loader

Topics (30)


loader Loading content ...

Explanations (34)


 • @አማን   10 hours ago
  Stop waiting for the perfect moment. Take the moment you've and make it perfect.

  ጠቅላይ ሚንስቴር መለስ ዜናዊ ወደ ፖለቲካዊ ትግሉ ከመግባታቸው በፊት መጠሪያቸው ለገሰ ይባል እንደ ነበርና መለስ የሚለውን ስም የወሰዱት ግን በትግል ላይ ሳለ ከተሰዋው የህወሃት አባል እንደሆነ ይነገራል። መለስ ዜናዊ ከአባታቸው ከአቶ ዜናዊ አስረስ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ አለማሽ ገብረ_ልዑል ተስፋማርያም በትግራይ ውስጥ በአደዋ ከተማ ተወለዱ። ስመ_ጥምቀታቸውም ገብረማርያም ይባላል። የትውልድ ዘመናቸውን በተመለከተ አቶ መለስ ግንቦት 1 ቀን 1946 ዓ.ም.፣ ግንቦት 1 ቀን 1947 ዓ.ም.፣ ግንቦት 1 ቀን 1948 ዓ.ም. ተወለድ የሚሉ የጊዜ አቆጣጠሮች በተለያዩ ጋዜጦችና መፅሄቶች ሰፍረው ይገኛሉ። በ1996 ዓ.ም. ታትሞ በወጣው “ዘ-አፍሪካን ኢኮኖሚስት” በተባለው በእንግሊዘኛ እየታተመ የሚወጣው መፅሄት በበኩሉ ሚያዚያ 30 ቀን 1947 ዓ.ም. መወለዳቸውን ፅፏል፡፡


  አቶ መለስ የአንደኛና የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት ተወልደው ባደጉበት በአደዋ ከተማ በሚገኘው በንግሥተ ሳባ ትምህርት ቤት እንደሆነ የተለያዩ መፅሄቶች ፅፈዋል፡፡ በህዳር ወር 1996 ዓ.ም. ታትሞ በወጣው "ኢንፎቴይመንት" መፅሄት የአቶ መለስን የወጣትነት ጊዜ የትምህርት አቀባበል በተመለከተ አባታቸው አቶ ዜናዊ አስረስ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጠ፦ ”ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ትምህርቱን የጨረሰው በግማሽ ሴሚስተር ከኣንዱ ክፍል ወደ ሌላው እያለፈ በአምስት ዓመት ብቻ ነበር፡፡ በ1960 ዓ.ም. የ8ኛ ክፍል ፈተና ወስዶ በ1961 ዓ. ም. ወደ አዲስ አበባ ሄዶ ዊንጌት ትምህርት ቤት ገባና በ1964 ዓ. ም. ማትሪክ ተፈተነ፡፡ በትምህርቱ ከ4ኛ ክፍል ጀምሮ እስኪጨርስ ድረስ ኣንደኛ ነው::“ ብለዋል:: በ1964 ዓ.ም. የማትሪክ ፈተና እንዳለፉ በህክምና ትምህርት ተቋም ውስጥ ገብተው እስከ 1966 ዓ.ም. ሲማሩ ቆይተው ወደ ትግሉ ዓለም ገቡ:: ከዚያም በየደረጃው በመጀመሪያ የህወሃት አባል፣ ቀጥሎም የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል፣ ከዚያም የህወሃት ፖሊት ቢሮ አባልና በመጨረሻም የህወሃት ፀሐፊና የኢህአድግ ሊቀ-መንበር በመሆን ለረጅም ዓመታት ሠርተዋል:: ህወሃት ኢህአድግን በመምራት ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. በትረ መንግሥቱን ከጨበጠ በኋላ እስከ ነሐሴ ወር 1987 ዓ.ም. የሽግግር መንግሥቱ ፕሬዘዳንት በመሆን አገልግለዋል፡፡ ከዚያም በኋላ በነሐሴ ወር 1987 ዓ.ም.፣ በመስከረም ወር 1993 ዓ. ም.፣ በግንቦት ወር 1997 ዓ.ም. እና በመጨረሻም በ2002 ዓ.ም. በተደረጉ ምርጫዎች ፓርላማው በአራት ተከታታይ ምርጫዎች በጠቅላይ ሚኒስትነት እንዲያገለግሉ መርጧቸዋል፡፡አቶ መለስ እስካሁን ባሳለፏቸው የሥልጣን ዘመናት ከጐናቸው የሚቆሙ ጠንካራ አቋም ያላቸው አጋሮች ባያጡም የተቃዋሚዎቻቸው ቁጥርም የበዛ ነው:: ጥንፈኛ አቋም ይዘው የመገንጠል ዓላማ የሚያቀነቅኑ ቡድኖችም ሆኑ አንድነት ወይ ሞት በሚሉ የፖለቲካ ቡድኖች እኩል የነቀፌታ ቅስቀሳ የሚደረግባቸው መሪ ናቸው:: የመበታተን ዓላማ ያላቸው ወገኖች ለመገንጠል እንቅፋታችን መለስ ነው ሲሉ የአንድነት ወገኖች ነን የሚሉት ደግሞ አገራችንን የሚበታትን መለስ ነው ሲሉ የትችት ናዳ ያወርዳሉ፡፡ ሁለቱም ወገኖች ግን ተራውን ዜጋ በአንድነት የሚቀሰቅሱት “መለስ ኤርትራዊ ሆኖ እንዴት ኢትዮጵያን ለመምራት ተቻለው?” የሚለውን ጥያቄ እንደ ትኩስ ርዕሥ መልስው መላልሰው በማንሳት በመጣል ነው::


  አዲስ አበባ ውስጥ ከምርጫ 97 አጀንዳ ጋር በተያያዘ በእያንዳንዱ ሰው የሞባይል መልዕክት ትልቁን ስፍራ ከያዙት የቅስቀሳ ነጥቦች አንዱ “ኤርትራውያንን መለስን እና በረከትን ከሥልጣን ማውረድ አለብን” የሚለው ነበር:: ይህ ቅስቀሳ ይበልጥ የሚያስተጋባው አንድነት በሚፈልጉትም በማይፈልጉትም ወገኖች ነው:: አቶ መለስ በትውልዳቸውም ሆነ በእምነታቸው ተዘርቶ የበቀለ የኤርትራዊነት መንፈስ ይኖር እንደሆነ ለአባታቸው ለአቶ ዜናዊ አስረስም ጥያቄው ቀርቦላቸው ነበር፡፡ አቶ ዜናዊ ሲመልሱ “መለስ ብቻ አይደለም ልጆቼ በሙሉ ኤርትራዊነት አይደለም በደማቸው በአእምሮአቸው ..በአስተሳሰባቸው ውስጥ የለም ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን ናቸው:: ወ/ሮ አለማሽ ራሷ ዓዲኳላ ውስጥ (ኤርትራ) ስለተወለደች ነው እንጂ ኢትዮጵያዊት ነች:: ሲቆጠር ወደ 8ኛ ዘር ኣካባቢ ላይ ብቻ ኤርትራዊነት አለባት፡፡ ይህ ደግሞ በብዙ ሰዎች የሚገጥም የተለመደ ነገር ነው:: ሆኖም ግን ይሄ ነገር የልጆቼን የኢትዮጵያዊነት ስሜት ጥያቄ ውስጥ አያስገባም:: ከወ/ሮ አለማሽ የወለድኳዋቸው ልጆች ስድስት ናቸው:: ስድስቱም ለኤርትራ ስሜት ሊኖራቸው ቀርቶ “ኤርትራ” ብለው እንኳን ስሟን አያነሷትም ነበር፡፡ ከወንዝ ማዶ ነበር የሚሏት፡፡ መለስ አንድም ቀን ኤርትራ ሄዶ አያውቅም ነበር። “ጋዜጦች መለስ ኤርትራዊ ነው ብለው ቢያወሩ ደግሞ ነውር የለውም፡፡ ምክንያቱም ስልጣን ላይ የወጣና ሃብታም ሰው ሁሌም እንደታማና ስም እንደወጣለት ነው:: ስለዚህ አይደለም ይህ ትንሽ ፍንጭ ያለው ቀርቶ በሬ ወለደ የሚል አይነት ወሬ የሚፅፉም ስላሉ በሁኔታው ምንም አይመስለኝም:: መለስ ቅንጣት ታክል የኤርትራዊነት ስሜት የለውም ሊኖረውም የሚያስችለው ምክንያትና ታሪክም የለውም” ብለዋል፡፡ አቶ ዜናዊ ከላይ ከተናገሩት መካከል “ስልጣን ላይ የወጣና ሃብታም ሰው ሁሌም ስም እንደወጣለት ነው” ሲሉ አፅንዖት የሰጡት ቀደምት ታሪኮቻችንን ዘወር ብለን እንድንፈትሽ የሚጠቁመን ነው:: ካለፉት መሪዎቻችን ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን እንደምሳሌ ብናነሳ ተመሣሣይ ቅስቀሳ ይደረግባቸው ነበር፡፡ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ልዑል መኰንን አይወልጿቸውም፡፡ አባታቸው ለዘመቻ በሚንቀሳቀሱ ጊዜ ከውጭ አገር ነጋዴ ነው እናትየዋ የወለዷቸው እየተባለ ዘመቻ ተካሂዶባቸዋል፡፡ ወሬው ንጉሠ-ነገሥቱን በማጥቃት ላይ ሳይገታ ቀጥለው በትረ-መንግሥቱን ይወርሳሉ የተባሉትን አልጋወራሽ አስፋወሰንንም የልጅ ኢያሱ ልጅ እንጂ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ልጅ አይደሉም" እየተባለ ተቀስቅሶባቸዋል፡፡ በሌሎች መሪዎች በልጅ ኢያሱ፣ በንግሥት ዘውዲቱ፣ በአፄ ምኒልክና በኋላም በኲሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ከትውልድ ጋር የተያያዙ ተመሣሣይ ቅስቀሳዎች ነበሩ፡፡ ኣቶ መለስ “ኤርትራዊ ናቸው” የሚለው ቅስቀሳ ከኢትዮጵያ ትውፊታዊ ፖለቲካ ጋር ቁርኝት ይኖረው ወይም አይኖረው እንደሆን ይህም የጎዳን ወይም የጠቀመን ኣካሄድ እንደሆነ መመርመር ያስፈልጋል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡


  የጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊን ዝንባሌና ተሰጥኦ በተመለከተ አንዳንድ ወገኖች ግልፅና ማንኛውንም ችግር ፊት ለፊት የመጋፈጥ ልማድ እንዳላቸው ሲገልፁ ሌሎች ደግሞ የትኛውንም ክስተት በጥልቀት የሚመረምሩና በባህሪያቸውም ድብቅ እንደሆኑ አስተያየት ይሰጣሉ፡፡ በፖለቲካዊ ኣስተሳሰብ የመረረ ቅራኔ ያላቸው አቶ አረጋዊ በርሄ በጥቅምት ወር 1989 ዓ.ም. ታትሞ ከወጣው “ጦቢያ” መፅሄት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ወደ ትግሉ ከገቡበት ጊዜ አንስቶ አቶ መለስ ብዙ መፅሃፍትን የማንበብና የመከራከር ልማድም እንዳዳበሩ መስክረዋል፡፡ በ1989 ዓ.ም. ኤርትራ ውስጥ የታተመው "ሕውየት” መፅሄት ከጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ጋር ባደረገው ቃለ-ምልልስ አምድ ላይ እንደመንደርደሪያ ይህን አስተያየት አስፍሯል፡፡ “ገና መጀመሪያ እንዳየኸው የሚመስጥህ ነገር ቢኖር ወጣትነቱ ነው:: ትህትናው ደግሞ እጅግ የበዛ ነው:: ስትጠይቀው እያንዳንዷን ቃል በቅርብ ይከታተላታል መልሱ ታዲያ ያረካሃል:: ያለቦታዋ የምትገባ አንዲትም ቃል አትኖርም:: የአዲስ አበባ ልጆች ”መልስ በኪሱ“ ይሉታል፡፡ ጥያቄዎችህን በጆሮው ሳይሆን በልቡ ይሰማቸዋል:: እናም ደግሞ በልሣኑ ሳይሆን በልቡ ይመልሳቸዋል” ብሏል:: በዚህ መፅሄት ሃተታ የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸው ሳይቀሩ አንስማማም የሚሉበት ሰበብ እንደማያገኙ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ከላይ እንደተገለፀው አቶ መለስ በንግግራቸው የታዳሚውን ስሜት የመግዛ ትችሎታ ያላቸው ሲሆን ብዙ ጊዜ በአደባባይ ሲናገሩ በፅሁፍ የተዘጋጀውን ከማንበብ ይልቅ ከያዙት ርዕሠ-ጉዳይ ሳይወጡ በቃላቸው ረጅም ጊዜ የመናገር ችሎታ አላቸው፡፡ የንግግር ችሎታቸውን የሚያሳዩት በአማርኛ ቋንቋ ብቻ ሳይሆን በትግሪኛና በእንግሊዘኛም እኩል ተደናቂነትን ያተረፉ ናቸው:: በፖለቲካዊ ታሪካቸውም ሆነ በግላዊ ባህሪያቸው አቶ መለስን ድብቅ ኣድርገው የሚያ ቀርባቸው ደግሞ የድሮው የትግል አጋራቸው አቶ አብርሃም ያየህ ናቸው:: ግንቦት 1992 ዓ.ም. ታትሞ በወጣው የኤርትራ ትግል ከየት ወዴት ግምገማ በተባለው መፅሃፍ አቶ አብርሃም ያየህ ይህን አስፍረዋል፦ “የመለስን ማንነት ለማወቅ ኢትዮጵያዊ መሆን አይበቃም:: በአደዋ ከተማ ካሉት አምስት ሰበካዎች ውስጥ እኔና መለስ ተወልደን ባደግንበት በደብረብርሃን ሰበካ ኗሪ መሆንም ብቻ አይበቃም:: መለስና መለስን ያሣደጉ ሰዎችን ማንነት ለማወቅ፣ ከነዚህ ሰዎች ጋር በሁለት መቶ ሜትር ቅርበት፣ በጉርብትና መኖርንና እንደ እኔ የአገሩንና የአካባቢውን ሰዎች ማንነት ለማወቅ ምክንያት ከነበራቸው ቤተሰቦች ስር ማደግን ይጠይቃል:: መለስንና የመለስን ማንነት በቅርብ ስለማውቅና ከዚህም የተነሣ የሰውየው ተልዕኮ ምን እንደሆነ በትክክል ስለምረዳም ነው ከሻዕቢያ በፊት መለስን እናስወግድ እያልኩ የምማጠነው” ብለዋል፡፡ የአቶ መለስን የአገር ውስጥ ፖለቲካዊ ተግባርና የውጭውን ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ በተመለከተ እንዲሁ የተለያዩ አስተያየቶች ይንፀባረቃሉ፡፡ ላዕላይ ፖለቲካዊ እውነታዎች ላይ የሚያተኩሩት የአንድነቱ ጐራ ደጋፊዎች አቶ መለስን በሚከተሉት ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ምክንያት አገራችን ለመገነጣጠል አደጋ ተጋልጣለች ይላሉ:: የመገንጠል ፖለቲካን እንደመጨረሻ ግብ አድርገው የሚታገሉ ሌሎች ወገኖች ደግሞ በእርግጥ አቶ መለስ “የራስን እድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል ድረስ” መመሪያ ከልባቸው ቢያምኑበት ኑሮ እስካሁን ነፃነታችንን በተጐናፀፍን ነበር ሲሉ ይናገራሉ።  እንደነዚህ ወገኖች እምነት “የራስን እድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል ድረስ” በተግባር ሊተረጉም የማይችል አዲሱ ስልት አዘል የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት አካሄድ ነው በማለት የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ኣስተዳደር ያማርራሉ፡፡ የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ተንትነው ለማስረዳት ሙያቸው የሚፈቅድላቸው ወገኖች ደግሞ መለስ የጠላትን ቁጥር ቀንሶ የወዳጅን ቁጥር በማብዛት መርህ ላይ ተመስርተው የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት በጥንቃቄ ይዘው የማራመድ ብቃት ያላቸው መሪ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ በጠቅላላው የጠቅላይ ሚኒስትር መለስን ፖለቲካዊ ቀመር በተመለከተ ደጋፊዎቻ ቸውና ነቃፊዎቻቸው በሁለት ተፃራሪ ጐራዎች በመሰለፍ ድምዳሜ ላይ የሚያደርሱ አውራ ሃሳቦችን ይሰነዝራሉ፡፡ እንደ ደጋፊዎቻቸው እምነት መለስ ለዘመናት የተከማቹ ችግሮችንና ውስጥ ለውስጥ ሲርመሰመሱ የኖሩ አሉታዊ አመለካከቶችን ወደ አደባባይ አምጥቶ እርስ በእርሳቸው የማፋለምና ህልውናቸውን አክስሞ የማለፍ ስልት ይከተላሉ፡፡ ተቀናቃኞቻቸው በአንፃሩ መለስ የቆዩ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊና ማህበራዊ ችግሮች ተባብሰው እንዲቀጥሉ የማድረግ ስልት ይከተላሉ ሲሉ ይወቅሟቸዋል፡፡ አባታቸው አቶ ዜናዊ አስረስ በአንድ ወቅት ስለአቶ መለስ አመራር ተጠይቀው ሲመልሱ “... እኔ ልጄ ስለ ሆነ ሳይሆን ስለእውነት እስካሁን ድረስ ያለው ታሪኩ የሚናቅ ነው አልልም:: ገንዘብ አለመውደዱ አንድ ትልቅ ታሪክ ነው:: በሥልጣን አለመስከርም ሌላ ትልቅ ታሪክ ነው:: ትምክህተኛ አለመሆንም ሌላ ትልቅ ታሪክ ነው:: እና እኔ በግሌ በነዚህ ሶስት ነገሮች መለስን አመስግነዋለሁ” ብለዋል፡፡


