loader

Topics (171)


loader Loading content ...

Explanations (70)


 • @Gosa   1 year ago
  ጎሳ ሰው ነው።
  የአባት ስም ቢኖር ጥያቄው የበለጠ ግልፅ ይሆን ነበር። የሆነ ሆኖ፣ ብላቴን ጌታ ማህተመ ስላሴ ወልደ መስቀል በድሮ ጊዜ የነበሩ ሹማምንትን የፈረስ ስሞች በዘረዘሩበት ቦታ ስለ ደጃዝማች ወንድይራድ ድፋባቸው የሚከተለውን አጭር ገለፃ አስቀምጠዋል።

  ደጃዝማች ወንድይራድ የሸዋ መንዝ ተወላጅ ሲሆኑ የተወለዱበትም ዘመን በ፲፰፻፵፯ ዓ/ም ነው። መጀመሪያ አካባቢ የልዑል ራስ መኮንን ሎሌ ሆነው ሃረርጌ ወረዱ። በኋላ ግን በቅያሜ ምክንያት ወደ ሸዋ ዓጼ ምኒልክ ዘንድ ተመለሱ። ደጃዝማች ወንድይራድ በጊዜአቸው ሃብታም ከሚባሉት ሰዎች አንደኛው ሲሆኑ፣ ጠላት አገራችንን ለመውረር በመጣ ጊዜ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ተከትለው በማይጨው ግንባር ዘምተው በጦርነት ውስጥ በየካቲት ፲፱፻፳፰ ዓ/ም ሞቱ።

  በነገራችን ላይ፣ የደጃዝማች ወንድይራድ ድፋባቸው የፈረስ ስም አባ ንጋት ይባላል።
 • loader Loading content ...
 • @Gosa   1 year ago
  ጎሳ ሰው ነው።
  በያመቱ የገና በዓል በሆነ ቀን ወጣቶች ቡድን ለይተው የገና ጨዋታ መጫወታቸው የተለመደ ባህል ነው። ወጣቶች እስኪደማክማቸው ድረስ ተጫውተው ሲያበቁ በመጨረሻው አሸናፊው ከታወቀ በኋላ "አንተ የቦና በግ" በሚል ርዕስ እንጉርጉሮ ይጀምራሉ። በዚህም ጊዜ የአሸናፊዎቹ ወገኖች በሚከተለው ግጥም አይነት ተሸናፊዎቹን ይሰድቧቸዋል።

  እሽ እነዝንቦ፣ እሽ እንበላቸው ሰውም የለባቸው፤
  ግፋው ግፋው አለኝ እኔ እንደምን ልግፋው፤
  ያንድ በሬ ጨጓራ እንደ ቅል የነፋው።
  እናትህ እውር፣ አባትህ እውር፣ አንተ ድንብርብር፤
  ኧረ ለስንታችሁ የቆረጣል ብትር።
  ይህን የቁም ግብድ ገብዶ ገብዶ፤
  ግማሹን ሙቀጫ ለጌሾ መውቀጫ፤
  ግማሹን ለቅሬ፣ ሲጠጣ ይውላል መቶ ታምሳ አቦሬ።
  የራሱ ውልጮ ያስቀምጣል ዶጮ፤
  የራሱ ገጣባ ያስቀምጣል ጣባ፤
  የብብቱ ሽታ የመንፈቅ በሽታ፤
  የጀርባው መረሬ ያውላል ጥንድ በሬ።

  በገና ጫወታ አይቆጡም ጌታ።

  የጋኔን ዘመድ ነው የይሁዳ ልጅ፤
  እገና ቢገባ ፍጥረቱን ሊፈጅ።
  የይሁዳ ልጅ ነው የጋኔን ዘመድ፤
  ወርውሮ ቢጥለኝ ሊያደርገኝ አመድ።
  ይህን አለኝ ብሎ በደስታ ሊሞት፤
  መላ ቅጥ የሌለው የግመል አንገት።
  በዚህ በቅልጥምህ አትበል እዢው እዚው፤
  እንደ ሰባራ ቅል አንድ አይንህ የሚያዠው።
  አፉ በምን ሰፋ መዛለያ ፈፋ።
  አፉ ቢሰፋበት ደላጎ ጣፈበት።
  አዝግመህ አዝግመህ እማርገጃ ሙት፤
  ማን ይሸከምሃል ይህንን ዳገት።
  ካንድ ጉርዝኝ አሻሮ አይበትን ለዶሮ፤
  ካምስት እንጀራ ገብስ፣ ለውሻም አያቀምስ።
  ካስር ጋን አተላ አይተርፈው ባንኮላ።
  ያንን ይውጥና ይላል በትግያ፤
  የይሁዳ ወንድም የጋኔን መንትያ።
  እግርህ የሸረሪት ሆድህ የንቁራሪት፤
  ቀን እንደጠላሁህ፣ እንዳትመጣ ሌሊት።

  ይህንን በመሰል አነጋገር፣ ባማረ ድምፅ እና ዜማ ተሸናፊዎቹን ይዘልፏቸዋል። እጅግም ስድብ ሲበዛ አምባጓሮ እንዳያነሱ የተቀመጡት ቄሶች እና ሽማግሎች ይጠብቃሉ። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ እየተጣሉ ወገን ለይተው እየተደባደቡ እስከ መፈናከት ይደርሳሉ። ሆንም ፀቡ ቂም ያለው እንዳይሆን ቄሶች ይገዝታሉ።

  ምንጭ፤
  የብላቴን ጌታ ማህተመ ስላሴ ወልደ መስቀል ስብስብ ስራዎች።
 • loader Loading content ...
 • @Gosa   1 year ago
  ጎሳ ሰው ነው።
  ሕጻኑ ሰባት አመት በሞላው ጊዜ የካህን ወገን ሲሆን፣ እዚያው ባቅራቢያው ወዳለ ቤተክርስቲያን ሄዶ ፊደል መቁጠር ይጀምራል። ጠንክሮ ከተማረና ጥቂት አመታት ካሳለፈ በኋላ ዳዊት ደግሞ፣ ዜማ ተምሮ ቅዳሴ ለመቀደስ ይበቃል። ወጣቱም ወደ መንፈሳዊ ተግባር ማዘንበል ስለሚገደድ፣ ከካህናቱ ሳይለይ የሚያደርጉትን እያደረገ ያድጋል። ተዝካር፣ ዝክር፣ ክርስትና ሲሆን አብሮ እየሄደ ይመገባል። ለትምህርት የተለየ ስጦታ ያለው እንድሆነ ባገሩ ውስጥ ወደሚገኙት ታላላቅ ደብሮች ይሄድና ቅኔና ዜማ ይማራል። መፃህፍት ይቀፅላል።

