loader

Topics (54)


loader Loading content ...

Explanations (43)


 • @wubante   2 years ago
  Sewasewer
  ሀብታምና ድ ኻ ሞተው ሲቀበሩ፣
  መቃብራቸውን ሰዎች ሲቆፍሩ።
  እጅግ አርጎ በጣም ስለ ተቃረበ፣
  ሀብታም ተቆጥቶ እንዲህ ተሳደበ።
  ምነው አንተ ድ ኻ እንደዚህ ደፈርከኝ፣
  ምንስ አንተን ዛሬ ለማጥቃት ቢያውከኝ።
  ራቅ እንደ ማለት እኔን ተመልከተህ፣
  አጠገቤ እንደዚህ ተጠግተህ።
  እንዴት የገባሃል ደፍረህ መተኛት፣
  ተነስ ሂድ አሁንም ከምትሄድበት።
  ኻም መለሰና እንዲህ ተናገረ፣
  ዐልጋና መከዳ ሲያማርጥ የኖረ፤
  ያነተ ገላ ነበር ያለ ቦታህ ገብተህ፣
  የተኛህ አንተነህ አሁንም ተነስተህ፤
  ያን የለመድከውን የምቾቱን ስፍራ፤
  ፈልግ እሌላ ዘንድ እዚህ ከኔ ጋራ፤
  ምን አምጥቶ ጣለህ እኔ ግን ከጥንት፣
  ወትሮም ልማዴ ነው መሬት መተኛት።
  ጎበዝ አይል ፈሪ ድ ኻ ባለጠጋ፣
  ሁሉን አስተካካይ ሞት የሙሉ አደጋ።

  ምንጭ
  • ታሪክና ምሳሌ (ከበደ ሚካኤል)

 • loader Loading content ...
 • @wubante   2 years ago
  Sewasewer
  ብዙ ህፃናት ሰብስቦ ከፊቱ፣
  አንድ መምህር ቆሞ ከተማሪ ቤቱ።
  በምሳሌ አድርጎ እየዘረዘረ፣
  ከፍ ባለ ድምጡ እየተናገረ፣
  ሰው በእግዚአብሔር አምሳል ሥለተፈጠረ።
  በተመልካችነት ብንመረምር፣
  ከእንስሳ ይበልጣል በሁሉም ነገር።
  ሰው የማይበልጥበት ምንም ነገር የለ፣
  እያለ ልጆቹን ሲያስተምራቸው ሳለ።
  ምንም ሳያስበው ሳይጠረጥር ከቶ፣
  ከመካከላቸው አንዱ ልጅ ተነስቶ።
  አንድ ነገር አለው ብንመለከት፣
  እንስሳ ከሰው ልጅ የሚበልጥበት።
  በሰዎች መካከል ሰካራሞች ሞልተው፣
  እንስሶች ግን መቼም አይሰክሩ ጠጥተው።
  አለና ቢናገር ሁሉም እየሳቁ፣
  ይህ ነገር እንዴት ነው ብለው ቢጠይቁ።
  እውነትም ነገሩን አይቶ ቢገምተው፣
  ይህን ለማስረዳት መምህሩም አቃተው።
  አወይ በመምህር ላይ ያለበት አባዜ፣
  የተማሪ አስተዋይ በጠየቀው ጊዜ።

  ምንጭ
  • ታሪክና ምሳሌ (ከበደ ሚካኤል)

