ ጀምሮ በሽታቸው ጠናባቸው፣
  እናም የሚከተለውን ግጥም አዜሙ ይባላል፣

  በጎጃም፣ በትግሬ፣ በሸዋ፣ በጎደር ሳገሳ ሳገሳ
  ስብርብር አረገኝ የጥቅሳ አንበሳ።

   

  እስኪ እነዚህን ግጥሞች ያንብቡና  ጉድ  ይበሉ:

  1.

  አንድ ዓመት ሲቀረው ምኒልክ ሊነግሥ
  አላህ መተማ ላይ ይስላል መቀስ
  በደም አጨማልቃ የምትቆራርስ
  እራስ የምትቆርጥ ያውም የንጉሥ
  አንደዜ ተመታች የማታላውስ::

  2.

  የምኒልክ ዘር አልቆ መነን ትቀራለች
  ተፈሪን አግብታ ዱቄት ትወልዳለች
  ልጆቿም ያልቃሉ እሷም ጉድ ታያለች
  የባሏን መከራ ሳታይ ትሞታለች
  ሐበሻ የዚያን ቀን ትነፋፍሳለች

  3.

  ተፈሪን አውርደው ተፈሪ ከገዛ
  ለትንሽ ቀን እንጂ እጅግም አይገዛ
  ለዕለት ተጠንቀቀው አይምሰልህ ዋዛ
  በጉልበት ካልሆነ በፍቅርም አይገዛ
  ኋላ ግን ሟች ናቸው ነገሩ ከበዛ::

  4.

  በአሥመራ ወያኔ ከመጣ ችግር
  መጀመሪያ አሥመራ ትሆናለች ቀብር
  አክሱም ትጠፋለች በአንድ ቀን ጀንበር
  ግሼን ላሊበላ ትሆናለች ቀብር
  ሁሉም ይሸፍታል ሴት እናኳን ሳይቀር:: (LoL)

  5.

  አሥመራ ልትጠፋ ገመዱ ሲላላ
  በሸዋ ከተማ ይኸለቃል በላ
  በሦስት ቀን ይያዛል ጎንደር ላሊበላ
  አክሱም የዚያን ጊዜ ትሆናለች ሌላ
  ማርያም ትጠፋለች አያዋጣም ብላ:: ( Really Funny)

  የሼህ ሁሴን ጅብሪል ትንቢታዊ ግጥሞችን https://zelalemkibret.files.wordpress.com/2011/03/gelaye4.pdf ላይ በመጫን ሙሉውን ማንበብ ይችላሉ ፡፡

  አቦ አላህ ይባርካቸው 

 • loader Loading content ...
 • @Befkadu Getachew   2 years ago
  Sewasewer

  የመጀመሪያው አውሮፕላን በ1921 ዓ.ም. አዲስ አበባ መድረስ ለኢትዮጵያውን ከውጭው ዓለም ጋር ለመገናኘት አዲስ ምዕራፍ የተከፈተበት ቀን ነበር፡፡ ለፈረንሳዮቹ ደግሞ በኢትዮጵያ አቪዬሽን ታሪክ ከሌሎች አገሮች በተለይ ዝግጅቱን አጠናቆ ከነበረው ጀርመን መቅደማቸው አስፈንድቋቸዋል፡፡ ለአብዛኛው ኢትዮጵያ ግን የአውሮፕላን መምጣት ግርምትና ትዕንግርት ፈጥሮበታል፡፡
  ‹‹ከቶ ምን አሳየኝ ይሠሩትን ያጡ
  ጠንቀቅ በል ጌታዬ ወደ አንተም ጋር መጡ›› ብሎ እስኪዘምር ድረስ፡፡ 
  መንገድ ሳይሠራለት፣ ሐዲድ ሳይነጠፍለት በአየር ላይ ተንሳፎ የመጣው ያን አውሮፕላን የአየር ባቡር የሚል ስም ወጣለት፡፡ በዚህ ሁኔታ ነበር የዛሬ 87 ዓመት በኢትዮጵያ የአቪዬሽን ታሪክ የተጀመረው፡፡ በኢትዮጵያ አቨየሽን የተጀመረው ንጉስ ተፈሪ በገዟቸው 3 ፈረንሳይ ስሪት ፖቴዝ አውሮፕላኖች ነው፡፡ አንደኛዋን ፈረንሳዊው ሙሴ አንድሬ ማዬ ከጅቡቲ በማብረር ነሀሴ 12 ቀን 1921 ዓ.ም “ስጋ ሜዳ” አውሮፕላን ማረፊያ ከቀኑ 7 ሰዓት ከ 10 ደቂቃ ላይ ባሳረፈበት ወቅት ነው፡፡ አውሮፕላኗም “ንስረ ተፈሪ” ተብላ ተሰየመች፡፡ ጅቡቲ ቀርተው የነበሩትን ሁለቱን ፖቴዝ አውሮፕላኖች አንዷን ካፕቴን ማዬ ፣ ሁለተኛዋን ደግሞ ጀርመናዊው ካውንት ሼዝበርግ እያበረሩ መስከረም 12 ቀን 1922 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ አመጧቸው፡፡ እነዚህ አይሮፕላኖች ከመጡ በኋላ “ንስረ አስፋወሰን” እና “ንስረ መኮንን” የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ ከዚያም የፈረንሳይ ተፎካካሪ የነበረው የጀርመኑ ጀንከርስ (Junkers) አውሮፕላን በባሮን ሻን ኢግል አብራሪነት በከተማዋ ውስጥ ጃን ሜዳ አረፈ፡፡ በጃንሜዳ ውስጥ በማረፉ ከፈረንሳዩ አውሮፕላን የበለጠ በርካታ ተመልካች እንዲኖር አድርጐታል፡፡
  የመጀመሪያ የአገር ውስጥ በረራ ጀንከርስ አውሮፕላን አዲስ አበባ ከደረሰ አንድ ወር በኋላ ነበር የአገር ውስጥ በረራውን የጀመረው፡፡ ያ ጉዞው የመጀመሪያው የአገር ውስጥ በረራ መሆኑ ነው፡፡ ያልተሳካው የመጀመሪያው በረራ ሊባልም ይችላል፡፡ ጀንከርስ የመጀመሪያ የአገር ውስጥ በረራው ወደ ጐን ሲሆን ተልዕኮውም የኢሊባቡር ጠቅላይ ገዥ የነበሩትን ራስ ናደውን ለማምጣት ነበር፡፡ ይህም አውሮፕላን በኢትዮጵያ በሽተኛ ለማጓጓዝ ሲበር የመጀመሪያው መሆኑ ነው፡፡ ራስ ናደው በጽኑ ታመው ነበርና የሚተኙበትን አልጋና ፍራሽ ጨምሮ ወደ ዋና ከተማቸው ጐሬ በረራውን ቀጠለ፡፡ ነገር ግን በአየር ሁኔታው አመቺ አለመሆን ምክንያት ተመልሶ እንድብር አካባቢ ለማረፍ ተገደደ፡፡ በማግስቱም ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ፡፡
  በኢትዮጵያ በ1922ዓ.ም በጅግጅጋ ከተማ የመጀመሪያው የአውሮፕላን በረራ ት/ቤት በፈረንሳዊው ሙሴ ጋስቶን ቨርዲየር መምህርነት ተቋቋመ፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያውን የአውሮፕላን በረራ ስልጠና የወሰዱት ኢትዮጵያውያን፡-