  የትምህርት ጣዕም የማያውቅ ወይም የችግረኛ ቤተሰብ ልጅ የሆነ እንደሆነ፣ በእረኝነት ያድጋል። ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ የመንፈስ ንቃት ኖሯቸው ትምህርት ሲጠማቸው ከናት ካባታቸው ሳይሰናበቱ ጠፍተው ተሰደው የሚማሩ ብዙዎች ናቸው።

  እረኞች ምንም የትምህርት እድል ባይገጥማቸው በዱር በገደል ከብቶቻቸውን በሚያሰማሩበት ሰዓት በተፈጥሮ አስተዋይነታቸው በሚያደርጉት ምርመራና ትናት ከመሬት ውስጥ እንጎችልኝ፣ እንቅርብጭ፣ እንግርግፎ፣ የወፍ ቆሎ፣ የላም ጡት፣ የስንዴ ሊት፣ አደንካሬ፣ የላም ጨው የሚባሉትን ስረ ፍሬዎች። ከዛፍ ላይ ደግሞ እንኮይ፣ ሾላ፣ ኮሽም፣ አጋም፣ ቀጋ፣ ዋንዛ፣ ቁርቁራ፣ ቧቧ፣ የወርካ ፍሬ፣ መሬንዝ፣ ደደሆ እና እነዚህን የመሳሰሉን ፍራፍሬዎች በየጊዜው ተራ በተራ እየለቀሙ በልዩ ልዩ ዘዴ ካዘጋጁ በኋላ ትንቢተ ነክ የሆኑ ነገሮችን በግጥም እያደረጉ ሲዘፍኑ ይውላሉ። ይኸውም "አረቦን" ይባላል። ህዝቡም እረኛው ያለውን ለማወቅ በቅርብ ይከታተላል። የሚበልጠውን ጊዜ የገዢዎችን አስተዳደር እየመረመሩና እያመዛዘኑ ያመሰግናሉ ወይም ይነቅፋሉ። ይህም የህዝብ ድምፅ ነው ለማለት ይቻላል።

  እረኛ ጧት ምሳውን ጭብጦ ወይም አነባበሮ፣ ጢቢኛ ወይም ሽልጦ ይዞ ስለሚሄድ ቀን ወደ ቤቱ አይመለስም። ዳሩ ግን ከደን ሲሳዮች ሌላ፣ የጊዜውን ሁናቴ እየተከተለ በእሸት በወጠላ፣ በእንኩቶ ይጠቀማል። ማታ ማታ ግን እናቱን ለማስደሰት የሰበረውን የማምሻ እንጨት ይዞ ከብቶቹን ነድቶ ሲመጣ እንጎቻ ወይም መክሰስ ይሰጠዋል። እራት እስኪደርስም ከእሳት ዳር ተቀምጦ አሹቅ ወይም ንፍሮ ወይም ደግሞ ቆሎ ይበላል። በዚህ ሁኔታ ጊዜው ያልፍና ከራት በኋላ እግሩን በሙቅ ውሃ ታጥቦ ይተኛል።

  ምንጭ፤
  የብላቴን ጌታ ማህተመ ስላሴ ወልደ መስቀል ስብስብ ስራዎች። 
 • loader Loading content ...
 • @Gosa   1 year ago
  ጎሳ ሰው ነው።
  በአብዛኛው የገጠር አካባቢዎች ሕጻኑ በእግዚአብሄር ፍቃድ እንጂ በሞግዚት አያያዝና ጥበቃ፣ በምግብ፣ በልብስ፣ በመኝታ፣ በፅዳት፣ በህክምና፣ በሌላም ይህንን በመሳሰለው ሁሉ ባለመጓደል በምቾት የሚያድግ አይደለም። ከሁሉ በፊት ምግቡ ጡት ነው። እናቲቱ ብዙ ወተት የማይወጣት ሲሆን ወይም ልጁ እንዲፋፋ ሲፈለግ፣ በተጨማሪ የላም ወተትና አብሽ ይጋታል። የሚጠጣውም ታፍቶት፣ ጥሞት በፈቃዱ ሳይሆን አፍንጫውን እየተያዘ በግድ እንዲውጥ እየተደረገ ነው። በታመመ ጊዜም ያገር መድሃኒተኞች፣ ሽማግሌዎች፣ ባልቴቶች የምች መድሃኒቱን፣ ግጃዋውን፣ ቀበሪቾውን፣ ወገርቱን፣ ዳማከሴውን፣ እንደሆህላውን፣ ጭቁኙን፣ ጤናዳሙን፣ ጥንጁቱን እነዚህን የመሳሰሉትን ሁሉ እንደ ሁናቴው እየተመለከቱ ያደርጉለታል።

  የጉሮሮ ህመም በደረሰበትም ጊዜ ወጌሻ ተጠርቶ ይቧጥጠዋል፤ እንጥሉንም ይቆርጠዋል። ይህ ሁሉ በእግዚአብሄር ኪነ ጥበብ ይፈፀማል እንጂ ተገቢው ፅዳት ኖሮ አይደለም።

  ከዚህም በስተቀር ህዝቡ እግዚአብሄርን በጣም ስለሚወድና ስለሚያከብር በታመመ ጊዜ ማቁረብ፣ ለታቦት መሳል፣ የቅዳሴ ጠበል ማጠጣት፣ ፀሎት ማብዛት ይወዳል። በዚህ አድራጎቱ ፈውስ እንደሚያገኝበት ስለሚያምን ልጁንም በዚሁ መንገድ ያስታምመዋል። ምርጫውም ከመድሃኒት ይልቅ ለመንፈሳዊ ህክምና ስለሆነ እጅግም ሲብስበት ወደ ሩቅ አገር ጠበል ወዳለበት ይዞ ይሄዳል። በዚህ አያያዝ የሚሞተው የበሽተኛ ቁጥር ቀላል ባይሆንም፣ የናት ያባቶች ድካምና ጥረት ተመልክቶ ጥቂጦቹን ለቁም ነገር ስለሚያበቃቸው፣ ለእግዚአብሄር ምስጋናቸውን ከማቅረብ ቸል አይሉም።