 • loader Loading content ...
 • @wubante   2 years ago
  Sewasewer
  የፀሃዩ ንዳድ ያጠቃት በብዙ፣
  ጠውልጎ የሚታይ የቅጠልዋ ወዙ።
  አንዲት ጽጌረዳ ቃልዋን አስተዛዝና፣
  እንዲህ ተናገረች ለሰማይ ደመና።
  ድርቀት በጣም ጎድቶኝ እየኝ ስንገላታ፣
  እባክህ ጣልልኝ የዝናብ ጠብታ።
  ቶሎ ካላርስከኝ ጉልበቴ እንዲጥናና፣
  ምንም ተስፋ የለኝ መሞቴ ነውና።
  አሁን መሄዴ ነው ለትልቅ ጉዳይ፣
  ስመለስ መጥቸ ሳልፍ ባንቺ ላይ።
  አዠንብልሻለሁ ጠብቂኝ እያለ፣
  ምንም ሳይጥልላት መንገዱን ቀጠለ።
  ጉዳዩን ጨርሶ ቆይቶ ሲመጣ፣
  ያቺ ጽጌረዳ ስርዋ ውሃ ያጣ።
  እንደዚያ አስተዛዝና ጭንቇን ያዋየቸው፣
  የፀሃዩ ንዳድ አድርቇት ቆየችው።
  እስኪጎርፍ ድረስ የወንዝ ውሃ ሙላት፣
  ወዲያው እንደመጣ ዝናቡን ጣለላት፣
  ግን ደርቃለችና አልቻለም ሊያድናት።
  ሳልደርስላት ቀረሁ አዬ ጉድ እያለ፣
  ደመናም ጎዞውን ወደፊት ቀጠለ።
  ሰውም እንደዚሁ ጭንቁን እያዋየ፣
  በችግሩ ብዛት እየተሰቃየ።
  ብዙ ጊዜ ኖሮ ቆይቶ ሲጉላላ፣
  የሚረዳው አጥቶ ከሞተ በሇላ።
  ዘመድ ወዳጆቹ እንባ እያፈሰሱ፣
  ተዝካር ቢያወጡለት አርባ ቢደግሱ፣
  የህ ሁሉ ከንቱ ነው አይጠቅመውም ለሱ።
  እውነት ከወደደ ሲቸገር ሲጎዳ፣
  በህይወቱ ሳለ ሰው ወዳጁን ይርዳ።

  ምንጭ
  • ታሪክና ምሳሌ (ከበደ ሚካኤል)
   
 • loader Loading content ...
 • @wubante   2 years ago
  Sewasewer
  እናቱ በጣም አድርጋ የምትወደው አንድ ልጅ ነበር። እሱም ከዐጥር ግቢያቸው ውስጥ ከሚገኙት የኮክ ዛፎች ላይ እየወጣ ፍሬውን ሲቆርጥ እናቱ ብዙ ግዜ ታየው ነበርና ከዛፉ ላይ ወድቆ አደጋ ያገኘዋል ብላ ስለሰጋች እንዳይወጣ መላልሳ ብዙ ጊዜ ከለከለችው።

  አንድ ቀን ከቤት ውስጥ ሆና ልጅዋ እንደ ልማዱ ከኮኩ ዛፍ ላይ ወጥቶ ፍሬ ሲለቅም በመስኮት አየችው። ከቤት ሲገባ ጠርታው "ከዛፍ ላይ አትውጣ ብየ ከልክየህ አልነበረምን? ለምንድን ነው ዛሬ ደግሞ የወጣሃው?" ብላ ጠየቀችው። እሱ ግን ደንግጦ አልወጣሁም ብሎ ካደ። እሷም በጣም ተቆጣችና "ከማጥፋትህ መዋሸትህ ይባስ፣ ባይኖቸ እያየሁህ ትክደኛለህ" ብላ ልትመታው ተነሳች። 

  እሱም አሳዛኝ የሆኑትን አይኖቹን እያንከራተተ ለዛ ባለው አንደበቱ "እማማ፣ እወድሃለሁ ትይኛለሽ፤ እንደምትይኝም እውነት የምትወጂኝ ከሆነ ባይኖችሽ ካየሽው ይልቅ እኔ የምነግርሽን አብልጠሽማመን ይገባሻል።" አላት። ደማሙ ልጅ ይህን ማለቱ ስለ እኔ ፍቅር ብለሽ ያየሽውን እንዳላየሽ አድርገሽ አሳልፊው እንጂ በጥፋቴ ለምን ትሞግችኛለሽ ብሎ መለማመጡ ነው። እናቱም በዚህ ለዛ ባለው ንግግር ከቁጣዋ በርዳ በመምታት ፈንታ  ልጅዋን አቅፋ ሳመችው። አይኖቿም እንባ አቅርረው ይታዩ ነበር።