  1. አስፋው አሊ
  2. ሚሽካ ባቢችፍ /በአባት ሩሲያዊ በእናት ኢትዮጵያዊ/
  3. ስዩም ከበደ
  4. ባህሩ ካባ
  5. ደምሴ ኃይለኢየሱስ
  6. ደመቀ ተክለወልድ
  7. ወ/ሮ ሙሉመቤት እምሩ ናቸው፡፡

  አስፋው አሊ እና ሚሽካ ባቢችፍ በመጀመሪያ ስልጠናቸውን በማጠናቀቅ ጥቅምት 3 ቀን 1923ዓ.ም ከንጉሰ ነገስቱ እጅ የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል፡፡ ት/ቤቱም ስራውን የጀመረው በሁለት አውሮፕላኖች ነበር፡፡ በኢትዮጵያ አቭዬሽን ታሪክ የመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያውያን አውሮፕላን አብራሪዎች አስፋው አሊ እና ሚሽካ ባቢችፍ ናቸው፡፡ ሁለቱም የብቻ በረራቸውን ያካሄዱት በ1923ዓ.ም ነበር፡፡
  እ.ኤ.አ በ1935 የታተመው የአሜሪካ ጋዜጣ ስናፒ ላንዲንግ ሌዲ በርድ የሚል አድናቆት የሰጣቸው ወ/ሮ ሙሉመቤት እምሩ የመጀመሪያዋ የሴት አውሮፕላን አብራሪ ናቸው፡፡ የመጀመሪያውን የብቻ በረራ ያካሄዱት በ1927ዓ.ም ነበር፡፡ ወ/ሮ ሙሉመቤት እምሩን አውሮፕላን መንዳት በማስተማር ታሪክ የመጀመሪያይቱ አፍሪካዊትም እንዲሆኑ ያስቻሏቸው ኮለኔል ጄ.ሲ.ሮ.ቢንሰን የተባሉ ጥቁር አሜሪካዊ ናቸው፡፡
  ከ ኢትዮጵያ ኤኒቲንግ ዶት ኮም የተወሰደ

