loader

Topics (548)


loader Loading content ...

Explanations (548)


 • @በህግ አምላክ   3 months ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!

  የ፲፱፻፶፬ ዓ.ም የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ፥ የአጥቢያ ዳኞች በአጭር ሥነ ሥዐዓት የሚያዩት ዳኝነት ፥ ስምንተኛ መጽሐፍ ፥ የአጥቢያ ዳኞች በአጭር ሥነ ሥዐዓት የሚያዩት ዳኝነት።


  ቁጥር ፪፻፳፫። ዳኝነቱ።
  (፩) የአጥቢያ ዳኛ በሥልጣኑ ውስጥ በሚገኘው ስፍራ ንኡሳን ወንጀሎች የሆኑትን የስድብን፤ የእጅ እልፊትን፤ በሰው ንብረት ላይ የሚደረግ ጉዳትን ወይም የንብረቱ ዋጋ ከአምስት ብር በላይ የማይሆን ስርቆትን ነገሩ በዕርቅ እንዲያልቅ የተቻለውን ያደርጋል።
  (፪) የአጥቢያው ዳኛ ነገሩን በዕርቅ ለመጨረስ ያልቻለ እንደ ሆነ፤ ከሁለት እማኞች ጋር ተቀምጦ እነዚህን ንኡሳን ወንጀሎችን አከራክሮ ውሳኔ ለመስጠት ይችላል። ከዐሥራ አምስት ብር በላይ ቅጣት መወሰን አይችልም። እማኞቹና የአጥቢያ ዳኛው በሚሰጠው ውሳኔ ባንድ ቃል ካልተስማሙ የአጥቢያው ዳኛው ውሳኔ የጸና ይሆናል።
  (፫) የአጥቢያው ዳኛ በፍርድ መዝገብ ከዚህ በታች የተመለከቱት እንዲጻፉ ያደርጋል።
  (ሀ) የከሳሹ ስም፤
  (ለ) ክስ የቀረበበት ወንጀል፤
  (ሐ) ማስረጃው ባጭሩ፤
  (መ) እማኞች የሰጡት አስተያየት፤
  (ሠ) ተከሳሹ የተፈረደበት እንደ ሆነ፤ የተወሰነበት ቅጣት እንዲባል።

  ቁጥር ፪፻፳፬። ይግባኝ።
  የአጥቢያው ዳኛ በቁጥር ፪፻፳፬ ንኡስ ቁጥር (፪) መሠረት በሰጠው ፍርድ ይግባኙ በዚያው ስፍራ ላለው የወረዳ ፍርድ ቤት ይቀርባል።

  ምንጭ:
  የ፲፱፻፶፬ ዓ.ም. የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት አዋጅ
 • loader Loading content ...
 • @በህግ አምላክ   3 months ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!

  የ፲፱፻፶፬ ዓ.ም የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ፥ በወንጀል ነገር የሚከፈል የኪሣራ ወጪ ፥ ሰባተኛ መጽሐፍ ፥ በወንጀል ነገር የሚከፈል የኪሣራ ወጪ።


  ቁጥር ፪፻፳። ዐቃቤ ሕጉ ለሚያቀርበው ክስ የኪሣራ ወጪ።
  (፩) በዐቃቤ ሕግ በኩል ለሚቀርበው ክስ የኪሣራ ወጪ በሙሉ ከይግባኙ ጭምር መንግሥት ኃላፊ ነው።
  (፪) በተፈረደበት ሰው ምክንያት በዐቃቤ ሕጉ በኩል የቀረበው ክስ የተለየ የኪሣራ ወጪ የሚደረግ እንደ ሆነና የተፈረደበት ሰው ንብረት ያለው እንደ ሆነ፤ በሕግ ከሚወሰንበት ቅጣት በላይ የፍርድ ቤቱ የመዝገብ ቤት ሹም የሚወስነውን የኪሣራ ወጪ በሙሉ ወይም በከፊል እንዲከፍል ፍርድ ቤቱ ሊያዝ ይችላል።
  (፫) በአቤቱታ በሚቀርብ ክስ በዐቃቤ ሕግ በኩል ክሱ ከቀረበ በኋላ የተበደለው ሰው አቤቱታውን የተወ እንደሆነ (በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቁጥር ፪፻፳፩) መሠረት ለወንጀሉ ክስ ለተደረገው የኪሣራ ወጪ ሁሉ ኃላፊ ይሆናል።

  ቁጥር ፪፻፳፩። የግል ክስ የኪሣራ ወጪ።
  (፩) በግል ክስ በሚቀርቡ ነገሮች ላለው የኪሣራ ወጪ ሁሉ በቁጥር ፵፮ መሠረት የግል ከሳሹ ኃላፊ ነው።
  (፪) በግል ክስ ቀርቦ ተከሳሹ ነጻ የተለቀቀ እንደ ሆነና ክሱ የቀረበው በቅን ልቡና አለመሆኑን ፍርድ ቤቱ የተገነዘበ እንደ ሆነ ተከሳሹ ያወጣውን የኪሣራ ወጪ በሙሉ ወይም በከፊል የግል ከሳሹ እንዲከፍል ፍርድ ቤቱ ለማዘዝ ይችላል።
  (፫) የግል ክሱ በቁጥር ፵፰ መሠረት የታገደ እንደሆን፤ ለግል፤ ክሱ፤ የኪሣራ ወጪ ሁሉ መንግሥት ኃላፊ ነው።

  ቁጥር ፪፻፳፪። የተበደለው ወገን።
  (፩) የተበደለው ወገን በወንጀል ነገር ውስጥ ካሣ እንዲከፈለው የጠየቀ እንደሆን ከዚህ የሚከተሉትን መፈጸም አለበት።
  (ለ) ምስክሮችና በምስክርነት ቃላቸውን የሚሰጡትን ልዩ ዐዋቂዎች ለመጥራት አስፈላጊውን ወጪ ይከፍላል።
  (፪) የተበደለው ወገን ካሣ እንዲያገኝ የተፈረደለት እንደሆነ በንኡስ ቁጥር ፩ የተጠቀሰውን የኪሣራ ወጪና የዳኝነት ተከሳሹ እንዲከፍል ፍርድ ቤቱ ያዛል።

  ምንጭ:
  የ፲፱፻፶፬ ዓ.ም. የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት አዋጅ
 • loader Loading content ...
 • @በህግ አምላክ   3 months ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!

  የ፲፱፻፶፬ ዓ.ም የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ፥ የቅጣት አፈጻጸም ፥ ስድስተኛ መጽሐፍ ፥ የቅጣት አፈጻጸም ፥ ምዕራፍ ፩ ፥ ጠቅላላ ድንጋጌዎች።


  ቁጥር ፪፻፫። መሠረቱ።
  (፩) ማንኛውም ፍርድ ቤት በወንጀል ነገር የቅጣት ፍርድ ከሰጠ በኋላ በዚህ መጽሐፍ መሠረት የቅጣቱ ፍርድ እንዲፈጸም ወይም ቍጥጥር እንዲደረግ ለአስፈላጊው ባለሥልጣን አስፈላጊውን ማዘዣ ወይም ማንኛውንም ትእዛዝ ይሰጣል።
  (፪) በቁጥር ፻፹፰ የተጻፈውን የዚህ ቍጥር ድንጋጌ አይለውጠውም።

  ቁጥር ፪፻፬። የሞት ፍርድ ስለ ተፈረደበት ሰው የሚሰጥ ትእዛዝ።
  (፩) ማንኛውም ሰው ሞት ሲፈረድበት ሰብሳቢው ዳኛ በፈረመበት ትእዛዝ በሦስተኛው ሠንጠረዥ በ፲፫ኛው ፎርም እንደ ተመለከተው ዐይነት ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ፍርዱን እስኪያጸኑ በእስራት እንዲቆይ ትእዛዝ ይሰጣል።
  (፪) ቅጣቱ የጸና እንደ ሆነ ቅጣቱ እንዲጸና በተደረገው ትእዛዝ ላይ በተጻፉት ሁኔታዎች መሠረት ይፈጸማል።
  (፫) ቅጣቱ የተቀነሰ እንደ ሆነ፤ ቅጣቱን በመቀነስ የተሰጠው ትእዛዝ በቂ ሆኖ በትእዛዙ መሠረት ይፈጸማል።

  ቁጥር ፪፻፭። የግል ነጻነቱን እንዲያጣ ስለ ተፈረደበት ሰው የሚሰጥ ትእዛዝ።
  (፩) ማንኛውም ሰው እንዲያዝ፤ እንዲታሰር ወይም በአንድ ቦታ እንዲወሰን ትእዛዝ ሲሰጥ ሰብሳቢው ዳኛ በዚህ መጽሐፍ በሦስተኛው ሠንጠረዥ ዐይነት በሚፈርምበት ትእዛዝ መሠረት ቅጣቱ እንዲፈረም ትእዛዝ ይሰጣል።
  (፪) ይህ ትእዛዝ በቂ ሆኖ የወህኒ ቤቱ ሹምና ሌሎችም ሰዎች ሁሉ በትእዛዙ ላይ የተነገረውን ቅጣት የመፈጸም ሥልጣን አላቸው።

  ቁጥር ፪፻፮። በአንዳንድ ነገሮች የቅጣቱ ጊዜ እንዲተላለፍ ለማድረግ የሚቻል ስለ መሆኑ።
  እንዲያዝ ወይም ከአንድ ዓመት ባልበለጠ ጊዜ በእስራት እንዲቀታ የተፈረደበት ሰው፤
  (ሀ) ነፍሰ ጡር የሆነች እንደ ሆነ፤ ወይም
  (ለ) የቤተ ሰቡ ደጋፊ ሰውዬው ብቻ የሆነ እንደ ሆነና ይኸውም ሰው ለሕዝብ ጸጥታ አሥጊ ያልሆነ እንደ ሆነ፤ ፍርድ ቤቱ ለመልካም ጠባዩ ዋስ አስጠርቶ ከስድስት ወር ላልበለጠ ጊዜ ቅጣቱ ከመፈጸሙ እንዲቆይ ሊያስተላልፍበት ይችላል።