  ምንጭ፤
  የብላቴን ጌታ ማህተመ ስላሴ ወልደ መስቀል ስብስብ ስራዎች። 
 • loader Loading content ...
 • @Gosa   1 year ago
  ጎሳ ሰው ነው።
  ብላቴን ጌታ ማህተመ ስላሴ ወልደ መስቀል በቡልጋ አካባቢ የነበረን የክርስትና አነሳስ (ጥምቀት) ስርዐት እንደሚከተለው ያቀርቡታል፤

  የተወለደው ወንድ ሲሆን በአርባኛው፣ ሴት ስትሆን ደግሞ በሰማንያኛው ቀን ጥምቀቱ ይፈፀማል። ወላጅ አባትም ወዳጅ የሆንውን ወይም ጥግ ሊያደርገው የፈለገውን ሰው መርጦ እቤቱ ይሄድና "በሃብተ ውልድና እንድንዛመድ" ብዬ መጥቻለሁና ልጄን ክርስትና ዓንሣልኝ ብሎ ይጠይቀዋል፤ እሱም ዝምድናን ለማጥበቅ የተደረገ መሆኑን በመገንዘብ ፍቃዱን የፈፅምለትና ለቅርብ ዘመዶቹ "እገሌ ልጁን ሠጥቶኛልና እንደዚህ ባለ ቀን ከቤተክርስቲያን ሄዳችሁ እንድታቋቁሙኝ" ብሎ ይነግራቸዋል።

  የልጁም አባት በተራው እንደተቻለው ደግሶ ዘመድ ወዳጁን እንድታቋቁሙኝ ብሎ ይጠራል፤ የክርስትናው እለት ካህናቱ የጥምቀቱን ፀሎት ሲያደርሱ ዲያቆኑ ልጁን ተቀብሎ "አሰግደከ ለአብ፣ አሰግደከ ለወልድ፣ አሰግደከ ለመንፈስ ቅዱስ፤ እኩን ስምከ "እገሌ"" እያለ ሶስት ጊዜ ወደ ምስራቅ ያስጎነብሰዋል። ቄሱም እናት አባቱ የክርስትና ስሙን መርጠውለት እንደሆነ ይጠይቃል፤ ያላዘጋጁ ሲሆን ግን በእለቱ የዋለውን የታቦት ስም አዛምዶ በመጥራት የክርስትና ስሙን ይሰይምለታል።

  ወዲያው የመንፈስ ቅዱስ አባት የሆነው ሰው ይጠራና የህፃኑን አውራ ጣት ይዞ ፀሎተ ሃይማኖትን እንዲደግም ይታዘዛል። የማይችል ሲሆን ዲያቆኑ ስለርሱ ይደግምለታል። ከዚህ በኋላ ቄሱ "ከልጅህ እንዳትለይ ቃለ ሃዋርያት ነው" ብሎ ያወግዘዋል። እሱም "ቃልዎ ይድረሰኝ ከልጄ አልለየውም" ብሎ ያረጋግጣል ከዚህ በኋላ ቄሱ ሶስት አይነት ቀለም ያላቸው ክሮች ገምዶ አንገቱ ላይ ካሰረለት በኋላ ለክርስትና አባቱ የመንፈስ ቅዱስ ልጅህን ተቀበል ብሎ ይሠጠዋል። እሱም ከቤቱ አዲስ ልብስ ወይም ሻሽ ይዞ መምጣት ስላለበት በዚያ ታቅፎ ይቀበለዋል።

  ከደጀ ሰላም ወደ ቤተክርስቲያን እንደገቡም ሕጻኑን ቄሱ ተቀብሎ ቅባ ቅዱስ ይቀባውና መልሶ ይሰጠዋል፤ እሱም በተራው ለናቲቱ ያስረክባል። ስርዓተ ቅዳሴው ከተፈፀመ በኋላ የልጁ አባት የተቻለው እንደሆነ ካህናቱን ይዞ ወደ ቤቱ ይሄዳል፤ ያለዚያ የደንባቸውን ይልካል። አንሺውም ያቋቋሙትን ይዞ ወደ ክርስትናው ቤት ይሄድና ከዚያው ያድራል። ባያድር ግን ታላቅ ነውር ስለሆነ ሁለት ጨው ወይም ሁለት ብር እንደመቀጫ ይከፍላል።

  የክርስትና አባት ኽጻኑን እስኪያድግ ድረስ ልብስ ያለብሰዋል። በዚህ ሁሉ ምክንያት ባንሺውና በህፃኑ ቤተሰብ መካከል የጠበቀ ዝምድና ይኖራል። የተወለደው ወንድ ሲሆን፣ አንሺው ወንድ መሆን አለበት። ሴት ስትሆን ደግሞ ሴት ታነሳታለች። ሆንም ስነ ስርዓቱ አንድ ነው። የክርስትና አባቱ ህፃኑን የሚጠራው በክርስትና ስሙ ነው። አንድ ሰው ብዙም ልጆች ቢወልድ አንሺ የሚሆነው ያው የመዠመሪያው ሰው ነው። አንዳንድ ጊዜ ሴትም ብትሆን ወንዱ ያነሳታል፤ ይህም የቆየ ልማድ ነው።

  አንድ ሰው መካን ሆኖ ሲኖር በስእለት ልጅ የወለደ እንደሆነ ክርስትናውን ለታቦት ይሰጣል፤ ቄሱ ወይም ዲያቆኑ ወንዱን፤ አቃቢቷ ደግሞ ሴቲቷን ልጅ በታቦት ስም ያነሳሉ። ስርዓተ ጥምቀቱ ተፈፅሞ ወደ ቤት መልስ ሲሆን ህፃኑን ማዘል የሚገባት የአንሺው ሚስት ነች። ከቤትም እንደገቡ ልጁን አልቃሽ ወይም አመለኛ እንዳይሆን እየተባለ ከወፍጮ ወይም ከእንጀራ ላይ ያስተኙታል። ሴትም ብትሆን እንደዚሁ ይፈፀማል።