  ምንጭ
  • ታሪክና ምሳሌ (ከበደ ሚካኤል)

 • loader Loading content ...
 • @wubante   2 years ago
  Sewasewer
  አንድ ቀን ብረት ድስት ሸክላ ድስትን አለው፣
  እኔን ነው በሁሉም መልክህ የሚመስለው።
  ወንድሜ ነህ እኮ ባታውቀው ነው እንጂ፣
  ከዛሬ ጀምሮ እንሁን ወዳጂ።
  እኔን እንደመቅረብ መሸሽህ ለምን ነው፣
  አካሌ አካላትህ የኔ ቤት ያንተም ነው።
  አሁንም በል ተነስ ፍቅራችንም ይጥና፣
  ሽር ሽር እያልን እንናፈስና ።
  መፋቀራችንን ይይልን ሰው ሁሉ ፣
  የማንተዋወቅ ለምን ነው መምሰሉ።
   አጥቂ ቢመጣብህ ዘሎ የሚመታ፣
  እኔ እሆንሃለሁ ኀይለኛ መከታ።
  ለፀሃይ ላቧራው እየሆንኩ ድንኯን፣
  እደግፍሃለሁ ቢነቅፍህ እንኯን።
  በደካማነቱ ቅር እያለው ሆዱ፣
  ተነሳ ሸክላ ድስት አንድነት ሊሄዱ፣
  አንድ መቶ እርምጃ እንደ ተራመዱ።
  ድንገት ተጋጩና አቶ ብረት ድስት፣ 
  ረግተው ሲቆሙ ያላንዳች ጉዳት።
  የሸክላው ድስት ግን በፈራው ጎዳና፣
  ተስብሮ ወደቀ እንክትክት አለና።
  ወዮ እንኯ ለማለት ጊዜ ሳያደርሰው፣
  የገሉ ስባሪ ምድሩን አለበሰው።
  እንዲያው ሰው ያላቻ እየተንጠራራ፣
  ለመሻረክ ቢያስብ ከበላዩ ጋራ።
  መቼም አይጠፋና ከኀይለኛ ግፍ፣
  ከጉዳት በተቀር ምንም አያተርፍ።
  ሰዎች ከሰው ጋር ሸሪክ ስትሆኑ፣
  ዐቅማችሁን በፊት አይታጩ መዝኑ።

  ምንጭ
  • ታሪክና ምሳሌ (ከበደ ሚካኤል)

 • loader Loading content ...
 • @wubante   2 years ago
  Sewasewer
  አንድ የምሥራቅ ጦረኛ ጎበዝ ንጉሥ ብዙ ጦር ድል አድርጎ ብዙ አገርም አስገብሮ ይኖር ነበር። ፍዳ አይቀርምና በመጨረሻው ባንዲት ትንሽ ጦርነት ተሸንፎ ድል ሆኖ ሳለ ተማረከ።  ዚያው  ከተማረከበት  ቦታ  ሁኖ  ረኃብ  ይዞት  ነበር ።  ረኃቡንም  ሊያበርድለት  አንድ  ወታደር  የተራ  ወታደር  ምግብ  ሲያሰናዳለት  ሳለ  መቀመጫውን  አቧራ  ላይ  አድር ገው  አግድም  አስቀመጡ