 • loader Loading content ...
 • @Befkadu Getachew   2 years ago
  Sewasewer

  ሐረ ሸይጣን ከአዲስ አበባ ወደ ደቡባዊው ኢትዮጵያ ክፍል ፻፵፫ ኪሎ ሜትር ከተጓዙ በኋላ የሚያገኙት ሐይቅ ሐረ ሸይጣን ይባላል፡፡ የሚገኘውም በደቡብ ክልል ስልጤ ዞን ርእሰ ከተማ ወራቤ በስተሰሜን አቅጣጫ ፴ ኪሎ ሜትር ተጉዘውም ያገኙታል፡፡ ሐይቁ ከኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ የቱሪስት መስህቦች አንዱ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ የሐይቁ ይዘት አስገራሚ ሁኔታዎች አሉበት፡- ሐይቁ የሚገኘው ከመሬት ንጣፍ በታች ሲሆን፣ የተለያዩ ተፈጥሯዊ ሀብቶችና ገጽታዎች እንዲሁም ክስተቶችን የያዘ ሐይቅ ነው፡፡ በመሆኑም የገበቴ ቅርጽ ያለውን ሐይቅ ከጉድጓዱ አፋፍ አንስቶ ቁልቁል ውኃው እስካለበት ለመድረስ በአማካይ የ ፪፻፷ ሜትር ርቀት ጉዞ ይጠይቃል፡፡ በሌላ አገላለጽ ከአፋፉ እስከ ውኃው ያለው አምዳዊ (Vertical) ርቀት አማካይ ከፍታ ፻፱ ሜትር ነው፡፡ ከዳገቱ አፋፍ በመነሳት ድንጋይ ወርውሮ ለማስገባት ፪፻፴፯ ሜትር የጎንዮሽ (Horizontally) የመወርወር አቅምን ይጠይቃል ማለት ነው፡፡ የሐረ ሸይጣን ሐይቅ የውኃ ቀለም ወቅትን ጠብቆ የሚለያይ ሲሆን፣ የአካባቢው ኅብረተሰብ (በተለይም የቀድሞው) የተለያዩ ትርጓሜዎችን ይሰጡት ነበር፡፡ ነገር ግን ከሰገላዊ እይታ፣ ከሐይቁ አፈጣጠርና ይዘት ጋር ሲታይ የውኃው መልክ የሚቀያየረው ከአካባቢው ነጸብራቅ (Reflection) ነው፡፡

  የሐረ ሸይጣን ሐይቅ አፈጣጠር ከተፈጥሮ ውስጣዊ ኃይል አንዱ በሆነው የእሳተ ገሞራ ነው፡፡ የሐረ ሸይጣን ሐይቅ ከመሬት ገጽታ በታች መገኘት፣ የገበቴ ቅርጽ ያለው መሆኑ፣ በአካባቢው የሚገኙ ሌሎች መልክዓ ምድራዊ ገጽታዎች ወይም አነስተኛ ኮረብታዎች፣ ተፈጥሯዊ ዋሻዎቸው፣ ፍል ውኃዎች፣ ሌሎች ሐይቆች፣ እሳተ ገሞራዎች በስምጥ ሸለቆ ሰንሰለት ውስጥ የሚገኝ መሆኑና በአካባቢው የሚገኙ ድንጋዮች እና አፈሮች ጋር በተያያዘ ስንመለከተው ሐይቁ የተፈጠረው በአንድ ወቅት በነበረ የእሳተ ገሞራ ውጤት መሆኑን መገመት ይቻላል፡፡ ስለሆነም በሰገላዊ አጠራሩ ክሬተር ሌክ (Crator Lake) ይባላል፡፡ ኅብረተሰቡ በአፈታሪክ እንደሚለው ሐይቁ የተፈጠረው ኑር ሁሴን ከሚባሉ የሃይማኖት አባት (ወለይ) ጋር በተያያዘ ሁኔታ ነው፡፡ ቦታው በሜዳ ላይ የሰፈረ ከተማ እንደነበረና በከተማው የነበሩ ሰዎች እንግድነታቸውን ስላልተቀበሏቸው በመራገማቸው ከተማው ሙሉ በሙሉ እንደሰመጠና በቦታው ትንሽ ውኃ በመፈጠሩ ይህ ውኃ ቀስ በቀስ እየሰፋ ሄዶ ያሁኑን ሐረ ሸይጣን እንደፈጠረ በአፈታሪክ ይነገራል፡፡

  የሐይቁ ስያሜ አመጣጥም ከቦታው ምትሃታዊ ክስተቶች ጋር የሚያያይዙት አሉ፡፡ "ሐረ ሸይጣን" ቃሉ የኦሮምኛ እንደሆነና ትርጉሙም የሰይጣኖች እናት ማለት /አውራ/ ነው ሲሉ በሌላ በኩልም "ሐር-አሽ-እጣን" ከሚለው የስልጥኛ ቃል የተወሰደ ሆኖ ትርጉሙም "እጣን አቀጣጥል/አጭስ" ማለት ነው ይላሉ፡