  የሁለተኛውን ሺ መደምደሚያ ምክንያት በማድረግ በዘመን መለወጫ ዋዜማ ላይ ኣቶ መለስ ባደረጉት ንግግር ዘመኑ የኢትዮጵያ ህዳሴ እንደሚሆን ገልፀው በዚህ ዘመን ጥይት መተኮስ ብቻ እንደማይበቃ አሳስበዋል:: አያይዘውም ዜጐች እራሳቸውን እያስተማሩ የእውቀት ደረጃቸውን ከፍ ማድረግ፣ መቆጠብ፣ አዳዲስ የሥራ መስኮችን መክፈት ድህነትን ለማጥፋት ኣዲሰ የውጊያ ስልት መሆኑን አውቀው እንዲንቀሳቀሱ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡ በመላ አገሪቱ ከሚገኙ ታላላቅ ባለሥልጣናት መካከል ኣቶ ፀጋዬ በርሄ፣ አቶ እስማኤል አሊሴሮ፣ አቶ አያሌው ጐበዜ፣ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ አቶ አብዱላሂ ሐሰን፣ አቶ ያረጋል አይሸሹም፣ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ አቶ ሙራዱ አብዱላሂና ኣቶ ዑባንግ ዑመድ ከየክልላቸው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር በመነሳት ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጋር የሚመሳሰል ንግግር አድርገዋል፡፡ "ለመጭው ትውልድ ልማትን እንጂ ልመናን አናወርስም” በሚል መፈክር በተደጋጋሚ ያሰሙ የነበሩት መለስ በዘመናቸው የትምህርትን፣ የጤናን፣ የመጓጓዣ አውታሮችንና የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ግድቦችን አብዝተው እንዲገነቡ በማድረግ የራሣቸውን ሚና እንደተጫወቱ የሚመሰክሩላቸው ብዙ ናቸው፡፡ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም. የታላቁን የህዳሴ ግድብ መሠረት ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ባለው የአባይ ወንዝ ዳር ተገኝተው በጣሉበት ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ያሰሙት ንግግር የበርካታ ኢትዮጵያውያንን አካልና መንፈስ የተቆጣጠረ እንደነበር ይታወሳል፡፡ መለስ ኢትዮጵያን በመሩባቸው ዘመናት ብዙ ፈተናዎች ያጋጠማቸው ሲሆን የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት፣ የድርጅታቸው የመሰንጠቅ አደጋና የ1997 ዓ.ም. የድህረ ምርጫ ብጥብጦች በአስጨናቂነታቸው ግንባር ቀደሙን ሥፍራ እንደሚይዙ ከሰጡት አስተያየት መረዳት ተችሏል፡፡


  አቶ መለስ በ2004 ዓ.ም. ወደመጨረሻ ወራት ሁኔታቸው ለህዝብ ሳይታወቅ ከአደባባይ ርቀው ቆዩ፡፡ በመሃሉ ግን ታመው ህክምና ላይ መሆናቸው ተሰማ፡፡ እስከዚህ ጊዜ ድረስም ሆነ በኋላም የአቶ መለስ ህመም በትክክል ምን እንደሆነ ይፋዊና መንግሥታዊ መግለጫ አልተሰጠም፡፡ በይፋ የተነገረ ነገር ቢኖር በዕረፍት ማጣት ምክንያት ታመው ሆስፒታል መግባታቸው ብቻ ነው። የደም ካንሰር፣ ስትሮክ፣ የጭንቅላት ቲውመር እና የአንጀት ካንሰር እየተባለ በተለያዩ ወገኖች በሰፊው ቢወራም ከሃኪሞቻቸው ግን የተሰጠ ማረጋገጫ የለም፡፡ ተባራሪ ወሬዎች በየአቅጣጫው ሲስተጋቡ ቆይተው ነሐሴ 15 ቀን 2004 ዓ.ም. ጧት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በውጭ አገር ህክምና ሲደረግላቸው ቆይቶ ማረፋቸው ይፋ ሆነ፡፡ በዚያው ዕለት ማታም አስከሬናቸው በቤተሰቦቻቸው ታጅቦ አዲስ አበባ ሲገባ የከተማው ህዝብ በነቂስ ወጥቶ አቀባበል አደረገላቸው፡፡ መንግሥት አቶ መለስ መሞታቸውን ከተናገረበት ዕለት አንስቶ የብሄራዊ ሃዘን ቀን አወጀ፡፡ ከከተማው አልፎ ከመላ አገሪቱ የሚመጣው ህዝብም አስከሬኑ ባረፈበት በመኖሪያ ቤታቸው እየተገኘ ሃዘን እንዲገልፅ ሲደረግ ቆይቶ ነሐሴ 27 ቀን 2004 ዓ.ም. የውጭ ኣገር መሪዎችና መልዕክተኞች፣ የአገር ውስጥ ባለስልጣናት፣ ታዋቂ ሰዎችና ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ-ክርስቲያን ሥርዓተ-ቀብራቸው ተፈፅሟል። በመስቀል አደባባይ በተደረገ የመጨረሻ ስንብት የአገር ውስጥና የውጭ አገር ተወካዮች ተራ በተራ ንግግር አድርገዋል። ከኢትዮጵያ ወገን ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሣለኝ፣ ወ/ሮ አዜብ መስፍንና የአቶ መለስ የሥራና የትግል አጋር የሆኑት አቶ አዲሱ ለገሠ ታሪካዊ ንግግር አድርገዋል። ከውጭ ከመጡ እንግዶች መካከል ደግሞ የኬኒያው መሪ ምዋይ ኪባኪ፣ የደቡብ ሱዳን መሪ ሳልቫ ኬር፣ የሱዳኑ መሪ ኦማር ሐሠን አልበ ሽር፣ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዘዳንት ጃኮክ ዙማ፣ የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ-መንበርና የቤኒን ፕሬዘዳንት ያያ ቦኒ፣ በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ፣ የአውሮፓ ህብረት መልክተኛና የተባበሩት መንግሥታት ፀሐፊ ንግግሮች ተደምጠዋል። ያልተጠበቀው የአቶ መለስ ድንገተኛ ሞት መላው ኢትዮጵያውያንን ከትልቅ ሃዘን ውስጥ የከተተ ነበር፡፡ ብሄረሰብ፣ ፆታ፣ ዕድሜና ሃይማኖት ሳይለዩ ኢትዮጵያውያን በእጃቸው የጨበጡት ተስፋ ሁሉ እንደ ጉም በኖ እንደጠፋባቸው በመቁጠር ያለማቋረጥ እንባቸውን እየተራጩ ሃዘናቸውን ገልፀዋል። ሁለቱንም ክስተቶች ጠንቅቀው የሚያውቁ ወገኖች የአቶ መለስ ሃዘን ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ልጅ ከልዑል መኮንን ኃይለሥላሴ የልቅሶ ሥርዓት ጋር ተመሳይነት እንደነበረው ሲናገሩ ተደምጠዋል። ቅኔዎች ተዘርፈዋል፣ መዝሙሮች ተዘምረዋል፣ የሃዘን እንጉርጉሮዎች ሁሉንም መገናኛ ብዙሃን አጣበው ከርመዋል።


  ጠቅላይ ሚንስቴር መለስ ዜናዊ የትዳርና የትግል አጋራቸው ከሆኑት ከቀዳማይ እመቤት አዜብ መስፍን ስምሃል መለስ፣ ሰናይ መለስ እና ማርዳ መለስ የተባሉ ሁለት ሴቶችና አንድ ወንድ ልጆችን አፍርተዋል።


  ምንጭ፦ ታሪካዊ መዝገብ_ሰብ

 • loader Loading content ...
 • @አማን   2 days ago
  Stop waiting for the perfect moment. Take the moment you've and make it perfect.

  ኰሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ግንቦት 19 ቀን 1933 ዓ.ም. አዲስ አበባ ውስጥ አራዳ ጊዮርጊስ አካባቢ ከአባታቸው ከአቶ ኃይለማርያም ወልዴ እና ከእናታቸው ወ/ሮ ብዙነሽ ወልደአማኑኤል ተወለዱ፡፡ አባታቸውም ሆኑ እናታቸው የሸዋ ሰዎች ናቸው:: የእናታቸው የትውልድ ሥፍራ ተጉለት ሲሆን የአባታቸው ደግሞ በደቡብ ምዕራብ አዲስ አበባ አቅጣጫ በሚገኘው ረጲ በተባለው አካባቢ ነው:: የሌተና ኰሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ትዝታዎች በተባለው መፅሃፍ ውስጥ እራሳቸው ኰሎኔል መንግሥቱ ተጠይቀው እንዳብራሩት "መንግሥቱ" የሚለው ስም የወጣላቸው የጣሊያን የወረራ አገዛዝ አብቅቶ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደገና ተቋቁሞ የአንድ ወር ጊዜ እንኳን ሳይቆዩ የመወለዳቸው ያንን ታሪካዊ ክስተት ለማስታወስ ሲባል ነው:: ከህይወት ታሪካቸው ለመረዳት እንደሚ ቻለው የአባታቸው አባት አቶ ወልዴ አያና የገበሬ ሠራዊት ነፍጠኛ ነበሩ፡፡ የእናታቸው አያት ወልደአማኑኤል ጐርፍነህ እንዲሁ በአፄ ምኒልክ ዘመን የገበሬ ሠራዊት አለቃ ነበሩ፡፡ የወልደአማኑኤል ሁለት ታላላቅ ወንድሞቻቸው ደግሞ አድዋ ዘምተው ሲዋጉ በጦር ሜዳ ወድቀዋል:: የእናታቸው አጐት አስፋው ወልደአማኑኤልና የእናታቸው ታናሽ ወንድም ድረስልኝ ተሰማ በጣሊያን ዘመን በአርበኝነት ሠርተዋል፡፡ እናታቸውም እንዲሁ ለአጐታቸው በድብቅ ስንቅ፣ ትጥቅና መረጃ በማቀበል በውስጥ አርበኝነት ተሣታፊ መሆናቸውን ኰሎኔል መንግሥቱ አስረድተዋል፡፡ የኰሎኔል መንግሥቱ እናት በመጀመሪያ ኪዳኔ ተፈራ ለተባለ የእናዋሪ ማርያም ቄስ ልጅ ተድረው ነበር፡፡ ነገር ግን በውስጥ አርበኝነት ተሳትፎ እንዳላቸው ጣሊያን ሰምቶ የአካባቢውን ቤቶች ማቃጠል ስለ ጀመረ በወላጆች ግፊት ባላቸውን ፈተው ወደ አዲስ አበባ ሄደው ወ/ሮ ታጠረች ውቤ ከተባሉ አክስታቸው ጋር መኖር ጀመሩ። በዚህ ጊዜ ነው የኰሎኔል መንግሥቱ እናትና አባት የተገናኙት:: የሰውም ሆነ የፅሁፍ ማስረጃዎች እንደሚያረጋግጡት የኰሎኔል መንግሥቱ አባት ከአክስታቸው ጋር የሚኖሩትን እናታቸውን ያገቡት በጠለፋ ነው:: ለእናትና ለአባታቸው ኰሎኔል መንግሥቱ የመጀመሪያ ሲሆኑ ከእሳቸው በታች አመለወርቅ ኃይለማርያም እና ጌታሁን ኃይለማርያም የሚባሉ ልጆችም ተወልደዋል፡፡ ከኰሎኔል መንግሥቱ የዘር ሀረግ ጋር በተያያዘ በየጋዜጦችና መፅሄቶች አልፎ ተርፎም በመፅሃፍት ሳይቀር እየተፃፈ ሲነበብ የኖረ ታሪክ አለ፡፡ ይህም ኰሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እና ከዚያም ቀደም ብሎ በንግሥተ– ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ ዘመነ-መንግሥት ትልቅ ሥፍራ የነበራቸው የደጃዝማች ከበደ ተሰማ የልጅ ልጅ ናቸው እየተባለ ሲነገር እና ሲፃፍ የኖረው ታሪክ ነው:: የተፃፈውና ሲነገር የኖረው ታሪክ እንዲህ የሚል ነው:- "ደጃዝማች ከበደ ተሰማ በንግሥተ–ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ ዘመነ-መንግሥት የኰሎኔል መንግሥቱን እናት ከቤት ሠራ ተኛቸው ይወለዳሉ:: ለልጅቱም እውቅና በመስጠት ያሳድጓታል:: በጦርነቱ ዘመንም ደጃዝማች ከበደ ወደ ውጭ ሲሄዱ ሌሎች የቤተሰብ አባሎቻቸውን ወደተለያዩ የሰሜን ሸዋ አካባቢዎች ሲልኳቸው ወጣቷን የኰሎኔል መንግሥቱን እናት ወደዘመድ ያስጠጓ ታል። እነዚያም ዘመዶች ባል ያጋባታል። አጋጣሚው ባይታወቅም ጣሊያን ከገባ ሁለት አመት ያህል እንደሞላው ወደ አዲስ አበባ ትመለሳለች:: አዲስ አበባ ከዘመድ ጋር ስትኖር ነፃነት ከመመለሱ አንድ አመት ቀደም ብሎ በጣሊያን መሥሪያ ቤት ያገለግሉ የነበሩት ኃይለማርያም ወልዴ ወጣቷን የኰሎኔል መንግሥቱን እናት ጠልፈው ያገባታል፡፡ ነፃነት በተመለሰም ጊዜ ኰሎኔል መንግሥቱ ተወለዱ:: ደጃዝማች ከበደም አዲስ አበባ እንደገቡ የልጃቸው ባለቤት ኃይለማርያም ወልዴን አስጠርተው ከእንግሊዝ ወታደራዊ መኰንኖች ጋር አስተዋውቀው የመሣሪያ ጥገና ትምህርት እንዲያገኙ አድርገው የውትድርና ሙያን እንዲቀላቀሉ አደረጉ" ይላል::


  በ1994 ዓ.ም. ታትሞ በወጣው በትዝታዎቻቸው ላይ በሚያተኩረው መፅሃፋቸው ግን ከደጃዝማች ከበደ ተሰማ ጋር አንዳችም ዝምድና እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ ኰሎኔል መንግሥቱ በቃለ-መጠይቃቸው እንዳስረዱት አንድ ወቅት በትንሽ ጥቆማ ሰውን ማሰር ስለተበራከተ ጀኔራል ግዛው በላይነህ፣ ጄኔራል ጌታቸው ናደው፣ አቶ ይድነቃቸው ተሰማና ደጃዝማች ከበደ ተሰማ እንዲታሰሩ ጥቆማ በመጣ ጊዜ አይታሰሩም ብለው በመከራከራቸው ነው ልጃቸው የተባለው ይላሉ፡፡ በዚያን ጊዜ ደጃዝማች ከበደ ተሰማ እንዲታሰሩ ጥቆማ ያደረገባቸው የሳቸው ልጆች በተማሪነት ዘመኑ ይረዱት የነበረውና በኋላ ከደርግ አባላት አንዱ የነበረው ኰሎኔል ደምሴ ዴሬሳ መሆኑን ይጠቅሳሉ:: ደጃዝማች ከበደ እንዲታሰሩ ሃሣብ አቅርቦ በሁሉም የደርግ አባላት ውድቅ በተደረገበት ምሽት ኰሎኔል ደምሴ ዴሬሳ ማምሻውን ደርግን ከሚቃወሙ የፖለቲካ ቡድኖች ጋር በመመካከር "መንግሥቱ ኃይለማርያም የከበደ ተሰማ ልጅ ነው" የሚል ወረቀት አባዝተው በቤተ-መንግሥቱ በመበተን ሃሣብ የማስለወጥ ሙከራም አድርገው እንደነበር አብራርተዋል:: ኰሎኔል መንግሥቱ ከደጃዝማች ከበደ ተሰማ ጋር ምንም ዝምድና እንደሌላቸው ቢናገሩም ግን ልጃቸው ካሣ ከበደ የወንድም ያህል ቅርብ ጓደኛቸው እንደነበር ጠቅሰው ይህም መቀራረብ ልጃቸው ነው ለመባል የራሱ አስተዋፅኦ ሊኖረው እንደሚችል ይናገራሉ::


  ከላይ ከቀረቡት ሃሣቦች ያልወገኑ ወገኖች ደግሞ ኰሎኔል መንግሥቱና ከሣቸው በተቃራኒ ያሉ ወገኖች ባቀረቧቸው ታሪኮች መካከል ጥርጣሬ ውስጥ የሚከቱ ጉዳዮች መኖራቸውን ይጠቅሳሉ:: በሁለቱም ታሪኮች የኰሎኔል መንግሥቱ ወላጆች የተገናኙበት አጋጣሚ ተመሳስሎ ያሳያሉ፡፡ የኰሉኔል መንግሥቱ አባት ወደ ውትድርናው ዓለም የገቡበትንም ሁኔታ በተመሳሳይ ያሳያሉ። ከዚህም ባሻገር የኰሎኔል መንግሥቱና የደጃዝማች ከበደ ተሰማ ገፅታና ተክለ ሰውነት መመሳሰልን እንደማስረጃ የሚጠቅሱ ወገኖችም አሉ:: ሌላው ጥርጣሬ ውስጥ የሚከተው ኰሎኔል መንግሥቱ በቃለመጠይቃቸው የእናታቸውን ስም እስከ አባታቸው ሳይጠቅሱ ማለፋቸው ነው።


  ሌላ ጊዜ ሰጡት በተባለው ቃለ-መጠይቅም ቢሆን የአባታቸውን ስም ትተው እናታቸውን በአያታቸው ስም ብዙነሽ ወልደአማኑኤል ብለው መጥራታቸው ተጠቅሷል። እነዚህ ጉዳዮች ሁሉ ሲጤኑ ኰሎኔል መንግሥቱ ሊጠቅሱት ያልፈለጉት ጉዳይ ያለ የሚመስል ስሜት ይፈጥራሉ። የውጭ ደራሲዎችም ይህን ሃሣብ በሚያግዝ መልኩ ኰሎኔል መንግሥቱ በደጃዝማች ከበደ ተሰማ ቤት ማደጋቸውን በኋላም በእሳቸው ኃላፊነት በሆለታ የወታደራዊ አካዳሚ እንዲገቡ መደረጋቸውን ፅፈዋል፡፡ ኰሎኔል መንግሥቱ በውትድርናው ዓለም በሚያገለግሉ ጊዜ የቁጡነት ባህሪ ያንፀባርቁ እንደነበር የሚናገሩ አሉ። ለበላይ አለቆች በቀላሉ የማይታዘዙ፣ በበላይ አለቆችም ላይ አስፈላጊ መስሎ ከታያቸው ከመሳደብም የማይመለሱ፣ ለሚሰነዘርባቸው ኃይለ ቃልም አስበልጠው አፀፋውን የሚመልሱ እንደሆኑ አድርገው ይገልፁኣቸዋል፡፡


  በ1966 ዓ.ም. ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ሲመሰረት ከ120 መስራች አባላት አንዱ ኰሎኔል መንግሥቱ ሲሆኑ ወክለውም የተገኙት የ3ኛ ክፍለ ጦር መሣሪያ ግምጃ ቤትን ነበር፡፡ የጊዜአዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ በተመሰረተ ጊዜም ኰሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም አንደኛ ምክትል ሊቀ-መንበር ሌተና ኰሎኔል አጥናፉ አባተ ደግም ሁለተኛ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ፡፡ ከየወታደራዊ ዕዙ ተመርጠው የመጡ የወታደሩ ተወካዮችና የደርግ አባላት በአንድነት ባደረጉት ስብሰባ የደርጉን ሊቀ-መንበር ጀኔራል አማን ሚካኤል አምዶምን ጨምሮ 60 ከፍተኛ ሹማምንት በተገደሉ ጊዜ የኰሎኔል መንግሥቱ ድርሻ ከፍተኛ እንደነበር ብዙዎቹ መረጃዎች ያረጋግጣሉ። ኰሎኔል መንግሥቱ በሰጡት ቃለ-መጠይቅ ደግሞ ለ60ዎቹ ሚኒስትሮች መገደል ትልቁን ሚና የተጫወቱት የመርማሪ ኮምሽኑ አባሎች፣ የደርጉ አባላትና ከየጦሩ ክፍል ተውጣጥተው በመምጣት "ይሙት በቃ" የወሰኑባቸው የወታደሩ ወኪሎች ናቸው:: የእሳቸው ድርሻ የመጨረሻ ውሳኔውን ፍፃሜ ላይ ማድረስ ነበር፡፡ የደርጉ ሊቀመንበር የነበሩት አማን ሚካኤል አምዶም ከሌሎች ትልልቅ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ባለሥልጣናት ጋር ከተገደሉ በኋላ በእሳቸው እግር ጀኔራል ተፈሪ በንቴ የደርጉ ሊቀመንበር ሆነው ተተኩ፡፡ ጀኔራል ተፈሪ በንቴ ለዘብተኛ አቋም ነበራቸው ቢባልም በመላ አገሪቱና በጎረቤት ሶማሊያም በኩል የተነሱ ትኩስ ችግሮችን የመቆጣጠር አቅም አልነበራቸውም:: በመሃል አገር ተማሪዎች፣ መምህራን፣ የፋብሪካ ወዛደሮችና አንዳንድ የከተማው ነዋሪዎች በየጊዜው ፀረደርግ ሰላማዊ ሠልፎችን ያዘጋጁ ነበር፡፡ በሰሜን የኤርትራ ነፃ አውጭ ድርጅቶች፣ ህወሃትና ኢዲዩ እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመሩበት ወቅት ነበር፡፡ በመሃል አገር ኢህአፓ፣ መኢሶንና ደርግ የተፋጠጡበትና አንዱ ሌላውን ሰርስረው ለመግባት የሚሰሩበት ጊዜ ነበር፡፡ በምስራቁም የሶማሌ መንግሥት የወረራ ዝግጅት የሚያደርግበት ጊዜ ነበር፡፡ እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጭ እየሆኑ የመጡበት ጊዜ ነበር። በዚህ ጊዜ ኰሎኔል መንግሥቱ በሚስጥር "ነበልባል ብርጌድ" የሚባል አቋቁመው በአስቸኳይ የደርግ አባላት ስብሰባ በሚካሄድ ጊዜ ሰብረው በመግባትና ተኩስ በመክፈት ጀኔራል ተፈሪ በንቲና ሌሎች አራት ባልደረቦቻቸውን ገደሉ። ግድያውን ተከትሎ የተሰጠውም መግለጫ ፀረ-አብዮተኞች ከኢህአፓና ኢዲዩ ጋር በመተባበር የመቀልበስ ሙከራ ሲያደርጉ ተገኝተው እርምጃ እንደተወሰደባቸው አብራራ። ከዚያም ኰሎኔል መንግሥቱ የደርጉ ሊቀ-መንበር ሆኑ፡፡ ኰሎኔል መንግሥቱ የኢህአፓ ተቀናቃኝ የነበረውን የመላው የሶሻሊስት ንቅናቄን (መኢሶንን) ለተወሰነ ጊዜ (የሲቪል አስተዳደር ይቋቋም የሚል ጥያቄ እስካነሳበት ድረስ) ተጠቅመውበታል፡፡ በመሃሉ የነጭና የቀይ ሽብር ፍጅት ተከተለ። ኰሎኔል መንግሥቱ የደርጉ ሊቀ-መንበር በመሆን ቁልፍ ሥልጣን እንደያዙ ከሶቪዬት ህብረትና ከኩባ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት እያጠበቁ መጡ። ብዙም ሳይቆዩ የኩባው መሪ ፊደል ካስትሮ ኢትዮጵያን በይፋ ጐበኙ። ከዚህ ጊዜ በኋላ በፖለቲካውና በወታደራዊ መስክ የሚያማክሩት ኩባውያንና የሶቪየት ህብረት ዜጉች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ቀጠሉ፡፡ ከቀይና ከነጭ ሽብር ፍጅት በኋላ የመሃል አገሩ ፀጥታ የተረጋጋ ቢመስልም በሰሜን እና በምዕራብ ኢትዮጵያ አንዳንድ ሥፍራዎች የሽምቅ ውጊያዎች እየጎለበቱ መጡ፡፡