  ምግቡም የፈረስ ስጋ በሚቀቀልበት ባንድ ማሰሮ ውስጥ ሲቀቀልና ሲፈላ ሳለ አንድ ውሻ መጣና ይህን ስጋ ለመውሰድ አንገቱን በማሰሮው ውስጥ አስገባው። የማሰሮው አንገት በጣም ጠባብ ስለሆነ ራሱን ለማውጣት አልቻለም  ነበርና ስጋውን አንዳለ ከነማሰሮው ይዞት በረረ።

  ኸውም ታስሮ የነበረው ንጉስ ይህንን ባየ ጊዜ በጣም ገርሞት ተደነቀ። ከልቡም ሳቀ። እርሱን ከሚጠብቁት ዘበኞች ውስጥ አንደኛው ዘበኛ "ምን ያስቅሃል? በእንደዚህ ያለ አደጋ ውስጥ ያለ ሰው ሊስቅ ይገባልዋልን?" ብሎ ጠየቀው። ንጉሱም "አሁን የምስቀው ዛሬ ጠዋት አንድ ውሻ መጥቶ ሶስት መቶ ግሞሎች እንኯ ቢመጡ የማያነሱትን የቤት ዕቃየን ፣ መብሉን ከነማሰሮው ይዞት በረረ ብሎ ከእልፍኝ አሽከሮቼ አንደኛው አለቃ ስለነገረኝ ነው" የሚል መልስ ሰጠው። 

  የንጉሱ መልስእክት ምን ይሆን?

  ምንጭ
  • ታሪክና ምሳሌ (ከበደ ሚካኤል)

 • loader Loading content ...
 • @wubante   2 years ago
  Sewasewer
  ሥትሰራ ስራ፣ ስትጫወትም ተጫወት፤ የተድላና የደስታ መንገድ ይህ ነው።  የምታደርገውን  ሁሉ  አስተውለህ  አድረግ ።  በችኮላ  የተደረገ  ነገር  ሁሉ  ከቶ  በትክክል  አይሰራም

  ያም ቢሆን ደህና ሆኖ ይደረግ። ብዙዎች ሊመሰክሩለት የሚችሉ መልካም ስርዐት ነው። ጊዜ አይታመንም፣ ቶሎ ያልፋል፤ እንግዲያስ ሥትሰራ ስራ፣ ስትጫወትም ተጫወት፤ ጊዜው ይበራል፤ ደቂቃውም ያልፋል አንድ ሰዓት ሆነ።  ቀኑ  በረረ  ፤  ለሊቱም  ቀረበ  ፤  አንድ  ሳምንት  ሄደ  ፤  ወሩ ፣  አመቱም  አለፈ

  ዘመኔ ከሚሮጥ ሰው ይፈጥናል። ንስር የሚበላውን አይቶ እንደሚበር፤ እንደምትፈጥንም መርከብ አለፈ፤ ኮበለለ፤ መልካም ነገርም አላየም።

  ምንጭ
  • ታሪክና ምሳሌ (ከበደ ሚካኤል)

 • loader Loading content ...
 • @wubante   2 years ago
  Sewasewer
  አንድ የፋኖስ መብራት በግብሩ የኮራ፣
  እንዲህ ሲል ተጣላ ከብርጭቆው ጋራ።
  እኔ ነኝ መብራቱ ብርሃን የምሰጥ፣
  ጨለማን አትፍቸ የምገላልጥ።
  አንተ ግን እፊቴ እንዲህ ተደንቅረህ፣
  ዙሪያየን ከበ ኝ እንዲህ ተደንቅረህ።
  አልገባኝም ከቶ የምትሰራው ስራ፣
  ብርሃኔ ሩቅ ደርሶ ደምቆ እንዳያበራ።
  ተሠራጭቶ በጣም እንዳይዘረጋ፣
  አንተን ፈጠረብኝ መንገድ የምትዘጋ።
  እንቅፋት እየሆንህ ስራዬን አታጥፋ፣
  ገለል በል ከፊቴ ብርሃኔ ይስፋፋ።
  አገልግሎቴማ ከሆንብኝ ጥፋት፣ 