 • loader Loading content ...
 • @Befkadu Getachew   2 years ago
  Sewasewer

  በአገሪቱ ዘመናዊ ትምህርት በ19ኛው መቶ ዘመን በነገሡት በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን በአሁን ዘመን ዳግማዊ ምኒልክ ተብሎ የሚጠራውና ዘመናት የተሻገረው ተቋም መቋቋሙ ይወሳል፡፡ እንደ ፕሮፌሰር ጆን ማርካኪስ አገላለጽ ‹‹… ምኒልክ ዘመናዊ ትምህርት ቤትን በመክፈት በኢትዮጵያ ውስጥ ዘመናዊ የትምህርት ዘር የዘሩ ናቸው፡፡ … ትምህርት ቤቱም የተሠራው ንጉሠ ነገሥቱ በሰጡት የግል ገንዘብ ነው፡፡ …››፡፡ በፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ የዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ድርሳን አገላለጽም፣ የመደበኛ ትምህርት በኢትዮጵያ ለመስፋፋት እንደ አንድ ዐቢይ ክስተት የሚቆጠረው ድርጊት በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን የተከናወነው በንጉሠ ነገሥቱ ስም የሚታወቀው ትምህርት ቤት በ1900 ዓ.ም. መከፈቱ ነው፡፡ ‹‹የ ዘመናዊ ትምህርት›› ፍላጎት እያደገ መምጣት የጀመረው በ19ኛው መቶ ዓመት መሆኑን ከዓድዋ ድል በኋላ ኢትዮጵያ ከአውሮፓና ከአውሮፓውያን ጋር ያላት ግንኙነት እየተጠናከረ ሲሄድ ዘመናዊ ትምህርት ለማስፋፋት አመቺ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን የታሪኩ ድርሳን ያመለክታል፡፡
  ይሁን እንጂ ነባሩ የኢትዮጵያ ትምህርት ሥርዓት የሚጀምረው ግን በዘመነ አክሱም ከአራተኛው መቶ ዘመን ጀምሮ መሆኑም ይገለጻል፡፡ የተለያዩ ጸሐፍትና የሥነ ትምህርት ምሁራን ነባሩን የትምህርት ሥርዓት ባህላዊ የትምህርት ሥርዓት፣ የቤተክህነት ትምህርት ቢሉትም ደስታ በርሀ ስብሐቱ በአንድ ጥናታቸው እንዳመለከቱት፣ ነባሩ የትምህርት ሥርዓት ‹‹የኢትዮጵያ ትምህርት ሥርዓት›› መባል አለበት ይላሉ፡፡›› ለዚህም ማገናዘቢያቸው እስከ 20ኛው መቶ ዓመት መባቻ ድረስ የኢትዮጵያ ትምህርት በተማከለ ወይም ባልተማከለ መልኩ በተለያዩ አካላትና ተቋማት አስተዳደርና ሥር መከናወኑ ነው፡፡ በ19ኛው መቶ ዓመት መገባደጃ ከዘመናዊነት ጋር የተያያዙ ባቡር፣ ሆስፒታል፣ ባንክ፣ መኪና ወዘተ. በኢትዮጵያ መከሰትን ተከትሎ ከውጭ አገሮች ጋር ከተፈጠረው ግንኙነት አኳያ ዘመነ ምኒልክ ብዙ ትሩፋቶችን አስገኝቷል፡፡ ከእነዚህም መካከል በአዲስ አበባ ከተማ ዘመናዊ ትምህርት ቤት መከፈቱ አንዱ ተጠቃሽ ነው፡፡ አራት ኪሎ እሪበከንቱ አፋፍ ላይ በአሁን ጊዜ በኮንዶሚኒየሞች መካከል ተሰንጎ በሚገኘው የቀድሞው የንጉሠ ነገሥቱ አማካሪ የሙሴ ኤልግ መኖርያ ቤት በነበረው ትምህርት ቤቱ መከፈቱ ይታወቃል፡፡ የትምህርት ዓይነቱም አማርኛ፣ ግእዝ፣ ፈረንሳይኛ፣ ዓረቢኛ፣ ጣሊያንኛ፣ ሒሳብ፣ ሳይንስና ስፖርትን የያዘ ነበር፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ልጁን የማያስተምር ወላጅ ሀብቱ እንደሚወረስ እስከ ማወጅ የደረሱት የመማር ፍላጎት ውስን በመሆኑ መኳንንቱ ወጣት ልጆችን እንዲያስተምሩ ማዘዛቸውም ሰነዶች ያሳያሉ፡፡