  ኰሎኔል መንግሥቱ ለ17 ዓመታት ኢትዮጵያን ቢመሩም የአገሪቱ የውጭ ፖሊሲ እንከን ያጋጠመው ጊዜ ነበር፡፡ ኰሎኔል አጥናፉ አባተ ይህን ችግር ከተመለከቱት የደርግ አባላት አንዱ እንደነበሩ ይነገራል፡፡ የውስጥ ፖለቲካውም አጥብቆ ሥርሰራ የበዛበትና በደል የተስፋፋበት ፍትህ የጉደለበት ዘመን እንደነበር ብዙ የታሪክ አጥኚዎች የሚስማሙበት ነው:: ኰሎኔል መንግሥቱ ከንግግሮቻቸውና ከተግባራዊ እንቅስቃሴዎቻቸው በመነሳት እንደተመዘኑት አገር ወዳድና አብዮተኛ ነበሩ፡፡ በዚህ ረገድ ኰሎኔል መንግሥቱ ከሚያስመሰግኗቸው ተግባሮቻቸው አንዱ ታጠቅ የተባለ የጦር ሠፈር መሥርተው በአጭር ጊዜ ውስጥ 300,000 ህዝባዊ ሠራዊት በማሠልጠን በዚያድባሪ የሚመራውን የሶማሊያን ወረራ ለመመከት መቻላቸው ነው፡፡ በውትድርናው ሙያቸው ደግሞ ጀብደኛና ቁጡ እንደነበሩ የውጭ ተመራማሪዎችም ፅፈዋል፡፡ ይሁን እንጂ የሚወስዷቸው እርምጃዎች ሁሉ የአገሪቱን የረጅም ጊዜ ጥቅም እና ታሪክ ከግምት ውስጥ የሚያስገባ አልነበረም:: አብዛኛው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎቻቸው በግብታዊነት የተሞላ በመሆኑ ለአፍራሽ ኃይሎች ፖለቲካዊ ስርሰራ የተጋለጠ እንደነበሩ በ1981 ዓ.ም. የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት ያረጋገጠው ሃቅ ነው:: በአስተዳደር ዘመናቸው የኰሎኔል መንግሥቱ ፎቶግራፍ በትልልቅ አደባባዮችና በየባለሥልጣናቱ ቢሮዎች በኢሠፓ ንዑሥ ፅህፈት ቤት አባላት አማካኝነት እንዲሰቀል ይደረግ ነበር፡፡


  የትዳር ጓደኛ እና የቤተሰብ ምሥረታ ህይወታቸውን ስንመለከት በአንድ የትዳር ጓደኛ ተወስነው እንደመኖራቸው ኰሎኔል መንግሥቱ የጭምትነት ባህሪ የሚታይባቸው ነበሩ ለማለት ይቻላል፡፡ የጉጃም ተወላጅ የሆኑት ወ/ሮ ውባንቺ ቢሻውን አግብተው ትምህርት፣ ትእግስት እና አንድነት የተባሉ ሶስት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ ወ/ሮ ውባንቺ ቢሻው አልፎ አልፎ በአደባባይ አብረው ለመታየት ከመቻላቸው በቀር በፖለቲካው ረገድ ተሣትፎ የነበራቸው አልነበሩም::


  ኰሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም የሥልጣን ዘመናቸው ምን ያህል ደም አፍሳሽና በውጥረት የተሞላ እንደነበር የሌተናል ኰሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ትዝታዎች በተሰኘው መፅሃፍ ከሰጡት ሰፊ ቃለ-ምልልስ ለመረዳት ይቻላል:: የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) በግንቦት ወር 1983 ዓ.ም. ከሥልጣን ካወረዳቸው በኋላ ዚምባብዌ የሚኖሩ ሲሆን ከሌሎች የደርግ አባላት ጋር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በሌሉበት ሲታይ ቆይቶ በአስተዳደር ዘመናቸው ሁሉ ለደረሰው በደል ጥር 3 ቀን 1999 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸዋል፡፡ የዚምባብዌ መንግሥት ግን ኰሎኔል መንግሥቱ ላጠፉት ጥፋት በአገራቸው እንዲዳኙ አሳልፎ ለመስጠት ፍላጎት አላሳየም።


  ኰሎኔል መንግሥቱ በታህሣስ ወር 2004 ዓ.ም. ትግላችን ቅፅ ፩ የተባለ ግለ-ታሪክ መዕሃፍ አሳትመው አውጥተዋል:: በዚህ መፅሃፍ አፅንኦት ሰጥተው ያብራራቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ:: ከእነዚህም ውስጥ በትምህ ርት ሰጭነታቸው የላቀ ሥፍራ ይስጣቸዋል ተብለው የሚታመንባቸው ቀጥለው የተጠቀሱት ርዕሠ-ጉዳዮች ናቸው፦

  1. የሞት ቅጣት እንዲተላለፍባቸው ከታጩ አንድ መቶ ሃምሣ (150) የአፄ ኃይለ ሥላሴ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል ስልሣ (60) ሚኒስትሮችና ታዋቂ ዜጎች የተገደሉበት ግብታዊ ውሳኔ፣

  2. ከ1966 እስከ 1970 ዓ.ም. የውጭ ወረራና የውስጥ የሥልጣን ሽኩቻ ትግሎች በአንድነት ተቀስቅሰው የአገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ የጣሉበትና በጭራሽ መረጋጋት የታጣባቸው ዓመታት የነበሩ ስለመሆናቸው፣

  3. የጐረቤት ሶማሊያ ጦር በምሥራቅ እና በደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ያስፋፋው መጠነ-ሰፊ ወረራና የደረሰው ውድመት፣

  4. የሶማሊያን ጦር ለመመከት ሶስት መቶ ሺህ (300,000) ህዝባዊ ሠራዊት በፈቃደኝነት ከመላው አገሪቱ ከትቶ በታጠቅ ጦር ሠፈር ለሦስት ወራት ሰልጥኖ እና ቀላል መሣሪያ ታጥቆ ወደጦሩ ግንባር መንቀሣቀሱ፣

  5. እስከ ግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም. የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ድረስ በጠቅላላው ለአሥራ አንድ ጊዜ ያህል በራሣቸው በኰሎኔል መንግሥቱ ላይ የመግደል ሙከራ የተደረጊባቸው ስለመሆኑ፣

  6. በደርግ ውስጥ የኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን)፣ የወዛደር ሊግ (ወገሊግ)፣ የኢትዮጵያ ጭቁኖች አብዮታዊ ፓርቲ: (ኢጭአት)፣ የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስት አብዮታዊ ፓርቲ (ማሌሬድ) እና አብዮታዊ ሰደድ የሚባሉ አንጃዎች መፈጠር እና እርስ በርስ ከማያቋርጥ ቁርቁስ ውስጥ መግ ባታቸው ያስከተለው ችግር፣

  7. በወታደራዊ ደርግና በኢትዮጵያ ህዝባዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) መካከል የተካሄዱት የነጭ እና የቀይ ሽብር ጭፍጨፋዎች፣

  8. በወቅቱ ኢትዮጵያ ከውጭ መንግሥታት በተለይም ከሶቪየት ህብረት፣ ከኪውባ፣ ከቼኮዝሎቫኪያ፣ ከምስራቅ ጀርመን፣ ከደቡብ የመን እና ከቻይና ጋር የለበራት ግንኙነት  በሰፊው ከተብራሩ ጉዳዮች መካከል ይገኛሉ።


  ምንጭ፦ ታሪካዊ መዝገብ_ሰብ

 • loader Loading content ...
 • @አማን   2 months ago
  Stop waiting for the perfect moment. Take the moment you've and make it perfect.

  • በእርግዝና ጊዜ አልኮልን አስወግዱ። አልኮል ያለግዜው መውለድን፣ የአዕምሮ እድገት ውስንነት፣ የልደት ጉድለቶች እና ዝቅተኛ  ክብደት ያላቸው የህጻናት ወሊድ ጋር የተያያዘ ነው።

  • ካፌይን በቀን ከ 300 ሚሊ ግራም  በላይ አለመውሰድ።  በተለያዩ መጠጦች ውስጥ ካፌይን ያለው ይዘት የሚወሰነው ጥቅም ላይ በሚውለው የቡና ፍሬ ወይም ቅጠልና እንዴት እንደተዘጋጀ ነው። 8 አውንስ ቡና በአማካይ ከ 150 ሚሊ ግራም ካፌይን ሲኖረው ጥቁር ሻይ ግን 80 ሚሊ ግራም አለው። የ 12 አውንስ ካፌይን ያለው አንድ ጠርሙስ የለስላሳ መጠጥ ከ 30 እስከ 60 ሚሊ ግራም ካፌይን የሚይዝ ይሆናል። ልብ በሉ፡- ቸኮሌት (በተለይ  ጠቆር ያለ ቸኮሌት) ካፌይን አለው - አንዳንድ ጊዜ ከፍተኛ መጠን።

  • በእርግዝና  ወቅት  በምግብ እና መድሐኒት ቁጥጥር ተቋም ተቀባይነት ያላገኙ አርቲፊሻል አጣፋጮች ወይም አልሚ  ንጥረነገሮች  ያልሆኑ  አጣፋጮች  መውሰድ አይመከርም። ምክንያቱም እንግዴ ልጅን በማለፍ ጽንሱ ሕብረ ሕዋሳት ውስጥ መቆየት ይችላል።  ነገር ግን ተቀባይነት ያገኙት እንደ  aspartame (Equal or NutraSweet), acesulfame-K (Sunett), and sucralose (Splenda) በመጠኑ መጠቀም ይቻላል።  ስለዚህ በእርግዝና ወቅት  ምን ያህል አርቲፊሻል አጣፋጮች ወይም አልሚ  ንጥረነገሮች  ያልሆኑ  አጣፋጮች ተቀባይነት እንዳላቸው ከጤና ባለሙያዎ ጋር ተነጋገሩ።

  • ከጠቅላላው የቀን ካሎሪዎ  የስብ ወይም ቅባታማ ምግቦች ኣወሳሰዶ ወደ 30% ወይም ከዚያ በማሳነስ ይቀንሱ። አንድ ሰው በቀን 2000 ካሎሪ የሚበላ ሰው በቀን 65 ግራም ቅባት ወይም ያነሰ እንዲሆን

  • የኮሌስትሮል መጠን በ 300 ሚሊ ግራም ወይም ባነሰ መጠን ይገድቡ።

  • ከፍተኛ መጠን ያለው ሜርኩሪ ያላቸው ዓሣዎችን ያስወግዱ። ለምሳሌ ሻርክ፣ ስዋርድፊሽ፣ ኪንግ ማክሬላ፣ ተርትልፊሽ ወይም ነጭ ስናፐር

  •ሊስተርያ ኢንፌክሽን እንዳያስከትል ፓስቸራይዝድ ያልሆነ ወተት እና የወተት ተዋጽዎ ከመውሰድ ይቆጠቡ።

  • ጥሬ ዓሣዎችን ያስወግዱ፤, በተለይም እንደ  ሼልፊሽ፦ ኦይስተር እና ክላምስ
 • loader Loading content ...
 • @አማን   2 months ago
  Stop waiting for the perfect moment. Take the moment you've and make it perfect.

  ብጉር "የተለመደ ብጉር" ተብሎ የሚጠራበት ምክንያት - ሁሉም ሰው ማለት ይቻላል፤ የሆነ ጊዜ ላይ በብጉር ይቸገራል። ብጉር የሚከሰተው ቅባት ከቆዳ የዘይት ዕጢዎች ሲመነጭና የፀጉር ሀረጎች መውጪያ ክፍተትን ሲደፈን ነው። ክፍተቶቹ ከፍ ያሉ ከሆኑ፤ በብላክሄድስ ይደፈናል( ብላክሄድስ ማለት ትንሽ ጠፍጣፋ ምልክት የሚመስል መሃሉ ጥቁር ነገር)። ክፍተቶቹ ትንሽ ሆነው ከቆዩ፤ በዋይትሄድስ ይደፈናል (ዋይትሄድስ ማለት ትናንሽ፣, ደም የሚመስል ኣበጥ ያለ ነገር)። ሁለቱም ኣይነት የተደፈኑ ክፍተቶች ወደ እብጣት፣ ህመም ያለው ብጉር ወይም ጠለቅ ያሉ እጢ ሊለወጡ ይችላሉ። እነዚ እጢዎች ከበድ ካለ ብጉር (ሲስቲክ አክኒ)ጋር ተዛማጅ ሲሆኑ ከቆዳ በታች ጠጠር ያለ እብጣት ሲሆን ወደ ማቃጠል፣ መለስለስ እና አንዳንዴ ሊበከልም ይችላል።


  ምንም እንኳ ብጉር በአብዛኛው የጉርምስና እርግማን ቢሆንም በአጠቃላይ 20% የሚሆኑት በአዋቂዎች ላይ ይከሰታሉ። አብዛኛውን ጊዜ በጉርምስና እድሜ ከ 10 እስከ 13 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ የሚጀምር ሲሆን ቅባታማ ቆዳ ባላቸው ሰዎች ላይ የባሰ ይሆናል። በአሥራዎቹ ዕድሜ ብጉር በአብዛኛው ከ5 እስከ 10 አመታት በመቆየት በ20 ዎቹ መጀመሪያ ላይ ይጠፋሉ። በሁለቱም ፆታዎች ይከሰታሉ፤ ነገር ግን በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙት ወንዶች በጣም ከበድ ያለው የብጉር ጉዳቶች ያጋጥማቸዋል። ሴቶች ከወንዶች ይልቅ ከቀላል እስከ መካከለኛ የሆነ የብጉር ጉዳቶች እስከ 30ዎቹ ወይም ከዚያ ባሻገር ድረስ ያጋጥማቸዋል። የብጉር ቁስሎች በአብዛኛው በፊትዎ ላይ የተለመዱ ቢሆኑም በአንገት፣ በደረት፣ በጀርባ፣ በትከሻና በክንድ ላይ ሊከሰቱ ይችላሉ። በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ካለው እምነት በተቃራኒ፣ ብጉር የሚመጣው ከጎጂ አመጋገብ፣ ንጽሕና ጉለት፣ ወይም ከቁጥጥር ውጪ በሆነ የወሲብ ፍላጎት አይደለም። ቀለል ያለ እውነታው ከዘር እና ሆርሞን አብዛኛዎቹ አይነት ብጉር ይከሰታል። ከቸኮሌት መታቀብ ወይም በቀን 10 ጊዜ ፊትዎን ማፅዳትን ይህን አስቀያሚ፣ አንዳንዴ የሚያም እና ብዙውን ጊዜ የሚያሳፍር የቆዳ ችግርን አይለውጥም።


  ብጉር መንስኤው ምንድን ነው?