  ቁጥር ፪፻፯። ግርፋት ስለ ተፈረደበት ሰው የሚሰጥ ትእዛዝ።
  በወንጀለኛው መቅጫ ሕግ ቁጥር ፮፻፴፭ ንኡስ ቍጥር ፫ ወይም ፮፻፴፯ ንኡስ ቍጥር ፩ መሠረት ግርፋት ስለ ተፈረደበት ማንኛውም ሰው ሰብሳቢው ዳኛ በሚፈርምበት ትእዛዝ በዚህ ሕግ በሦስተኛው ሠንጠረዥ በ፲፮ኛው ፎርም በተጻፈው ዐይነት በወንጀለኛው መቅጫ በቁጥር ፻፳ (ሀ) መሠረት የግርፋቱን ቅጣት የሚፈጽመውንና የሚፈጸምበትን ስፍራ ለይቶ ትእዛዝ ይሰጣል።

  ቁጥር ፪፻፰። ለወንጀሉ አላፊ ስላልሆኑ ሰዎች የሚሰጥ ትእዛዝ።
  ለተግባሩ ሙሉ አላፊ ያልሆነ ሰው በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቁጥር ፻፴፬ ወይም ፻፴፭ መሠረት ሕክምና እንዲደረግለት ወይም በአንድ ቦታ በጥንቃቄ ግዞት ተወስኖ እንዲጠበቅ ፍርድ ቤቱ በወሰነ ጊዜ ሰብሳቢው ዳኛ በሚፈርምበት የትእዛዝ ወረቀት በዚህ ሕግ በሦስተኛው ሠንጠረዥ በአሥራ አምስተኛው ፎርም በተመለከተው ዐይነት ተከሳሹ ተስማሚ በሆነ ድርጅት ውስጥ በግዞት ተወስኖ እንዲጠበቅ ወይም የአእምሮ ሕክምና እንዲደረግለት ትእዛዝ ይሰጣል።

  ቁጥር ፪፻፱። የቅጣት ገንዘብን ስለ ማስገባት።
  (፩) በፍርድ ቤቱ ትእዛዝ መሠረት ፍርድ አስፈጻሚው በወንጀለኛው መቅጫ ሕግ ቁጥር ፺፩፤ ፻፸፩ ንኡስ ቍጥር ፩፤ ፯፻፰ እና ፯፻፲ መሠረት የመቀጫውን ገንዘብ ገቢ ያደርጋል።
  (፪) የመቀጫውን ገንዘብ በሙሉ ወይም በከፊል ፍርድ አስፈጻሚው ማስገባት ያልቻለ እንደ ሆነ ጉዳዩን ለፍርድ ቤቱ ያስታውቃል፤ ፍርድ ቤቱም ለአፈጻጸሙ ወይም በወንጀለኛው መቅጫ ሕግ ቁጥር ፺፪፤ ፺፬፤ ፺፮፤ ፻፸፩ ንኡስ ቁጥር ፪ እና ፯፻፱ መሠረት የመቀጫውን ገንዘብ በግዴታ ሥራ ወይም በማረፊያ ቤት እስራት ወይም በአነስተኛ እስራት እንዲለወጥ አስፈላጊውን ትእዛዝ ይሰጣል።
  (፫) ሰውየው በሌለበት መቀጫ እንዲከፍል ሲፈረድበት ፍርድ ቤቱ በተፈረደበት ሰው ንብረት ላይ ትእዛዙ እንዲፈጸም ያደርጋል እንጂ ንኡስ ቊ ፩ ተፈጻሚ አይሆንም።

  ቊ ፪፻፲። ንብረት ስለ መውረስ።
  (፩) በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቊ ፩፻፸፪ መሠረት ንብረቱ እንዲወረስ ትእዛዝ የተሰጠ እንደ ሆነ፤ ፍርድ ቤቱ በወንጀለኛው መቅጫ ሕግ ቊጥር ፺፯ መሠረት የሚያዘውን ንብረት ለይቶ በመግለጽ ፍርድ አስፈጻሚ ይህንኑ ንብረት እንዲይዝ ትእዛዝ ይሰጣል።
  (፪) ፍርድ አስፈጻሚው ንብረቱን ከያዘ በኋላ ለዚህ ነገር መብት ያለው የመንግሥት ባለሥልጣን ፍርድ አስፈጻሚው የያዘውን ንብረት ለሚያስረክበው ሰው ወይም ሰዎች በትእዛዝ እስኪገልጽለት ድረስ ይዞ ይቆያል። ፍርድ አስፈጻሚው ንብረቱን ሲያስረክብ ንብረቱን በዝርዝር የሚያስረዳ ደረሰኝ ካስረከበው ሰው ወይም ሰዎች ይቀበላል።
  (፫) የተፈረደበት ሰው ቤተሰቦች በስሕተት የተወረሰባቸውን ንብረት እንዲለቀቅላቸው ፍርድ ቤቱን መጠየቅ ይችላሉ።

  ቊ ፪፻፲፪። ንብረትን ስለ ማስያዝ።
  (፩) አንድ ሰው በሌለበት በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቊ ፪፻፸፪ መሠረት ለተመለከተው ወንጀል ንብረቱ እንዲያዝ ሲፈረድበት ፍርድ ቤቱ ከዚህ በሚቀጥለው ዐይነት ትእዛዝ ይሰጣል።
  (ሀ) ፍርድ አስፈጻሚው በወንጀለኛው መቅጫ ሕግ ቊ ፺፰ መሠረት መያዝ የሚገባውን ንብረት እንዲይዝና ትእዛዙም የሚያዘውን ንብረት ለይቶ መግለጽ አለበት።
  (ለ) ንብረቱን የሚያስተዳደር (ጠባቂ) መሾምና አስተዳዳሪውም በተሾመ ጊዜ ፍርድ አስፈጻሚው የንብረቱን ዝርዝር ደረሰኝ ተቀብሎ ንብረቱን ለአስተዳዳሪው ያስረክባል።
  (፪) በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ በቊ ፺፯ ንኡስ ቊ ፫ የተጠቀሰው ማንኛውም ንብረት እንዳይያዝ ማድረግ ኃላፊነቱ የፍርድ አስፈጻሚው ነው፤ የተፈረደበት ሰው ቤተሰቦች በስህተት የተያዘ ማንኛውም ንብረት እንዲለቀቅላቸው ለንብረቱ አስተዳዳሪ ማመልከት ይችላሉ።
  (፫) በንኡስ ቊ ፩ መሠረት የተሰጠው የማስያዙ ትእዛዝ ለዚህ ነገር ሥልጣን ያለው የመንግሥት ባለሥልጣን እንዲነሣለት ፍርድ ቤቱን እስኪጠይቅ ድረስ ትእዛዙ ተፈጻሚ ይሆናል፤ ነገር ግን ይኸው ባለ ሥልጣን ትእዛዙ እንዲነሣለት ባመለከተ ጊዜ ንብረቱ እንዲያዝ የተሰጠው ትእዛዝ ተነሥቶ ንብረት አስተዳዳሪው ትክክለኛ ሒሳብ አቅርቦ ከግዴታው ነጻ እንዲሆን ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ይሰጣል።

  ቊ ፪፻፲፫። አካለ መጠን ስላላደረሱ ወጣቶች የሚሰጥ ትእዛዝ።
  (፩) ፍርድ ቤቱ በወንጀለኛ ሕግ ቊ ፩፷፪፤ ፻፷፭፤ ፻፷፮፤ ፻፸፫፤ ወይም ፯፻፫ መሠረት አካለመጠን ስላላደረሰ ወጣት ትእዛዝ በሰጠ ጊዜ፤ ሰብሳቢው ዳኛ ፈርሞ እንደ ነገሩ ሁኔታ ለክፍሉ ኃላፊ ሥራ አስኪያጅ፤ ለትምህርት ቤቱ ዳሬክተር፤ ለዲሬክተሩ ወይም ኃላፊ ለሆነው መኰንን ትእዛዙን ይልካል፤ በትእዛዙ ላይ በተገለጸው መሠረት አካለመጠን ባላደረሰው ወጣት ላይ አስፈላጊውን ለመፈጸም በቂ ሥልጣን ነው።
  (፪) አካለ መጠን ስላላደረሰ ወጣት በወንጀለኛው መቅጫ ሕግ በቊ ፻፷፫ መሠረት ትእዛዝ ሲሰጥ፤ ሰብሳቢው ዳኛ በወንጀለኛው መቅጫ ህግ ቊጥር ፻፷፫ ከተጠቀሱት ሰዎች ለአንዱ ፈርሞ ትእዛዙን ይልካል። በትእዛዙ ላይ በተገለጸው መሠረት አካለ መጠን ባላደረሰው ወጣት ላይ አስፈላጊውን ለመፈጸም በቂ ሥልጣን ነው።
  (፫) አካለ መጠን ያላደረሰው ወጣት የአርጩሜ ቅጣት በወንጀለኛው መቅጫ ሕግ ቊ ፻፸፪ መሠረት ሲፈረድበት የአርጩሜ ቅጣት ሰውነቱ የሚችል እንደሆን በሐኪም ተመርምሮ እንዲረጋገጥ ሰብሳቢው ዳኛ ያዛል። ሰውነቱ የሚችል መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ የአርጩሜውን ቅጣት በገለልተኛ ስፍራ ከቤተሰቡ በዕድሜ የላቀው ወይም ሰብሳቢው ዳኛ የመረጠው ሌላ ሰው የመረመረው ሐኪምና አካለ መጠን ያላደረሰው ወጣት ወላጆች፤ ቤተ ዘመዶቹ ያሉ እንደ ሆነ፤ ወይም ሞግዚቱ ባሉበት ይፈጸማል።