  እውነትማ ላንተ ከሆንኩህ ዕንቅፋት። 
  ልሂድልህ ብሎ ሲልቅለት ቦታ፣ 
  ከጎን የነፈሰ የነፋስ ሽውታ፣
  መጣና መብራቱን አጠፋው ባንድ አፍታ።
  አጭር እየሆነ ተመልካችነቱ፣
  መለየት አቅቶት ጥቅሙን ከጉዳቱ።
  እወቁኝ እወቁኝ እያለ ሲነሣ፣
  ሰውም እንደዚሁ ያመጣል አበሳ።

  ምንጭ:
  • ታሪክና ምሳሌ (ከበደ ሚካኤል)

 • loader Loading content ...
 • @wubante   2 years ago
  Sewasewer
  ቁጥራቸው ወደ አንድ ሺህ የሚጠጋ የቀንድ ከብቶች የነበሩት አንድ ከብት አርቢ የሆነ ባለጠጋ ሰው "እነሆ ከጥቂት ቀን ወዲህ ከብቶቼ ሌሊት ለሊት በበረታቸው ውስጥ እርስ በእርሳቸው እየተተራመሱ ሲታወኩ ያድራሉ። ከዚህም ቀደም በመካከላቸው ይህን የመሰለ ሁከት አልነበረም። አሁን ግን ይህ የሆነበት ምክንያት ጠፍቶኛል፤ ምን ይሆን" ብሎ ጎረቤቶቹን ቢያማክራቸው፤ አስተዋይ የሆነ አንድ ሽማግሌ "ለዚህ ነገር ብልሃቱ አጭር ነው። ሌላ ትልቅ በረት አሰርተህ ከብቶችህን ከሁለት ክፈላቸውና ለየብቻ አሳድራቸው" አለው። ባለጠጋውም ሽማግሌው እንዳለው አደረገ። ይህንን ባደረገ በማግስቱ "ከብቶችህ ዛሬስ እንደምን አደሩ" ብሎ ቢጠይቀው፤ "ያንደኛው በረት ከብቶች ደህና አደሩ፣ ያንደኛው ግን ሲተራመሱ አደሩ" ብሎ መለሰለት። "በል አሁን ከግሞ ሌላ ሶስተኛ ትልቅ በረት አሰርተህ ሲታዎኩ ያደሩትን ከብቶች ከሁለት ከፍለህ ለየብቻ አሳድራቸው" አለው።

  አሁንም ደግሞ ባለጠጋው እንዲሁ ሽማግሌው እንደመከረው አደረገ። በማግስቱም ቢጠይቀው "ባንዱ በረት ያሉት ከብቶች ድህና አደሩ ባንደኛው የነበሩት ግን ሢበጠበጡ አደሩ" አለው። ሽማግሌውም መለሰና "እነዚያን ደህና ያደሩትን ከፊተኞቹ ጋር ቀላቅለህ ሲታወኩ ያደሩትን ከብቶች አሁንም ከሁለት ክፈላቸውና ለየብቻ አሳድራቸው" አለው። እንዲሁ እያደረገ የታወኩትን ከብቶች ከሁለት እየከፈለ ደህና ያደሩትን ግን ለብቻ ለይቶ ከደህኖቹ ጋር እየቀላቀለ ስድስት ጊዜ ይህንን ስራ ደጋግሞ ከሰራ በሇላ በመጨረሻ ከሚተራመሱ ከብቶች ወገን አስር ብቻ ቀሩ።