  የብጉር መንስኤ ሙሉ በሙሉ ለመረዳት አልተቻለም። ምንም እንኳን ውጥረት እና ጭንቀት ሊያባብሰው ቢችልም በግልጽ ችግሩን አያመጣም።


  ሆሞኖች (Hormones)፦ የተለመደው ብጉር በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ለሆኑ፤ የሆርሞን ምርት ሲጨምር ይጀምራል። ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በአቅመ-ጉርምስና ወቅት ከፍተኛ አንድሮጅን፣ የወንድ ሆርሞን ቴስቴስሮን ጨምሮ ያመርታሉ። ቴስቴስሮን ሰውነት ተጨማሪ ሰበም (sebum፦ በቆዳ ዘይት ዕጢዎች የሚመረተው ዘይት)እንዲያመርት ያመላክታል።


  ተህዋሲያን (Bacteria)፦ ከልክ በላይ የሆነ ሰበም (sebum)የፀጉር ሀረጎች መውጪያ ክፍተትን ሲደፈን - በተለይም በፊት፣ በአንገት፣ በደረት እና በጀርባ ላይ። ባክቴሪያዎች በእነዚህ ውስጥ ያድጋሉ። ይህም ብላክሄድስ ወይም ዋይትሄድስ ይፈጥራል በተጨማሪ 'comedones' በመባል ይታወቃሉ። አንዳንድ ጊዜ የቅባቱ ክምችት የሚፈጥረው ግፊት የፀጉር ሀረጎች መውጪያ ግድግዳ በመስበር ሰበም ባቅራቢያ ባሉ ሕብረ ሕዋሶች ውስጥ በመፍሰስ ትንንሽ እብጠቶች እና እንዲህ አይነቱ ህመም ያለው ብጉር ይፈጥራል። ትልልቅ ለስላሳ እብጠቶች nodules ተብለው ይጠራሉ።

  እንደ መድሃኒቱ አይነት, በአፍ የሚወሰድ የወሊድ መከላከያ ዘዴዎች በአንዳንድ ሴቶች ላይ ብጉር ያባብሳል በሌሎች ላይ ሊገታው ይችላል። አንዳንድ የሚወጉ ውጫዊ የወሊድ መከላከያ እና intrauterine የወሊድ መቆጣጠሪያ መሳሪያዎችን (IUD) ብጉር ሊያመጣ ይችላል። በአንዳንድ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ባለሙያዎችና ሌሎች አትሌቶች አማካኝነት የሚወሰዱት ስቴሮይዶች ከባድ ለሆነ ብጉር ሊጋለጡ ይችላሉ።

 • loader Loading content ...
 • @አማን   3 months ago
  Stop waiting for the perfect moment. Take the moment you've and make it perfect.

  ረዳት ፕሮፌሰር ደበበ ሰይፉ በኢትዮጵያ የኪነ-ጥበብ ታሪክ ሁለገብ አስተዋፅዖ ከነበራቸው ጥቂት ምሁራን አንዱ ናቸው:: ደበበ ሰይፉ በሥነ-ተውኔትና ሥነ-ፅሁፍ መምህርነት፣ በተውኔት ደራሲነትና ተርጓሚነት፣ በገጣሚነትና በሃያሲነት ብዙ ተግባራትን አከናውነዋል:: ደበበ ሰይፉ ከአባታቸው ከበጅሮንድ ሰይፉ አንተንይስጠኝ እና ከእናታቸው ከወ/ የማርያምወርቅ አስፋው ሐምሌ 5 ቀን 1942 .. በሲዳሞ ውስጥ በይርጋለም ከተማ ተወለዱ:: እድሜአቸው ለትምህርት በደረስ ጊዜ በተወለዱበት አካባቢ የቤተ-ክርስቲያን ትምህርት ተምረዋል:: ቀጥሎም በራስ ደስታ ዳምጠው ስም ይጠራ በነበረው /ቤት ገብተው እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምረዋል:: ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ከተማ መጥተው በኮከበ ፅባህ /ቤት ገብተው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀቁ:: በማስከተልም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአርትስ ፋካልቲ ገብተው በመማር 1965 .. በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ-ፅሁፍ በማዕረግ በቢኤ ዲግሪ ተመረቁና በዚያው በዩኒቨርሲቲው መምህር ሆነው ተቀጠሩ:: 1970 . . ደግሞ በእንግሊዘኛ ሥነ-ዕሁፍ አሁንም በማዕረግ የኤም ዲግሪያቸውን አገኙ:: ደበበ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ካገኙበት 1965 .. አንስቶ ለሃያ ዓመታት በኢትዮጵያ ሥነ-ፅሁፍና በቲያትር ጥበባት ትምህርት ክፍሎች አስተምረዋል:: ደበበ ከማስተማሩም ጐን ለጐን የምርምር ፅሁፎችን በመፃፍ በአገር ውስጥና በውጭ መድረኮች አቅርበዋል የተወሰኑትንም አሳትመዋል:: የኩራዝ አሳታሚ ድርጅት አባል፣ በኢትዮጵያ ሬዲዮ የኪነ-ጥበቡ ዘርፍ አማካሪ፣ የቋንቋዎች ተቋም ጆርናል አሳታሚ ኮሚቴ ሊቀ-መንበ ር፣ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ሊቀ-መንበር፣ በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ሥር የሚታተመው "ብሌን ̈ መፅሄት አሳታሚ ኮሚቴ ሊቀ-መንበር እና በፖለቲካውም የኢትዮጵያ ሠርቶ አደሮች ፓርቲ (ኢሠፓ) አባል በመሆን አገልግለዋል:: ደበበ የፃፏቸው ግጥሞችም የብርሃን ፍቅር እና ለራስ _ የተፃፈ ደብዳቤ በሚሉ ሁለት መድብሎች ታትመው ወጥተዋል:: የመጀመሪያው መድብል ደበበ ራሣቸው በህይወት በነበሩ ጊዜ 1980 .. የታተመ ሲሆን ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ የሚለው መድብል ደግሞ ከዚህ ዓለም በሞት በተለዩበት 1992 .. በሜጋ አሳታሚ ድርጅት አማካኝነት ታትመዋል:: ደበበ ሰይፉ የቡና _ ቤት ሥዕሎችና _ ሌሎች ወጕች የሚለው የመስፍን ብተማርያም ኢ-መደበኛ የወ ስብስብ በታተመ መግቢያውን የፃፉት እሳቸው ናቸው፡፡ "ብድር በምድርእንዲሉ የደበበ ሁለተኛ የግጥም ስብስብ የሆነው ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ በታተመ ጊዜ ደግሞ መግቢያውን የፃፉት መስፍን ሃብተማርያም ናቸው:: በዚሁ ፅሁፋቸው መስፍን ስለደበበ ግጥሞች አጠቃላይ ባህሪያት እንዲህ ብለዋል:: "ደበበ ሰይፉ በርዕስ አመራረጡና በሚያስተላልፋቸው ልብ የሚነኩ መልዕክቶች ብቻ ሳይሆን በስንኞቹ አወራረድና በቤት አመታቱ በአጠቃላይ በውብ አቀራረቡ ተደራሲያንን የሚመስጥ ገጣሚ ነው:: ስለተፈጥሮ ሲገጥም ፀሐይና ጨረቃ፣ ቀስተ ዳመናና የገደል ማሚቶ ያጅቡታል፡፡ ስለፍቅር ስንኞች ሲቋጥር የፍቅረኞችን ልብ እንደስዕል ቆንጆ አድርጐ በቃላት ቀለማት ያሳያል:: ክህደት ላይ እንደ አንዳንድ ገጣሚያን አያላዝንም:: ይልቁንም ውበትና ህይወትን አገናዝቦ 'ያውላችሁ ስሙት፣ እዩት' ማለትን ይመርጣል:: ... እኔ እንደማውቀው ደበበ ሰይፉ በገጣሚነቱ ሁሌም ዝምተኛ ነው:: አይጮህም:: ጮሆም አያስበረግግም :: ይልቁንስ ለዘብ ለስለስ አድርጐ ' እስቲ አጢኑት' ይለናል:: ደጋግመን እንድናነብለት የሚያደርገንም ይኸው ችሎታው ነውብለዋል::

  የደበበ ሰይፉ ግጥሞች አልፎ አልፎ እንደ " ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ ̈ ያሉት እረጅም የሚባሉ ከመኖራቸው በቀር ብዙዎቹ አጫጭሮች ናቸው:: ግጥሞቻቸው አጫጭር ይሁኑ እንጂ የተፈለገውን መልዕክት በማስተላለፍ ረገድ ጉልበት ያላቸውና ለትንታኔም የሚመቹ ናቸው:: ለምሳሌም "ያላዋቂ ጠያቂ" በሚል ርዕስ የሚጠራውን ግጥማቸውን ቀጥሎ እንመ ልከተው::

  ከመቼው፣

  ከመቼው በል ጦነቸኸው?

  የገሉህን ልትገድል፣

  የጣሉህን ልትጥል፣

  ከመቼው በል ከመቼው ጦነቸኸው?

  ብለው፣

  መቼ .... መቼ ገና አየህና

  ጉልበቴን ለካህና፣

  ብሎ አለፍ እንዳለ፣

  ከፈን በላዬ ተጣለ::

  ደበበ ሰይፉ ከግጥም መድብሎች ሌላ ሶስት አጫጭር ልቦለድ ታሪኮች 1960 . ማርክሲዝምና የቋንቋ ችግሮች (1973) እና የቲያትር ጥበብ ከፀሐፊ ተውኔቱ አንፃር (1973) የተባሉ መዕፃፍትን አሳትመዋል:: ከነዚህም ሌላ ደበበ ቀጥለው የተዘረዘሩትን ተውኔቶችን ፈውና ተርጉመው ብዙዎቹን ለመድረክ አብቅተዋል ::

  1. ከባህር የወጣ አሳ፣

  2. እናትና ልጆቹ ፣

  3. እነሱ እነሷ፣

  4. ሳይቋጠር ስ.ተረተር፣

  5. የህፃን ሽማግሌ፣

  6. ክፍተት፣

  7. ማክቤ እና

  8. ጋሊሊዮ ጋሊሊ ናቸው::

  ደበበ በሃያሲነትም በልዩ ልዩ የኪነጥበብ ፕሮግራሞች ታትመው የሚወጡና ተዘጋጅተው በመድረክ ላይ ይቀርቡ በነበሩ የፈጠራ ሥራዎች ላይ ጥልቀት ያለው ሙያዊ ትንታኔ በመስጠት ይታወቃሉ:: ብዙዎቹ ተውኔታዊ ዳዬ ቃላትም አቻ የአማርኛ ፍቺ የተፈለገላቸው በደበበ ሰይፉ እንደሆነ ይታወቃል:: ደበበ ሰይፉ ወደአማርኛ ከመለሷቸው ተውኔታዊ ቃላት መካከል "ገፀ-ባህሪ፣ ሴራ መቼት፣ ቃለ-ተውኔትእና የመሳሰሉት ተጠቃሾች ናቸው:: ደበበ ከግንቦት 1985 .. አንስቶ የማስተማሩን ሥራ አቁመው ለሰባት ዓመታት ያህል ከቤት ውለው ነበር:: አንዳንድ ወገኖች ከሚናገሩት እና እንዲሁም አንዳንድ ጋዜጦች ከፃፉት ለመረዳት እንደሚቻለው ደበበ በሃላፊነት ላይ በነበሩበት ዘመን ከብልሹ ምግባራቸው እንዲታረሙ የታገሏቸው ወገኖች የተደረገውን የመንግሥት ለውጥ እንደአጋጣሚ ተጠቅመው በደርግ-ኢሠፓ ዘመን በደል እንዳደረሱ አስመስለው አውርተው በማስወራት ክፉኛ ያበሳቸው ነበር:: ደበበ ሰይፉ ሚያዚያ 16 ቀን 1992 .. ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተው በቅዱስ ዮሴፍ ቤተ-ክርስቲያን ተቀበሩ:: 

  ምንጭ:- ታሪካዊ መዝገበ-ሰብ 

 • loader Loading content ...
 • @አማን   3 months ago
  Stop waiting for the perfect moment. Take the moment you've and make it perfect.

  አፄ ገላውዴዎስ የአፄ ልብነድንግል እና የእቴጌ ሰብለወንጌል ልጅ፣ የአፄ ናኦድ የልጅ ልጅ እና የአፄ ሠርፀ-ድንግል አጐት ናቸው:: አፄ ገላውዴዎስ ከአፄ ልብነድንግል አራት ልጆች ሁለተኛው ናቸው:: የመጀመሪያው የአፄ ልብነድንግል ልጅ ፊቅጦር 1531 .. ሸዋ ውስጥ ከግራኝ አህመድ ወታደሮች ጋር ሲዋጋ ጦር ሜዳ ላይ ሞተ:: ሶስተኛው ወንድ ልጃቸው ሚናስ ትግራይ ውስጥ ከግራኝ አህመድ ወታደሮች ጋር ሲዋጋ ተማርኮ ወደ የመን አገር ተሸጠ:: አፄ ልብነድንግል በሞቱ ጊዜ የተረፉት ወንዶች ልጆች ሁለተኛው ልጅ ገላውዴዎስና አራተኛው ልጃቸው ያዕቆብ ብቻ ነበሩ:: ከፊቅጦር ሞት በኋላ በትምህርት ኮትኩተው ያሳደጓቸው ገላውዴዎስ አልጋ ወራሽ ሆኑ:: በታሪከ ነገሥት እንደተፃፈው አፄ ልብነድንግል በትምህርት የጐለመሱ ሊቅ ስለነበሩ ወጣቱን ገላውዴዎስን ቅዱሣ መፃህፍትን ከነትርጓሜያቸው እያስተማሩ አሳደጓቸው:: ከዚህም ሌላ ገላውዴዎስ ፈረስ ግልቢያን፣ አውሬ አደንን፣ ቀስት ውርወራን፤ የጦር ስልትን እየተማሩ አደጉ:: ገላውዴዎስ ከልጅነት ዘመናቸው ጀምሮ ለትምህርት ጥማት ስለነበራቸው አባታቸው የሚያስተምሯቸውን ሁሉ በብሩህ ልቡና ሲማሩ አደጉ:: ብዙ የታሪክ ፀሐፊዎች እንደፃፉት አፄ ልብነድንግል ከትልቁ ልጃቸው የበለጠ ብልህ መሆናቸውን በመገመት የአስተዳደርንና የቤተ-ክህነትን እውቀት በተለየ ትኩረት እያስተማሩ አሳደጓቸው::