  ቊ ፪፻፲፬። ስለ ግዴታ ሥራ፤ ስለ ተጨማሪ ቅጣትና ስለሚወሰደው ጥንቃቄ፤
  በወንጀለኛው መቅጫ ሕግ ቊ ፻፪፤፻፫፤፻፳፪፤፻፵፬፤፻፵፮፤ ፻፵፯፤ ከ፻፵፱፤ እስከ ፻፶፬፤ ከ፻፶፰፤ እስከ ፻፷፤ ፻፸፰፤ ፻፸፱፤ ፯፻፲፭፤ ፯፻፲፮፤ ወይም ከ፯፻፲፰፤ እስከ ፯፻፳ መሠረት ትእዛዝ የሰጠ እንደ ሆነ የፍርዱ ፍሬው ነገር ግልባጭ አግባብ ላላቸው ባለሥልጣኖች እንዲደርስና አስፈላጊውን እንዲያደርጉ ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ይሰጣል።

  ቊ ፪፻፲፭። የፍርድ አፈጻጸም ትእዛዝን በመዝገብ ስለ መጻፍ።
  ስለ ቅጣቱ አፈጻጸም የሚሰጠውን ማንኛውንም ትእዛዝ ፍርድ ቤቱ በመዝገብ ይጽፋል። ትእዛዙ የተፈጸመበትን ቀን የሚገልጽ በመዝገቡ ላይ ይጽፋል፤ አስፈላጊ ሲሆንም ትእዛዙ ሊፈጸም ያልተቻለበት ምክንያት በመዝገብ ይጻፋል።

  ምንጭ:
  የ፲፱፻፶፬ ዓ.ም. የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት አዋጅ
 • loader Loading content ...
 • @በህግ አምላክ   3 months ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!

  የ፲፱፻፶፬ ዓ.ም የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ፥ ስለ ይግባኝ ተከሳሹ በሌለበት የተሰጠውን ፍርድ ለማሻር ስለሚቀርበው ማመልከቻ ፥ አምስተኛ መጽሐፍ ፥ ስለ ይግባኝ ተከሳሹ በሌለበት የተሰጠውን ፍርድ ለማሻር ፥ ስለሚቀርበው ማመልከቻ ፥ ፩ኛ አንቀጽ ፥ ይግባኝ።


  ቊ ፻፹፩። መሠረቱ።
  (፩) የወንጀል ፍርድ ቤት በተከሳሹ ላይ ጥፋተኛ መሆኑን በመፍረዱ ለጊዜው የመልቀቅ ወይም ነጻ የመለቀቁ ፍርድ በመሰጠቱ የሚቀርቡ ይግባኞች ሁሉ በዚህ መጽሐፍ በተመለከተው መሠረት ይፈጸማሊ።
  (፪) ሁለተኛ ይግባኝ በቊ ፻፹፪ መሠረት ይቀርባል።

  ቊ ፻፹፪። ይግባኝ ለማየት ሥልጣን ያላቸው ፍርድ ቤቶች።
  (፩) በሚሰጠው ፍርድ ይግባኙ ከዚህ በሚቀጥው ደረጃ ይቀርባል።
  (ሀ) ከወረዳው ፍርድ ቤት ወረዳው በሚገኝበት አውራጃ ግዛት ውስጥ ሥልጣኑ ለሆነው አውራጃ ፍርድ ቤት፤
  (ለ) ከአውራጃ ፍርድ ቤት ለከፍተኛው ፍርድ ቤት፤
  (ሐ) ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ለጠቅላይ ፤
  (፪) በሚሰጠው ፍርድ የሚቀርበው ሁለተኛው ይግባኝ ለከፍተኛው ደረጃ ይቀርባል።
  (ሀ) አውራጃ ፍርድ ቤት የሚቀርበው በይግባኝ ሰሚነት ያየው ይግባኝ ለጠቅላላ ንጉሠ ነገሥት ፍርድ ቤት።
  (ለ) ከፍተኛው ፍርድ ቤት በይግባኝ ሰሚነት ያየው ይግባኝ ለጠላላ ንጉሠ ነገሥት ፍርድ ቤት።

  ቊ ፻፹፫። ለግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ችሎት ስለሚቀርቡ ማመልከቻዎችን።
  (፩) በቊ ፻፹፪ መሠረት የይግባኝ መብቱን የፈጸመ ባለጉዳይ ነገሩ እንደገና እንዲታይለት ለግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ለማመልከት በቊ ፻፹፪ የተመለከተው አይከለክለውም።
  (፩) ለግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ከሚቀርበው ማመልከቻ ጋራ
  (ሀ) አመልካቹ ያልተስማማበትን ፍርድ ወይም ፍርዶችና
  (ለ) አመልካች ነገሩ እንድ ገና እንዲታይለት የሚጠይቅበትን ምክንያት ባጭሩ የሚገልጽ የይግባኝ ማመልከቻ አያይዞ ማቅረብ አለበት።

  ቊ ፻፹፬። የትእዛዝ ይግባኝ ስላለመኖሩ።
  ከዚህ በታች ባሉት ሁኔታዎች ፍርድ ቤት በሚሰጠው ትእዛዝ ይግባኝ ለማለት አይቻልም።
  (ሀ) በቊ ፺፬ መሠረት ቀጠሮ መስጠት ወይም አለመስጠት ወይም
  (ለ) በቊ ፻፴፩ መሠረት ስለሚቀርብ መቃወሚያ ወይም
  (መ) በቊ ፻፵፮ መሠረት ማስረጃን ስለ መቀበል ወይም ስላለመበል ነገር ግን የጥፋተኛነት ውሳኔ በተሰጠበት ለጊዜው በመልቀቅ ወይም ነጻ በመልቀቅ ፍርድ ተሰጥቶ ይግባኝ በተባለበት ጊዜ እነዚህ የተሰጡት ትእዛዞቸ ይግባኝ ለማለት ምክንያቶች ለመሆን ይችላሉ።

  ቊ ፻፹፭። የጥፋተኛነት ውሳኔ በተሰጠበት ወይም በቅጣቱ ይግባኝ ስለ ማለት።
  (፩) የተፈረደበት ሰው የጥፋተኛነት ውሳኔ በተሰጠበትና በቅጣቱ ይግባኝ ማለት ይችላል።
  ነገር ግን ተከሳሹ የተከሰሰበትን ወንጀል ያመነ ሆኖ በእምነቱ መሠረት ጥፋተኛነቱ ከተወሰነ በኋላ ስለ ቅጣቱ ልክ ወይም ቅጣቱ ሕጋዊ ላለመሆኑ ይግባኝ ማለት ይችላል እንጂ የጥፋተኛነት ውሳኔ በተሰጠበት ላይ ይግባኝ ማለት አይችልም።
  (፪) ዐቃቤ ሕጉ ወይም የግል ከሳሹ ፍርድ ቤት በሚሰጠው ለጊዜው በመልቀቅ ወይም ነጻ በመልቀቅ ፍርድ ላይ ወይም ቅጣቱ በቂ አይደለም በማለት ይግባኝ ማለት ይችላል።
  (፫) አካለ መጠን ያለደረሰ ወጣት ወይም ችሎታ የሌለው ሰው ይግባኝ ሲል ይግባኙን የሚያቀርብለት እንደራሴው ነው።

  ቊ ፻፹፮። ሰው ካሣ በሚጠይቅበት ነገር ይግባኝ ስለ ማለት።
  (፩) በወንጀለኛው መቅጫ ሕግ ቊ ፻ መሠረት ፍርድ ቤቱ ካሣ ማግኘት አይገባውም ብሎ የፈረደ እንደ ሆነ፤ የተበደለው ወገን በውሳኔው ይግባኝ ለማለት ይችላል።
  (፪) ፍርድ ቤቱ የተበደለው ሰው ካሣ መቀበል ይገባዋል ብሎ በፈረደ ጊዜ ተከሳሹ በውሳኔው ይግባኝ ማለት ይችላል።
  (፫) በተፈረደው የካሣ ልክ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁ ፪ሺ ፻፶፫ መሠረት ይግባኝ ለማለት ይቻላል።
  (፬) በዚህ ቁጥር መሠረት ይግባኝ ሲባል የጥፋተኛነት ውሳኔ በተሰጠበት ወይም በቅጣቱ ውሳኔ ይግባኝ ሲቀርብ ይግባኙን የሚሰማው የወንጀል ይግባኝ ፍርድ ቤት ነው፤ ነገር ግን የጥፋተኛ ውሳኔ በተሰጠበት ወይም ስለ ቅጣቱ ይግባኝ ባልተባለ ጊዜ ወይም ይግባኙ በተተወ ጊዜ የካሣውን ፍርድ ይግባኝ የፍትሐ ብሔር ይግባኝ ችሎት ይሰማል።