  "በነዚህ በአስሩ ከብቶች መካከል የቀሩትን ሁሉ የሚበጠብጡ ሁለት ወይም ሶስት ከብቶች ሳይሆኑ አይቀርምና ሌሊት ጨረቃ ስትወጣ ጠብቀህ ከዳር ቆመህ ከብቶችን ተመልከታቸው" አለው። እውነትም ባለጠጋው ሽማግሌው እንደመከረው አድርጎ ቢመለከት በከብቶቹ መካከል እየሮጠ ሌሎችን እየወጋ ፀትታ ነስቶ ሁሉንም የሚበጠብጣቸው አንድ ወይፈን መሆኑን አየ። "እንግዲህ ይህን ወይፈን ወይም ሽጠው ወይም እረደው" አለው።

  ወይፈኑም ከከብቶቹ መካከል ከተወገደ በሇላ ከብቶቹን ሁሉ መልሶ እንደ ቀድሞዋቸው ቢቀላቅላቸው ረግተው በሰላምና በፀትታ ያድሩ ጀመር። እነዚህን ሁሉ ከብቶች የሚበጠብጣቸው አንድ ወይፈን እንዳለ ሁሉ በሰዎችም መካከል ሰላምና ስምምነት ጠፍቶ ሁከትና ብትብጥ ሲነሳ ነገሩን ሁሉ እያጣሩ ቢመረምሩት እንዲሁ ሆኖ እንደሚገኝ አያጠራጥርም።

  ምንጭ:
  • ታሪክና ምሳሌ (ከበደ ሚካኤል)

 • loader Loading content ...
 • @wubante   2 years ago
  Sewasewer
  እድሜያቸውን ሙሉ መፅሀፍ በማንበብና ጥበብን በመመርመር የሚኖሩ ሦስት ሰዎች ነበሩ። እነሱም በጣም የጠለቀና የረቀቀ እውቀት ስለነበራቸው ለጥበባቸው የተገባ ክብርና ማእረግ ማግኘት ይገባልና ብለው ስራ ለመለመንና ደጅ ለመጥናት ወደ ቤተ መንግስት ሊሄዱ ጉዞ ጀመሩ። የዘመናቸው ንጉስ ጥበብ የሚወድ መሆኑን ያውቁ ስለ ነበር ይህ ምኞታቸው እንደሚፈቀድላቸው ባለመጠራጠር ተረድተው እየተጫወቱ ሲሄዱ እነሱ ወደሚሄዱበት ከተማ የሚሄድ አንድ ሌላ መንገደኛ አግኝቶዋቸው አብሮዋቸው ይጏዝ ጀመር። እርሱም የተማረው ትምህርቱ ጥቂት  ነበር። ግን ከነሱ የበለጠ የተፈጥሮ አስተዋይነት ነበረው። እነዚያ ሶስት ሰወች የጥበብን ነገር አንስተው እየተከራከሩና ወደፊትም የሚያገኙትን ክብር እየተጫወቱ ሲሄዱ ካንድ ጫካ ውስጥ ደረሱ።እዚያም ቦታ ከብዙ ጊዜ በፊት አንድ አንበሳ ሞቶ ኖሮ አጥንቱ በያለበት ተበታትኖ አገኙ። ከሶስቱም አዋቂዎች አንደኛው "እንግዲህ የእውቀታችን ልክ የሚታወቀው አሁን ነው። እነሆ ይህ ተበታትኖ የምናየው የአንበሳ አጥንት ነው። እኔ ጥቂት ቃላት ደግሜ የህ አጥንት ሁሉ ተሰብስቦ ቀድሞ እንደ ነበረ በየቦታው ገብቶ እንዲገጣጠም አደርገዋለሁ" አለ። ሁለቱ ባልንጀሮቹ "በል አድርግ" አሉት። እሱም ድግምቱን ደግሞ እውነትም እንደ ተናገረው የአንበሳውን አጥንት ሁሉ በየቦታው ገብቶ እንዲገጣጠም አደረገው።