  108 ዓመታት ያስቆጠረውን ይህን ታሪካዊ አጋጣሚ ነው ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት ጅማሪ አንድ ማዕዘን ሆኖ እየተወሳ እየተጻፈ የሚገኘው፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ዘመናዊ ትምህርት የበቀለው ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ከመቋቋሙ ከስድሳ ሦስት ዓመት በፊት ከአዲስ አበባ 903 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ዓዲግራት ከተማ (ትግራይ) አካባቢ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አማካይነት መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉት አቶ ሙሉ ወርቅ ኪዳነማርያም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዘመናዊ ትምህርት ቤት የተከፈተው ታኅሣሥ 1 ቀን 1837 ዓ.ም. ዓዲግራት ከተማ ዳርቻ በሚገኝ ጎልዓ መሆኑን ትምህርት ቤቱንና ዓሊቴናን በሚመለከት የተዘጋጁ ሰነዶችን በማጣቀስ ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ አምስት መምህራን የያዘውና በፋዘር ቢያንቸሪ በሚመራው የጎልዓ ትምህርት ቤት ሥራውን የጀመረው በ13 ወንድ ተማሪዎች ነበር፡፡ ይሰጥ የነበረው የትምህርት ዓይነትም ግእዝ፣ አማርኛ፣ ላቲን፣ ቲኦሎጂና ሥነ ቅርፅ ሲሆን፣ የማስተማሪያ ቋንቋው በአብዛኛው አማርኛ እንደነበረ የቀድሞው የፅንሰታ ትምህርት ቤት ምክትል ዳይሬክተርና መምህር የአሁኑ የዓሊቴና ቅድስት ማርያም ካቶሊካዊ ገዳም አስተዳዳሪው አባ ኃይለ ሓጎስ ያደረጉት ጥናት ያሳያል፡፡ በዓድዋ ጦርነት (1888 ዓ.ም.) ዋዜማ ወራሪው የኢጣሊያ ሠራዊት ዓዲግራትን በመያዙና ከተለያዩ የአውሮፓ አገሮች የመጡት ካህናት በመባረራቸው ትምህርት ቤቱ በ1887 ዓ.ም. ከተዘጋ በኋላ ተመልሶ የተከፈተው ሦስት ዓመት ቆይቶ ነበረ፡፡ የትምህርት ዓይነቶቹም ከቀደሙት ጋር ቢመሳሰልም የፈረንሣይኛ ቋንቋን ግን አክሏል፡፡ የተማሪዎች ቁጥርም 32 ደርሷል፡፡
 • loader Loading content ...
 • @Befkadu Getachew   2 years ago
  Sewasewer
  አብዲሳ አጋ በ1928 ዓ/ም የጣልያን ወረራ ወቅት ተማርኮ ወደ ጣልያን ከተወሰደ በኋላ ብርድ ልብሱን ቀዳዶ በመቀጣጠል በመስኮት አምልጦ በርካታ ጀግንነቶችን የፈጸመ የኢትዮጵያ ወታደር ነው። ኮሎኔል አብዲሳ አጋ የተወለደው በ1912 ዓ.ም ፣ ወለጋ ነበር።
  በ12 ዓመቱ አባቱ በንዴት ወንድማቸውን በመግደላቸው ሲታሰሩ አብዲሳ አባቱን ለማስፈታት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ቢያደርግም ሳይሳካ በሞት ተቀጥተዋል። በኋላም በ14 ዓመቱ የኢትዮጵያን ጦር በመቀላቀል ሀገሩን ማገልገሉን ሀ ብሎ ጀመረ። አብዲሳ ጦሩን ከተቀላቀለ ከሁለት አመት በኋላ የአድዋን ሽንፈት ለመበቀል የዛተው ፋሺስት ሙሶሎኒ በድጋሚ ኢትዮጵያን ሲወር ሀገሩን ለመከላከል በ16 ዓመቱ ወ ራሪውን ጦር መዋጋት ጀመረ።
  ውጊያ ላይ ባጋጠመው የመቁሰል አደጋ ህክምና ላይ ከቆየ በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ ፒያሳ አካባቢ በሚገኝ ቤት በቁም እስር ላይ ነበር። በኋላ ጣልያን ኢትዮጲያን እንዲያስተዳድር በሾመችው ግራዚያኒ ላይ የመግደል ሙከራ ከተደረገ በኋላ አብዲሳ አጋ እና ሌሎች 37 የሚሆኑ የቁም እስረኞች ተጠርጣሪ ተብለው በከባድ ስቃይ እስር ቤት ከቆዩ በኋላ በወቅቱ የጣልያን ግዛት በነበረችው በሶማሊያ በኩል ወደ ጣልያን ተወስዶ በሲሲሊ ደሴት በሚገኝ እስር ቤት እስረኛ ተደረገ።
  አልሸነፍ ባይነት መለያው የሆነው አብዲሳ ሁሊዮ ከተባለ ዩጎዝላቪያዊ የጦር እስረኛ ጋር በመተባበር ከባድ ጥበቃ ከሚደረግበት እስር ቤት ለማምለጥ ማሰላሰል ጀመረ። ተሳክቶለት ቢያመልጥ እንግዳ አገር እንደሚጠብቀው ቢያውቅም በነጻነቱ የማይደራደረው አብዲሳ የተሰጠውን የብርድ-ልብስ ቀዳዶ በመቀጣጠል በመስኮት በኩል አመለጠ።