  በ18 ዓመታቸው ገላውዴዎስ በእናታቸው ከእቴጌ ሰብለወንጌል ረዳትነት በትረ-መንግሥቱን ይዘው በጐንደር፣ በትግራይ፣ በጐጃም፣ በሽዋበወሎ ልዩ ልዩ ሥፍራዎች ከግራኝ አህመድ ግዙፍ ጦር ጋር ውጊያ ሲያደርጉ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት አልከበዳቸውም። ገላውዴዎስ የውጊያ ችሎታቸውን ያህል በባህሪያቸው ደግና ትዕግሥተኛ ከመሆናቸውም እኩል መሃሪ ነበሩ:: በታሪካቸው መቅድም ስለበዛው ደግነታቸውና መሃሪነታቸው ስለመልካም ገዥነታቸው የሚከተለው ሰፍሮ ይገኛል:: “ለአፍና ለጉሮሮ ከማርና ንኮራ አገዳ የሚጣፍጥ ለሚሰሙ ጆሮዎች መደነቅን የሚያበዛ፣ ለሚሰሙትም እንደዘፈን ደስታ የሚሰጥ ስሙ የተከበረ፤ ትሩፋቱ የተነገረ ሥርዓቱ ያማረ፣ ልቡ ንፁህ የሆነ፣ ግብረገብ፣ የተመሰገነ፣ ፍርዱ የቀና ትዕዛዙ የፀና በኢትዮጵያ በደጋዋ በቆላዋ በመስኮቿና በተራራዎቿም፤ በባህሮቿና በደሴቶቿም፣ በብልሆቹና በሰነፎች ሁሉ ከፅንፍ እስከፅንፍ ተከራካሪ ሳይኖርበት ከአዲም በር እስከ አዲም ስለነገሠው ስለአፄ ገላውዴዎስ ታሪክ እንጀምራለንይላል:: 

  አፄ ገላውዴዎስ በእርግጥም አስተዋይ ስለነበሩ ወንድማቸውን ሚናስን የሸጠባቸውን የኢማም ኢብራሂምን ልጅ በጦር ሜዳ ማርከው በእጃቸው በገባ ጊዜ በወንድማቸው ልዋጭ ወደአገሩ እስኪ መለስ ድረስ አንድም ስቃይ ሳይደርበት በክብር እንዲቀመጥ አድርገውታል:: አፄ ገላውዴዎስ በትረ-መንግሥቱን ይዘው ወታደራዊ አቋማቸውን እንዳደራጁ በግራኝ አህመድ ላይ ተከታታይ የመልሶ ማጥቃት ጦርነት አደረጉ:: በተለይም በትግራይ ተንቤንና በጐንደር ሰሜን ተራራ አካባቢ ተዋግተው ሁለት ወሳኝ ድሎችን ካገኙ በኋላ የመልሶ ማጥቃት ጦርነቶችን እያሰፉ መጡ:: የውጭ የታሪክ ዘጋቢዎች ካሰፈሩት ለመረዳት እንደሚቻለው አፄ ገላውዴዎስ ግራኝ አህመድን ለማሸነፍ ያበቋቸውን ጦርነት ያደረጉት 1535 .. ሲሆን ሲል ከተደረጉ ጦርነቶች የተረፉ የዘመናዊ ጦር መሣሪያ ተኳሽ የነበሩ 200 የፖርቱጋል ወታደሮች ሳትፈዋል:: የኢትዮጵያ ቀደምትና ታላላቅ ዑላማዎች ታሪክ የተባ ሃፍ ይህንኑ የአፄ ገላውዴዎስንና የግራኝ አህመድን የመጨረሻ ጦርነት አስመልክቶ ቀጣዩን አስፍሯል:: ”አህመድ ግራኝ መላ ሀበሻን ለኣስ አምስት ዓማታት ከገዙ በኋላ እንዴት ተሸነፉ የሚል ጥያ መነሳቱ አግባብነት አለው:: ቅቱ ሀበሻ ንጉሥ ለክርስቲያን ፈረንጆች የድረሱልኝ ጥያቄ በስፋ አቀረቡ:: እነሱም አፋጣኝ ምላሽ ይሆን ዘንድ መሣሪያና ወታደር ወደ ሀበሻ በመላካቸ በለሱ ዞረና ነሳራዎች (የክርቶስ ከታዮች) ሊያሸንፉ እና አህ ግራኝ ወታደር ሊሸነፍ ችሏል:: ነሳራዎችም ዚህ በፊት በማንኛቸውም የጦር ግንባር ይቶ በማይታወቅ መልኩ ሰይፍና ጦር በታጠቀው የአህመድ ግራኝ ጦር ላይ ጠብመንጃና ሌላም ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ተጠቅመው ያልተቋረጠ ድብደባ ፈፀ:: በዚህም ወቅት ኢማም አህመድ ግራኝ በመስዋዕትነት ወደቁብሏል:: የአገር ውስጥና የውጭ ደራሲዎች እንደፃፉት የአውሮፓውያን ክርስቲያኖች በተለይም የፖርቹጋልን እገዛ የጠየቁት አፄ ገላውዴዎስ ሳይሆኑ አባታቸው አፄ ልብነድንግል ናቸው:: አፄ ልብነድንግል የአውሮፓ ክርስቲያኖችን እርዳታ የጠየቁበት ምክንያት ግራኝ አህመድ ከቱርክ መንግሥት ዘመናዊ መሣሪያና በአጠቃላይም ወታደራዊ እርዳታ እያገኘ ስላጠቃቸው ይህንን ጥቃት ለመቋቋም ሲሉ ያደረጉት መሆኑ ተፅፏል::

  አፄ ገላውዴዎስ ሥልጣን ከያዙበት 1533 .. አንስቶ ያለእረፍት አስር ዓመታትን ሲዋጉ ቆይተው የካቲት 21 ቀን 1543 .. ወይናደጋ ላይ ትልቅ ጦርነት ተደርጐ ግራኝ መገደሉን ጋስፒሪኒ ፅፈዋል:: አፄ ውዴዎስ በትግራይ፣ በጐንደርና በጐጃም ያሉ ግዛቶችን በሙሉ ድል አድርገው ከተቆጣጠሩ በኋላ በወሎ በኩል አድርገው ወደሸዋ በመሻገር ከተረፈው የግራኝ አህመድ ጦር ጋር መዋጋት ቀጠሉ:: በሪሁን ከበደ የአቶ አጽሜን የታሪክ መፅሃፍ ጠቅሰው የአፄ ኃይለ ሥላሴ ታሪክ በተባለው መፅሃፍ እንዳብራሩት አፄ ገላውዴዎስ የመጨረሻውን ጦርነት ያደረጉት 1551 .. ነው:: አፄ ገላውዴዎስ አሚር ኑር ከተባለ የጦር መሪ ጋር ተዋግተው ድል ካደረጉ በኋላ እንደገና ባገረሸው ጦርነት ተገደሉ:: ከሶስት መቶ አመታት በኋላ አፄ ዮሐንስ አራተኛ መተማ ላይ ሲዋጉ በሞቱ ጊዜ ጭንቅላታቸው ተቆርጦ እንደ ተወሰደ ሁሉ አሚር ኑርም የአፄ ገላውዴዎስን ጭንቅላት ቆርጦ በአህያ በመጫን ወደሀረር ወስዷል:: የግራኝ አህመድ የእህት ልጅ የሆነው አሚር ኑር የተቆረጠውን የአፄ ገላውዴዎስን አንገት ይዞ አዲስ ላገባት የአጐቱ ሚስት ባቲ ድል ወንበራ ግዳይ ለመጣል በመገስገስ ላይ እንዳለ አዛሎ በተባለ ቦታ ላይ በደረሰ ጊዜ አድፍጠው ይጠብቁት ከነበሩ ኦሮሞዎች ጋር ጦርነት ገጠመ። አሚር ኑር ከኦሮሞዎች ጋር ባደረገው ጦርነት አብዛኛው ጦሩ አልቆበት ጥቂት ራሱን ሆኖ ፈረስ አምልጦ ሀረር ገባ:: አፄ ገላውዴዎስ እንደሞቱ ወዲያ ወንድማቸው አፄ ሚናስ (የአፄ ሠርፀ-ድንግል አባት) ተተኩና ሐመልማል በተባለ የጦር አበጋዝ የሚመራ ጦር የአፄ ገላውዴዎስን አንገት ቆርጦ የወሰደውን አሚር ኑርን እንዲወጋ ወደ ሀረር ላኩ:: ሐመልማል ወደሀረር በመገስገስ ላይ እንዳለ ተቆርጦ የተወሰደው የአፄ ገላውዴውስ አንገት እንደተመለሰ ከውንድማቸው ከአቤቶ ያዕቆብ መቃብር መንዝ ውስጥ ገማ ኮረብታ በሚገኘው ቤተ-ክርስቲያን እንዲያርፍ ተደረጓል:: ዋናው የአፄ ገላውዴዎስን አካል ግን ሲዋጉ ከሞቱበት  ከፈጠጋር እንደ ተቀበረ በልዩ ልዩ መፅሃፍት ተፅፎ ይገኛል:: 

  ምንጭ:- ታሪካዊ መዝገበ-ሰብ 

 • loader Loading content ...
 • @አማን   3 months ago
  Stop waiting for the perfect moment. Take the moment you've and make it perfect.

  ከጎራው ዘልቄ - እስኪ ልነጋገር

  ካለሰው ቢወዱተ - ምን ያደርጋል አገር?

  ህንፃ መች ሆነና - የድንጋይ ክምር፣

  መንገድ መች ሆነና - የድንጋይ አጥር፣

  ህንፃው ምን ቢረዝም - ምን ቢፀዳ ቤቱ፣

   መንገዱ ቢሰፋ - ቢንጣለል አስፋልቱ፣

   ሰው ሰው ካልሸተተ - ምንድነው ውበቱ?

   የኔ ውብ ከተማ - የኔ ውብ አገር፣ የሰው ልጅ ልብ ነው፣

   የሌለው ዳርቻ - የሌለው ድንበር፣

  (ግጥም - በአሉ ግርማ)

   

 • loader Loading content ...
 • @አማን   3 months ago
  Stop waiting for the perfect moment. Take the moment you've and make it perfect.

  ፕሮፌሰር አስራት ላው አማራ ህዝብ ድርጅት መስራችና መሪ ናቸው:: ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ሰኔ 12 ቀን 1920 .. በአዲስ አበባ ተወለዱ:: የሶስት አመት እድሜ እንዳስቆጠሩ ከቤተሰብ ጋር ወደ ድሬዳዋ ከተማ ሄዱ:: ገና በህፃንነት እድሜ እንዳሉ ባህላዊ ትምህርት በመግባት ዳዊትን አጠናቀው መድገም እስከሚችሉ ድረስ ተማሩ:: ቀጥሎም በፈረንሣይኛ ቋንቋ ይሰጥ ወደነበረው ዘመናዊ ትምህርት ቤት ለመግባት በመዘጋጀት ላይ እንዳሉ የጣሊያን ጦርነት መጣና ምኞታቸው ተሰናከለ:: ወላጅ አባታቸው አቶ ወልደየስ በጠላት ተይዘው ከመገደላቸውም በላይ አያታቸው ቀኛዝማች ወረደ ቃል ወደጣሊያን አገር ተወስደው ታሰሩ:: ወላጅ እናታቸውም እንዲሁ ሃዘኑና ችግሩ ፀንቶባቸው ብዙ ሳይሰነብቱ በሞት ተለዩ:: በዚህ ሁኔታ የቤተሰቡ ኑሮ በመናጋቱ ፕሮፌሰር አስራት ከትምህርት ገበታቸው እርቀው ተቀመጡ:: አያታቸው ከሶስት አመት ተኩል እስር በኋላ ተለቀው ወደአገራቸው ተመለሱ:: ወጣቱ አስራትም ከአያታቸው ጋር ወደትውልድ አገራቸው አዲስ አበባ እንደ ገና ተመልሰው መጡ:: ነፃነት ተመልሶ አንድ አመት ከተቆጠረ በኋላ 1934 .. በተፈሪ መኰንን /ቤት ዘመናዊ ትምህርት መማር ቀጠሉ:: 1935 .. የትምህርት ዘመን ከክፍላቸው ከሁ ተማሪ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ በመቻላቸው ተሸለሙ:: በሁለቱ ዓመታት የተማሯቸው ትምህርቶች የከፍተኛ ትምህርት ለመከታተል እንደቅድመ ዝግጅት የሚቆጠሩ ስለነበሩ አመት ግብፅ አሌክስሣንደሪያ ሄደው ቪክቶርያ ኮሌጅ በሚባለው ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ገቡ:: በመጀመሪያው ግማሽ ወሰነ-ትምህርት ባስመዘገቡት ከፍተኛ ውጤት የተነሳ ወደሁለተኛ ደረጃ እንዲሸጋገሩ ተደረገ:: በግብፅ-አሌክሣንድሪያ የሚሰጠውን ትምህርት ለአምስት ዓመታት ተምረው በጥሩ ውጤት እንዳጠናቀቁ ወደ እንግሊዝ አገር ተጉዘው ስኮትላንድ ውስጥ በሚገኘው ኤዳንብራ ዩኒቨርስቲ በመግባት በህክምና ትምህርታቸውን ቀጠሉ:: ለስድስት ዓመታት የሚሰጠውን ትምህርት ተምረው እንዳጠናቀቁ ለአንድ ዓመት በየሆስፒታሉ ልምምድ አድርገው ንድፈሃሣብን ከተግባር ያጣመረ ልምድ በማካበት በ1947 .. የዶክትሬት ዲግሪ ተቀብለው ወደ አገራቸው ተመለሱ::