  ቊ ፻፹፯። ይግባኝ ማለትን ስለ ማስታወቅና የይግባኝ ማመልከቻ
  (፩) ይግባኝ ማለቱን ለማስታወቅ የሚጽፈውን ማመልከቻ ይግባኝ ባዩ ወይም ጠበቃው ይግባኝ የሚልበት ፍርድ በተሰጠ በአሥራ አምስት ቀን ውስጥ ማቅረብ አለበት።ይግባኝ ማለቱን ለማስታወቅ የጻፈው ማመልከቻ ለፍርድ ቤት መዝገብ ሹም (ለሬጂስትራሩ) ሲደርሰው ይግባኝ የተባለበትን ፍርድ አስገልብጦ ለይግባኝ ባዩ ወይም ለጠበቃው ይሰጣል። ይግባኝ ባዩ በእስር ቤት ያለ እንደ ሆነ ይግባኝ የተባለበትን ፍርድ ግልባጭ የፍርድ ቤት መዝገብ ሹም ለይግባኝ ባይ እንዲሰጥ ለወህኒ ቤቱ ሹም ይልካል። ፍርድ ተገልብጦ ያለቀበት ቀንና ኋላም ለይግባኝ ባዩ ወይም ለጠበቃው ወይም ለወህኒ ቤቱ ሹም የደረሰበትን ቀን የፍርድ ቤት መዝገብ ሹም በፊርማው ያረጋግጣል።
  (፩) በ ቊ፻፹፱ መሠረት የሚቀርበው የይግባኝ ማመልከቻ የፍርድ ግልባጭ በደረሰው በሠላሳ ቀን ውስጥ ፍርድን ለሰጠው ፍርድ ቤት መዝገብ ቤት መቅረብ አለበት።
  (፫) ተከሳሹ በእስር ቤት የሆነ እንደ ሆነ የወህኒ ቤቱ ሹም ሳይዘገይ የይግባኙን ማመልከቻ ይግባኝ የተባለበትን ፍርድ ለሰጠው ፍርድ ቤት መላክ አለበት።
  (፬) የይግባኙ ማመልከቻ ግልባጭ ለመልስ ሰጪው እንዲደርሰው መደረግ አለበት።

  ቊ ፻፹፰። ፍርድ እንዳይፈጸም ስለ ማገድ።
  (፩) ጥፋተኛ ሆኖ የተፈረደበት ይግባኝ ባይ የይግባኝ ማስታወቂያ የሰጠ እንደ ሆነ ይግባኙ ሳይሰማ ወይም ይግባኙን ይግባኝ ባዩ ካልተወ በቀር የግርፋቱ ቅጣት አይፈጸምም።
  (፪) ተከሳሹ ይግባኙ እስኪወሰን ድረስ በዋስትና ወረቀት የተለቀቀ እንደ ሆነ፤ የእስራቱ ቅጣት የይግባኙ ፍርድ ቤት ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ አይጀመርም።
  (፫) ይግባኝ የተባለበት ፍርድ ቤት እንዲፈጸሙ ለጥንቃቄ የሰጣቸው ትእዛዞች ይግባኝ የተባለባቸው ቢሆኑም መፈጸም አለባቸው።
  (፬) ስለ ካሣ ወይም ስለ ኪሣራ ወጪ የተሰጠ ፍርድ ከመፈጸም አይታገድም።
  (፭) ይግባኙ ከመሰማቱ በፊት በማንኛውም ጊዜ ወይም ይግባኙ በሚሰማበት በማንኛውም ጊዜ ፍርድ እንዲታገድ ለይግባኝ ፍርድ ቤት ማመልከት ይቻላል።

  ቁጥር ፻፹፱። በይግባኝ ማልከቻ ላይ ስለሚጻፈው።
  (፩) ይግባኝ ማመልከቻ ይግባኝ በተባለበት ፍርድ ላይ ያሉትን የመቃወሚያ ምክንያቶች ባጭሩ ለይቶ ዋና ዋናዎቹን ነገሮች በክርክር መልክ ሳይተቹ በተራ ቍጥር በዝርዝር መጻፍ አለባቸው። ከይግባኝ ማመልከቻው ጋራ ይግባኝ የተባለበት ፍርድ ግልባጭ መቅረብ አለበት። የይግባኙ ማመልከቻ ይግባኝ ባዩ እንዲወገድለት የሚጠየቀውን የፍርድ ልመናውን መግለጽ አለበት።
  (፪) የይግባኙን ማመልከቻ ይግባኝ ባዩ ራሱና ጠበቃ ያለው እንደ ሆነ፤ ጠበቃው ይፈርማሉ።

  ቁጥር ፻፺። ለይግባኝ ፍርድ ቤት ስለሚላኩ የይግባኝ ማመልከቻዎች መረጃዎችና (ኤግዚቢቶች) እና መዝገብ።
  (፩) ይግባኝ የተባለበትን ፍርድ የሰጠው ፍርድ ቤት የይግባኙ ማመልከቻ እንደ ደረሰው ካ፲፭ ቀን ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የመዝገቡን ግልባጭና የይግባኝ መዝገብ (ያለ እንደሆን) ይግባኝ እላለሁ ሲል ያስታወቀበትንም ከይግባኙ ማመልከቻ ጋራ መረጃዎችን ጭምር ለይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ይልካል።
  (፪) መዝገቡን መገልበጥ የነገሩን በይግባኝ መታየት የሚያዘገየው ሲሆን ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የመዝገቡ መገልበጥ እንዲቀርና ዋናው መዝገብ በትውስት እንዲቀርብለት ለማድረግ ይችላል።

  ቁ፡ ፻፺፩ የይግባኝ ጊዜ ካለፈ በኋላ ይግባኝ ለማቅረብ ፈቃድ ለማግኘት የሚቀርብ ማመልከቻ።
  (፩) ይግባኝ የተባለበትን ፍርድ የሰጠው ፍርድ ቤት የይግባኙ ማስታወቂያ ወይም ማመልከቻ ጊዜው ካለፈ በኋላ የቀረበለት እንደ ሆነ፤ አልቀበልም ለማለት ይችላል። በዚህ ጊዜ የይግባኙን ማስታወቂያ ወይም ማመልከቻ የሚያቀርበው ሰው የይግባኙ ጊዜ ካለፈ በኋላ ይግባኙን ለማቅረብ እንዲፈቀድለት ማመልከቻውን በጽሑፍ ለይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት እንዲያቀርብ ያደርጋል።
  (፪) ማመልከቻውም የይግባኙ ጊዜ ካለፈ በኋላ ነገሩ ሊሰማ ይገባል የሚባልበትን ምክንያትና የዘገየበትን ምክንያት ገልጾ ማስረዳት አለበት።
  (፫) የይግባኝ ፍርድ ቤት የይግባኙ ጊዜ ያለፈው በአመልካቹ ጥፋት ባልሆነ ምክንያት ለመሆኑ ካልተረዳ በቀር ጊዜው ያለፈ ይግባኝ እንዲሰማ አይፈቀድም።
  (፬) ጊዜው ካለፈ በኋላ ይግባኙ እንዲሰማ የይግባኝ ፍርድ ቤት የወሰነ እንደ ሆነ፤ የይግባኙ ማመልከቻ የሚቀርብበትን ቀን ይወስናል።

  ቁጥር ፻፺፪። የነገሩ መሰማት።
  የይግባኙ ፍርድ ቤት ሰብሳቢ ዳኛ ይግባኙ የሚሰማበትን ቀን ወስኖ ለነገረተኞቹ ይነገራቸዋል። ይግባኝ ባዩ ይግባኙን ማስረዳት ይጀምራል፤ መልስ ሰጪውም መልስ ይሰጣል፤ ይግባኝ ባዩ የመልስ መልስ የመስጠት መብት አለው።

  ቁጥር ፻፺፫። ከነገረተኞቹ አንዱ ወገን ይግባኙ በሚሰማበት ቀን ስላለመቅረቡ።
  (፩) ይግባኝ ባዩ ወይም ጠበቃው የይግባኙ ቀን ተነግሯቸው በተወሰነው ቀን ያልቀረቡ እንደ ሆነ፤ ይግባኙ ይሰረዛል። ነገር ግን ይግባኝ ባዩ ወይም ጠበቃው ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ሳይቀርብ መቅረቱን ያረጋገጠ እንደ ሆነ ይግባኙ እንዲሰማ ማድረግ ይቻላል።
  (፪) መልስ ሰጪው ወይም ጠበቃው ያልቀረቡ እንደ ሆነ፤ በሌሉበት ነገሩ ይቀጥላል።

  ቁጥር ፻፺፬። ተጨማሪ ማስረጃ።
  (፩) የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ይግባኝ በሚያይበት ጊዜ ተጨማሪ ማስረጃ የሚያስፈልግ መስሎ ከታየው አስፈላጊ መስሎ ሊታየው የቻለበትን ምክንያት በመዝገብ ጽፎ ማስረጃውን መቀበል ይችላል።
  (፪) በንኡስ ቍጥር (፩) መሠረት የሚቀርብ ማስረጃ በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ነገሩ በተሰማበት ጊዜ እንደ ቀረበ ዐይነት ሆኖ ይቆጠራል።

  ቁጥር ፻፺፭። የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ሥልጣን።
  (፩) ይግባኙ በሚሰማበት ጊዜ በነገሩ ውስጥ ለመግባት በቂ ምክንያት የሌለ መስሎ ከታየው ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ይግባኙን ማሰናበት አለበት።
  (፪) በነገሩ ለመግባት በቂ ምክንያት ያለ በመሰለው ጊዜ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ከዚህ የሚቀጥሉትን ይፈጽማል።
  (ሀ) ተከሳሹን ነጻ በመልቀቅ ወይም ለጊዜው በመልቀቅ በተሰጠ ትእዛዝ ይግባኝ የተባለ ሲሆን፤ ትእዛዙን ሰርዞ ሥልጣን ያለው ፍርድ ቤት ነገሩን እንደ ገና እንዲያይ ማዘዝ ወይም ጥፋተኛ ነው ብሎ እንደ ሕጉ ፍርድ ቤት ሊፈርድበት ይችላል፤ ወይም
  (ለ) ጥፋተኛ ነው የተባለበትን ውሳኔ በቅጣቱ ይግባኝ በተባለ ጊዜ
  (፩) ጥፋተኛ ነው የተባለበትን ውሳኔና ቅጣቱን ሰርዞ ተከሳሹን በነጻ ለመልቀቅ ይችላል፤ ወይም
  (፪) ፍርዱን ለውጦ ወይም ሳይለውጥ ቅጣቱን ያጸናል፤ ይጨምራል፤ ወይም ይቀንሳል።
  (ሐ) ጥፋተኛ ነው በተባለበት ውሳኔ ላይ ብቻ ይግባኝ በተባለ ጊዝ ፍርዱንና ቅጣቱን ሰርዞ ተከሳሹን በነጻ ለመልቀቅ ይችላል።
  (መ) በቅጣቱ ላይ ብቻ ይግባኝ በተባለ ጊዜ ቅጣቱን ያጸናል፤ ይጨምራል፤ ወይም ይቀንሳል።
  (፫) የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ነው የተባለበትን ውሳኔ አጽንቶ ቅጣቱን የለወጠ እንደ ሆነ ወይም ቅጣቱን አጽንቶ ጥፋተኛ ነው የተባለበትን ውሳኔ የለወጠ እንደ ሆነ ጥፋተኛ ነው በተባለበት ወይም ቅጣቱ እንዲለወጥ በተወሰነው ላይ ብቻ ሁለተኛ ጊዜ ይግባኝ ለማለት ይቻላል።