  ከዛ በኋላ ግን ሽሽት አልነበረም የጀመረው አብዲሳ። ከጥቂት ቀናት በኋላ በማታ ወደ እስር ቤቱ በመመለስ ጠባቂዎቹ ላይ ጥቃት በመፈጸም እስረኞቹን በመሉ ነጻ ማውጣት ችሎ ነበር። ያመለጡት እስረኞች ከእስር ቤቱ ጠባቂዎች በወሰዱት መሳሪያ በመታገዝ የአማጽያን ጦር ያደራጁ ሲሆን ጦሩን እንዲመራም የመረጡት ጀግናውን አብዲሳን ነበር። ከዛም የተለያዩ የጣልያን ወታደራዊ ሠፈራዎች ላይ ጥቃት በመፈጸም ወራሪዎቹ ጣልያኖች ኢትዮጵያ ውስጥ ከነበረው የአርበኛ እንቅስቃሴ ያልተናነሰ ጥቃት በሀገራቸው ያጋጥማቸው ጀመር።
  በአብዲሳ ጦር እጅግ የተረበሹት ጣልያኖችም በርካታ ስጦታዎችን ቃል በመግባት ውጊያውን እንዲያቆም እና የነሱን ጦር እንዲቀላቀል ለምነውት ነበር። አብዲሳ ግን ከፋሺስት ሥርዓት ጎን እንደማይቆም በማስረገጥ ጥያቄውን ውድቅ አደርጎ ጣልያኖችን በሀገራቸው ማስጨነቅ ቀጠለ።
  በወቅቱ እየተጋጋለ የመጣው የጀርመን ናዚ ሥርዓት ሁለተኛው የዓለም ጦርነትን ሲጀምር ፋሺስት ሙሶሎኒ ከጀርመኖች ጋር ሲያብር እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና አሜሪካን ጨምሮ በርካታ የምዕራብ አገሮች የሕብረት ጦር መስርተው የሙሶሎኒን ጦር መውጋት ጀምረው ነበር።
  በወቅቱ ይህ የሕብረት ጦር የአብዲሳን ዝና በመስማታቸው ጣልያንን ለማዳከም ለአብዲሳ ጦር የቁሳቁስ ድጋፎች ማድረግ ጀመሩ። በድጋፉ በመጠናከር ፋሺስቱን ሰራዊት ማርበድበድ የቀጠለው አብዲሳ የጣልያን ጦር ተሸንፎ ዋና ከተማዋሮም በአሜሪካን እና እንግሊዝ የሚመራ ጦር እጅ ስር ከወደቀች በኋላ የሚመራቸውን ከተለያዩ አገር የወጡ ወታደሮች በሙሉ ክንዳቸው ላይ የኢትዮጲያን ባንዲራ እንዲያስሩ በማድረግ የሃገሩን ባንዲራ እያውለበለበ ሮም ከተማ ሲገባ በአለም አቀፉ ህብረት ጦር ትልቅ አቀባበል ተደርጎለት ነበር።
  ከዛም በኋላ ከተጨማሪ ወታደሮች ጋር በአለም አቀፉ ህብረት ስር የሚመራ ጦር መሪ በመሆን ጀርመንን ለማሸነፍ በሚደረገው የመጨረሻ ውጊያ ላይ ተሳትፎ ግዳጁን በሚገባ በመወጣት የኢትዮጲያን ባንዲራ ከእጁ ሳይለይ በርካታ የጀርመን ከተሞችን ነጻ ማውጣት ችሎ ነበር። ከጦርነቱ መገባደድ በኋላም የእንግሊዝ፣ የካናዳ እና የአሜሪካ መንግሥታት ጦራቸውን ተቀላቅሎ እንዲቀጥል በርካታ ጥቅማ ጥቅሞችን አቅርበውለት ነበር። አብዲሳ ግን ኢትዮጵያ ምንም ያህል ድሃ ብትሆንም ሕዝቡን እና መንግሥቱን ጥሎ እንደማይሄድ አስረግጦ በመናገር ጥያቄውን ሳይቀበል ቀረ።
  ተቀላቀለን የሚለውን ጥያቄ ውድቅ ማድረጉ ያልተዋጠላቸው አንዳንድ የሕብረት ጦሩ አባላት ሁለተኛ የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ በወንጀል ከሰው አብዲሳን እስር ቤት አስገብተውት ነበር። በኋላም እስሩ ወደ ገንዘብ ቅጣት ተቀይሮ ገንዘቡ ተከፍሎ አብዲሳ ለዓመታት ወደተለያት ሀገሩ በክብር ተመለሰ። ከዛም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በክብር ከተቀበሉት በኋላ በጊዜው የመከላከያ ሚኒስቴር ወደነበሩት ራስ አበበ አረጋይ መርተውት ነበር።
  ሚኒስቴሩ ውደመሩት ወደ ሆለታ ወታደራዊ ሠፈር የገባው አብዲሳ አነስ ባለ ወታደራዊ ቦታ የተወሰነ ጊዜ ከቆየ በኋላ ለጉብኝት የሚመጡ የውጭ ሀገር የጦር መሪዎች ስለ ዝናው ሲያወሩ የሰሙት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ወደ ቤተ መንግሥታቸው በማምጣት በኮሎኔልነት ማዕረግ የንጉሡ ጠባቂ ሆኖ አድርገው ሾሙት። እስከ ንጉሣዊ ሥርዓቱ መውደቅ ድረስ በቦታው ያገለገለው አብዲሳ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
 • loader Loading content ...
 • @Befkadu Getachew   2 years ago
  Sewasewer