  ምንጭ፤
  የብላቴን ጌታ ማህተመ ስላሴ ስብስብ ስራዎች።
 • loader Loading content ...
 • @Gosa   1 year ago
  ጎሳ ሰው ነው።
  በገጠሪቱ ኢትዮጵያ፣ በተለይም በቡልጋ አካባቢ ያለን የግዝረት ስነስርዓት ብላቴን ጌታ ማህተመ ስላሴ እንደሚከትለው ይገልፁታል፤

  የተወለደው ህፃን ወንድ ሲሆን በስምንተኛው ቀን፣ ሴት ስትሆን ደግሞ በሰባተኛው ቀን መግረዝ የቆየ ልማድ ነው። አገራረዙም የዚህ ስራ እውቀት ባለው ሰው ይፈፀማል። የተወሰነው ቀን ሲደርስ ገራዡ ይጠራል፤ ወዲያውም የጎረቤት ባልቴቶች ይሰበሰቡና ከወጌሻው ጀምሮ እዚያ የሚገኙት በሙሉ ራሳቸውን ቅቤ ይቀባሉ። ከዚህ በኋላ ህጻኑ "የአይን አባት" ተብሎ የሚጠራ አንድ ሰው አማቻችቶ ታቅፎ ሲይዝለት፣ ሸንኮፉን በሰላ ምላጭ ይቆርጠዋል። ወዲያው የልጁ አባት ዶሮ አርዶ ደሙን በቁስሉ ላይ ያፈሳል፤ ህጻኑ ደም እንዳይፈሰውም ዶሶ፣ የእምቧጮ እና የቀረጥ ቅጠል በቅቤ ይታሹና በእራፊ ከተጠቀለሉ በኋላ እሳት ላይ ሞቅ እየተደረገ ቁስሉ ይተኮሳል። ሴት የሆነች እንደሆነም ታቃፊዋ ሴት መሆን አለባት። ስራው እንደተፈፀመ እዚያ ያሉት ሁሉ የተሰናዳውን ገንፎ እንዲበሉ ይጋበዛሉ።

  ለገራዙ ስላገልግሎቱ አንድ ቁና እህል እና አንድ አነባበሮ ይሠጠዋል። ይህም የተለመደና የቆየ ያገር ባህል በመሆኑ፣ ምንም አይነት መሻሻል ሳይደረግበት በትክክል መፈፀም ያለበት ግዴታ ነው። የመግረዙ ተግባር የሚከናወነውም ሕጻኑ ወንድ ሲሆን በወንድ፣ ሴት ስትሆን በሴት ወጌሻ አማካኝነት ነው።

  ከዚህ በኋላ እናቲቱ ችግር የሌለባት ሃብታም የሆነች እንደሆነ በወለደች በሃያ ቀኗ፣ ያልተመቻት ችግረኛ ከሆነች ደግሞ ከዘጠኝ እስከ አስራ አንድ ቀን ውስጥ እደጅ ወጥታ ህፃኑን ፀሃይ ታስመታለች። በምትወጣበትም ቀን፣ የጎረቤት ሴቶች ሁሉ ተጠርተው ገንፎ ይጋበዛሉ። ከዚህ በኋላ ምንም ያህል ሳትቆይ ከናት ካባቷ ተሰነባብታ ልጅዋን ይዛ ወደ ግል ቤቷ ትመለስና የተለመደውን ኑሮዋን ትቀጥላለች።

  ምንጭ፤
  የብላቴን ጌታ ማህተመ ስላሴ ወልደ መስቀል ስብስብ ስራዎች።
 • loader Loading content ...
 • @Gosa   1 year ago
  ጎሳ ሰው ነው።
  ወጣቷ ሴት ፀንሳ ለመውለድ ስትቃረብ፣ የወላጆችን እርዳታ ማግኘት ጠቃሚ ስለሆነ እሷም ቀደም ብላ እናት አባቷ ዘንድ ትሄዳለች። እናቲቱም ወዲያው የገንፎ እህል፣ ተልባ፣ አጃና ዱቄት፣ ሽሮ፣ ድልህ፣ ቅቤ፣ እንዲሁም ማር ታዘጋጃለች። ምጥም በያዛት ጊዜ አዋላጅ የሆነች ሴት ተፈልጋ ትጠራና ካንዲት ሌላ ሴት ጋር ሆና ትይዛታለች። እሷም ከጥጥ መዳመጫ ድንጋይ ላይ ጠቀምጣ ታምጣለች። እናት አባቷ፣ የቅርብ ዘመዶቿ እና ጎረቤቶቿ የሆኑት ሴቶች ሁሉ ተሰብስበው "ማሪያም፣ ማሪያም" እያሉ እየለመኑ ያማምጣሉ። ምጡ የጠነከረባትም እንደሆነ ባልየውን "ሱሪህን ፍታና ወዲያ ወዲህ ተንጎራደድ" ይሉታል። በወለደችም ጊዜ ኽጻኑን አንስተው ራሱን እንደ ማስተካከል እያደረጉ በመሃል እጃቸው ይጫኑታል። ወዲያውም ትኩስ ቂቤና ከቡሃቃ የተወሰደ ሊጥ አፉ ላይ ያደርጋሉ።

  ገና ምጥ ሲጀምራት ገንፎ ማዘጋጀት ደንብ ስለሆነ የተሰበሰቡት ሁሉ ተጋብዘው ይለያያሉ። የተወለደውም ኽጻን ወንድ የሆነ እንደሆነ ስለምስራች ጠመንጃ ይተኮሳል። ባሏም በጣም ከመደሰቱ የተነሳ እንደ አቅሙ ለመታረሻ ከጠቦት እስከ ሙክት ያርዳል።

  ዘመድና ወዳጅ የሆኑ ሁሉ የአራስ ጥሪ እያሉ ከብር እስከ ሩብ፣ ያለዚያም የስንዴና የጤፍ ዱቄት እስከ ሁለት ቁና ወይም አነባበሮ ጋግረው እስከ ክርስትናው ድረስ ያመጡላታል። በክርስትናውም ቀን በተለይ የሚጠሩትም እነዚሁ በወለደች ጊዜ ያራስ ጥሪ ያመጡላት ሰዎች ናቸው።