  ቁጥር ፻፺፮። የተፈረባቸው ብዙ ሰዎች ሆነው አንዱ ብቻ ይግባኝ ሲያቀርብ።
  (፩) ለይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የቀረበው ይግባኝ ስለ ተፈረደባቸው ብዙ ሰዎች የሚመለከት ሆኖ ይግባኝ ያለው ግን የተፈረደበት አንድ ሰው ብቻ በሆነ ጊዜ፤ ከዚህ በታች እንደተመለከተው ሲሆን፤ የይግባኙ ፍርድ ቤት የሚሰጠው ፍርድ ይግባኝ ላሉትም ሰዎች ይግባኝ እንዳሉ ተቆጥሮ ይፈጸምላቸዋል ለማለት የሚችለው፤
  (ሀ) በይግባኝ የተሰጠው ፍርድ ለይግባኝ ባዩ የሚጠቅም በሆነ ጊዜና
  (ለ) ተከሳሾቹ ይግባኝ ቢሉ ኖሮ በፍርዱ እነሱም ሊጠቀሙ ይችሉ ነበር የሚያሰኝ ሲሆን ነው።
  (፪) ፍርዱ በይግባኝ ባዩ ላይ ጉዳት የሚያመጣበት እንደ ሆነ ይግባኝ ባላሉ ሰዎች ላይ አይፈጸምም።

  ምንጭ:
  የ፲፱፻፶፬ ዓ.ም. የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት አዋጅ
 • loader Loading content ...
 • @በህግ አምላክ   3 months ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!

  የ፲፱፻፶፬ ዓ.ም የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ፥ ክሱ በፍርድ ቤት ስለ መሰማት ፥ አራተኛ መጽሐፍ ፥ ክሱ በፍርድ ቤት ስለ መሰማት ፥ ምዕራፍ ፩ ፥ ጠቅላላ ድንጋጌዎች


  ቁጥር ፺፬። የቀጠሮ ቀን የሚሰጡበት ምክንያቶች።
  (፩) ዐቃቤ ሕጉ ወይም ተከሳሹ ሲያመለክት ወይም ፍርድ ቤቱ በራሱ አስተያየት ትክክለኛፍርድ ለመስጠት የሚረዳ ከሆነ ክሱ በሚሰማበት በማንኛውም ጊዜ ቀጠሮ ለማድረግ ይችላል።
  (፪) በተለይም ከዚህ በታች በተዘረዘሩት ምክንያቶች ካልሆነ በቀር ቀጠሮ ሊሰጥ አይቻልም።
  (ሀ) ዐቃቤ ሕጉ የግል ከሳሹ ወይም ተከሳሹ በበቂ ምክንያት ሳይቀርቡ የቀሩ እንደ ሆነ ወይም
  (ለ) የዐቃቤ ሕጉ ወይም የተከሳሹ ምስክሮች ሳይቀርቡ የቀሩ እንደ ሆነ፤ ወይም
  (ሐ) በከፍተኛው ፍርድ ቤት በሚፈረድ ነገር ቀዳሚ ምርመራ ያልተደረገበት ሆኖ ዐቃቤ ሕጉ ለምርመራ ጊዜ የሚያስፈልገው ሲሆን፤ ወይም።
  (መ) ተጨማሪ መረጃ ማቅረብ አስፈላጊ ሲሆን፤ ወይም
  (ሠ) ዐቃቤ ሕጉ ወይም ተከሳሹ እንደሚቀርብ ቀደም ብሎ ሊገምት የማይችለው ወይም እንደሚቀርብ ያላሰበው አዲስ ማስረጃ በድንገት የቀረበ እንደ ሆነ፤
  (ረ) የክሱ ማመልከቻ በተለወጠ ወይም በጨመረ ጊዜ ዐቃቤ ሕጉ ወይም ተከሳሹ ክሱን ወይም መከላከያውን እንደ ገና ለማመዛዘን ጊዜ የሚያስፈልገው ሲሆን ወይም
  (ሰ) ተከሳሹ የክሱ ወይም የቀዳሚው ምርመራ መዝገብ ግልባጭ ያልደረሰው ወይም የደረሰው ክሱ የሚሰማበት ቀን አቅራቢያ በመሆኑ የሚገባውን መከላከለያ ለማቅረብ ጊዜ ያጠረው ሲሆን፤ ወይም
  (ሸ) የነገሩ መሰማት ከመጀመሩ በፊት ዐቃቤ ሕጉ ክሱን እንዲጀምር ፈቃድ የሚያስፈልገው ሲሆን፤ ወይም
  (ቀ) በሌላው ፍርድ ቤት የቀረቡ ክሶች በመጀመሪያ ውሳኔ ካላገኙ በቀር በተሰማው ነገር ውሳኔ የማይሰጥ ሲሆን ወይም
  (በ) የተከሳሽን አእምሮ ትክክለኛነት በልዩ ዐዋቂ መወሰን የሚያስፈልገው ሲሆን ወይም
  (ተ) ተከሳሹ አካለመጠን ያላደረሰ በሆነ ጊዜ ፍርድ ቤቱ በጥበቃ ሥር እንዲቆይ የሚስፈልግ ሆኖ ሲያገኘው ወይም
  (ቸ) የነገሩ መሰማት በአንድ ቀን ለመፈጸም የማይቻል በመሆኑ ለሚቀጥለው ቀን የሚቀጠር ሲሆን ነው።
  (፫) በ (ሀ) እና ከ (ረ) እስከ (ሸ) ድረስ ባሉት ምክንያቶች ከአንድ ሳምንት የበለጠ ቀጠሮ አይሰጥም።

  ቁጥር ፺፭። አዲስ ቀጠሮና መጥሪያዎች።
  (፩) በቁጥር ፺፬ ንኡስ ቁጥር ፫ የተመለከተው እንደ ተጠበቀ ሆኖ የነገሩ መስማት የሚቀጠረው ለቀጠሮ ምክንያት የሆነውን ጉዳይ ለመፈጸም በቂ እስከሚሆንበት ጊዜ ብቻ ነው።
  (፪) በዐቃቤ ሕጉ ወይም በተከሳሹ ጥፋት ሳይሆን ቀጠሮ የተሰጠበት ምክንያት ሳይፈጸም የቀረ እንደሆን ያንኑ ያህል ወይም አጭር ቀጠሮ ይሰጣል።
  (፫) በቁጥር ፺፬ ንኡስ ቁጥር ፪ (ሐ) እና ከ (ቀ) እስከ (ተ) በተጻፈው መሠረት የነገሩ መሰማት ከተቀጠረ በኋላ ቀጠሮ የተሰጠበት ምክንያት ሲፈጸም ባለጉዳዮቹና ምስክሮቹ እንዲቀርቡ አዲስ መጥሪያ ፍርድ ቤቱ ይሰጣል።

  ቁጥር ፺፮። የቀጠሮ ውጤት።
  (፩) ቀጠሮ በተሰጠ ጊዜ ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ የተሰጠበት ምክንያት እንዲፈጸም አስፈላጊውን ትእዛዝ ይሰጣል። ይኸውም በቁጥር ፴፫ ፶፫ እና ፻፳፭ በተመለከቱት ሁኔታዎች መሠረት ከሚሰጠው የመያዝ ትእዛዝ ጭምር ነው።
  (፪) በቍጥር ፺፬ ንኡስ ቁጥር ፪ (በ) ወይም (ተ) መሠረት ቀጠሮ ሲሰጥ ተከሳሹ አእምሮውን ልዩ ዐዋቂ ሊመረምረው በሚቻልበት ስፍራ ተይዞ እንዲቆይ ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ይሰጣል።

  ቁጥር ፺፯። መረጃዎች (ኢግዚቢቶች)።
  መረጃዎች (ኢግዚቢቶች) ሁሉ ላይና በቁጥር ፴ መሠረት ምስክር በሰጠው ቃልና በቍጥር ፳፯ መሠረት ተከሳሹ የሰጠው ቃል ጭምር ላይ የፍርድ ቤት መዝገብ ሹም ቍጥርና ምልክት ያደርግባቸዋል። እነዚህን መረጃዎች የፍርድ ቤት መዝገብ ቤት ሹም በተጠበቀ ስፍራ ያስቀምጣቸዋል፤ ያለ ፍርድ ቤትም ትእዛዝ አይወጡም።