  የተመስገን ገብሬን ግለ ታሪክ “ሕይወቴ” ን አንብቤ በመገረሜ እና በመደመሜ  የተመስገንን ታዋቂ ስራ “የጉለሌው ሰካራም”ን መለጠፍ አሰኘኝ:: እንዲህ ብሎ ይጀምራል ልብ-ወለዱ:-

  ‹‹ በጉለሌ የነበረው የታወቀ ዶሮ ነጋዴ ማነው ብለው ከገፈርሳ እስከ ደጃዝማች ይገዙ ሰፈር ለጠየቁ ሰዎች፤ ተበጀ ሰካራሙ ተበጀ ዶሮ ነጋዴው፤ ተበጀ ነው ብለው ይነግሯቸዋል፡፡

  የሕይወቱ ታሪክ ፍፁም ገድል ነው፡፡ ጢም ያለው ሽማግሌ ሰው ነው፡፡  ራሱን ጠጉር ውሃ ወይም መቀስ ነክቶት አያውቅም፡፡ ማለዳ አይናገርም፡፡ በጠርሙስ የከመረውን ከጠጣ በኋላ ሲራገም ወይም ሲሳደብ ሲፈክር ወይም ሲያቅራራ ድምጡ ከፈረንጅ ውሻ ድምጥ ይወፍራል፡፡ ቢያውቀውም ባያውቀውም ላገኝው ሁሉ ማታ ሰላምታ ይሰጣል፡፡ ቢያውቀውም ባያውቀውም ካገኝው ሁል ጋር ማታ ይስቃል፡፡ ቢውቀውም ባያውቀውም የሰላምታው አይነት እንደ ወታደር ወይም እንደ ሲቪል ቢሆን ለእርሱ እንደተመቸው ነው፡፡ ከሰላምታው ጋር ድምጥ ትሰማለችሁ፡፡ ከአፉ ከሚወጣው ከሚወጣው ግን አንድ ቃል መለየት አትችሉም፡፡›› …

  እያለ እያለ ይቀጥላል::

  ለማንኛውም፤ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው እና ፈር ቀዳጅ አጭር ልብ ወለድ (አስፋው ዳምጤ ፣ ዘሪሁን አስፋው…) የሆነውን  “የጉለሌው ሰካራምን” በብሎጋችን እነሆ ብለናል፡፡  https://zelalemkibret.files.wordpress.com/2012/03/yegulelew-sekaram.pdf  ላይ ጣ ያድርጉ:: ጣ ስላደረጉም “ምድርን እንደ ስጋጃ ሰማይን እንደ መጋረጃ” የዘረጋ አምላክ ውለታውን ይክፈልልኝ::

 • loader Loading content ...
 • @Befkadu Getachew   2 years ago
  Sewasewer

  እናንት ዳኞች የበየናችሁብኝን የሞት ፍርድ ያለ ይግባኝ ተቀብያለሁ፡፡ ይግባኝ ብየ ጉዳየን የሚመለከትልኝ የኢትዮጵያ ህዝብ ቢሆን ኖሮ ይግባኝ ማለት በፈለግሁ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ እንደማይሆን አውቃለውና በይግባኝ የአፄ ኃ/ስላሴን ፊት ማየት አልፈቅድም፡፡ በእግዚያብሄር ስም ተሰይማችሁ ከተቀመጣችሁበት የፍርድ ወንበር ላይ ከመቀመጣችሁ በፊት በእኔ ላይ የምትሰጡትን የዛሬውን ፍርድ ታውቁት እንደነበር ሳስብና ፍርድ እስከዚህ መርከሱን ስታዘብ ሀዘኔ ይበዛል፡፡

  ለኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት፣ ነፃነትና እርምጃ የተነሳሁ ወዳጅ ነኝ እንጅ ለማፋጀት የተነሳሁ ወንበዴ አይደለሁም፡፡ ይህንን ማድረግ ፈልጌ ቢሆን ኖሮ ማንም የማይወዳደረው ሰራዊትና መሳሪያ ሳላጣ ዛሬ እዚህ ከእናንተ ፊት ለመቆም ባልበቃሁ ነበር፡፡

  እኔ ከየአፄ ኃ/ስላሴ ድንክ ውሾች ያነሰ ደመወዝ የሚያገኙ ሁለት የተራቡ ወታደሮችን አጣልቼ ለማደባደብና አገር ለማፍረስ አለመምጣቴን የሚያረጋግጥልኝ እናንተ በትዕዛዝ ያገኛችሁትን ፍርድ ለመቀበል እዚህ መቆሜ ነው፡፡

  ከእኔ በፊት በግፍ የፈሰሰው ንፁህ የኢትዮጵያዊያን ደም ብዙ ነው፡፡ በየአፄ ኃ/ስላሴ ዘመነ መንግስት ግፍ ሽልማት በመሆኑ  እኔ ለመሞት የመጀመሪያው ሰው አልሆንም፡፡ ስልጣን አላፊ ነው፡፡ እናንተ ዛሬ ከጨበጣችሁት የበለጠ ስልጣን ነበረኝ፡፡ ሀብትም አላጣሁም፡፡ ነገር ግን ህዝብ የሚበደልበት ስልጣንና ድሃ የማይካፈለው ሀብት ስላልፈለግሁ ሁሉንም ንቄ ተነሳሁ፡፡

  አሁንም እሞታለሁ፡፡ ሰው ሞትን ይሸሻል ፡፡ እኔ ግን በደስታ ወደሞት እሄዳለሁ፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝብ ታላቅነት ቀድመውኝ መስዋዕት የሆኑትን አብረውኝ ተነስተው የነበሩትን ጀግኖች ወንድሞቼን ለመገናኝት ናፍቄአለሁ፡፡

  የጀመርኩት ስራ ቀላል አይደለም፡፡ አልተሸነፍኩም፡፡ ወገኔ የሆነው ድሃው የኢትዮጵያ ህዝብ የጀመርኩለትን ስራ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ፈፅሞ ራሱን በራሱ እንደሚጠቅም አልጠራጠርም፡፡ ከሁሉ በበለጠ የሚያስደስተኝ ለኢትዮጵያ ህዝብ ልሰራለት ካሰብኳቸው ስራዎች አንዱ የኢትዮጵያ ወታደር ዋጋና ክብር ከፍ ማድረግ ሲሆን ይህ ሃሳቤ ህይወቴ ከማለፉ በፊት ሲፈፀም ማየቴ ነው፡፡