  ሁለተኛው አዋቂ ይህንን ባየ ጊዜ "እኔ ደግሞ ስጋውን መልሼ ደሙን ሞልቼ ቆዳውን አለብሰዋለሁ" ብሎ ድግምቱን ደገመና እሱም እንዲሁ እንደተናገረው አደረገ። ያ ብዙ ትምህርት የሌለው አራተኛው መንገደኛ የአንበሳውን አጥንት እንደተገጣጠመና ስጋውን፣ ደሙንና ቆዳውን አግኝቶ አካላቱ እንደሞላለት በአይኑ ባየ ጊዜ የነገሩ አኯሇን አላምርህ አለው። ሶስተኛው አዋቂ ተነሳና "እናንተ ይህንን ብታደርጉ እኔ ደግሞ የህይወት ትንፋሽ የሚሰጥ ድግምት አውቃለሁ" ብሎ ሊደግም ሲጀምር አራተኛው መንገደኛ "ወንድሞቸ ሆይ ይህ አያያዛቹህ ከቶ አላማረኝም፤ እናንተም እውቀታቹህን ብቻ እንጅ ይህ የምታስነሱት አውሬ አንበሳ መሆኑን ዘንግጣችሁታል መሰለኝ። ነፍስ ዘርቶ የተነሳ እንደሆነ ከያዝነው ብትር በቀር የምንከላከልበት ሌላ የበቃ መሳሪያ በእጃችን ስሌለለ ህላችንንም ያበላሸናል፤ ተው ይቅር" ብሎ ቢያሳስባቸው ያ የመጀመሪያው የአንበሳውን አጥንት የገጣጠመው አዋቂ ከት ብሎ ሳቀና "አየ የኛ ጅል፣ ደንቆሮ፣ እኛ የምንሰራውን ጥበብ እየተመለክትክ መደነቅ አነሰህና ምን ጥልቅ አደረገህ በማታውቀው ሙያ ገብተህ ምክር ልትሠተን ደፈርህ" ብሎ ዘለፈው። ለአንበሳው ስጋ፣ ደምና ቆዳ የመለሰለት ሁለተኛው አዋቂ ደግሞ ተቀብሎ "ምንስ አስር ደንቆሮ ብትሆን ከሞት ያስነሳነው አውሬ መልሶ እኛኑ ይበላናል ብለህ ማሰብህ ከጅልም ጅል ነህ" ብሎ ሳቀበት። "እንግዲያውስ ለኔ ለደንቆሮው ፍቀዱልኝና እዚያ ዛፍ ላይ እሥክወጣ ድረስ ጊዜ ስጡኝ" ብሎ ሸሽቶ ከዛፍ ላይ ሆኖ መጨረሻቸውን የመለከት ጀመር።

  ሶስተኛው አዋቂ ከጏደኞቼ አንሼ አልቀርም በማለት ድግምቱን ደግሞ ሲጨርስ አንበሳው ነፍስ ዘርቶ ተነስቶ በተራበ አንጀቱ ዘልሎ አጠገቡ የነበረውን ነፍስ የዘራለትን ሰው መጀሪያ በላው። ቅጥሎም ስጋ፣ ደምና ቆዳ የሰጠውን ሰው ደገመው። ከዚህ በሇላ ራቡ ታገስ ሲልለት አጥንቱን የገጣጠመለትን ሰው ገድሎ ሬሳውን ጎትቶ ወደ ዋሻው ይዞት ሄደ።

  ደንቆሮ የተባለው ድንቁርናው አዳነው። ሶስትን ጥበበኞች ግን የሰሩት የጥበብ ስራ አጠፋቸው። ማንኛውም ነገር በመጠን ሲሆን መልካም ነው። ከመጠን ሲያልፍ ግን ይልቁንም ፉክክር ሲጨመርበት ሌላው ይቅርና ያቺ መልካሚቱ ጥበብ እንኯን ትጎዳለች።

  ምንጭ:
  • ታሪክና ምሳሌ (ከበደ ሚካኤል)

 • loader Loading content ...
  Load more...
loader Loading content ...

Comments (3)


loader Loading content ...