  ቁጥር ፺፰። በመዝገቡ ውስጥ መኖር ስለሚገባው ነገር።
  (፩) በፍርድ ቤት ነገሩ የሚመረመርበትን መዝገብ ዳኞች ይፈርሙበታል። በመዝገቡም ላይ ቀጥሎ የተመለከቱት ሊኖሩበት ያስፈልጋል።
  (ሀ) የክሱ ወይም የአቤቱታው ግልባጭ፤
  (ለ) የቀዳማዊ ምርመራ ፍርድ ቤት መዝገብ፤ ያለ እንደ ሆነ፤
  (ሐ) የመያዝ ትእዛዝ የተሰጠበት ቀን (ያለ እንደ ሆነ)፤ ወይም ተከሳሹ መጀመሪያ የተያዘበት ቀን፤
  (መ) ለመጀመሪያ ጊዜ ተከሳሹ ፍርድ ቤት የቀረበበት ቀን፤
  (ሠ) ዐቃቤ ሕጉ ወይም የግል ከሳሹ ያቀረበው የክስ ማመልከቻና በክሱ ማመልከቻ የተለወጠው ወይም የተጨመረው ነገር እንዲሁም የግል ከሳሽ ያቀረበው ክስ በሆነ ጊዜ ዐቃቤ ሕግ የፈቀደበት የምስክር ወረቀት አብሮ ይያያዛል፤
  (ረ) ዐቃቤ ሕጉ ወይም የግል ከሳሹ የሰጠው የክስ መክፈቻ ንግግር ግልባጭ፤
  (ሰ) የተከሳሹ እምነት ክደት፤
  (ሸ) ምስክሮች የሰጡት ቃል በሙሉ፤ መስቀልያና ዳግመኛ ጥያቄ ጭምር፤
  (ቀ) ዐቃቤ ሕጉ ወይም ተከሳሹ የተቃወመው ማንኛውም ነገር እና ለተቃወመው ጉዳይ የተሰጠው ውሳኔ፤ ወዲያውኑ በመዝገብ ይጻፋል። ምስክር ቃሉን በሚሰጥበት ጊዜሲሆን የምስክሩን ቃል መስጠት አቁሞ እዚሁ ቦታ መቃወሚያው መጻፍ አለበት።
  (በ) የቀረበው መረጃ የተሰጠው ቍጥርና ያቀረበው ዐቃቤ ሕጉ ወይም ተከሳሹ መሆኑ ተለይቶ ይጻፋል፤
  (ተ) ስለ ሕግ የቀረበ ክርክር እና የተሰጠው ውሳኔ ይኸውም በመዝገቡ የሚጻፈው ክርክሩ በተነሳበት ጊዜ ነው፤
  (ቸ) የተሰጠውን ቀጠሮ ሁሉና የክሱ መሰማት እንዲቀጠር የተደረገበት ቀንና ለቀጠሮው ምክንያት የሆነው ጉዳይ ጭምር፤
  (ነ) ዐቃቤ ሕጉ ወይም ተከሳሹ ይግባኝ ለማለት መብት ያላቸው ለመሆኑ መነገራቸውን ነው።
  (፪) ነገሩ በሚሰማበት በማንኛውም ቀን መዝገቡ ከዚህ በታች በተመለከተው ዐይነት ይጀመራል፤
  (ሀ) የነገሩ ስምና ቁጥር፤
  (ለ) ቀኑና ሰዓቱ ፤
  (ሐ) የዐቃቤ ሕጉና የተከሳሹ ጠበቃ ስም፤
  (መ) የዳኞቹ ስም፤
  (፫) ነገሩ በሚሰማበት ጊዜ ሁሉ ነገሩ ምን ሰዓት እንደ ተቋረጠና የተቀጠረበት ቀንና ሰዓት መጻፍ አለበት።

  ምንጭ:
  የ፲፱፻፶፬ ዓ.ም. የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት አዋጅ
 • loader Loading content ...
 • @በህግ አምላክ   3 months ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!

  የ፲፱፻፶፬ ዓ.ም የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ፥ ቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍርድ ቤትና ክሱ ፍርድ ቤት እንዲሰማ ስለ ማድረግ ፥ ሦስተኛ መጽሐፍ ፥ ቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍርድ ቤትና ክሱ ፍርድ ቤት እንዲሰማ ስለ ማድረግ።


  ቁጥር ፹። መሠረቱ።
  (፩) በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ በቍጥር ፭፻፳፪ (ከባድ የግፍ አገዳደል) ወይም በቍጥር ፮፻፴፯ (ከባድ የሆነ የወንበዴነት ሥራ) በመሥራት የተከሰሰ ማናቸውም ሰው በዚህ መጽሐፍ በተመለከተው መሠረት ለቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍርድ ቤት ነገሩ እንዲጣራ መቅረብ አለበት።
  ስለሆነም ወዲያውኑ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ነገሩ መታየት አለበት ብሎ ዐቃቤ ሕጉ ያቀረበውን አሳብ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ከተረዳ፤ ፍርድ ቤቱ ነገሩ ለቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍርድ ቤት መቅረብ የለበትም ብሎ ለመወሰን የዚህ ቍጥር ድንጋጌ አያግደውም።
  (፪) በከፍተኛው ፍርድ ቤት ብቻ መታየት በሚገባው በሌላ ወንጀል የተከሰሰ ማናቸውም ሰው በቍጥር ፴፰ (ለ) መሠረት ዐቃቤ ሕጉ ካላዘዘ በቀር ቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍርድ ቤት ነገሩ እንዲጣራ መቅረብ የለበትም።

  ቁጥር ፹፩። ሥልጣን ያለው ፍርድ ቤት።
  ከቍጥር ፺፱ እስከ ፻፯ የተመለከተው እንደ ተጠበቀ ሆኖ ወንጀሉ በተፈጸመበት ስፍራ ሥልጣን ያለው የወረዳ ግዛት ፍርድ ቤት የቀዳሚ ምርመራ ያደርጋል።

  ቁጥር ፹፩። ሥነ ሥርዓት።
  (፩) የቀዳሚ ምርመራ ሁሉ ከዚህ በሚከተሉ ቍጥሮች መሠረት ይፈጸማል።
  (፪) በቍጥር ፺፬ በተመለከተው ሁኔታ መሠረት ቀጠሮ ሊሰጥ ይቻላል።

  ቁጥር ፹፫። የቀዳሚ ምርመራ አጀማመር።
  (፩) ዐቃቤ ሕግ በቍጥር ፹ ንኡስ ቁጥር ፪ መሠረት በቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍርድ ቤት ነገሩ እንዲቀርብ የሚያስፈልግ መሆኑን ሲወስን የውሳኔውን ግልባጭ ሥልጣኑ ለሚፈቅድለት ወረዳ ግዛት ፍርድ ቤት አስፈላጊ በሆነ ጊዜም ለዚሁ ፍርድ ቤት ዐቃቤ ሕግ ይልካል።
  (፩) ፍርድ ቤቱም ምርመራው የሚደረግበትን ቀን ወስኖ ዐቃቤ ሕጉ ለክሱ ማስረጃ የሚሆኑት ምስክሮች እንዲቀርቡለት መጥሪያ ያዝለታል።
  (፫) ቀዳሚ ምርመራ በሚደረግበት ፍርድ ቤት ያለው ዐቃቤ ሕግ ስለ ክሱ ክርክሩን ያመለክታል።

  ቁጥር ፹፬። የዐቃቤ ሕግን ማስረጃ ስለ መቀበል።
  የተከሰሰው ሰው ራሱ ሲቀርብ ወይም እንዲቀርብ ከተደረገ በኋላ ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ሕጉ ነገሩን እንዲጀምርና ምስክሮቹን እንዲጠራ ያደርጋል።

  ቁጥር ፹፭። ተከሳሹ ቃሉን ለመስጠት ፈቃደኛ እንደ ሆነ፤ ስለ መጠየቅ።
  (፩) የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ከተሰሙና ቃላቸውም ከተመዘገበ በኋላ ለክሱ መልስ ተከሳሹ ቃሉን ለመስጠት ፈቃደኛ እንደ ሆነ፤ ፍርድ ቤቱ ይጠይቀዋል።
  (፪) ቀዳሚ ምርመራ የሚያደርገው ፍርድ ቤት ክሱ የሚያሟግት ያለመሆኑንና የተከሳሹን ጥፋተኝነት ወይም ነጻ መሆን በዚሁ በቀዳሚ ምርመራ ፍርድ ቤት ሳይሆን በከፍተኛው ፍርድ ቤት የሚወሰን መሆኑን ለተከሳሹ ይነግረዋል።
  (፫) ቃሉን እንሰዲሰጥ የማይገደድ መሆኑንና በፈቃዱ የሰጠው ቃል ግን በጽሑፍ ሆኖ በማስረጃነት ነገሩ ሲሰማ የሚቀርብ መሆኑን ለተከሳሹ ይነግረዋል።

  ቁጥር ፹፮። ተከሳሹ ስለሚሰጠው ቃል።
  (፩) ተከሳሹ ቃሉን መስጠት ያልመረጠ እንደ ሆነ፤ ነገሩ እንዲሰማ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ያቀርባል።
  (፪) ተከሳሹ ቃሉን መስጠት የመረጠ እንደ ሆነ ቃሉ ተጽፎ ለተከሳሹ ተነቦለት ፍርድ ቤቱ ከፈረመበት በኋላ በመዝገቡ ውስጥ ይቀመጣል።

  ቁጥር ፹፯። ተጨማሪ ምስክሮች።
  ምስክርነታቸው ትክክለኛ ፍርድ ለመስጠት አስፈላጊ መስሎ ከታየው ዐቃቤ ሕግ ያልቆጠራቸውን ምስክሮች ፍርድ ቤቱ በማንኛውም ጊዜ መጥራትና ማስመስከር ይችላል።

  ቁጥር ፹፰። ማስረጃን ስለ መመዝገብ።
  በቍጥር ፻፵፯ በተነገረው መሠረት ማስረጃ መመዝገብ አለበት። እንዲሁም የየአንዳንዱ ምስክር ቃል ለየብቻው በወረቀት ላይ መጻፍ አለበት።