  1948 .. በልዕልት ፀሐ ሆስፒታ ራቸውን ከመጀመቸው በፊት ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ፊት ቀርበው የሚከተለውን መመሪያ መቀበላቸውን መጋቢት 11 ቀን 1991 .. የታተመው "አንድነት" ጋዜጣ ዘግቧል:: "እስከዛሬ የህክምና ትምህርት ተምረህ አገርህንና ወገንህን እንድታገለግል በማለት እኛ በበኩላችን የተቻለንን ያህል ደክመናል:: አሁን ደግሞ የድካማችንን ፍሬ የምንቀበለው ካንተ ነውና በርትተህ በተማርከው ትምህርት አገርህንና ወገንህን እንድታገለገል እግዚአብሄር ዳህ የሚል ነበር:: ፕሮፌሰር አስራት ከዚህ በኋላ በልዕልት ፀሐይ ሆስፒታል (በአሁኑ ጦር ኃይሎች) ለአምስት ዓመታት አገልግሎት ከሰጡ በኋሳ እንደገና ወደእንግሊዝ አገር ሄደው ሮያል ኮሌጅ ኦፍ ሰርጀንስ በቀዶ ህክምና ልዩ ትምህርት ተምረው ተመለሱ:: ፕሮፌ ሰር አስራት በጠቅላላው ለሠላሣ አምስት ዓመታት በልዕልት ፀሐይ እና በጥቁር አንበሳ ሆስፒታሎች በህክምና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ደግሞ በመምህርነት ያለ እረፍት አገልግለዋል:: ከሙያ ባልደረቦቻቸው አስተያየት ለመረዳት እንደሚቻለው ፕሮፌሰር አስራት በቀዶ ህክምና ተግባራቸው ተወዳዳሪ የላቸውም ከሚባሉ ኢትዮጵያውያን አንዱ ነበሩ:: ልጅ ሚካኤል እምሩ ግንቦት 1992 .. ታትሞ ለወጣው "ምኒልክ ̈ መፅሄት በሰጡት ቃለ-መጠይቅ ፕሮፌሰር አስራት በባህሪያቸው ሚዛናዊ፣ በትምህርታቸው ጐበዝ እና በአጠቃላይ ብዕናቸው የተሟሉ ሆነው እንዲያድጉ በመቅረፀ ረገድ ሃኪም ወርቅነህ እሸቴና የእናታቸው አባት ቀኛዝማች ወረደቃል ትልቅ ድርሻ እንደነበራቸው መስክረዋል። 

  በመማር ማስተማሩም ዘርፍ ብዙ ጥናቶችን ከማበርከታቸውም በላይ በቀዽሞው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የህክምና ፋካልቲ ዲን በመሆን ሠርተዋል፡፡ የህክምናውን ዘር በተመለከተም መንግሥት በሚያወጣቸው ሊሲዎች ሁሉ ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆን አገልግለዋል:: የህክምና ዳይሬክተር በነበሩበት ጊዜ የልዕልት ፀሐይ ሆስፒታል እንዲሰፋ እንዲናከር አድርገዋል:: ፕሮፌሰር አስራት 1970ዎቹ ወደመጀመሪያ የአገር ድንበር ለማስከበር በሰሜንና ምሥራቅ የዘመተውን ሠራዊት በህክምና ለመርዳት አብረው ዘምተዋል:: እንደ አንድ ተዋጊ ወታደርም በምሽግና በድንኳን ውስጥ ተቀምጠው በሞትና በህይወት መካከል የሚገኙ ቁስለኞችን በማከም ህይወታቸውን ታድገዋል:: የመንግሥት ለውጥ ከተደረገበት 1983 .. አንስቶ ፕሮፌሰር አስራት ብዙ ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመጋፈጥ ተገደዋል:: በሰኔ ወር በተካሄደው የሽግግር ወቅት ቻርተር ኮንፈረንስ አዲስ አበባ ዩኒርሲቲን በመከል በስብሰባው ላይ በመገኘት አገሪቱን ይበጣጥሳል በሚል በቻርተሩ የፀደቁ ድንጋጌዎችን በይፋ ተቃውመዋል:: ከዚያው ዘመን መጨረሻ አንስቶ በአማራ ተወላጆች ላይ ከሥራና ከመኖሪያ አካባቢያቸው መፈናቀል፣ የንብረት ዝርፊያ፣ ስደት እና የጅምላ ፍጅት በተለይም በሀረር፣ በአርሲና በወለጋ ተባብሶ በመቀጠሉ / አልማዝ በሚባሉ ሴት አማካኝነት የዓላማ ደጋፊዎቻቸውን በማሰባሰብ የመላው ዐማራ ህዝብ ድርጅትን (መዐህድን) መሠረቱ:: የድርጅቱም ፕሬዝዳንት ሆኑ:: "በዚች አገር ውስጥ በድህነት ጠርዝ ላይ እየኖረ፣ በየአመቱ በርሃብ አለንጋ እየተገረፈ፣ የለውጥ አየር በነፈሰ ቁጥር ሊፈናቀል፣ ሊዘረፍና ሊጨፈጨፍ አይገባም፤ በአማራ ላይ ወንጀል የፈፀሙትም ለፍርድ ሊቀርቡ ይገባል" በሚል አቤቱታ ለሽግግር መንግሥቱ ማቅረብ ቀጠሉ:: ፕሮፌሰር አስራት "የአማራ ህዝብ የአስተዳደር በደል ደረሰበት፣ ተሰደደ፣ እጅ እግሩ ታስሮ በቤት ውስጥ ተቆልፎበት በእሣት ተቃጥሎ እንዲሞት ተደረገ፣ ከነነፍሱ ገደል ውስጥ ተወረወረ፣ ሴቶች ተደፈሩእያሉ በድርጅታቸው አማካኝነት አቤቱታ በሚያቀርቡ ጊዜ ሁለት አይነት ቅሥቀሳ ተከፍቶባቸው ነበር:: አንደኛው ወገን "ትምክህተኛ፣ ነፍጠኛ፣ ጦረኛና የድሮ ሥርዓት ናፍቂ" የሚል ቅጥያ ሰጥቶ የማጥላላት ዘመቻ ከፈተባቸው:: ሌላው ወገን በተለይም ደግሞ "ተማርን ባይእና መስሎ ማደር ይቻላ" የሚሉ የአማራ ተወላጆች የረባ ጐጆ የሌለው፣ ከደበሎ ለባሽነት ያልወጣ፣ ዓለም ለደረሰበት ስልጣኔ በእጅጉ ባይተዋር የሆነው የአማራ ህዝብ የጐ ጥላቻ ባደረባቸው ፖለቲከኞች ቁም ስቅሉን እያየ መሆኑን አይተው እንዳላየ ሰምተው እንዳልሰማ በመምሰል ኖረው አሁን "አስራት የወያኔን አላማ ለማስፈፀም በጐሳ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ድርጅት አቋቋመእያሉ እንደትልቅ ኃጢያት በመቁጠር የውግዘት ቅስቀሳ ማድረግን ቀጠሉ:: በሁለቱ ኃይሎች ግፊት ሲደረግባቸው ከቆዩ በኋላ 1986 .. ደብረብርሃን ላይ የመዐህድ አባላትና ደጋፊዎች በተሰበሰቡበት ለጦርነት የሚያነሳሳ ንግግር አድርገዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸው ሰኔ 10 ቀን 1986 .. የእስራት ቅጣት ተፈረደባቸው:: በጥቅምት ወር 1989 .. ታትሞ የወጣው "ኢትዮጵ" ጋዜጣ ከአቀረበው ዘገባ ለመረዳት እንደሚቻለው ፕሮፌሰር አስራት ከታሰሩበት ከሰኔ 10 ቀን 1986 እስከ 1989 .. ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ 150 ጊዜ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተደርገዋል:: ፕሮፌሰር አስራት ከታሰሩ ጊዜ በፊትና በኋላም ቀጥለው የተዘረዘሩት የድርጅቱ የአመራር አባላት የእስራት ቅጣት አጋጥሟቸዋል ::

  1. ሻለቃ ጌታቸው መንግሥቴ (ዋና ፀሐፊ)

  2. አቶ ወንድአየሁ ካሣ (የአዲስ አበባ መዐህድ ሰብባቢ)

  3. ኩሎኔል ጌታሁን እጅጉ (የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ )

  4. አቶ ዓሊ እንድሪስ (የአስተዳደር ዘርፍ ሃላፊ)

   5. አቶ ግርማ ዕንቁሥላሴ (የሂሣብ ሹም) ነበሩ::

  ፕሮፌሰር አሰራት ለአምስት አመታት ያህል በእስር ቤት እንደቆዩ በጠና በመታመማቸው የመላ ዐማራ ህዝብ ድርጅት፣ የአለም ሰብአዊ መብት ተከራካሪዎችና ህዝቡም ባቀረቡት ተደጋጋሚ ጥያቄና ባሳደሩት ጫና እንደታሰሩ ከሚታከሙበት ሆስፒታል ተፈተው ለከፍተኛ ህክምና ወደ አሜሪካን አገር ሄዱ:: ፕሮፌሰር አስራት ወደ አሜሪካን በሚጓዙ ጊዜ የጤንነታቸው ችግር ተባብሶ ስለነበር በአውሮፕላን ላይ እርዳታ የሚሰጧቸው የህክምና ያተኞች አብረዋቸው ተጉዘዋል:: ፕሮፌሰር አስራት 1991 .. አሜሪካን አገር በህክምና ላይ እንዳሉ አርፈው አስከሬናቸው ወደኢትዮጵያ መጥቶ ቅድስት ሥላሴ ጐን በሚገኘው በባለወልድ ቤተ-ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዲያርፍ ተደረገ:: ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ የሁለት ወንዶች ልጆች አባት እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ::

   ምንጭ:- ታሪካዊ መዝገበ-ሰብ  

   

 • loader Loading content ...
 • @አማን   3 months ago
  Stop waiting for the perfect moment. Take the moment you've and make it perfect.

  / ባፈና የአፄ ምኒልክ ሁለተኛ ባለቤት ናቸው:: ይህም ከወ/ አልጣሽ ቴዎድሮስ በኋሏ ከእቴጌ ጣይቱ በፊት ያገቧቸው በእድሜ ብዙ የሚበልጧቸው ነበሩ:: / ባፈና ትውልዳቸው ሰሜን ሸዋ ውስጥ በመርሐቤቴ አውራጃ ነው:: አፄ ምኒልክን ከማግባታቸው በፊት ካገቧቸው ከመጀመሪያ ባለቤታቸው ብዙ ልጆችን ወልደው ድረው ነበር:: / ባፈና ልጆቻቸውን ከትልቅ የሥልጣን ደረጃ የማድረስ ህልም ስለነበራቸው ብዙዎቹን የዳሯቸው ለትልልቅ መኳንንት ነበር:: ለምሣሌ አንደኛዋ ልጃቸውን የአፄ ምኒልክ የአጐት ልጅ ለሆኑት ለደጃዝማች መሸሻ ሰይፉ ሲድሩ፣ ሌላዋን ደግሞ ለወሎው ገዥ ለራስ (በኋላ ንጉሥ) ሚካኤል ድረዋል:: / ባፈና የአፄ ምኒልክ ባለቤት ይሁኑ እንጂ በፖለቲካዊ አስተሣሰብ ግን ምንጊዜም ከንጉሠ-ነገሥቱ በተቃራኒ ይቆመው እንደነበር በታሪክ ተፅፏል:: ተክለፃዲቅ መኩሪያ ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በሚለው መፅሃፍ የወ/ ባፈናንና የአፄ ምኒልክን ቅራኔ እንዲህ ሲሉ ገልፀውታል:: « .... / ባፈና ከአፄ ምኒልክ ከተጋቡ በኋላ እንደሌሎቹ ሴቶች ለባላቸው ክብር ከመቅናትና ባላቸውን በማገልገል ፈንታ ብዙ ጊዜ ከአፄ ምኒልክ ባላንጦች ከነደጃዝማች ሰይፉ ከአማቻቸው ይማም መሃመድ ጋራ ውስጥ ውስጡን እየተላላኩ በባለቤታቸው በአፄ ምኒልክ ላይ አድማ ይሠሩባቸው ነበር:: እንደዚሁም በአፄ ዮሐንስ ግጭት በመጣ ጊዜ አሳባቸውን ወደ አፄ ዮሐንስ እያደረጉ ይስማሙ ነበር ይባላል:: ይሁን እንጂ አፄ ምኒልክ ይኸንንም ቢያውቁ ፍቅር የማያሸንፈው ነገር አይገኝምና ክህደታቸውንና አድማቸውን በፍቅር ምክንያት እየታገ አብረው ይኖሩ ነበር:: በኋላ ግን / ባፈና ይኸንኑ ያድማ ነገር እየቀጠሉ ስለሄዱ 1875 .. በጭራሽ ፈቷቸው» ብለዋል:: የውጭ የታሪክ ፀሐፊዎች እንደገለፁት / ባፈና 1869 .. በአፄ ምኒልክ ላይ ተቀስቅሶባቸው በነበረው አመፅ ላይ ተካፋይ ነበሩ:: ፍላጐታቸው ሁሉ የልጃቸው ባለቤት ደጃዝማች መሸሻ ሰይፉ ሥልጣኑን ጠቅልለው እንዲይዙ ነበር:: / ባፈና አፄ ምኒልክ ከፈቷቸው በኋላ ተፈቅዶላቸው በቤተ-መንግሥቱ ቅጥር ግቢ ይኖሩ ነበር:: እቴጌ ጣይቱን በሃይማኖታዊ ሥርዓት እንዳገቡ ከቤተመንግሥት ወጥተው ሲኖሩ ሳለ 1889 .. በድንገት ታመው ሞቱና በደብረሊባኖስ ገዳም ሥርዓተ-ቀብራቸው ተፈፀመ::   

  ምንጭ:- ታሪካዊ መዝገበ-ሰብ 

 • loader Loading content ...
 • @አማን   3 months ago
  Stop waiting for the perfect moment. Take the moment you've and make it perfect.

  ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ከአባታቸው ከአቶ እሸቴ ጉቤ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ወለተያስ ሀብቱ ሐምሌ 20 ቀን 1869 ዓ.. ሰሜን ሸዋ ውስጥ በምንጃር ወረዳ ልዩ ስሙ ቀርሾ አጥር በሚባል ሥፍራ ተወለዱ:: አባታቸው አቶ እሸቴ ጉቤ ከጎጃም እና ከወሎ አማራ ሣይንት ይወለዳሉ:: እናታቸው ወ/ሮ ወለተያስ ሀብቱ ደግሞ ቡልጋ ውስጥ የመስኖ ማርያም አካባቢ ተወላጅ ናቸው:: የነጋድራስ ተሰማ አባት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ኦባት የልዑል ራስ መከንን ወልደሚካኤል ጭፍራ ነበሩ:: አፄ ምኒልክ 1879 .. ሀረርን ከውጭ ወራሪዎች ተከላክለው ከተማዋን ለመቆጣጠር በሚል የጦር አለቆቻቸውን ይዘው ወደ ሥፍራው በሄዱ ጊዜ ልዑል ራስ መኰንን በቡልጋና አካባቢዋ የሚገኙ የሠራዊት አባላትን ይዘው ተጓዙ:: ልዑል ራስ መኰንንን ተከትለው ከሄዱት አንዱ የነጋድራስ ተሰማ አባት እሸቴ ጉቤ ነበሩ:: አካባቢው ከተረጋጋ በኋላ ቤተሰባቸውን ወደዚያው ስለወሰዱ ነጋድራስ ተስማ 10 አመት እድሜያቸው አንስቶ ያደጉት በሀረር ከተማ ነው:: ብዙም ሳይቆዩ አባታቸው አቶ እሸቴ ሀረር ላይ እንዳሉ በመሞታቸው ነጋድራስ ተሰማ አፄ ምኒልክን ተከትለው ወደአዲስ አበባ በመምጣት በንጉሠ-ነገሥቱ ቤተ-መንግሥት እየተማሩ መኖር ቀጠሉ:: በቤተ-መንግሥት እድገታቸውና ኑሯቸው ከሙዚቃ በተጨማሪ የሥዕል ያንም አጥንተው ስለነበር በሚሰሩት ሥራ ሁሉ በአፄ ምኒልክ ዘንድ ተወዳጅነትን ለማትረፍ ቻሉ:: ሰምና ወርቁ ተሰማ እሸቴ በሚለው መፅሃፍ እንደተብራራው 1900 .. ወደውጭ አገር ሄደው የመማር እድል አጋጠማቸው:: ሆልስ የተባለ ጀርመናዊ በኢትዮጵያ የሚያደርገውን ቆይታ ጨርሶ ወደአገሩ ሲመለስ ለስንብት ከአፄ ምኒልክ ፊት በቀረበ ጊዜ ወደአገሩ ወስዶ የሚያስተምራቸው ሶስት ወጣቶች እንዲሰጡት ጠየቀ:: አፄ ምኒልክም ነጋድራስ ተሰማ እሸቴን በጥሩ ሰዓሊነታቸው ያመሰግኗቸው ነበርና « ተሰማ እሸቴ እጀ ብልህና ነውና መኪና መንዳትና መጠገን እንዲማር እሱ ይሂድ» ብለው ፈቀዱላቸው:: ነጋድራስ ተሰማም ወደጀርመን አገር ሄደው የአውቶሞቢልን አሠራር አጠኑ:: በዋናነት የሜካኒክነትና የሾፌርነት ቢያጠኑም በሙዚቃም ብዙ ስራ ለመሥራት ቻሉ:: ነጋድራስ ተሰማ መሰንቆ መምታትና ዜማ አወጣጥን ከአባታቸው ተምረው ስለነበር ጀርመን አገር ሄደው በቆዩበት ጊዜ "ሂስ ማስተር ቮይስ ̈ ከሚባለው ኩባንያ ጋር በመዋዋል 17,000 የጀርመን ማርክ ተከፍሏቸው በዘለኛና በመዲና ላይ ያተኮሩ 17 ዲስኮችን ለማስቀረፅ ቻሉ:: በህይወት ታሪካቸው ላይ ከተፃፈው ለመረዳት እንደሚቻለው እነፈረደ ጐላ፣ ንጋቷ ከልካይና ተሻሰ መንግሥቱ 1925 .. ዲስኮችን ለማስቀረፅ እስከቻሉ ድረስ 20 ዓመታት የአማርኛ ዲስኮች በአዲስ አበባና በሌሎች ትልልቅ ከተሞችም ይደመጡ የነበሩት የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ብቻ ነበሩ:: ከሙዚቃ ችሉታቸው እኩል ነጋድራስ ተስማ እሽቴ በግጥም ችሎታቸው እጅግ የተደነቁ ናቸው :: ብዙዎቹ ግጥሞቻቸው የሰምና የወርቅ ፍችዎችያሏቸው፣ የሚያስተላልፉት መልዕክት ንካራ እና በአፃፃፍ ቴክኒካቸ የተዋጠላቸው ኛቸው:: ብዙዎቹ የነጋድራስ ተሰማ እሸቱ ጥሞች በወቅታዊ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የተመሰረቱ ሲሆኑ የተነት ባህሪ ይንፀባረቅባቸዋል። ቀጥለው የተጠቀሱት ስት ምሣሌዎ የነጋድራስን የግጥም ርዕሠ-ጉዳዮችና የግጥሞቹን ደረጃዎች ሊያመለክቱ ይችላሉ፡፡

  1. የአገሬ ወንዞች መጥኔውን ይስጣችሁ፣

  ክረምት ሲመጣ እየጨነቃችሁ፣

  ዋጋ አትቀበሉ አስታዋሽ የላችሁ፣

  ከአዳም ጀምሮ እስከአሁን እድሜያችሁ፣

  ሰውንም ከብቱንም እቃ እንዳጋዛችሁ፣

  የማትታመኑ በዋል ፈሰስ ናችሁ፣

  ለውቂያኖስ ዓሣ እያስረከባችሁ፣

  አንድ እንኳ አታመጡ ወዲህ መልሳችሁ ::

  2. አገሬ ታውቂያለሽ እንደምንወድሽ፣

  በታመምሽ ጊዜ ተዘግቶ ጆሮሽ፣

  በነፃነት ፀጋ እስክትፈወሽ፣

  በአራቱ ማእዘን ዓለም ሲጠራሽ፣

  ያምላክ ውለታ ምነው ማጥፋትሽ፣

  አትናገሪም ወይ ተሰማ ብለሽ?

  3. የወዲያ ሰዎች ክፋታቸው፣

  እሬሳ አጋድመው መብላታቸው፣

  የሸዋ ሰው መልካም፣

  ወዳጁን ሳይቀብር አይበላም::

  ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ በአፄ ምኒልክ፣ በልጅ ኢያሱ፣ በንግሥት ዘውዲቱና በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥታት ሲኖሩ በመኪና መካኒክነት፣ ሹፌርነት፣ በሥዕል፣ በሙዚቃና በሌሎችም ተጓዳኝ ያዎች የሚታወቁትን ያህል በቀልድ አዋቂነታቸውም የተደነቁ ነበሩ:: ነጋድራስ ተሰማ እሸቴን በቅርብ እናውቃለን ከሚሉ ወገኖች አስተያየት ለመረዳት እንደሚቻለው ከወቅታዊ ሁኔታ የሚያመነቸው ቀልዶች ከአለቃ ገብረሃና ቀልዶች ጋር ተመሳሳይነት አላቸው:: ነጋድራስ ተሰማ በህይወት ዘመናቸው ከቀለዷቸውና ሰምና ወርቁ ተሰማ እሸቴ በሚባለው መፅሃፋቸው ውስጥ ከታተሙት አሽሙሮች መካከል ሁለቱን ቀጥሎ እንመልከታቸውና ምላተ- ድለታቸውን እንመርምር።

  1. ነጋድራስ ተሰማ አንድ ጊዜ ከመኳንንት ጋር ቁጭ ብለው ሲጫወቱ «አሁን ሁላችሁም በሆዳችሁ የምታስቡትን አውቃለሁ» በማለት ተናገሩ:: መኳንንቱም አያውቁም ሲሉ ተከራከሯቸው። ከመኳንንቱ አንዱ «አያውቁም» ሲሉ በመቶ ብር ተወራረዷቸው:: እሳቸውም «ሁላችሁም ለንጉሡ ነው የምታስቡት በሆዳችሁ ያለው ይህ ነው» ብለው ተናገሩ:: በዚህ ጊዜ ደፍሮ  ̈አይደለም ̈ ብሎ የሚከራከር በመጥፋቱ ውርርዱን ረቱ።

  2. ንጉ ባሉበት የኢላማ ተኩስ ሲደረግ እልፍኝ አስከልካዩ በመጀመሪያ ጥይት ተኩሶ ዒላማውን መታ:: በዚህ ጊዜ ነጋድራስ ቀስ ብለው «ባንዴ ቡን አደረጋት» ሲሉ ተናገሩ:: የእልፍ አስኮልካዩ በጠላት ዘመን ባንዳ ስለነበረ ያንን ለመንካት ሲሉ የተናገሩት ጣምራ ትርጉም ያለው ንግግር ነበር::

  ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ በልጅ ኢያሱ ዘመን ጉልህ ፖለቲካዊ ተሣትፎ ነበራቸው:: አብዛኛው በአዲስ አበባ ከተማ የነበረው የመሃል አገሩ መኳንንት ልጅ ኢያ ከሥልጣን ለማውረድ በተሰለ ጊዜ ሁሉ ነጋድራስ ተሰማ የልጅ ኢያሱ ታማኝ ባለሟል ሆነው እስከ መጨረሻው ዘልቀዋል:: ልጅ ኢያሱ ከሥልጣን ወርደው ደጋፊዎቻቸውም በየጦር ሜዳው ድል ከሆኑ 1909 እስከ 1916 .. ለሰባት አመታት ጅማ ውስጥ በግዞት ተቀምጠው ቆዩ:: ከግዞት ሲመለሱ አዲስ አበባ ውስጥ ራስ መኰንን ድልድይ አጠገብ ካለው ቤትና ቦታቸው በቀር ያለው ንብረታቸው ሳይመለስላቸው እንደ ተወረሰ ቀረ:: ከውጭ አገር በልጅ ኢያሱ ፈቃድ ጠበንጃና ጥይት እያስመጡ ይነግዱ ስለነበር በታሰሩ ጊዜ የጉምሩክ መሥሪያ ቤትና አንድ ግሪክ ነጋዴ ቤት ያስቀመጡትን ግምቱ 300,000 ብር የሚያወጣ ጠበንጃና ጥይትም ሳይመለስላቸው ቀረ:: በጣሊያን የወረራ ዘመን በተለይም ከየካቲት 12 ቀን 1929 .. አንስቶ በአዲስ አበባ ሲኖሩ ቆይተዋል:: ጣሊያን እሳቸው የልጅ ኢያሱ ደጋፊና የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ተቃዋሚ ናቸው ብሎ ስላሰበ አልተቃወማቸውም ነገር ግን በመጨረሻ ጣሊያን በሰሜን ሸዋ ከሚንቀሳቀሱት ከነራስ አበበ አረጋይ ጋር እንዲያስታርቁት ሽምግልና ልኳቸው ነበር ግን አርበኛውን የሚጠቅምና ጠላትን የሚጐዳ ድርድር አድርገው መመለሳቸው ስለታወቀ ለተወሰነ ጊዜ በግዞት እንዲቆዩ አደረጋቸው:: ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ በዚህ ጊዜ ጠላትን የሚቃወሙ ብዙ ግጥሞችን ገጥመዋል:: ቀጥሎ ያለው ግጥም ለምሣሌ በትረመንግሥቱን የጨበጠውን ጣሊያንን የማይገባ ምግባር የሚተች ነው::

  እገበያ መሀል ፈስ እያንዛረጡ፣

  አውራ ጐዳና ላይ ዳቦ እየገመጡ፣

  ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ ትምባሆ እየጠጡ፣

  እንዲህ ነው ወይ ጣልያን አልጋ ላይ ሲወጡ። 

  መጋቢት 28 ቀን 1933 ዓም. የኢትዮጵያ አርበኞችና የእንግሊዝ ወታደሮች በቅንጅት ተዋግተው አዲስ አበባን ከጣልያን ይዞታ እንለቀቁ የእንግሊዝ ጦር አዛዥ ነጋድራስ ተሰማ እሸቴንና ባላምባራስ ግርማ ያየህይራድን የኢትዮጵያን ባንዲራ ይዘው ከደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ዘንድ ሄደው የሚማረኩት ጣሊያኖች ሁሉ በጦር ምርኮኞች ሥርዓት እንዲይዙ የሚል መልእክት እንዲያደርሱ ላኳቸው:: ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ግን እነነጋድራስ ተሰማ እሸቴን ከጣሊያን ጋር ኖራችኋል በማለት አሠሯቸው፡፡ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ባላምባራስ ርማ ሲፈቱ ነጋድራስ ተሰማ ወሊሶ ውስጥ ስድስት አመታት በግዞት እንዲቀመጡ ተደረጉ። ከግዞት ነፃ ከወጡ በኋላ ልዩ ልዩ ሥራዎችን ሲሠሩ ኖሩ:: 1952 .. የአየር ኃይል ፓይለት የነበረው ልጃቸው መቶ አለቃ ኤልያስ ተሰማ በአውሮፕላን አደጋ በአሥመራና በምፅዋ መካከል በሞተ ጊዜ በድንጋጤ በአንጐላቸው ውስጥ ደም በመፍሰሱ የልሣን ማዕከላቸው ጉዳት ሊደርስበት በቃ:: ለአምስት አመታት ያህል በህክምና ሲረዱ ቆይተው ጥቅምት 3 ቀን 1957 .. በተወለዱ 87 ዓመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለዩ:: የጋብቻ ህይወታቸውን በተመለከተ ነጋ ድራስ ተሰማ እሸቴ የመጀመሪያ ጋብቻቸውን የፈፀሙት የአፄ ምኒልክ የአጐት ልጅ ከሆኑት / ላቷ ገብረሥላሴ ጋር ሲሆን ታዋቂውን የእስፖርት ሰው ይድነቃቸው ተሰማን ጨምሮ ሰባት ልጆችን አፍርተዋል:: ከውጭ የወለዱትን ጨምሮ የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ልጆች የሚከተሉት ናቸው።

  1. አይናቸው ተሰማ               5. ይድነቃቸው ተሰማ

  2. ታምሩ ተሰማ                   6. አዘነች ተሰማ

  3. መታሰቢያ ተሰማ              7. ኤልያስ ተሰማ

  4. የምሥራች ተሰማ              8. ማሚቴ ተሰማ ናቸው ::

  ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ከአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ከአማርኛ ሌላ ከአገር ውስጥ ኦሮምኛና አደርኛን፤ ከአገር ውጭ ፈረንሣይኛን፣ ጣሊያንኛን፣ ጀርመንኛንና አረብኛ ቋንቋዎችን አጣርተው ይናገሩ እንደ ነበር ታሪካቸው ያስረዳል::


   ምንጭ:- ታሪካዊ መዝገበ-ሰብ 

 • loader Loading content ...
  Load more...
loader Loading content ...

Comments (0)


  This user has no comment yet.