  ምንጭ፤
  የብላቴን ጌታ ማህተመ ስላሴ ወልደ መስቀል ስብስብ ስራዎች። 
 • loader Loading content ...
 • @Gosa   1 year ago
  ጎሳ ሰው ነው።
  በቡልጋ አካባቢ ወጣቱ ለአቅመ አዳም በደረሰ ጊዜ ወይም ከመድረሱ አስቀድሞ በጋብቻ ለመዛመድ የሚፈለገውን ሰው ከአጥቢያውም ሆነ ከሌላ ቀበሌ በተገኘ ጊዜ ወላጆቹ ለቅርብ ዘመዶቻቸው እና ወዳጆቻቸው ያማክራሉ። እነዚህም መልካም ምርጫ ለመሆኑ ሃሳባቸውን የገለጡ እንደሆነ አማልጅ የሚሆኑ ሰዎች ይመረጡና ወደ ልጅቷ አባትና እናት ይልካሉ። ተለማኞቹም ምንም ጥያቄውን ባይቃወሙና ባይገፉ በልዩ ልዩ ምክንያት ብዙ ጊዜ ደጅ ማሥጠናት የሃገሩ ልምድ ስለሆነ፣ መልስ ለመስጠት እምብዛም አይቸኩሉም። በመቸረሻው ግን እሽታቸውን ካሰሙ በኋላ ጉዳዩ እንደተፈፀመ ያህል ይቆጠርና በቃል ያደረጉትን ንግግር እንደ ውል ፀንቶ ብዙ ጊዜ በመጠባበቅ ይቆያሉ። ሆኖም ዳሪዎቹ በየበኩላቸው ለልጃቸው የጎጆ መውጫ የሆነውን ሁሉ ከማሰናዳት ቸል አይሉም።

  ከዚህም በላይ ልጁንም ሆነ ልጅቷን አባትና እናት በየፊናቸው የወንድ እና የሴት ሙያ ጠንቅቀው ያስተምሯቸዋል። በመጨረሻው የልጆቹ እድሜ ለመጋባት የሚያበቃ ሲሆን ፍጥምጥሙ እንዲደረግ ቀጠሮ ይጠየቃል። በተወሰነው ቀን ሽማግሌዎች ተመርጠው ይላኩና እሸንጎ ሄደው ዋስ ይጠራሉ። ይህ ሁሉ ሲሆን ከቶ አግቢውም ሆነ አግቢዋ መተጫጨታቸውን በፍፁም አያውቁም። ሰርጉ ሲቃረብና ጠመቃው ሲጀመር ግን፣ ያግቢው አባት ልጁን "እሽማግሌ ቤት ጨምረንሃልና ታማኝ ጓደኞችኅን ፈልግ" ብሎ ይነግረዋል። እሱም በባልንጀራነት የመረጣቸውን ሰዎች ካስታወቀ በኋላ ለምክትል ሚዜነት የታጨው በጠመቃው እለት ሄዶ ለልጅቷ አባትና እናት ጨው ሠጥቶ መልሱን ተቀብሎ እንዲመጣ የነገረዋል።

  የሴት አባት አቅማቸውን በመገመት አምስት ሰው ሲል አስር፣ አስር ሲል ሃያ ሆኖ መምጣት የተለመደ ስለሆነ ይህንን ያህል ሆናቹ ኑ ብለው ያስታውቃሉ። ብሰርጉም እለት ሙሽራው የተቻለውን ያህል ያጌጣል፣ በፀዱ ሱሪና እጀ ጠባቡ ላይ ድጉን ደርድሮ፣ ዝናር ታጥቆ፣ ያማረ የቤት ስር ኩታውን ይለብሳል። በላዩም በርኖስ ወይም ካባ ይደርባል። ጠጉሩን ያበጥራል ወይም ራሱን ገርዳሳ ያስራል፣ ባፉ መፋቂያ ይይዛል፤ በእጁም ነጭ ሽቱ (ኣጡምባር) የጨብጣል።

  ሙሽራይቱም በበኩሏ ያላትን ጌጥ ሁሉ ዐውጥታ አምራ ትቆያለች። የቤት ስር ቀሚስ ኩታዋን ከለበሰች በኋላ ካባ ትደርባለች። ሰውነቷን በልዩ ልዩ ቅመም በተዘጋጁ ቅባቶች ታሳምራለች። እግሯን እና እጇን እንሾሽላ ወይም ግርሽጥ ወይም ደግሞ ሂና ስለምትሞቅ ጥፍሮቿ ሳይቀሩ ይቀላሉ። እንደ ጊዜውም ሁናቴ እያየች ጠጉሯን ጎፈሬ ወይም ሹሩባ ታደርገዋለች፣ ወይም ሻሽ ታስራለች። ጥርሷንም እንዲሁም አንዳንዴ ሽፋሏን ትነቀሳለች። ከዚህ በተረፈ ካገሩ ከሚበቅሉ እፅዋቶች የተዘጋጁትን የሚያስደስት ሽታ የሚሰጡትን ወገርት፣ ብርጉድ፣ ቡክቡካ፣ እንግጫ፣ ጠጅ ሳር የመሳሰሉትን መጥነው በማጤስ ትጣጠናለች። በዚህ ሁናቴ ሙሽሮቹ ተዘጋጅተው ሳለ ሰርገኞቹ ከሙሽራይቱ ቤት ይሄዳሉ። የሚያስፈልገው ወግና ልብስ ሁሉ ይያዛል።