  ቁጥር ፹፱። ነገሩ እንዲሰማ ለፍርድ ቤት ስለ ማቅረብ።
  (፩) ተከሳሹ ቃሉን የሰጠ እንደ ሆነ የሰጠውን ቃል በመዝገብ ከጻፈ በኋላ የቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍርድ ቤት ነገሩን አጣርቶ ክሱን ወይም ክሶቹን ሳይለይ ከሳሹ በከፍተኛው ፍርድ ቤት እንዲቀርብና ነገሩ እንዲሰማ ያደርጋል።
  (፪) ክሱን ወይም ክሶቹን በዚህ ሕግ ከቁጥር ፻፱ እስከ ፻፳፪ በተመለከተው መሠረት ዐቃቤ ሕጉ በሚያዘጋጀው የክስ ማመልከቻ ውስጥ መዘርዘር አለበት።
  (፫) ከዚህ በኋላ ተከሳሹ መጥራት የሚፈልጋቸውን ምስክሮች ዝርዝር እስከ አድራሻቸው እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ይሰጣል።

  ቁጥር ፺። ምስክሮች የሚፈርሙት የራስ ዋስትና ወረቀት።
  (፩) ቀዳሚ ምርመራ በሚያደርገው ፍርድ ቤት የመሰከሩ ምስክሮች ሁሉ በሚጠሩበት ቀን ከዚህ ፍርድ ቤት እንዲቀር ቀዳሚ ምርመራ አድራጊው ፍርድ ቤት የራስ ዋስትና ወረቀት ያስፈርማቸዋል።
  (፪) ማንኛውም ምስክር የራስ ዋስትና ወረቀት አልፈርምም ባለ ጊዜ ፍርድ ቤት ክሱ እስከሚታይበት ድረስ ወይም እቀርባለሁ ብሎ የራስ ዋስትና ወረቀት እስኪፈርም ድረስ በማረፊያ ቤት እንዲቆይ ማድረግ ይችላል።

  ቁጥር ፺፩። ለመዝገብ ቤቶች ሹም የሚላክ መዝገብ።
  (፩) ተከሳሹ ወደ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ነገሩ እንዲታይ ሲላክ ዋናው መዝገብና ለፍርድ ቤት የሚቀርብ ማንኛውም መረጃ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት መዝገብ ቤቶች ሹም ይላካሉ፤ በብዛቱ ወይም በሌላ ምክንያት ለከፍተኛው ፍርድ ቤት መዝገብ ቤት ሹም ለመላክ አስቸጋሪ የሆነ ማንኛውም መረጃ በፖሊስ እጅ ሊቆይ ይችላል።
  (፪) በፖሊስ እጅ የቆዩትን ለከፍተኛው ፍርድ ቤት መዝገብ ቤት ሹም የተላኩትን መረጃዎች የሚገልጽ ዝርዝር ከመዝገቡ ጋራ ይላካል።
  (፫) የከፍተኛው ፍርድ ቤት የመዝገብ ቤት ሹም ከቀዳሚ መርማሪው ፍርድ ቤት የመጣውን መዝገብ ግልባጭ ማድረግና ለዐቃ ሕግና ለተከሳሹ የመስጠት ኃላፊነት አለበት።

  ቁጥር ፺፪። በመዝገቡ ውስጥ ስለሚገኘው ዝርዝር።
  (፩) መዝገቡ ከዚህ በታች የተመለከቱት ዝርዝሮች ይገኙበታል።
  (ሀ) የክሱ መዝገብ ቍጥር፤
  (ለ) ወንጀሉ የተፈጸመበት ቀን፤
  (ሐ) የክስ አቤቱታ ቀርቦ እንደ ሆነ የቀረበበት ቀን፤
  (መ) የክስ አቤት ባዩ እንዳለ፤ ስምና አድራሻው
  (ሠ) የታወቀ እንደ ሆነ፤ የተከሳሹ ስም፤ አድራሻ ሥራውና ዕድሜው፤ ዜግነቱ፤
  (ረ) በክስ ማመልከቻው የተገለጸው ወንጀልና ተገቢነት ያለው ሲሆን ወንጀሉ የተፈጸመበት ንብረት ዋጋና ወንጀሉ የተፈጸመበት ሰው ልዩ ሁኔታ
  (ሰ) ተከሳሹ እንዲያዝ የፍርድ ቤት ትእዛዝ የተሰጠበት ቀን ያለ እንደ ሆነ፤ ወይም መጀመሪያ ተከሳሹ የተያዘበት ቀን፤
  (ሸ) ተከሳሹ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ፍርድ ቤት የቀረበበት ቀን፤
  (ቀ) የዐቃቤ ሕጉ ስምና አስፈላጊ ሲሆን የተከሳሹ ጠበቃ ስም፤
  (በ) ቀጠሮ የተሰጠ እንደ ሆነ፤ ቀጠሮው የተሰጠበት ቀንና ምክንያት፤
  (ተ) ቀዳሚው ምርመራ የተፈጸመበት ቀን፤
  (ቸ) በቀዳሚው ምርመራ ፍርደ ቤት የተሰጠ ማንኛውም ቃል ተከሳሹ የሰጠው ቃል ጭምር፤
  (ኘ) የመከላከያ ምስክሮች ዝርዝር ሊስት፤
  (፪) ለዐቃቤ ሕጉና ለተከሳሹ በሚላኩት የመዝገብ ግልባጮች ላይ እንደ እነዚህ ዝርዝሮች መገት አለባቸው።

  ቁጥር ፺፫። ተከሳሹ በማረፊያ ቤት እንዲቆይ ስለ ማድረግ
  በዋስትና ወረቀት መልቀቅን የሚመለከት የዚህ ሕግ ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ ቀዳሚ ምርመራ ያደረገው ፍርድ ቤት ክሱ እስከፍተኛው ፍርድ ቤት እስኪታይ ድረስ ተከሳሹ ማረፊያ ቤት እንዲቆይ ለማዘዝ ይችላል።

  ምንጭ:
  የ፲፱፻፶፬ ዓ.ም. የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት አዋጅ
 • loader Loading content ...
 • @በህግ አምላክ   3 months ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!

  የ፲፱፻፶፬ ዓ.ም የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ፥ የመክሰስና የምርመራ ሥነ ሥርዐት ፥ ሁለተኛ መጽሐፍ ፥ የመክሰስና የምርመራ ሥነ ሥርዐት ፥ አንቀጽ ፩ ፥ የመክሰስና የምርመራ ሥራ አጀማመር ፥ ምዕራፍ ፩ ፥ የሥነ ሥርዐቱ አጀማመር ፥ ክፍል ፪ ፥ የእጅ ተፍንጅ ወንጀል ክስ አጀማመር።


  ቁጥር ፲፱። እጅ ተፍንጅ የሚባሉ ወንጀሎች።
  (፩) አንድ ወንጀል እጅ ተፍንጅ ነው የሚባለው ወንጀል አድራጊው ወንጀሉን ሲሠራ የተያዘ ሲሆን ወይም ለመሥራት ሲሞክር ወይም የወንጀሉን ሥራ እንደ ፈጸመ ወዲያውኑ የተያዘ ሲሆን ነው።
  (፪) ወንጀል አድራጊው የወንጀሉን ሥራ ከፈጸመ በኋላ ወዲያውኑ ሲሸሽ ምስክሮቹ ወይም ሕዝቡ የተከታተሉት ወይም የሕዝቡ ጩኸትና እሪታ የተሰማ እንደሆነ፤ ወንጀሉ የእጅ ተፍንጅ መሰል እንደሆነ ይቆጠራል።

  ቁጥር ፳። ተመሳሳይ ሁኔታዎች።
  አንድ ወንጀል የእጅ ተፍንጅ ነው ተብሎ በቁ ፲፱ ሊጠቀስ የሚቻለው፤
  (ሀ) ወንጀሉ በተሠራበት ቦታ ወዲያውኑ ፖሊስ የተጠራ እንደሆነ ወይም
  (ለ) ወንጀሉ ሲሠራ ወይም እንደተፈጸመ ወንጀሉ ከተሠራበት ቦታ ላይ የይድረሱልኝ እሪታ የተሰማ እንደሆነ ነው።

  ቁጥር ፳፩። የክስንና የመያዝን ሥነ ሥርዐት አጀማመር ስለሚመለከቱ ውጤቶች፡
  (፩) በቍጥር ፲፱ እና ፳ በተዘረዘሩት ወንጀሎች መሠረት ወንጀሉ የክስ አቤቱታ ሳይቀርብ ክስ ሊቀርብበት የማይችል ካልሆነ በቀር ክስ ወይም የክስ አቤቱታ እንዲቀርብበት አስፈላጊ ሳይሆን ክስ ለማቅረብ ይቻላል።
  (፪) እንደዚህ ያለው ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ ፍርድ ቤት የሚሰጠው የመያዝ ትእዛዝ ሳይኖር በቍጥር ፵፱ እና በተከታታዮቹ ቁጥሮች መሠረት ወንጀለኛውን ለመያዝ ይቻላል።

  ምንጭ:
  የ፲፱፻፶፬ ዓ.ም. የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት አዋጅ
 • loader Loading content ...
 • @በህግ አምላክ   3 months ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!