  ዛሬ መኖራችሁን በማየቴ ነገ መሞታችሁን ረስታችሁ አሜን ብላችሁ ቀናችሁን በማስተላለፍ በመገደዳችሁ በእኔ ላይ ሳትፈርዱ በራሳችሁ ላይ የፈረዳችሁ መሆናችሁን አላስተዋላችሁም፡፡ እኔ የተነሳሁት ከትክክለኛ ህግና ከህሊናችሁ ውጭ ለመፍረድ እንዳትገደዱ ለማድረግ ነበር፡፡ በአጭሩ በእኔ ላይ ለመፍረድ የቸኮላችሁትን ያህል  አስር እና አስራ አምሰት ዓመት በቀጠሮ የምታጎላሉትን ህዝብ ጉዳይ እንደዚህ አፋጥናችሁ ብትመለከቱትና  ብትሸኙት ኖሮ የእኔ መነሳት ባላስፈለገም ነበር፡፡

  ከእናንተ ከዳኞቹና የሞት ፍርድ እንድትበይኑብኝ ካዘዛችሁ ሰው ይልቅ እኔ ፍርድ ተቀባይ የዛሬ ወንጀለኛ የነገ ባለታሪክ ነኝ፡፡ የኔ ከ ጓደኞቸ መካከል ለጊዜው በህይወት መቆየትና ለእናንተ ፍርድ መብቃት የመመዘኑን ፍርድ ለመጭው ትውልድ የሚያሳይ ይሆናል፡፡

  ዋ ! ዋ ! ዋ ! ለእናንተና ለገዢአችሁ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ  ሃሳቤ በዝርዝር ገብቶት በአንድነት በሚነሳበት ጊዜ የሚወርድባችሁ መዓት አሰቃቂ ይሆናል፡፡

  በተለይ የአፄ ኃ/ስላሴ የግፍ መንግስት ባላደራዎች ሆነው ድሀውን የኢትዮጵያ ህዝብ ሲገሸልጡት ከነበሩት መኮንን ሀ/ወልድና ገ/ወልድ እንግዳወርቅን ከመሳሰሉት በመንፈስ የታሰሩ በስጋ የኮሰሱ መዠገሮች መካከል ጥቂቶቹን ገለል ማድረጌን ሳስታውስና የተረፉትም  ፍፃሜያቸውን በሚበድሉት በኢትዮጵያ ህዝብ እጅ ላይ መውደቅ ሲሰማኝ ደስ ይለኛል፡፡

 • loader Loading content ...
 • @Befkadu Getachew   2 years ago
  Sewasewer

  በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ ሚኒስትሮች የተሾሙት በጥቅምት ፲፬ (14) ቀን ፲፱፻ (1900) ዓ/ም ነው። በዚያን ጊዜም በዳግማዊ አጤ ምኒልክ የተሾሙት የመጀመርያዎቹ ሰባት ሚኒስትሮች የሚከተለት ናቸው።
  ፩ኛ/ አፈንጉስ ነሲቡ መስቀሉ -- የዳኝነት ሚኒስትር
  ፪ኛ/ ፊታውራሪ ሃብተጊዮርጊስ -- የጦር ሚኒስትር
  ፫ኛ/ ፀሃፌ ትእዛዝ ገብረስላሴ ወልደአረጋይ -- የፅህፈት ሚኒስትር
  ፬ኛ/ በጅሮንድ ሙሉጌታ -- የገንዘብ እና የጏዳ ሚኒስትር
  ፭ኛ/ ሊቀ መኯስ ከተማ -- ያገር ግዛት ሚኒስትር
  ፮ኛ/ ነጋድራስ ሃይለጊዮርጊስ -- የንግድ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
  ፯ኛ/ ከንቲባ ወልደፃዲቅ ጎሹ -- የእርሻና የመስሪያ ሚኒስትር

  ዓጼ ምኒልክ እነኚህን ሚኒስትሮች እንደሾሙ በአዲስ አበባ ያሉ የውጭ አገር መንግስታት ተወካዮች ሹመቱን እንዲያውቁት የሚከተለውን ደብዳቤ ፃፉ።
  "... የዩሮፓን ስርዓት በአገራችን በኢትዮጵያ ካሰብን ብዙ ጊዜ ነው። እናንተም የሮፓ ስርዓት በኢትዮጵያ ቢለመድ መልካም ነው እያላችሁ ስታመለክቱኝ ነበር። አሁንም የእግዚአብሄር ፍቃዱ ሆኖ ለመፈፀም ቢያበቃኝ ሚኒስትሮች ለመሾም ዠምሬ አፈንጉስ ነሲቡን፣ ፊታውራሪ አብተጊዮርጊስን፣ ፀሃፌ ትእዛዝ ገብረስላሴን፣ በጅሮንድ ሙሉጌታን፣ ሊቀመኯስ ከተማን፣ ነጋድራስ ሃይለጊዮርጊስን፣ ከንቲባ ወልደፃዲቅን አድርጌአለሁና ይህንን እንድታውቁት ብዬ ነው።"
  ትቅምት ፲፬ (14) ቀን ፲፱፻ (1900) አመተ ምህረት አዲስ አበባ ተፃፈ። 

  ምንጭ: አጤ ምኒልክ በጳውሎስ ኞኞ
 • loader Loading content ...
  Load more...
loader Loading content ...

Comments (0)


  This user has no comment yet.