  እቤትም በደረሱ ጊዜ ባለቤቶቹ ከበር አንጥፈው ይቀበሏቸዋል። በዚህም ጊዜ "ምነው ምን ሆናችኋል፣ ከበር ቆማችኋል?" ብለው ይጠይቃሉ። እነሱም "ልጅ ታደርጉን ብለን ነው።" ብለው ይመልሳል። ንግግር እና ክርክር አስቀድሞ አልቋልና፣ እጃችሁ ከምን ብለው ተቀባዮች ሲጠይቁ "ከሸማ ጥቅል፣ ከወርቅ እንክብል" ይሉና ያመጡትን የሙሽራ ልብስ፣ ጌጣጌጥ ሁሉ ወጉን በመጠበቅ አቅርበው ያሳያሉ። የሚያሳድርበትን ሃብት ኤንደማሥቆጠሩ መጠን፣ በሴት ወገን ተገዳዳሪው ይነገራል። ርስቱም ሆነ ከብቱ በሚቆጠርበት ጊዜ ተደብቆ ቢቀር ወይም የግል መሆኑ ባይገለጥ፣ በሚፋቱበት ጊዜ ሚስቲቱ መገለል ሳይኖርባት እኩል የመካፈል መብት ይኖራታል። በዚህ አይነት አነሰ ጨምሩ በመባባል ጥቂት ክርክር አድርገው በመጨረሻው ደግሞ ለናት ላባት የሚገባውን ወግ ይጠይቃሉ።

  የሚሰጠውም ለናት ኩታና ቀሚስ፣ ላባት ኩታ ነው። ይህንን ሳይዙ መተው እንደሆነ ዋስ ጠርተው የጎደለውን ይሞላሉ። የጥሎሹ ነገር ካለቀ በኋላ ለአይን ለጥርስ ዋስ ይጠራና ባልየው በጊዜው በነገሰ ንጉስ ስም  ተፈጥሞ እከሊትን በሚስትነት አግብቻለሁ ይላል። የሴት ወገንም ልጃችንን እገሊትን ከእገሌ አጋብተናል ብለው በፈጠም ያረጋግጣሉ። ምንም የሚፈረም ወረቀት ባይኖር የነበሩት እማኞች በቂ ምስክሮች ሊሆኑ ይችላሉ። በተፋቱም ጊዜ ውሉ የሚፈርሰው እንዲሁ እገሌ ይሙት ፈትቻለሁ ሲባባሉ ብቻ ነው።

  ከዚህ በኋላ ወደ ቤት ግቡ ይባሉና የተዘጋጀውን ድግስ ይጋበዛሉ። አግቢው ከሌላ አጥቢያ የሆነ እንደሆን፣ አዳር ገብቶ በማግስቱ ይሄዳል። የዚያው አጥቢያ ሲሆን ግን ምንም ሩቅ ቢሆን ሙሽራይቷ በሚዜዎች ጀርባ ሆና ታዝላ ትጓዛለች፤ ስፍራውም ሩቅ ሆኖ ማዘሉ ቢደክማቸው፣ በፈረስ ትሄዳለች እንጂ በበቅሎ አትቀመጥም ምክንያቱም በበቅሎ የተጓዘች እንደሆነ መካን ሆና ትቀራለች የሚል ስጋት ወይም ተያይዞ የመጣ እምነት ስላለ ነው። ምናልባት ሚዜዎቹ ሙሽራይቱን ከማዘል ቸል ቢሉ፣ የሴት ወገኖች አምባጓሮ ከማንሳትና ከመደባደብ ይደርሳሉ።

  ለሙሽራዋ ከናት ካባቷ ቤት ዳቦ በመሶብ፣ አንድ ትልቅ ልቃቂት ድር፣ ሁለት እንዝርት፣ ጥሬ ጥጥ፣ አንድ ቁርበት ቡሉኮ፣ ባንድ አገልግል ውስጥ ቅቤና አደስ የያዙ የተሸለሙ ቅሎች፣ የጥፍር መቁረጫ ምላጭ፣ መርፌና ወስፌ ይይዙላታል። ከዚህ የተረፈውን የቤት እቃና የሴት መሳሪያ ዱቄት፣ ድልህና ሽሮ ጨምረው አባትና እናቷ በሌላ ቀን እቤቷ ይልኩላታል።

  ሰርጉ በተፈፀመ ማግስት ደግሞ ሚዜዎቹ ከናት ካባቷ ቤት በማለዳ ሄደው የደስታ መግለጫ ቃል የምስራች ያሰማሉ። በዚህም ወላጆቿ በጥንቃቄ በማሳደጋቸውና ክብሯንም ጠብቃ በመገኘቷ ይደሰቱና የምስራች ያሉትን ሚዜዎች እንደየአቅማቸው ይሸልማሉ። 

  ከጥቂት ቀናት በኋላም መልስ ይጠራሉ። በዚህ ጊዜ አግቢው ደህና ሙክት አሲዞ ይሄዳል። እቤት በገቡም ጊዜ የመጣውን ከብት ተቀብለው አርዶ እንዲገባ ሌላ ሙክት ያቀርቡለታል። እሱም ደህና አድርጎ ቆዳውን ስልቻ ማውጣት እና ብልቶቹን በደምብ ማዘጋጀት አለበት።

  የሙሽርነቱ ጊዜ ካለፈ በኋላ ራስን ችሎ መተዳደር ግድ ስለሚለው፣ ሁለቱም በየበኩላቸው ለስራ ይሰማራሉ። ከሁሉ አስቀድሞ የወጣቷን ሙያ ለመመርመር አማቲቷ አንድ ሲካካ ዶሮ ከነ እንቁላሏ ወጥ እንድትሰራ ትሠጣታለች። ብልቷንም በደምብ ማውጣቷን ትቆጣጠራለች፤ እሷም በበቷ ሰልጥና የመጣች ስለሆነች በሚያስደስት አይነት አዘጋጅታ ታቀርብና ትመሰገንበታለች። ከዚህ ቀን ጀምሮ ደምበኛ ኑሯቸው ይጀምራል።

  ያባት የናት ድጋፍ የማይለያቸውም ቢሆን ወጣቱ ባለትዳር ለዘመዶቹም ሆነ ለጓደኞቹ እንዲሁም ላማቶቹ ትጋቱን፣ ብራታቱንና ችሎታውን ለማሳየት ጭምር በቆራጥነት መንፈስ ያመቱን ልዩ፣ ልዩ ወቅቶች በመከተል እና በመጠበቅ የግብርና ተግባሩን ለማከናወን ይዘጋጃል።