  የ፲፱፻፶፬ ዓ.ም የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ፥ የመክሰስና የምርመራ ሥነ ሥርዐት ፥ ሁለተኛ መጽሐፍ ፥ የመክሰስና የምርመራ ሥነ ሥርዐት ፥ አንቀጽ ፩ ፥ የመክሰስና የምርመራ ሥራ አጀማመር ፥ ምዕራፍ ፩ ፥ የሥነ ሥርዐቱ አጀማመር ፥ ክፍል ፩ ፥ ክስና አቤቱታ ስለ ማቅረብ።


  ቁጥር ፲፩። ስለ ወንጀል ክስ በጠቅላላው።
  (፩) ማንም ሰው ማንኛውንም ወንጀል ሲሠራ ያየ ወይም ያላየም ቢሆን የወንጀል ክስ እንዲቀርብ ወንጀሉን ለማስታወቅ መብት አለው።
  (፪) ማንም ሰው በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ውስጥ በቍጥር ፪፻፷፯፤ ፫፻፵፬ እና ፬፻፴፰ በተመለከተው መሠረት የተሠራውን ወንጀል የማስታወቅ ግዴታ አለበት።

  ቁጥር ፲፪። ጠቋሚው ሳይታወቅ የሚቀርብ የወንጀል ክስ።
  ካልታወቀ ጠቋሚ የቀረበ የወንጀል ማስታወቅ ከፍ ያለ የሕግ መጣስን የሚገልጽ ሆኖ ወንጀሉ ለመሠራቱ በአካባቢ ሁኔታ የተደገፈና የሚታመን መስሎ የተገኘ እንደ ሆነ በቍጥር ፳፪ እና በተከታዩ በተመለከተው መሠረት እውነትን ለማግኘት ያለዚያም የቀረበውን ክስ ለማረጋገጥ ሥልጣን ባለው ፖሊስ ይመረመራል።

  ቁጥር ፲፫። በክስ አቤቱታ አቅራቢነት ብቻ የሚያስቀጣ ወንጀል።
  በተበዳዩ ወይም ስለተበዳዩ ባለመብት በሆኑ ሰዎች ክስ አቅራቢነት ብቻ በሕጉ መሠረት የሚያስከስሱና የሚያስቀጡ ወንጀሎች ከሆኑ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ውስጥ በቍጥር ፪፻፲፯ እስከ ፪፻፳፪ እና ፯፻፳፩ የተመለከቱት ድንጋጌዎች ተፈጻሚዎች ይሆናሉ።

  ቁጥር ፲፬። የወንጀል ክስ ወይም የክስ አቤቱታ የማቅረብ ሥነ ሥርዐት።
  (፩) ማናቸውም የወንጀል ክስ (ቍጥር ፲፩) ወይም የክስ አቤቱታ (ቍጥር ፲፫) የቀረበለት ሰው በጽሑፍ ከተቀበለ በኋላ የክሱን አቤቱታ ላቀረበው ሰው ተነቦለት ቀኑን ጽፎ ይፈርምበታል።
  (፪) በወንጀለኛ መቅጫ በቁጥር ፪፻፲፱ እንደተመለከተው የወንጀል ክስ ወይም የክስ አቤቱታ አቅራቢዎች ብዙ ሰዎች የሆኑ እንደሆነ ሁሉም በወንጀሉ ክስ ወይም በክስ አቤቱታው ላይ መፈረም አለባቸው።

  ቁጥር ፲፭። ባልታወቀ ሰው ላይ የሚቀርብ የወንጀል ክስ ወይም የክስ አቤቱታ።
  የወንጀል ክስ ወይም የክስ አቤቱታ ያቀረበው ሰው ወንጀለኛውን ለይቶ ለማወቅ ያልተቻለው እንደሆነ፤ ወንጀለኛውን ለይተው የሚያሳውቁትን ልዩ ልዩ ምልክቶች ሁሉ በዝርዝር መስጠት አለበት።

  ቁጥር ፲፮። ክስን ወይም የክሱን አቤቱታን ለመቀበል መብት ያለው ባለሥልጣን።
  (፩) ማናቸውንም የወንጀል ክስ (ቍጥር ፲፩) ወይም ማናቸውንም የክስ አቤቱታ (ቁጥር ፲፫) ለፖሊስ ወይም ለዐቃቤ ሕግ ማቅረብ ይቻላል። አካለመጠን ባልደረሰ ወጣት ላይ የሚቀርብ ክስ ወይም የክስ አቤቱታ በቍጥር ፩፸፪ መሠረት መቅረብ አለበት።
  (፪) የወንጀሉ ክስ ወይም የክሱ አቤቱታ ለዐቃቤ ሕጉ ሲቀርብለት በቍጥር ፳፪ እና በተከታዮቹ ቁጥሮች መሠረት የተባለው ወንጀል እንዲመረመር ዐቃቤ ሕጉ ሥልጣን ላለው ፖሊስ ማስተላለፍ አለበት።

  ቁጥር ፲፯። የወንጀል ክስ ወይም የክስ አቤቱታ መብት ለሌለው ባለሥልጣን ስለ ማቅረብ።
  የወንጀሉ ክስ ወይም የክሱ አቤቱታ ለፖሊስ ወይም ለዐቃቤ ሕግ መቅረቡ ቀርቶ ለአንድ ሰው ወይም ለሌላ ባለሥልጣን ወይም ይህንኑ ጉዳይ ለመቀበል መብት ለሌለው ለፖሊሲ ባለሥልጣን ወይም ለዐቃቤ ሕግ የቀረበ እንደሆነ ይኸው ሰው ባለሥልጣን ወይም ዐቃቤ ሕጉ ሳይዘገይ በቶሎ ጉዳዩ ለሚመለከተው ሥልጣን ላለው ፖሊስ ወይም ዐቃቤ ሕግ ይህንኑ ክስ ወይም የክስ አቤቱታ መላክ አለበት።

  ቁጥር ፲፰። ሐሰተኛ ክስ ወይም ሐሰተኛ የክስ አቤቱታ።
  ሐሰተኛ ክስ ወይም ሐሰተኛ የክስ አቤቱታ ያቀረበ ማናቸውም ሰው በወንጀለኛው መቅጫ ሕግ ቍጥር ፬፻፵፩ እና ፭፻፹ በተመለከተው መሠረት ይቀጣል።

  ምንጭ:
  የ፲፱፻፶፬ ዓ.ም. የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት አዋጅ
 • loader Loading content ...
 • @በህግ አምላክ   3 months ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!

  የ፲፱፻፶፬ ዓ.ም የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ፥ የፍርድ ቤቶች ሥልጣን የዐቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤትና ፖሊስ ፥ አንደኛ መጽሐፍ ፥ የፍርድ ቤቶች ሥልጣን የዐቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤትና ፖሊስ ፥ ምዕራፍ ፩ ፥ የፍርድ ቤቶች ሥልጣን።


  ቁጥር ፬። ወንጀልን ስለሚመለከት ሥልጣን
  (፩) በአንደኛው ሠንጠረዥ በሦስተኛው ዐምድ ሠንጠረዥ የተገለጹት ፍርድ ቤቶች በመጀመሪያውና በሁለተኛው ዐምዶች የተገለጹትን ወንጀሎች ለማየትና ሕጉ የሚያዘውን ቅጣት ለመፍረድ ሥልጣን አላቸው።
  (፪) የፍርድ ሚኒስትር በነጋሪት ጋዜጣ በሚወጣ ትእዛዝ በአንደኛው ሠንጠረዥ ለመለወጥ ወይም ለማሻሻል ይችላል።

  ቁጥር ፭። ስለሚከሰሱ ሰዎች።
  (፩) በወንጀለኛ መቅጫ ቁጥር ፶፫ እንደተመለከተው ዕድሜው ከ፱ ዓመት እስከ ፲፭ ዓመት የሆነ አካለ መጠን ያላደረሰ ልጅ ዕድሜው አካለ መጠን ከደረሰ ሰው ጋር በተከሰሱበት የወንጀል ነገር አብሮ ሊታይ አይቻልም።
  (፪) በወታደር ፍርድ ቤት ሥልጣን የሚታይ ካልሆነ በቀር የጦር ሠራዊት አባልና የሲቪል ሰው አብረው ሊሞገቱ ይችላሉ።

  ቁጥር ፮:። የሥልጣኑ ክበብ።
  ከቍጥር ፺፱ እስከ ፻፯ በተመለከተው መሠረት ፍርድ ቤቶች በተወሰነላቸው ቦታዎች (አጥቢያዎች) የዳኝነት ሥልጣን አላቸው።

  ቁጥር ፯። የይግባኝ ሥልጣን።
  በቍጥር ፻፹፪ በተመለከተው መሠረት ፍርድ ቤቶች ይግባኝ የማየት ሥልጣን አላቸው።

  ምንጭ:
  የ፲፱፻፶፬ ዓ.ም. የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት አዋጅ
 • loader Loading content ...
 • @በህግ አምላክ   3 months ago
  ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!

  የ፲፱፻፶፬ ዓ.ም የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ፥ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት መግቢያ


  ቍጥር ፩/፲፱፻፶፬ ዓ.ም.
  የ፲፱፻፶፬ ዓ.ም. የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት አዋጅ።

  ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፤ ሥዩመ እግዚአብሔር ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ።
  ይህ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት በኛ መሪነት እንዲዘጋጅ አድርገን የሕግ መወሰኛና የሕግ መምሪያ ምክር ቤቶቻችን ስለተቀበሉት።
  በተሻሻለው ሕገ መንግሥታችን ቍ.፴፬ እና ፹፰ መሠረት የሕግ መወሰኛና የሕግ መምሪያ ምክር ቤቶቻችን የመከሩበትን አይተን ቀጥሎ ያለውን አውጀናል።

  (፩) ይህ አዋጅ የ፲፱፻፶፬ ዓ.ም የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል።
  (፪) ይህ የ፲፱፻፶፬ ዓ.ም. የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዐት አዋጅ በተለይ በቍጥር ፩/፲፱፻፶፬ ዓ.ም. ነጋሪት ጋዜጣ ውስጥ ታትሞ በወጣ በሦስተኛው ወር የጸና ይሆናል።

  አዲስ አበባ ጥቅምት ፳፫ ቀን ፲፱፻፶፬ ዓ.ም.
  ጸሐፈ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተ ወልድ፤
  ጠቅላይ ሚኒስትርና የጽሕፈት ሚኒስትር።

  ምንጭ:
  የ፲፱፻፶፬ ዓ.ም. የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት አዋጅ
 • loader Loading content ...
  Load more...
loader Loading content ...

Comments (0)


  This user has no comment yet.