  ባቅራቢያው የሚያገኘውን ምንጭ ቆፍሮ ውሃው እንዲጠራቀም ኩሬ ካዘጋጀ በኋላ ችግኝ ያፈላል። የፍሬ አትክልቶችም ሎሚ፣ ትርንጎ፣ ሙዝ እንዲሁም ጌሾና በርበሬ ይተክላል። ቀጥሎም ካባቱ የጠሰጠውን ጉልማ መንትሮ፣ ጨፍልቆ ያወጣል። በሰዓቱም አለስልሶ ካረሰ በኋላ ዘር ይዘራል። እስከ ከሰም ወርዶ ፋልማ ያለማል ይህንን ስራውን በሚያከናውንበት ጊዜ ሁሉ ወጣቷ ሚስቱ እንዲሁ በቤት ያለውን መሰናዶ በደምብ ታደራጃለች። ቁርሱ፣ ምሳው፣ መክሰሱ፣ መቆያው፣ እራቱ በየጊዜው ይቀርብለታል። ጠላውን በሽክናው ታሥጨብጠዋለች።

  ምንም እንኳን ወፍጮ መፍጨት፣ ውሃ መቅዳት፣ እንጀራና ዳቦ መጋገር፣ ውጥ መስራት የተለመደ የዘወትር ተግባሯ ቢሆንም፣ ማታ ማታ ባሏን እራት ካበላች በኋላ ጥጧን አቅርባ ከእሳት ዳር ሆና ትፈትላለች። በቡልጋ ድርና ማጉን ፈትሎ እዚያው በሚገኘው ሸማኔ አሰርቶ ለቤተሰብ አስፈላጊ የሆነውን ልብስ ማዘጋጀት የተለየ የሴቶች ባልትና ነው። በዚህም ጊዜ እንደዚህ ስትል ታንጎራጉራለች፤

  ባሰላው፣ ባሰላው እምቢ አለኝ እንዝርቱ፣
  ከታችም አይደለ ከላይ ነው ጥመቱ።

  ይህንን የምትዘፍነው ከባሏ በተሰብ ስትጋጭና ትካዜ ሲገባት ነው።

  በተጨማሪ ከብት በሚገባበትና በሚወጣበት ጊዜ ታግዘዋለች። በሮች ሲጠመዱ፣ እሱ ሞፈሩን እና ቀንበሩን ሲይዝ እሷ ደግሞ ዘር ታቀብለዋለች። በአረምና በነዶ ማጋዝ ጊዜም ትረዳዋለች። ደክሞት ሲመለስ ሙቅ ውሃ አዘጋጅታ እግሩን ታጥበዋለች። በስራ ቀኖች በዚህ ሁናቴ ሲደክሙ ይሰነብቱና በመጨረሻው ሰንበት ሲገባ እንዳገሩ ስርዓት እነሱም እረፍት ያደርጋሉ። ይህም እንደሚከተለው ይፈፀማል፤

  ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ በመንፈቀ ሌሊት ሁሉም በየቤቱ ከወይራ የተፈለጠ እንጨት የሰንበት እሳት ያነዳል። ባልቴቱ እና ሽማግሌውም ሰንበትን በማክበር፣ ፅድቅ፤ ባለማክበር ኩነኔ የሚመጣ መሆኑን ለምስገንዘብ ሲሉ ቀጥሎ እንደተፃፈው ያለውን ግጥም ብዙዎቹ በማዜም ምህላ በማድረግ ያድራሉ።

  በሰንበት፣ በሰንበት አንድደን እሳት፣
  እንለምንሃለን ማረን መለኮት፤
  በሰንበት፣ በሰንበት በሃዋርያው እለት፣
  የተፈጨ እንጀራ ለምን በላሁት፤
  የተቀዳ ውሃ ለምን ጠታሁት፤
  እንዲያገባኝ ሳውቀው ገሃነመ እሳት።

  ከነጋም በኋላ፣ በጋን የተከተተውን በእንዶድ ታጥቦ ፀድቶ የተቀመጠውን የክት ልብስ ለብሰው እቤተ ክርስቲያን ሄደው፣ ስመው አስቀድሰው ይመለሳሉ።

  ምንጭ፤
  የብላቴን ጌታ ማህተመ ስላሴ ወልደ መስቀል ስብስብ ስራዎች።
 • loader Loading content ...
 • @Gosa   1 year ago
  ጎሳ ሰው ነው።
  ብላቴን ጌታ ማህተመ ስላሴ በድሮዋ መንዝ አካባቢ መልከኛ ማለት ባጭሩ የሚከተለው ነው ብለው ያብራሩታል፤

  መልከኛ፣ እንደ አገሩ ስፋትና እንደ መሬቱ ብዛት ከጉንዶ እስከ ቁና፣ ማር በጋሻ በጋሻው ይቀበላል። ሁዳድም ሲሶ ያሳርሳል። የጉልት አገር ሲሆን አምስት አምስት ቁና እህል ያስፈጫል፤ በበዓል ቀን ቤት ያሰራል፣ አጥር ያሳጥራል፣ ጭነት ያስጭናል፣ ማንኛውንም መልእክት ይልካል፤ በጥቅምት የማር እሸት ይቀበላል፤ በሁለት በሁለት ወር የኮሶ ምሳ እየተባለ በተራ ከየገባሩ ሲካካ ዶሮ ከነ እንቁላሏ ይቀበላል።

  በመልከኝነቱ ያለ ሰው ሁሉ ማንኛውንም ድግስ በደገሰ ጊዜ "የጫንቃ ጠላ" የተባለውን አንድ ገንቦ ጠላ ይልካል። ደግሞ ሙክት ባረደ ጊዜ እግር፣ በሬ ባረደ ጊዜ ደግሞ ታላቅ ይልካል። ሳይወስድ የቀረ እንደሆነ ሁለት ጨው ዳፈን ይከፍላል። መልከኛውም ባጥቢያው በዓል ድግስ ሲደግስ ባገሩ ግብር ያበላል፤ ከብት ማቆሚያ መኖም ይሰጣል።

  ምንጭ፤
  የብላቴን ጌታ ማህተመ ስላሴ ወልደ መስቀል ስብስብ ስራዎች።
 • loader Loading content ...
 • @Gosa   1 year ago
  ጎሳ ሰው ነው።
  ብላቴን ጌታ ማህተመ ስላሴ ጭቃ ሹምን እና የጭቃ ሹምን ማዕረግ እንደሚከተለው ያብራሩታል፤

  ጭቃ ሹም ከገባሮቹ ውስጥ በተራ ላንዳንድ አመት ለዘመን መለወጫ ይሾማል። የጭቃ ሹሙም ስራ ከወረዳው ዱግና ከመልከኛው በታች ሆኖ ከበላይ የሚሰጠውን ያስተዳደር ትዕዛዝ እየተቀበለ ጧት ማት በከፍተኛ ቦታ ጋራ ላይ ሆኖ እየለፈፈ ለህዝቡ ማሰማት ነው። ለመንግስት የሚከፈለውን አስራትና ግብር የሚያስገባውም እሱ ነው።

  የወረዳ ዱግ ሹም ባገር ላይ የመጣ እንደሆነ ህዝቡ መስተንግዶ ምጥን እህል፣ ውሃ እንዲያመጣ ያደርጋል። ለቤተ ክርስቲያንም መገበሪያ የሙጋድ እንጨት፣ የፀሎተ በረድ፣ የአቃቢት ቀለብ ባላገሩን እያዘዘ ያስገባል። በተሾመበት አገር ለማንኛውም ነገር ሃላፊ ስለሆነ በየድግሱ ቤት እየተጠራ በክብር ይቀመጣል።

  አምባጓሮ እና ፀብ ቢነሳም ፀጥታ ጠባቂ እሱ ነው። ባለድግሱ ሳይጠራው ቢቀር ዳፈን ሁለት ጨው ይቀበለዋል። ነገር ግን ተዝካርና ዝክር የሆነ እንደሆነ ጭቃ ሹሙን የሚጠራው ሊቀ ዲያቆኑ ነው። እሱም ሳይጠራው ቢቀር ሁለት ዳፈን ጨው ይከፍለዋል። ድግሱ ቤት ካህናቱ ፀብ ክርክር ቢያደርጉ፣ አፈ መምህሩ መሪጌታቸው ይዳኟቸዋል። ሹማምንቶቹ የተጣሉ እንደሆነ ግን የሚዳኛቸው ጭቃ ሹሙ ነው። ከደጀ ሰላምም እየተጠራ ይገባል፤ በማንኛውም ምክንያት ከብት በታረደ ጊዜ ምላሱ ለጭቃ ሹሙ ይሰጠዋል።

  ጭቃ ሹሙ ትእዛዝ በሚሰጥበት ጊዜ ቃሉን በማቃለል ሃይለ ቃል የተናገረ ወይም የተሳደበ ሰው ቢኖር ከሃያ እስከ ሃምሳ ወቄት ይቀጣል። እንዲሁም ማንንም ሰው የሚሳደብ በጭቃ ሹሙ እየተከሰሰ የተሰደበው ሽማግሌ ከሆነ አስር ወቄት፣ ልጅ እግር ከሆነ አምስት፣ አስቀድሞ ሹም ሆኖ ለተሻረ አስራ አምስት ወቄት ይከፍላል። ምንም ይህ ደምብ ለማስገንዘብ ያህል የተሰራ ቢሆን ህዝቡ በተፈጥሮ ባገኘው አስተዋይነት እርስ በርሱ ከመተሳሰብና ከመፋቀር በስተቀር እምብዛም ህገ ወጥ የሆነ ስራ አይሰራም።  

  ምንጭ፤
  የብላቴን ጌታ ማህተመ ስላሴ ወልደ መስቀል ስብስብ ስራዎች።
 • loader Loading content ...
  Load more...
loader Loading content ...

Comments (16)


 • @Gosa   1 year ago
  ጎሳ ሰው ነው።
  እናመሰግናለን ተፈሪ! አንዴ ታሪኳ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርቦ ሰምቼው ደስ ብሎኝ ነበር። የሌሎች ሰዎችንም ታሪክ እንዲህ ባጭሩ እንደምታቀርብልን ተስፋ አለኝ :)
 • @Gosa   1 year ago
  ጎሳ ሰው ነው።
  እናመሰግናለን @Abebe Haregewoin! እንደ እኔ፣ እንደ እኔ ምላሽህን እንደ አስተያየት (Comment) ሳይሆን እንደ መልስ (Explanation) አድርገህ ብታስገባው አሪፍ ነው እላለሁ። እዚህ ላይ አንድ ሌላ ሲባል የሰማሁት ግጥም የሚከተለው ነው፤

  አቶ ሙሶሎኒ ምን አቅበጠበጠው፣
  አልነገረውም ወይ ካዷ ያመለጠው።
 • @Gosa   1 year ago
  ጎሳ ሰው ነው።
  አስተዋዩ ሽማግሌ አደገኛ ፕሮግራመር ይወጣቸው ነበር በዚህ ዘመን ቢኖሩ :) እናመሰግናለን ውባንተ!
 • @Gosa   1 year ago
  ጎሳ ሰው ነው።
  ሃሃ ... "ፋኖስና ብርጭቆው" ልጅነቴን አስታወሳቹኝ :)
 • @Gosa   1 year ago
  ጎሳ ሰው ነው።
  እውነት ብለሃል! የጫት ጉዳይ ለዚህ መንግስት "ላም ወለደች እሳት፣ እንዳትስመው ፈጃት እንዳትጥለው ልጇ ሆነባት" አይነት ነገር ሆኖበታል :) አቤት እኔ የምኖርበትን ሰፈርማ ያየ ጉድ ነው የሚለው --
 • @Gosa   1 year ago
  ጎሳ ሰው ነው።
  "በትግራይ ክልል" የምትለዋ ተመችታኛለች :)
 • @Gosa   1 year ago
  ጎሳ ሰው ነው።
  እናመሰግናለን ማርታ! በነገራችን ላይ፣ እነዚህ ሶስቱም እቃዎች ሰውን ለመዝለፍ "ያገለግላሉ" :) ለምሳሌ፤
  አበበ፤ አንተ! ያ ሙሉቀን በጣም ከመወፈሩ የተነሳ ድብኝት መስሎልህ አይደል እንደ!
  ከበደ፤ ኧረ እኔ እንደውም ጎተራ ነው የመሰለብኝ :)
 • @Gosa   1 year ago
  ጎሳ ሰው ነው።
  Thank you all!
 • @Gosa   1 year ago
  ጎሳ ሰው ነው።
 • @Gosa   1 year ago
  ጎሳ ሰው ነው።
 • Load more...
loader Loading content ...